You are here: HomeOpinionsምን እንጠጣ?

ምን እንጠጣ?

Written by  Tuesday, 28 July 2015 12:28

“ለጥፋት ለቀረበው ሰው ብርቱ መጠጥ ስጡት፥ ነፍሱ ለመረረውም የወይን ጠጅ ስጡት፤ ይጠጣ ድህነቱንም ይርሳ፥ ጕስቍልናውንም ከእንግዲህ ወዲህ አያስብ።ሳሌ 31፡6-7

"Beer and wine are only for the dying or for those who have lost all hope. Let them drink and forget how poor and miserable they feel" Proverbs 31:7

 

ቢራ፣ ወይን ወይም የትኛውንም የአልኮል መጠጥ መጠጣት ችግር አለው ወይ? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መጠጥና ስለ ስካር ምን ያስተምራል? በዚህ ጽሑፍ እነዚህንና ተዛማጅ ጉዳዮችን ለአንባቢው በማቅረብ የክርስቶስ ቤተሰብ የአልኮል መጠጥን በተመለከተ ያለውን ግንዛቤ ከፍ በማድረግ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አንመክራለን፡፡ 

 

በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣው የአልኮል መጠጥ ፍላጎት በተለይም የቢራው ገበያ የዓለም-አቀፍ ኩባንያዎችን ትኩረት እየሳበ ነው፡፡ የኔዘርላንዱ ሀይኒከን ከናይጄሪያና ከደቡብ አፍሪካ ቀጥሎ በኢትዮጵያ ግዙፉን ፋብሪካ በአቃቂ ገንብቶ በመጨረስ ማምረት ጀምሯል፡፡ ከዚህ ቀደም ሁለት የሀገሪቱን ግዙፍ የቢራ ፋብሪካዎችን ማለትም በደሌና ሀረር ቢራን በ200 ሚሊዮን ዶላር ግዢ የራሱ አድርጓል፡፡ የእንግሊዙ ዲያጂዮም እንዲሁ ሜታን ጠቅልሎታል፡፡ ሌሎችም በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣውን የደራ የአልኮል መጠጥ ገበያ የተረዱ የውጭ የቢራ ጠማቂዎች ወደ ምድሪቱ ሊመጡ ተነቃቅተዋል፡፡ በሀገራችንም የቢራ ቢዝነሶችን ለማቋቋም አክስዮኖች በከፍተኛ ሁኔታ እየተሸጡ ወደ ጠመቃው በመገባት ላይ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትራችንም ቀደም ብለው ዝዋይ አካባቢ የሚገኘውን በሀገሪቱ ትልቁን የወይን መጥመቂያ በመቀጠልም አቃቂ ላይ የተገነባውን ግዙፋን የሄይኒከን የቢራ ፋብሪካ አስመርቀው የፊታውራሪነት ድርሻቸውን አበርክተዋል፡፡ ከሞኑ በርካታ የኢኮኖሚ መሻሻሎችን እያሳየች እደሆነ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጭምር እየተነገረላት ያለችው ሀገራችን "በቤተሰብ ደረጃ በምግብ ራሷን ለመቻል" ከመዳኽ አልፋ በመጠጥ “ወፌ ቆመች” ችግሯን በአልኮል አጥምቃ ለመቅረፍ ላይ ታች እያለች ያለች አስመስሎባታል፡፡ የጠጪ ወጣቱ ትውልድ አባል መበራከት፡ - ያኛው ትውልድ “ተራሮችን ያንቀጠቀጠ” ሲሆን ይህ ትውልድ ደግሞ የመጠጥ ቤት “ባንኮኒዎችን ያንቀጠቀጠ” ትውልድ የሚል ሥያሜ በአንዳንዶች እንዲሰጠው ሆኖአል፡፡ ይህ ሥያሜ ሁሉንም የትውልዱን አባል ባይወክልም ግና ብዙ የትውልዱ አባላት ከ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ በከፍተኛ ጠጪነት ውስጥ እየተዘፈቁ መምጣታቸው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡

 

ቀደም ባሉት ጊዜያት በበርካታ ወንጌላዊያን አማኞች ዘንድ እንደ ነውር ይቆጠር የነበረው የአልኮል መጠጥን መውሰድ እንደ ቀላልና ተራ ነገር መታየት ከጀመረ ሰነበተ፡፡ ብዙ ወዳጆቼና ወገኖቼ የአስተሳሰብ “ትራንስፎርሜሽን” በማምጣት የአልኮል መጠጥ የሚወስዱ በመሆኑ አንዳንዴ ኋላ ቀር እንደሆንኩ ሊሰማኝ ይዳዳዋል፡፡ ቆየት ብዬ በአንዳንድ አጋጣሚ የማገኛቸው አንዳንድ የቀድሞ ጓደኞቼ፣ የሥራ ባልደረቦቼ፣ የአንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያን አባላት የነበርን ወዘተ ምግብ ልንበላ በተቀመጥንበት አስተናጋጁ “የሚጠጣ?” ሲል ወይን ወይም ቢራ ምናምን ሲያዙ መመልከት በመጀመሪያ ቀልድ ሲመስለኝ የምራቸውን እንደሆነ ስረዳ ግን ትንፋሼ ለሰከንዶች የተቋረጠበትን ጊዜ አስታውሳለሁ፡፡ ይህንን ሁናቴ “የመጠጥ አብዮት” ልበለው ወይስ ምን? ኢትዮጵያዊ ድህነቱን በቢራና በወይን እንዲረሳ እየተጣረ መሆኑ ነው እንግዲህí

 

ብዙዎች ባዶ ሆዳቸውን በሚያድሩባት ሀገር በሚያሳዝን ሁኔታ የአንደኛ ደረጃ ህጻናት ተማሪዎች ሳይቀሩ አልኮል መጠጥ የሚጨልጡባት ሀገር እየሆነች ነው ኢትዮጵያ፡፡ "ዴይ ፓሪ፣ ናይት ፓሪ" (Day party, Night party) በሚባሉ ከሆሊዉድ "School life" ፊልሞች በተኮረጁ የርኩሰት መለማመጃ ስፍራዎች ልጆች ወላጆቻቸዉን ተደብቀው በመጠጥ፣ በአደንዛዥ ዕፅና በዝሙት ይነከራሉ፡፡ ያለአግባብ በአቋራች የከበሩና ሕዝቡን በዝብዘው አንቱ የተባሉ የምድራችን ነጋዴ “ሹገር ዳዲዎች” እምቦቃቅላ ሴቶቻችንን በእንቡጥነታቸው በመቅጠፋቸው በምድርም በሰማይም ተጤቂዎች ናቸው፡፡

 

ከጥቂት አመታት በፊት ሴቶቻችን አልኮል በአደባባይ መጠጣት ቀርቶ ሆቴል ቡና ቤት ለብቻቸው መታየትን  እንደነውር ነበር የሚያዩት፡፡ መሰለኝ፡፡ ዛሬ ላይ ግን ለምግብ ማወራረጃ ቢራና ወይን እንደውሀ ሲጨልጡ በየጥጋጥጉ መመልከት ተራ ነገር ሆኗል፡፡ አልኮል በአደባባይ ከመውሰድ ባለፈ ጭምትነቱ በሁሉም ቦታ መጥፋቱ ለትዳሮች መፈራረስ፣ ለቤተሰብ መበተን፣ ለሞራላዊ እሴቶች መናድ ወዘተ ትልቁን ሚና ይጫወታል፡፡ ከምዕራቡ ዓለም የቀዳነው እርባና ቢስ ዘመናዊነት አቅል አሳጥቶ ወደማንወጣው አዘቅት ውስጥ አንደርድሮ እየዘፈቀን ነው፡፡ ችግሩን ቆም ብሎ ተመልክቶ መፍትሔ ከማፈላለግ ይልቅ ሁሉም በቸልተኝነት ለገዛ ንግዱ ይሮጣል፤ ሀይ ባይ ጠፍቷል፤ ጎበዝ ምን ይበጀናል ትላላችሁ?

 

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ መጠጥ መጠጣት አለበት ወይስ የለበትም ወደሚለው የተለመደ አሰልቺ ንትርክ ውስጥ ልከታችሁ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱሴን ሳጠና የተረዳሁትን እንደገባኝ መጠን ላካፍላችሁ በማሰብ ነው፡፡ ከላይ በመግቢያው ላይ የጠቀስኩት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሚናገረው ለጥፋት ስለቀረበና ነፍሱ ስለመረረው ሰው ስለሚሰጥ መጠጥ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ለጥፋት ለቀረበ ሰው የሚሰጥ ብርቱ መጠጥ ነበር፡፡ ይህንን መጠጥ በርካታ የእንግሊዝኛ ቅጂ መጽሐፍ ቅዱሶች “beer” ይሉታል፡፡ ቢራ መሆኑ ነው እግዲህ፡፡ ነፍሱ ለመረረው ደግሞ የወይን ጠጅ ሥጡት ይላል፡፡ በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ከተጠቀሱት አውዶች ጋር በማመሳከር ስንመለከት የነፍስ ምሬት በሕመም ምክንያት ለከፍተኛ ስቃይ የተዳረገንና ለሞት የቀረበን ሰው ወይም የሞት ፍርድ ተፈርዶበት በጭንቀት ላይ ያለን ሰው ይወክላል፡፡

 

ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል(ምሳ 31ን) ከመጀመሪያው ጀምረን ስናጠናው የሚያሰክር መጠጥ ለነገስታት የተከለከለ መሆኑን እንመለከታለን፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ፍርድን እዳያዛቡ ነው፡፡ ነገስታት በመጠን እንዲጠጡ ስለ መጠጥ አወሳሰድ ምክር የሚሠጥ ክፍል ሳይሆን የሚያሰክርን መጠጥ በጭራሽ እንዳይጠጡ የሚመክር ክፍል ነው፡፡ ይሁንና በጊዜው የነበረው ልማድ በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ለነበሩ ሰዎች መጠጦቹ እንደማደንዘዣ ወይም ስቃይ ማስረሻ ይሰጡ እንደነበር ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በዘመናችንም ከተለመደ ህመም መቀነሻ የህክምና ዘዴ ጋር የተወሰነ መመሳሰል አለው፡፡ በዘመናችን በህመም ምክንያት በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ላሉ የአልኮል መጠጥ መስጠቱ እምብዛም የተለመደ ባይሆንም በእደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ላሉ ሰዎች የተለያዩ ዓይነት ማደንዘዣዎችና የሕመም ማስታገሻዎች ይሰጣሉ፡፡ ጠጪ የሆኑ ሰዎች ላይ የሰመመን መድኃኒቶች (anesthesia) በአብዛኛው በሚፈለገው መልክ አይሰሩም፡፡ መጠጥ ሰውነትን የማደንዘዝና ጤናማ አሠራሩን የማዛባት አቅም ስላለው ጠጪ ሰዎችን አሁን ባለው የህክምና ዘዴ አደንዝዞ ማከም አስቸጋሪ ነው፡፡ በመጽመፍ ቅዱሳዊው ዘመን እንደዚህ አይነት የተራቀቁ መድሐኒቶች አልነበሩም፡፡ በወቅቱ የነበረው በስፋት የሚሰራበት አማራጭ ሰዎችን የሚያሰክርና የሚጎመዝዝ መጠጥ በማጠጣት ጊዜአዊ እፎይታን በስቃይ ወይም በጭንቀት ውስጥ ላሉት መስጠት ነው፡፡ ከክፍሉ አውድም የምንረዳው ይህንን ነው፡፡ የወይን ጠጅ ለከባድ የሆድ ሕመምም በማስታገሻነት የተጠቆመበትን ሁኔታ በመጽሀፍ ቅዱሳችን ውስጥ ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የሰውን የኃጢአት እዳ ሊከፍል በመሥቀል ላይ ተንጠልጥሎ ሳለ ስቃዩን በሞት እስኪገላገለው በጊዜው በነበረው የማደንዘዝ ዘዴ መሠረት ከስቃዩ ጊዜአዊ እፎይታን እንዲያገኝ ያመጡለት ሆምጣጤ ድብልቅ መጠጥ ነበር፡፡ ይህ ድብልቅ መጠጥ የሚሰራው ከወይን ጠጅና ከሆምጣጤ ነበር፡፡

 

 

መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚያሰክር መጠጥና ስለ ሰካራሞች ብዙ ይናገራል፡፡ በአጠቃላይ ሰካሮች እንዳንሆንና ከሰካሮች ጋር ሕብረት እንዳይኖረን (1ቆር 5፡11) ፤ የሚያሰክር መጠጣትና ስካር ወደ ሞት እንዲሚያመራና ሰካሮች የእግዚአብሔርን መንግስት እንደማይወርሱ (1ቆሮ 6፡10) ይናገራል ፡፡ ጳውሎስ የኤፌሶንን ሰዎች “መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ ብሏቸዋል፡፡” ጠቢቡ ሰለሞን የወይን ጠጅን አታላይነትና ክፋት በሰፊው አስተምሯል፡፡ “ወደ ወይን ጠጅ አትመልከት በቀላ ጊዜ፣ መልኩም በብርሌ ባንጸባረቀ ጊዜ፣ እየጣፈጠም በገባ ጊዜ፡፡ በኋላ እንደ እባብ ይነድፋል፣ እንደ እፉኝትም መርዙን ያፈስሳል፡፡ ዓይኖችህ ጋለሞታዎችን ያያሉ፣ ልብህም ጠማማ ነገርን ይናገራል፡፡” (ምሳ 23፡31-33) ፡፡ በሌላ ሥፍራ ደግሞ “የወይን ጠጅ ፌዘኛ ያደርጋል፣ ብርቱ መጠጥም ጠበኛ ያደርጋል፤ በዚህም የሳተ ሁሉ ጠቢብ አይደለም… የወይን ጠጅ ከሚጠጡ ጋር አትቀመጥ…” ይላል፡፡ የኢዮብ ልጆች በዐውሎ ነፋስ በሞቱበት ወቅት ሲበሉና የወይን ጠጅ ሲጠጡ ነበር (ኢዮ 1፡18) ፡፡   

 

ወይን ጥንትም አሁንም እጅግ ተወዳጅ ፍሬ ነው፡፡ ወይንን ፍሬውን መብላት የሚቻል ሲሆን ወይም ጭማቂውን መጠጣት ይቻላል፡፡ ይህ ዓይነቱ መጠጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን በእስራኤላውን ዘንድ የተለመደ እንደ ነበር ከአንዳንድ ምንጮች መረዳት ይቻላል፡፡ የወይን ጭማቂን ወደሚያሰክር መጠጥም ቀይሮ መጠጣትም የተለመደ ነው፡፡ ገብስም በራሱ ለመልካም የተፈጠረ ሰብል ሲሆን በተለያየ መልኩ ተዘጋጅቶ ለምግብነት ይውላል፡፡ ሰዎች ለዘመናት ቢራ እየጠመቁበትም ኖረዋል፤ የሚያሰክር ቢራ ወይም “ከአልኮል ነፃ” መጠጥም ሲጠመቅበት ቆይቶአል፡፡ ጉዳዩ ያለው እንግዲህ አንድ ተመሳሳይ ነገርን ለበጎም ለጥፋትም መጠቀም መቻሉ ላይ ነው፡፡ እንደየሰው ምርጫ፡፡ የኒኩለር ኃይልን ለኤሌክትሪክ ኃይል ወይም ሕይወት ያለውን ነገር ሁሉ ከምድረ ገጽ ለማጥፋት መጠቀም እንደሚቻለው ሁሉ፡፡ ሌላውንም ሁሉ ነገር እንደዛው፡፡ ሰው ነፃ ፈቃድ ተሰጥቶች የተፈጠረ ፍጡር ነውና፡፡

 

ከጥፋት ውሀ በኋላ ኖህ ገበሬ መሆን እንደ ጀመረና ወይንን እደተከለ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ ገበሬ መሆኑና ወይን መትከሉ በራሱ ምንም ጥፋት ባይኖረውም ግን እግዚአብሔር የሰጠውን የእርሻ ጥበብና መሬት ተጠቅሞ ያመረተውን ወይን ግን አስካሪ መጠጥ ጠምቆ ራቁቱን በድንኳኑ እስኪጋደምና ራሱን እስኪጥል መድረሱ ግን በደል ነበር፡፡ እግዚአብሔር የሰጠንን ነገር ተጠቅመን ራቁታችንን የሚያስቀረንን ነገር የምናደርግ ሰዎች ብዙ ነን፡፡ እግዚአብሔር በሰጠን እውቀት ተጠቅመን የምንታበይና የአመጻ መሣሪያ የምናደርገው ብዙዎች አለን፡፡ እግዚአብሔር የሰጠንን መልክና ቁመና፣ ሀብት፣ ክብር፣ ስልጣን፣ ጤና ወዘተ ተጠቅመን ሌሎችን የምናስጨንቅ፣ ለጣኦት የምንሰዋ ወዘተ ብዙዎች ነን፡፡ መጠጥም እግዲህ እደዚሁ ነው፡፡ ሰዎች እግዚአብሔር የሰጣቸውን ነገር ተጠቅመው ጤናማ አሠራራቸውን በማዛባት አቅል አሳጥቶ በተንኮልና በአዋራጅ ማንነት እንዲተካ የሚደርጋቸውን መጠጥ ይሰሩበታል፡፡ ሰዎች መንፈሳዊ ኪሳራቸውን ለመሸሽ መጠጥ ውስጥ ይደበቃሉ፡፡ በስካር ሞቅታ ተንኮልን ይናገራሉ፣ በዝሙት ቀንበር ሥር ይወድቃሉ፣ ወደማይወጡበት የሱስ ቀንበር ሥር የወደቁትን በርካታ ወገኖች ቤታቸው ይቁጠራቸው፡፡

 

ብዙዎች መጠጥን ሲጀምሩት ሰካራም ለመሆን አቅደው ላይሆን ይችላል፡፡ ተማርን አወቅን የሚሉ ኬሚስቶችና የሕክምና ባለሞያዎች ሰውነታችን አልኮልን በተወሰነ መጠን እንደሚፈልገው ይነግሩናል፡፡ ሌሎች ደግሞ “አንስከር እንጂ አትጠጡ አይልም” በሚል ፈሊጥ መጠጥን ይጀምራሉ፡፡ ይሁንና ብዙዎች እንደዋዛ መቀማመስ የጀመሩት አልኮል መርዝ ሆኖባቸዋል፡፡ ደፋሮቹ በአደባባይ በመጠጣት ገንዘባቸውን ያለአግባብ ሲረጩ፣ ትዳራቸው ሲፈርስ፣ ቤተሰባቸው ሲበተን፣ ጤናቸው ሲታወክ፣ ሥራቸውን ሲያጡና ተግባራቸውን ሲፈቱ፣ ጤናቸው ሲቃወስ ሌሎች መድፈር የተሳናቸው ደግሞ ጨለማን ተገን አድርገው በየጥጋጥጉ ሲጠጡ፣ የሚያያቸው ሲሰናከል፣ በዝሙትና በመዳራት በከንቱ ዘመናቸውን ሲፈጁ እንዲያው እንደዋዛ አሉ፡፡

 

የአልኮል መጠጥ በክርስቲያኑ ሕብረተሰብ ዘንድም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እየተዘወተረ ይገኛል፡፡ በስራ፣ በፊልድና በተገኘው አጋጣሚ ወደ ሌላ አካባቢ ሲሄዱ ከቢራና ከወይን ጀምሮ ሌሎች ብዙ ነገሮች በዓይናቸው ሲዞሩ ቀኑ አልቆ ምሽት ላይ እስኪገናኙት ቀኑ አልመሽ፣ ሥልጠናው፣ ስብሰባው አላልቅ የሚላቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ መጠጥን ተከትለው ለሚመጡ መንፈሳዊ እርቃን የተጋለጡ ብዙዎች ናቸው፡፡ ብዙ አማኞች የቢራውን ኢንዱስትሪ በአክስዮን ግዢ፣ በቢራ ፋብሪካዎችና የሽያጭ ማዕከላት ተቀጥሮ በመሥራትና በመጎንጨትም ጭምር እየተቀላቀሉት ነው፡፡ "ምናለበት? አትስከሩ እንጂ አትጠጡ አላለም...ወዘተ” የሚባሉ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት የጎደላቸው አባባሎች ተበራክተዋል፡፡" አዳዲሶቹ ከውጭ የመጡ የቢራ ድርጅቶች አማላይ ክፍያና ጥቅማ ጥቅሞች የብዙውን አማኝ ልብ ሰርቀዋል፡፡ አዳዲስ የትምህርት ንፋሶች ብዙዎችን እንደወሰዱት ሰሞነኛው ቢራም ብዙዎችን ከጎናችን ማርኮ ወስዷል፡፡

 

አንድ የቅርብ ወዳጄ ከአዲሶቹ የቢራ አቅራቢዎች በአንዱ ተቀጥሮ ለመስራት ተወዳድሮ ካለፈ በኋላ አስተያየቴን መስማት ፈልጎ ላቀረበልኝ ጥያቄ የሰጠሁት ምላሽ ትዝ ይለኛል፡፡ በአጭሩ ያልኩት "አንተ ትክክል እንደሆነ የማታምንበትን ነገር ሌሎች እንዲያደርጉት ለምን ታመቻቻለህ?" ነበር፡፡ እርሱ በወቅቱ አይጠጣም ነበርና፡፡ በኋላ ላይ ግን ወዳጄ በቢራ አቅራቢው ድርጅት ቁልፍ መደብ ላይ ሥራ ተቀጥሮ የአቋም ማሻሻያ አድርጎ ነበርና ቤቱ በሄድኩበት አጋጣሚ ፍሪጁ ውስጥ በርካታ ከተለመደው ጠርሙስ ለየት ባለ ሁኔታ የታሸጉ ቢራዎችን ተመለከትኩ፡፡ መጤው ግዙፉ ፋብሪካ ለሠራተኞቹ በሣምንት 2 ሣጥን ቢራ በነፃ ይሠጣል፡፡ አዳዲሶቹ የቢራ ጠማቂዎች ሳይመጡ ከዓመታት በፊት እኔም ከታዋቂዎቹ የቢራ ፋብሪካዎች በአንዱ ማርኬቲንግ ማናጀር ሆኜ እንድሠራ በአንድ ወዳጄ “ሪኮመንዴሽን” እድሉ ገጥሞኝ ነበር፡፡ አጭሩ ምላሼ "እግዚአብሔር ያስተማረኝ ቢራ እንዳሻሽጥና እንዳጣጣ አይደለም!" ነው፡፡ በእኔ ላይ የበለጠ የመንግስቱ ሥራ ዓላማ አለውና፡፡

 

በዚህ ዘመን በኃይማኖት በዓላት ላይ ዳሶች ተጥለው ሲጠጣ፣ ሲሰከርና ሰዎች ሲዳሩና ሲዘሙቱ ውሎ ማደርና መሰንበት የኃይማኖታዊ ስርዓቶች ዋና አካል ተደርጎ እየታየ የመጣበት ነው፡፡ ዓመታዊ ኃይማኖታዊ በዓላትን ስፖንሰር የሚያደርጉት ታዋቂ የቢራ ጠማቂዎች ከሆኑ ሰነባብቷል፡፡ ለዚህም የሚሰጠው የተለመደው ምክንያት “መጽሐፍ ቅዱስ መጠጣትን አይቃወምም” የሚል ነው፡፡ ይሁንና መጽሐፍ ቅዱሳችን በሰዎች ስርዓት ላይ ተመሥርቶ የተጻፈ እንደመሆኑ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ከማሳየት ባሻገር የሚያሰክር መጠጥን ስለመጠጣት የሚመክርበት አጋጣሚ የለም፡፡ እንዲያውም ሰካሮች የእግዚአብሔርን መንግስት እንደማይወርሱ ይናገራል፡፡ ስካር አዋራጅና እርቃንን የሚያስቀር መሆኑን ይናገራል፡፡

 

በብሉይ ኪዳን ዘመን ነፍሳቸው ለመረረችባቸው እንዲሁም ሞት ለተፈረደባቸው ሰዎች ብርቱ መጠጥ ይሰጥ እንደ ነበር ተመልክተናል፡፡ ጌታችን ኢየሱስም በመስቀል ላይ እያለ እንደ ጊዜው ሥርዓት የቀረበለት ድብልቅ መጠጥ ነበር፡፡ እርሱ ግን አልተቀበለውም እንጂ፡፡ የነፍስ ምሬትና ተስፋ የመቁረጥ ጨለማ ከእግዚአብሔር መንገድ በመውጣትና በዓለም ጨለማ ጋር ከመኖር የሚመጣ ነገር ነው፡፡ አምላካቸውን የማያውቁና በትክክለኛው መንገድ ላይ ያሉ ሰዎች ተስፋ ይኼው ነው፡፡ በጨለማና በነፍስ ምሬት ውስጥ ያለ ሰው ያለበትን ሁኔታ ለመርሳት ብርቱ መጠጥ ይጠጣል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣው በጨለማ እንኖር የነበርን እኛ ወደ ብርሀን እንድንወጣና የእግዚአብሔር መንግስት ወራሾች እንሆን ዘንድ ነው፡፡

 

ብሉይ ኪዳን አካል የሆነው ክርስቶስ የክህነት አገልግሎት ጥላ ነው፡፡ እግዚአብሔር በክርስቶስ በኋለኛው ዘመን ላደረገው ራሱን ከሰዎች ልጆች ጋር የማስታረቅ ሥራ ምሳሌና ጥላ ነው (ዕብ 8÷5፣ 10÷1) ፡፡ በአዲስ ኪዳን ብርቱ መጠጥ ሳይሆን የኢየሱስ ደም ነው ነፍሱ ለመረረችበት መፍትሔው፡፡ እርሱ ኢየሱስ “ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፡፡ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሳዋለሁ፡፡ ስጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነው፡፡ ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ” እንዳለው፡፡ 

 

የመጠጥ ጅማሮ በድጥ ቁልቁለት ሥፍራ ላይ ወይም በበረዶ መንሸራተቻ ላይ አንድ ሁለቴ ቁልቁል ተራምዶ ለመቆም እንደመሞከር ነው፡፡ መንሸራተቻው ቁልቁል አንደርድሮ ታች ሳያደርስ እንደማይበርድ ሁሉ መጠጥም አንዴ ይጀምሩት እንጂ ወደማይወጡበት አረንቋ ለመወረዱ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ቃሉ “ርኩሱን ነገር አትንኩት” የሚለው ለዚያ ይመስለኛል፡፡ አንዴ ከነኩት በኋላ መላቀቁ ከባድ ነውና፡፡ ከመጠጥ ጋር በተጓዳኝ ከሚመጡ የርኩሰት ልምምዶች መላቀቁም የዚያኑ ያክል ከባድ ነው፡፡ ብዙ አማኞች በዚህ ጠንቅ ተይዘው በዝሙት፣ በለብታ ክርስትና፣ በፍሬ አልባ ሕይወት፣ በገንዘብና በዚህ ዓለም ፍቅር፣ በሥጋዊነት ወዘተ ውስጥ የየዕለት ኑሮአቸውን ይገፋሉ፡፡ በቤቱ አሉ፣ “ትልልቅ” አሥራትና መባ ያወጣሉ፣ ይሰብካሉ፣ የከበሬታ ሥፍራ ይቸራቸዋል… ግን ኑሮአቸው ሕይወት አልባ የሆነባቸው በርካቶች በዚህ የመጠጥ ጠንቅ በመጠመዳቸው የዓለምና የሥጋ እንዲሁም የሰይጣን ሽንገላ በመታለለል ስለወደቁና ከቃሉና ከመንፈሱ ስለራቁ ነው፡፡    

 

በጌታ ቤት ላለን ርኩሱን ነገር ተራ እደሆነ የሚያሳዩንና የሚመክሩን፣ የሚወተውቱንና የሚያማልሉን ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡ “ቢዝነስና ክርስትና የተለያዩ ናቸው” በሚል አጉል ፈሊጥ በርካታ ወገኖች የትርፍ የሚመስል የኪሳራ ኑሮ ውስጥ ናቸው፡፡ በአንድ ሰሞን በቢዝነሳቸው የአልኮል መጠጥ የማይሸጡና በሆቴላቸው መጠጥና ሴተኛ አዳሪነትን የማያስተናግዱ ነጋዴዎች ዛሬ ላይ “ተወዳዳሪ መሆን አልቻልንም” በሚል እስከ አንገታቸው ድረስ ተነክረውበታል፡፡ ጸንተው ለሚቃወሙ ደግሞ ሌላ አማራጭ ቀርቧል፡፡ ሀረር ሶፊ፣ ማልታ ወዘተ በሚል የቁልምጫ ስም ክርስቲያኑን የቢራ ጠርሙስ ለማስጨበጥ የሚደረጉ ጥረቶችን ነቅቶ መከላከል ያስፈልጋል፡፡ ዛሬ ላይ ብዙ የመድረክ አገልጋዮች የመጠጥ ምርጫ ቀን ቀን ገና ቁጭ እንዳሉ ማልታ ወይ ሀረር ሶፊ ሲሆን ማታ ማታ ደግሞ አክሱሚት፣ ወዘተ የሚባሉ ስማቸውን በቅጡ የማላውቃቸው የወይን ጠጆች ናቸው፡፡ ይህንን የሚመለከቱ መንጎቻቸው የእነርሱን አርኣያ ተከትለው በጠጭነትና ስካር የከንቱነት ኑሮ ውስጥ ገብተዋል፡፡ እነዚህ “አገልጋዮች” በመድረኮቻቸው “አትስከሩ እንጂ ብትጠጡ ምንም አይደለም” የሚል አንድምታ ያለው ስብከት ሲዳዳቸው ይታያል፡፡ “ጌታ የሱስም እኮ ውሀውን ወደ ወይን ጠጅ ለውጦአል… ዋናው አለመስከር ነው…” የሚል አስተምህሮ እየጀማመረው ነው፡፡ ወገኖቼ በቅድሚያ ያ የወይን ጠጅ ይዘቱ ምን እንደሆነ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ መጠጥ እግዚአብሄር በሰጠን ነገር አመጽን እንድንለማመድ የሚያደርግና የእግዚአብሄርን ቁጣ ወደሚቀሰቅስ ተግባር የሚመራንን ተግባር እንዲንፈጽም የሚያደርገን ነገር ነው፡፡ እንደ ዋዛ የተጀመረ አልኮል መቀማመስ ነገ መላ መንፈሳዊ ሕይወታችንን በመግፈፍ እርቃን አስቀርቶ ከእግዚአብሔር ክብር የሚያጎድለን ጣፋጭ መርዝ ነው፡፡ በአንድም በሌላም በዚህ ሕይወት ውስጥ የገባን ሰዎች ንስሀ ገብተን ወደ ቀደመው ሕይወታችን ልንመለስ ዘንድ ያስፈልጋል፡፡

 

አበቃሁ

 

Read 11121 times Last modified on Tuesday, 28 July 2015 14:50
Mesay Matusala

Mesay Matusala is a single (unmarried) man and a member of Hawassa Tabor Mekane Yesus congregations in Hawassa. He is a business and development professional, working employed for the last 7 years. Currently is focusing on writing, translation, and preparing to start a company in children and youth development and entertainment.

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 186 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.