You are here: HomeOpinionsየስማበለው ክርስትና

የስማበለው ክርስትና

Written by  Tuesday, 30 December 2014 00:00

“ሕይወት የሚገኝበትን ትምሕርት የማይታገሱበት ዘመን ይመጣልና ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለ ሆነ እንደገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ፡፡ 2ጢሞ 4፣3”

 

ሰሞኑን በአንድ የባጃጅ ታክሲ ውስጥ ተሳፍሬ ሳለሁ የገጠመኝን ላውጋችሁ፡፡ በባጃጁ የፊት መስታወት ላይ ባማረና አይንን በሚስብ መልኩ የተለጠፈ የመጽሐፍ ቅዱስ የሚመስል ጥቅስ ተመለከትኩና ወትሮ እንደማደርገው አነበብኩት፡፡ “የቀረበ ወዳጅ ከራቀ መንገድ ይሻላል፡፡ ምሳሌ 27፣1” ይላል፡፡ የጥቅሱ እንግዳነት በጣም ስለገረመኝ በተንቀሳቃሽ ስልኬ ላይ የነበረውን መጽሐፍ ቅዱሴን ከፈትኩና ምሳሌ 27፣1ን ተሳፋሪዎችና ሾፌሩ እስኪሰሙኝ ድረስ ድምጼን ከፍ አድርጌ አነበብኩት፡፡ በቀ.ኃ.ስ የአማርኛ ትርጉም ክፍሉ (ምሳሌ 27፣1) እንዲህ ይነበባል፡- “ቀን የሚያመጣውን አታውቅምና ነገ በሚሆነው አትመካ” በታክሲውና በመጽሀፍ ቅዱሱ ጥቅስ መካከል ያለው ልዩነት የሚገርም ነው፡፡ አይደል? ምናልባት በቁጥር ስህተት ይሆናል ብዬ ተቀራራቢ ጥቅስ ስፈልግ በምሳሌ 27፡10 ላይ እዲህ የሚለውን አገኘሁ፡- “ወዳጅህንና የአባትህን ወዳጅ አትተው፤ በመከራህም ቀን ወደ ወንድምህ ቤት አትግባ፤ የቀረበ ወዳጅ ከራቀ ወንድም ይሻላል፡፡” እንግዲህ እዚህ ላይ በታክሲው ጥቅስ ጸሐፊዎች የተፈጸሙ ሁለት መሠረታዊ ስህተቶችን ወይም ቅጥፈቶችን እናያለን፡፡ አንደኛው ጥቅሱ በተባለበት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ተጽፎ ያለመገኘቱ ነው፡፡ የምዕራፉ ቁጥር ምናልባት የታይፕ ስህተት ይሁን ብንል እንኳን “ከራቀ መንገድ” የሚለው ሀረግ ግን ሆነ ተብሎ ለማወናበድ የተጨመረ እንደሆነ በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡ የዚህ አይነት የሀሰት ጥቅሶች በየታክሲው፣ በየትራንስፖርት ተሸከርካሪው፣ በፌስቡክና በተገኘው ሚዲያ ሁሉ ሆነ ተብሎ በመሰራጨት ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ምናልባትም መጽሀፍ ቅዱሳቸውን በአግባቡ የማንበብ ልምድ የሌላቸው ብዙዎች እየተወናበዱና እየሳቱ ይሆናል፡፡ “የቃል እውቀታቸው” በአብዛኛው ከመድረክ በሚሰሙትና በጨረፍታ ከየሚዲያው ላይ ከሚመለከቱት “ጥራዝ ነጠቅ” ጥቅሶች ላይ የተመሰረተ ሰዎች በቀላሉ ለመታለል የተጋለጡ ናቸው፡፡ ዛሬ ዛሬ የተዛነፉና ከእውነታው በዘዴ ፈቀቅ የተደረጉ ትምህርቶች መድረኮቻችንንም እየተቆጣጠሩት ነው፡፡ የወንገጌሉና የክርስቶስ ጠላቶች የሚከፈለውን ሁሉ ከፍለው መንጋውን ለማሳት ተግተው እየሰሩም ነው፡፡ 

 

በዘመናችን መጽሐፍ ቅዱስን በርዞ መተርጎም በአንዳንድ ተቋማትና ቡድኖች እየተለመደ ነው፡፡ አንዳንዶች የራሳቸውን ፈሪሳዊ ክብርና ኃይማኖታዊ ሥልጣን እንዲሁም “የአደባባይ ከበሬታ” ፍለጋ ራሳቸውን “አምላክ” እያደረጉ እውነተኛውን የአምላክ ቃል እለወጡ ይገኛሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ ተገፍተው እውነተኛውን ወንጌል ለመቀየጥና ለመሸቃቀጥ ላይ ታች የሚሉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የተለያዩ ከኢንግሊዝኛ ቋንቋ ወደ አማርኛችን የሚተረጎሙ መንፈሳዊ መጽሐፍት ሆነ ብለው አጣምመው፣ እውነቱን አንሻፍፈውና በራሳቸው አስተምህሮ በርዘው በሚተረጉም ክፍሎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ እውነተኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት (የቃሉን ወተት) በመመኘት የማይተጋው የዘመናችን አማኝ ለዚህ አስፈሪ ሐሰተኛ አስተምህሮ እጅጉን ተጋልጦ ይገኛል፡፡ ከየመድረኩና “ኮንፈረንሱ” እንዲሁም በየጊዜው ከተነሳውና ነቢይ ነኝ ባይ ሁሉ ስብከት በተለቃቀመ ሽርፍራፊ ትምሕርት ክርስትና የማይዘለቅበት ዘመን ላይ እንገኛለንና ወገን እንንቃ!

 

የሀሰት ትምኅርት አስተማሪዎች ጥንት በብሉይ ኪዳን ዘመንም ነበሩ (ዘዳ 18፡22፣ 2ዜና 18፣ ኤር 14፡11-16፤ 23፡16፤ 29፡26፤) እነዚህ ነቢያት ነን ባዮች እግዚአብሔር ያላለውን አለ እያሉ ከራሳቸው የሚናገሩ ደፋር ነቢያት ነበሩ፡፡ ሀሰተኛ መምህራን በአዲስ ኪዳን ዘመን በይበልጥ ጎልተው ይታያሉ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ የነበረውን ቆይታ ፈጽሞ ወደ ሰማይ ወደ አባቱ ከአረገ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ የሚያሰራጩትን እውነተኛ ወንጌል በሀሰት ትምህርታቸው የሚገዳደሩ ብዙዎች ነበሩ፡፡ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በላከው መልእክት ውስጥ የጠቀሳቸው ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ እንዲሁም ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ በጥንቷ ቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥም ጎልተው የወጡና እውነተኛውን ትምህርት የሚያውኩ እንደ አሪዮስ ያሉ ሐሰተኛ አስተማሪዎች ነበሩ፡፡ በወቅቱ የነበሩ የእምነት አባቶች እውነተኛው ወንጌል ሳይበረዝ ለትውድ እንዲተላለፍ ብዙ ጥረዋል፣ የህይወታቸውንም መስዋዕትነት የጠየቀ የሰማዕትነትን ዋጋ ከፍለው እውነተኛው ወንጌል ከዛሬ እንዲደርስ አድርገዋል፡፡

 

ዛሬም በዘመናችን በርካታ እውነተኛውን ወንጌል በሌላ ውሸተኛ ወንጌል ደባልቀው የሚያስተምሩ በመካከላችን ብዙዎች ናቸው፡፡ ብዙዎቹ ሐሰተኞች በአዲስ ቋንቋ(በልሳን) እየተናገሩ፣ ታምራትና ድንቅ በእነርሱ እየተደረገ፣ “ቸርች ወይም ሚኒስትሪ ከፍተው” ወዘተ ነው የሚያስቱት፡፡ ግባቸው እንጀራ፣ ከበሬታና ዝና ብሎም ገንዘብና ተዛማጅ ስጋዊ ፍላጎት ስለሆነ ስለ መንጋው ግድ የላቸውም፡፡ ጥቂት የማይባሉት በእነርሱ ድንቅና ተአምራት እየተደረገም እያለ አሳሳች ትምህርት ስለሚስተምሩ ብዙዎችን በቀላሉ ያስታሉ፡፡ የሕይወት ምስክርነትና ፍሬአቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባይሆንም በእነርሱ የሚከናወነው ድንቅና ተአምራት ትክክለኛ እንደሆኑ እንዲቆጠር ስለሚያደርግ አኗኗራቸው በብዙዎች ይኮረጃል፡፡  ዛሬ ላይ ፍቺ መፈጸም፣ ከጋብቻ በፊት ሩካቤ መፈጸም፣ የሀሰት ረብ መሰብሰብ፣ ግፍ፣ አታላይነት፣ ማጭበርበር፣ ውል ማፍረስ እና ሌሎችም መጽሐፍ ቅዱሳችን በግልጽ ኃጢአት እንደሆኑ የሚያስተምራቸው ነገሮች ሐጢአት መሆናቸው ቀርቶ “ክርስትና በመነሳት” የብዙዎች የክርስቶስ ተከታይ ነን ባዮች የየእለት ኑሮ አካል ሆነዋል፡፡ ዛሬ ላይ በሚያሳዝን መልኩ ብዙዎች ስተው ጳውሎስ የገላቲያን ሰዎች ወደሚላቸው አይነት ሌላ የምቾትና የመንቀባረር ልዩ ወንጌል ገብተዋል፡፡ እምነትና በጎ ህሊና ሳኖራቸው ብዙዎች የእውነት በሚመስል ትምህርት ተጠምደው ሌሎችን በማሳት ላይ ይገኛሉ፡፡ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ስለወንጌል ዋጋን መክፈል የማይፈልጉና “መልካሙን የሕይወት ቃል እንዳይሰሙ ጆሮአቸውን አውቀው የደፈኑ” የሚላቸው አይነቶቹ ዛሬ ብዙዎች ሆነዋል፡፡ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ራሳችንን መመርመር ያለብን ወቅት ቢኖር አሁን ነው፡፡

  

ትልቁና በአሳሳቢ መልኩ ዛሬ ላይ ጎልቶ የሚታየው የችግሩ ምንጭ አማኙ በግሉ መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ አለማጥናቱና ከእግዚአብሔር ጋር በግሉ ኅብረት አለማድረጉ ነው፡፡ የቡድን ጩኸት፣ የቡድን አምልኮ፣ ቅይጥ ክርስትና፣ እንዲሁም ችግር ወይም መከራ የለሽና ራስ ተኮር ክርስትና ፋሽንና የዘመናዊነት መገለጫ እየሆነ የመጣበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ ራስን መለየትና ማዳን ያስፈልጋል፡፡ ከቃሉና ከመንፈሱ ጋር ኅብረትን ማደስ ያስፈልጋል፡፡ መጽሐፍም እንደሚል “ሆኖም ጌታ ለእርሱ የሆኑትን ያውቃል፡፡ በትልቅም ቤት የእንጨትና የሸክላ ዕቃ ደግሞ አለ እንጂ ወርቅና የብር ዕቃ ብቻ አይደለም፤ እኩሌቶቹ ለክብር እኩሌቶቹ ደግሞ ለውርደት ይሆናሉ፡፡ እንግዲህ ማንም ራሱን ከነዚህ ቢያነጻ ለክብር የሚሆን የተቀደሰም ለጌታውም የሚጠቅም ለበጎም  ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ እቃ ይሆናል፡፡” 2ተኛ ጢሞ 2፤19-22 

Read 8485 times Last modified on Tuesday, 30 December 2014 08:15
Mesay Matusala

Mesay Matusala is a single (unmarried) man and a member of Hawassa Tabor Mekane Yesus congregations in Hawassa. He is a business and development professional, working employed for the last 7 years. Currently is focusing on writing, translation, and preparing to start a company in children and youth development and entertainment.

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 281 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.