You are here: HomeOpinionsየማንን ጥያቄ ልጠይቅ?

የማንን ጥያቄ ልጠይቅ?

Written by  Monday, 27 July 2015 04:25

በርካቶች ይጠይቃሉ፤ የጥያቄያቸውም መዳረሻ  ግን ራሳቸው አይደሉም፡፡ ጉጉታቸውም ሆነ ኳተናቸው ሸልቅቆ መመልከት የሚፈልገው የሌላን ሰው ህይወት ነው፡፡ እንዲያ አይነቱ ፍላጎት በልጓም ተገቶ፣  ከምንም በፊት የራሱን መንገድ እንዲጠበጥብ ሊደረግ ያሻል፡፡ ደግሞስ ከአጭር እድሜያችን ጋር የማይመጣጠን ስንት ስራ ባለበት በዚህች ምድር መቼስ ግዜ ተረፈን!? ተመትሮ በተሰጠ እድሜ፣ የሰውን ሚስጥር እያነፈነፉ መፈለግ በእርግጥም ከብኩንነትም እጅጉን የከፋው ነው፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ እንዲህ አይነት አእምሮሮ ለሌላው ሰው ጓዳ ወይም ግለኝነት አክብሮት ያለው አይመስልም ፡፡ የሌላ ሰው ህይወት አንኳክተን ሲፈቀድልን፣ በብዙ ምስጋና፣ እንዲሁም እግዚአብሔርንም በመፍራት ልብ የምንገባበት ስፍራ መሆን አለበት፡፡ በምንም መልኩ ቀን ተሌት ነቅተን፣ አጋጣሚ ጠብቀን፣ በማድባት የምንሰልለው ስፍራ ሊሆን አይገባም። እንዲህ ካደረግን ደግሞ ለሀጢያት ፈንታ መስጠታችን ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ለእህቴ ህይወት ካለኝ ትልቅ ክብር የተነሳም የቤታችን ሳሎን ጠረጴዛ ላይ የተቀመጠው የየግል ህይወቷን የሚከተብበት ማስታወሻ፣ ያለ ፍቃድ ተደብቀህ ተመልከተኝ በሚል አይፈትንኝም፡፡ ባየሁት ቁጥርም አንፋጠጥም፡፡ ያለ መፈተኔ ምክንያት ደግሞ ሌላ አይደለም፤ የህይወት ጥያቄዎቼ በዋነኛነት የእኔው ጥያቄ መሆን አለባቸው ከሚል ፈርጣማ አቋም እንጂ!

 

ከሁሉ በፊት ደግሞ ስለ የራሳችን ጥያቄዎች በመጠየቁ ተጠቃሚው እኛው ነን፡፡ የሌሎችን ጥያቄ ከእኛው አስቀድሞ የማቡካቱ ችግር ራሳችንን አዘንግተው ስለሌሎች በማብሰልሰል እኛውኑ አብሳዮቹን በጠኔ መጥበሳቸው ነው፡፡ በዚሁ ስሌት ከቀጠልን ከሚያበስለው አንዳች የማይቀምስ ከሲታ ወጥ ቤት መምሰላችን አይቀርም፡፡ በዚህ መንፈስ የተጠየቁ ጥያቄዎች ብቻ ሳይሆን መልሶቻቸውም ችግር አለባቸው፤ ያውም እጅግ የከፋ! ከምንም በፊት፣ መልሶቻችን አርቴፊሻል የመሆን እድላቸው ሰፊ ነው፡፡ የሚያረኩትም አውነተኛ ባለጥያቄዎችን ሳይሆን እኛን መሰል ጥያቄያቸው ሳይሆን የሚሰሙንን ነው፡፡ መልሶቻችን፣ በጥያቅው እሳት በበቂ አለመለብለባችን ያስታውቃሉ፡፡ ጥልቀት የሌለው ምልከታችን ደግሞ ርህራሄ በሌለውና በሌላው ማላገጥ ተለውሶ እንደመቅረቡ የተጋገረበት ምጣድ በደንብ እሳት እንዳልመታው ያስታውቃል፡፡ ጥያቄዎቻችን መልሶች አለመሆናቸውን ከሚያሳብቁ መረጃዎች አንዱ አገልግሎቻንን የከበቡት በሌሎች ድካም መሳቅ የሚወዱ መሆናቸው ነው፡፡ ባለ እውነተኛ ጥያቄዎቹ ግን ሁል ጊዜ ይሸሹናል፡፡

 

ጥያቄዎቹ የተውሶ እንደ መሆናቸው፤ ልብ ብሎ ላየውና ጥያቄው ለሆነ ተመልካች ሁሉ ያሳብቃል፡፡ በህይወት ስንጠይቅ ስንል፣ ልባችን ቦታ ያገኙ ማለት እንጂ የግድ እኛው በግለቱ በቀጥታ ተተኩሰን ማለፍ አለብን ማለት ግን አይደለም፡፡ አለበለዚያማ፣ ”ያልፈታ ስለፍቺ አያውራ” አይነት ነው ነገሩ! ሳይፈቱ ስለፍቺ በሚራራ ልብ ለማውራት የሚደፍር ልብ ግን ከምንም ቀደም ጥያቄውን በባለቤትነት በልቡ ማሳደር ይኖርበታል፡፡ የጥያቄው ክብደት፣ ልክ የፈታ ሰውን ያህል ሊያሳድደው  ያሻል፡፡ ጥያቄው የእኛ ሲሆን ባለ ጥያቄዎቹ እኛው ጋር መጥተው ያርፋሉ፡፡

 

የእኛ ያልሆኑ ጥያቄዎችን መጠየቅ ሌላው ችግሩ፣ እርካታችንን በተቀበልነው ሽልማት የመመዘን አባዜ መፍጠሩ ነው፡፡ ሌሎች እስካልሰሙት ወይም በአደባባይ መልስ አግኝተውለታል ተብሎ ካልተነገረለት ያመናል፡፡ መልስ ያገኘን የመሰለን ቀን በአብሮነት መድረክ ያምረናል፡፡ ምኞት ደግሞ ያቅበዘብዝ የለ! ያለ ርህራሄ እግራችን እስኪነቃ የሰሚ ፍለጋ እንሾራለን፡፡ በዚሁ ስሌት አምጠን እንካችሁ ላልነው መፍቴም እውቅና ስናጣም፣ ለሌሎች ያለን መራርነት ይጎመራል፡፡ የተገፋን ያህል ይሰማናል፡፡ የእኛውኑ ጥያቄ መጠየቅ ግን መልስ ነው፤ ያውም ለራሳችን! እረፍቱም የሚጀምረው እኛው ልብ ነው፡፡በዚህ ልብ ውስጥ ቢበዛ የሚፈጠረው ፍላጎት ሸክም እንጂ አደባባይነት አይደለም፡፡ ሸክም ደግሞ በሀላፊነት እንዲሁም በብዙ ርህራሄ የሚወጡት ተልእኮ እንጂ ታዋቂነትን ለመሸመት የሚወጡበት የአደባባይ ገበያ አይደለም፡፡ እርካታው ከብዙ ጭብጨባ በፊት የውስጥ ሰላም ነው፡፡

 

ጥቂት ቆርሰው እውቅና የሰጡንም በዛው ጉዳይ የምንፈልገውን ያህል አያላዝኑም፤ ትተውን ይሄዳሉ፡፡ ጥያቄያቸው ወይ ይመለስና ይዘነጉታል አሊያም ሌላኛው ያልተመለሰላቸው ጥያቄያቸው ይበልጡኑ ጠንግፎ ይይዛቸዋል፡፡ ጥያቄያችንን ከሌሎች የምንጀምር ከሆነ ግን የምንፈልገው ሁሌ እንዲወራልን ነው! በሰዎች ልብ መቆየት በተለይም ደግሞ ለዘላለም መቆየትን ማሰብ በእርግጥም ተላላነት ነው፡፡ ሰው እኮ ልቡ እንኳን ለሌላ ለራሱ ጉዳይ እየጠበበችው ነው! ለዚህም ነው መሰለኝ አንዱን ሲያነሳ ሌላውን የሚጥለው፡፡ ሰው ልብ የመቆየት እውነታችን አናሳ ሆኖ ሳለ፣ ሌላውን መአከል ባደረገ መልኩ መሾራችን በእርግጥስ ምን ይሉታል! ጥረታችን በሌላ መልኩ ሲታይ እንካችሁ ያልነው መልሳችን በነገረ ጉዳዩ ያሉትን ቀደምት እይታዎች የሚገዛ ሀሳብ ማመንጨትና ለክብራችን በአደባባይ ታንቡር እንዲመታልን ከመናፈቅ ጋር ይያዛል፡፡

 

ናፍቆታችን ግን ከንቱ ነው! እንንቃ፤ በተለይ በአደባባይ ያውም ዘመንኛ የመገናኛ ብዙሀን በፈጠሩልን መድረክ ያወቅናቸው፣ እኛኑ ለዘላለም የሚያኖሩበትን ሰፊ ትከሻም ሆነ ልብም የላቸውም፡፡ በፍጥነት ይተኩናል፤ ጣእማቸውም ይለወጣል፡፡ ከመድረክ ስንወርድ ሞቅ ባለ ፈገግታ ስለሸኙን ወይም ትከሻችንን ስለጠበጠቡን ለሁሌው በልባቸው የታተም አድርገን መቁጠር የለብንም፡፡ ይኽ መራሩ ህይወት አልዋጥልህ ካለን ደግሞ በርካቶችን በማስረጃነት መቁጠር እንችላለን፡፡ በማህበራዊ ድህረ ገጽ  ፈልገን የለጠፍናቸው ደግሞም መልሰን የረሳናቸውን ስንቶች ናቸው! አዎን! በብዙዎች ልብ መረሳት የአብዛኛዎቻችን እጣ ፈንታ ነው፡፡ እርግጥ ነው፤ አንዳንዶች መታወስንም ሌላ ተጨማሪ ስራ አድርገውተ ቆይታቸውን ማራዘም ችለዋል፡፡ እነርሱም ቢሆኑ ግን ቢረዝም ነው እንጂ ይረሳሉ፡፡

 

ለዘላለም መረሳት ካልፈለግን፣  ትኩረታችንም ለዘላለም ማስታወስ በሚችለው ላይ መሆን ይገባዋል፡፡ ትልቅ ትከሻ እንዲሁም ሰፊ ልብ ስላው እርሱ ከቶውን ያሳየነውን በጎነት አይረሳም፡፡ አውነተኛ ከፋይም እርሱ ነው፡፡ ስለዚህም ነው (ዕብ 6፡10) ፣ ” እግዚአብሔር፥ ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው፥ ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና።” በሚል መተማመን የተነገረለት፡፡ ዛሬም ታዲያ እንደ ነህምያም (13፡14) ፣ ”አምላኬ ሆይ፥ ስለዚህ አስበኝ ለአምላኬም ቤት ያደረግሁትን ወረታዬን አታጥፋ።” ብለንም መለመን እንችላለን፡፡ እርሱም በእርግጥ አያሳፍረንም ፡፡ የማይረሳን አስታዋሻችን እንዲሁም ዋጋችን ከፋይ እርሱ መሆኑን ስናውቅ በበጎነታችን ምላሽ ሳንጠብቅ መጽናት እንችላለን፡፡ ከሁሉ በፊት ደግሞ ጥያቄዎቻችንን እንጠይ፡፡ መልሶቻችን ደግሞ እረፍት ይሆኑልናል፡፡ ከበዛም ደግሞ በርህራሄና በሀላፊነት የምንተገብራቸው ሸክም ይሆናሉ፡፡ አምላካችን የሚያሳርፉንና ሸክም የሚያሳድሩ የራሳችንን ጥያቄዎች መጠየቅ እንድንችል ይርዳን!

Read 7841 times
Tekalign Nega

Tekalign Nega is a columnist of Hinstet, Psychology corner. He is a lecture at Addis Ababa University. He specialized at post graduate level Accounting and Finance, counseling psychology, and theology. He teaches also at theological colleges, trains leaders, and preaches the word of God upon invitation. He has burden to the church of Christ in various areas of counseling and Islam. Currently he is a PhD student at Tilburg University, the Netherlands.

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 118 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.