You are here: HomeOpinionsአምስት መሠረታውያን የእንግዳው ወንጌል ሕጸጾች።

አምስት መሠረታውያን የእንግዳው ወንጌል ሕጸጾች።

Written by  Monday, 07 September 2015 04:42

በጥንታዊትነቷ በምትታወቀው በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ብዙ ዘመን ዘለል አባቦሎች እንዳሉ ባውቅም መልዕክቴን ያጎሉልኛል የምላቸውን ላስታውሳችሁ፤ “ለነፍሱ ያደረ ለእግዚአብሔር ኖረ” ….. ‹‹ለሥጋው የኖረ ከመንገድ የቀረ›› ፡፡ ምናልባትም የዚህ ዐይነት አባባሎች ብህትውናን ያስፋፋሉ በመባል በመረሳት ላይ ይገኙ እንጂ ውስጣቸው ያለው ቁም ነገር  ዘመን ተሸጋሪ ስለመሆኑ አያከራከርም፡፡

 

የእኔ ዐይነቱ፡-በሃይማኖት ቤት ውስጥ ያደገ ፤ በተለይም በወንጌላዊያኑ ቤተ እምነት ውስጥ በአዲስና መጤ ትምህርቶች በእውነተኛው ክርስትና ትምህርትና እምነት ላይ ውዥንብር ባደረሰው የእንግዳ ወንጌል ትምህርቶች ቅየጣ ምክንያት ወዲህና ወዲያ ሲነወልል የኖረና ፤  በኮሙኒስት ርዕዮት ሊደፈጠጥ ባልቻለው ትመህረተ ክርስትና ባግባቡ  ተኮትኩቶና ስር ሰድዶ ያደገ አማኝ ቢኖር፡ ሊያስታውሳቸው የሚገቡ ትዝታዎች ይኖሩታል፡፡

 

ለምሳሌ በአንድ ወቅት ተነስቶ የነበረ የሐዋርያና የእርሱ ተማሪዎች የኢ ደብሊው ኬንየን እና የኬነት ሔገንን ትምህርት ያስፋፉበት ፣ ብሎም ከፍተኛ የሆነ የቅድመ ኢሕአዴግ አብያተክርስቲያናት በድኅረ ኢሕአዴግ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ያደርጉ የነበረው የማግለልና የማገድ ተግባራት ትዝታዎች ሊኖሩት ይገባል ብዬ አስባለሁ፡፡ በዚህ ዐይነቱ የትምህርት ነፋስ የተገፉ ብሎም ቀምሰው የተመለሱ ታላላቅ ወንድሞቼ የዚሁ ትምህርት ተሳታፊዎች እንደነበሩ አስታውሳለሁ፡፡ እኔም  በዕድሜ ትንሽ ልሁን እንጂ አብሬአቸው እሄድ ነበር፡፡

 

በክርስትና መሠረታዊ ትምህርት ተኮትኩቼ ያደኩት በምዕራብ አጥቢያ መሠረተ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ቢሆንም አዘውትሬ የእንግዳውን ወንጌል በሚያሰተምሩ አብያተ ቤተክርስቲያናትና አብያተ አገልግሎቶች  በመሄድ በርካታ መንፈሰዊ  ትምህርቶችን ተምሬያለሁ ፡፡

 

በርከት ያሉም የኬኒየንን ፣ የኬነት ሔገንና መሰሎቻቸውን መጻሕፍትን አነብ ነበር፡፡ የማነብብት ምክንያት ይቀየር እንጂ ፤ አሁንም ማንበቤን አላቋረጥኩም፡፡የእነዚህ አስተማሪዎች መሠረታዊ ትምህርት  ትኩረቱ ፡- ሃብት፣ ጤና እና ስኬት ላይ መሆኑን  በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ሃብት፣ ጤናና ስኬት ‹‹ሰው›› ለሆነ ማንኛውም ፍጡር የዘወትር ጥያቄዎቹ አንደሆኑ መገንዘብ ልብ ይሏል፡፡

 

ኢትዮጲያዊ ነኝ ፤ ኢትዮጲያ የጋራ ጥያቄዎቿን ለመፍታት በመንግሥት ከተቀረጸው የአመስት ዓመቱ የልማትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ  ባካተታቸው ዐበይት ግቦች ውስጥ ሦስቱ ፡- የኢኮኖሚ ልማትና ድኽነትን ቅነሳ  ፣ የጤና ዘርፍ ግቦችና ዓመታዊ ዕቅዶች እንዲሁም በአጠቃላዩ አገራዊ ስኬቶች ላይ ያተኮረ ነው፡፡

 

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከተናገሩዋቸው ንግግሮች  መካከል ‹‹ድኽነት ዋነኛው ጠላታችን ነው!›› የምትለውን  አባባል መላው የኢትዮጲያ ህዝብ በሚገባ የሚያስታውሰው  ነው፡፡  እኔም ድኽነትን አልወደውም ፤ አልፈልገውም፡፡ ድኽነትን አፍቅሮ ስለድኽነት የሚሟገትም ግለሰብ አላውቅም ለዚያውም ኢትዮጲያ ውስጥ፡፡ ስለ ጤንነትም ብጠየቅ በሽታን የምፈለግበት አንዳችም ምክንያት የለኝም፡፡ ለምንስ ብዬ እፈልግዋለሁ? የሰው ልጅ ባደረገው ከፍተኛ ትግል ድኽነትን ለማሸነፍና ሰዎች ሁሉ ከድኽነተ ወለል በታች እንዳይኖሩ ለማድረግ ቢጥርም እንስካሁን ሊሳካለት እንዳልቻለ ግን ዐውቃለሁ፡፡

 

የቅደመ ኢሕአዴግ አብያተክርስቲያናትን ጨምሮ በታላላቅ አብያተ ክርስቲያናት ሳይቀር የምንሰማው የወንጌል ‹‹አንኳር መልእክት›› መቀየሩን ሳናስተውል የቀረን አይመስለኝም፡፡ ይህ አዲስ ወንጌል ብዙ ተከታዮችን አፍርቶ ፣ ብዙ ሰባኪዎችን አስታጥቆ ለአያሌ ማኅበረ ምዕመናን ለጆሮ ጣፋጭ ከሆነም ሰነባብቷል፡፡

 

ይህ ልዩ ወንጌል በተለይም ሲታገዱና ሲገለሉ በነበሩት በአብዛኛው ሊባሉ በሚችሉ በድኅረ ኢሕአዴግ አብያተ-አገልግሎቶች  ውስጥ ሲሰበክ ቢቆይም እንደአሁኑ ተንቦርቅቆ የተወራበት ዘመን አልነበረም፡፡ ይህን ‹‹ወንጌል›› ወንጌል ካልነው፤ የብልጥግና ወንጌል  በመባል ቢታወቅም - ፤ እኔ ግን ይህን ወንጌል ‹‹ገዳይ›› ወንጌል እለዋለሁ፡፡ ትኩረቱን ሐብት፣ ጤና እና ስኬት አድርጎ ቀና ተናገር ቀና ይሆንልሃል በሚል ሳይኮሎጂ ታጅቦ አዲስ አባባን ብሎም በኢትዮጲያ ወንጌላውያን አማኞች ዘንድ አዲስ የተገኘ መገለጥ ሆኖ እንደገና ነፍስ በመዝራት  ላይ የሚገኝ ትምህርት ነው፡፡

 

ማንም ይስበከው ማንም ፤ ይህን ‹‹-አዲስ ወንጌል›› የሚሰብኩ ሰዎች አትኩሮትና ይዘት አንድ ብቻ ነው፡፡ ይህ አዲስ ወንጌል ‹‹ስግብግብነትን መሃከለኛ›› አድርጎ የሚያስተምረው ትምህርት፡- ሰዎች  ቁሳዊ ብልጥግና  እና ሐብት፣ ጤናማና የተሳካላቸው እንዲሆኑ  እግዚአብሔር ክርስቶስን ሰጣቸው የሚል ትምህርት ነው፡፡ የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ አስምልክቶ ከብልጽግናውም የከፋ ትምህርት እንዳለው ልብ ይላል፡፡

 

ኢትዮጲያ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ስም መጥራት አግባብ አይደለም የሚሉ ሰዎች በመበራካተቸው ያው ፈረንጆችን ልጠቅስ ፡- እንደ ሮበረት ቲልቶን ያሉ የእንግዳ ወንጌል ሰባኪዎች እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል ፡-‹‹እግዚአብሔር ሰዎች ሁሉ የተከናወነላቸው እንዲሆኑ ይፈለጋል ይህን የምለው የተከናወነላቸውን ሰዎች ስላየሁ ሳይሆን ፤ ቃሉ ይህንን ስለ ሚያረጋግጥልኝ ነው፤ በአንድ ሰው ሕይወት ውስጥ በዚሁ መንገድ በመሥራቱም አይደለም የምሰብከው፡፡ ዐይኖቼን በሰዎች ላይ አላደርግም ነገር ግን ለማበልጠግ ኀይልን በሚሰጠኝ በእርሱ ላይ ኣደርጋለሁ፡፡ አዘውትራችሁም በመጸለይ ለሚያስፈልጋችሁ ቁሳቁሶች ሁሉ ታዕምራታችሁን ጠብቁ››

 

አምስት መሠረታውያን የእንግዳው ወንጌል ሕጸጾች

ቅርብ ጊዜ  ወንድም ራስል ውድብሪጅ ‹‹, Wealth, and Happiness to Examine the Claims of Prosperity Gospel Advocates.›› የሚል ርዕስ ያላት መጽሐፍ የማንበብ ድል ገጥሞኝ ነበር፡፡ እንደዚህ ዓይነት መጽሃፍ በሃገሬ ቢታተም የሚል ቅናትም አድሮብኝ ነበር፡፡ እንደ ስሕተት መጽሐፍ ቅዱሳችን የሚቃወማቸውንና ከመጽሐፍ ቅዱስ እይታ በእንግዳው ወንጌል እንደ እውነተኛ ትምህርት የሚስፋፉ  የ‹‹አብርሃም ኪዳን ፣  ሥርየት ፣  መስጠት ፣  እምነትና  ጸሎትን›› በሚመለከቱ  አምስት  ዐበይት ጉዳዮች ላይ የእንግዳውን ወንጌል ስሕተቶች ለማሳየት  እሞክራለሁ፡፡

 

1ኛ.  ‹‹አብርሃም ኪዳን›› ለምድራዊ ቁሳቁሶች ይዞታና ማረጋገጫ ነው

የእንግዳው ወንጌል ተማሪዎችና አስተማሪዎች የ‹‹አብርሃም ኪዳን›› ለምድራዊ ቁሳቁሶች ይዞታና ማረጋገጫ እንደሆነ ያስተምራሉ፡፡ በዘፍጥረት 12 ፣ 15 ፣ 17 ፣ 22 እግዚአብሔር ከአብርሐም ጋር ኪዳን እንደገባ እናነባለን፡፡ የዚህን ኪዳን ፍጻሜ  ክርስቶስ በመሆኑ  - እኛም በክርስቶስ በኩል የተስፋው ወራሾች መሆናችንን በተሳሰተ መንገድ ያስተምሩታል፡፡ 

 

ክርስቲያኖች የአብርሃም መንፈሳዊ ልጆች እና በእምነት የበረከቱ ወራሾች ናቸው፡፡  በእንግዳው ወንጌል ሰባክያን ዘንድ ቀዳሚው የአብርሃም በረከት ቁሳዊ ይዞታን የሚያመለክት እንደሆነና በባርኮቱም ኪዳን መሠረት ስምምነቱ እግዚአብሔርን አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ያሰገባው ኪዳን እንደሆነ ያስተምራሉ፡፡ አማኞች በእምነት የአብርሃም በረከት ወራሾች በመሆናቸው ፤  ኪዳኑ  ‹‹እግዚአብሔርን››  የአብርሃም ወራሾች ለሆኑት  በቁሳቁሳዊ ባርኮት እንዲባርክ ያስገድደዋል፡፡ አማኞችም በዚህ ባርኮት ተባርከዋል፡፡

 

የኬኒየንን ትምህርት በመውሰድ በከፍተኛ ደረጃ በማስተዋቃቸወ ቀዳሚ በመሆን የሚታወቁት የዚህ እንግዳ ወንጌል መምህር ኬነት ኮፕላንድ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል ‹‹እግዚአብሔር ለአብርሐም የሰጠው ኪዳን በመፈጸሙና ፤ ብልጥግናም የኪዳኑ ዳረጎት ስለሆነ፤ ብልጥግና አሁን የእናንተ መሆኑን ልትገነዘቡ ይገባል››በማለታቸው ፡ ትምህርታቸው የአብርሃም በረከት ቁሳቁሳዊ በረከት እንደሆነ ይገልጣል፡፡

 

ይህንኑ ሃሳባቸውን ለማጽናት የእንግዳው ወንገል ሰባኪዎች ገላቲያ 3÷14 ‹‹…….የአብርሃም በረከት ወደ አሕዛብ ይደርስላቸው ዘንድ፡፡›› የሚለውን ቢጠቅሱም ፤  ይህችን ቁንጽል ጥቅስ በመውሰድ ለትምህርቱ ማጠናከረያ ቢያደርጉትም ፡ ‹‹….. የመንፈስን ተሰፋ በእምነት እንድንቀበል›› የሚለውን ክፍል ባለመጠቀማቸው ተስፋው ድነታችንን ያገኘንበት ክርስቶስን ማመላከቱ ይቀርና  ቁሳቁስ ወደ መሆን እንዲቀየር ያደርገዋል፡፡

 

ጳውሎስ በዚህ ክፍል ላይ የገላቲያን አማኞች ሊያስታውሰቻው የፈለገው  ደኅንነታቸውን  ለማረጋገጥ የሚያስፈልጋቸው ሃቅ ፤ ከሥጋ ፣ ከምድራዊ ሥራና አስተሳሰብ በመላቀቅ በአብርሃም በኩል እግዚአብሔር የሰጣቸውን ተሰፋ እርሱም ክርስቶስ በማወቅ የሚገኘውን ተሰፋ እንዲቀበሉ  እንጂ ቁሳዊ የሆነ ባርኮት እየጠበቁ እንዲኖሩ አልነበረም፡፡ እርሱም (ቁሳቁሳዊ ባርኮት) ለዘመናት የሚጠበቅ ተስፋ አልነበረም፤ ብዙም ባለጠጎች ይኖሩ እንደነበረ ቃሉ ይናገራል፡፡ ሀብትን እዲጠብቁ ተነግሯቸውስ ቢሆን ምነኛ ምሰኪኖች ነበሩ፡፡

 

2ኛ.  ‹‹ስርየት››  የጌታ ኢየሱስ የመስቀል ላይ ሞት  ‹‹ከኀጢአት ማስተሰርያነት›› እኩል  የብልጥግናችን  ማረጋገጫ ነው

የብልጥግና ወንጌል በክርስቶስ ሞት ባገኘነው ‹‹ስርየት››  ፈውስ እና የገንዘብ ብልጥግና እንደ ተሰጡ የሚያሳየውን ኬነት ኮፕላንድ የሰጡት አስተያየት እንመልከት፡፡ ‹‹መሠረታዊ የሆነው ክርስቲያናዊ መርሕ የሚያስተምረን እግዚአብሔር ኀጢአታችንን፣ በሽታችንን፣ ሕመማችንን፣ ሐዘናችንን፣ መገፋታችንና ደኻነታችንን (ገንዘብ ማጣታችንን ) ሁሉ  በመስቀል ላይ በክርስቶስ ላይ አኑሮታል›› የሚል ትምህርት ነው፡፡ ይህ ዐይነቱ መሠረቱን የሳተ የስርየት ትርጓሜ ከሁለት የብልጥግና ወንጌል መምህራን ፍላጎትና አቅጣጫ ይመነጫል፡፡

 

የመጀመሪያው ስሕተት የብልጥግና ነገረ መለኮት በጌታ ኢየሱስ ሕይወት ላይ የተንሸዋረረ አመለካከት መያዙ ነው፡፡ ለምሳሌ እንደነ ጆን አቫንዚኒ ያሉት ታላላቅ የልዩ ወንጌል መምህራን እንዲህ ይላሉ፡- ‹‹ጌታ ኢየሱስ በጣም ድንቅ ዐይነት ቤት ነበረው፣ ዛሬ ቪላ የምንለው ዐይነት›› ‹‹ጌታ ኢየሱሰ በይዞታነት ከፍተኛ ቁጥር የነበረው ገንዘብ ነበረው›› እንዲሁም ‹‹ ጌታ ኢየሱስ በዲዛይነር የተሰፋ ልብስን ያዘወትር ነበር›› በጌታ ኢየሱስ የምድር ላይ ሕይወትና ቆይታ እንደዚ የተንሸዋረረ አመለካከት ያላቸው መምህራን በሞቱ ላይም ተመሰሳይ መንሸዋረር የላቸውም ለማለት ይከብዳል፡፡

 

በሁለተኛ ደረጃ  የብልጥግናው ወንጌል የሚመነጨበት   2ኛ ቆሮ 8÷9  በአግባቡ ያለመረዳትና በአግባቡ ያለ መተርም ስሕተት ነው፡፡ ‹‹ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቸር ስጦታ ዐውቃችኋልና፤ ሀብታም ሲሆን፥ እናንተ በእርሱ ድኽነት ባለ ጠጎች ትሆኑ ዘንድ ስለ እናንተ ድኻ ሆነ።›› ይህ በመሆኑም እናንተም ያላችሁን ነገር በማካፈል ለችግረኞችና ለድኾች አካፍሉ የሚል መልዕክት እንዳለው ቁጥር 14 ያሰየናል፤ ‹‹ የእነርሱ ትርፍ ደግሞ የእናንተን ጉድለት እንዲሞላ በአሁኑ ጊዜ የእናንተ ትርፍ የእነርሱን ጉድለት ይሙላ፤ በትክክል እንዲሆን፥ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ።›› ክርስቶስ አምላክ ሆኖ ሳለ ራሱን ባዶ ያደረገው ከሃብት ወይም ከምድራዊ  ብልጥግና አልነበረም፡፡ መለኮት ሆኖ ይኖርበት ከነበረው አምላካዊ ስፍራ ወደ ሰው  መኖሪያ ከሰውም የባሪያን መልክ ይዞ የመጣበት ሂደት እንደ ጳውሎስ ገለጻ ድኽነት ይባላል፡፡ ጳውሎስ በእርሱ ‹‹ድኽነት››  ለ‹‹ድኽነት›› አቻ ሆኖ የተቀመጠው የግሪክ ቃል        (Pto-khyoo’-0) የሚል ቃል ሲሆን ትርጓሜውም ‹‹ለማኝ መሆን፣ መደኽየት፣ የነበረውን ነገር ማጣት›› የሚል እንደሆነ ስትሮንግ የሚባለው የግሪክ እንግሊዘኛ መዝገበ ቃላት ያመለክታል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ሰው ሲሆን ያጣው ነገር ቢኖር ይዞት የነበረውን ማንነትን (አምላካዊ ማንነትን) ነበር፡፡       

ፊሊጲሲዩስ 2÷ 6 ‹‹እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት (ማጣት) እንደሚገባ ነገር አልቆጠረውም›› 

 

ታዲያ ጌታ ኢየሱስ ያጣው ‹‹ድኽነቱስ›› ምን አይነት ነው? የቆሮንቶስስ  ቤተክርስቲያን እንደ ሙላት ልትየዘው የተገባት የቱ ነው? ክርስቲያኖች ከዚህ ትልቅ ማጣት፣ ‹‹ድኽነት›› የምንማረው እውነታ ለቅዱሳንና ክርስቶስ በእኛ ሕይወት ውስጥ ላስቀጠለው ቅዱስ አገልግሎት ምን ያህል መሰጠት እንዳለብን ነው፡፡ የክርስቶስ ኢየሱስ ድኽነት ምን ነበር? ጌታ ኢየሱስ አምላክ ሆኖ በሰማያዊ ስፍራ በሚኖርበት በዚያ ዘመን ሰው ከመሆኑና ከሰዋዊው ሕይወቱ  ፍጹም የተለየ ሕይወትን ይኖር ነበር፡፡ በምድራዊ ሕይወቱም ቢሆን ጌታ ኢየሱስ በዘመኑ ይኖሩ ከነበሩት አይሁዳዊያን ይሁን ፍልስጤማውያን ይልቅ በከፋ ድኽነት ውስጥ ይኖር እንደነበረ የሚናገር አንድም ማስረጃ አናገኝም፡፡ አስተዳደጉም ቢሆን ራሳቻውን ችለው በሚኖሩ ፣ የራሳቸውን ሥራ ሠርተው በሚያድሩ ቤተሰቦች ውስጥ ነበር፡፡ ኑሮውም ቢሆን ከሌላው ይሁዲ የተለየ አልነበረም፡፡ ታዲያ የጌታ ድኽነት ምን ነበር?

 

ጌታ ኢየሱስ ገደብ ያልነበረበት ሕይወቱ በገደብ የተሞላ ወደ መሆን በመቀየሩ፤ ጊዜ፣ በሰፈር፣ በውስንነት ለ33 ዓመታት ከመኖር የሚበልጥን ድኽነት (ማጣትን) ሊኖር አልተገባውም ያም ቢሆን ለእኛ ኀጢአተኛ ለነበርን ስርየትን ያስገኝልን ዘንድ ነው፡፡ የጌታ ኢየሱስ የብልጥግና ሕይወት በአምላክነት ይኖርበት የነበረው ሕይወቱ እንጂ፤ ገንዘብ በየመንገዱ  የሚበትንበት ፣ በታላቅ ድንቅ ቤት የሚኖርበት፣ ልብሱን በዲዛይነር አሠርቶ የሚዘንጥበት አምላካዊ ሕይወት አልነበረውም፡፡ የእርሱ ብልጥግና አምላክነቱ፣ ድኽነቱ ደግሞ ሰውነቱ (ሰው መሆኑ) ስለመሆኑ መገንዘብ ከእንግዳው ወንጌል ትምህርትና ስሕተት ይጠብቀናል፡፡

 

3ኛ.  ‹‹መስጠት›› ክርስቲያኖች መስጠትን የሚለማመዱት ቁሳዊ ባርኮትን አትረፍርፈው ለመቀበል  ነው

ሦስተኛው የብልጥግና ወንጌል ስሕተት ክርስቲያኖች መስጠትን መለማመድ ያለባቸው ቁሳቁሳዊ ይዞታዎችን ከእግዚአብሔር በመስጠታቸው አትርፈው የሚቀበሉበት መንገድ እንደሆነ ማሰተማራቸው ነው፡፡ የብልጥግና ወንጌል ሰባኪያኑ ልክፍት ሊባል በሚችል መልኩ መሰጠት ላይ ትኩረት የሚያደርጉበት ምክንያት አንዱ የሰባኪዎቹን ገቢ ለማዳበርና ሃብት ለማካበት ሲሆን ትንሽ ገንዘብ ያለው ድኻ ደግሞ በመስጠቱ በዝቶለት ሃብታም ከሚባሉት ሰዎች ተርታ ለመመደብ አቋራጭ የመክበሪያ መንገድ እንደ ሆነ በማሰብ ነው፡፡

 

 

ይህን ድብቅ ስግብግብነት ከዳር ለማድረስ፤ የሚጠቀሙባቸው መቀስቀሻ ንግግሮቻቸውን አዘውትረው ከምስባክ መናገር በየመርሓ ግብሩ መረሳት የሌለበት የትምህርታቸው አካል አድርገው ይቀበላሉ፡፡ እንደ ሮበረት ቲልቶን አባባል ሰዎች ለመስጠት መነሳሳት ያለባቸው ‹‹ሰጥቶ መቀበል የሚለውን መርሕ (Law of Compensation)›› ላይ ተማምነው መሆን እንዳለበት ያስተምራሉ፡፡ ይህ መርሕ  መሠረቱ የማርቆስ ወንጌል 10÷30  እንደሆነና  ይህንን በማድረጋቸው እንግዚአብሔር ከሰጡት አብልጦ በምላሹ  ይሰጣችኋል የሚል  ሃሰቡን በጽሕፉ ገልጾታል፡፡

 

 

ይህንን መርሕ አዘውትሮ በመከትል ወደ ከፍተኛ የገንዘብ መባረክ ውስጥ መግባት እንደሚቻል አበክረው ይናገራሉ፡፡ግሎሪያ ኮፕላንድ ‹‹› 10 ዶላር ስጥ 1000 ተቀበል ፤ 1000 ዶላር ስጥና 100000 ተቀበል በአጭሩ ማርቆስ 10÷30 ራስህን ለማልጠግ መልካም አጋጣሚ ነው›› ማለታቸውን መጽሕፋቸው ያሳብቃል፡፡

 

በሌላው ጐን ጌታ ኢየሱስ ደቀመዛሙርቱን ሲያስተምር ‹‹ስጡ›› ስትሰጡ አንዳች በምላሹ ሳትጠብቁ አድርጉ በማለት ተወዳጅነት ያተረፈውን የደጉን ሳምራዊ ታሪክ አሰተማራቸው ሉቃስ 10÷35፡፡ ጌታ ኢየሱስ በዚህ ትምህርቱ ሰጥቶ መቀበል የሚልን መርሕ ታሳቢ በማድረግ ሳይሆን ፤ ሰጥቶ ምላሽ አለመጠበቅን ሲያስተምር ፤ የዚህ እንግዳ ወንጌል ሰባኪያን በአቋራጭ መክበረን በማሰብ ፤ ስጡ እኔም ገንዘባችሁን እበለጽግበታለሁ እናንተም ሃብታም ትሆናላችሁ ይሉናል፡፡

 

4ኛ.  ‹‹እምነት›› ከግል ሕይወት የሚመነጭ መንፈሳዊ ጉልበት ሲሆን በብልጥግና ላይ ብልጥግና የምንጨምርበት ዐቅም  ነው

እምነት ከግል ሕይወት የሚመነጭ  ‹‹በራሱ ›› መንፈሳዊ ጉልበት እንደሆነና ከድኽነት ወደ ተትረፈረፈ የገንዘብ፣ የጤና፣ የስኬት ሕይወታችን የምነገባበትና የምናስለቅበት ዐቅም እንደሆነ ያምናሉ ያስተምራሉ፡፡ በሌላ በኩል ጤናማ ክርስትና  እምነትን የሚረዳበትና የሚያስተምረው በክርስቶስ ላይ ባለን መደገፍ እንጅ ፤ በእራሱ የቆመ እምነት (ከግል ሕይወት የሚመነጭ መንፈሳዊ ጉልበት) ላይ አይደለም፡፡ ኬነት ኮፕላንድ  በ The Laws of Prosperity   በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ‹‹ እምነት መንፈሳዊ ጉልበት ነው፣ መንፈሳዊ ዐቅም ነው፡፡  እንግዲህ ይህ የእምነት ዐቅምና ጉልበት ነው የመንፈሳዊውን ዓለም የሚያንቀሳቅሰው …እንዲሠራ የሚያደርገው፡፡ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የተገለጡ በርከት ያሉ የብልጥግና መርሖች አሉ፣ እነዚህን መርሖች እንዲሰሩ የሚያደርጋቸው ዐቅም እምነት ነው›› እንዳሉ አንብቤያለሁ፡፡

 

የዚህ ዐይነቱ የ ‹‹እምነት›› (ከግለሰብ ሕይወት የሚመነጭና  ‹‹በራሱ ›› መንፈሳዊ ጉልበት የተባለው እምነት) አስተሳሰብ ‹‹እምነት›› ከተናጋሪውና ከቃሉ ባለቤት  ከእግዚአብሔር ይልቅ የላቀ ኃያልና ዐቅም እንደ-ሆነ በማስተማራቸው ከ-እነሱ እምነትና ከቃሉ ባለቤት እምነት፤ የእነርሱ እምነት ሊመለክ ይገባዋል፡፡ ይህ ደግሞ ገሃድ የወጣ ዐይን ያፈጠጠ ስሕተት ነው፡፡

 

 

እንደ እንግዳው ወንጌል ሰባኪያን ፤ እምነት ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ባለመሆኑና ግለሰቡ በግል ልምምዱ የሚያዳብረው ጡንቻ በመሆኑ ፤ ትኩረቱ በሁሉ መካከለኛ በሆነው በክርስቶስ ላይ ሳይሆን ፤ ከእግዚአብሔር ፈቃድ በልጦ ሊያስለቅቅ ፣ ሊለውጥ በሚችል ሃሳባዊ ጉልበት ላይ ነው፡፡  በሌላ ቋንቋ እምነት  እግዚአብሔርን ማስፈራሪያ ብቸኛው መሣሪያ ነው፡፡  ይህን እምነት (ጡንቻ) ማጐልበት ደግሞ የገንዘብ ጥርመሳንና ሌሎች መከናወን የሚባሉትን ይዞታዎች ማግኛ ነው፡፡

 

 

ለእኛ ግን ‹‹እምነት›› ከእግዚአብሔር በአዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደህነትና የዘላለም ሕይወት የተቀበልነበት፣ ርስታችንን ያረጋገጥንበት ፣ የማናየውን ዓለም የተረዳንበት፣ ተስፋ የምናደርገውን የያዘንበት፣ የዘላለም አንባችንን የተተገንበት፣ መንፈሳዊ መደገፊችን ነው፡፡ እምነት በእግዚአብሔር ላይ እንጂ ከግል ሕይወት የሚመነጭ      ‹‹በራሱ ›› መንፈሳዊ ጉልበት በመሆን ሐሰብ ሠራሽ ትምህርት ላይ አይደለም፡፡

 

 

5ኛ.  ‹‹ጸሎት›› እግዚአብሔርን አስገድደን ቁሳቁሳዊና  የገንዘብ ብልጥግናችን የምናስለቅበት ጉልበት ነው

ለጽሑፌ የመጨረሻ ለብልጥግና ወንጌል ደግሞ የመጨረሻው ያለሆነውን ስሕተት ልጠቁማችሁ፡፡ ‹‹ጸሎት›› እንደ ብልጥግና ወንጌል ሰባኪያኑ እግዚአበሔር አምላክን የምናሰገድደበት፤ ቁሳቁሳዊና የገንዘብ ብልጥግናችንን የምናስለቅቅበት መሣሪያ ነው፡፡  የእንግዳው ወንጌል ሰባኪያን ያዕቆብ 4÷2 ‹‹…አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም..›› የሚለውን የያዕቆብን ቁንጽል ሐሳብ በማንሣት ጸሎት የአማኞችን የብልጥግና ሕይወት ለማበረታትና የግል ስኬታቸውን ማስፈጸሚያ እንደ-ሆነ ዶክተር ክሪፌሎ ዶላር ጽፏል፡- ‹‹ ስንጸልይ ፤ የጸለይነው ጸሎት እንደተመለሰልን ቈጥረን መሆን ይኖርበታል፤ ይህን በማድረጋችን እግዚአብሔርን ምርጫ እናሳጣዋለን ስለዚህም ጸሎታችንን መመለስ ግድ ይለዋል….. እንደ ክርስቲያንም ውጤታማ እንሆናለን፡፡››

 

በእርግጥ እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ መከናወን እዲሰጠን መጸለይ ስሕተት አይደለም ፤ እንዲያውም የሚበረታታ ክርስቲያናዊ ተግባር ነው፡፡ ፡፡ አንድ አማኝ የጸሎት ሕይወትም ሊኖረው የተገባ ነው፡፡  ይሁን እንጂ የእንግዳው ወንጌል መምህራን ፤ ጸሎትን የልባቸውን ሃብና ፍላጎት የአምላክን ፈቃድ ባላገናዘበ መልኩ  ፣ የእግዚአብሔርን እጅ መጠምዘዢያ አድረገው ማሰተማራቸው ለክፋት ይዳርጋል፡፡ በዚህ ዐይነቱ የጸሎት አስተሳሰብ፡-   ጸሎት ‹‹ሰውን›› እንጂ ‹‹እግዚአብሔርን›› ማዕከላዊ አያደርግም፡፡ እግዚአብሔርን ያላማከለ ጸሎት በምን መልኩ ጸሎት ሊባል ይችላል ፡፡  ጸሎት እግዚአብሔርን የምናዝበት ሌላኛው የብለጥግና መሣሪያ ነው ብለውም ያምናሉ፡፡

 

በሌላ መልኩ የያዕቆብን መልክት ቁጥር 3 ያለማንበባቸው ነገር ደግሞ በተጨማሪ ስለጸሎት ያላቸው ግንዛቤን አንሸዋሮታል፡፡ ያዕቆብ 4÷3 ‹‹ ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም።›› ቃሉ እግዚአብሔርን በማያከብር ጸሎትና ልመና ላይ እግዚአብሔር መልስ አይሰጥም ብሎ በግልጥ ይዘጋል፡፡ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁ፣ የሚገርም ነው! እግዚአብሔርን ለማዘዝ የሚገዳደር ጸሎት ፣ በእግዚአብሔር አምላክነት ላይ ተቃውሞ ባለው  በአጋንንት መንፈስ ካልሆነ በቀር (እርሱም አይችልም!)  -በጸሎት አምላክ አይታዘዝም፡፡ በጸሎት እግዚአብሔር ይለመናል  ፤ ይጠየቃል፡፡

 

ፊልጵስዩስ 4÷6 ‹‹ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ።››  የጌታን ሃሰብ ገሸሽ በማድረግ፤ የብልጥግናው ወንጌላውያን ‹‹ጸሎት›› የሰውን ፍላጎትና ቅዥት  ያውም ደግሞ እግዚአብሔርን አስገድዶ የመንጠቂያ መሣሪያ  እንደሆነ በማሰብና ስግብግባዊና ቁሳቁስ ተኮር፣ ባዶ ፣ ጊዚያዊ ፣ አስመሳይ ያምልኮ መልክ ያለው ፣ የእግዚአብሔርን አምላክነት የካደ፣ ለእግዚአብሔር ክብር የማይሰጥ፣ እርሱንም ማዕከል ያላደረገ ጸሎትን ያሰተምራሉ ይሰብካሉ፤ ይጸልያሉ፡፡

 

ከብልጥግናው የ‹‹እምነት›› አስተምህሮ ጋር የብልጥግናው ‹‹ጸሎት›› ሲጣመሩ የእምነት ጸሎት  (ከሰው የሚመነጭ መንፈሳዊ ጉልበትና እግዚአብሔርን መጠምዘዣ ) ዐቅም ናቸው ብለው ስለሚያስቡና በልምምዳቸውም ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጣቸው በመሆናቸው ‹‹ሰው›› እንደ ፍላጎቱ በቀላሉ ‹‹አምላክን››  የሚያዝበት ኀይሎች ናቸው፡፡ በእርግጥ እነዚህ መምህራን እኛ በምናምነው የዓለማት ሁሉ ፈጣሪ በሆነ ሥሉስ አምላክ፣ የሚያዝ እንጂ የማይታዘዝ ፈጣሪ ፣ የሚመለክ እንጂ ማንንም የማያመል ከሃሊ አምላክ ያምናሉን የሚል ጥያቁን መጠየቅ አግባብ ሳይሆን ይቀራልን?

 

እንግዳው ወንጌል

በቅዱሳት መጻሕፍት እይታ ይህ እንግዳ ወንጌል እውነተኛውን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይወክልና በመሠረቱም የዘቀጠ አስተምህሮ እንደሆነ ለማየት ሞክረናል፡፡ በእርግጥም ይህ እንግዳ ወንጌል የስሕተት ትምህርትና ልምምድ ነው፡፡

 

በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ሊሆን ይገባ የነበረውን ግንኙነት አግባብ በሌለው ሁኔታ የሚያስተምር ከመሆኑም በላይ የአምላክንና የሰውን ሥልጣናዊ  ቅደም ተከተል ያዛባል፡፡ ምንም እንኳን በንግግራቸው መኻል ከጤነኛው የክርስትና ትምህርት ጋራ ተመሳሳይ ቃላቶችንና የቤተክርስቲያን ሥርዐትን ቢከተሉም በልምምዳቸውና በትምህርታቸው ግን ፈጽመው ርቱዕ ወይም ቀጥተኛ ከሆነው ከሐዋርያት ትምህርት ፈጽሞ የራቀ ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ለመሆኑም ማረጋጋጫዎች ጠቅሰናል፡፡

 

እነርሱ እንደሚያስተምሩት የብልጥግና ወንጌል እውነት ‹‹ቢሆን ኖሮ !›› ጸጋ ባላስፈለገ ፣ እግዚአብሔርም  በሌለ፤ ሰውም  ብቻውን የሁሉ ነገር መሥፈሪያ በሆነ ነበረ፡፡ አምላክም  በተገላቢጦሽ ሰውን ባመለከው ነበር፡፡ ከላይ እንደ ተመለከትነው   ‹‹አብርሃም ኪዳን፣ ሥርየት፣ መስጠት፣ እምነትና ጸሎትን›› ሁሉ ጨፍልቀው በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ሊኖር የተገባውን ኅብረትና ግንኙነት የ‹‹ሰጥቶ …መቀበል›› ቀመር አድርገውታል፡፡ 

እንደ ጄምስ አር ጎፍ እባባል የእግዚአብሔር አስፈላጊነት ‹‹አንሶ አንሶ እርሱን አንደ ደጅ ጠባቂ ልጅ (“cosmic bellhop”) የፈጠረውን ሰውን ፍላጎት ከሥር ከሥር እየተከታተለ የሚያሟላ ሎሌ ሆኖል›› ይህ ደግሞ ፈጽሞ ምድራዊ አስተሳሰብ አንጂ የዘላለሙን ጌታ የሚያከበር አይደለም፡፡ የብልጥግና ወንጌል ከምድር ምድራዊ ሆኖ  ፣  ከምድር ጋር  የሚያጣብቅ ፣  ምድራዊ በሚሆኑ ግለሰቦች የሚዘወተር ፣ መንፈሳዊ በሚመስሉና ለሰው ፍላጎት ምቹ በሆኑ ቃላት የተቀመረ የሰው ትመህርት ነው፡፡ ከዚህ ዐይነቱም ትምህርት አንድንጠበቅ ሐዋርያው ጳውሎስ መክሮናል፡፡

 

ገላቲያ 1÷ 8 ‹‹ ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን።››s

Read 8957 times Last modified on Monday, 07 September 2015 05:15
Yoseph Lemma

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 140 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.