You are here: HomeSocial Issues እንጀራ እና ዓላማ ፡- ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ

እንጀራ እና ዓላማ ፡- ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ

Written by  Wednesday, 01 April 2015 00:00

አብዛኞቻችን ለእንጀራ ወይም ለዓላማ፣ እንኖራለን። ለእንጀራ የምንኖር ሰዎች፣ አንድን ሥራ ወደድነውም ጠላነውም እንሰራዋለን፡፡ እንጀራ ነዋ! አንድን ትምህርትም በእርግጥ የምንፈልገውን ገንዘብ ካስገኘልን እንማረዋለን! ምክንያቱም ዋናው ጉዳይ ከምናገኘው እርካታ ሳይሆን ከምናገኘው «ርዝቅ» ነው። ከዚህም የተነሣ ጎሮሯችንን መድፈን የዕለት ከዕለት የኑሯችን ገፅታ ሆኗል። ሌሎች ደግሞ የሚኖሩት ለዓላማ ነው! ገንዘብ ያስገኝላቸውም አያስገኝላቸውም ነፍሳቸውን ሁሉ ዓላማዬ ብለው ለሚያስቡት ነገር ሰጥተው ይኖራሉ። እነዚህ በጣም ጥቂት ሰዎች ገንዘብ ሳይሆን እርካታ አሳዳጆች ናቸው። አንዳንዶቻችን ደግሞ በሁለቱ ሐሳቦች መካከል እንደ ዋዠቅን እንኖራለን። እንዲያው ግን ወዳጆቼ ለእንጀራ እንኑር ወይስ ለዓላማ?

 

ሁላችንም ለእንጀራም እንኑር ለዓላማ ወደዚህች ምድር የመጣነው በዓላማ ነው። እያንዳንዳችን ከእናቶቻችን ማህፀን ስንከፈል የታቀደልን ዓላማ (ጥሪ፣ህልም ወ.ዘ.ተ) አለ። አገጣጠማችን (ስሜት፣ ፍቃድ፣ አዕምሯችን) ሁሉ ያንን የታቀድንለትን እንድንሰራ ነው። መፅሐፍ ቅዱስም እግዚአብሔር ለክብሩ እንደሰራን ቁልጭ አድርጎ ይናገራል። ይህንን ክብር የምናመጣለት አያንዳንዳችን ለተጠራንለት ዓለማ በሙሉ መሰጠት መኖር ስንችል ብቻ ነው። አስገራሚው ነገር ግን ሁላችንም በእንጀራ እና በህልማችን መካከል እንደተጣበቅን ለዘለላ እንኖራለን።


ለዚህም መነሻው እንጀራ እና ጥሪ በህይወታችን ውስጥ ተያይዘው ወይም ተለያይተው የሚገኙ ነገሮች መሆናቸው ነው። እንጀራ የዕለት ጉርሳችን ለመሸፈን ወይም ደግሞ ጥሩ ብር ማግኘት ስንል ብቻ የምንሰራው ነገር ነው። ይሄ ምናልባት የማንወደውን ግን ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችልበት ነገርን መርጦ ከመስራት ይጀምራል። ሕልም በበኩሉ ደግሞ ገንዘብ ልናገኝበት ባንችልም እንኳን ስንሰራው ነፍሳችን እርክት የምትልበት ነገር ነው። ለምሳሌ እኔ ለእኔ «የትርጉም ሥራ» እንጀራዬ ነው። አልወደውም! ነገር ግን የእኔ እና የቤተሰቤ መተዳደሪያ ነው፡፡ ለእኔም ነፍሴ ሐሴት የምታደርገው የእግዚአብሔርን ቃል ሳስተምር ነው። ምን ያደርጋል የእግዚአብሔርን ቃል ከማስተምርበት ጊዜ በትርጉም ሥራ የምሳተፍበት ጊዜ ብዙ ይሆንብኝ እና ክፍት ይለኛል። ከህልሜ እንጀራዬ በልጦብኝ ይሆን?

 

ኤልዳና (ለዚህ ፅሁፍ ሲባል ስሟ የተቀየረ) ወደ አንድ የህክምና ተቋም ገብታ የጤና ረዳትነትን የተማረችው ከነበረችበት ሥራ አጥነት ወጥታ የዕለት ጉርሷን ለማግኘት ነበር። ይህንንም ትምህርቷን በሙሉ መሰጠት ተማረች። ያንን ትጠላው ከነበረው ሥራ አጥነት መውጣት ብቻ ሳይሆን ረብጣ ብር ማግኘት ጀመረች። አገባች ወለደች። ባለቤቷ በቂ ገቢ የነበረው ሰው በመሆኑ መስራት አያስፈልጋትም ነበር፡፡ ነገር ግን በበለጠ ትጋት ትሰራ ነበር ። ድንገት ሳታውቀው የምትወደውን ሥራ መጥላት ፣ መሰልቸት ጀመረች። ምስጉን ሠራተኛ እንዳልነበረች በስልቹነት እና በቸልተኝነት ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ የሚሰጣት ሴት ሆነች። እኮ ለምን?
ይሄ ለእንጀራ ስትል ትሰራው የነበረው ሥራ የታቀደለትን ዓለማ ከግብ ቢያደርስም፣ ለእሷ ግን ተገቢውን እርካታ ሊፈጥርላት አልቻለም። ገንዘብን ቢያስገኝላትም እርካታን ግን ከየትም ሊያመጣላት አልቻልም። ሁለተኛ ልጇን ወልዳ በምትታረስበት ጊዜ ስለዚህ ጉዳይ አጥብቃ ማሰብ ጀመረች። ለምንድን ነው ሁሉ ነገር የሰለቸኝ? ለምንድን ነው በተለመደ ትኩረት ሥራዬን መስራት ያልቻልኩት? ብላ ሯሳን ጠየቀች፤ መረመረች፤ በመጨረሻ ያገኘችው ነገር ግን የምትስራውን ሥራ አትወደውም። ለሥራው ያላት ፍቅር ገንዘብ ለማግኘት ካለት ጉጉት የመነጨ ስለ ነበረ ገንዘብ ስታገኝ ሥራዋ አስጠላት። ታዲያ ምንድን ነው የምትውደው? ኬክ መጋገር!! ከልጅነቷ ጀምሮ ይህንን ሥራ ስትሰራ ከፍተኛ ደስታ ይሰማታል፤ ብዙ ሰዎችም እንደሚዋጣለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ስለዚህ ስራዋን አቁማ ይህንኑ የኬክ ሥራ ተማረች። አሁን ታዲያ በዚሁም ሥራዋ ካፍቴሪያ ከፍታ ደንበኞቿን ምርጥ ኬክ እየመገበች፤ እሷም ደስታን እየተመገበች ትገኛለች። ያለፈውን ጊዜ ስታስበው “ግን ምን ነክቶኝ ነው?” ስትል ራሷን ትጠይቃለች፡፡

 

ታዲያስ ምን ይጠበስ “እሷ ስላላት ነው!” ህልም ከዳቦ ባሻገር ነው የሚመጣው ትሉኛላችሁ ፤ ወይስ ደግሞ ባክህ ምንም ዋጋ ያስከፍል ህልምን መከተል ነው? አሊያም ደግሞ ህልምን እና እንጀራን ጎን ለጎን ማስኬድ ይቻላል። እኔ ግን አንድ ምሳሌ ልጨምር እና ፍርዱን ለእናንተው ልተው።

 

ድል ነሳ (ለዚህ ፅሁፍ ሲባል ስሙ የተቀየረ) ከልጅነቱ ጀምሮ በኪነ ጥበብ ፍቅር የተነደፈ ነው። ማንበብ ልብ ወለድ፣ ቲያትር፣ መጣጥፎችን መፃፍ ከልጅነቱ ጀምሮ የሚያስደስቱት ነገሮች ናቸው። ስለዚሁ ጉዳይ ሲናገር “ ከልጅነቴ ኪነ ጥበብ በደሜ ውስጥ እንዳለች አውቅ ነበር። ከጨረቃ ፍቅር ስለያዘው ሰው ልብወለድ የፃፍኩት የ9ኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ነበር ይላል።” ሁላችንም እንደምንገምተው ድል ነሳ ሲያድግ ወደ ኪነ ጥበብ ትምህርት ቤት መግባት ነበረበት፡፡ ያደገበት ቤተሰብ እጅግ ደሃ ከመሆኑ የተነሳ እራሱን እና ቤተሰቡን ለመደገፍ የማስተማር ሥራ ውስጥ መግባት ነበረበት። ሥልጠናውን ወሰዶ የተሰካለት አስተማሪ መሆን ቻለ ። በቂ ባይባልም በትንሹ ራሱን ለመደጎም የሚበቃው ያህል ገንዘብ አገኘ። ጊዜ እየገፋ ሲሄድ ግን ልክ እንደ ኤልዳና በሱ ውስጥም መሰላቸት ተፈጠረ። ሁኔታውን እንዲህ ይገልጠዋል። “ ባክህ አታድረቀኝ! ምርጥ አስተማሪ መሆን ችዬ ነበር፡፡ ነገር ግን በጣም ይደብረኝ ነበር። ጠዋት ከእንቅልፌ የምነሳው በብዙ ጉትጎታ ነው። አንዳንድ ጊዜ ከመሬት ተነስቼ ሣምንት እቀራለሁ። አሠሪዎቼ ይወዱኝ ስለ ነበረ ከትንሽ ተግሳፅ ጋር ይመልሱኝ ነበር። ይህንን ሥራ መተው እፈልጋለሁ፤ ግን ምን ልብላ? ምን የቤት ኪራይ ልክፈል? ምንስ ልልበስ።

 

የእነዚህ የሁለት ጉዳዮች ግጭት በእያንዳንዳችን ውስጥ እንዳለ እገምታለሁ። እያንዳንዳችን እግዚአብሔር የፈጠረን ለዓላማ ስለ ሆነ ውስጣችን የተቀመጠው ያ ጥሪ ነፍሳችንን ወጥሮ ይይዛታል። እረፍት ይነሳታል! በዚህ በኩል ደግሞ እንጀራ የሚሉት ጉዳይ ፋታ ይነሳናል። በእነዚህ ሁለት ሃሳቦች መካከል ስንዋዥቅ እድሜያችንን እንፈጃለን። እንዲያው እናንተዬ ህልሙና እንጀራው የገጠመለት ሰው ምንኛ ደስተኛ ነው። የእናንተስ ህልማችሁ እና እንጀራችሁ ገጥመው ይሆን? ሥራችሁን የምትሰሩት ያለማጉረምረም ይሆን? በየመሥሪያ ቤቶቻችን ለምናየው መሰላቸት እና ሥራ ጠልነት ምክንያቱ የእንጀራችን እና የህልማችን አለመግጠም ይሆን? እስቲ እንነጋገርበት።

Read 7135 times Last modified on Wednesday, 01 April 2015 08:14
Abinet Ababu

I am Abinet Ababu a disciple, a husband and a father of two. A graduate of for Evangelical Theological college (ETC) in Bible Translation and Literacy. A student at at Africa Nazarene University (Nairobi, Kenya). A Bible school teacher, speaker and writer. An Interpreter by trade (to Amharic,English to Ormiffa -pending). 

Website: abinetababu.wordpress.com Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 300 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.