You are here: HomeSocial Issues ገሊላ ማዕከል ፡- ባቡገያ ሐይቅ ራስጌ የምትገኝ የጸጥታ መንደር

ገሊላ ማዕከል ፡- ባቡገያ ሐይቅ ራስጌ የምትገኝ የጸጥታ መንደር

Written by  Wednesday, 25 March 2015 00:00

ነፍሳችንን ጸጥታ ይርባታል፣ ፋታ ግን የላትም፡፡ ሰዉ ይንጫጫል፡፡ መኪናው ይንጫጫል፡፡ «ዝማሬው»፣ ዘፈኑ፣ ከየታክሲው የሚሰማው የድረሱልኝ ጥሪ ወ.ዘ.ተ ጫጫታ ነው፡፡ ወደ ቤት ስንገባም ወደን፣ ቀለብ እየሰፈርን፣ ማደጎ ያደረገናቸው ቲቪ እና ተንቀሳቃሽ ስልክ አይነተኛ የጩኸት ምንጮች ናቸው፡፡ ታዲያ ነፍሳችን ጭንቅ ብሏት ወደ ቤተ ሰኪያን ብንሄድም ያው ነው፡፡ ስፒከሩ መስማት ከምንችለው በላይ ይጮኻል፡፡ አንዳንዴ ከጫጫታ ከራቅን የአየር ቧንቧችን የሚዘጋ ሳይመስለን አይቀርም፡፡

 

እውነቴን ነው የምላችሁ በጣም ጸጥታ ናፍቆኝ ነበር፡፡ ታዲያ አምና ፣ ማለቴ አሮጌው ዓመት መጨረሻ ጳጉሜ ወር ላይ ይህንን የነፍሴን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል የምሥራች ሰማሁ፡- የገሊላ ማዕከል፡፡ እንደ እኔ ጸጥታ የራባቸው ወዳጆቼ ተሰባስበን፣ መከርን፤ ወሰንን፡፡ ዕለተ አርብ ማለዳ እቃችንን በአንዲት መኪና ሰብስበን የመገናኛ-ቃሊቲን የቀለበት መንገድ ተከትለን ቁልቁል ነጎድን፡፡ ሰማዬ ደመና አርግዟል፡፡ ከየመኪናዎቹ የሚወጣው ጭስ ፍጥረትን ሲጃራ የሚያጤስ አስመስሎታል፡፡ ከመሐላችን የጎደለውን ወንድም እያነሳሳን የወንድማችን ደረጄ ሙላት አዲስ መዝሙር እያደማመጥን ጉዛችንን ቀጥለናል፡-

 

«ሐሳቤን አንተን አንተን ብሏል

አንተን አስከብሮ ሊኖር ወስኗል ልቤ…»

 

ቃሊቲ ማሰልጠኛ ጋር ስንደርስ መኪናዎች አሰከሬን የሚሽኙ እንጂ ወደ ሥራ የሚነጉደውን ሕዝብ የሚያጓጉዙ አይመስሉም፡፡ ከማለዳው 12፡00 (በእኛ ቡድን የቀጠሮ አከባበር!) የተገናኘን ሰዎች አዲስ አበባን ለቀን ስንወጣ 1፡05 ደቂቃ ሆኖ ነበር፡፡ ትንፋሽ ማግኘት የቻልነው ከአቃቂ በኋላ ነበር፡፡

 

ከአቃቂ እስከ ቃሊቲ ባለው መንገድ ላይ ሰራተኛ በሚወጣበት እና በሚገባበት ሰዓት ተገኝተው ከሁለት እስከ አምስት ሰዓት የፈጀባቸውን ወዳጆቻችን እያነሳሳን፤ ጌታን ስለ ምህረቱ እየባረክን ቁል ቁል ወደ ዱከም ከነፍን፡፡ ዱከም ሥጋ ቤቶቿን ዘግታ አኩርፋለች፡፡ ሥጋ ቤቶቿ ሲከፈቱ ፍልቅልቅ ሴት ወይዘሮ የምትመስለው ከተማ እንቅልፍ ተጫጭኗታል፡፡ ከተማይቱን መሃል ለመሃል እየሰነጠቅን ቁሉ ቁል ወደ ቢሾፍቱ ገሰገስን፡፡ ቢሾፍቱ ብዙ ባጃጅ፣ ብዙ ታክሲ፣ ብዙ ሕዝብ ፣ ብዙ ጫጫታ ይዛ ተቀበለችን፡፡ ቢሾፍቱ … አንዳድ የከተማይቱ ተወላጅ ወደጆቼ በቁልምጫ እንደሚጠሯት ደ.ዘ (ደብረ ዘይት ለማለት ነው!) በጠዋቱ ሥራ በዝቶባታል፡፡

 

ሁሌ ደ.ዘ ስደርስ ለምን ቅልል እንደሚለኝ አላውቅም፡፡ በቃ የአየር ፀባይዋ ይሁን ሌላ አላውቅም ! አንድ ወዳጄ «ቅንድብህ የገጠመ ስለ ሆነ ቆሪጥ እየጠራህ ነው» ብሎኛል! ቀልዶ ሞቷል! አባባ ጃንሆይ (ንጉስ ሃይለ ስላሴ) በዚች ከተማ ውስጥ ቅንድባቸው የገጠመ ሰዎችን ይሰዉ ነበር የሚባል «አፈ ታሪክ» አለ፡፡ የእኔ ቅንድብ ደግሞ ግጥም ነው! ምንም ይባል ምን ደ.ዘ ታምራለች፡፡ በውስጧ ሰባት ሐይቆችን የያዘች የስምጥ ሸለቆ ፈርጥ ናት (ዕንቁ በአዳማ ተይዞባት ነው እንጂ እንደዛም ብትባል አያንስባትም!) በርካታ የመዝናኛ ሥፍራዎች የተፈጥሮ መስህቦችን ስብስባ ይዛለች፡፡ (የልጅነት ህልሜ ስለ ነበረው «ሆራ» አንድ ቀን አወራችኋለሁ!) ከእነዚህ ሃይቆቿ መካከልም አንዱ ባቡገያ ነው፡፡ እኔ እና ባቡገያ የተለየ ትስስር አለን የጫጉላ ሽርሽሬን የሳለፍኩት እዚያው ነው (እሱንም ሌላ ቀን!)

 

መኪናችን የደብረ ዘይትን እምብርት ይዛ ቁልቁል እያዘገመች ነው፡፡ ድንገት ወደ ግራ ታጥፋ የመኮንኖች ክለብ ፣ የሥራ አመራር ኤንስቲትዩትን መንገድ ተከትላ ነጎደች፡፡ በመስኮት የሚገባው ነፋሻ አየር ፣ ከውስጥ የምንሰማው የደረጄ መዝሙር እና ከመኪናው ጭስ ሽታ ጋር የተለየ ስሜት ይፈጥራል፡፡ ኩሪፍቱ ቃለ ሕይወትን አቀርቅሬ አለፍኩ፡፡ ደ.ዘ እና እኔ ከአንድ ደርዘን ዓመታት በፊት ከልባችን የተዋወቅነው እዚሁ ግቢ ውስጥ ነው፡፡ በእርግጥ ፈጣሪ በስምጥ ሸለቆ መካከል ሸጉጦ ያስቀመጣት የመዳፉ አሻራ ያሳረፈባት ከተማ መሆኗን ያወቅኩት የዚያን ጊዜ ነበር(መዝ 8 እና 19 ያታውሷል!) ፡፡

 

መንታ መንገዶች ላይ ስንደርስ ግራውን ተከትለን ጥቂት ከተጓዝን በኋላ ወደ መንደር ውስጥ ታጥፈን አንድ ግቢ ውስጥ ገባን፡፡ ገሊላ ማዕከል፡፡ ግቢው ውስጥ በርካታ መኪኖች ቢኖሩም የእኛ ማረፊያ ቀድሞ የተያዘ በመሆኑ ስጋት አልገባንም፡፡ ጥበቃው እየተፈለቀለቀ ሲስተርን ጠብቁ ስላለን፤ እኔ ስለ ገሊላ ማዕከል ጥቂት ስለ ገሊላ ማዕከል ላውራችሁ፡-

 

ገሊላ ማዕከል በካቶሊካውያን ሚሲዮናውያውያን የተመሰረተ በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሥር የሚተዳደር የጸሎት እና የጥሞና ማዕከል ነው፡፡ ባቡገያ ሐይቅ ራስጌ በሚገኝ በግምት 4 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን በግቢው ውስጥ ገላጣ ሜዳ ላይ በርከት ያሉ ጥንድ አልጋዎች ያሉባቸው ማረፊያ ክፍሎች ፣ የምግብ ማብሰያ እና መመገቢያ አዳራሽ፣ የተለያዩ ቢሮዎች፣ የተለያዩ አነስተኛ እና ትልቅ የስብሰባ አዳራሾች እና ቤተ መቅደስ ይዟል፡፡ ግቢው ውስጥ ቁልቁለቱን ተከትላችሁ ወደ ባቡገያ ሐይቅ ስትወርዱ ነጠላ አልጋ የያዙ ኮረብታው ብብት ሥር የተሸሸጉ የማረፊያ ክፍሎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ክፍሎች የሚያገናኘው ቁልቁለታማው መንገድ እስከ ባቡገያ ሃይቅ ዳርቻ ድረስ ይወስዳችኋል፡፡ ምንም እንኳን ማረፊያ ክፍሎቹ የተቀናጡ ባይሆኑ «የጌታን ፊት ለመፈለግ» ለሄደ ሰው ድንቅ ናቸው፡፡

 

ሲስተር መጣች ፡፡ የማሪፊያ ክፍላችን በቀሳውስት ስለ ተያዘ እስኪለቀቅ ጸሎታችሁን መቀጠል ትችላላችሁ ብላ በግምት አራት ሜትር በአራት ሜትር የሆነ ክፍል አሳየችን ፡፡ ጽድት ያለች ነች፡፡ ውስጧ የአንድ ሳሎን ምቹ ወንበሮችን ይዛለች፡፡ በግምት ከአምስት እስከ ሰባት ሰው ትችላለች (እንደ እኔ ሞላ ሞላ ያሉ ሰዎች ማለቴ ነው፡፡ ከሲታ ከተገኘ እጥፍ አትይዝም ብላችሁ ነው?) ጸሎት ተጀመረ ፕላኔት የቀየርኩ እንጂ ከተማ የቀየርኩ አለመሰለኝም፡፡ ከአዲስ አበባ 47 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ያለሁ አልመስልህ አለኝ፡፡ ግቢው ውስጥ ከወፎች ጫጫታ፣ ከንፋስ ሽውታ እና ከዛፎች ዳንኪራ በስተቀር የሚሰማ አንዳች ነገር የለም፡፡ ለእንደ እኔ አይነቱ ጫጫታ ውስጥ ተወልዶ ጫጫታ ውስጥ ላደገ ሰው አስደንጋጭ ነው፡፡

 

ገሊላ ማዕከል ውስጥ ወሬ አይፈቀድም፡፡ ማውራት አንገብጋቢ ከሆነ ወይም አንደ እኔ ሱስ ካለባችሁ፡፡ ማውራት የምትችሉት ድምጻችሁን ዝቅ አድርጋችሁ ነው፡፡ ጸሎት ሲደክማችሁ ቁሉ ቁል ወደ ሃይቁ ዳር ሄዳችሁ ንፋሱ ውሃው ላይ ሲያርፍ የሚፈጥረውን ቀለበት ትቆጥራላችሁ ወይም የዛፎቹን ሽብሸባ ታደንቃላችሁ ካለሆነም ወደ ማረፊያችሁ ገብታችሁ ሙቅ ሻወር ወስዳችሁ ጋደም ማለት ትችላላችሁ፡፡

 

እኔና ወዳጆቼ ግን እጅ አልሰጠንም ላፕ ቶፕ (ጨኔ ኮምፒውተር ነው ያላችሁኝ!) ይዘን ሄደን ነበር፡፡ ኔት ወርክ የለም፡፡ ተንቀሳቃሽ ስልኩን ሳያጠፋ ምሽግ ገብቶ ድምጹን ዝቅ አድርጎ «ምሽግ ነኝ» ያለኝ ወዳጄን እዚህ ነበር ማምጣት፡፡ ታዲያ ኔት ወርክ የለም ስል ሁል ጊዜ እንዳይመስላችሁ እኛ በሄድን ሰሞን ደ.ዘ በኔት ወርክ ድርቅ ውስጥ ስለ ነበረች ነው፡፡

 

የምግብ ሰዓት ደረሰ … ጠዋት 12፡30-1፡30፣ ቁርስ 4፡00 ሻይ፣ ከሰዓት 10፡00 ላይ ሻይ፣ ምሽት 12፡00 ራት ይቀርብላችኋል፡፡ ብፌ ነው፡፡ ምግቡ ለ«ከተማ ባህታዊ» ይበዛል፡፡ በገሊላ ማዕከል ምናልባት በሕይወታችሁ ለመጀመሪያ ጊዜ በዝምታ ልትመገቡ ትችላላችሁ፡፡ እኔ እንኳን «ምግብ ሲበላ አይወራም!» እያለች አያቴ በዝምታ ካበላችኝ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ዝም ብዬ የተመገብኩት ገሊላ ነው፡፡ በቃ አለ አይደል የምትሰሙት ብቸኛ ድምጽ የመቁረስ፣ የመቦጨቅ፣ የማላመጥ፣ የመጠጣት ድምጽ ሲሆን፤ ለገሊላ ልክ እንደ «ህብረ ዝማሬ» ነው፡፡ አንዳዶቻችንን፣ የጩኸት ሱሰኞችን ወፈፍ ሊያደርገን ይችላል፡፡

 

ገሊላን ያችን የጸጥታ መንደር የምንለይበት ቀን ደረሰ፡፡ ይህቺ ጳጉሜ እኮ የማጠሯ ነገር፡፡ ቁርስ በላን፣ ሻወር ወስድን ሻንጣችንን ሸካከፍን፡፡ ራሴን በመስታወት ሳየው ወዜ ጨቅ ብሏል፡፡ ጴንጤ ወዛም ነው ይለኝ የነበረውን አያቴን አስታወስኩ፡፡ እናንተዬ ዝምታ እና ወዝ ያላቸውን ግንኙነት የሚያጠና ዝምተኛ ሰው ፈልጉልኝ እስቲ!? ከዚያም ባሻገር ቆም ብዬ እዚህ መንደር ያገኘሁትን ነገር ሁሉ አሰላሰልኩ ፡- ጌታን አዳመጥኩ፣ እሱን ሳዳምጥ ራሴን አዳመጥኩ፡፡

 

ይሄን ሁሉ ደስታ ስንት ያወጣል አትሉኝም፡፡ «መሸጫውን ንገረን?» አትሉኝም፡፡ ቁርስ ፣ ምሳ፣ራት እና ማረፊያ ለሦስት ሰው፣ ለሁለት ቀን ውሎ እና ለአንድ ቀን አዳር 1000USD (ስቀልድ ነው የኢትዮጵያ ብር!!!) ! መኪናችንን አዙረን ከግቢው ውስጥ ስንወጣ ገሊላን ከነጸጥታዋ ትተን ደ.ዘ ጫጫታ ውስጥ ገባን፡፡ የዛሬውን ጫጫታ ከወትሮው የሚለየው ነፍሳችን ጫጫታ ሲሰለቻት የት መምጣት እንዳለባት ታውቅ ነበር፡- ገሊላ፡፡

Read 6618 times Last modified on Wednesday, 25 March 2015 06:29
Abinet Ababu

I am Abinet Ababu a disciple, a husband and a father of two. A graduate of for Evangelical Theological college (ETC) in Bible Translation and Literacy. A student at at Africa Nazarene University (Nairobi, Kenya). A Bible school teacher, speaker and writer. An Interpreter by trade (to Amharic,English to Ormiffa -pending). 

Website: abinetababu.wordpress.com Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 220 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.