You are here: HomeOpinionsቀኝና ግራ - ታችና ላይ

ቀኝና ግራ - ታችና ላይ

Written by  Friday, 18 September 2015 11:55

በቡና ሲኒዎች ቀኝና ግራ ተቀምጦ ማውራት ደስ ይላል፤ ቃልና አሳብ ቅብብሎሽ፡፡ የሰው ፍጥረት ተግባቦት ቀለቡ ነው፡፡ ያለ ውሉ ዝም በል የተባለ እንደሆነ የሰው ልጅ ይታመማል፤ ይታፈናል፤ ወደ ውስጥ የታፈነው ይታመቃል፤ የታመቀው ያልፈነዳ እንደሆነ ይገለማል፡፡

 

እንግዲያው ሰው ይናገር፡፡ አሳቡን ስሜቱን ይጨዋወት፡፡

"እኔ የምለው የጤፍ ዋጋ አሻቅቦ የት ሊደርስ ነው?"

"የዝናሙ መጥፋት አያሳስብህም?"

"የአካባቢ ብክለት በዚህ ከቀጠለ መጪው ትውልድ ይኖራል ትላለህ?"

"ፖለቲካ ሚባል ባይኖር እኛ መኖር አንችልም?"

 

ወይም

"እንዲያው በሞቴ የመኖር ፍቺው ገብቶሃል?"

"እግዜሩ ከሰማይ ሲያየን ምን ይሰማው ይሆን?"

 

ወይም 

"እውነተኛ ሰው፣ እውነተኛ ቤተክርስቲያን በዚህ ምድር አለ ትላለህ?"

"ንጹህ ህይወት መኖር የሚቻለው እንዴት ነው?"

 

የመነጋገሪያው፣ የወሬው፣ የውይይቱ አርእስተ ነገር ብዙና ልዩ ልዩ ናቸው፡፡ ወሬውም ሁልጊዜ መቋጫ እንዲኖረው አይጠበቅም ይሆናል፡፡ የምናወራው ስለሚቋጭ ብቻ ሳይሆን መተናፈሻው ጤና ስለሚሰጠንም ነው፡፡

 

ክርስቲያኖች ወሬያቸውን ወደ ጸሎት የመለወጥ ልማድ አላቸው፣ ወይም ነበራቸው፡፡ የቡና ስኒዎቹን ፈቀቅ አድርገው ሌላ የውይይት ተሳታፊ ይጋብዛሉ፡፡ መለኮት ዳር ቆሞ ታዛቢ ሳይሆን ተናጋሪ ሰሚ መልስ ሰጪ እንዲሆን ይጠራል፡፡ ቁጭ ባልንበት ወይ ተንበርክከን ወይም ቆመን ዐይናችንን ከፍተን ወይም ጨፍነን "እስኪ ደግሞ አንተ ስማ፣ የምትለንንም እኛ እንስማ" ማለት ስንጀምር ልዩ ነገር ይሆናል፡፡ ጸሎት ብርቱ የለውጥ ሞገድ ነው፡፡ ዜማ ሰባሪውን ዋልጌ ድምፅ ሁሉ ረጭ ያደርጋል፤ የኋላ ኋላ ሁላችንን በመለኮት የዜማ ምት ሰልፍ ውስጥ ያስገባናል፡፡ ጸሎት ታላቅ የስምረት ጸጋ ነው፡፡ ቅብጥርጥሩንና ስብጥርጥሩን ነገር ሁሉ ሁባሬ (Harmony) እየሰጠ በአንድ ወንዝ የሚያፈስስ ፈዋሽ ቃና ነው፡፡

 

ጸሎት በወዲህኛው ተጨባጭ ቁሳዊ ዓለም እና በወዲያኛው የመንፈስ ዓለም መካከል የተዘረጋ መሰላል ነው፡፡ መሰላሉ መወጣጫ ብቻ አይደለም መውረጃም ነው፡፡ ሰብአውያን ከመለኮት ጋር በውጣ ውረዱ ይገናኛሉ፡፡ ሁለቱንም ዓለማት የሠራ ልዑል ፈጣሪ እዚያ ነው ሲሉት እዚህ ነው፡፡ የምንጣራው ስላለበት ቦታ ርቀት ሳይሆን የመነጋገሪያ ሞገዱን ከእኛ የመስሚያ ሞገድ ጋር ለማያያዝ ነው፡፡ እርሱ እንዲከሰት ብቻ ሳይሆን እኛም እንድናየው ነው፡፡ ጉዳያችንን አይቶ እንዲፈርድልን "አቤት! አቤት!" የምንለው የተሰወረበት ነገር ኖሮ ሳይሆን እርሱን የምር መፈለጋችንን ማሳያ ነው፡፡

 

"ጌታ ቅርብ ነው በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን በእግዚአብሔር ዘንድ አቅርቡ እንጂ ስለ ማንኛውም ነገር አትጨነቁ፡፡" (ፊል 4፡5-6)

 

ጸሎትን ንግግር ብቻ ነው ያለው ማነው? ጸሎት የመላ ነፍስ ቅርጽ ነው፡፡ ወደ መለኮት ዘመምታ ነው፡፡ ለምን እናዘምማለን የተባለ እንደሆነ፡- ሕይወትን ፍለጋ፣ ርካታን ፍለጋ፣ ጥበብን ፍለጋ፣ ብርሃንን ፍለጋ፡፡ ጸሎት የአፍታ መነባንብ ሳይሆን የዕድሜ ልክ ዘመምታ ነው፡፡ ወዴት የተባለ እንደሆነ ወደ ትፍስሕተ ገነት÷ ወደ መካነ ሰላም÷ ወደ ደብረ ኃይለ መለኮት÷ ወደ ማኅበረ ሥላሴ÷ ወደ ጸጋው ዙፋን፡፡ ጸሎት የህይወት አቋም ነው፤ የሕይወት አቋቋም ነው፡፡

 

እንግዲያው ጸሎት ጉዳይ ማቅረቢያ ብቻ ሳይሆን ቅርጽ መያዣ አቅል ማግኛ ልምምድ ነው፡፡

 

"እንደዋላ ውሃ እንዳማረው

በበረሃ ጥም እንደያዘው

ልቤ አንተን ይላል ልቤ አንተን ይላል፡፡"

 

ይህ ሁሉ ይሁን እንጂ ጸሎት ከምድራለም የተነጠለ ተጨባጭ እውነታ እንደሌለ የሚቆጥር ምናባዊ ሰመመን አይደለም፡፡ ዕለታዊ እንቅስቃሴን አያወግዝም፡፡ ከኑሮ ከሥራ ከማኅበራዊ ተሳትፎ ከዜግነት ኀላፊነት ወጥቶ አይመንንም፡፡

 

ሥራና ጸሎትን ባላንጦች ያደረገ ሰው ጸሎት ሰሚው አምላክ ምን ዐይነት ብርቱ ሠራተኛና አሠሪ መሆኑን ያልተረዳ ሰው ነው፡፡ ዘልማዳዊው ተጽእኖ ጸላዩ ሰው እጅና እግሩ ኩርትም ያሉ ዐይንና ልቡናው የፈዘዘ ከሥራ የተፋታ መንፈሱ ከመሬታዊው እውነታ የራቀ ሥራ ጠል ቦዘኔ መስሎ እንዲታይ አድርጎአል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ዘልማዳዊ ተጽእኖ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የለውም፡፡ ጸሎት አዘውታሪዎች ከሥራ የሚሸሹበት መስክ በቃለ እግዚአብሔር ላይ የለም፡፡ ጸሎት አዘውታሪነቱ ሰበብ ሆኖ አናብስት ጉድጓድ ውስጥ የተጣለው ብርቱው ጸሎተኛ ዳንኤል በሥራ ትጋቱና ጥራቱ የተመሰከረለት በሦስት ነገሥታት ዘመን አንጸባራቂ ሆኖ የዘለቀ የእውነተኛና የታታሪ ሠራተኛ አርኣያ ነው፡፡ ለጸሎት ብሎ ቢሮ ጥሎ በመዞር ባለ ጉዳይ አንከራተተ የሚል ክስ አልቀረበበትም፡፡ ጸሎት በማብዛቱ ልቡናው ፈዞ ፍርድ አዛባ ተብሎ አልተወቀሰም፡፡ ነገር ግን ተከብሮ ዘመኑን ፈጸመ፡፡ ታላቁ ግንበኛ ነህምያ ከብርቱ ጠላቶቹ ጋር እየተፋለመ የኢየሩሳሌም ቅጥር ሥራ በ52 ቀናት ውስጥ ተጠናቅቆ እንዲያልቅ ያሳየው ትጋት ያስደንቃል፡፡ ይህ ነህምያ ከፕሮጀክቱ መጀመሪያ እስከ መጨረሻ ከሰማይ ጋር ያለውን ግንኙነት መስመር ለአንድ አፍታ ሳይዘጋ በጥልቅ ጸሎታዊ ትህትናና ትምክህት የተጓዘ የአምላክ ወዳጅ አገር ወዳድ ነበረ፡፡ እንግዲያው እውነተኞች ጸሎተኞች ብርቱ ሠራተኞች ናቸው፡፡

 

እንዲያውም ብርቱ ሥራ ወደ ብርቱ ጸሎት የሚገፋፋን ሊሆን ይገባል፤ ተርታው ቢዞርም እንዲሁ፡፡ ታላቁ የተሐድሶ መሪ ማርቲን ሉተር የሚነገርለት አባባል አለው፡፡

 

"ዛሬ ብዙ ሥራ ስላለብኝ ብዙ ጸሎት ያስፈልገኛል" ጸሎትና ሥራን ምን አዛመዳቸው የተባለ እንደሆነ ጸሎት የሥራ ራዕይና የተግባር ዐቅም ምንጭ መሆኑ ሥራ ደግሞ የጸሎት መፈተሻ መስክ መሆኑ ነው፡፡

 

የተባለው ሁሉ ተብሎ ይህ ጉዳይ እኛን ኢትዮጵያውያንን ይመለከተናል ወይ ብንልስ? አዎን ምክንያቱም አሁን ኢትዮጵያ አገራችን ያለችበት ሁኔታ መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት የሚሻ ሁኔታ ነው፡፡ የሻከሩ የተወሳሰቡ ልቦች ለዝበውና ተታትተው በአንድ ልማታዊ ወንዝ ውስጥ እንዲፈስሱ፣ "እስቲ ምን ታደርጉኝ" የሚል የሚመስለው ተፈጥሮ ከበላይ ትእዛዝ ደርሶት "እሺ ተጠቀሙብኝ" ባይ እንዲሆን፤ የተስፋና የዕድገት ጉጉት እያንደረደረን ለሥራ የነቃ መንፈስ እንድናገኝ፤ ዐሲድ ብትክትክ እንዳደረገው ጨርቅ ውስጥ ውስጡን ተበልቶ የተብሰከሰከው የሞራል ሕይወታችን የጽድቅ መጎናጸፊያ እንዲለብስ፣ አብረን የመኖርና አብረን የመክበር ጥበብ እንድንቀበል የመለኮት ርዳታ ያሻናል፡፡

 

መጸለይ የምኞት ነፋስ ማሽተት አይደለም፡፡ ሕያው አምላክ ስላለ ከእርሱ ዘንድ ረድኤት እንዲገኝ የሚያደርግ ርግጠኛ ርምጃ ነው፡፡ ይህ ሕያው አምላክ የሰውን ውስጣዊና ቅን ልመና የሚሰማ ጆሮ አለው፡፡

 

"ጆሮን የፈጠረው አይሰማምን?

ዐይንንስ የሠራው አያይምን?"

ተብሎ እንደተጻፈው፡፡

 

ጸሎት መፈናፈኛ ስናጣ የምንወስደው የመጨረሻ ርምጃ መሆኑ መስተባበል አይገባውም፡፡ ሀለስቢ የተባሉ ጸሐፊ እንደሚሉት ከሆነ አማራጭ ስናጣ ወደ አምላክ ቀና ስለማለታችን ይቅርታ መጠየቅ አያስፈልገንም፤ እንዲያውም እውነተኛው ጸሎት ሰብአዊ ጉልበትና ጥበብ ያልቻለውን ነገር በኀይሉና በጥበቡ ወሰን ወደሌለው አምላክ አቅርቦ መፍትሔ መቀበል ነው፡፡ ምስኪንነት ያልተሰማው ጸሎተኛ ገና ጸሎት አልጀመረም፡፡ ከምስኪንነት ቀጥሎና ከእሱ ጋር የክርስቲያንን ጸሎት ተቀባይነት የሚያሰጠው እምነት ነው ይላሉ፡፡

 

"ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሁሉ እግዚአብሔር መኖሩንና ከልብ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጥ ማመን አለበት፡፡" (ዕብ 11፡6)

 

በቡና ስኒው ዙሪያ ማውራታችንን እንቀጥል፤ ቡናውን እያጣጣምን በሰብአዊ ሱታፌ እየተደሰትን ነገር ግን ውይይቱን ከፍ ወዳለ ደረጃ ማሸጋገር ያስፈልጋል፡፡ ወሬው ሁሉ በከንፈር መምጠጥ እንዳይዘጋ ወይም በሳቅ በሁካታ እንዳይተንን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት በትሕትና እንጥራው ጉዳያችንን እናሰማው፣ ጉዳዩን እንስማው፡፡ ምን ይል ይሆን?

Read 8236 times
Negussie Bulcha

Website: www.negussiebulcha.com Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 268 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.