You are here: HomeYouth Cornerወሲብ ቀስቃሹ ... ሕይወት አፍራሹ

ወሲብ ቀስቃሹ ... ሕይወት አፍራሹ

Written by  Monday, 11 August 2014 00:00

ዛሬ ዛሬ በአለማችን ላይ ከሚገኙት ትናንሽ ሚዲያዎች አንሰቶ እስከታላላቆቹ እንደ CNN, BBC, እና Aljazeera በመሣሠሉ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ‘አመጽ’ የሚለው ቃል ላይ እየተንተራሱ ህዝብ በመንግስት፣ መንግስት በመንግስት፣ መንግስት በህዝብ ላይ የሚያደርገውን አመጽ ሲነግሩን ሲወተውቱን ይውላሉ፡፡ እርግጥ ነው ጦርንም የጦርንም ወሬ ልትሰሙ ግድ ነው ይላልና ቃሉ (ማቴ 24፡6) እርሱን መዘገቡ ባልከፋ፡፡ ነገር ግን ችግሩ የአመፃዎች ሁሉ አባት የሆነውን አመፃ መዘንጋቱ ላይ ነው… አመፅ በእግዚአብሔር ላይ! 

 

አሁን ብዙዎቻችን ልብ ያላልነው ነገር ግን በዚህ ዘመን በተለይም ባለፉት ሁለት እና ሦስት አስርት አመታት ውስጥ ብዙዎችን እየመለመለ ሞትንና የሱስ ባርነትን እያስታጠቀ በልዑል እግዚአብሔር ላይ የተጠራን አመፅ የሚያስተባብር ልዩ ኃይል አለ፡፡ ይህ ኃይል ከሚያስተባብራቸው ታላላቅ አመፆች አንዱ Pornography በመባል ይታወቃል፡፡

 

ለዚህ ፅሁፍ መሠረታዊ ምክንያቶች የሆኑትን ስንመለከት 

  1. Pornography ለበርካቶች ስር የሠደደ ውል አልባ ችግር ከመሆኑም በላይ ለብዙ ወጣቶች ፣ ታዳጊዎች ፣ ባለትዳሮች ፣ ለአገልጋዮች ብሎም ለቤተክርስቲያን የአደባባይ ገበናዋ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡

  2. ሌላ ደግሞ አንድ በፖርኖግራፊ ሱስ የተያዘን ሠው በአጭር ጊዜ ውስጥ የሞራል እና የህሊና ባርነት ውስጥ ከመክተቱም አልፎ ከፍተኛ የአካል እና የስነልቦና ቀውስ ውስጥ በመክተት ህይወትን የማመሣቀል አቅም ስላለው ነው፡፡

ለመሆኑ ፖርኖግራፊ ምን ማለት ነው?

Pornography ከሁለት ጥምር ቃላት የተገኘ ሲሆን ነገር ግን እንዲው በግርድፍ ትርጉሙ የተመለከትነው እንደሆነ፡-

Porn ማለት prostitute ከሚለው ቃል የተወሠደ ሲሆን ሴተኛ አዳሪነት ወይም ዝሙት አዳሪነት የሚለውን ቃል ሲያመለክት

Graphy የሚለው ቃል ደግሞ ስዕላዊ የሆኑ አቀራረቦችና ምስሎችን ያመለክታል ስለዚህ Pornography የሚለው ሀሳብ ማንኛውም የወሲብ ድርጊቶችን የሚያሣዩ ፎቶግራፎች ፣ ፊልሞች ፣ አልባሣት ፣ ጽሑፎችን እና ንግግሮችን ይወክላል ማለት ነው፡፡

ታዲያ የፖርኖግራፊን ስር የተመለከትነው እንደሆነ ሁልጊዜ የሚያውጠነጥነው መሠረታዊ እና ፍጹም ተፈጥሮአዊ በሆነው የሠው ልጅ ፍላጎት ላይ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱሣዊ እና ተፈጥሮአዊ በሆነ መልኩ ስንመለከተው ይህ ፍላጎት የሚለው ሀሳብ በራሱ ምንም ችግር የሌለውና ሊኖር የተገባ ሆኖ ሳለ ነገር ግን ይህ ፍላጎት ገደብና ልጓም እስካልተበጀለት ድረስ ትልቅ ጥፋት የተሞላበት ብሎም ነፍስን እስከመንጠቅ ድረስ ኃይል እንዳለው ልንገነዘብ ይገባል፡፡

 

አንድ ሰው በፖርኖግራፊ ሱስ እንዴት ሊያዝ ይችላል?

ይህንን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት ግን ሁኔታዎችን በጥንቃቄ መመልከት ይኖርብናል፡፡

ለምሳሌ እኔ በምሠራበት የህክምና ሙያ ውስጥ ለአንድ ታካሚ ምርመራና መድሀኒቶችን ከማዘዜ በፊት ስለ በሽታው አጀማመር ስለሚያሳያቸው ምልክቶች (sign & symptom) በሚገባ ማድመጥ ይኖርብኛል፡፡ ምክንያቱም የህክምናው ውጤታማነት የሚወሰነው በበሽታው ምክንያት እና ማንነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ነው፡፡

ታዲያ ይሄንን ስል በርካቶች የፖርኖግራፊ ፊልሞችን፣ፎቶዎችን፣ስዕሎችና ጽሁፎችን ለማየት አስከፊ በሆነው የፖርኖግራፊ ሱስ ከመጠመዳቸው በፊት ቀጥሎ ከምናያቸው 3 መሠረታዊ ሂደቶች ቢያንስ በአንዱ ውስጥ ያለፉ ናቸው፡፡ በመሆኑም መፍትሔዎቹን ከማየታችን በፊት በዚህ ህይወት ሊጠመዱ የቻሉበትን ምክንያት አስቀድሞ ማወቁ ተገቢ ነው፡፡
 

ከምክንያቶች ሁሉ በላይ በዋነኛነት ሊጠቀስ የሚችለው ደካማ የሆነ የመንፈሣዊ ህይወት ሲሆን ይህም ታዲያ ለበርካታ መንፈሣዊ እና ምድራዊ ውድቀቶች ምክንያት እንደመሆኑ መጠን ለአንድ ሰው በፖርኖግራፊ ህይወት መጠመድ እንደ ዋና መንገድ ጠራጊ ሆኖ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ አንድ ሠው የመንፈሣዊ ህይወቱ ደከመ ስንል በተለይ በቃል እና በጸሎት ህይወቱ ላይ ትልቅ ጥያቄ ተፈጥሮአል ማለት ነው፡፡ ታዲያ የእነዚህ ሁለት መሠረታዊ ምሠሦዎች መንገዳገድ ለአንድ ሰው በተለይም እንደወጣት ከፍተኛ መናፍስታዊ ኢላማ ላለው እና በመግቢያችን ላይ ለጠቀስነው ገደብ አልባ ፍላጎት አጅ አስሮ በመስጠት ለፖርኖግራፊ ህይወት ያጋልጣል፡፡

ሌላኛው ጠርዝ ደግሞ ከእድሜ ጋር የተያያዘ ጉዳይ ሲሆን ይህም ወጣትነት በሚጀማምርበት adolescence (ጉርምስና) የእድሜ ክልል ውስጥ የሚካሄደው በርካታ አካላዊ እና ሆርሞናል ለውጦች ከሁኔታዎች እና ዘመኑ ከሚያመጣው ነገሮች ጋር ተደምረው በቀላሉ ሊወሰዱ እንደሚችሉ ልብ ልንል ይገባል፡፡ በተለይም ድህረ ዘመናዊነትን ተከትለው የመጡት ገደብ እና ገመድ አልባ Internet access, smart phones መጽሔቶች እና የመሣሠሉት ነገሮች ለዚህ አፋላ ለሆነው እና እንደለም አፈር በሚቆጠረው የእድሜ ክልላቸው ላይ ሰይጣን ሊዘራ ለሚንደረደረው Pornography ለተባለው ክፉ ዘር በሚገባ የዳበረን ፍግ እንደማቅረብ ሣይሆን አይቀርም ብዬ እሰጋለሁ፡፡


በሦስተኛነት ደረጃ ልናስተውለው የሚገባው ጉዳይ  ማህበረሰባችንም ሆነ ቤተክርስቲያን ስለ Pornography በመጠኑም ቢሆን ያለው የተዛባ አመለካከት ነው፡፡ ይህንንም ስንል የዚህ አመለካከት መጠነኛ መዛባት የሚጀምረው የጉዳዩን ጥልቀት እና እያደረሰ ያለውን ጥፋት በሚገባ ካለመረዳት ይጀምራል Pornography ስንል የግድ ግልጽ ወሲብ እና ርኩሰት የሚፈጸምባቸው ፊልሞች ወይም መጽሔቶችን ብቻ ማየት እንዳልሆነ ልንገነዘብ ይገባናል፡፡ ይልቁንስ የ Pornography ምንጭና መንደርደርያ የሆነውን የዘፈንና ዘፋኝነትን ጉዳይ እንደ የስልጡንነት መገለጫ መሆኑ ነው፡፡ በተለይም ቤተሰብ እና ማህበረሰቡ የሚያሳየው የተለሳለሰ አቋም የዮሐንስን አንገት ያስቀላው የሔሮድያዳ የዘፈን መንፈስ ዛሬም በፖርኖግራፊ ሠይፍ ብዙዎችን እየጨረሠ መሆኑን ልንገነዘብ እና ዘፈንና Pornography የአንድ ሣንቲም ሁለት ገጽታዎች መሆኑን ልናውቅ ይገባል፡፤ በ2005 ዓ.ም. የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው እድሜያቸው ከ14-35 ዓመት የሚሆኑ ወጣቶች በ Pornography ህይወት ከመጠመዳቸው በፊት 78% የሚሆኑት ከዘፈን ጋር ልዩ ወዳጅነት እንደነበራቸው ገልፀዋል፡፡

 

ታዲያ ሰው ከዚህ የፖርኖግራፊ ህይወት ሊወጣ ይችል ይሆን?

መልሱ፡- አዎ በሚገባ ሊወጣ ይችላል፡፡

ነገር ግን ከላይ በተነጋገርናቸው መሠረታዊ ምክንያቶች ላይ ራስን ለክርስቶስ በማስገዛት ሊሰራ ይገባዋል፡፡ ማንኛውም ወጣት ከፖርኖግራፊ ጋር በሚያደርገው ትንቅንቅ ውጊያው እና ፈተናው ከመንፈሣውያን ሠራዊት ጋር እንደሆነ መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሣሌ እንዲሆነን የዮሴፍን ህይወት ማየቱ መልካም ነው፡፡

ዮሴፍ ከጌታው ጲጥፋራ ሚስት ለቀረበለት የዝሙት ግብዣ ያመለጠበትን ሦስት ቀላል እና መሠረታዊ መንገዶች ዛሬ ለበርካታ በፖርኖግራፊ ህይወት ለተጠመዱት እና ሊገቡ ለሚግደረደሩት ትልቅ ምሣሌ ሊሆን ይችላል፡፡

ዮሴፍ ያስተዋለው ትልቁ ጉዳይ የቀረበለትን የዝሙት ኃጢአት ፈጽሞት ቢሆን ኖሮ የበደለው ጌታውን/አሰሪውን/ ብቻ ሣይሆን ይልቁንም በልዑል እግዚአብሔር ላይም ማመጽ እንደሆነ በሚገባ ተረድቶታል (ዘፍ 39፡9) በመሆኑም ይህ ክፉ ወጥመድ በተዘረጋበት ጊዜ ከዚህ ነገር እንዲያመልጥ የረዳው ይህ የዝሙት ግብዣ ከዲያቢሎስ የቀረበና በእግዚአብሔር ላይ የሚደረግ አመጽ እንደሆነም ጭምር ማወቁም ነው፡፡ ታዲያ ይህ እውቀት እንዲው ከመሬት ተነስቶ የተገኘ ሣይሆን በደህና ጊዜ ያሳደገው እግዚአብሔርን የመፍራት ህይወት ነው የሠጠው እውቀት ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ከፖርኖግራፊ ህይወት መውጣት የሚፈልግ ሰው ጉዳዩ ከስጋ ያለፈ ነገር መሆኑን ተገንዝቦ በእግዚአብሔር ፊት በመሆን የጸጋውን ኃይል በመጠየቅ መጾምና መጸለይ ይገባዋል፡፡

ለዮሴፍ ምንም እንኳን ሁኔታዎች ለዝሙት ኃጢአት የተመቻቹ ሆነው ቢገኙም ዘወትር ከዚህ የዝሙት ግብዣ እና ፈተና ራሱን ያሸሽ ነበር የጲጥፋራ ሚስት ዮሴፍን ለማጥመድ የተጠቀመችበት የዮሴፍ የገዛ ልብሱን መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ ልክ እንደዚሁ ሁሉ ዛሬ ብዙዎችን በፖርኖግራፊ ህይወት ለማጥመድ ዲያቢሎስ ከሚጠቀምባቸው መንገዶች ውስጥ የገዛ ንብረቶቻችን የሆኑትን የሞባይል ስልኮችን ፣ ኮምፒውተሮችን እና በየቤታችን የሚገኙትን ቴሌቭዥኖች ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በመሆኑም ዮሴፍ ምንም እንኳን በዋጋ የገዛው ልብሱ ቢሆንም ካለበት አደገኛ ጥፋት ለማምለጥ ልብሱን ጥሎ መሸሽን መርጧል፡፡ ስለዚህም ሰዎች ከዚህ ህይወት ለመውጣት እስከፈለጉ ድረስ ከስልኮቻቸው እና ከኮምፒውተሮቻቸው እንዲሁም ማንኛውም የፖርኖግራፊ ምስሎችን የሚያሳዩ ቪድዮና መጽሔቶችን ማስወገድ እግዚአብሔር ከዛ ሰው የሚጠብቀው ዋና እና መሠረታዊ እርምጃ ነው፡፡

 

ማጠቃለያ

በመጨረሻም በዚህ ዘመን አጅግ ብዙ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ፣ ታዳጊዎች እና ባለትዳሮች በዚህ አስከፊ ህይወት ውስጥ ተዘፍቀው ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም የፖርኖግራፊን ሱስ ከክርስቶስ ኃይል በቀር እንዲሁ በቀላሉ የተለያዩ መንገዶች እና ዘዴዎችን ብቻ በመጠቀም ልንወጣው የማንችለው ትልቅ መንፈሳዊ ውጊያ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ በመሆኑም ብዙዎቻችን ዳር ላይ ቆመን ፖርኖግራፊ ኃጢአት ነው ፣ ጎጂ ነው ብቻ የሚለው አባባላችን በዚህ ህይወት ውስጥ ላሉ ሰዎች ከክስ የዘለለ ፋይዳ ላይኖረው እንደሚችል ተገንዝበን ቤተሰብ ማህበረሰብ እና ቤተክርስቲያን ከላይ ላየናቸው መሠረታዊ መንስኤዎች ላይ በመስራት የዲያቢሎስን ስራ ማፍረስ እና የእግዚአብሔርን መንግስት ማስፋት ይገባል፡፡

Read 19485 times Last modified on Tuesday, 12 August 2014 04:14
Dr. Ahadu Alemayehu

Ahadu Alemayehu is a medical doctor   graduated from HMC  and working as a physician.  serving the youth in city of refugee church with youth ministry.He also  wright  articles and prepare training about sexual behaviors and related issues.

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 116 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.