You are here: HomeSermonእንደተወደድን መዉደድ

እንደተወደድን መዉደድ

Written by  Thursday, 01 May 2014 00:00
Yared Tilahun (Eva.) Yared Tilahun (Eva.)

‹‹አብ እንደወደደኝ እኔ ደግሞ ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬ ኑሩ፡፡ እኔ የአባቴን ትዕዛዝ እንደ ጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር ትዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ፡፡ ደስታዬም በእናንተ እንዲሆን ደስታችሁም እንዲፈፀም  ይህን ነግሬአችኋለሁ፡፡

 

እኔ እንደወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትዕዛዜ ይህች ናት፡፡ ነፍሱን ሰለወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለዉም፡፡ እኔ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ብታደርጉ እናንተ ወዳጅቼ ናችሁ……………. እርስ በርስችሁ እንድትዋደዱ ይህን አዛችኋለሁ፡፡›› ዬሐ 15፡9-17

 

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የ33 ዓመት የምድር ቆይታዉን፣ የ 3ዓመት ተኩል የአገልግሎት ጉዞዉን ሊያገባድድ የቀሩት በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ናቸዉ፡፡ እናም እነዚህን ዉዱ ቀናት ማሳለፍ የፈለገዉ በምድር አገልግሎቱ ትልቅ ትኩረት ከነበሩት፣ ሊሾማቸዉና ሊልካቸዉ ከመረጣቸዉ ደቀ መዛሙርቱ ጋር ነበር፡፡ በኢየሩሳሌም ከተማ በምትገኝ በትዉስት በገባባት ባለአንድ ፎቅ ቤት ዉስጥ ከደቀመዛሙርቱ ጋር የፋሲካን ራት ከበላ በኋላ በመጨረሻ ሰዓት የሚነገሩ ቁም ነገሮችን ያወጋቸዋል፡፡ ዬሐንስ ይህም ‹‹የመጨረሻዉ ስብስባ›› በመባል የሚታወቀዉን ክፍል መተረክ የጀመረዉ በፍቅር ቋንቋ ነዉ፡፡

 

‹‹ኢየሱስም ከፋሲካ በዓል በፊት ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄርበት ሰዓት እንደደረሰ አዉቆ፣ በዚህ ዓለም ያሉት ወገኖቹን የወደዳቸዉን እስከመጨረሻዉ ወደዳቸዉ፡፡›› ዬሐ 13፡1 በማለት፡፡ ጌታ ኢየሱስ ደቀመዛሙርቱን እግር ካጠበና የፋሲካዉን ራት አብሮአቸዉ ከበላ በኋላ ንግግሩን በመቀጠል አሁን ልናየዉ ወዳለዉ ክፍል ደርሷል፡፡ መልዕክቱም ሰለፍቅር ነዉ፡፡

 

እግዚአብሔር ፍቅር እንደሆነ እናዉቃለን፡፡ ነገር ግን ይህ ፍቅር እንዴት ተገለጠ? መጠየቅ አግባብ ነዉ በእርግጥ ‹‹ እኛን ሰለወደደ ነዋ!›› የሚል ፈጣን መልስ እንደሚሰነዘር ጥርጥር የለዉም፡፡ ሆኖም ይህ ክፍል አንዳች ብርሃን ይፈነጥቅልናል፡፡

 

የእግዚአብሔር (አብ) ፍቅርነት የመጀመሪያ መገለጫ እኛ አለመሆናችንን የምናዉቀዉ እኛ ከመፈጠራችንም አስቀድሞ በዘላለም ዘመናት ዉስጥ እግዚአብሔር ፍቅር መሆኑም ስንረዳ ነዉ፡፡ ፍቅር እንደ ብርሃን ሁሉ የሚያርፍበትና የሚንፀባረቅበት ካላገኘ አይታይም፡፡ የአፍቃሪዉ ፍቅር የሚታወቀዉ ተፈቃሪ ሲኖር ብቻ ነዉና፡፡ 

 

በዘላለም ዘመናት ዉስጥ የአብ የክብር ብቻ ሳይሆን የፍቅሩም መንፀባርቅ ልጁ እንደነበር፡፡ ዬሐንስ የጌታን የፍፃሜ ጸሎት ጠቅሶ እንዲህ ይተርክልናል፡፡ ‹‹ አባት ሆይ ዓለም ሳይፈጠር ሰለወደደኋኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ እኔ ባለሁበት የሰጠኸኝ እነርሱ ደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ፡፡›› ዬሐ 17፡24

 

‹‹ አሁንም አባት ሆይ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ፡፡›› ዬሐ 17፡5 ለዚህ አይደል ጌታ ኢየሱስ በመጥምቁ ዬሐንስ እጅ በዬርዳኖስ ዉሃ ተጠምቆ ሲወጣ ሰማያት ተከፍተዉ 

‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ ምወደዉ ልጄ ይህ ነዉ፡፡ ›› ማቴ 3፡17 የሚል ድምፅ የመጣዉ?

ጌታም እያየነዉ ባለዉ ክፍል ‹‹አብ እንደወደደኝ እኔ ደግሞ ወደድኋችሁ›› ዬሐ 15፡9 በማለት ይህንን ሃሳብ ያፀናልናል፡፡ እግዚአብሔር ፍቅር ነዉ፡፡ ፍቅሩም አንድ ነዉ፡፡ ይኸዉም ልጅን የወደደበት ፍቅር ነዉ፡፡ አብ ልጅን የወደደበት ፍቅር ሰሜትና ቃል ብቻ አይደለም በሥጦታ የታጀበ ነዉ፡፡ ዬሐንስ ቀደም ሲል እንደጻፈዉ፡-

‹‹አባት ልጁን ይወዳል፣ ሁሉንም በእጁ ሰጥቶታል፡፡›› ዬሐ 3፡35

 

ስለዚህ ወልድ ለማይቆጠሩ የዘላለም ዘመናት በአብ የፍቅር እቅፍ ዉስጥ ፍቅር ሲመገብ፣ ፍቅር ሲጠጣ ኖሯል፡፡ ሆኖም ይህን ከአብ ልብ የሚፈልቅ የፍቅር ዥረት በእርሱ ዘንድ ገድቦ ማስቀረት አልፈለገም፡፡ ስለዚህ ይህ የፍቅር ወንዝ ወደ እኛም ይፈስ ዘንድ ግድብ ሳይሆን መንገድ መሆን መረጠ፡፡ ስለዚህ በሥጋ ወደ ምድር መጣ አብ የሰጠዉንም ተከታዮች ወደዳቸዉ የወደዳቸዉንም ሰዋዊ ወይም ተፈጥሮአዊ በሆነ ፍቅር አልነበረም፡፡ ከአባቱ እንደየዉ፣ አብ እርሱን እንደወደደዉ ወደዳቸዉ፡፡

 

አብ እኛን የወደደበት የተለየ ፍቅር የለዉም ወይም እያንዳንዳችንን በተናጠል ፍቅር አልወደደንም ነገር ግን በልጁ ዉስጥ አደረገንና ልጁን በወደደበት ፍቅር ወደደን፡- ‹‹….. እንደሁም ዓለም አንተ እንደላክኸኝ በወደድኽኝም መጠን እነርሱን እንደወደድኋቸዉ ያዉቃል… እኔም የወደድህባት ፍቅር በእነርሱ እንድትሆን እኔም በእነርሱ……›› ዬሐ 17፡23 ይህም ፍቅር የተገለጠልን በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ነዉ፡፡

 

አብ ልጁን ወደ ዓለም ሲልከዉ ትዕዛዝ ሰጥቶት ነበር፡፡ አሁንም ጌታ ኢየሱስ ወደ አብ ከመሄዱ በፊት ወደ ዓለም ለሚልካቸዉ ደቀ መዛሙርቱ ትዕዛዝ ሲሰጣቸዉ እናያለን፡፡ ለመሆኑ ይህ ትዕዛዝ ምንድነዉ?

 

‹‹ እኔ የአባቴን ትዕዛዝ እንደጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር፣ ትዕዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ፡፡›› ዬሐ 15፡10

 

ከዚህ ክፍል እንደምንረዳዉ አብ ወልድን ወደ ዓለም ሲልከዉ የሰጠዉ ትዕዛዝ ‹‹እኔ እንደወደድሁህ ዉደዳቸዉ!›› የሚል ነበር፡፡ ክርስቶስም ወደ ዓለም መጥቶ ምንም እንኳ እንደማንኛችንም ቤተሰብ፣ ዘር፣ ቋንቋ፣ ወገን የነበረዉ ቢሆንም የራሱ የሆኑትን ብቻ ይወድ ዘንድ፣ ከእርሱ ክበብ ዉጪ የሆኑትን ያገለል ዘንድ በተፈጥሮአዊ ፍቅር አልኖረም፡፡ ይልቅ በአባቱ ፍቅር ኖረ፣ እንደተወደደ ወደደ ከአብ ልብ ለእርሱ የፈሰሰዉን የፍቅር ዥረት ሳይገድብ ወደ ደቀ መዛሙርቱ አፈሰሰዉ፡፡

 

እኛ አብ ወልድን በዘላለም ዉስጥ እንዴት እንደወደደዉ አናዉቅም፡፡ ነገር ግን ወልድ እኛን እንዴት እንደወደደን በጥቂቱም ቢሆን አዉቀናል፡፡ ሰለዚህ የአብን ፍቅር የምናየዉ በክርስቶስ ፍቅር ዉስጥ ነዉ፡፡ ይህም ፍቅር ለማስተዋል ከመታወቅ የሚያልፍ ደርዝ አልባ ፍቅር ነዉ፡፡

‹‹ ነፍሱን ሰለወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለዉም›› ዬሐ15፡13

‹‹ እርሱ ሰለ እኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቷልና በዚህ ፍቅርን አዉቀናል…..›› 1ዬሐ 3፡16

 

‹‹ የእናንተ ሥርና መሠረት በፍቅር ይፀና ዘንድ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታዉም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል ከመታወቅም የሚያልፈዉን የክርስቶስ ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ ….›› ኤፌ 3፡18

 

እንግዲህ ወልድ ከአባቱ ትዕዛዝን እንደተቀበለ፣ እንደተወደደም እንደወደደን፣ እኛም ከወልድ ትዕዛዝን ተቀብለናል፡፡ ይህም ትዕዛዝ እንደተወደድን እንድንወድ ነዉ፡፡ ነፍስን በመስጠት ወደ እኛ የፈሰሰዉን የፍቅር ዥረት ልናቁረዉ አይገባም ይልቅ እነርሱም ይህንኑ ያደርጉ ዘንድ እያዘዝን እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሌሎች ልናፈስዉ ይገባል፡፡ የምንጀምረዉም ከሩቅ አይደለም፡፡ በዙሪያችን ያሉ በፍቅር እየተቃጠሉ የሩቁን ብናጠጣ ምን ፋይዳ አለዉ? ሰለዚህ በአጠገባችን ያሉ የእፍታዉ ተቋዳሽ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ለዚህ ነዉ ጌታ፡- ‹‹ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትዕዛዜ ይህች ናት፡፡›› ዬሐ 15፡12 የሚለን፡፡

 

በኢዲስ ኪዳን እንደቀደሙት ስድስት መቶ አስራ ሦስት ወይም አሥርት ትዕዛዛት አልተሰጡንም ነገር ግን እንደተወደድን መጠን እርስ በርሳችን እንድንዋደድ አንድ ትዕዛዝ ተሰጥቶናል፡፡ ታዲያ ምን ያህል እየወደድንና እየተዋደደን ነዉ፡፡

 

 የክርስቶስን መስቀል በላዩም ያለዉን መከራ የፈጠረዉ ዲያቢሎስ አይደለም፣ ወይም አይሁዳዉያን፣ ወይም ሮማዉያን አይደሉም፡፡ የፈጠረዉ ፍቅር ነዉ፡፡ እዉነተኛ መስቀል እንደተወደድን ለመዉደድ ስንሄድ የምናልፈበት የህይወት ጎዳና ነዉ፡፡ ሰለፍቅር የምንከፍለዉ ዋጋ ነዉ፡፡

 

ለመሆኑ የምንወደዉ ማንን ነዉ? የማይወደዱትን፣ ፍቅራችን የማይገባቸዉን፣ በማህብረተሰብ የተገፉት፣ አፍቃሪ ወዳጅ ያጡትን ጭምር ነዋ! የሚወዱንን ብቻ ብንወድማ ምን ትርፍ አለን? 

 

ታዲያ እንደተወደድን እየወደድን ነዉ? እንደተወደድን ለመዉደድ መጀመሪያ የተወደድንበትን ልክ ማወቅ አለብን፡፡ ይህን ማወቅ የልምምድ እንጂ የመረጃ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ የአብ ፍቅር ወደ ወልድ የፈሰሰዉ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ነዉ፡፡ ወደእኛም የሚፈሰዉ በመንፈስ ቅድስ አማካይነት ሲሆን እኛም ወደ ሌሎች ልናፈሰዉ የምንችለዉ በመንፈስ ቅድስ አማካኝነት ብቻ ነዉ፡፡

 

‹‹ በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ሰለፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም፡፡›› ሮሜ 5፡5

 

‹‹… ደግሞም በመንፈስ ሰለሚሆን ሰለፍቅራችሁ አስታወቀን፡፡›› ቁላ 1፡8 ታዲያ ምን ያህል እንደተወደድን እየወደድን ነዉ? ማንም ሰዉ በዚህ ምድር የሚጥረዉና የሚለፋዉ ደስታን ለማግኘት ነዉ፡፡ ነገር ግን እዉነተኛ ደስታ ራስን ለማስደስት በመጣር የሚመጣ አለመሆኑን የተረዱ ስንቶች ይሆኑ? ራስን ለማሰደሰት የሚደረግ ሙከራ ለጊዜዉ ይሳካ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ወሎ ሳያድር እንደጉም ተኖ ይጠፋል፡፡ የራሳን ደስታ ሰዉቶ ሌሎችን ለማፍቀር ሲኬድ ግን በምላሹ ለዘላለም የማይነጥፍ የፍቅር ደስታ ይሸመታል፡፡ ለዚህ ነዉ ጌታ፡- ‹‹ ደስታዬም በእናንተ እንዲሆን ደስታችሁም እንዲፈፀም ይህን ነግሬአችኋለሁ፡፡›› ዬሐ 15፡11 የሚለን፡፡ ሥጦታ የሌለበት ፍቅር የቃላት ድርድራና የስሜት ጋጋታ እንጂ እዉነትኛ ፍቅር አይደለም፡፡ አብ ወልድን በዘላላም ዘመናት ዉስጥ ክብሩን በመስጠት፣ ሁሉን በእጁ በመሰጠት እንዴት እንደወደደዉ ቀደም ብለን ተመልክተናል፡፡ እርሱም ነፍሱን በመስጠት እንዴት እንደወደደን ለማየት ሞክረናል ፡፡ እኛስ ዛሬ እጃች ከምን ይሆን? ዬሐንስ ‹‹ እርሱ ሰለእኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቷልና በዚህ ፍቅርን አወቀናል እኛም ሰለወንድሞቻችን ነፍሳችንን አሳልፈን እንድንሰጥ ይገባናል፡፡›› 1ዬሐ 3፡16 ይለናል፡፡

 

ሆኖም በዚህ አይበቃም ምናልባት ዛሬ ነፍሱን የሚጠይቅ ነገር ላይኖር ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ኪስን የሚጠይቅ ነገር ሞልቷል፡፡ ዛሬ ሰለፍቅር የኪሱን ሊያፈስ የማይወድ ነገ ነፍስን የሚጠይቅ ነገር ቢመጣ እንደምን ይሰጣል? ለዚህ ነዉ ዬሐንስ በመቀጠል፡- ‹‹ ነገር ግን የዚህ ዓለም ገንዘብ ያለዉ ወንድሙም የሚያስፈልገዉን ሲያጣ ኣይቶ ያልራራለት ማንም ቢሆን የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ እንዴት ይኖራል? ልጆቼ ሆይ በሥራና በእዉነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ፡፡›› ዬሐ 3፡17 የሚለዉ፡፡ ሁሉ ጊዜ እንደተወደድን ለመዉደድ ለፍቅርና ለመልካም ስራ እንድንነቃቃ የፍቅር መልዕክቴን ወደ እናንተ አደርሳለሁ፡፡

Read 14111 times Last modified on Thursday, 08 May 2014 08:14
Yared Tilahun

President, Golden Oil Ministry

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 148 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.