ፊደል ላልቆጠረ፣ አስኳላ ላልደፈረ ገጠሬ “ጨረቃ እኮ የራሷ ብርሃን የላትም!” ቢባል አሻፈረኝ ሊል፣ ከባሰም ቆመጥ ሊያነሳ ይችላል። ታዲያ ማን ይፈርድበታል? በጨቅላነቱ “ጨረቃ ድንብል ቦቃ . . .” እያለ የዘመረላትን፣ በወጣትነቱ ምሽቱን ያደመቀችለትን፣ በውድቅት ጨለማውን ያፈካችለትን ጨረቃ የራሷ ብርሃን የላትም ቢባል እንዴት ሊዋጥለት ይችላል? እውነቱ ግን ያ ነው። ጨረቃ ለራሷ በቆፈን የተቆራመደች ቀዝቃዛ ፈለክ (ፕላኔት) እንደሆነች ለዘመናት ያጠኗት ይመሰክራሉ።
ምድር በምትገኝበት የሕዋ ንፍቀ ክበብ ብቸኛዋ የብርሃን ምንጭ ፀሐይ ናት። ም...