You are here: HomeSermonየክህደት እምነት

የክህደት እምነት

Written by  Tuesday, 01 April 2014 00:00
Negussie Bulcha Negussie Bulcha

ክርስቲያንነት ምዝገባ ሆነ እንዴ? እንዴት ማለት ያው ስመ እግዚአብሔርን ጠርቼ፣ የሚባለውን የኑዛዜ ዓይነት አድርሼ፣ ወይም ከእናት ከአባቴ የወረደልኝን “ስሜ ነው፣ መጠሪያዬ ነው፣ አለሁበት” ብዬ ወይም ቅዳሴውን፣ መዝሙሩን፣ ቋንቋውን ጓዳውን አጥንቼ የቤተክርስቲያን አባልነቴን አረጋጬ ሂደቱ (ፕሮሰሱ) ሲያልቅ ካርድ የምቀበልበት የክለብ ዓይነት ሆነ ወይ ማለቴ ነው፡፡

 

በነገር ለመጋረፍ ዳር ዳር ማለቴ አይደለም፤ ማን ማንን ይገርፋል? ይልቁን፤ ዙሪያ ገባችንን የልቡናችንንም ዓይነት ስንፈሽ የሚፋጠጠንን እውነታ እንድንነጋገርበት ወዲያውም መጽሐፍ ቀዱሳዊ መልስ እንድንፈልግ ሜዳ ለማበጀት ነው፡፡ ይህን ያህል አሳሳቢ አነጋጋሪ ሁኔታ አለወይ የተባለ እንደሆነስ? አሳሳቢና አነጋጋሪ ብቻ ሳይሆን አስጨናቂ አስተካዥ ሁኔታ ላይ መሆናችንን መመልከት ይቻላል እላለሁ፡፡ ማዕድ ፊታችን ሲቀርብ ቡራኬ የምንሰጥ ቢሆንም፣ ሰላምታችን እልፍ ጌዜ “ጌታ ይባረክ” በሚል መፈክር ቢያስገመግምም በጓዳ ጸሎታችን ግን “የወንድም ቀበኛዬን ዶግ ዐመድ አድርገህ አሳየኛ” እያልን የምንራገም ነን፡፡ ጸሎታችን አንዱ ታዛቢ እንዳለው የሟርት ጸሎት ሆነ፡፡ “እሷ ዓለማዊት ናት ክርስቲያን?” እያልን የማኅበራችንን ወንበር የምንነፍግና የምንመጻደቅ ብንሆንም “ዓለማውያን” ከሆኑት ይልቅ ዓለም በደንበኝነት የምታውቀን እኛኑ ሆነ፡፡ ምክንያቱም ዓለማዊነት በዓለም ውስጥ መኖር ሳይሆን በገዳምም ሆነን ዓለም በእኛ ውስጥ መኖሯ ነው፡፡ መዝሙሮቻችን ደጋግመው “አምላኬ ጌታዬ” እያሉ የታላቁን አምላክ ስም ቢጠሩም ቁርጡን ስንጠየቅ ዕቃ አምላኪዎችና የገንዘብ ሎሌዎች መሆናችን እስከዚህም ድብቅ አልሆነም፡፡

 

ሟች ስንሸኝ ስለዘላለም ቤት፣ ስለ ሰማይ መንግሥት ብናወራም የየዕለት የሕይወት ዘይቤያችን ግን ያላዩት አገር አይናፍቅም፣ የሚያዋጣኝ የዛሬውንና የእዚሁን አጥብቄ መያዝ ነው፤ የሚመጣውን ሲመጣ እናያለን፡፡ የሚል ይመስላል፡፡ አበሳችንን እያበዛሁ ክስ እያጠራቀምሁ ለማሳቀል አልፈልግም፣ ፋይዳ የሌለው አዙሪት ውስጥ ስለሚከተን፡፡ ይልቁን እንዲህ ያደረገን ምንድነው? እንዴትስ እንድንሆን ተጠርተናል? መባባል የተሻለ መንገድ ነው፡፡

 

እኛ አማኞች ነን፡፡ ያመንነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ በገለጠውም የእውነት ትምህርት ነው፡፡ እርሱ ያለ አንዳች የሰው ጥረት፣ ያለምንም የኛ አስተዋጽኦ እንዲያው በጸጋው አዳነን፡፡ መጽሐፍ አረጋግጦ እንደሚነግረን፡- “ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፣ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንት አይደለም፡፡ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም፡፡” በከንቱ አልባሌ ኑሮ፣ በጨለማ ድንብርብር ሕይወት፣ በታላቅ መንፈሳዊ ድንቁርናና ልበ ድፍንነት የኖረ ማንም ዐመፀኛ የአዳም ልጅ የጌታችን የፍቅር ጥሪ ሲገባውና አለኝታውን በእርሱ ሲያደርግ አመንሁህ ብሎ እጅ ሲሰጥ በዚህ ብቻ ከሞት ወደ ሕይወት ተሻገረ፡፡ እንዴት ያለ ታላቅ ጸጋ ነው! አድርግ፣ አታድርግ በሚሉ ሺህ ደንቦች ክስ ሥር የወደቅን ጎስቋሎች በጸጋ ብርቱ ክንድ ተነሣን፡፡ ምንም ምን ክፋት እንዳላደረግን ተቆጠርን፡፡ ወንጀለኛነታችን በእንከን የለሹ ክርስቶስ ላይ ሲያርፍ እኛ ጻድቃን ሆንን፡፡

 

ይህ ከመዓት ያተረፈን ጸጋ ሥራው እዚያ ላይ ተደምድሟልን? ከትቢያ ካነሣን በኋላ “እንግዲህ ዕወቁበት” ብሎ ትቶን ሄዷልን? መጽሐፍ እንደርሱ አይልም፡፡ ይልቁን አዳኙ ጸጋ አሠልጣኙም እርሱ ራሱ እንደሆነ አረጋግጦ ይነግረናል፡፡ “ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤ ይህም ጸጋ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊ ምኞት ክደን የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል” (ቲቶ 2÷11-13)

 

የጸጋን ድነት የተቀበልን ሁላችን የጸጋን ሥልጠና የምንሸሸው ስለምንድነው? ጸጋ ኮ ሲያድነን ጉልበት እንደሆነን ሁሉ ሲያሠለጥነንም ዐቅም የሚሰጠን ከነስሙ ባለጸጋ ነው፡፡ እርግጥ ትምህርቱ ቆፍጣና ነው፡፡ በወለም ዘለምታ የሚያዝ አይደለም፡፡ ምን ያስተምራል የተባለ እንደሆነ ጳውሎስ እንደሚነግረን አንዱ ዋና ኮርሱ ክህደት ነው፡፡ እኛ የምናውቀው የእምነት ትምህርት ቢሆንም እምነት የሚጸናው የማይታመነውን በመካድ ነው፡፡ የነፍሴን መድኃኒት መድኃኔአለምን ሙጥኝ አልኩት፣ ታመንሁበት የሚል አንድ ምስኪን የአዳም ልጅ ወዲያው አያይዞ ነፍሴን አውዳሚ መርዝ የሆነውን ኃጢአተኛነትንና ዓለማዊ ምኞትን እክዳለሁ እንዲል ጸጋ ይጠይቀዋል፡፡ በደባልነት ሊኖሩ ለማይችሉት ለእነዚህ ለሁለቱ ቁርጥ መልስ መስጠት ይጠበቅበታል፤ ለአንዱ አመኔታ ለሌለው ክህደት፡፡ በእሁድ ጧት ስብከታችን “ጌታን ለማመን የወሰናችሁ ወደፊት ኑ” እንደምንል ሁሉ “ዓለማዊነትን ለመካድ የቆረጣችሁ ወደፊት ኑና ይጸለይላችሁ” ማለት የሚገባን ይመስለኛል፡፡

 

በአሁኑ ዘመን እያንዳንዱን አማኝ እና ቤተክርስቲያንን በጥቅሉ እየናጡ ካሉ ከፍተኛ ኃይላት መካከል ምናልባት ዋነኛው ዓለማዊነት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ይህች ዓለም አሮጌ ብትሆንም፣ ዘዴዎቿ ድሮ ገና የታወቁ ቢሆንም፣ “እኔን ያየህ ተቀጣ” የሚሉ እርሷ ወግታ የጣለቻቸው አያሌ ቢሆኑም÷ዛሬም እንኳ ወይንጠጇ ያንገዳግዳል፤ ዛሬም የደጃፏ ድጥ ሙልጭልጭ ነው፡፡

ዓለማዊነትን ብርቱ ያደረገው ምንድነው ቢባል አባባይነቱ ነው፡፡ የደስታና የርካታ ገበታ አቅርቦ ማስጎምጀቱ፣ የባልጀራ የአጫፋሪ ብዛት አሳይቶ ማባባሉ፣ የዋስትና የአለኝታ ዜና እየለፈፈ ማሳሳቱ፣ የክብር የዝናና የታዋቂነት ሥዕል እየሳለ ማማለሉ፣ ይህን ይህን የሚመስል ደመነፍሳዊ፣ ሥነ ልቡናዊና ማኅበራዊ ፍላጎታችንን ተገን ያደረጉ ብዙ ማባበሎች እንደ ሠራዊት በፊታችን ማሰለፉ ነው ያርበተበተን፡፡ ጉልበቱ የእኛ ልዩ ልዩ ዐይነት ራብ ነው፡፡ እንግዲያው ዓለማዊነት የማይደፍረው ወይም ቢቃጣም የማያንበረክከው የጠረቃውን ሰው ነው፡፡ በልቶ የጠገበ፣ ጠጥቶ የረካ፣ እግሩ የፈረጠመ፣ ልቡ ሙሉ የሆነ፣ ዓይኑ ያተኮረ፣ ልቡናው የሰመረ ሰው ሲያገኝ ትግሉን አይችለውም፡፡

የዓለማዊነት መርዝ ማርከሻው እግዚአብሔር መሰልነት (Godliness) ነው ይህም ማለት እውነተኛ መንፈሳዊነት ማለት ነው፡፡ ከእርካታ ሁሉ ምንጭ ከሰማዩ አምላክ የሚያገኘውን የመንፈስ ቅዱስ ፍስሓ ያገኘ ሰው ሌላው ሌላው ፈንጠዝያ ተራና አልባሌ ይሆንበታል፡፡ በሰው ቋንቋ ከመገለጽ በላይ ከፍ ያለውን የክርስቶስን ፍቅር የሚያጣጥም ሰው የዓለም ፍቅር መናኛ ይሆንበታል፡፡ ከማርና ከወለላውም የሚጣፍጠውን የቃለ እግዚአብሔርን ማዕድ የቀመሰ ሰው እንቶ ፈንቶ የሆነውን ያሁኑን ዓለም ትዕይንት ይንቃል፡፡ በሕይወት መጽሐፍ ስሙ መጻፉን የተገነዘበ ሰው ለአላፊ ጠፊ የዚህ ዓለም መዝገብ እጅግም አይጨነቅም፡፡ “ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፣ እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጠው አይደለም” “አእምሮን ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል፡፡” ተብሎ የተነገረውና ይኸው ተስፋ የዘለቀው ሰው ዓለም ዋስትናና መተማመኛ እያለች የምታቀርብለትን ሁሉ ዝቅ አድርጎ ለመመልከት ጉልበት ያገኛል፡፡ ወዳጆቼ ዓለማዊነት “ዞር በል” በማለት ብቻ የምንረታው ጠላት አይደለም፤ እኩይ መሠሪ ስለሆነ በየራባችን ቀዳዳዎች ሁሉ እየገባ “አለሁ” ይለናል እንግዲያው ሥራችን ራብን ማጥፋት ሊሆን ይገባል፡፡ ለቅልውጥ ችግር አብነቱ ይኸው ነው፡፡ እቤት በልቶ መሠማራት፡፡ የእግዚአብሔርን አርኪነት በዝርዝር እየገባን መረዳት፤ በዚሁ ርካታ ውስጥ ለመኖር ራሳችንን ማሠልጠን፡፡ የእግዚአብሔር ቤት የእርካታ ቤት እንጂ ጠኔ ያጠላበት የተራቆተ ቤት እንዳይሆን የፍቅርን ገበታ፣ የሰላምን ማዕድ፣ የደስታን ዘይት ቶሎ ቶሎ ከመንፈስ ቅዱስ እየተቀበልን ሲጎድል እያስሞላን ማዕዱ እንዳያጥጥ፣ ራብተኛም እንዳይደነግጥ መትጋት የጊዜው ዋና ጥሪ እንደሆነ አምናለሁ፡፡

የጸጋ ሥልጠና የራስ መግዛትም ሥልጠና ነው፡፡ ለካ ራስ መገዛት ያለበት ነገር ነው፡፡ ያልተገዛ እንደሆነ አፈትልኮ ወጥቶ አምባውን ሁሉ ያሸብራል፡፡ የሚይዘውን የሚጨብጠውን እንደማያውቅ ድንጉላ ፈረስ ሜዳውን ሁሉ ይጎደፍራል፤ አጉራ ዘለል ይሆናል፡፡ ክልክል የሚባል እንደሌለ እያመነና እያሳመነ አገሩን በማን አለብኝነት ይሞላል፡፡ የድፍረቱን ዕዳ ጽዋ እያንገሸገሸው እስኪጠጣ ድረስ ማረፊያም የለውም፡፡ አዳኙ ጸጋ ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ እንዳወጣን ሁሉ ከራሳችንም ሊያድነን ነው የመጣው፡፡ የራስን ገናን ጉልበት የሚያንቀሳቅሰውን የሥጋ ሞተር በመንፈስ ቅዱስ ብርቱ ኃይል ሊተካው ነው የተዛመደን፡፡ ወዳጆቼ ራስ በምን ይገዛል በጌታ ቃል እውነት ብርሃን ያገኘ ኅሊና በመንፈስ ቅዱስ ዐቅም ካላንበረከከው በቀር! “መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ… የጌታ ፈቃድ ምን እንደሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ፡፡” የተባለው እኮ የራስ ፈቃድ እየገነነ በሚያቅራራበት ክፉ ዘመን ዐውድ ውስጥ ነው፡፡ እንግዲያው ወገኖቼ በራስ እንዳንሞላ፣ ናላ በሚያዞር በነገርና በምናምንቴው ሁሉ እንዳንሰክር የልባችንን ማድጋ ተሸቀዳድመን ቅዱሱን መንፈስ እናስሞላው፡፡ የዘመናዊው ሰው አንድ በሽታ የዐይኑ መቃበዝ ነው፤ የዙሪያ ገባው ውልብልብታ እረፍት አልሰጠውምና ውልብ ያለውን ሁሉ ለማየት ሲዟዟር የአንገቱ ዋልታ ላላ፡፡ የገበያ ጋኔን ከሁሉ ሳይከፋም አይቀር፡፡ የዕቃ፣ የአስተሳሰብ፣ የቄንጥ፣ የአላፊ አግዳሚ ወረት ሁሉ ልቡናችንን አቅበዘበዙት፡፡ ትክ ብሎ የሚታይ እየጠፋ እይታ የአፍታ የአፍታ ብቻ እየሆነ ሕይወት አዙሪት ጨዋታ ውስጥ ወደቀች፡፡ የጸጋ ትምህርት የትክታ ትምህርት ነው፡፡ አትኩሮ የማየት፤ ጸንቶ የመጠበቅ፡፡

 

“የተባረከ ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ ክብር መገለጥ እየጠበቅን እንድንኖር ያስተምረናል፡፡” አትኩሮት ለመላ አካላችን ቅርጽ ይሰጣል፤ ወደ አተኮርንበት አቅጣጫ እናዘምማለን፡፡ ከሰማይ የሚመጣውን ይህን ክቡር ጌታ ስንጠብቅ የተነጣጠረ ሕይወትና ደማቅ መስመር እናገኛለን፡፡ ዓይናችንም መንከራተቱን ይገታና ሁነኛ ነገር ላይ ይውላል፡፡ የየዕለት እርምጃችን ከየስላቹ በሚያንባርቅ ጥሩምባ ሳይሆን በሰማይ ቅኝት ይመራል፡፡ ባለ ክቡር ዓላማ ገስጋሽ ሠራዊት እንሆናለን፡፡ ጸጋው አማኞች ብቻ ሳይሆን ጠባቂዎችም ያደርገናል፡፡ ክርስቲያንነት ጥበቃ ነው፤ የዘወትር ተጠንቀቅ ነው፤ ሁሉ ነገር ያው የሆነበት ምድር ዓለሙ ሳይቋረጥ የሚጓዝበት የሰው ልጅ ታሪክ ዞሮ እየገጠመ እንደገና ዝንተዓለሙን የሚዞርበት ሽክርክሪት ሳይሆን ታሪክ ሁሉ ወደ አንድ ሁነኛ መድረሻ የሚገሠግስበት በዚህም ሳቢያ አማኙ ሰው “በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ፣ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋሁ” የሚልበት ንቁ (active) ሕይወት ነው፡፡ እነዚህ ቆፍጣና የጸጋ ትምህርቶች መነሻቸው የክርስቶስ ሞት ዓላማ ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ከጸጋ መገለጥ ከጸጋም ሥልጠና ጋር አያይዞ የሚያነሣ መሠረቱና ድምድማቱ መስቀለ ኢየሱስ ነው፡፡ “ኢየሱስ ክርስቶስ የሞተው ለምንድነው?” የሚለውን ዋና ጥያቄ ለወትሮ በምንመልስበት “የሰማይ ቤት ሊያወርሰኝ” በሚል ወደፊታዊ መልስ ብቻ አያቀርበውም፡፡ የጌታችን ሞት ፋይዳ የዛሬም ጉዳይ ነው፡፡ የዛሬ ኑሮ ጉዳይ ነው፡፡ “ከዐመፅ ሁሉ ሊቤዠን” ሞተ ይለናል፡፡ የዐመፀኛነት፣ የመለኮትን ሃሳብ የመቃወም የራስን ሃሳብ የማግነን የጌታችንን ትዕዛዝ የመግፋት፣ የእንቢታ፣ የሽፍትነት ባሕርያችንን ሊለውጥልን ከዚህ ዲያብሎሳዊ ክፉ ዐመል ሊያላቅቀን ሞተ ይለናል፡፡ “መልካሙን ለማድረግ የሚቀና ሕዝብ” ፈልጎ ሞተ ይለናል፡፡ በመስቀሉ የተዋጀው ሕዝብ ሥራው ባያድነውም ከዳነ በኋላ ግን ብርቱ የመልካም ሥራ ዐርበኛ እንዲሆን ተፈልጎአል፡፡ “በጎ ሥራ የት ይገኛል? ብሎ በዓይኑ የሚማትር ሲያገኘውም በትጋት የሚፈጽመው ቅን ኅብረተሰብ የመስቀሉ ምርት ነው፡፡ “ገንዘቡ የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ” ሞተ ይለናል፡፡ የክርስቶስ ሞት አንድም የግዢ ውል ነው፡፡ በደሙ ስለገዛን የባለቤትነት ሙሉ መብት አለው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የራሱ ሕዝብ፣ ለወደደው ዓላማና ተግባር የሚያሰማራው ሠራዊት ፈልጎ ነው የሞተ፡፡ ታላቁ ጠቢብ በዚህ ሙዐለ ሕይወት (ኢንቨስትመንት) ሊከስር አይሻም፡፡ የተባለው ሁሉ ተብሎ እንደ አንድ የክርስቶስ ተከታይ እንደ ቤተክርስቲያንም ልናስብባቸው የሚገቡ ሁለት ዋና ነገሮች ይታዩኛል፡፡ የተያያዙም ቢሆኑ በየስማቸው ቢጠሩ ይወዳሉ፡፡ መጀመሪያ ነገር እስከዛሬ ስንማር ስናስተምር የቆየነው ስለማመን ስለመቀበል ጌታን እሺ ስለማለት ነበርና አሁን ደግሞ ጨምረን ክህደትን እንማር፣ እናስተምር፡፡ ያው እንደተባባልነው በወደር የለሹ ክርስቶስ ላይ ያለንን እምነት ለማጽናት ተፎካካሪ ገናኖችን ልክ ልካቸውን ነግረን ቦታቸውን እናሳያቸው፣ ለአንድ ጌታ ሎሌነት ማደራችንን እናስታውቃቸው ብዙ የሚካዱ ኅሳዌ መሲኃን (እንደዚህ ሲባል ሥጋ የለበሱ ሰዎችን ብቻ ለምን እናስባለን) ከጽድቅ የሚያፈናቅሉንን የራሳችንን አጓጉል ምኞቶችና ዐመፀኛነቶች እንዳሉ ለባልጀሮቻችን ሁሉ እንንገር፡፡ ክፉውን ደግ ደጉን ክፉ የሚያደርገውን፣ ክቡሩን ቀሊል ገለባውን ፍሬ የሚያስመስለውን የዓለሙን የተዛባ ሥራተ እሴት አንቀበልም ብለን እንካድ፡፡

 

ሁለተኛ ነገር ይህን ዓለም ማሸነፊያ ዮሐንስ እንደነገረን በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ያለ እምነታችን ነውና በእርሱ ያለንን እምነት ስንኖርበት የሚያዩ ሁሉ “ውይ እንዴት ያማረ እንዴት የሰመረ ሕይወት ነው” እንዲሉ በጌታ ዘንድ ያለውን ሀብት እንጠቀምበት፡፡ “ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ” እንደተሰኘው ተረት እንዳይሆንብን ከመለኮታዊ ጸጋው የሚመነጨውን ደስታ፣ ፍቅር፣ ሰላምና ርካታ የሚያጣጥም ምላስ እናዳብር፡፡ ጤነኛ አፒታይት (የምግብ ፍላጎት) እንዲፈጥርልን የነፍሳችንን ጌታ እንለምነው፡፡ እናምናለን በመስቀሉ እንቆማለን በወንጌሉ ሕያው ሆኖ ይሠራል አልተለወጠም ቃሉ፡፡

Read 26277 times Last modified on Monday, 05 May 2014 08:21
Negussie Bulcha

Website: www.negussiebulcha.com Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 167 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.