You are here: HomeSermonእስቲ መታወቂያ?!

እስቲ መታወቂያ?!

Written by  Tuesday, 19 August 2014 00:00
Dr. Mamusha Fanta Dr. Mamusha Fanta

በምንዘዋወርባቸው ቦታዎች ሁሌ የምንጠየቃት ጥያቄ ናት፥ መታወቂያ። የሕጋዊ መንግሥት ዜጎች መሆናችንን ለማረጋገጥ መዘዝ አድርገን እናሳያታለን። ዛሬ ጠዋት ቢሮዬ ቁጭ ብዬ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ዜግነቴ ሳስብ ነበር። የመጣልኝ ብርቱ ጥያቄ “ለመሆኑ የዜግነት መታወቂያ ብጠየቅ ምንድን ነዉ የማሳየው?” የሚል ነበር። ጥያቄዬም ወደ ማቴ 5፡ 1-12 መራኝ። የተማርኩትንም ላካፍላችሁ ወሰንኩ።

 

እነኝህ ቁጥሮች በተለምዶ “የተራራው ስብከት” ተብሎ ለሚጠራው ክፍል እንደመግቢያ የሚያገለግሉ ሲሆን “ብጽዕናዎች” የምንላቸውን ባህርያት ይዘረዝራሉ። 

 

“ብጹዓን ናቸው” የተሰኘዉ ቃል አንዳንድ ጊዜ “ደስተኞች ናቸው”፣ “ምስጉኖች ናቸው”፣ “ቡሩካን ናቸው” እየተባለ ይተረጎማል። ከእነኝህ ሁሉ ቃላት ጋር የሚነካካ ትርጉም ስላለዉ ነው እንዲያ የሚተረጎመው። በዋናነት ግን እግዚአብሔር በመንግሥቱ የተቀበላቸው ዜጎች ባህርያት ናቸው። እነኝህ የእግዚአብሔር መንግሥት ዜጎች እግዚአብሔር የሚጠብቅባቸውን ኑሮ ከመኖራቸው የተነሳ የተባረኩና የሚደሰቱ ናቸው። 

 

እነኝህ ባህርያት ወደ መንግሥቱ መግቢያ መመዘኛዎች አይደሉም። ቢሆኑ ኖሮ አንዳችንም አሟልተን አንገባም ነበር። ወደ መንግሥቱ መግባት የክርስቶስን ሥራ በእምነት በመቀበል የሚገኝ እንጂ በእኛ ሥራ መች ሆነና! ይልቁንስ ወደ መንግሥቱ የገቡ ሰዎች የባህርይ መታወቂያ ናቸዉ። በረከቶቹ “መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና” (ቁ 3) በማለት ጀምረዉ፤ ሌሎች ባርኮቶችን በመሀል በመዘርዘር እንደ ገና “መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና” (ቁ.10) በሚል ባርኮት ያጠቃልላሉ። ይህ የተለመደ ያጻጻፍ ዘይቤ ሲሆን የሚያስተምረንም በመንግሥቱ ዉስጥ የሚኖሩ ሁሉ በእነኝህ ባህርያት ይታወቃሉ። “እስቲ መታወቂያ?!” ተብለዉ ሲፈተሹ እነኝህ ባሕርያት ይታዩባቸዋል ማለት ነዉ። 

 

የእግዚአብሔር መንግሥት ዜግነት መታወቂያ የባሕርይ ፍሬ ነዉ። ጌታችንስ “ከፍሬያቸዉ ታውቋቸዋላችሁ” አይደል ያለው? ቀጥሎም፡- “መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፤ ክፉ ዛፍም ክፉ ፍሬ ያደርጋል” ብሎ አስተምሯል (ማቴ 7፡ 16-20)። በገላትያ 5፡ 22 ላይም በመንፈስ አዲስ ሕይወት የጀመሩ ሁሉ የሚያሳዩአቸው ፍሬዎች ተቀምጠዋል፣ “የመንፈስ ፍሬ” በመባልም ይታወቃሉ። አንድ ሰዉ ስለ ክርስትና የተናገሩትን በግርድፍ ትርጉም ላስቀምጥ 

 

“ክርስትና በፓልስታይን ሲጀምር ሕይወት ነበር፣ ወደ ግሪክ ሲሄድ ፍልስፍና ሆነ። ወደሮም ሲገባ ወደ ተቋምነት ተቀይሮ በአዉሮፓ ባህል ሆነና አሜሪካ ሲደርስ ንግድ ሆኖ አረፈዉ!” 

 

በእኛ ሕይወትስ? 

 

“በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብጹዓን ናቸዉ” (ማቴ 5፡ 3) 

 

የመጀመሪያው የእግዚአብሔር ልጆች መታወቂያ “የመንፈስ ድህነት/ በመንፈስ ድሃ መሆን” ተብሎ ተጠቅሷል። ብዙዎቻችን እንደምናውቀው “በመንፈስ ድሃ መሆን” መቼም “የመንፈስ ቅዱስ ድህነት” ሊሆን አይችልም። መንፈስ ቅዱስን በተመለከተ የእግዚአብሔር ልጆች በመንፈስ ቅዱስ እንዲጠመቁ፣ እንዲሞሉ፣ በመንፈስ የሚቃጠሉ እንዲሆኑ፣ በአጠቃላይ እንዲበዛልን እንጂ የመንፈስ እጥረት እንዲኖረን መጽሐፍ ቅዱስ አያስተምረንም። 

 

ታዲያ ይህ “በመንፈስ ድሃ መሆን” ምን ማለት ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ ከመረመርን ይህ ድህነት የብሉይ ኪዳን ሥረ-መሠረት ሳይኖረው አይቀርም። ለምሳሌ ኢሳ 57፡15 እንዲህ ይላል፡- 

 

“የተዋረዱትን ሰዎች መንፈስ ሕያው አደርግ ዘንድ፤ የተቀጠቀጠውንም ልብ ሕያው አደርግ ዘንድ፤ የተቀጠቀጠና የተዋረደ መንፈስ ካለዉ ጋር በከፍታና በተቀደሰ ስፍራ እቀመጣለሁ።” 

 

በኢሳ 66፡2 ደግሞ እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፡- “ወደዚህ ወደ ትሑት፣ መንፈሱም ወደተሰበረ፤ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ።” 

ስለሆነም “የመንፈስ ድህነት” ከልብ መዋረድ/ከትህትና ጋር ተያይዞ እናገኘዋለን። የመጀመሪያው የመንግሥቱ መታወቂያ እንግዲያውስ ትሕትና ነዉ። በሉቃስ 18 እና ሌሎች ሥፍራዎችም ኢየሱስ እንዳስተማረው መንግሥቱ ለትሑታን፣ እንደ ሕጻናትም ለሆኑ ናት። ማቴ 5፡ 3 ላይም የትሕትና በረከት “መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና” የሚል ነዉ። 

 

ትሕትናና የተሰበረ ልብ እግዚአብሔርን የማወቅ ምልክቶች ናቸው። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ከዳር እስከ ዳር ብናገላብጥ እግዚአብሔርን በትክክል አይቶ በፊቱ የታበየ አናገኝም። “በፊቱ ተደፋሁ፣ እንደሞተ ሰዉ ሆንኩ፣ ቆሻሻነቴ ገባኝ” የሚሉ ቃሊት እንጂ “ጀግንነት አመልካች” ቃላት አይገኝም። 

 

እግዚአብሔርን የሚያውቁ ትሑታን ናቸዉ። እግዚአብሔርም የበለጠ ጸጋ ይሰጣቸዋል። ትዕቢተኞችን ግን ይቃወማል። ትህትና ከዘመናዊው ዓለም ጋርም ሆነ ከዘመን አመጣሹ ‘መንፈሳዊ’ የሚመስል ራስን ከፍ የማድረግ አስተሳሰብ ጋር አይሔድም። ሆኖም ግን ጨክነን በልዩነት በመቆም በትህትናችን ዓለም ክርስቶስን ያይ ዘንድ ይህ ታላቅ መታወቂያ ከሕይወታችን አይጥፋ።

 

“የሚያዝኑ ብጹዓን ናቸው” (ማቴ 5፡ 4) 

 

ዓይናችን የሚያየው፣ ጆሮአችን የሚሰማው፣ ልባችን የሚያስበው ብዛቱ! የሚያምረውን፣ የማያምረውን፣ የሚያስደስተውን፣ የሚያሳዝነውን፣ የምንፈልገውን፣ የማንፈልገውን ሁሉ ወደኛ ሲያነጉድ ይውላል ያድራል። ውስጣችን ያለው የሃሳብ ማጠራቀሚያ ጆንያ አለመሙላቱ ያስገርማል! 

 

አንዱ የማይሞላበት ምክንያት አንዳንዱን እየመረጥን ገሸሽ (delete) ስለምናደርግ ይሆን እንዴ? (ግምት እንጂ እኔ በርግጥ አላውቅም)። የምንደመስስ ከሆነ ግን መርጠን የምንረሳው በአብዛኛው ክፉና አሳዛኝ ነገሮችን ሳይሆን አይቀርም። ለምሳሌ አንዳንድ ጊዜ የሚዘገንን እልቂት ያለበት ዜና በቴሌቪዥን እመለከትና ትንሽ ለማዘን ስጀምር ወዲያው ቀጥሎ የሚመጣው የታዋቂ ተጫዋች አዝናኝ ጎል ያስረሳኛል። በእጄ ላይ ያለች አንዲት መዝናኛ ሳየው የዋልኩትን ግፍና ሰቆቃ ስታስጥለኝ እታዘባለሁ። ይህ አይነት ዝንጉነት ደግሞ ሸክም-አልባና ዋዘኛ ሰው ያደርጋል። 

 

የእግዚአብሔር መንግሥት ዜጎች ግን መታወቂያቸው ሸክምና ርህራሄ ነዉ። በማቴ 5፡4 ላይ የሚገኘው ይህ መታወቂያ ‘የሚያዝኑ’ ተብሎ ተጠቅሷል። ይህ ማለት ክርስቲያኖች ሁልጊዜ የተኮሳተረ ፊት ያላቸው ቆዛሚዎች ናቸው ለማለት አይደለም። እንደውም እነርሱ “ሁልጊዜ…ደስ ይበላችሁ” የተባለ ደስተኞች ናቸው። ደስታ የእግዚአብሔር ልጆች ሃብት ናትና። 

 

ሆኖም ግን ግፍን፣ በደልን፣ የሰዎችን ጉስቁልና፣ ጽድቅ የጎደለውን ነገር ሁለ በራሳቸውና በሌሎች ሕይወት ሲመለከቱ ያዝናሉ፣ ያለቅሳሉ፣ ይጦማሉ፣ ይጸልያሉ፣ ሁኔታውንም ለመለወጥ እርምጃ ይወስዳሉ። ባጭሩ የመንግሥቱ ዜጎች የሸክም ሰዎች ናቸዉ። 

 

የኢየሱስን ፈለግ ከተከተልንም አንዱ መታወቂያው ይህ ሐዘኔታና ርህራሔ መሆኑን ማወቅ ይገባናል። የተራበውን የመገበው፣ የታመመውን የፈወሰው፣ የተጨነቁትን ያጽናናው፣ ግፈኞችን የገሰጸው በውስጡ ካለው ርህራሄና ሸክም የተነሳ ነበር። ቅዱስ ጳውሎስም ከክርስቶስ ተለይተው ስለነበሩ የስጋ ዘመዶቹ “ብዙ ኀዘን የማያቋርጥም ጭንቀት” በልቡ እንዳለበት ይናገራል (ሮሜ 9፡1)። እግዚአብሔር የተጠቀመባቸው ቅዱሳን ሁሉ የሸክምና የርህራሄ ሰዎች ነበሩ። እንደዚህ አይነት ሰዎች ከእግዚአብሔር ዘንድ “መጽናናትን ያገኛሉ” (ማቴ 5፡4) 

 

የሚሰሙትንና የሚያዩትን ግፍና ድካም ከመልመዳቸው የተነሳ ምንም የማይመስላቸው፤ ከዚያም አልፎ በሚያዩት ችግር የተመሰረተ ቀልድ (ጆክ) በመቀለድ የሚዝናኑ፣ የሌሎችንም ሆነ የራሳቸውን ድካም ማየት ያቃታቸው ብዙ ሰዎች የሚኖሩበት ዘመን ነው። እናንተስ ምን ይሰማችኋል? ጌታን የሚያሳዝን ሁሉ የሚያሳዝነን ሩህሩሆችና የሸክም ሰዎች በመሆን የአባታችን ልጆች መሆናችንን እንግለጥ። የወንድማችንን የመጋቢ እንድርያስ ሀዋዝ “የእንባ ሰው አርገኝ ባለ ራእይ” መዝሙር መዘመርና “አሜን” ማለት የሚያስፈልግበት ዘመን ይመስለኛል።

Read 13759 times Last modified on Friday, 22 August 2014 10:17
Dr. Mamusha Fenta

Mamusha Fenta is a Bible expositor and conference speaker residing in Addis Ababa, Ethiopia.

Studied at

Website: mamushafenta.com Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 357 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.