በዚህ ባለንበት ዘመን በሐገራችን የወንጌላውያን ክርስትና የአደባባይ ገጽታ የተሟላ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ለዚህ ዋነኛው ማስረጃ የወንጌሊውያን ክርስትና በዋነኛነት እየተወከለ የሚገኘው አምልኮ፣ ፈውስ፣ ጸሎት፣ ትንቢት በመሳሰለት ነገሮች ብቻ ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች እጅግ በጣም አስፈላጊና መሠረታዊ ናቸው ፡፡ ቢሆንም ግን የወንጌላውያን ክርስትና አማኝ ተኮር ፣ ልብ- ተኮር እንጂ አመለካከት እና ዓለም- ተኮር ሲሆን አይታይም፡፡
ከዚህም የተነሳ በርካታ ችግሮች ተከስተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ጥቂቶቹ የሚከተለት ናቸው፡-
1. አማኞች ስለ መጽሐፍ ቅደስ ያላቸው ዕውቀት ሲታይ አናሳ የሚባል ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው፡፡
2. አማኞች ከመናፍቃን የሚነሱባቸው እምነትን የሚነቀንቁ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ተስኗቸው አንገታቸውን ሲደፉ ይታያሉ፡፡
3. አማኞች በሐገራችን ሰፊ ስፍራ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ያላቸው ተሰሚነት አናሳ ነው፡፡
4. ከላይ ከዘረዘርናቸው ችግሮች የተነሳ አማኞች ወንጌልን ለመኖር እና ለመመስከር ያላቸው ድፍረት እየደበዘዘ መጥቷል፡፡
እነዚህ ከላይ የዘርረዘርናቸው ችግሮች መፍትሄ ተደርጎ ሊታይ የሚገባው ዘመን ባፈራው መንገድ አማኞች ክርስቲያናዊ አመለካከት እንዲያዳብሩ እና ክርስቲያናዊ ሕይወትን እንዱኖሩ ከዚህም የተነሳ ደግሞ ስለ ጌታ የማያምኑ ሰዎች በድፍረት መመስከራቸው ነው፡፡ ይህን ለማምጣት የሚረዳን የሚዲያውን አድማጭ-ተመልካች በሚመጥን መልኩ የተዘጋጀ ተከታታይ እና ጥልቅ ትምህርት ነው፡፡