You are here: HomeYouth Cornerፌስቡክን እንደክርስቲያን...

ፌስቡክን እንደክርስቲያን...

Written by  Sunday, 30 November 2014 00:00
Selam Asg. Selam Asg.

21ኛው ክፍለ-ዘመን በኮምፒውተር ቴክኖሎጂ አለማችን የናኘችበት ዘመን ነው። በዚህ ቴክኖሎጂ የሚሠሩትን-በተራ ሰው አዕምሮ መገመትና ማወቅ አይቻልም። ነገር ግን አብዛኞቻችንን ከኮምፒውተር ጋር ያስተዋወቀ አንድ ግኝት ይዞ መጥቷል:- ፌስቡክ። ድሮ ኮምፒውተርን እንደ ጦር የምንፈራ ሰዎች-አሁን እድሜ ለፌስቡክ እንኳን ልንፈራው፤ ውሏችን ከእርሱ ጋር ሆኗል። ኧረ አንዳንዴም በውሎ ብቻ ካለፈ መልካም ነው-አዳርም እኮ አለ!! ይህንን በማለቴ አላግባብ የሆነ የፌስቡክ አጠቃቀምን ማበረታቴ እንዳልሆነ መቼስ ማስረዳት ያለብኝ አይመስለኝም-እንኳንና ተበረታተን እንዲሁም አልተቻልንምና። ታዲያ ማበረታቴ ካልሆነ "የዚህ ጽሁፍ አላማው ምን ይሆን?" የሚል ጥያቄ በአንባቢያን አዕምሮ ውስጥ መፈጠሩ አይቀርም። እኔም እንግዲህ ነገሬን አሳጥሬ ወደ ዋናው ሃሳቤ ልግባ። 


ፌስቡክ-የተጠፋፉ ጓደኞችን የሚያገናኝ መረብ፣ያሳለፉትን ጊዜያት እንደትውስታ እየቃኙ የሚስቁበትና የሚገረሙበት፣ የህይወት ልምዳቸውን እየተካፈሉ የሚወያዩበት መልካም ድረ-ገጽ ነው። ከዚያም ባለፈ መልኩ ለሌሎች ይጠቅሙ ዘንድ ሃሳቦችን ፅፎ በግል ግድግዳ ላይ በመለጠፍ "what is in your mind?" እና "note" የሚሉ ነገሮችን በውስጡ ይዟል። እንዳስፈላጊነቱም "Group" መፍጠር እንዲቻል ተደርጎ ተቀርጿል።በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የዚህ ድረ-ገፅ አባላት ሆነው ሳለ፤ ስለምንፅፋቸው ነገሮች ግድ ቢለን አለማችን ምንኛ በተቀየረች ነበር! ሌሎች ጠቃሚ መረጃዎችን ወደ ጎን አድርጌ፤ ክርስቲያን የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ማድረግ አለባቸው ብዬ የማምነውን ላካፍላችሁ:-


በዚህ በዘመኑ መጨረሻ-የጌታ መምጣት ቅርብ በሆነበት ወቅት-የገባንን እውነት ለራሳችን አፍነን ይዘን-ከሰው ሰው የግል ገፅ እየዘለልን የፎቶ ጥናት ማድረጉና የሚፃፉ አሉባልታዎች ላይ ጊዜ ማቃጠሉ ተገቢ እንዳልሆነ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ልረዳ ችያለሁ። የጌታን ፍቅርና የምህረቱን ብዛት ለመመስከር በዚህ ዘመን ከፌስቡክ የበለጠ መንገድ የለም። ጌታ በሰጠን በዚህ ዕድል ተጠቅመን ሰዎችን ወደ ፍቅሩ መንግስት እናፈልስ ዘንድ ፌስቡክን ለዚህ የከበረ ስራ ማዋል እንዴት ደስ ያሰኛል!! ፌስቡክ ላይ ተቀምጠን የምናጠፋው ጊዜ እንደመጥፋትና መባከን ሳይቆጠር በሠራነው ስራ የመንፈስ እርካታን የምናገኝበት ጥሩ የአገልግሎት መድረክ ይሆንልናል ብዬ አምናለሁ። ከምስክርነትም ባለፈ ሁኔታ የእግዚአብሔር ቃልን በመለዋወጥ እርስ በእርሳችን የምንተናነፅበት መልካም መንገድ ልናደርገው እንችላለን። "ሥጋ ሁሉ እንደ ሣር ክብሩም ሁሉ እንደ ሣር አበባ ነውና ሣሩ ይጠወልጋል አበባውም ይረግፋል የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ይኖራል።"(1ጴጥ 1፥23-24) ተብሎ በቃሉ እንደተፃፈ፤ የሚያልፈውን ትተን የማያልፈውንና ለዘላለም ፀንቶ የሚኖረውን የእግዚአብሔር ቃል በየቀኑ የምንናገርበት መድረክ ማድረግ እንዴት መታደል ነው? የጌታን ቃል ደግሞ በእምነት ከተናገርን ፍሬን ሳያፈራ አይመለስምና፤ በእውነት ለጓደኞቻችን ግድ እያለን ቃሉን በእምነት እንዝራ።

"የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል"ዕብ 4፥12. 

Read 8954 times Last modified on Sunday, 30 November 2014 05:58
Selam BeSelam

I am a member in ethiopian evangelical church Boston, studied at University of Massachusetts Boston and love writing poem!

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 49 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.