You are here: HomeYouth Cornerወይ….አዳም?

ወይ….አዳም?

Written by  Saturday, 12 July 2014 00:00
Zeleka (Kaku) Zeleka (Kaku)

 . . . .ጊዜው የመጀመሪያው የአሜሪካ ጥቁር ፕሬዚዲንት ባራክ ኦባማ የሚወዳደሩበት ጊዜ ነበረ:: ዜናው የሰውን ሁሉ ቀልብ ያገኘበት ስለነበረ ሁላችንም እሳቸውን እየደገፍንም፣ እየነቀፍንም ባለንበት በሞቀ ውይይት መካከል ውበት ከመጸዳጃ ክፍል ወጣችና የሚያምሩ ጣቶቿን እያሻሽች እንዲህ አለችና አስደነገጠችን። "እስቲ አሁን ባራክ ኦባማን እንተዋቸው! " አለችና "ለመሆኑ ጥሩ ባል እንዴት ነው የሚገኘው?" በማለት ከነበርንበት ውይይት አወጣችን። መውጣታችን ግድ ቢሆንም ጥያቄዋን ግልፅ እንድታደርግልን ሁላችንም የተለያየ ጥያቄ እንጠይቃት ነበር። ፍኖት ግን እንዺህ አለቻት! ጥሩ ባል አልሽ! ወይ ባል፣ መጥፎውም አልተገኘም! አለችና አሰፈገገችን። ትዕግሥት ደግሞ በተራዋ "ጥሩ ባል እንዴት ነው የሚገኘው ነው ወይስ ጥሩ ባል እንዴት ነው የሚታወቀው ነው ጥያቄሽ?" አለቻት። ውበት ጥያቄዬን ላስተካክል አለችና፣ ጥያቄዋን ብቻ ሳይሆን ወንበርዋንም አሰተካክላ እንዲህ አለች፤ "ጥሩ ባል የሚገኘውም ደግሞም የሚታወቀውስ እንዴት ነው?" ቀጠል አድርጋ "እኔ ሥራ ከያዝኩኝ ጊዜ ጀምሮ ለማግባት ዝግጁ ነኝ" አለችና በረጅም ተነፈሰች፣ ግራ መጋባት የሞላበት በሚመስል አነጋገር። ውበት ጌታን የምትወድ ቆንጅዬ ልጅ ናት። ዕዴሜዋ ሃያዎቹ መካከል ላይ ነው። የዕድሜ ማለፍ ፍርሃት እንዲያስቸግራት ገና ነች ብዬ አሰብኩ። ውበት የመጀመሪያ ድግሪዋን ሠርታ ሁለተኛውን ልቀጥል አልቀጥል እያለች ከራሷ ጋር በመሟገት ላይ ያለች ወጣት ነች። ተምሮ ሥራ መያዝ ነው እንዴ ባል ለማግባት የሚያዘጋጀው? ብዬ መንደርደሪያ ጥያቄዬን አነሳሁና ወደ ተጋጋለው ውይይታችን ገባን። ታዲያ ከእነዚህ ወጣቶች ጋር ስንወያይ የደረስንባቸውን ዋና ዋና ሃሣቦች እንደ ውበት ዓይነት ጥያቄ ላላቸው ሊረዱ ይችላል ብዬ አሰብኩና በጽሁፍ ላቀርበው ወሰንኩኝ። 

 

ማንኛውም ሰው ዕዴሜው በደረሰ ጊዜ ቤተሰብ ለመመስረት ማሰቡ አይቀሬ ነው። ወዳጆች፣ አብሮ አደጎች እንዲሁም ሌላው ሁሉ በሚያገባበት ጊዜ ልብ ይነሳሳል፤ እንደውም ምነው አንቺስ ሠርግ የምታበይንም? መቼ ነው? የሚል ደግሞ የባሰውን ይቀሰቅሳል። እነዚህ ልባችንን የሚያነሳሱት ነገሮች ደግሞ ከማሰብ አልፎ ፍለጋ ያስጀምሩናል። ይሄ ይሆን የእኔ ባል? በሚል ውስጣችንን ከስሜታችን ጋር ያታግላል። ይሁን እንጂ ምንም ሰው ሁሉ የሚሔደው መንገድ ተመሳሳይ ቢሆንም እግዚአብሔርን ለምትፈራ ሴት ግን አካሄድዋ ሊለይ ይገባል እላለሁ። እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ የመጣንበት መንገድ አንድ ነው እሱም፣ ራሳችንን አይተን፣ ሃጢያተኛነታችንን አውቀንና ተፀፅተን ለሃጢያት መድሀኒት የሆነው እርሱ ክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ እንደሆነ አምነን ለሃጢያታችን ሥርየት አግኝተን ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወታችን ጌታ አደረግነው። እንደዚሁ ሁለ ከመዳናችን ቀጥሎ ራሳችንን ልናይበት የሚገባን ጉዳይ ትዳር ወይም ጋብቻን ለማሰብ በተዘጋጀንበት ጊዜ ነው። 

 

እንግዲህ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ወጣት ሴቶችም ትዳር ለመያዝ ሲያስቡ ትምሕርት ተምሮ ሥራ መያዝ አስፈላጊ ቢሆንም፣ ዋና ሊሆን የሚገባው ግን ራስን ከእግዚአብሔር ዕይታ አንፃር ማየት እና እንደ እግዚአብሔር ቃል ማዘጋጀት ደግሞም ማስታጠቅ ቀዳሚ ሊሆን ይገባዋል ብዬ አምናለሁ። 

 

1. የሕይወትሽ ዋና ማነው? 

“አንቺ በሴቶች ዘንድ የተዋብሽ ሆይ፣ ከሌላ ወዳጅ ይልቅ ውድሽ ማነው?” መሃ. መሃልይ 5፡9 

 

ተወልደሽ ጡት እየጠባሽ አድገሽ፣ ከዚያም በአራት እግርሽ ድኸሽ፣ ቆመሽ ተራምደሽ፣ አፍሽ ተንተባትቦ አባባ፣ እማማ እያልሽ፣ ቀጥሎም ትምሕርት ቤት ሄደሽ ተምረሽ ከክፍል ወደ ክፍል እያለፍሽ፣ ብለሽም ሥራ ይዘሽ እዚህ እስከ ደረስሽበት ጊዜ ድረስ በሕይወትሽ ብዙ የጠቀሙሽ ሊኖሩ እንደሚችሉ ግልፅ ነው። ማለትም የሚመሩሽ ነገሽን ሊያሳዩሽ የሚችሉ፣ ወላጆች ቢሆኑ፣ ወዳጆች ቢሆኑ፣ አስተማሪዎች ቢሆኑ…ወዘተ በሕይወትሽ ውስጥ ያለፉ ብዙዎች ነበሩ። የእኔ ጥያቄ ግን ከእነዚህ ሁሉ በላይ አንቺ ላይ ባለቤት የሆነው፣ ሃብቱ ያደርገሽ ማነው? ስለ አንቺ የሚያገባው፣ በሕይወትሽ ጥያቄ ቢኖርሽ በመጀመሪያ የሆነው፣ የምታማክሪው፣ የአንቺ ሚስጥረኛ እና ፍቅረኛ ማነው? ነው። 

 

ጌታ ኢየሱስ የአንድ ሴት ነገር ግድ ብሎት በሰማሪያ ማለፍ እንደነበረበት ታሪኩን እናስታውሳለን። (ታሪኩን በዮሐ. 4 ይገኛል) ከዚህች ሰማሪያዊት ሴት ጋር ውይይታቸው ጌታ ኢየሱስ ውሃ አጠችኝ! ይላታል፣ እርሷ ደግሞ እንዴት ውሃ አንተ ከእኔ ትለምናለህ? የሚል ነበር። በውይይታቸው መሐከል አንዴ ጥያቄ ጠየቃት 

 

ከውይይታቸው ጋር የማይገናኝ ነገር፣ (ዮሐ. 4፡16) ሂጂና ባልሽን ጠርተሽ ወዲህ ነይ አላት። ባል የለኝም አለችው፣ እርሱም ባል የለኝም ማለትሽ መልካም ተናገርሽ፣ አምስት ባሎች ነበሩሽ፣ አሁን ከአንቺ ጋር ያለው ባልሽ አይደለም በዚህስ እውነት ተናገርሽ አላት። 

 

ጌታ ኢየሱስ የተመለከተው የሕይወቷን ክፍተት ነው። ማንም እየገባ የሚወጣበት፣ አምስት ወንዶች ሲፈልጋቸው ገብተው ሲፈልጋቸው ወጥተዋል። የሚመራት የሌላት፣ የልቧን በር ለመቆለፍ አቅም ያጣች ሴት ነበረች። ጉልበቷን ብዙዎች ያደከሟት፣ አንዱ ከአንዱ ይሻላል እያለች በሙከራ ሕይወት የኖረች ሴት ነበረች። ማንነቷን ያየ የራራላት ጌታ በሰማሪያ ለማለፍ ግድ አለው የእርሱ ሆነች፣ ጌታዋም ሆነላት እንደውም የልቤን ያወቀልኝን እወቁት እያለች ወደ እርሱ ሰዎችን የምትሰበስብ ሆነች። 

 

አንቺስ! ልብሽ ላይ የተቀመጠው ዋና ፍቅረኛሽ ማነው? ልብሽን የያዘውስ ማነው? ለዚህ ጥያቄ መልስ ልታገኝለት ይገባል። 

 

2. የሕይወትሽ ዓላማ ምንድን ነው? 

ስልጣኔ እያደገ በመጣበት ዘመን ስለ ዓላማ ማውራት የተለመደ ሆኗል። ማንኛውም ሰው የሚኖረው፣ የሚማረው፣ የሚሰራው….ወዘተ በዓላማ ይመስላል። ዓላማው ግን የአንዱ ከአንዱ የተራራቀ ሊሆን ይችላል። እኔ ግን እያነሳሁት ያለው ዓላማ እግዚአብሔር አንቺን የፈጠረበት ዓላማ ምንድን ነው? ለምን እግዚአብሔር መኖርሽን ፈለገው? የሚል ነው። ይህንን ጥያቄ ራስሽን አልጠየቅሽ እንደሆነ ዛሬ ራስሽን ጠይቂ። 

 

ይህንን የእግዚአብሔርን በአንቺ ላይ ያለውን ዓላማ ማወቅ፣ ነገ የምታገቢውን ሰው ዓላማው ከሕይወትሽ ዓላማ ጋር አብሮ ሊገመድ ይችል እንደሆነ የምታውቂው አንቺ ዛሬ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሲኖርሽ ነው። ይህንን ዓላማ መረዳት ባል አግብቶ፣ ልጅ ወልዶ አንቱ ከመባል ያለፈ ጉዳይ ነው። ይህንን ፍጥረት ሁሉ በእግዚአብሔር የመባዛት ሥርዓት ይወልዳል ይዋለዳል። ይህ የምንጋገርበት ዓላማ ግን እግዚአብሔር ያየልሽ ምንድን ነው? ያየልሽን አይተሻል ወይ? ነው። መልስ በሕይወትሽ ሲኖርሽ፣ አመለካከትሽ እና የሕይወትሽ አካሄድ ይለወጣል፣ ነገን ስለ ራስሽ የምታይበት የተለየ ይሆናል። ስለምታገቢው ባል ስታስቢ የምታስቢው ከዚህ ከእግዚአብሔር ዓላማ ጋር ለመሄድ እንችላለን ወይ? ይሆናል ጥያቄሽ! የቀድሞ መስፍርቶችሽ ይለወጣሉ። ይህ ዓላማ ሙሉ ሕይወትሽን ይይዘዋል። የምትኖሪለት፣ የምትኖሪበት እንዲሁም የምትሞችለት ይሆናል። ምንም ዓይነት ዋጋ ለመክፈል፣ ሕይወትን ለመስጠት፣ መብትን ለመተው ሁሉ ውስጥሽ ይቆርጣል። ከተወሰነልሽ የእግዚአብሔር ነገር መጉደልን፣ አመቻምቾ መኖርን እየጠላሽው መኖር ትጀምሪያለሽ በዚህ ጊዜ ይሄ አካሄዴሽ ምናልባትም ከሚቀርቡሽ ሊያራርቅሸ ይችል ይሆናል። ስለሆነም ለተረዳሽበት እውነት መኖር እንዳለብሽ የእግዚአብሔርን ሐሳብ በማክበርና ፍቃዱን በመፈለግ በተሰጠ ሕይወት ለመኖር አቅም ታገኛለሽ። 

 

3. በሕይወትሽ ውስጥ እሴት (value) የምትሰችው ምንዴን ነው? 

ዘመናዊነት ባለንበት ዘመን ብዙ የእሴት ልኮቻችን ደረጃቸውን እንዳይጠብቁ አድርጎብናል። አንዲት እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት በውስጧ እሴት የምትሰጣቸው ነገሮች ልታጤንና ልታተኩርባቸው ያስፈልጋል። እነዚህ እሴት የምትሰጥባቸው ነገሮች በየዕለቱ ከምትራመደው መንገድ ጋር ተቆራኝቶ የሚሄድ ነገር ነው። የሕይወት ውሣኔዎቿ ሁሉ እርሷ ውስጥ ያለውን እሴት ይለካል። 

 

3.1. ለመንፈሣዊ ነገር እሴትሽ ምንድን ነው? 

በየዕለቱ ከቤትሽ ወጥተሽ ሥራ ሰርተሽ እስከምትመለሺ ድረስ ውሎሽ እያንዳንዱዋን ሰዓት የአመለካከትሽን እሴት ወይም ቫልዩ ይለካል። ሁኔታዎችን የምታያቸው እነደወዳጆችሽ ነው? ወይስ እንደ እግዚአብሔር ቃል? የእግዚአብሔር ቃል እሴት ወይም ቫልዩ የሚያደርገውን ታደርጊያለሽ? ከማያምን ሰው ጋር ለመኖር ክፍተት በሕይወትሽ አለ ወይ? ነገ ሊለወጥ ይችላል የሚል ልብ አለሽ ወይ? እነዚህን የመሳሰለ ጥያቄዎችን ራስሽን ስትጠይቂ ለመንፈሳዊ ነገር ያለሽን እሴት ወይም ቫልዩ ደረጃውን ለማወቅ ወይም ያለሽበትን ቦታ ለመፈተሽ ይረዳሻል። 

 

3.2. በገንዘብ እና ለባለ ገንዘቦች 

ጌታ ኢየሱስ ሰው ለሁለት ጌታ መገዛት አይችልም። ገንዘብ ሰው ልቡን ከፈቀደለት ጌታው ነው ማለቱ ነው። ለባለገንዘቦች ያለሽ አመለካከት እንዴት ነው? አንድ ጊዜ ያጋጠመኝ ነገር ትዝ አለኝ፣ አንዴ ትልቅ ሆቴል ውስጥ ሠርግ ተጠርተን በልተን ጠጥተን ስንወጣ አንድ ዘመዴን አግኝቼ ሰላምታ እየተለዋወጥን እያለን፣ ሌላ የማውቃት እህት በከተማው ውስጥ እጅግ ሐብታም የሆነች ሴት አብራት ወደ እኛ ስላምታ ሊሰጡን መጡ እኔ ደግሞ ያችን ሐብታሟን ሴት አላውቃትም፤ አብራኝ የነበረችው ዘመዴ አነጋገሯ፣ ስላምታዋ ሁሉ ተለወጠብኝና ምነው አገር ሰላም ነው? ስላት ሳቅ አለችና አይ የአንቺ ነገር አለችና ማን መሆኗን ብታውቂ ኖሮ አለችኝ። ገንዘብ ማንነታቸውን የወሰናቸው ሰዎችስ ጋር መለኪያሽ እስከ የት ድረስ ነው? ልታገቢ የምታስቢውስ ሐብታም ወይስ የእግዚአብሔር ሐብት የሆነ? እነዚህ ስሌቶች ዛሬ ላይ ቆሞ ብል ማሰብ ይጠይቃሉ። 

 

ስለዚህ እንደ ውበት ጥያቄ ላላችሁ ሴት ወጣቶቸ የሚያገቡትን ከማሰብ በፊት እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ መሞከር እንዲሁም ራስንም ቆም ብሎ መመልከት በጣም አሰፈሊጊ ነው በማለት ሃሣቤን እየጠቀልለኩኝ፣ እህቶች ምነው እኛን ብቻ እንዳትሉኝ በሚቀጥለው ፅሁፌ ወደ ወጣት ወንዶች ፊቴን አዞራለሁ ብዬ ቃል እገባለሁ።

 

ጌታ ይባርካችሁ!!! 

Read 11045 times Last modified on Saturday, 12 July 2014 06:42
Zeleka (Kaku) Mersha

ዘለቃ(ቃቁ) በቀለ መርሻ እባላለሁ።  በአሁን ጊዜ አሜሪካን በሜሪላንድ ሲለቨር ስፕሪንግ ከባለቤቴ ጋር እኖራለሁ። በትዳር አርባ አንድ አመት አሳልፍናል። የአራት ልጆች እናት እና የአምስት የልጅ ልጆች አያት ነኝ። ቤተሰብን በማማከር ከሰላሣ አመት በላይ ጌታን አገልግያለሁ አሁንም በትዳር ውድቀታችንም ሆነ መነሳታችንን ለሚቀጥለው ትውልድ በማካፈል ያገቡትንም ሆነ ያላገቡትን ሕይወታችንን እናካፍላለን። በጁን 2013 "ትዳር ሲቃኝ" የተባለ መጽሐፍ ከባለቤቴ ከኮ/ል ክፍሌ ሥዩም ጋር ጽፈናል። የ"ትዳር ሲቃኝ የቤተሰብ አገልግሎት"  በ2014 ዓመት ምሕረት የቲቪ. አገልግሎትም ጀምረናል። 

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 20 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.