You are here: HomeSermonየተወደደመሥዋዕት

የተወደደመሥዋዕት

Written by  Thursday, 02 April 2015 00:00

በሮሜ ምዕራፍ 121-2 ያለውን ክፍል ስንመለከት የተወደደ መሥዋዕት ማለት ለአእምሮ የሚመች አገልግሎት እንደ ሆነ ተገልጿል፡፡ለአእምሮ የሚመች አገልግሎት የሚለውን ሐሳብ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱሶች “Reasonable service” ይሉታል፡፡ይህ ቃል የሚስማማ፣ የሚመጥን፣ አግባብነት ያለው ወዘተ የሚሉ ሐሳቦችን የያዘ ቃል ነው፡፡ለአእምሮ የሚመች አገልግሎት በተግባር ደረጃ ምን እንደሚመስል ከቁጥር 7 ጀምሮ እስከ 21 ድረስ ያሉትን በዝርዘር ማየት ይቻላል፡፡ እንዳውም ሌላ እስከማያስፈልግ ድረስ በሙላት ተሰድረዋል፡፡ የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል፡-

 

አገልግሎት ቢሆን በአገልግሎታችን እንትጋ፤ የሚያስተምርም ቢሆን በማስተማሩ ይትጋ፤ የሚመክርም ቢሆን በመምከሩ ይትጋ፤ የሚሰጥ በልግስና ይስጥ፤ የሚገዛ በትጋት ይግዛ፤ የሚምር በደስታ ይማር። ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን። ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ፤ በወንድማማች መዋደድ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ፤ ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ፤ በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ፤ ለጌታ ተገዙ፤ በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ…..”

 

እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ተግባራት በአእምሮ ሲታዩ እጅግ ከባድ ናቸው፡፡በተለይ በዚህ ዘመን ቀላል የተባሉት ነገሮችን እንኳ ማድረግ እያቃተንና እየተንገዳገድን እንገኛለን፡፡እነዚህን ዝርዝር ተግባራት በጥልቀት ስንመረምራቸው የተወደደ መሥዋዕት መሆን በራሳችን የሚቻል ነገር እንዳይደለ በግልጽ ያሳዩናል፡፡ በርግጥም የእግዚአብሔር ጸጋ በኃይል እንደሚያስፈልገን ነው የሚጠቁሙን፡፡አዘውትሮ ይህንን ዝርዝር(checklist) እየቃኙ ራስን መፈተሹ አግባብነት ያለው ይመስለኛል፡፡እስቲ አንዱን ከነዚህ ውስጥ ልሳብና ልጠይቃችሁ፡- ምላሽን ሳይንተራሱ ወይም ሳይጠብቁ በልግስና መስጠት በሥጋ ይቻላል እንዴ ? በፍጹም፡፡ ለዚህ ነው አቅም አግኝተን የተግባር ሰዎች እንድንሆን፣በብዙ ጩኸት ወደ ጌታችን መቅረብ የሚያስፈልገን!

 

የተወደደ መስዋዕት ሆኖ ራስን ስለመስጠት ሳስብ ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም(ዮሐንስ 155) የሚለው የኢየሱስ ቃል ነው ወደ አእምሮዬ የሚመጣው፡፡ አዎ! ያለ እሱ ረድኤት በፍጹም ምንም ነገር ማድረግ እንደማንችል የታመነ ነው፡፡ ጌታችን ሐዋርያው ጳውሎስን ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኃይሌ በድካምህ ይፈጸማል (2 ቆሮንቶስ 129) ሲለው በአንድ በኩል ያለ እኔ ምንም ማድረግ ስለማትችል፣ ከምሠራው ሥራ ላይ እጅህን አንሣ መባሉ ይመስለኛል፡፡ እርግጥ ነው፤ ደካማ ሰው ምንስ ሊያደርግ ይችላል? ከዚህም ብርሃንና መረዳት የተነሣ ይመስለኛል በተለያዩ መከራዎች ውስጥ ሲያልፍ እጅግ ደስ ይለው እንደ ነበረ የተናገረው (2 ቆሮንቶስ 1210) ፡፡

 

የተወደደ መሥዋዕት መሆን በእያንዳንዱ የሕይወታችን ምልልስ በጎና ደስ የሚያሰኘው የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ በሚገባ ማወቅን ይፈልጋል፡፡ከዚያም ባወቁት ነገር ላይ አቋም ይዞ መራመድን ግድ ይላል፡፡ይህ ደግሞ በሮሜ 122 እንደተገለጸው የልብ መታደስን የሚፈልግ ጉዳይ እንደሆነ ተጽፏል፡፡ ታዲያ የልብ መታደስ እንዴት ይመጣል የሚለው መጠየቅ ያለበት ጥያቄ ነው? ለእኔ እንደሚገባኝ በማያቋርጥና እየጠለቀ በሚሄድ ጸሎትና ከቃሉ ጋር በሚኖረን የጠበቀ ሕብረትና ትጋት የሚመጣ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ለዚህ ደግሞ በሚገባ መሰጠት እንደሚያስፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ እዚህጋ ነው ዋጋ ለመክፈል መዘጋጀት ያለብን፡፡እዚህጋ ነው መጨከን ያለብን፡፡ያኔ ውስጣችን እየተለወጠና መንፈሳችን እየጠነከረ፣ቀድሞ አቅም ባጣንባቸው ነገሮች አሸናፊና የበላይ ሆነን ለአእምሮ የሚመች አገልግሎት ከውስጣችን ያለ ትግል ይወጣል፡፡

 

አዎ! እያንዳንዱ የክርስትና ርምጃችን በመታዘዝ የተወደደ መስዋዕት መሆንን ይጠይቀናል፡፡እንዳውም ሕይወቱ በራሱ ወደ እኛ የሚያመጣቸው ምርጫዎች ይኖራሉ፡፡ታዲያ ከነዚያ አሻሚ ምርጫዎች መካከል ከእግዚኢብሔር ቃልና መንፈስ ጋር የሚሄደውን ለይተን፣ከጌታ ጋር ለመስማማት(በሥጋዊ ዓይን አነስተኛ ዋጋ ቢኖረውም) መስማማት ይኖርብናል፡፡ይህንን ነው መጽሐፍ ቅዱስ የተወደደ መስዋዕት የሚለው፡፡ታዲያ ራሳችንን በትሕትና ዝቅ አድርገን፣ከጌታ ጋር እየተስማማን፣ቢያመንም ጣሉ የተባልነውን እየጣልን ስንሄድ፣ጌታችን ኢየሱስ በሕይወታችን እየከበረና ለብዙዎች ከሩቅ የምንነበብ መልእክት እንሆናለን፡፡በተጨማሪም እሺ በማለትና በመስማማት ቃሉ እንደሚለን ወስነን ስንራመድ፣እግዚአብሔር በእኛ ደስ ይሰኛልና፣በበጎ ሥራዎች ብዙ ፍሬ የምናፈራ የክብር ዕቃዎቹ እንሆናለን፡፡

እግዚአብሔር ይርዳን!

Read 7156 times Last modified on Thursday, 02 April 2015 06:40
Bekele Berhanu (MD)

ዶ/ር በቀለ ብርሃኑ በ1990 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሜዲካል ፋኩልቲ በኤም.ዲ ተመርቀዋል፡፡በተጨማሪም ቤልጂየም ውስጥ በሚገኝ አንድ ዩኒቨርሲቲ ለዐሥር ወራት የስትራቴጂክ ማኔጅመንት ኦፍ ሄልዝ ሰርቪስስ (strategic management of health services) ሥልጠና ተከታትለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት አሜሪካ ጌትስበርግ በመኖሪያቸው አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል በሳምንት ሦስት ቀን ይሠራሉ፡፡ጌታን እያገለገሉ ከባለቤታቸው ከወይዘሮ አባይና ከሦስት ልጆቻቸው ጋር በአሜሪካን አገር በመኖር ላይ ይገኛሉ፡፡በ2014 አመተ ምሕረት የራሳቸውን ግለ-ታሪክ ጽፈዋል፡፡፡፡ርእሱም ከጨለማ ወደ ሚደነቅ ብርሃን የሚል ሲሆን በኢትዮጵያና በእዚህ በአገረ አሜሪካ በተለያዩ ቦታዎች እየተሸጠ ይገኛል፡፡እንዲሁም በዚህ በ2015 ዓ.ም ገጣሚው በሚል ርእስ የግጥም መድብል ለሕዝብ ንባብ አበርክተዋል፡፡በተጨማሪም በተለያዩ ድረ-ገጾችና ሶሻል ሜድያዎች የተለያዩ መጣጥፎችንና ግጥሞች በማበርከት ላይ ይገኛሉ፡፡

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Latest from Bekele Berhanu (MD)

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 235 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.