You are here: HomeSermonትጸልዩ ዘንድ በመጠን ኑሩ

ትጸልዩ ዘንድ በመጠን ኑሩ

Written by  Wednesday, 25 March 2015 00:00

የእግዚአብሔር ኃይል ድንቅ ነው፡፡ ይህንን ኃይል የምንስበው ደግሞ ከቃሉ ጋር ባለን ቁርኝትና ጸሎት መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ነገር ግን እውነተኛ እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝበት ጸሎት መጸለይ እንደ ቀላል መታየት የለበትም፡፡

 

አንደኛው ተግዳሮት የጨለማው ጥላ በጸሎት ላይ ያለ የሌለ ኃይሉን ስለሚያሳርፍ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በተለይ በዚህ በምዕራቡ ዓለም ካለው የሥራ ጫናና ባተሌነት የተነሣ፣ ጉልበትን ለጸሎት ማጠፍ እጅግ ከባድ ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ አንዳንዴ የጭለማው ዓለም ተጽዕኖ በሕይወታችን ላይ በግልጽ ይታያል፡፡

 

ከሚታወቁት ተጽዕኖዎች አንዱ ነፍሳችንን ማዋከቡና መረጋጋትና ሰላም እንዳይኖረን ማድረጉ ነው፡፡ ታዲያ ከዚህ ወከባ ለመዳን የተገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ጨክኖ በሱ ፊት መሆንን ግድ ይለናል፡፡ ጌታ በምሕረቱ የእረፍት ጊዜዎችን ሲያመቻችልን ደግሞ፣ ሳይሰስቱ ለጸሎት መጠቀሙ አስተዋይነት እላለሁ፡፡

 

ሰይጣን ምንጩን በማናውቀው ምክንያት በኀዘንና በድብርት ሊመታን ይችላል፡፡ እርካታ የለሽና ቅብጥብጥ ሊያደርገንም ይችላል፡፡፡ ከአፋችንም የምስጋና ቋንቋ በማራቅ ነፍሳችን ከማትወጣበት ወኅኒ ሊያኖራት ይችላል፡፡ ለዚህ ነው በተለያዩ ነገሮች ሊውጠን ያሰፈሰፈ ባላጋራ በየደጃችን እንደሚገኝ መገንዘቡ አስተዋይነት የሚሆነው፡፡ ለዚህም ነው “በመጠን ኑሩ ንቁ” (1 ጴጥሮስ 5) የተባልነው፡፡ “አንተ የምትተኛ ንቃ፣ ክርስቶስም ያበራልሃል” (ኤፌሶን 5፡14) ተብለንም ተመክረናል፡፡

 

ለመጸለይ ስናስብ የማይመጣ የአዚም ዓይነት የለም፡፡ ስልኩ ይንጫጫል፣ሰውነታችንን እንቅልፍ እንቅልፍ ይለዋል፣ ጆሮአችን ወሬ ያምረዋል፣ ሌሎች የሚሠሩ ነገሮች ትዝ ይሉናል፤ ሌላም ሌላም፡፡ እኒህን ተግዳሮቶች አሽቀንጥረን ነው ለጸሎት በጌታ ፊት የምንወድቀው፡፡ ቢሆንም ተግዳሮቱ ጸሎት ጀምረንም አያባራም፤ እየጠነከረ ይቀጥላል፡፡ እንዳውም ከምንጸልይበት ሳያስነሳን አያርፍም፡፡ ስለዚህ አንዳንዴ በኃይል በእምነት እየተቃወሙ የጠላትን ሥራ ማፍረስ ጥሩ ነው ብዬ እመክራለሁ፤ በተደጋጋሚ ጠቅሞኝ አይቻለሁና፡፡

 

ይህንን ጽሑፍ ከማዘጋጀቴ በፊት፣ ባልተሳኩልኝና ባልሆኑልኝ ነገሮች ኀዘንና ድብርት ተጫጭኖኝ ከአልጋዬ ላይ መነሣት አቅቶኝ ነበር፡፡ በዛ ከባድ መንፈስ ውስጥ እያለሁ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ አንድ ቃል ወደ መንፈሴ አመጣና አነበብኩት፡፡ ደስ የሚለው ነገር፣ የጊዜው መልእክት ነበር፡፡ እንዲህ ይላል፡- “የሚቀጠቅጥ በአንተ ላይ ወጥቶአል፤

 

-ምሽግን ጠብቅ፣

-መንገድንም ሰልል፤

-ወገብህን አጽና፣

-ኃይልህንም እጅግ አበርታ”! (ናሆም 2፡1፤ አፅንዖት የእኔ)

 

አዎ! እጅግ ገራሚ የሆነ የሰዓቱ የመንፈስ ቅዱስ መልእክት ነበር፡፡ ለመጣልኝ መልእክትም ጌታን አመስግኜ፣ በመሀል በመሀል በኃይል በእምነት እየተቃወምኩኝ ቢያንስ ለሁለት ሰዓት ጸለይኩ፡፡ ከዚያም የሆነ የአዚም ጉም ከላዬ ላይ ሲነሣ ታወቀኝ፡፡ መለቀቅና መፈታት ተሰማኝ፡፡ የምስጋና ዝማሬም ካፌ መውጣት ጀመረና የመንፈስ ቅዱስ ኃይል እጅግ አስደነቀኝ፡፡ ከዚያም ተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ያለ አይጠፋም ብዬ ይህችን አጭር መልእክት ጫጭሬ አስተላልፍኩ፡፡

 

ዋናው መልእክቴም ይሄ ነው፡-ቃሉ “እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ” (ዕብራውያን 4፡16) ይላልና፣ በነፍሳችን መታገሉን ትተን፣ የተትረፈረፈ እረፍትና ሰላምን በሚሰጠው አምላክ ፊት እራሳችንን ሳናቅማማ እንጣል!!

Read 8016 times
Bekele Berhanu (MD)

ዶ/ር በቀለ ብርሃኑ በ1990 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሜዲካል ፋኩልቲ በኤም.ዲ ተመርቀዋል፡፡በተጨማሪም ቤልጂየም ውስጥ በሚገኝ አንድ ዩኒቨርሲቲ ለዐሥር ወራት የስትራቴጂክ ማኔጅመንት ኦፍ ሄልዝ ሰርቪስስ (strategic management of health services) ሥልጠና ተከታትለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት አሜሪካ ጌትስበርግ በመኖሪያቸው አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል በሳምንት ሦስት ቀን ይሠራሉ፡፡ጌታን እያገለገሉ ከባለቤታቸው ከወይዘሮ አባይና ከሦስት ልጆቻቸው ጋር በአሜሪካን አገር በመኖር ላይ ይገኛሉ፡፡በ2014 አመተ ምሕረት የራሳቸውን ግለ-ታሪክ ጽፈዋል፡፡፡፡ርእሱም ከጨለማ ወደ ሚደነቅ ብርሃን የሚል ሲሆን በኢትዮጵያና በእዚህ በአገረ አሜሪካ በተለያዩ ቦታዎች እየተሸጠ ይገኛል፡፡እንዲሁም በዚህ በ2015 ዓ.ም ገጣሚው በሚል ርእስ የግጥም መድብል ለሕዝብ ንባብ አበርክተዋል፡፡በተጨማሪም በተለያዩ ድረ-ገጾችና ሶሻል ሜድያዎች የተለያዩ መጣጥፎችንና ግጥሞች በማበርከት ላይ ይገኛሉ፡፡

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Latest from Bekele Berhanu (MD)

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 145 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.