You are here: HomeOpinionsለቤተክርስትያን ፈላጊዎች!

ለቤተክርስትያን ፈላጊዎች!

Written by  Friday, 15 July 2016 10:51

“እርሱም ከመቅደስ ሲወጣ ከደቀማዛሙርቱ አንዱ መምህር ሆይ፥ እንዴት ያሉ ድንጋይዎችና እንዴት ያሉ ሕንጻዎች እንደሆኑ እይ አለው። ኢየሱስም መልሶ እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያለህን? ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አለው” (ማር. 13:1-2)

 

የክርስቶስ ደቀመዛሙርት የሚፈርሰውን ከማይፈርሰው፣ የሚጠፋውን ከማይጠፋው፣ ጊዜአዊውን ከዘላለማዊው፣ ዓለማዊውን ከመንፈሳዊው መለየት ሲሳናቸው በእጃቸው ስራ ሰዎችንም ሆነ እግዚአብሔርን ማስደመም ይፈልጋሉ። ይህ ግን ሥጋዊነታቸውን ከማስረገጡ ውጭ ፋይዳ አይኖረውም። ኢየሱስ ወደመቅደስ ሲሄድ ወደመቅደሱ የሚተመውን ሕይወት የሌለውንና በሕግ የተጠፈረውን ሕዝብ አስቦና ፈልጎ እንጂ የእርሱ የራሱ በሥጋ መከሰትና ሕያውነት መቅደሱን ያንኑ ጊዜ እንኳ አስረጅቶት ነበር (ዮሐ. 2:17-25)፤ መቅደሱም በእርግጥ በመጨረሻ እስከዛሬ ድረስ እንኳ ላይነሳ ፈርሶ ቀረ።

 

በጥንት ዘመን እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ውስጥ ድንጋይ ለቤት፣ ለሕንጻ ግንባታ፣ ለዋሻ፣ ለመቃብር ሥፍራ፣ ለምንጮች መዝጊያ፣ለተለያዪ ዓይነት የጦር መሣሪያነት፣ ታሪካዊ ወቅቶችንና ሁኔታን ለማስታወሻነት፣ እየተቀረጸም ለጣዖት አምልኮና የመሳሰሉትን ሁሉ ለማድረግ በስፋት ጥቅም ላይ ይውል ነበር። ነገር ግን የድንጋይ ምሳሌነቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በአብዛኛው ጥንካሬን፣ጽኑነትን (ዘፍ. 49:24፣ 2ኛ ሳሙ. 23:3፣ ኢሳ. 30:29) እንዲሁም በአንጻሩ የሰውን ልብ ድንዳኔና ሸካራነት (1ኛ ሳሙ. 25:37፣ ሕዝ. 11:19፣ 36:26) ለማመልከት ነው። ቤተክርስትያን ሕያው ድንጋይ በሆነው በክርስቶስ ኢየሱስ የተመሰረተችውን ያህል (1ኛ ቆሮ. 3:11) እንዲሁም የማዕዘን ድንጋይ ወደሆነላት ወደእርሱም በገሰገሰች መጠን ጸንታ ትቆማለች (ኢሳ. 28:16፣ 1ኛ ጴጥ. 2:4-7)፤ ጥንካሬዋ፥ ጽናቷ እርሱ ነውና። ሆኖም መንፈሳዊነትን ባቀለሉ ወይም በጣሉ፣ በድንጋይ ልብ ድንዳኔና ሸካራነት በሚመላለሱ ምድራዊያን ከእርሱ ፈቀቅ ብላ በራሷ “ልጆች” ምክንያት ውድቀቷ ዛሬም የሚታይ ነው። እግዚአብሔር ከእርሻው ድንጋዮችን ለቅሞ ያውጣ (ኢሳ. 5:1-2)! የወይን ተክሎቹም በየሥፍራው ከነጣቂውና ከአውሬው በእውነት ተቀጥረውና ተከልለው ይለምልሙ፣ ያብቡ፣ ያፍሩ።

 

ሕንጻዊ ቤተክርስትያን?

 

በዓለም ከተሞች መልክና እንቅስቃሴ ተማርኮ ቤተክርስትያንን ያለሕንጻ ማሰብ መቸገርና በሰው መዋቅር ለማቆም መድከም ጣዖቶቻቸውን እንደማምለክ ነው። ቅብዝብዝ ዓይኖቻችንና መመኘት የለመደው ልባችን በዓለማዊ ሚዛን ከዓለም የተዋሰውን አምጥቶ የእግዚአብሔርን ቤት በሰው እጅ ለመገንባት ይዋትታል። የአክሱም ሐውልትና የላሊበላ ጥርብ ድንጋይ አብያተ-ክርስትያናት ምድር ተወላጆች የሆንን አብዛኞቻችን አማኞች እስካሁን የተሳካልን አክርሚኞቻችንን[1] ብቻ መቀለስ ቢሆንም ጸሎትና ናፍቆታችን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የዋሁን አማንያን ገንዘብና ስጦታ የምንነዘንዝበት ጉዳይ በየዓለማቱ እንዳየነውና እንደጎመዥነው ዓይነት ሕንጻ ቤተክርስትያንን “ድንጋይ በድንጋይ ላይ” ለመገንባት ነው። 

 

ረጅም ክርስትያናዊ ታሪክ ባላቸው በአውሮፓ የተለያዩ አገራትና ከተሞች ከተገነቡ እጅግ ብዙ መቶ አመታት የሆናቸው በጣም የተዋቡ የሕንጻ አብያተ-ክርስትያናት በአሁኑ ጊዜ ወና የጎብኚዎች መዳረሻ ብቻ ሳይሆኑ ወደምሽት ክበብ ቤት፣ ወደምግብ ቤት፣ የስፖርት ማዘውተሪያነት ስፍራዎችና ወደ መስጊድነት ጭምር እየተለወጡ መሆኑን ሰምተን ይሆን?[2] በሰሜን አሜሪካ ደግሞ ጥቂት የማይባሉ የሕንጻ አብያተ-ክርስትያናት የተለያዩ ከፍተኛ ወጪያቸውን ለመሸፈን በመቸገራቸው ዕዳ ውስጥ መዘፈቃቸውንስ እናውቅ ይሆን? ቆመዋል ግን ፈርሰዋል ምክንያቱም የማይፈርስ ቤት ሰው ሊሰራ አይችልምና። በሰሜን አሜሪካ በዕዳ ከተዘፈቁት የሕንጻ አብያተ-ክርስትያናት ውስጥ የአንዱ “መጋቢ” የሆነ ሰው ስለጉዳዩ ሲጠየቅ “ሕንጻ ቤተክርስትያንን አይሰራም። የምንቀጥልበትን መንገድ እናገኛለን።” ሲል ተናግሯል።[3] “ሕንጻ ቤተክርስትያንን አይሰራም።” – ከእዳ ወደመገለጥ እንበለው ይሆን?! ጌታ ራሱን በሰጠለት በማይፈርሰው፣ በማይጠፋው፣ በዘላለማዊውና በመንፈሳዊው ቤት ኪሳራ ብዙዎች ድንጋይ ልባቸውን ተመትሮና ተለክቶ በሰው እጅ በሚሰራው ሕንጻ ላይ አኑረዋል! ጠርበን ያቆምነውንም ለማጽናት ሰዎችንም እንዳሻን እናዋቅራለን። ዛሬም የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ! የእግዚአብሔር እርሻ እኛው ነን! የእግዚአብሔር ሕንጻ ሌላ ሳይሆን ቅዱሳኑ ናቸው!! (1 ቆሮ. 3:9) የእግዚአብሔር ቤት ሠራተኞችና ጠባቆችም ሥራቸው በመጨረሻ እንዳይቃጠል በሰዎች ላይ ይድከሙ!! (መዝ. 127:1፣ 1ኛ ቆሮ. 3:10-15)

 

ዘማሪ ደረጀ ከበደ በቅርብ ስለዘመናችን ቤተክርስትያን በትክክል ከተቀኘው ዝማሬ ውስጥ የሚከተለው ሀቁን በሚገባ ሳይገልጸው አይቀርም -

 

“... ዛሬ ቤተክርስትያን እያሉ የሚጠሩት

በየመንገዱ ዳር አስጊጠው የሰሩት

አናጢ የዋለበት ከመሰረት ከላይ

በቁመት በስፋት ባሻገር የሚታይ

ለአይን ጥጋብ እንጂ ሕይወት የሌለበት

ያዘነ የራበው ደጅ የሚቆምበት...”

 

ዘማሪት ሐና ተክሌም ደህና አድርጋ እንደሚከተለው ተቀኝታለች -

 

ባመረ ባጌጠ ቤት ውስጥ ተሰይሜአለሁ

በተዋበ ሕዝብ ተከብቢያለሁ

ዙሪያዬን የማየው ሁሉ ለአይን ይስባል

እኔ ግን ታምሜ ውበቴ ጠፍቶኛል

ከቤት ውስጥ እያለሁ እኔ ጎድያለሁ

ለሚያየኝ ለስሙ እኔ እንዳለሁ አለሁ

ቤትህን ሲሞላው እልልታና ሆታ

እኔን የሚያውከኝ የነፍሴ ጭንቀቷ

 

የአንተ ቤት እኔ ነኝ

የእኔ ቤት ሌላ ነው

ቤተ-ሰሪው በዝቶ መላ ‘ሚለኝ ማነው

ቀርበህ ሳለህ ከደጅ ልትመጣ ወዳጄ

እንዴት ይሆን ‘ማይህ እሩቅ ሀገር ሄጄ

 

የአዳራሹ ውበት እኔን ሸፍኖኛል

ግዑዝ ከእኔ በልጦ አልፎ ይኮንነኛል

በጌጥ ይታጀባል ቤቱ ተሰርቶ አልቆ

ልብ ሁሉ በእጁ ነው የእኔን ቦታ ወስዶ...

 

ቀኑ ቀርቧል እያልን ፍጻሜ የዘመን

ከንቱ ቤት ስንሰራ የዘላለሙን ትተን

ተላልፈን እንዳንቀር አቤቱ አደራ

የተጣልን እንዳንሆን የነበርን ስምህን ስንጠራ (3x)

 

 

ነገር ግን ከአውሮፓውያኑና ከሰሜን አሜሪካውያኑ በተቃራኒ መልኩ ጨቋኝ መንግስታት ባሉባቸው ለምሳሌ በቻይና በኢራንና በሰሜን ኮርያ ቤተክርስትያን ተጠብቃ ውስጥ ለውስጥ ደግሞ እያደገችና እየሰፋች በጥቂት ወይንም ያለምንም ሕንጻ በቅዱሳን ንጹህ ፍቅርና እውነተኛ ህብረት በምስጢር ነው።[4] ሕንጻ ለቤተክርስትያን የግድ እንዳልሆነ ምስክሮች ናቸው። የቤተክርስትያን መውደቅ ወይንም መነሳት ዋና ምክንያት ቅዱሳን ራሳቸው እንጂ መንግስታት ወይንም ሌላ ውጭያዊ ሀይልና ምድራዊ ነገሮች አይደሉም።

 

አፍቅሮ በዓላት በቤተክርስትያን!

 

ለቤተክርስትያን የተሰየመው ግዑዙ ሕንጻ ራሱ ግን የአንድ የተንሻፈፈና አዲስ ኪዳናዊ ሳይሆን ሰው ለስሙ እንዳቆመውና ወደሰማይ እንደተንጠራራበቱ የባቢሎናዊ ዓይነት ትምክህትና አስተሳሰብ መገለጫ ውጤት ነው። በአንድ ቋንቋና በአንድ ንግግር እየተጠራሩ ባገኙት ሜዳ ሁሉ እርስ በርሳቸው “ኑ” በመባባል ለአምላካቸው ሳይሆን ለራሳቸው ከተማንና ግንብን የሚገነቡ ሰዎች በፍጥረት ውልደት ማግስት ጀምሮ በመሓላችን አሉ። መሰብሰብንና በራሳቸው ጩኸት ኃይል ለስማቸው ወደላይ መገንባትን እንጂ መበተንን እጅግ ይፈሩታል (ዘፍ. 11:1-9)። ዛሬም - “ኑ ለእኛ ከተማና ራሱ ወደ ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንሥራ፤ በምድር ላይ ሳንበተንም ስማችንን እናስጠራው።” ሲሉ በየአደባባዩ ይሰማሉ። ቤተክርስትያን የተወለደችበትን የአዲስ ኪዳኑን ዘፍጥረት በሐዋ. 2 ስንመለከት ግን ጌታቸው “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” ብሎ የሰጣቸውን የመታጠቅንና የመበተንን ተስፋ ይዘው ራሳቸውን ባዋረዱት ላይ መንፈስ ቅዱስ ወርዶ እንደባቢሎናውያኑ በቁጣ ሳይሆን ለመንግስቱ ዓላማ በብዙ ዓይነት ቋንቋና ልሳኖች እንዳናገራቸው እናያለን። ጌታ ኢየሱስ “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ... የምድር ጨው ናችሁ...” ብሎ ሲለን “ኑ” እየተባባልን “በየቤተ-እምነቶቻችን ቅርጽ” ከተበጁ እንቅቦቻችን በታች ብርሃናችንን እንድናበራና ዓለምን የበለጠ ለጨለማ እንድንተዋት ወይንም መጣፈጥና ማጣፈጥ አቅቶን ድንጋይ ሆነን እንድንቀር ሳይሆን በየማህበረሰቡ መካከልና ከተማ በከተማ የሰማዩ መንግስት ማህበረሰብ ለመሆን እንድንበተን ነው። የክርስትናችንን ዋናው ማዕከል በየአዳራሾች በመከማቸት ዙሪያ አድርገነው ሳለ መበተን - በጨለመበት ሁሉ ለማብራትና ጣዕም በጠፋበት ሁሉ ለማጣፈጥ - ከወዴት ይገኛል? በትላልቅ አዳራሾች መሰባሰብን ዋነኛ እንደማድረግ ቤተክርስትያንን ያከሰራት ሌላ ምን ነገር ይኖር ይሆን? የመቶና የሺህ አመታት ስምና ታሪክ ያካበቱትን ሳይቀር የትኞቹንም ቤተ-እምነቶች ብንጠቅስ ከዚህ የተሻለ የሚገልጻቸው የለም! እግዚአብሔር በሉዓላዊነቱ በሁሉ ስለሚሰራ ሁሉ ልክና የመጨረሻ የአሰራሩ ማሳያ ነው ማለት እንዳልሆነ ለብዙዎቻችን አጠያያቂ አይሆንም። ነገር ግን አሁንም ቤተክርስትያን ለዓመታት ከአዲስ ኪዳኑ መንገድ ስታ የመጣችበትን መንገድ መጠየቅ እንደ ትልቅ ነውር ተደርጎ ይቆጠራል።

 

ለጊዜው ሌሎቹን ብዙ ውድቀቶቻችንን ትተን አንዱንና ምናልባትም ዋነኛውን እናንሳ ቢባል የአፍቅሮ-በዓላት ክፉ አመላችንን መጥቀስ ይገባል። ነውና! በእግዚአብሔር ቤት ቤተኞች የሆንን እየመሰለን በሳምንት አንዴ ሲልም ሁለቴና ሶስቴ ወደ “ቤተ ክስያን” የምንተመው መቶዎችና ሺሆች ሆነን በሙዚቃ አጀብና ቅጥ ባጣ ዝላይና ፍንደቃ በዓል ለማድረግ ነው። አጀበኝነት ወይንም አፍቅሮ-አጀብ - በብዛትና በድምቀት በሰፋፊ አዳራሾች መሰባሰብ[5] የቆየ ዋነኛ መለያ ገጽታችን በመሆኑ አፍቅሮ-በዓላት እያደር ሌላው መገለጫችን ሆነ። ከቶውኑም ምንም ዓይነት ይሁኑ እንበልና በዓላት ቢበዛ በአመት ለጥቂት ቀናት ይሆኑ ይሆናል እንጅ በየሳምንቱ ቀርቶ በየወሩና በየሁለት ወሩ እንኳ ሊሆኑ ይችላሉን? ሆኖም በቤተክርስትያን በአጠቃላይ የሚታየው አፍቅሮ በዓላትና ወላጅ አባቱ አጀበኝነት እውነተኛውን የቅዱሳንን ህብረትና ህይወት አቀጭጮ የሚያስለመልም ከሆነ ሰነባበተ። የየመድረኩም እንቅስቃሴ ያንኑ ያህል አስደሳችና የሚማርክ እንዲሆን ሲባል በየጊዜው የትያትር ቤትን አይነት ገጽታ እየተላበሰ ይገኛል፤ ጥቂት የማይባሉ ሰባኪዎችና አስተማሪዎችም የቃሉ በራዥ-ከላሽ ተዋንያን እየሆኑ ንግግራቸውም ሰማያዊው ቀለም ጭራሹኑ የማይደምቅበት የወየበና ከድግግሞሽ ብዛት የነተበ ምድራዊ ነው። በቤተክርስትያን ለሚታየው መንፈሳዊ መታከትና ዝቅጠት አንዱና ዋነኛው ይኸው ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በየሰንበቱ በተመሳሳይ ወንበሮች ላይ በአካልም በግንኙነትም ፊትና ጀርባ ተቀምጠን ሁላችንም እንደትያትር ቤት ተመልካቾች ተዋንያኑን ወይ እያሞገስን አልያም እያጥላላን ለሁለት ለሶስት ሰዓታት ቁጭ ብድግ ብለን ወደ የገዛ ቤቶቻችን መመለስ እንደዘመዶቻችንና ጎረቤቶቻችን የሳምንቱን ከማድረስ በቀር በእርግጥ ምን ሊሆን ይችላል? እንደ ማንኛውም ተፈጥሮአዊ ኑሮ እውነተኛ መንፈሳዊ ኑሮም የበዓላትንና የአጀብን ጋጋታ አይፈቅድም። በብዙ ቅዱሳን ሕይወት ውስጥ የተዘራው እውነተኛው ዘር ሲጸድቅ ከእሾህ ባልተናነሰ መንገድ እንደ አረም ሆኖ የሚያንቀውና የሚያፍነው የዚህኛው ዓለም አሳብና የባለጥግነት መታለል (ማቴ. 13:22) ከመሆኑ ይልቅ በየቤተክርስትያኑ የተለመዱት በዓላትና አጀቦች ናቸው ልንል እንችላለን። ከላይ በጠቀስነው በሐና ተክሌ ዝማሬ ውስጥ - 

 

ቤትህን ሲሞላው እልልታና ሆታ

 

እኔን የሚያውከኝ የነፍሴ ጭንቀቷ

 

የሚሉት ዓይነት ስንኞች ባፈዘዙንና ባነፈዙን የበዓላትና የአጀቦቻችን ሙቀት መካከል ቅዱሳን በብቸኝነት ቆፈን እየተሳቀቁ እንደሚኖሩ የሚያሳብቁ ናቸው። በብቸኝነት ቆፈን ተቆራምደን እንደሆን መፍትሔው የበዓላትና የአጀብ ጋጋታ ሳይሆን እውነተኛ መንፈሳዊ ቤተሰብን ማግኘት ነው። ከውጪው እሾህ የውስጡ አረም ስንቱን አቀጨጨ፥ ለፍሬ-ቢስነት ዳረገ! ስንቱንስ አኮስምኖ ገደሎ ይሆን?! ከመንገድ ዳርነት፣ ከጭንጫነትና ከእሾሃማ ስፍራዎች ሁሉ ድኖ መልካሙን የእግዚአብሔርን እርሻ የተቀላቀለ ከሥጋዊነት ወጥቶ መንፈሳዊ ሆኖ በመለወጥ በሕይወቱ ሳያፈራ ግን አይቀርም! ስለዚህም ኑሮአችንን በሰማያዊ ብርሃንና ልምላሜ ለመኖርና ዳግም ለተፈጠርንበት ዓላማ ለመታጠቅ (ኤፌ. 2:10፣20-22፤ ዕብ. 10:24-25) “በቂ ትንፋሽ” ከበዓላትና ከአጀብ ውጭ ለቤተክርስትያናዊ ሕይወታችን ያስፈልገናል!

 

“እንግዲህ በመብል ወይም በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለ ሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ። እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና፥ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው።” (ቆላ. 2:16-17)።

 

የቀደሙት የአይሁዳውያን ኃይማኖታዊ ሥርዓትና በዓላት በክርስቶስና በአካሉ ፍጻሜአቸውን አግኘተው ካበቃላቸው የእኛዎቹስ እስከመቼ በእግዚአብሔር ቤት ላይ ጥላቸውን አጥልተው እንዲኖሩ እንፈቅዳለን?

 

ልናዘወትረው የሚገባን የቤተክርስትያን ሕይወት

 

በማይናወጠውና ዘላለማዊ በሆነው በክርስቶስ ፍቅር መሠረት ላይ ተደላድለው (ሮሜ 8:35-39) ቅዱሳን በህብረት ሲኖሩና በዓለም መካከል እንደ አንድ ልዩ ማህበረሰብ ሲመላለሱ ምን መምሰል እንዳለባቸው ጳውሎስ በሮሜ 12፡3-15:14 የሚዘረዝረውና አጥብቆ የሚያሳሰበው አስቀድሞ በመጀመርያዎቹ ሁለት ቁጥሮች (ሮሜ 12:1-2) ውስጥ ሰውነታቸውን ህያውና ቅዱስ መስዋዕት አድርገው ለእግዚአብሔር እንዲያቀርቡና በአምሮአቸው መታደስ እየተለወጡ ዓለምን እንዳይመስሉ ከመከረ በኃላ ነው፡፡ ለእግዚአብሔር ራሳችንን ያቀረብንበት ማንነታችን ‘ግልባጭ’ ህይወታችንንና ኑሮአችንን ለቅዱሳን በማቅረብና በዓለም መካከል አብሪና ጨዋማ ሆኖ በመገኘት መታየት መቻል እንዳለበት ያለመታከት እየዘረዘረ ከሶስት ተኩል ምዕራፎች በላይ ይመክራል፤ ያሳስባል (አንባቢው እነኚህን ምዕራፎች በጥንቃቄ በግልና በሕብረት ቢያጠናቸው ይመከራል!)፡፡ በቤተክርስትያን ቤተኛ የሆነ አማኝ የሚቆምበትን የተቀደሰ መሬትና የተቀደሰ ሕንጻ ሳይሆን የሚፈልገው አስቀድሞ በክርስቶስ የተቀደሰ ማንነቱን በእውነት እንደ ህያው መስዋዕት (ሮሜ 12፡1) ለእግዚአብሔርና ለቅዱሳን ማቅረብን ነው፡፡ የተቀረው ሁሉ ቦታ ቦታውን እያየዘ ይመጣና ሕይወት ትርጉም ያለው መሆን ይጀምራል።   

 

“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- ሰማይ ዙፋኔ ነው፥ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ የምትሰሩልኝ ቤት ምን ዓይነት ነው? የማርፍበትስ ስፍራ ምንድር ነው? ...ነገር ግን ወደዚህ ወደ ትሁት መንፈሱም ወደ ተሰበረ፥ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ፡፡ (ኢሳ. 66፡1-2)

 

እግዚአብሔር በዙፋኑ ላይ እስካለ ድረስ ምድር የእግሩ መረገጫ ናት፡፡ እርሱ ያልረገጠበት የምድር ስፍራ፣ እርሱ የማይገኝበት የምድር ጥግ የትም የለም፡፡ በትሁት ልቦና፣ በተሰበረ መንፈስና ለሕያው ቃሉም በመታዘዝ የሚኖር ማንም ሰው በየትኛውም ስፍራ የእግዚአብሔር ማደሪያና ማረፊያ ሊሆን ይችላል፡፡ በመሆኑም ልናዘወትረው የሚገባን የቤተክርስትያን ህይወት ክርስቶስ ፍጹም የበላይና ማዕከል በሆነበት ሥፍራ ከተወሰኑ ቅዱሳን ጋር ቤተሰባዊ ትስስርን በትጋት በመከተል ኑሮአችንንና ሕይወታችንን እየተከፋፈልን በተወሰነ ቦታና ጊዜ በምንተያይበት መንገድና ሥፍራ ነው፡፡ “ልናዘወትረው” የሚለው ቃል ይሰመርበት! “ክርስቶስ ፍጹም የበላይና ማዕከል በሆነበት ሥፍራ” ስንል የሰዎች፣ የአስተምህሮና የምድራዊ አሰራሮች የበላይነት የሌለበት÷ በተጨማሪም እያንዳንዱ ቅዱሳን ክርስቶስን ሊገልጥበትና በመታዘዝ ሊያከብርበት በሚችልበት ሥፍራ ለማለት ነው፡፡ “ከተወሰኑ ቅዱሳን” ጋር ሲባል ደግሞ የወሰኑን ልክ ለመረዳት ከሁለትና ሶስት (ማቴ. 18፡20) ጀምሮ እስከ አንድ የመካከለኛ ቤተሰብን ቁጥር ማሰብ ለማነጻጸር ይበቃል፡፡ ቤተሰባዊ ትስስርን ለመፍጠር ከሚያስችል በላይ የሆነ ቁጥር መከሰት ሲጀምር በተመሳሳይ የህይወት ሥርዓት በሌላ የተወሰነ ቦታና ጊዜ የተወሰኑት ለብቻ ህብረት እንዲያደርጉና እንዲተያዩ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ሥፍራው ለትኩረትና ለጸሎት የሚመች እስከሆነ ድረስ ከቤት ጀምሮ እስከመስክ የትም ሊሆን ይችላል። ቁምነገሩ በቤተሰባዊ መተሳሰር “ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስ የሆነ ደስታ” የሰፈነበትን የእግዚአብሔር መንግስት (ሮሜ 14:17) በመካከላቸው ማጽናትና ለዙሪያቸው ምስክርነትን መትከል ነው፡፡ በየሥፍራው ያሉ የቅዱሳን ህብረቶች በመንፈስና በህይወት ተሳስረው በበሳል ሽማግሌዎቻቸውና ዋኖቻቸው መካከል በሚደረግ ምክር እየተመሩ እንደአስፈላጊነቱና እንደወቅቱ ሁናቴ ለተከታታይ ሳምንታት ወይንም በዓመት በጣት ለሚቆጠሩ ቀናት ተጠራርተው ጌታን ለማምለክ፣ ሥራውን ለመተረክ እንዲሁም “ቅዱሳን አገልግሎትን ለመስራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ” (ኤፌ 4:13) ከእውነተኛ ነቢያትና አስተማሪዎች አፍ በመማር አንድነታቸውን ለማጽናት በዓል ሊያደርጉ በታላቅ ጉባኤ ቢገናኙ እንዴት ያለ ብርቅና ድንቅ ይሆናል!? አልፎ አልፎ ወይንም ወቅታዊ በሆነ መንገድ መደረግ ያለበትንና ዘወትር መደረግ ያለበትን ግን እንዳናምታታና እንዳንስት እንጠንቀቅ።

 

የቤተክርስትያን ተልዕኮ!

 

ቤተክርስትያን በየመንደሩ ሰርጋና በድምቀት በማትታይበት ልክ በዓለም ሰጥማ እንዳትቀር የሚሰጉ ሰዎች ከሚጠይቋቸው ጥያቄዎች አንዱ “ቤተክርስትያን በዋናነት እኮ ትናንሽ ህብረቶችን ማደራጀትን በተመለከተ ልትሆን አትችልም፤ የቤተክርስትያን ዋና ጥሪ ታላቁ ተልዕኮን መፈጸምና ወንጌልን ማሰራጨት ነው” ሲሉ እንሰማለን፡፡ ነገር ግን “ታላቁ ተልዕኮ” ተብሎ የሚጠቀሰውና በማቴ. 28፡16-20 የምናገኘው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትዕዛዝ በቅድሚያና በዋናነት የተሰጠው ለመጀመሪያዎቹና ለቀደሙት ሐዋርያትና በኋላም ለተተኪዎቻቸው የወንጌል ሠራተኞች ሁሉ ነው፡፡ ሐዋርያትና የወንጌል ሠራተኞች ማለት ግን የክርስቶስ የአካሉ ልዩ ልዩ ብልቶች ማለት እንጂ ሙሉ አካሉ ማለትም ቤተክርስትያን ማለት አይደሉምና የታላቁ ተልዕኮ ትዕዛዝ የተሰጠው እንደ ዋና ዓላማዋ እንድታደርገው ለቤተክርስትያን ነው ልንል አንችልም። ይልቁኑ የወንጌል ሠራተኞች ለቤተክርስትያን የተሰጡ ስጦታዎች ናቸው (ኤፌ. 4፡11-13)፡፡ ጌታ ኢየሱስ በትንሳኤው እነርሱን እንደስጦታዎች የሰጠን እንድናጌጥባቸው ወይንም እንዲሰለጥኑብን ሳይሆን ከሌሎች ቅዱሳን በተለየ ጸጋና ጥሪ ለክርስቶስ አካልና ለወንጌል እንዲደክሙ ነው። በተጨማሪም ለመርከቧ ቤተክርስትያን የወንጌል ሥራ ወጀብና ማዕበል በሞላው ባህር ተሳፋሪዎቿን ይዛ ከዚህኛው ዓለም ወደ ወዲያኛው ለምታደርገው የማይቋረጥ ጉዞ አንድና ወሳኝ አካል እንጂ ዓላማ ሊሆን አይችልም። የወንጌል ተልዕኮ ብቻውን ለቤተክርስትያን ያንሳታልና! በፊተኛው በር የተሳፈሯትን በኋለኛው በር እያጣች ብትሄድ ምኑ ነው የድካሟ ትርፉ? ቤተክርስትያን በማጥመቅ ብቻ ከተጠመቀች “ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” የተባለውን ሥራ ሩብ እንኳ አልፈጸመችም ማለት ሊሆን ነው። የሚታዘዙ ደቀ መዛሙርትን ማፍራት “ዓላማ ይዞ እንደተሰለፈ ሠራዊት” (መኃ. 6:4) የሚያስፈሩትን ለእግዚአብሔር መንግስት ሥራ ማብቃት ነው። እናም ቅዱሳን ሁሉ የወንጌል ምርኮኞች ናቸውና ለወንጌል በወንጌል ሰዎችን ሊማርኩ ይገባል፤ ሁላችንም ግን በእኩል ጥሪና ደረጃ የወንጌል ሠራተኞች አይደለንም (1ኛ ቆሮ. 12፡27-31)። አንዳንዶቻችን በሙያችንና በዕውቀታቸን የተለያዩ አገራት መንግስቶች ሌሎቻችን ደግሞ የግልና የመሳሰሉት ሠራተኞች ነን። መጽሐፍ ቅዱስም ይመክራል፤ የተገባም ነው (1ኛ ተሰ. 4፡12፣ 2ኛ ተሰ. 3፡10-13)። ሁሉ ሰው እንደ ጳውሎስ መጋቢነትን በአደራ ተቀብሎ ያለ ደመወዝ እየደከመ “ወንጌልን ባልሰብክ ወዮልኝ” (1ኛ ቆሮ. 9፡16-18) ማለት ይችላልን? ሊልስ ይጠበቅበታልን? ሁላችን ግን በአንድነት በክርስቶስ ውስጥ ስንገኝና እርሱን እየተማርን በእርሱ ሕይወት ስንበዛ፥ የወንጌል ሠራተኞችም እንደየስጦታቸውና ጥሪያቸው በየመስካቸው ሲሰማሩ ጌታም የሚድኑትን በየጊዜው ይጨምርልናልና በክርስቶስ አካል ሕንጻ ግንባታ ውስጥ መትጋትን አጥብቀን እናዘውትር (ሐዋ. 2፡46-47)። ለማጠቃለልም የቤተክርስትያን ዋና ትኩረቷ ሊሆን የሚገባው ቅዱሳን እንደተሰሎንቄ ሰዎች ‘የእምነታቸው ሥራ፣ የፍቅራቸው ድካም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያላቸው የተስፋቸው ጽናት’ (1ኛ ተሰ. 1:2-3) በዝቶ እንዲትረፈረፍ ማብቃትና በጽኑና ዘላለማዊ ሀብት (1ኛ ቆሮ. 13:10-13፣ 1ኛ ቆሮ. 15:58) እንዲበለጽጉ ማገዝ ነው።

 

በሰው ዘንድ ወደተናቀው፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ወደተመረጠውና ክቡር ወደሆነው ወደዚህ ሕያው ድንጋይ እየቀረባችሁ፣ እናንተ ደግሞ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕት ታቀርቡ ዘንድ፣ ቅዱሳን ካህናት ለመሆን እንደ ሕያዋን ድንጋዮች መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ትሠራላችሁ (1ኛ ጴጥ. 2፡4-5)

 

በመሆኑም የዘመናችን “ሐዋርያት” የየመድረክ ላይ ‘ነብሮች’ ሳይሆኑ ይልቁኑ ቀደም ሲል እንዳልነው ወቅታዊ ምላሽን ለመስጠት አልያም በዓመት ጥቂት ጊዜ ብቻ ካልሆነ በቀር በመጨረሻ በእሳት ለሚገለጥና ለሚፈተን ደመወዝንም ለሚያገኙበት ሥራቸው ሲሉ (1ኛ ቆሮ. 3:11-15) በታላላቅ ጉባኤዎች ራሳቸውን በከንቱ ከማጥመድ ራሳቸውን የሚገቱት ናቸው።  እውነተኛና ዘላቂን መንፈሳዊ ሥራ እንጂ ባዶ ግርግርን ይሸሻሉ። ዋና ትጋታቸው ትናንሽ ህብረቶች በሚታዘዙ ቅዱሳን አማካኝነት “ብዙ ልዩ ልዩ የእግዚአብሔር ጥበብ” (ኤፌ. 3:10) እየፈለቀባቸው ለምድር የእንቆቅልሽ ዓይነቶች ሁሉ ብርሃን ሲፈልቅባቸው  ማየት ነው። ቋሚ የቅዱሳን አኗኗር ባህልም እንደቤተሰብ በተሳሰሩ ህብረቶች ላይ እንዲመሰረት እንዲሁም በየማህበረሰቡና መንደሩ እንዲተከል እልፍ “ጢሞቴዎስና ቲቶ” መሪዎችን ለማፍራት (2ኛ ጢሞ. 2:2) ነፍሳቸው በእነርሱ ዘንድ ሳትከብር ያለመታከት ይደክማሉ። በውኑ ወዴት ናቸው?

 

መንፈሳዊ ቤት ሆኖ ለመሰራት እንደህያዋን ድንጋዮች ወደ ሕያው ድንጋይ! ጸጋው ይብዛልን!!

 

[1] አክርሚኝ - ትልቅ ቤት እስኪሰራ ድረስ የሚቀለስ ትንሽ ጎጆ፣ የችግር እህል፤ እስኪያልፍ ድረስ የሚመገቡት እህል [ባህሩ ዘርጋው ግዛው (1994 ዓ.ም)፣ ዘርጋው የአማርኛ መዝገበ ቃላት]
[2] Underhill, W. (2007, Feb. 12). Good God! Why Europe is turning Churches into Gyms, Pizzerias and Bars. Newsweek, 50.
[3] Banjo, S. (2011, January 25). Churches Find End Is Nigh: The Number of Religious Facilities Unable to Pay Their Mortgage Is Surging. Retrieved from The Wall Street Journal: http://online.wsj.com/article/SB10001424052748704115404576096151214141820.html?mod=WSJ_hp_MIDDLENexttoWhatsNewsSecond
[4] Gospel Fellowships (2013). Principles for the gathering of believers under the headship of Jesus Christ. -:-.
[5] እግዚአብሔር በአንጻራዊ የነጻነት ዘመን እውነተኛ የቤተክርስትያንን ሕይወትና ተልዕኮ እንመርጥ እንደሆን ሊፈትነን ሳይሆን እንደማይቀር ማሰብ አያስፈልገንም ይሆን?

Read 10491 times Last modified on Friday, 15 July 2016 11:08
Henok Minas Brook

ሔኖክ ሚናስ ከሁለት አሥርት አመታት በላይ ለእግዚአብሔር መንግስት በመቅናትና የቤተክርስትያንንም አንድነትንና ፍቅርን በመሻት በተለያየ መልኩ ጽሑፎችን የሚያዘጋጅና ከሁሉ አብልጦ ከቅዱሳን ጋር እንደቤተሰብ መኖርን የሚከታተል፥ በሙያው የፕሮጀክት አመራርና አስተዳደር አማካሪ ሲሆን ባለትዳርና የሁለት ሴት ህጻናት ልጆች አባት ነው።

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 254 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.