You are here: HomeOpinionsየአንድ ትውልድ ሙሾ

የአንድ ትውልድ ሙሾ

Written by  Wednesday, 22 July 2015 12:49
Gash Negussie Gash Negussie Photo credit: Tedi Moges

በዚህ መጣጥፍ ‘ትውልድ’ ማለት በተመሳሳይ የዘመን ክፍል ውስጥ አብሮ የሚኖረው ከሕፃን እስከ ሽማግሌ ያለው የሰብአውያን ማኅበር ነው፡፡ ልማድ እየጎተተን ትውልድ ሲባል ወጣቱ ይመጣብናል እንጂ ቃሉ ሁሉን የሚወክል ነው፤ ይህም ሙሾ ስለ ሁላችን የቀረበ ነው፡፡

 

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ይህችን ትውልድ በምን እመስላታለሁ?” ማለቱ ትልቅ የትውልድ ትንተና ሥራ ከተከታዮቹ እንደ ሚጠበቅ ያመለክታል፡፡ እርሱ የነበረበት ትውልድ በዘፈንም በልቅሶም የማይጨበጥ ሙልጭልጭ ትውልድ ነበረ፡፡ ቁርበት ለብሶ፣ አንበጣ እየበላ የኖረውን ባህታዊ ሰባኪ በሰይፍ ያስገደለ፣ ጨርቅ ለብሶ እንጀራ እየበላ ያስተማረውን ሰው ወዳጅ ሰባኪ በእንጨት ላይ የሰቀለ መናጢ ትውልድ ነበረ፡፡ ሆኖም ምንም የማያግደው ልዑል እግዚአብሔር በዚያው ትውልድ መካከል ለትውልዶች ሁሉ የሚበጅ አስገራሚ ሥራውን ሠራ፡፡

 

ወዳጆቼ፣ የእኛ ትውልድ ምን ይመስላል? እኛ ምን እንመስላለን? ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡ ይህን ትውልድ መልክ ትንተና በአንዲት መጣጥፍ እሠራለሁ ብዬ እኔም አልሞኝ፡፡ ሰውም አላሞኝ፡፡ ነገር ግን ዓይናችንን በጤና የከፈትን  እንደሆነ ፈጥጠው የምናያቸውን ጉልሃን አካሄዶች መናገር ክርስቲያናዊም ሰዋዊም ግዴታችን ይመስለኛል፡፡

 

በዚህ ሰፊ-ጠባብ ዓለም ሁሉ ነገር የተነካካ ቢሆንም እንኳ አቅማችንን የሚመጥን ትግል ለማድረግ እንዲቻል ትኩረታችንን በምናውቀው ሕዝብ ላይና ከዚያም በጠበበ ሁኔታ ኃላፊነቱ ከባድ በሆነው ክርስቲያን ኅብረተሰብ ላይ ማድረግ ግዴታ ነው፡፡

 

የአበሻ ሕዝብ መታመስ ከጀመረ ቆይቷል የቅርቡ በቻ ቢቆጠር ግማሽ ምዕተ ዓመታት ያልፋሉ፡፡ እነዚህ ዓመታት አልፎ አልፎ ብቅ ካሉ የብርሃን ጮራዎች በስተቀር በአብዛኛው የመደናገር፣ የሁካታ፣ የግርግር፣ የጥላቻ፣ የበቀል፣ ድብብቆሽ፣ የተንኮል፣ የዝርፊያ፣ የጭከና፣ የራብ፣ የርዛት፣ የሕመም፣ የሞት፣ ፈጣን የኋሊት ግሥገሣና የቀቢጸ-ተስፋ ዓመታት ነበሩ፡፡

 

ችግሮቻችን በከፊል የተፈጥሮ ሂደት መዛባት፣ የዓለም ኢኮኖሚ ሥርዓት አድሎአዊነትና ቴክኖሎጂያዊ ኋላቀርነት ቢሆኑም ፊታውራሪያቸው የሰው ልጅ የልብ ጥመት ነው፡፡ የመሪም የተመሪም፡፡ የቀብር ጉድጓዳችን ፈጣን ቆፋሪዎች ነን፡፡

 

“እነዚህ ዓመታት ያፈሩት የሰው ዓይነት ምን ይመስላል? የተባለ እንደሆነ ጉራጌዎች “አውከሬ” ብለው የሚጠሩት፣ ወፎች ማሽላውን በልተው እንዳይጨርሱት ገበሬ በቡትቶና በሣር ባርኔጣ አውተፍትፎ የሠራው “ቁራ - አስፈሬ” አሻንጉሊት ነው ብንል ግነቱ ከመጠን አያልፍም፡፡

 

ይህ ማሽላ ጠባቂ አሻንጉሊት ራሱ ምንድን ነው? ቢባል ሕያው ሰው ለመምሰል የሚሞክር፣ በተለይ ከሩቅ ሲያዩት የሚያሳስት ሲቀርቡት ግን ሰው ሠራሽ ዕቃነቱ ጎልቶ የሚታወቅ ተዋናይ ነው፡፡ ትጉህ ሠራተኛ መስሎ በእጁ በትር ቢጤ ይዞ በንቃት የተሰለፈ ዘበኛ ወይም የሚያነጣጥር ወታደር ይምሰል እንጂ ምንም የተጨበጠ ሥራ አይሠራም፡፡ በልምጩ ዘንግ ርዝመት ያስፈራራ እንጂ “ቢከፍቱት ተልባ” ነው፡፡

 

ከሁሉ ከሁሉ የከፋው ነገር ይህ አሻንጉሊት ነፍስ የሚባል የለውም፡፡ ማንነቱ ገበሬው የፈጠረለት የውሸት መስፈራርቾ ማንነት ነው እንጂ “እኔ” ብሎ አስተንትኖ የሚያውቀው፣ የሚያሳውቀው፣ በዚያውም መሠረት የሚኖርበት ማንነት አይደለም፡፡ ትውልዱ ማንነቱ የተጥበረበረበት ድንግርግር ትውልድ ነው፡፡

 

ይህ ትውልድ የዓላማ ጭካኔ ያጣ ትውልድ ነው፡፡ ለምን እንደቆመ አስተንትኖ ስለማያውቅ በነፍሱ አይወራረድም፡፡ ለሞት ለሽረት ራሱን አያጋልጥም ሲያባብልና ሲባበል መኖር ይወዳል ኃይማኖቱ ሸቀጥ ሆኗል፡፡ ክርስትና ገበያ እንዲያገኝ ጌጥና ድምቀት፣ ሆይ ሆይታና ጩኸት የሚያስፈልገው መስሏል፡፡ ክርስቲያን መሆን የሞት የሕይወት ውሳኔ መሆኑ ቀርቶ ከመንገድ አላፊና ከጎረቤት የሚኮረጅ የመጨረሻው ፋሽን ሆኗል፡፡ ስለዚህ ዘመናውያን ስልጡኖችና ንቁዎች እንዲሻሙት ብልጭልጭ ማስታወቂያ አበዛን፡፡ ይህም ደቀመዛሙርት ሳይሆን “ቲፎዞዎች” አፈራልን፡፡ “የኢየሱስ ክርስቶስ ክለብ” ደጋፊ ነው፡፡ የሚያስፈልገውን የሜዳ ታክቲክ ሁሉ ተጠቅሞ ለክለቡ ማሸነፍ ይሟሟታል፡፡ ክለቡ ተስፋ የሌለው ከመሰለው ሌላ ለማቋቋም የሚከለክለው የለም፡፡ ኳስ ሜዳው ላይ ተገኝቶ መጯጯሁን ነው ሊያጣ የማይፈልገው፡፡ መሰጠት፣ ዲሲፕሊን፣ መታገሥ፣ መጠበቅ፣ መገዛት የሚሉት ቃላት ያረጁና የማይጠቅሙ ወይም የሚያስፈራሩ ናቸው፡፡ በምትካቸው ፍጥነት፣ የዛሬ ድል፣ በእጅ ማድረግ፣ መወርወር፣ ማንሳት፣ አቋራጭ መፈለግ፣ ታዋቂ መሆን ዝነኞች ሆኑ፡፡

 

ትውልዱ ግላዊና ስግብግብ ሆነ፡፡ እግዚአብሔር የፍጥረተ - ዓለም ጠባቂነቱ ሳይሆን የግል ፍላጎት ሞይነቱ ጎላ፡፡ ከችግራችን ብዛት ይሁን ከዓይነ ልቡናችን ጥበት የማኅበረሰብን ደህንነት ከማሰብ ይልቅ የየግላችንን “እንጀራ ማብሰል” ዋና ጉዳያችን ሆነ፡፡ የምንወዳቸው የስብከት አርእስት “እንዴት በቂ እንጀራ ሊገኝ እንደሚችል” “እንዴት ከዚያኛው ሰው እንደ ምንበልጥ” የሚነግሩንን ነው፡፡ “ተስማሚ” ጥቅሶች ከመጽሐፍ ቅዱስ አይታጡም፡፡

 

ትውልዱ ዓላማ - ስስ ነው፡፡ ዘልቀው ቢመረምሩት ከጥቂት ወራት የበለጠ የኑሮና የሕይወት ሕልም የለውም፡፡ ሁሉም ነገር ከቁጥጥር ውጪ እንደሆነ ስለሚያስብ አራዝሞ ለማየት ፍላጎትም አቅምም አንሶታል፡፡ ስለዚህ የዕለት የዕለቱን እየጫረ ነው የሚተኛው፡፡ ደግሞ ዓላማ እኮ ረጅም እንዲሆን ትልቅ መሆን አለበት፡፡ እና በጣም ትልቅ ከሆነ አምላክ ጋር እንዳለን በድንግዝግዝ ቢታወቀንም ገና የትልቅነቱን ግዝፈት ለማየት አልተሰናዳንም፡፡ እርሱ እንደ አቅሙ ብርታት ብርቱ ነገር በእኛ እንደሚሠራ ማሰብ አልቻልንም፡፡ “እግዚአብሔር ትልቅ ነው” ስንል እዚያ ማዶ ብቻውን ሆኖ ነው የሚታየን እንጂ ከእኛ ጋር፣ በእኛ ውስጥ ገብቶ፣ በእኛ ዘመን ትልቅ ነገር እንደሚያደርግ መቁጠር አልቻልንም፡፡ ስለዚህ ሕልማችን ቁጥቁጥ ናት፡፡

 

ትውልዱ ተድላ አሳዳጅ ነው፡፡ ርካታ የሚገኘው ስሜት - ሕዋሳታዊ ፍላጎቶቻችንን በማሟላት እንደሆነ ስለሚቆጥር ሞቶ ተሟሙቶ ነጥቆና ተባልቶ በድኩማን ሬሳ ላይ ተረማምዶም ቢሆን ሥጋዊ ጩኸቱን ማስታገስ አለበት፡፡ ይህ ፈንጠዝያ ፍለጋ ሃብታም ድሃ የሚመርጥ ልባም ነገር አይደለም፡፡ ያንን የውስጥ ውትወታ ለማለዘብ ሁሉም እንደ አቅሙ ይሯሯጣል፡፡ ባይሳካለት እንኳ የምኞቱን ጣዖት እያባበለ ያስተኛዋል እንጂ በምንም ዓይነት ዓይኑን ሞልቶ ሊጋፈጠው አይደፍርም፡፡ ይህ ሰው ክርስቲያን የሆነ እንደሆነ ያንኑ አውሬ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቀለም ቀባብቶ በተለሳለሰ ጮሌ ቋንቋ ተጠቅሞ “ለጌታ ክብር እንዲውል ብዬ” ደግሞ “ለራስ ማሰብም እኮ መንፈሳዊ ነው” በሚሉ ሐረጎች እየደባበሰ ያነግሠዋል፡፡ ሌሎች እንዲበለጽጉ፣ ሌሎች ከሕመማቸው እንዲተርፉ መስዋዕታዊ ኑሮ ለመኖር መወሰን ትልቅ ዳገት ሆኖብናል፤ የኑሮ ዘዬአችን “ከራስ በላይ ነፋስ” ነው፡፡

 

ትውልዱ በጥላቻ፣ በቂምና በበቀል ደድሯል፡፡ ጠብ ለመጫር ፈጣን ነው፡፡ የጫረውን ትንሽ እሳት አፋፍሞ ጫካውን ሁሉ የሚበላ ሰደድ ለማድረግ ጊዜ አይወስድበትም፡፡ ይህ ትውልድ እርስ በእርሱ የተፈራራ ጥላውን የማያምን ደንባራ ትውልድ ሆነ፡፡ ራሱ ከራሱ ጋር ስምረት ስለሌለው ከሌላው ጋር ተጣጥሞ መኖር ርቆታል፡፡ የርኅራኄ ሕዋሱ ደነዘ፤ ብዙ መራቀቅ የማይጠይቀው ሰብዓዊ ሐዘኔታ እንኳ ከሕሊናው ተሟጠጠ፡፡ እርቅና ሰላም የፌዝ ቃላት ሆኑበት፡፡ የባልንጀራውን ሕይወትና ኑሮ እንደ አሮጌ እራፊ ብስክስክ አድርጎ ሲጥል በእብድ ፍጥነትና ጉልበት ነው፡፡

 

ትውልዱ ፈሪ ነው፡፡ ምንድነው የሚፈራው? ነገን አጥብቆ ይፈራል፡፡ ምክንያቱም በነጋ ቁጥር የውድቀትና የሞት ድምጽ እየበረታ የሕይወትና የልምላሜ ተስፋ እየሸሸ ሲሄድ ስላየው ነው፡፡ “ምን እበላለሁ?” ከሚለው ጀምሮ “ማንን ማመን ይቻላል?” እስከሚለው ድረስ በፍርሃት ጥያቄ ተወጥሯል፡፡ የነካው ነገር ሁሉ ተስፈንጥሮ የሚገድለው ስለሚመስለው ምንም ነገር ሳይነካ “ጎመን በጤናውን መኖር መርጧል”፡፡ ይህን የፈሪ መንገድ ይምረጥ እንጂ በሽሽቱ ብዛት የሚፈራውን ነገር አላመለጠውም፡፡ እንዲያውም ድንጉጥ እንግዳውን እንዳወቀ ውሻ ፍርሃቱ እየተከታተለ ከቀዬው እስኪርቅ ያሳድደዋል፡፡

 

የትውልዱን አበሳ ላበዛ አልፈልግም፡፡ ለመፍረድም አልተሾምሁም፡፡ ማድረግ የሚገባንን ከመናገሬ በፊት ግን መመራመሪያ ጥያቄዎች ላስቀምጥ አንደኛው የቀደመው ትውልድ ለዚህ ትውልድ ትቶት የሄደው ወይም እየሄደ ያለው ምንድን ነው? የሚል ነው፡፡ አንዱ ትልቅ በሽታችንና ሰቀቀናችን በእኛ ዘመን የሚታዩ “የእምነት አባቶች”፣ “የፍቅር አባቶች”፣ “የቅድስና አበጋዞች” ሲጨንቀን ሄደን ምክር የምንጠይቃቸው አስተዋዮች ከሩቅ ፈለጋቸውን ተከትለን ለመሮጥ የምንደፍርባቸው መሪዎች አሉን ወይ? የሚለው ነው፡፡ ሽማግሌዎች እጃቸው ከግፍ ያልጸዳ ከሆነ፣ መሪዎችና የእውነት መምህራን የምንላቸው ከምስባኩ ሲወርዱ የሚኖሩት የተጭበረበረ ሕይወት ከሆነ ምን ዓይተን ነው የምንተርፈው? መሪዎቻችን የጠራውን ውሃ ለማደፍረስ የሚቸኩሉ ከሆነ እንዴት እኛ የሠላም አርበኞች እንሁን? ከአባቶቻችንና ከእናቶቻችን ጋር ለአፍታ ብንቀመጥ ውዳሴ ከንቱና አሉባልታ ያጠመቀው ወሬያቸው እየገፈተረ ካወጣን እኛ እንዴት የቁም ነገር ሰዎች እንሁን? ሁለተኛው የመመራመሪያ ጥያቄ - ይህ ትውልድ አሁን የሆነውን ነገር ተቀብሎት ወዶት የተቀመጠ ነው? ወይስ በላዬ ከተጫነበት ቀንበር ለመላቀቅ የሚታገል ተሸናፊ ነው? ጠጋ ብለን በሰከነ ልቡና ካየነው ይህ ትውልድ ብርቱ ጥማት ያከሰለው፣ ርኅራኄያችንንና የጥንቃቄ ሕህምናችንን የሚሻ ምስኪን ትውልድ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የእውነት የዓላማ - የነጻነትና የፍቅር ጥማት አለበት፡፡ መላ መንፈሱን አደራርቆ የቁም አስከሬን ያስመሰለው ይኸው ለረዥም ጊዜ የተጠናወተው መሠረታዊ የነፍስ ምግብና ውሃ እጦት ነው፡፡ እየተዋከብን በጎዳና ላይ ስንጋፋ “ራስ ወዳድነቱ”ን እንኮንናለን እንጂ “እስቲ አረፍ ብለን እንጫወት” ብንለው ለፍቅርና ለእውነተኛ ቅርርቦሽ ነፍሱ ሲዋትት እናገኘዋለን፡፡ ከሩቅ ሲጣደፍ ስናየው ወይም በንግግሩ ብዛት ሰው ለማሳመን ሲወተውት ስንሰማው ጥራዝ ነጠቅ ወሽካታ ይመስለናል እንጂ ነፍሱን ካዳመጥን ዙሪያውን ቃኝቶ ፍሬ እውነቱን ባለማግኘቱ ምክንያት ያገኘውን ገለባ ነገር ማናፈስ ልማድ የሆነበት የእውነት ራብተኛ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ሊያምነውና መንፈሱን ሁሉ ሊማርከው የሚችል ነገር ካገኘ ራሱን ለመስጠት ወደ ኋላ የሚል አይደለም፡፡ ፍርሃቱ የመነጨው በጨለማ በድንግዝግዝ ከፎቅ እንደሚወርድ ሰው በዳበሳ ከሚያደርገው አካሄዱ ነው፡፡

 

መዳኛችን ምንድን ነው? ምን እናድርግ? ሁላችንን የሚመለከት ጥያቄ ነው፡፡ በሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለነው ሁላችን በአርምሞ ነገሩን ዓይተን መልስ ልንሰጥበት ይገባል፡፡ ይሄ ትውልድ ካልዳነ የሚቀጥሉት ሦስትና አራት ትውልዶች ወዮላቸው ብል የመዓት ነቢይ አልሆንም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል በአንድ ትውልድ የተሠራው ሥራ የሚቀጥሉትን ተከታታይ ትውልዶች እንደሚነካ በቂ ምስክር አስቀምጧል፡፡

 

“እግዚአብሔር፣ እግዚአብሔር መሐሪ ሞገስ ያለው……እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ…. የአባቶችንም ኃጢአት እስከ ሦስትና አራት ትውልድም በልጅ ልጆች ላይ የሚያመጣ አምላክ ነው፡፡” (ዘፀ 34፡6-7?

 

ስለዚህ ትውልድ የሚገደን የጌታ ልጆች ልናደርግ የሚገባንና ልናስተላልፈው የሚያስፈልግ መልእክት አለ፡፡ ይህን የምንናገር እኛ እዚያ ማዶ በጠዳ ሰገነት ላይ ሆነን ሌሎች ትቢያው ላይ ተቀምጠው አንጋጠው እየሰሙን ሳይሆን ራሳችንም አለንበትና ለእኛው እንደምንናገር ሆነን ነው፡፡

 

ይህ ትውልድ - ክርስቲያኑ ሕዝብ - እውነተኛና ክቡር የሆነውን ማንነቱን እንዲገነዘብ ማገዝ ያሻል፡፡ መነሻ መድረሻ ያለው፣ ባለብዙ ማዕረግና ባለ ዘላለማዊ ዕጣ መሆኑን ማሳወቅ ይገባል፡፡ ምንም ኃጢአት ሊከሰው ባልተቻለው በክቡር የክርስቶስ ደም የተገዛ፣ በእምነት የሰማይና የምድር ፈጣሪ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ፣ እንከን፣ እድፈት ለማይገኝበት መንግሥት የታጨ ሰማያዊ ዜጋ እንደሆነ አጥብቆ ይረዳ፡፡ እንደ ድመት እየተፍረገረገ በየስኒው ጥጋጥግ የወተት ጭላጭ እንዳይቀላውጥ ከማይነጥፍ የህይወት ምንጭ ጋር መያያዙን ይወቅ፡፡ አንገቱን ቀና አድርጎ መራመድ ያለበት ኪሱ በረብጣ ስለሞላ ሳይሆን የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር አሳዳሪው ስለሆነ መሆን አለበት፡፡

 

ትውልዱ የነገሮችን ዋጋ ተመን መለዋወጥ ያስፈልገዋል፡፡ ዘመነኛው ነፋስ ያላግባብ እያራገበ ጣራ የሰቀለውን ገለባ በስሙ ጠርቶ ገለባ ማለት መቻል አለበት፡፡ የከበረውን ከተዋረደው እየለየ ለሁሉም ልክልኩን ማስቀመጥ አንዱ ትልቁ ሥራው ነው፡፡

 

ለምሳሌ፡ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው”፡፡

በጮሌነት ራስን ከማዳን ይልቅ በትሕትና መሥዋዕት መሆን የከበረ ነገር ነው፡፡

በመሪነት መሰላል ወደላይ ከመሽቀዳደም ይልቅ ሰላማዊ ዝምታ ጤና ይሰጣል፡፡

በአገልግሎት ብዛት እየባከኑ የማይጠቅም አቧራ ከማስነሳት ይልቅ የጌታችንን ድምጽ ለማዳመጥ አደብ መግዛት ይጠቅማል፡፡

 

ክርስቲያኑ ኅብረተሰብ ይህች ምድር የእግዚአብሔር ሥሪት እንደሆነች ልብ ብሎ ከፍጥረተ - ዓለም ጠባቂ ጋር መተባበር እንዳለበት ይወቅ፡፡ ሣር ቅጠሉ-አፈር ጠጠሩ ሁሉ እኮ የእኛ ጌታ የእግዚአብሔር ነው፡፡ ስለ ዛፍ መጨፍጨፍ - ስለ ሐይቅ መበከል - ስለ ጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናት ዕጣ ፈንታ መጨነቅና ማልቀስ - የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግም መነሣሣት ንጹሕ ክርስትና ነው፡፡ “ለድሃ አደጉ ተምዋገት ሊታረዱ የተፈረደባቸውን ታደግ” የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ነው፡፡

 

ትውልዱ ባለ ጥሪ መሆኑን በጥልቅ ይረዳ፡፡ “እናንተ ግን ከጨለማ ወደ ሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁ የእርሱን በጎነት/ድንቅ ሥራ እንድትነግሩ የተመረጠ ትውልድ ናችሁ” ያለን ቅዱስ ጴጥሮስ በሚያስገርም የቃላት ስብስብነት የመኖራችንን ዓላማና ተልዕኮ ሲያስታውቀን ነው፡፡ ከተልዕኮ ውጪ መኖር እንዴት አሰቃቂ ዕዳ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመንገድ እየተንጠራወዝን እንዳናዛጋ ብሎ ነው “ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ፣ ከእኔም ተማሩ” ያለን፡፡ ትውልዱን የዚህ የዋህና ትሑት ሰው ቁርጠኛ ተከታይ ካደረግነው መንገዱን በወርቃማ ፍሬ ሞላነው፡፡

Read 19389 times Last modified on Wednesday, 22 July 2015 13:03
Negussie Bulcha

Website: www.negussiebulcha.com Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 375 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.