You are here: HomeOpinionsክርስትናና ጦርነት

ክርስትናና ጦርነት

Written by  Wednesday, 22 April 2015 00:00

በዘመነ ደርግ ሃይማኖት በሕግ ውጉዝ ተግባር ስለነበር፣ሰዎች በሃይማኖታቸው ሰበብ የሚደርስባቸውን ግፍ አቤት የሚሉበት አንዳችም የበላይ አካል አልነበረም፡፡ በዚህ ምክንያት ክርስቲያኖች በመንግሥትም ሆነ በሰፈር ቦዘኔዎች እጅግ ብዙ በደል ሲፈጸምባቸው መቆየቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው (ለነገሩ ሃያ ዓመት ዐለፈው እሳ፣ ጊዜ እንዴት ይሮጣል ጃል)፡፡ በዚያ ክፉ ዘመን፣ ክርስቲያኖች ወደ ቤተ አምልኮዎች የሚሄዱት ጨለማን ተገን አድርገው አልያም ሰዎች በብዛት አያዝወትሩባቸውም የሚሏቸውን መንገዶች አሳብረው ነበር፡፡ ከታሪክ ዳኛው ከእግዚአሔር በስተቀር፣ ያገባኛል በሚል ጥቃታችንን የሚከላከል አንዳችም አካል አልነበረም፡፡ ይህን በቅጡ የተገነዘቡ የመንደራችን ቦዘኔዎች፣ ከአምልኮ ከስብሰባ የሚመለሱትን ክርስቲያኖች አሳቻ ቦታ እየጠበቁ ያለአንዳች ገደብ አገላብጠው በደብደቡን ሥራቸው አደረጉት፡፡

 

ይህ ጕዳይ እጅግ ያስመረረውና ያስቆጣው አንድ ክርስቲያን ወንድማችን፣ ጥቃቱን እንደ አመጣጡ መመከት አግባብ ነው ወደሚል ድምዳሜ ላይ ደረሰ፡፡ ይህ ወንድም የፈረጠመ ጡንቻ ባለቤት መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በኮማንዶ ትምህርትም የተካነ ነበረና እነዚያን ግብር አልባ ቦዘኔዎች እንደ ዛፍ እየገነደሰ እንደ ፋሲካ ብቅል ያሰጣ፣ እንደ መጅሊስ ስጋጃ ያነጥፋቸው ጀመር፡፡ በወንድማችን ችሎታ ያልተደመመ፣ በክሎቱም አጀብ ያላለ ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ የአካባቢውም ነዋሪ፣ “ጴንጤዎች የአቋም ለውጥ በማድረግ፣ አጸፋዊ ምላሽ መስጠት ጀመሩ!”፣ የሚለውን ወሬ በከተማው ሁሉ ነዛው፡፡ ጥቃቱ መቀልበሱ ሁሉንም ቢያስደስትም፣ ይህ ወንድም በዚህ መልኩ ጣልቃ መግባቱ ትክክል ነው ስሕተት የሚለው ጕዳይ ግን ክርስቲያኑን ማኅበረሰብ በእጅጉ አወዛገበ፡፡ በተገኘው ጸጥታ ጮቤ ያልረገጠ ክርስቲያን ነበር ማለት ግን በፍጹም አይቻልም፡፡ ቡጢና የጫማ ጥፊ ዕሩምታ ፊቱን ያከሰለበት እንደ እኔ ያለውማ ሰው፣ አንጀቱ ቅቤ ጠጥቷል ብል ከመንፈሳዊነት የሚያወጣኝ አይመስለኝም፡፡

 

እንዲያውም በዚህ ወንድም ጣልቃ ገብነት የተገኘውን ይህን ታላቅ ሰላም፣ አንዳንድ ወገኖች ፓክስ ሮማና የሚል ስም አወጡለት (ይህ መቼም በወቅቱ የነበረውን ግፍ ከተገኘው ሰላም ጋር የሚያነጻጽር የእፎይታ አስተያየት ይመስለኛል--ሮማ ገናና በነገረችበተ ዘመን ለረጅም ጊዜ በምድር ላይ ሰፍኖ የነበረውን ታላቅ የጸጥታ ዘመን፣ “ፓክስ ሮማና” በመባል ይታወቃል “Pax Romana” በላቲን የሮማ ሰላም ማለት ነው)፡፡ አንዳንድ ክርስቲያን ወገኖች፣ “አጸፋ መመለስ ክፋት የለውም” የሚል አቋም በመያዝ፣ ለአቋማቸው ግብኣት ይሆንም ዘንድ እስራኤል ራሷን ከተለያዩ ጥቃቶች የተከላከለችባቸውን በርካታ የብሉይ ኪዳን ምንባባት፣ በተለይ በዘመነ መሳፍንት የነበረውን የመከላከልና የማጥቃት ፖሊሲ በማጣቀስ የዚህን ወንድም ትድግና አወደሱ፡፡ እንዲያውም አንዳንዶች የጅዶውን ትምህርት ከዚህ ወንድም በመቅሰም “ጦሩ” እንዲጠናከር ሐሳብ አቀረቡ (የዚህ መፍትሔ አቅራቢዎች፣ “በወዶ ዘማጅ” ራሳቸውን እንደ መለመሉ አያጠራጥርም)፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ይህ አካሄድ “ጌታ ክፉን በክፉ አትመልሱ ሲል ያስተማረውን ትምህርት በግልጽ ይጻረራል” የሚል የዚህን ወንድም አካሄድም ሆነ “እንጠናከር” የሚለውን ሐሳብ በጽኑ ተቃወሙ፡፡ ነገሩ ማወዛገቡን ቀጠለ፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች፣ “ድርጊቱን እናስቁም አናስቁም” በሚለው አሳብ ለሁለት ተከፈሉ፡፡ አንዳንድ ክርስቲያን ወገኖች፣ “ራስን መከላከል ትክክል ነው ወይስ አይደለም” በሚለው ርእሰ ጕዳይ ትምህርት እንዲሰጥ፣ በተጻራሪ ጐራ የቆሙትንም መረጃዎች በትክክል በመመርመር አማኒው ማኅበረሰብ ወደ አንድ አቋም ላይ እንዲደርስ ሐሳብ ቢያቀርቡም፣ በወቅቱ በነገረ መለኮት ዕወቀት ዘልቆ የሄደ ሰው በመካከላችን ስላልነበረ፣ ሐሳቡ ከሐሳብነት በመዝለል ወደ ገቢር መቀየር አልቻለም፡፡ መቼም፣ አንዳንድ የታሪክ አጋጣሚዎች አንዳንድ ርእሰ ጕዳዮችን በትክክለ ለመመርመር ጥሩ ዕድል ይዘው ቢመጡም፣ ይህን ዕድል የሚጠቀሙባቸው ግን እጅግ ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው፡፡ ሌላ ናሙናዊ ተሞክሮ ላቅርብ፡፡

 

ጐጆ ቀልሰን የገባንበት አካባቢ ከዋነው መንገድ የሚርቅ ነው፡፡ የከተማ አውቶቡስና ታክሲ የሰፈሩን ነዋሪ የሚጥለው፣ ከመኖሪያ ቤታችን ከዐሥር እስከ ዐሥራ አምስት ደቂቃ በሚርቅ አደባባይ ላይ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት፣ በተለይ ሴት እኅቶቻችንና ሚስቶቻችን ጨለማን ተገን ባደረጉ ወሮበሎች ቦርሳቸውን እየተነጠቁ፣ ተንቀሳቃሽ ስልካቸውን እየተቀሙ፣ አንዳንዴም እየተደበደቡ መግባታቸው የዘወትር ገጠመኝ ሆነ፡፡ ያለብንን ችግር ለከተማው ፖሊስ በተደጋጋሚነት አቤት ብንልም፣ የፓሊስ ጽፈት ቤቱ፣ “የሰው ኀይል ዕጥረት አለብን” በሚለው ሐሳቡ ስለጸና፣ ችግሩ መፍትሔ ሳያገኝ ለረጅም ጊዜ ቀጠለ፡፡ በአንድ ወንድማችን ቤት በየሳምንቱ እየተገናኘን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የምናጠና ክርስቲያኖች መደበኛውን ጥናታችንን በማቋረጥ፣ ለችግሩ መፍትሔ ይሆናሉ ባልናቸው አማራጮች ላይ በሰፊው ተወያየን፡፡ አንዳንዶች “ዘበኞችን ቀጥረን እናስታትቅ” የሚል አማራጭ ሲያቀርቡ፣ ሌሎች ደግሞ “መንግሥት አካባቢውን የሚያገለግሉ ፖሊሶችን እንዲቀጥር የገንዘብ ድጋፍ እናድርግለት” አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ፣ “ችግሩ በተለይ የሚከሠተው በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት ስለሆነ፣ ተራ በተራ ሮንድ እንዙር፣ ባይሆን ራሳችንን ለመከላከል የሚሆን የጅዶና የካራቴ ትምህርት እንማር ወይም ከመንግሥት ፈቃድ ጠይቀን የጦር መሣሪያ እንታጠቅ” የሚል መፍትሔ ሐሳብ አቀረቡ፡፡ በዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባን ትልቁ ቊም ነገር፣ ወደ ሰላሙ ግብ እንዴት እንደርሳለን በሚለው የአፈጻጸም ሄደት ላይ ሰዎች የተለያየ አቋም ቢኖራቸውም፣ በተገኘውና ዐቅም በፈቀደው ሁሉ መንገድ ችግሩን ማስቆም፣ ፍትሓዊ አካሄድ ነው በሚለው ጭብጥ ላይ ግን ሁላችንም መስማማታችንን ነው፡፡ ምክንያቱም “እጃችንን አጣምረን በመጠቃታችን እንቀጥል” የሚል አማራጭ ሐሳብ አልቀረበምና)፡፡ በአገር ደረጃ ሊካሄድ የሚችልን ውይይት ደግሞ በናሙናነት መዘን እንመልከት፡፡

 

ዐፈሩን ገለባ ያድርግላቸውና (“ነብስ ይማር” እንዳልል መሠረተ እምነቴ አይፈቅድልኝም፡፡ “ዐፈሩን ገለባ ያድርግላቸው” የሚለው አገርኛ አባባል ግን ጨዋነቴን ሳያሳይ አይቀርም) ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጦራቸው፣ የሱማሌን ድንበር አቋርጦ በመግባት በአልሻባብ ተዋጊዎች ላይ ጥቃት ማድረስ ለምን እንደ ጀመረ በተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ የሚከተለውን መልስ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ “በሱማልያ የሚገኘው አልሻባብ ለእኛ እንደማይተኛ ስለምናውቅ እንዲሁም አገሪቱን የጦር ዐውድማ እንደሚያደርጋት በይፋ ስለተናገረ፣ ይህን ዐላማውን ገዳር ከማድረሱ በፊት ጦር በማዝመትና አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት፣ እርሱ በሚፈልገውና በሚገባው ቋንቋ ልናናግረው ይገባል፡፡ ይህን ማድረጋችን ነገ በድንበር አካባቢም ሆነ በመኻል አገር ሊቃጣ ያለውን አደጋ ከምንጩ ማድረቃችን እንጂ፣ ጠብ መጫራችን አይደለም” የሚል የመከላከያ ነጥብ አቀረቡ፡፡ አንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲ ሰዎች ግን፣ “አልሻባብ ኢትዮጵያን አተራምሳለው የሚል ነገር ተናግሯል እንዲሁም ነገ ይህን ንግግሩን እውን በማድረግ ትልቅ የጸጥታ ሥጋት ይደቅናል በሚል፣ የአንድን ሉዓላዊ አገር ድንበር ሰብሮ በመግባት ጦርነት መክፈታችን ጦርነታችንን ፍትሓዊ ጦርነት አያደርገውም፡፡ እንዲያውም ከጐረቤት አገር ጋር በዚህ መልኩ ጦር መማዘዝ የኋላ ኋላ መዘዙ ብዙ ከመሆኑ ባሻገር፣ ነገ ትልቅ የጸጥታ ሥጋት የሚጋርጥ ጕዳይ ነው” የሚል ሐሳብ በመያዝ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተሟገቱ፡፡

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ የሰጡት ምላሽ፣ “አሜሪካ በበዙ ሺህ ኪሎሜትሮች አቋርጣ በመሄድ በኢራቅና በአፍጋኒስታን ጦርነት በማካሄድ ላይ ያለቸው እነዚህ አገሮች የአሜሪካን ተጐራባች አገሮች በመሆናቸው ሳይሆን፣ ዛሬ በኢራቅና በአፍጋኒስታን እያቈጠቈጠ ያለው ሽብርተኝነት፣ ነገ ድንበር ተሻግሮና በርካታ ኪሎሜትሮችን አቋርጦ በመገሥገሥ፣ በመስከረም አንድ የተፈጸመው ዐይነት ትልቅ ውድመት እንደሚያስከትል ስለተገነዘቡ፣ ይህን ትልቅ የደኅንነት ሥጋት በእንጭጭነቱ ማድረቅ አግባብ ነው የሚለውን አካሄድ ታሳቢ አድርገው ነው፡፡ ስለዚህ የእኛም ተገደን የገባንበት ጦርነት ስለሆነ፣ ጦርነቱ ፍትሓዊ ጦርነት ነው” የሚል ነበር፡፡

 

በማግስቱ በቴሌ ቪዥን የተላለፈውን የፓርላማውን እሰጥ አገባ በተመለከተ አስተያየት የጠየቅሁት አንድ ክርስቲያን ወንድም የሚከተለውን አሰትያየት ሰጠኝ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ተቋዋሚዎች ከአልሻባብ ጋር መዋጋት ያለብን መቼ ነው በሚለው ጕዳይ ላይ የተለያየ ሐሳብ ቢኖራቸውም፣ “ራስን ለመከላከል ነፍጥ ማንሣት ትክክለኛ አካሄድ ነው” የሚለውን አቋም፣ የፓርላማ አባላት ሁሉ የተቀበሉት ይመስላል፡፡ እኔ በግሌ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ተቋዋሚዎች ከመስመር ውጪ ናቸው ባይ ነኝ፡፡ ወደዚህ ድምዳሜ እንዴት ሊደርስ እንደቻለና የእርሱ አማራጭ አካሄድ ምን እንደሚመስል በማስረጃ እንዲሞግት በጥያቄዬ ላይ ጥያቄ ጨመርሁ፡፡ እኔ ክርስቲያን እንደ መሆኔ መጠን ትክክለኛ የሰላም አማራጭ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሯል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡ ይህም አቋሜ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥትም ሆነ ተቋዋሚ ፓርቲዎች ስሕተት ናቸው ወደሚለው ድምዳሜ እንድደርስ ያስገድደኛል፡፡ ክርስቶስም ሆነ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ሰላምን እንደ ብቸኛ አማራጭ አጥብቀው ይከተሏት ነበር፡፡ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በቀልን በመተው “አንድ ጕንጭህን ለሚመታህ ሌላውን አዙርለት” አለ እንጂ፣ ስሕተቱን በሌላ ስሕተት ቀልብስ አላለም፡፡ መቼውንም ቢሆን፣ ሁለት ስሕተቶች በአንድ ቢደመሩ ውጤታቸው ትልቅ ስሕተት እንጂ እውነት ሊሆን አይችልም፡፡ ጌታ ምንባባተ ብጽዕና በሚማለው የማቴዎስ ወንጌል ክፍል፣ “የሚያስታርቁ፣ ስለጽድቅ የሚሰደዱ፣ የሚምሩ ወዘተ ብጹዓን ናቸው” አለ እንጂ፣ አስገዳጅ በሆነ ሁኔታ ውስጥ አጸፋ መመለስን በአማራጭነት አላቀረበም፡፡ በመጀመሪያው ሦስት መቶ ዓመታት ውስጥ የነበረችው ቤተ ክርስቲያን፣ ከነፍጥ ጋር ግንኙነት እንደ ነበራት የሚገልጽ አንዳችም መረጃ የለም፡፡ በጦር ሠራዊት ውስጥ ገብተው የሚያገለግሉ ክርስቲያኖችም መኖራቸው አልተዘገበም፡፡ የጦርነት ጕዳይ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ርእስ መሆን የጀመረው ሮማውያን ቄሳሮች ክርስትናን ከተቀበሉ በኋላ እንደ ሆነ በርካታ የታሪክ ድርሳናት ያትታሉ፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ጦር ድንበር ተሻግሮ መሄዱም ሆነ ልዕለ ኀያሏ አገር አሜሪካ፣ አገር አቋርጣ በኢራቅና በአፍጋኒስታን ጥርነት መክፈቷ ስሕተት ብቻ ሳይሆን ኢሥነ ምግባራዊ ተግባር ነው፡፡

 

እኔም “እንግዲያው አንድ ጦርነት ፍትሓዊ የሚሆነው ምን ምን ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልቶ ሲገኝ ነው” የሚል ጥያቄ አቀረብሁ፡፡ ወዳጄም፣ “ጦርነትና ፍትሕ የሚሉት ቃላት አንዳችም የአብሮነት ግጣም ያላቸውም፡፡ ጦርነት ባለበት ቦታ ሁሉ ፍትሓዊነት የለም”፡፡ ሲል ምላሹን ቈፍጠን ባለና ጽኑ መንፈሱን በሚገልጽ ገጽታ ተነተነ፡፡ እኔም፣ “ስለሰብአዊ መብት በመሟገት ትልቅ ስም ያተረፈው አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባለው ዓለም ዐቀፋዊ ድርጅት እንዲሁም በርካታ ግብረ ሰናይ ተቋማትና በሰብአዊ መብት አያያዛቸው የተመሰገኑ አገሮች፣ የሱዳን ግዛት በሆነው በዳርፉር ክልል የሰብአውያን ጭፍጨፋ እንደ ተካሄደ፣ እጅግ በርካታ ሰዎችም እንዳለቁ ገልጸዋል፡፡ ከዚህም የተነሣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይህን ከፍተኛ ዕልቂት ለማስቆም ወታደሮችን በማሰማራት በሁኔታው ውስጥ ጣልቃ በመግባት ዕልቂቱን ማስቆም ተችሏል፡፡ ኢትዮጵያም ለዚሁ ተግባር ጦር እንዳዋጣች እናውቃለን፡፡ መንግሥታት ይህን የጦር ጣልቃ ገብነት እንደ አማራጭ አድርገው የተከተሉት፣ የዲፕሎማሳዊው መፍትሔ ሙሉ ለሙሉ ከነጠፈ በኋላ ነው፡፡ ይህን መሰል ሁኔታ ባለባት በዚህች ምድር፣ ጦር መምዘዝ ፍትሓዊ የሚሆነው መቼና በምን ዐይነት ሁኔታ ውስጥ ነው? አንተ በማናቸውም ሁኔታ የጦር ጣልቃ ገብነት ስሕተት ነው የሚል አቋም ካለህ፣ ይህን ጣልቃ ገብነት እንዴት ትመለከተዋለህ? ነፍጥ ማንሣት ጭራሹኑ ስሕተት ከሆነ፣ የውትድርናን ሙያ ክቡር ነው ማለት እንዴት ይቻላል? ውትድርና የተሳሳተ የሙያ ዘርፍ ከሆነ፣ የጦር መሣሪያ የሚያመርት ወይም መሸጥ እኵይ ተግባር ሊሆን ነው? ለእነዚህና እነዚህን መሰል ለሆኑ ጥያቄዎች ምላሽህ ምንድን ነው?”፡፡

 

እስካሁን የተመለከትናቸውን ናሙናዊ ተሞክሮዎች በተመለከተ ያልዎት አቋም ምንድን ነው፡፡ በእነዚህ ተመክሮዎች ውስጥ እውነት የሚመስሉ በርካታ ስሕተቶች እንዳሉ ልብ ብለዋል? የክርስትና ሃይማኖት ጦርነትን በተመለከተ ያለው አስተምህሮ ምንድን ነው? ጦር በማንገትም ሆነ ቡጢ በመሰንዘር ራስንም ሆነ የንጹሓንን ሕይወት መታደግ ትክክል ነው ወይስ ስሕተት? ክርስቲያን ራስን ለመከላከል የቴኳንዶ/የካሬቴ ትምህርት መማር አለበት ወይስ የለበትም፡፡ ፓሊስ ጠመንጃ ታጥቆ የሕዝብን ሰላም ማስከበሩ ትክክል ነው ወይስ ስሕተት? ወቅታዊ ርእስ ይመስለኛል፤ እንግዲያው እንወያይ፡፡ ሠናይ ውእቱ፡፡

Read 8635 times Last modified on Saturday, 25 April 2015 20:09
Tesfaye Robele

ዶክተር ተስፋዬ ሮበሌ በኢንተርናሽናል የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የአዲሱ መደበኛ ትርጒም ተርጓሚ ሆኖ ሠርቶአል፡፡ በኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን የቤተ እምነቱ የሥነ ጽሑፍ ክፍል ኀላፊና የ“ቃለ ሕይወት” መጽሔት ዋና አዘጋጅ ሆኖ አገልግሎአል፡፡ ለዐቅብተ እምነት አገልግሎት ካለው ትልቅ ሸክም የተነሣ፣ ተስፋ ዐቃብያነ ክርስትና ማኅበርን መሥርቶአል፤ በዐቅብተ እምነትም ላይ በርካታ መጻሕፍትን አዘጋጅቶአል፡፡ የዶክትሬት ዲግሪውንም የሠራው ለረጅም ዓመት በሠራበትና ወደ ፊትም በስፋት ሊያገለግልበት በሚፈልገው በክርስቲያናዊ ዐቅብተ እምነት (Christian Apologetics) አገልግሎት ነው፡፡

Website: www.tesfayerobele.com Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 252 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.