You are here: Home

የእግዚአብሔር ስጦታዎች

Written by  Thursday, 30 July 2015 11:49

ጥር 16 ቀን 2003 ዓ.ም ከምሽቱ አምስት ሰዓት በኋላ ነው፡፡ ቢ.ጂ.ኤም በሚባል የማዋለጃ ሆስፒታል ውስጥ ባለቤቴ የመጀመሪያ ልጃችንን ለመውለድ ማዋለጃ ክፍል ውስጥ ተኝታ የምጥ ጣር ይዟት ትጮኻለች፡፡

 

እኔም በሀገራችን ሚስት ስትወልድ በማዋለጃ ክፍል መገኘት ያልተለመደ ስለሆነ (ከኮሪያ ሆስፒታል በስተቀር) እያማጠች ያለችበት ክፍል መስኮት አጠገብ ቆሜ ከውስጥ የሚወጡ ድምፆችን ጆሮዬን ተክዬ አዳምጣለሁ፡፡ ወዲያውም ደግሞ ወደ እግዚአብሔር ልመናዬን አቀርባለሁ፡፡ በህይወቴ እንደዛች ቀን ተጨንቄ የማውቅ አይመስለኝም፡፡ ባለቤቴን እንደምወዳት በትክክል የገባኝ በዛች የጭንቀት ሰዓት ነው፡፡ ከዛች ዕለት በፊት የነበሩ ኃጢአቶቼን ሁሉ ተናዘዝኩ፡፡ እግዚአብሔር ያቺን ቀን በሰላም እንዲያሳልፋት ያለኝን የጸሎት አቅም አሟጥጬ ጸለይኩ፡፡ በወቅቱ በጣም ተጨንቄና ባለቤቴን ላጣ እችላለሁ ብዬ ሰግቼ ነበር፡፡ ስጋቴ ከፍ እንዲል ያደረገው ሁኔታ የተፈጠረው እንዲህ ነበር፡፡

 

እኔና ባለቤቴ ማርገዟን ካወቅንበት ወቅት ጀምሮ እንደ ጀማሪነታችን ብዙ እንጨነቅ ጀመር፡፡ ከፍርሃታችን የተነሳም በተለያዩ ስፍራዎች ጉዳዩን የጸሎት ርእስ አድርገን በተንን፡፡ በብዙዎች ተጸልዮልን ብዙ ምክርም ተቀበልን፡፡ በርካታ መጻሕፍቶችንም አገላበጥን፡፡ እናም "አይዟችሁ ግብጻውያን አዋላጆች እንደመሰከሩት የዕብራውያን ሴቶች ብርቱ ናቸው ተብሏልና ጌታ ብርታት ይሰጣችኋል፡፡" "እግዚአብሔር ከምጥ የምገላግልሽ እኔ ነኝ ያለው ልጅ ልትወልድ ያለችን ሴት ነውና እናንተንም ይገላግላችኋል፡፡" "ልጅ የማስወልድ አጥንትን ከጅማት የሚዋድድ እኔ አይደለሁምን?" ያለው ጌታ በእናንተ ቤትም እየሠራ ነውና አይዞአችሁ የሚሉ የሚያበረታቱ መልዕክቶችን አደመጥን፡፡ እኛም በባለቤቴ ማህጸን ያለው ጽንስ እያደገ ባለባቸው ወራት ተግተን ጸለይን፡፡ ዘጠነኛው ወር ሲገባም በእምነትና በድፍረት የመውለጃዋን ጊዜ መጠባበቅ ጀመርን፡፡ አንድ ምሽትም ምጥ መጣ፡፡ ቀስ ብሎ የጀመራት ቁርጠት ምሽቱ እየገፋ ሲሄድ ወደ የተፋፋመ ምጥ ተቀየረ፡፡ ወደ ሆስፒታል የሚያደርሰን መኪና እስኪመጣ እኔና ባለቤቴ ሰዓቱን ለጌታ አሳልፈን ሰጠን፡፡ ሆስፒታል ስንደርስም እናትና አባቴ ቀድመው ደርሰው ስለነበር ባለቤቴ ከመኪና ከመውረዷ በፊት እናቴ በላብ የራሰው የባለቤቴ ግንባር ላይ እጇን ጭና ጸለየችላት፡፡ እኔንም ትክክለኛ የመውለጃ ሰዓቷ እንደደረሰ በጆሮዬ ሹክ አለችኝ፡፡

 

የሆስፒታሉ ዶክተር የመጀመሪያ ምርመራ አድርጎላት ወደ ማማጫ ክፍል ስትሄድ ግን ደም ይፈሳት ጀመር፡፡ ይኼም እናቴ ላይ ጥያቄ ስለፈጠረባት እኔም ስጋት ገባኝ፡፡ ለአንድ ሰዓት ያህል ባለቤቴ ባለችበት ማማጫ ክፍልና ዘመዶቻችን የተሰባሰቡበት እንግዳ ክፍል እየተመላለስኩ ቆየሁ፡፡ ድንገት የባለቤቴ ስም ተጠርቶ ባሏ እንደሚፈለግ ሲነገር በማማጫ ክፍሉ ውስጥ ወደሚገኘው ዶ/ር ሮጥኩ፡፡ ዶ/ሩም ባለቤቴ በመልካም ሁኔታ እያማጠችና ማህጸኗ እየተከፈተ ያለ ቢሆንም ብዙ ደም እየፈሰሳት በመሆኑ ነገሩ ለሷም ሆነ ለልጇ አስጊ እንደሆነ ገለጸልኝ፡፡ ስለዚህም በአፋጣኝ በቀዶ ህክምና ሊያገላግሏት እንዳሰቡና ፈቃደኛ እንድሆን ተጠየቅኩ፡፡

 

እኛም ምንም አማራጭ አልነበረንም፡፡ ባለቤቴን ሲከታተል የነበረው ሀኪም ተደውሎለት ሲጠየቅ ደግሞ ስለ ወቅታዊ ሁኔታዋ ከጠየቀ በኋላ ጥቂት ጊዜ እንዲጠብቁ አዘዘ፡፡ እንግዲህ ይህ ነው በኔም ሆነ በሌሎች ዘመዶቻችን መካከል ከፍተኛ ጭንቀት የፈጠረው፡፡

 

እኔም የባለቤቴን የምጥ ጣር እየሰማሁ አንዳች ክፉ እንዳይደርስና እግዚአብሔር ነገሮችን በሙሉ መልካም እንዲያደርግ ስጸልይ ቆየሁ፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኋላ የባለቤቴ ጣርም ሆነ ከአዋላጆቿ ግራ የምታደርገው መጯጯህ በጣም ጨመረ፡፡ ድንገት አዲስ የተወለደ ህጻን ድምፅ ሰማሁ፡፡ የደስታ እምባ እያነባሁ እግዚአብሔርን ማመስገን ጀመርኩ፡፡ ዘመዶቼም "የህጻን ልጅ ድምፅ ተሰማ ወይ?" እያሉ በቅርብ ወደ ነበርኩት ወደ እኔ ተሯሯጡ፡፡ ወዲያው ነርሷ ወጥታ ሴት ልጅ መገላገሏን አበሰረችኝ፡፡

 

ይህ አጋጣሚ እንግዲህ እግዚአብሔር በሕይወቴ ካመጣቸው ታላላቅ ምዕራፎች አንዱና ዋና ሊባል የሚችል ነው፡፡ ልጄ ከተወለደች በኋላ ባሉት ወራት ልጅ የመውለድ ጣዕምን በደንብ አየሁ፡፡ የራስን ልጅ የአብራክ ክፋይን በእጅ መያዝና ዓይንን በዓይን ማየት እጅግ አስደሳች ነገር ነው፡፡ አዲሲቷ እምቦቃቅላ ልጄ ሳያት ደስ ይለኛል፤ ስነካት ደስ ይለኛል፤ ድምጿ ደስ ይለኛል፤ ጠረኗም እጅግ ደስ ይለኛል፡፡ ምን ልበላችሁ እያደገች ስትሄድማ ለቅሶዋ እና የለሊት ብጥበጣዋ ሳይቀሩ እግዚአብሔር ሆይ ለዚህ ወልዶ የመሳም (ዘርቶ የመቃም) ክብር ያበቃኸኝ እኔ ማን ነኝ እንድልና በምስጋና እንዳነባ የሚያደርጉኝ ሀሴት የሚፈጥሩ ክስተቶች ሆነዋል፡፡

 

 

ይህን ሳስብ የሀገራችን የቀድሞ ገናና ንጉሥ አጼ ቴዎድሮስ ልክ ነበሩ እላለሁ፡፡ አጼ ቴዎድሮስ የበኩር ልጃቸው ልዑል አለማየሁ በተወለደበት ጊዜ መኳንንቶቻቸውን እንዲህ ብለው ጠይቀው ነበር ይባላል፡፡ "በዚህ ዓለም ላይ እጅግ ደስ የሚያሰኝ ሽታ ምንድነው?" መኳንንቱም እንደመሰላቸው የሚያውቁትን ባለ መልካም መዓዛ ሽቱም ሆነ ሌላ ነገር ለመጥራት ተሸቀዳደሙ፡፡ ንጉሡ ግን የሁሉን መልስ ካደመጡ በኋላ "አላወቃችሁትም በዓለም ላይ አዲስ እንደተወለደ ህጻን ልጅ ጠረን ደስ የሚያሰኝ ነገር የለም!" አሉ፡፡

 

በእውነቱ ልጅ ካገኘሁ በኋላ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታዎች እንደሆኑ ገባኝ፡፡ እግረ መንገዴንም ይህ የእግዚአብሔር ስጦታ እጅግ ክቡር እንደሆነም አስተዋልኩ፡፡ ይህን ስጦታ ከእግዚአብሔር የተቀበሉ ባለትዳሮች እጅግ ከፍ ያለ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ተረዳሁ፡፡ ረ እንደውም የእግዚአብሔር እርዳታ ካልታከለበት የእግዚአብሔር ስጦታ እና አደራ የሆኑ ልጆችን ማሳደግ እጅግ አዳጋችና ፈታኝ ነው፡፡

 

በእርግጥ እግዚአብሔርም ስጦታውን ሰጥቶ ለስጦታው የሚያስፈልጉትን ነገሮች አይነፍግም፡፡ ስለዚህም እኔም በራሴ እንዳየሁት አዲስ ከተወለደችው ልጄ ጋር በርካታ የገንዘብ፣ የጊዜ፣ የእውቀት፣ የጸጋ፣ የፍቅር እና የወዳጅ በረከቶች ጎርፈዋል፡፡ ‹‹እነሆ፥ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው፥ የሆድም ፍሬ የእርሱ ዋጋ ነው።›› (መዝ 127፡ 3) እንዲል ቅዱስ ቃሉ፡፡ ይኼንን ክቡር ስጦታ ከነአጃቢዎቹ በማስተዋልና በመረዳት በጥንቃቄም ለመልካም ማዋል ደግሞ አደራውን የተቀበሉት ወላጆች ኃላፊነት ነው፡፡

 

 

ቃሉም ለዚህ እኮ ነው ልጅ ስጦታ መሆኑን እንደነገረን ሁሉ እንዴት ባለ መልኩ ልናሳድገው እንደሚገባን መልሶ መላልሶ ያሳሰበን፡፡ ‹‹ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው፥ በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም።›› (ምሳሌ 22፡6)፤ ‹‹ …ለልጆችህም አስተምረው፥ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም፥ ስትነሣም ተጫወተው።›› (ዘዳግም 6፡7)

 

ይህን ጉዳይ በአእምሮዬ እያመላለስኩ እያለም "ልጆች የእውነት የእግዚአብሔር ስጦታዎች ከሆኑ ለምን የእግዚአብሔር ተወዳጅ ሕዝቦች በሙሉ ይህን ስጦታ አያገኙም?" የሚለው ከባድ ጥያቄ በውስጤ ተፈጠረ፡፡ "ለምን ሰዎች ሁሉ ካልሆነም እግዚአብሔርን የሚያምኑና የሚፈሩ ሁሉ የልጅ ስጦታን አያገኙም?" ጭራሽ መኖሩን የማያውቁ ሰዎች ከ10 በላይ መውለድ እየቻሉ ለምን የስጦታውን ባለቤት የሚያውቁትና የሚፈሩት ስጦታውን ይከለከላሉ?" በእውነቱ ይኼ ከባድ ጥያቄ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ተቀጥታ መኻን እንደሆነችው የሳዖል ልጅ ሜልኮል ተቀጥተው ይሆንን? ይህን እውነት እንዳንል ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም ሆነ በታሪክ በርካታ ጻድቃንና ፈሪኃ እግዚአብሔር ያላቸው ሰዎች ይህን ስጦታ ሳያገኙ እንዳለፉ እናያለን፡፡ እንደውም ከመጽሓፍ ቅዱሶቹ ሴቶች ታሪክም ሆነ እኔ በግሌ ከማውቃቸው በርካታ ያልወለዱ እህቶች ህይወት እንዳየሁት ልጅ ሳይወልዱ የሚቀሩ አማኝ ሴቶች በአብዛኛው መልካም መንፈሳዊ ህይወት ያላቸው እና ይህንን ፈታኝ ሁነት በጸጋ ተቀብለው ለእግዚአብሔር ክብር እየሰጡ እና በነጻነት እያገለገሉ የሚኖሩ ናቸው፡፡ ሌላው የሚያስገርመኝ የአገራችን መሃን ሴቶች ሁኔታ ደግሞ ብዙዎቹ እራሳቸውን በሆነ መንገድ ለሌሎች ወላጅ ላጡ በዝምድናም ሆነ በተለያየ አስገጅ ሁኔታ ሌሎች ልጆችን በወላጆቻቸው እግር ገብተው አሳድገዋል፡፡ ምንም የመውለድን እና የእናትነትን ክብር ምኅበረሰባችን ባያጎናጽፋቸውም፡፡ በእውነቱ ግን እኔ የመሰለኝን ልበል እንጂ ከላይ ያነሳሁትን ጥያቄ መልሱን ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂ፣ የሁሉ ባለቤት፣ በትክክል የሚፈርድና የሚያደርግ አምላክ እንደሆነ ተማምኜ በሚያደርገው ሁሉ ጻድቅ ነው ብዬ ጥያቄውን ብተወው ብዙዎች የሚስማሙ ይመስለኛል፡፡

 

ቀጥዬም የልጅ ስጦታን በትዳራቸው ስላላዩ ፈሪኃ እግዚአብሔር ስላላቸው ብዙ ሰዎችም አሰብኩ፡፡ አንዳንዶችም ጭራሽ ትዳር ያልያዙ ናቸው፡፡ በዚህ ዓይነት ሕይወት ስላለፉ የእግዚአብሔር ሰዎች ሳስብ ሐዋርያው ጳውሎስ እንኳን የልጅን የትዳርንም ወግ እንዳላየ አስታወስኩ፡፡ በእርግጥ እርሱ ስለ ጌታና ስለተሰጠው የወንጌል አደራ ሲል ሁሉን በመተዉ ነው ይባላል፡፡ ታዲያ ወደ ትዳር ዓለም ገብተው በትዳራቸው ጌታን እያስከበሩ ያሉ ሰዎች ለምን በዚህ ነገር ይፈተናሉ? አንዳንዶች ነገሩን በጸጋ ተቀብለው ጌታን እያመሰገኑ ይኖራሉ፡፡ ለዚህም ነገሩ ምሳሌ የሚሆነን አንድ መኖሪያውን በአሜሪካ ያደረገ የሀገራችን መጋቢ ነው፡፡ ይኸው ሰው በቅርቡ ከባለቤቱ ጋር የጋብቻቸውን 25ኛ ዓመት በዓል አክብረዋል፡፡ መጋቢው ይኼን የሚያደርገው የልጅ በረከት ባያገኙም የእርሱና የባለቤቱ ፍቅር እንዲሁም የትዳራቸው ጣዕም ሳይቀንስ ከአገልግሎት እና ከደስታ ህይወት ሳይታቀቡ እዚህ በመድረሳቸው ይኼ ሌሎችን ያስተምራል በሚል መሆኑን ከበዓሉ መከበር በፊት አጫውቶኛል፡፡

 

 

አንዳንዶች ደግሞ በጣም ያዝናሉ፡፡ አንዲት የቅርብ ዘመዴ ትዳር ከያዘች በኋላ ለሰባት ዓመታት ያህል ልጅ አለማግኘቷ ክፉኛ ሲያስጨንቃት እና ሲያስለቅሳት ኖሯል፡፡ የእግዚአብሔር ስም ብሩክ ይሁንና ይህቺ ዘመዴ ከዓመታት በኋላ ሀኪሞች በሙሉ የመውለድ ተስፋ የለሽም ማኅጸንሽ ተበላሽቷል የተባለችበት ሁኔታ በጌታ ኃይል ተለውጦ ሬይንሃርድ ቦንኬ አዋሳ መጥተው ባገለገሉበትና ለመካኖች በጸለዩበት ወቅት ተፈውሳ ዛሬ የሦስት ልጆች እናት ሆናለች፡፡ ይህቺው አክስቴ በመጀመሪያ ልጇ ልደት ላይ ምስክርነቷን ስታቀርብም እንዲህ ብላ ነበር፡፡ ያኔ መውለድ ባልቻልኩበትና ሀኪሞችም ማህጸንሽ ጽንስ መያዝ አይችልም ተበላሽቷል ባሉኝ ጊዜ በመንገድ ላይ የወለደች ውሻ እንኳን ሳይ "ጌታ ሆይ እኔ ከውሻ አንሳለሁ ወይ እያልኩ በጌታ ፊት አለቅስ ነበር፡፡" ብላለች፡፡ ባለቤቴ ምንም መልካም እና እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ቢሆንም አንድ ቀን ጥሎኝ ይሄዳል ብዬ ሁሉ ፈራ ነበር ብላለች፡፡ በእውነቱ ይህ ክስተት ለምን ይፈጠራል ብሎ መጠየቅ ከባድ ነው፡፡ በሰማይና በምድር፣ በባህርና በየብስ የወደደውን የሚያደርገውን እግዚአብሔር አምላክን ለምን እንዲህ አደረግክ? ብሎ መጠየቅ አይቻልምና፡፡

 

ይኼን ሃሳብ በማሰብ በዚህ ነገር ለመጨነቅ ጊዜና ዘመናትን ማባከንም ተገቢ መስሎ አይታየኘም፡፡ ይልቁንም ከእግዚአብሔር ጋር ተስማምቶ እርሱ በዚህ አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ከሚያልፉ ጋር አብሮ በሁኔታዎቹ ውስጥ እንዲገኝ መልካም ምክር እየመከረ እንዲያጽናና እንዲያበረታ መጋበዙ የተሻለ ነው፡፡ ምክንያቱም እንደ እርሱ ያለ ድንቅ መካር የትም አይገኝምና፡፡

 

በእኔ እይታ የእግዚአብሔር ስጦታ የሆኑት ልጆች የግድ በመወለድ ብቻ ይገኛሉ ብዬም አላምንም፡፡ አንዳንዶች አደራ የተባሏቸውን፤ የሙት ዘመዶቻቸውን ልጆች ከገዛ ልጆቻቸው በላይ ወደውና ተንከባክበው አሳድገው ለፍሬ አብቅተዋል፡፡ በዚህም የራሳቸውን የእናትነት ወግ የአባትነት መሻት አሟልተው ከእግዚአብሔር እንደተቀበሉት ስጦታ ለፍሬ አብቅተው ለራሳቸውም ላሰደጓቸው ልጆቻቸውም ሀሴትን ፈጥረዋል፡፡

 

አንዳንዶችም እግዚብሔር የግድ ልጅን ከሚስታቸው ማህጸን ወደ ክንዳቸው (እቅፋቸው) እንዲያሻግር ሳይጠብቁ፤ በመንገድ ዳር ተጥሎ ብርድ የሚያንሰፈስፈውን ህጻን ወደ ሞቀ ቤታቸው ሰብስበው በአማረ የስጦታ ወረቀት ያልተጠቀለለውን ግን ታላቁንና ታላቅ ዋጋም ያለውን ስጦታ አግኝተዋል፡፡ አንዳንዶች ቤት ሰዎች የራሳቸውን ልጅ መውለድ የማይችሉት ምናልባት በበራፋቸው እና በዙሪያቸው የሞሉትን ወላጅ አልባ ወይም ወላጆቻቸው ሊያሳድጓቸው የማይችሉትን ልጆች እንዲያሳድጉ እግዚአብሔር የከበረ አደራውን ሊሰጣቸው ወዶ ይሆናል፡፡

 

 

የአንድ ሌላ የሩቅ አጎቴን ታሪክ ላንሳ (አጎት ብሎ የሩቅ አለ ወይ አትበሉኝና)፡፡ ይህ አጎቴ እና ሚስቱ እርሱ ኢንጂነር እርሷም እንዲሁ የተማረች እና ጥሩ ስራ ያላት የዘነጠ ቤት እና መኪና ያላቸው ቢሆኑም ልጅ መውለድ ግን አልቻሉም፡፡ ለረጅም ጊዜ በጉዳዩ ላይ እንደ እምነታቸው (አጎቴ እና ሚስቱ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡) ሲጸልዩ እና እግዚአብሔር የሚያደርገውን ሲጠብቁ ቆዩ፡፡ በኋላ ግን ነገሩ የእግዚእብሔር ፈቃድ ነው ብለው አንዲት ፍቅር ብለው የሰየሟትን በጣም የምታምር ልጅ በጉዲ ፈቻ ወስደው (adopt) አድርገው ማሳደግ ጀመሩ፡፡ ፍቅር ጭር ብሎ የነበረውን የአጎቴን የተንጣለለ ቪላ የእውነትም ፍቅር እና ደስታ ዘራችበት፡፡ ፍቅር እንዳየናት በጣም የምታምር አሳዳጊ አጥታ የነበረች ልጅ ናት፡፡ ምናልባት አጎቴ እና ሚስቱ ባይወስዷት እጣ ፈንታዋ ጎዳና ወይም ከዛ የከፋ ሊሆን ይችል ነበር፡፡ አጎቴ እና ባለቤቱ ምንም መልካሞች እና ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላቸው ቢሆኑም ልጅ ቢወልዱ ኖሮ ፍቅርን ጨምረው ያሳድጉ ነበር ብዬ አላስብም፡፡ (እናንተም ሳትስማሙ አትቀሩም፤ ይሄን ለመገመትም ጥሩ ጠርጣሪ መሆን የሚያስፈልገውም አይመስለኝም፡፡) ታዲያ ማን ያውቃል ፍቅርን ከአጎቴ እና ሚስቱ እኩል የሚወደው ሁሉን ቻዩ የፍቅር ፈጣሪ እና አምላክ በዚህ መንገድ ፍቅርን እና ያንን ቤተሰብ አጣምሮ ቢሆንስ?

 

 

ለዚህ ተጨማሪ ማስረጃ የሚሆነንም እግዚአብሔር ህይወታቸውን በብዙ የባረከው ለልጆቻቸው የሚያበሉት እና የሚያወርሱት የተረፋቸው አንዳንድ የውጪ ዜጎች የሚያደርጉት ተግባር ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ ከጌታ እንደተሰጠ አደራ ቆጥረው ለራሳቸው ቢፈልጉትም ግን ጌታ ደስ የሚሰኘው በዚህ አይደለም ብለው መውለድ እየቻሉ አንድም ልጅ ሳይወልዱ የጉዲ ፈቻ ልጅ ከአፍሪካ እና ከሌላ ደሃ አገሮች እየወሰዱ ያሳድጋሉ፡፡ ያንን የሚያሳሳ ሃብትም ያወርሳሉ፡፡ በዚህ መልኩ እስከ ስድስት የሚደርሱ የጉዲፈቻ ልጆችን የሚያሳድጉ እግዚአብሔርን የሚፈሩ እና የሚታዘዙ ቤተሰቦችን ምስክርነትም ሰምቻለሁ፡፡ ታዋቂዋ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ ኦፕራ ዊንፍሬይም ያላትን እንኳን መንዝረው ቆጥረው የማይጨርሱትን ዶላር ለአንዲት ከአፍሪካ በጉዲ ፈቻ ለወሰደቻት ልጅ እንደምታወርስ መናገሯን ሰምቻለሁ፡፡

 

 

ለማንኛውም የአብራክ ክፋይን ለማግኘት አለመታደል አሳዛኝ ቢሆንም ይህንን ሁነት በእግዚአብሔር ላይ ያለንን ፍጹም እምነት እና ጽናት ብሎም መልካም እንድናደርግበት እንደተፈጠረ አጋጣሚ ቆጥረን መልካም አድርገንበት ብናልፍ ከሁሉ ይበልጣል ዘ ለ አ ለ ማ ዊ ነው በምንለው ህይወት ተመስጋኞች ‹‹አንተ/ አንቺ ታማኝ ባሪያ›› የምንባልበት እንዲሆን ማድረግ እንችላለን፡፡      

 

በስተመጨረሻም ከሁሉም የላቀው የልጅ ስጦታን መቀበል ግን የሚከተለው ይመስለኛል፡፡ ብዙዎች ከባል ወይም ከሚስት ጋር ባለ ኅብረት ከሚገኝ ልጅ በላይ ከክርስቶስ ጋር በፈጠሩት ኅብረት እና ውኅደት የሚያገኙአቸውን በጌታ የወለዷቸውን ታላቅ ስጦታና መክሊቶች የሆኑ ልጆች በማሳደግ እጅግ ይባረካሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ጌታ በመልካም መሬት ላይ እንደ ወደቀችው ዘር አድርጓቸው ሠላሳ፣ ስድሳ፣ መቶ ፍሬ በማፍራታቸው ያመሰግናሉ፡፡ አደራውንም ተወጥተው እነዚህኑ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ያገኟቸውን ስጦታዎች እንደገና ለፍሬ እንዲበቁ ያደርጋሉ፡፡ አንዳንዶችም ‹‹በጌታ ልጄ ነው! እኔ ነኝ በጌታ ቤት ያሳደግኳት!›› እያሉ በኩራት ሲናገሩ የሚሰማው፡፡ ይህ እውነት ከሆነ በጌታ ልጆችን የወለዱ ታላቅ በረከት ይጠብቃቸዋል፡፡ እኚህ መሰሎቹን ልጆች ያበዙትማ ዋጋቸው የላቀ መሆኑ እንዲህ ተገጿል፡፡ ጥበበኞቹም እንደ ሰማይ ፀዳል፥ ብዙ ሰዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት ለዘላለም ይደምቃሉ። (ዳን. 12፡3)

 

 

እንግዲህ ይህችን አነስተኛ ጽሐፍ ሳጠቃልል ከላይ ለመዘርዘር የሞከርኳቸው ሁሉ የህያው እግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው፡፡ ምናልባትም እኔ በዝንጋኤ ያጎደልኩት ካለ አንባቢ ሊጨምርበት ይችላ፡፡ ስለዚህም በእውነት እግዚአብሔርን የሚያውቅ እግዚአብሔርን በጽናት የሚጠብቅ ከእነዚህ ስጦታዎች ቢያንስ አንዱን እንደሚያገኝ አልጠራጠርም፡፡ ስለዚህም ከክቡር ስጦታው የሚጎድልበት የለም፡፡ 

Read 50773 times Last modified on Friday, 31 July 2015 07:15
Temesgen Sahle

Communication and Literature Department Head at Ethiopian Kale Heywet Church,
Studied MA in Literature 
PGD in Theology
A proud husband of one wife and father of two daughters.
  

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Most Read

ከእግዚአብሔር ጋር የሚሠራ...

Written bySolomon Abebe Gebremedhin

It is Okay not t...

Written byMeskerem T. Kifetew, PharmD

Lust On a Driver...

Written byMeskerem T. Kifetew, PharmD

የአገር ያለህ!...

Written byNegussie Bulcha

 

 

 

.

Right Now

We have 32 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.