You are here: HomeSocial Issues እባክህ አሁን አድን፥ እባክህ አሁን አቅና፤ ሆሣዕና

እባክህ አሁን አድን፥ እባክህ አሁን አቅና፤ ሆሣዕና

Written by  Friday, 22 April 2016 21:00

ሆሣዕና፤ እነሆ፥ የዐቢይ ጾም ስምንተኛ ሳምንትና የሕማማት ሳምንት ፤ እንኳን አደረሳችሁ።

 

ሆሣዕና የዕብራይስጥ ቃል ሲኾን፥ ትርጓሜውም “እባክህ አሁን አድን፥ እባክህ አሁን እርዳ” እንደ ማለት ነው። የኀጢአት ዋጋ የኾነው ሞትና ኵነኔ ካስከተለበት የሕይወት መነፈግ የተነሣ የተሠቃየው የሰው ልጅ ረዳትና መድኅን አስፈልጎት ነበር። ሰው ወደ ራሱ የጽድቅ መፍጨርጨር፣ ጥረት፣ ጥበብና ኀይል ቢመለከት ተስፋ አልነበረውም፤ “የሰውም ማዳን ከንቱ ነው” (መዝ. ፻፰፥፲፪)። ይኸን የአድነኝ፣ የታደገኝ፣ የድረስልኝ ሕቅታውን ወደ ሰማይ እንጂ ወደየትስ ይልክ ዘንድ ይችል ነበር? ስለ ኾነም፣ ቃሉ የመጣላቸው፣ በምሕረቱ ባለጠጋ የኾነው አምላክ፥ እንደ ተስፋ ቃሉ፥ በማዳኑ እንዲገለጥ ሲማጠኑ ኖረዋል። “አቤቱ፥ ማረን አንተን ተማምነናል፤ ጥዋት ጥዋት ክንድ በመከራም ጊዜ ማዳን ኹነን” (ኢሳ. ፴፫፥፪) ይሉ ነበር። “ማዳን የእግዚአብሔር ነውና” (መዝ. ፫፥፰)፥ ነቢያቱ ለሕዝቡም ጥሪያቸውን አቀረቡ፤ “ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረት፥ በእርሱም ዘንድ ብዙ ማዳን ነውና እስራኤል በእግዚአብሔር ይታመን” (መዝ. ፻፴፥፯) አሉ። ዐይናቸው ወደ የትኛውም ፍጥረት መዳንን ፍለጋ ተስፋ እንዳያደርግ ማስጠንቀቅን ችላ አይሉም ነበር፤ “ማዳን በማይችሉ በሰው ልጆችና በአለቆች አትታመኑ” (መዝ. ፻፵፮፥፫) በማለት ወትውተዋል።

 

እንግዲህ “ሆሣዕና” ከዚህ የትድግናና ድኅነት ጥሪ የመነጨ ሐሳብ ነው። እግዚአብሔር በሰጠው ተስፋ መሠረት፥ የመሐሪው አምላክ ታዳጊነት እንዲገለጥ የቀረበ የእርዳንና አድነን ጩኸትን አጣምሮ የያዘ ወካይ ቃል ነው — ሆሣዕና። ንጉሥ ዳዊት ከዘመናት በፊት በመንፈስ ተመርቶ በዚሁ ቃል እግዚአብሔርን ሲማጠን በማህሌቱ ውስጥ አንብበናል፤ “አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አድን፤ አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አቅና” (መዝ ፻፲፰፥፳፭) በማለት።

 

በቅዱሳን ነቢያት በኩል የተነገሩትን የእግዚአብሔር መሲሐዊ ተስፋዎች ለማግኘት ቀደምት አባቶችና እናቶች በጸሎትና ልመና ሲማጸኑ መኖራቸውን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ። የድኅነት ተስፋው መካከለኛ እውነት አስቀድሞ ትንቢት የተነገረለት የመሲሑ መገለጥ ነበር። በዚሁም መሠረት፣ ተስፋውን ከተናገሩ ነቢያት መካከል አንዱ፣ ነቢዩ ዘካርያስ የነገሥታት ንጉሥ የኾነው መሲሕ በትሕትና ዝቅ ብሎ እንደሚመጣ አስቀድሞ በመንፈስ አመለከተ፤ “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ። እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው። ትሑትም ኾኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል” (ዘካ ፱፥፱ )።

 

የነገሥታት ንጉሥና የመላለሙ ጌታ ራሱን ዝቅ አድርጎ ወደ ሰው መውረዱ ሳያንስ፣ በድል አድራጊ ንጉሣዊ ክብሩ ለመግባት በአህያ ውርንጫ ጀርባ መቀመጥን መረጠ። ይህ ክብር ምን ይደንቅ? ይህስ ምሥጢር ምን ይረቅ? እንግዲህ፣ የበዓለ ሆሣዕና ዐቢይ ሐሳብ በዚህ ታሪካዊ ክዋኔ ላይ ያረፈ ነው። እኛን ለማዳን “ከዘላለም ዘመናት በፊት ተስፋ የሰጠው” (ቲቶ. ፩፥፩-፪) የማይዋሽ እግዚአብሔር እኛን ለማዳንና ለመታደግ በማንምና በምንም አልታመነም፤ “የገዛ ክንዱ መድኃኒት አመጣለት፥ ጽድቁም አገዘው” (ኢሳ. ፶፱፥፲፮) እንጂ።

 

እነሆ፥ የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ፣ የትንቢቱ ቃል ሞላ፤ ተስፋው ተፈጸመ። አካላዊ ቃል በሥጋ ተገለጠ። አምላክ ሰው ኾነ (ዮሐ. ፩፥፩-፬)። የዘላለም ንጉሥ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለዘርዓ ብእሲ ተፀንሶ ተወለደ (ሉቃ. ፩፥፳፮-፴፭፤ ፪፥፯)። ጸጋንና እውነትን ተመልቶ በመካከላችን አደረ (ዮሐ. ፩፥፲፬)። ለእግዚአብሔር ክብር፥ ለሰው ልጅ ሰላም፥ ለምድርም በጎ ሥምረት እንዲኾን የምሥራች ታወጀ (ሉቃ. ፪፥፲፬)።

 

ይመጡ ዘንድ የተጠበቁት መሲሐዊ ተስፋዎች ሁሉ በናዝሬቱ ኢየሱስ ሕይወትና ሥራዎች “አሜን” (አዎን) ኾኑ (፪ቆሮ. ፩፥፳)። ትንቢት ሞላ፤ ተስፋ ተፈጸመ፤ እግዚአብሔር ዓለሙን ለማዳን ወደ ሰው ወረደ። ሰማይና ምድር ታረቁ። እግዚአብሔር በጸጋው አሠራር፣ በኀይሉ ታላቅነትና በጥበቡ ጥልቀት ለሙታን ሕይወትን ለመስጠት በጨለማው ዓለም ላይ አበራ። ጨለማም አላሸነፈውም፥ ሊያውቀውም አልተቻለውም (ዮሐ. ፩፥፭)። ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለድኾች ወንጌልን እየሰበከ፥ የተጠቁትን ነጻ እያወጣ፥ የታሠሩትን እየፈታ… የተወደደችውን የጌታ ዓመት ገለጣት፣ ዐወጃት፣ ሰበካትም (ሉቃ. ፬፥፲፯-፲፱)። “እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ በኀይልም ቀባው፥ እርሱም መልካም እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ” (ሐዋ. ፲፥፴፰)። የመንግሥቱን መምጣት ዐወጀ (ማቴ. ፬፥፲፯፤ ሉቃ. ፲፯፥፳፩)። የምድራዊ አገልግሎቱ መደምደሚያ ከኾነው የመስቀል ላይ ሞቱ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎም የሆሣዕና ተስፋን ፈጸመ።

 

እነሆ፥ ዘካርያስ እንደ ተነበየው፥ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ በንጉሣዊ ድል ወደ ኢየሩሳሌም ገባ። በዚያ የነበሩት ሕዝብ የዘንባባ ዝንጣፊዎች ይዘውና ልብሶቻቸውን በሚያልፍበት መንገድ ላይ ጐዝጕዘው “ሆሣዕና በአርያም” ብለው በዝማሬ ተቀበሉት፤ በመሲሐዊ ማዕረጉ “የዳዊት ልጅ” ተብሎ የተጠራው ጌታ በንጉሣዊ አጀብ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ። “የሚቀድሙትም ሕዝብ የሚከተሉትም፦ ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር” (ማቴ ፳፩፥፱)። እነሆ፥ በቀደምት አበው የተነገረው የተስፋ ቃል ፍጻሜ አገኘ። ያድነን ይረዳን ዘንድ አምላክ ወደ እኛ ወረደ።

 

ሊቁ ጎርጎርዮስ፣ በቅዳሴው እንዳመሰጠረው፥ “የካህናት አለቃ ወደ መጋረጃ ውስጥ በገባ ጊዜ በጸሎት ቤት የተደረገውን ድንቅ ነገር ታዩ ዘንድ፥ ኑ። ሁሉም መለኮትን የምትሸሽግ ሕሊናትንም የምትሰውር ናት ይሏታል። የአጋዕዝትና የመናፍስት ጌታ በተዋረደ አህያ ውርንጫ ተቀምጦ ገባ። በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው። ‘አንተም የአማልክት የእስራኤልም ንጉሥ እግዚአብሔር ቡሩክ ነህ’ እያሉ ለሚያመሰግኑ ሕፃናት ሁሉ ጌትነቱን አሳየ። ከመድኀኒትነቱ የተነሣ ከቤቱ መሠረት ሳይናወጥ ከልዑል መንበሩ ወርዶ ጸጋንና ኀይልን አሳየ።” ንጉሠ ነገሥቱ የዘላለም አምላክ ወደ ኢየሩሳሌም በትሕትና ገባ።

 

ይሁን እንጂ፥ ኢየሩሳሌም ለሆሣዕና አልተዘጋጀችም ነበር። ሕይወቷን በዐመፃ አጥለቅልቃ፣ መቅደሱን ወደ ወንበዴዎች ዋሻነት ለውጣ ነበር። የተስፋው ቃል ተፈጽሞ እግዚአብሔር በሰው ፊት ያዘጋጀውን ማዳን በዐይናቸው ያዩ ሁሉ ምላሻቸው ተመሳሳይ አልኾነም። ጊዜው ደርሶ መድኅኑ በመካከላቸው ሲገኝ እነርሱ በጠበቁት መንገድ ሳይኾን፣ “የዋሕና ትሑት ኾኖ” የመጣውን ጌታ ለመቀበል ተቸገሩ (ዮሐ. ፩፥፲፩-፲፪)። የተስፋውን ቃል እያሰቡ ስለሚመጣው ንጉሥ ሲናገሩና መጽሐፍትን ሲመረምሩ ቢኖሩም በሕይወታቸው ሳያነግሡት ቀሩ። “የካህናት አለቆችና ጻፎች ያደረገውን ድንቃ ድንቅ በመቅደስም፦ ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ፥ ተቈጥተው” (ማቴ. ፳፩፥) ተቃወሙ። በዚህም አላበቁም፤ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሕዝቡን አስተባብረው መሲሑን ለመግደል መስቀል ይዘው በአድማ ወጡ፤ አመጣጡ ጥያቄ ኾኖባቸው ነበርና። ያ ትውልድ መድኅኑን ጥሎ፥ ባህሉን አንጠልጥሎ፥ ክፉኛ ወደቀ። ጥያቄውን በአግባቡ ስላልመለሰ፥ በመከራ ወጥመድ ተሰነከለ።

 

ዛሬም እኛ ስለ እርሱ እንጠየቃለን። ጌታ ኢየሱስ የሰው ልብ ወይ ከዚህ ወይ ከዚያ የተንጠለጠለበት ጥያቄ ኾኗል። ገና በጠዋቱ ተቃዋሚዎቹ “እርሱን ከበውት ‘እስከ መቼ ልባችንን አንጠልጥለህ ታቈየናለህ?’” (ዮሐ. ፲፥፳፬ ዐመት) “ለመኾኑ አንተ ማን ነህ?” (ዮሐ. ፰፥፳፭ ዐመት) “እነዚህን በምን ሥልጣን ታደርጋለህ” (ማር. ፲፩፥፳፰-፳፱) በማለት ሲጨነቁ ቈይተዋል። ልደቱ ቤተ መንግሥት አናውጧል፤ ቤተ ክህነት በጥብጧል፤ እረኞችን በደስታ አስደንግጧል፤ ሰማይና ምድርን በአንድነት አስዘምሯል (ማቴ. ፪፤ ሉቃ. ፪)። መች ይኸ ብቻ፤ “በሕዝብም መካከል ስለ እርሱ ብዙ ማንጐራጐር ነበረ፤ አንዳንዱም፦ ደግ ሰው ነው፤ ሌሎች ግን፦ አይደለም፥ ሕዝቡን ግን ያስታል ይሉ ነበር” (ዮሐ. ፯፥፲፪)። ገሚሱ በደግነቱ ሲያምን ገሚሱ እንደ “አሳች” ፈረጀው (ማቴ. ፳፯፥፷፫)።

 

ከታላላቅ የእምነት ተቋማት ጀምሮ እስከ ትንንሽ ቡድኖች ድረስ በተለያየ መንገድ ስሙ ተጠርቶአል። ሃይማኖተኞች፥ ጦረኞች፥ ጠቢባን፥ ዐዋቆች፥ ጸሓፍት፥ ድኾች፥ ሃብታሞች ወዘተ. እርሱን በሚመለከት ዐቋም ይዘዋል። የሃይማኖት ምሁራን፥ ፈላስፎች፥ አሰላሳዮች፥ አርቲስቶች፥ ጠቢባን፥ የታሪክ ተመራማሪዎችና ፖለቲከኞች፥ የቻሉትን ያህል፥ በትምህርቱና በሕይወቱ ተመስጠዋል። ፍተሻው ዛሬም መቋጫ አላገኘም። ከአይሁድ ጀምሮ እስከ ለየላቸው አረማውያን ድረስ በእርሱ ጕዳይ ተሟግተዋል። ጽፈውለታል፥ ጽፈውበታልም። እኔና እናንተም አለንበት።

 

ኢየሩሳሌም በልደቱ እንደታወከች ሁሉ (ማቴ. ፪፥፫) በንጉሣዊ አገባቡም “ይህ ማነው?” ስትል ተናውጣለች (ዮሐ. ፳፩፥፲)። ጥያቄው ለእኔና ለእናንተም ቀርቦልናል። እርሱ ለእኛ ማንነው? ሆሣዕና፥ አሁን አድን በማለት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን አምላካችንና ንጉሣችን አድርገን እንቀበለዋለን? ወይስ ከነቃፊዎቹና ከሚጠሉት ጋር እንተባበራለን? እርሱን ብቻ የሕይወታችን አለኝታ፣ ጌታና መድኀኒት እናደርገዋለን? ወይስ በሌሎች ፍጡራንና ምድራዊ ነገሮች ልባችንን እናስማርከለን።

 

በሆሣዕና ዝማሬ፣ ጩኸትና አጀብ የተከፉት የካህናት አለቆችና ጻፎች ባስተባበሩት ኹካታ እየተነዳ የሰው ልጅ ለመሲሑ ያዘጋጀው “ከፍታ” የመስቀል እንጨት ነበረ፤ በዘረጋው የፍቅር እጁ ላይም ችንካር አኖረበት። ንፉጉ ዓለም፥ ክፉውም የሰው ልብ የእግዚአብሔርን ልጅ በጭካኔ ሰቀለ። ሊቤዠው የወረደለትና የተዋረደለትን መድኅን በክፋት ገደለ፤ ቀበረም። የተቀበረውም በተውሶ መቃብር ነበረ (ማቴ. ፳፯፥፷)።

 

ኢየሱስ ለጨለመባቸው “ግንበኞች የናቁት ድንጋይ” (ሉቃ. ፳፥፲፯) ተብሏል። ለበራላቸው ግን ሕይወታቸው የሚድንበትና የሚጸናበት “የማዕዘን ራስ ድንጋይ” (ኢሳ. ፳፰፥፲፮፤ ማቴ. ፳፩፥፵፪፤ ሐዋ. ፬፥፲፩) ይኾንላቸዋል። የሰላሟን ጌታ የገፋችው ኢየሩሳሌም ቅጥሯቿ ፈራርሰው ወደቀች፤ የሕይወትን ራስ ስለ ጣለች ሕዝቦቿ ታረዱ፤ ንጉሧን አቃልላ አባራለችና ልጆቿ በሰይፍ ስለት ወደቁ። እኔና እርስዎ የትኛው ወገን ነን? ክብሩ ለሚያምኑበት ነው፤ የሚጥሉት ግን ተሰነካክለው ይወድቁበታል፤ ይፈጠፈጡበታል፤ ወይም ይፈጩበታል፤ ወዮታቸውም ማብቂያ የለውም (ሉቃ. ፳፥፲፰)።

 

“በመጽሐፍ፦ እነሆ፥ የተመረጠና የከበረን የማዕዘን ራስ ድንጋይ በጽዮን አኖራለሁ። በእርሱም የሚያምን አያፍርም ተብሎ ተጽፎአልና። እንግዲህ ክብሩ ለእናንተ ለምታምኑት ነው፤ ለማያምኑ ግን አናጢዎች የጣሉት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ የዕንቅፋትም ድንጋይ የማሰናከያም ዓለት ኾነ” (፩ጴጥ. ፪፥፮-፯) እንደ ተባለው ነው። መዳናችንን በመከራ ይፈጽም ዘንድ ዝቅ ብሎ የመጣው (ዕብ. ፪፥፲) የዋሑና ትሑቱ ንጉሥ የምስጋና ዘውድ ጭኖ፣ የጌትነቱን መንበር ይዞ ክብርና ታላቅ መለኮታዊ ኀይል ተላብሶ ይገለጣል። የእሾኽ አክሊል ደፍቶ በመስቀል ላይ የተዘናበለው ራስ የክብርና ዘላለማዊ ግርማ አክሊል ተጭኖ እናየዋለን። ሆሣዕናችን ወደዚያ ይጣራል።

 

አሜን፥ እባክህ ሕይወቴን አሁን አድን፣ እባክህ አሁን አቅና፤ እኔም እላለሁ ሆሣዕና። ሆሣዕና በአርያም! ሃሌ ሉያ!

 

በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሳናምንና በእርሱም አለኝታን ተቀብለን ከእግዚአብሔር ጋር ሳንታረቅ “ሆሣዕና”ን ብናከብር ከዐመታዊ ዘመን መቍጠሪያነት የተለየ አይኾንልንም። በልባችን ያልነገሠውን ጌታ እንዴት እናመሰግነዋለን? ያላመንነውን እንዴት እንጠራዋለን?

 

በተጨማሪም፣ በክርስቶስ ክርስቲያን ኾነናል የምንል ሁላችን የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ በመከተል በትሕትናችን የሌሎች ብርሃን እንሁን። በጭንቅላታችን የዘንባባና ቀጤማ ዝንጣፊ እንደ አክሊል ማሰራችን፣ በየደጃፋችን ለምለም ሣር ቅጠሉን ማኖራችን፣ የዘንባባ ቀለበት ሠርተን በጣቶቻችን ማሰራችን ስሕተት ባይኾንም፣ ሕይወታችንና አኗኗራችን ግን በክርስቶስ ድኅነት እንደ ተቀበሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች የወንጌልን እውነት የሚመስል መኾን አለበት። ሕይወት ከበዓልም በላይ ነውና።

 

ስብሐት ወክብር ይደልዎ ለእግዚአብሔር፤ አሜን።

Read 7458 times Last modified on Monday, 10 April 2017 08:03
Solomon Abebe Gebremedhin

ከሁለት ደርዘን ዓመታት በፊት በእግዚአብሔር ቸርነት በተሐድሶ የወንጌል አገልግሎት ውስጥ የዳግም ልደት ብርሃንን ያየው ሰሎሞን አበበ መጋቤ ወንጌል ሲኾን በኢቫንጀሊካል ቲዎሎጂካል ኮሌጅ  (ETC) እና በኢትዮጵያ ድኅረ ምረቃ ነገረ መለኮት ት/ቤት (EGST) የቅዱሳት መጻሕፍት መምህር ነው፤ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ምስባኮች በመስበክም ይታወቃል። ሰሎሞን ባለትዳርና የሁለት ሴቶች ልጆች አባት ነው።

Website: solomonabebe.blogspot.com Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 30 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.