You are here: HomeOpinions“ከፍታው”ን ስናሳድድ “ዝቅታው”ን እንዳንረሳ

“ከፍታው”ን ስናሳድድ “ዝቅታው”ን እንዳንረሳ Featured

Written by  Tuesday, 12 September 2017 04:39

የ“ከፍታ” ተስፋ ያነገበው ሰሞነኛው አገራዊ መሪ ቃል ኹለት ነገር አስታውሶኝ ነበር።

 

አንደኛው ትውስታዬ፥ “የከፍታ ዘመን ለኢትዮጵያ” የተባለውና በሦስት ዐሠርት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ [እና ኤርትራ?] ስለሚከሠቱ ነገሮች የሚዘረዝረው የቄስ በልእና ሳርካ ትንቢታዊ ንግር ነው። ታወሰኝ ስላችሁ ራእዩ እውነት ነው ወይም ስሕተት ነው ለማለት አይደለም። መባሉን ብቻ ነው ያስታወሰኝ። “የከፍታ ዘመን ለኢትዮጵያ”።

 

ኹለተኛው፥ ትዝ ያለኝ ነገር፥ ደራሲ እንዳለ ጌታ ከበደ ከጥቂት ዓመታት በፊት በአንድ የግል ጋዜጣ (መጽሔት) ላይ በትንቢቱ መጽሐፍ ላይ የሠራው ሐተታና ሒስ ነው። ጸሐፊው የመጽሐፉን ሐሳብ በዐጭሩ ከዳሰሰ በኋላ፥ በመደምደሚያው ላይ ኰርኳሪ ጥያቄ ቸንክሮ ነበር የዘጋው። ጥያቄውም፥ የተባለውን “የከፍታ” ራእይ “ቄሱ አይተውታል? ወይስ እንዲያዩት ተደርገዋል?” የሚል ነበር። ጥያቄው የአንድ ሚሊየንም… የአንድ ትሪሊየንም … ዋጋ ያለው ቢኾን እንኳ፥ እኔ በበኩሌ መልሱን አላውቀውም። መልሱ የሚገኘው በእግዚአብሔር ዘንድ ነው። ዞሮ ዞሮ፥ ኹሉንም ጊዜ ነው የሚፈታው።

 

አኹን ደግሞ ሐሳቡን አገራዊ መሪ ቃል ውስጥ ብናገኘው ከግራ ከቀኝ የተለያዩ ሐሳቦች ሲሠነዘሩ እያየንና እየሰማን ነው። “መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ከፍታ ነው” ብሏልና። የኾነ ኾኖ፥ መሪ ቃሉን ወድጀዋለሁ። የአገሩን ከፍታ የሚጠላ ሰው ወይ ክፉ ነው፤ ወይ ባንዳ ነው። በጎ መመኘትን ማን ይጠላል? በኾነልንና የተባለው “ከፍታ” መሬት ወርዶ ባየነው ያሰኛል። ቀና ቀናውን ማሰብ ምን ይገርማል? የሚገርመው፥ መፈክሩን ከሰሙ በኋላ “ጌታ የተናገረው ደረሰ” በማለት “ኧረ፥ እሰይ ስለቴ ሠመረ” ያሰኛቸው ወገኖች በደስታ ሢቃ ሲቦርቁ መታየታቸው ነው። ይኸን የምለው፥ የውጭውን ትቼ፥ የወንጌል ማኅበርተኛ ነኝ ስለሚለው ወገን ብቻ መናገር ስለሚገባኝ ነው። ስለ ከፍታና የከፍታ ዘመን …

************************************

ርግጥ ነው፥ በዘመቻም በኩንፈሳም “የከፍታውን” ዐዋጅ ተላምደነዋል። “ከፍ” ስለማለታችን በጽሑፉም፥ በስብከቱም፥ በትንቢቱም፥ በመዝሙሩም … ኮምኩመናል። የቢኾን ዓለማችን ውስጥ የኾነ “ከፍታ” እንደሚገኝ ተነግሮናል፤ እየተነገረንም አለ። ከፍታውን እንጂ ይዘቱን ባናውቀውም እንኳ በያወጣው ያውጣው እየተራመድን እንገኛለን። ይመጣ ዘንድ የሚጠበቀው “ታላቁ ሪቫይቫል” እንኳ በብዙ ጐኑ ሲተረጐም የምንሰማው ይኸንኑ የኾነ “ከፍታ” ያመጣል በሚለው አንደምታው በኩል ከባድ ሚዛን ተሸክሞ ነው።

 

“ከፍታው” ተሰብኮለታል፤ ተዘምሮለታል፤ ተተንብዮለታልም። ነገሩ ሃይማኖታዊም ፖለቲካዊም ደርዝ እየተበጀለት እስቲበቃን ድረስ ተግተናል። የዓለም ጭራ ብንኾንም፥ አንዳንድ “መልእክተኞቻችን” እግዚአብሔር የመላ ዓለሙን አሰላለፍ ለመለወጥ፥ “በቅርቡ ቀኝ-ኋላ-ዙር ያዛል” እያሉ ሲያሳክሩን ከርመዋል። አሳዛኙ ጕድ፥ እኛ እንድንቀድም ሌላው ዓለም የግድ ወደ ኋላ እንዲሽቀነጠር የሚያምረን መኾኑ ነው። የእነዚህ ወገኖች ምኞት እግዚአብሔር ዓለሙን ያለ መርሕና እውነት የሚያስተዳድር አስመስሎታል። (ግብጽ “የአረቡ ጸደይ” ተብሎ ይቈላመጥ በነበረው ሕዝባዊ ዐመፅ ትናጥ በነበረበት ሰሞን፥ ለአገልግሎት በተጋበዝሁበት በአንዲት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ተገኝቼ ሳለሁ፥ ለጸሎት መድረክ ላይ የወጡ አንድ መሪ፥ “ዐባያችንን እንድንገድብ እግዚአብሔር ለባላንጦቻችን የቤት ሥራ ሰጠልን” እያሉ የምስጋና አጀብ ከጉባኤው ሲጠይቁ እንደ ሰማሁት ዐይነት መኾኑ ነው።) በትክክለኛ መጽሐፍ ቅዱሳዊና ክርስቲያናዊ ንጽረተ ዓለም ያልተቃኘና ያልተዳኘ አስተሳሰብ ሲዛብር መኖሩ አይቀርም።

 

እንግዲህ “ከፍታውን” የቀየድንበት መሠረታዊ ቢጋር ግልጽ ያለመኾኑ ብቻ ሳይኾን፥ ከቤተ ክርስቲያን ዐቢይ ተልዕኮና ሚና ባፈነገጠ መልኩ ስለ ተሰጠ፥ ከፍታውን በየምኞታችን መሥፈሪያ ተርጕመን የልባችንን ክጀላ ልናስታግሥበት ይዳዳናል። ትልቅ መኾን ያስመኘናል፤ ዐናት ላይ መፈናጠጥ ያስጐመጀናል። የተከፈተ በመሰለን በር ኹሉ መግባት ያስመኘናል። ጭብጨባ ይማርከናል። ጭብጨባ የእውነትንና የእምነትን ሚዛን ማዘናበሉን ኹሉ ከዘነጋን ቈይተናል። ቢኾን ነው እንጂ፥ በዐምስት የተደራጀ የነቢያት ሴኔት በአገራዊ ምክር ቤት መመሪያ ሰጪ ለመኾን ለተጐመዠበት የምኞት መቃተት በሺ የሚቈጠር ክርስቲያን ክንዱ እስኪዝል ሲያጨበጭብ መታየት ነበረበት?

 

ታስታውሱ እንደ ኾነ፥ ከጥቂት ዓመታት በፊት፥ “ጎልድ ኮስት” በሚባል የንግድ-ድር ድኻ በጠራራ ፀሓይ ሲዘረፍ፥ “እግዚአብሔር ኢትዮጵያን የሚባርክበት የከፍታ ዘመን መጣ” በማለት ያለ ኀፍረት የሚቀባጥሩ ሰባክያን ነበሩ። “እኔ ከተማውን ስረግጥ አገሪቱ ላይ ዝናብ ዘነበ” ያሉንን አይተናል። … ብዙ ብዙ ምሳሌ ማቅረብ ይቻላል። ዐዲስ ዓመት በመጣ ቍጥር ለዘመኑ ስም እያወጣን በምኞት ስንዳክር ይኸው እንደ ተኰረኰድን ቀርተናል። … ፈርዶብናልና፥ በሽታውን ትተን ምልክቶቹን ለማከም ስንታገል እንገኛለን። በአጠቃላይ፥ ሐሳቡን ቀድሞውኑ እስኪያጥወለውለን ድረስ ስለተጋትነው፥ የአኹኑን ስንሰማ፥ አንዳንዶቻችን አልሞቀንም፤ አልበረደንምም።

**************************************

 

ከፍታን መፈለግና መመኘት ክፋት ባይኖረውም፥ ክርስቲያናዊ የፍቅርና የትሕትና መንፈስን ማጕደፍ ግን አይገባውም። “በዚህ የምትኖር ከተማ የለችንምና፥ ነገር ግን ትመጣ ዘንድ ያላትን እንፈልጋለን” (ዕብ. 13፥14) እያለ የሚያውጅ ክርስቲያን ከፍታን በንቀት እንዳያጨቀይ መጠንቀቅ የመንፈስ ከፍታው ነው። “ሲንቁን የኖሩትን” በመብለጥ እንቍልልጭ የምንልበት የዕብሪተኝትን “ከፍታ” ሳይኾን፥ የወንድሞችን ዝቅታ ለመካፈል “ታች ታቹን” የምንወርድበት መረዳት ቢመጣልን ነው የሚበጀን። በወርቅ ሰረገላ ተቀምጠን የምንገላምጠው ድኩማን ቍጥር ከመብዛቱ፥ ወይም እጁን የሚያወዛውዝልን ወፈ ሰማይ ከመኰልኰሉ ይልቅ ከእነርሱው መካከል ዐብሮ መቈጠሩ የሚያስፈነድቀን ቢኾን ነው ብፅዕናው። የማንንም ትኵረትና ልቡና የሚያለሰልሰውም እርሱ ነው፤ ዝቅ የማለት መሰጠት። እስቲ አንድ ምሳሌ ልምዘዝላችሁ፤

 

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ (በራስ ካሳ የሚመራው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን አባል ኾነው) በአውሮጳና መካከለኛው ምሥራቅ ያደረጉትን ጕዞ የሚመለከት ድንቅ ዘገባ አዘጋጅተው ነበርና ፕሮፌሰር ባሕሩ ከተደበቀበት አውጥተው ስላሰናዱት ለንባብ በቅቷል።* በዚያ መጽሐፍ፥ የልዑካን ቡድኑ ጕዞ ዋነኛ ተግባር በኾነው በንጉሥ ጆርጅ ዐምስተኛ በዓለ ንግሥ ላይ ለንደን ውስጥ ተገኝተው የተመለከቱትን ዘግበዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት መልእክተኞች በተመለከቱት ነገር እንደ ተደነቁና እንደ ፈዘዙ ከርመው ተመለሱ። ከነዚያ መኻል፥ ለያዝነው ሐሳብ የሚበጀውን ኹለት ተነጻጻሪ ነገሮች ብቻ ላንሣላችሁ።

 

የንጉሣዊውን ቤተ ሰብና መንግሥት ታላቅነት (ከፍታ) ለማሳየት በበዓሉ ላይ ከታዩት ነገሮች አንዱ የወርቁና የአልማዙ ዐይነት በተለያየ ኹኔታ ጥቅም ላይ ውሎ መታየቱ ነበር። ልዑካኑም በተመለከቱት ኹሉ ሲደነቁና ሲገረሙ ዋሉ። ይኹንና ኅሩይ “ሰሎሞን ዐይን ለማየት አትጠግብም [ቢልም] በዚህ ቀን፥ ሌላውስ ይቅርና፥ በወርቅና በአልማዝ ያጌጡትን ሰዎች እንኳ ለማየት ዐይናችን ሰለቸች” (112) ይላሉ። ለምን? ምንም ለጊዜው ቢያስጐመዥም፥ የዚህ ዓለም “ከፍታ” ማሰልቸቱ አይቀርማ።

 

ይኹንና የልዑካኑን፥ በተለይም የኅሩይን፥ ቀልብ የገዛውና አስተምህሯዊ ፋይዳውን ለአገራቸው መንግሥትና ሕዝብ የተመኙት ከልዑላኑ “ከፍታ” ይልቅ “ዝቅታውን” ነበር። እንዲህ ይላሉ፥ “የእንግሊዝ ንጉሥና ንግሥት ከተቀመጡበት ተነሥተው ቆመው ለሕዝቡ ሰላምታ ሰጡ ብዬ ብናገር ካየ ሰው በቀር ማን ያምናል” (120)። እንዲያውም ከመንግሥቱ አገልጋዮች ቤት ለግብዣ ኼደው በመታየታቸው፥ …. “ይልቅስ የሚደንቀው ነገር ንጉሥና ንግሥት ወደ አሽከራቸው ቤት ኼደው መብላታቸው ነው” (121) ብለዋል። “ከፍ” ያለው ታች ታቹን ሲኼድ እንዲህ የሰው ልብ ይማርካል።

 

በማጋበስ ሥሥት ከተጠናወተው ከፍታ ላይ ተቈንነን ከገበታችን ተርፎ የተደፋውን ጥራጊ በዝቅታችን ግርጌ ከተደፋው ወገናችን ላይ ለመወርወር መቋመጥ እንዳይጣባን ተግተን “ማጐንበስ” በወንጌል ትምህርት ያገኘናት የፍቅር ትምህርት ናት። ኢየሱስ እኮ፥ ኹሉ የነበረው ጌታ ሳለ፥ በምስሉ እንደ ሰው ተገኝቶ የባርያን መልክ በመያዙ ነው ልናገኘው የቻልነው፤ አብም ከፍ ከፍ አድርጎ ያከበረው (ፊል. 2፥6-10)። የከፍታውን ሰገነት ለማግኘት ስንፋጅ የእግዚአብሔርን ስጦታ እንዳናጣ መጠንቀቅ ይሻለናል። የማናገኘውን ብናገኘውም የማይረባንን መከጀል ምን ይረባናል?

 

የማይገኘውን ከመፈለግና ከእኔነትን ርኵሰት ራሳችንን ካልገታን የሕይወት ጕዞ አይሳካም። በአንድ ወቅት ፈላስፋው ዲዮጌነስ፥ አንዳች ነገር እንደሚፈልግ ሰው፥ የዐፅም (ዐጥንት) ክምር ላይ አፍጥጦ እያለ ታላቁ እስክንድር ይመለከተውና ጥያቄ ያቀርብለታል።

 

“ዲዮጌነስ፥ ምን እየፈለግህ ነው?” 
“ፈጽሞ ላገኘው የማልችለውን ነገር እየፈለግሁ ነው” ይላል። 
“እኮ፥ ምን?”
“በአባትህ (ዳግማዊ ፊሊጶስ) ዐጥንትና በባሪያዎቹ ዐጥንቶች መካከል ያለውን አንዳች ልዩነት እያሰስሁ ነበር፤ ኾኖም ምንም ልዩነት አላገኘሁባቸውም” አለው። የማይገኘውን የመፈለግ ከንቱ ልክፍትን ያሳየበት ምሳሌ መኾኑ ነው።

*************************

 

ኢየሱስ በገዛ ደሙ ሕዝቡን ለማዳን “ከበር ውጭ” መከራን እየተቀበለ ፍቅርን እንደ ገለጠ እኛም “ነቀፌታውን እየተሸከምን” ከሰፈር ውጭ መውጣት ነው ጥሪያችን (ዕብ. 13፥12-13)። “ከፍታው” ላይ የተሰቀለውን ብቻ ለማፈስ ከመንጠራራት፥ “ዝቅታው” ዘንድ የፈሰሱትን ለመሰብሰብና ለማቀፍ “መውደቅን” አለመዘንጋት መልካም ነው። በመስቀል ካልገሩት በቀር፥ የከፍታ ጥማት በወንድም ዐንገት ላይ በጭካኔ ቆሞ የመጨፈርን ደዌ ሊያስከትል ይችላል። ለመታወቅ ስንል ሌሎችን በመድፈቅ ውጋት ቀስፎ ያስይዘናል። የጎረቤታችን የቤቱን ማገር መዝዘን ባነደድነው እሳት እንድንሞቅ ሲገፋፋን ይገኛል።

 

በ “የተቈረሱ ነፍሶች” መዝለቂያ ውስጥ እንደ ተባለው፥ “እነሆ፥ ዕውቀት አፍኖ እንዳያፈነዳን በፍቅሩ ያንጸናል። ትምክሕት እንዳይከሰክሰን ትሕትናው ያረጋጋናል። በጭብጨባ ብዛት “አንጎል አሳብጠን፥ አንጎል እንዳንኾን” (ገጣሚው እንዳለው፥ “ከመድረኩ ግርጌ ጭብጨባ ጨፍልቆን” ድፍት ብለን እንዳንቀር) የመውረድ-መነሣትን ሰማያዊ ጥበብ ያበዛልናል። እንጂማ እኛ ምንድር ነን? ትምክሕታችንስ ከእርሱ በቀር ከየት ይገኛል?” (ገጽ 18)

 

ካልተጠነቀቅን ይህ አታላይ ልባችን በአንድ ወይም በሌላ ጊዜ አጕል ሊያደርገን ይችላል። ጠንካሮች የምንመስለው እኛ ምንኛ ደካሞች ነን! መስቀል ያልፈተነው ጕብዝና ስንቱን ቀጭቶ በመንገድ አስቀርቶታል። ስለዚህ ረድኤቱን እንዲሰጠን ወደ እርሱ እንገሠግሣለን (መዝ. 63፥1)። ከግሪክ አገር ተቀምጦ (ፈረንጅ አንድ ነገር ቅኔ ሲኾንበት “It is still Greek to me” እንደሚለው) በአማርኛ ጽፎ “ግሪክ” ማመስጠር የተካነበት ወዳጃችን ሔኖክ በቀለ “ልብህ ከቁመትህ በላይ ካደገ፥ የገዛ ቤትህ [እንኳ] አያስገባህም። (በረንዳ አዳሪ ከመኾን ይሰውረን)” ያላት የምክር ቃል የዋዛ አይደለችም።

 

ተወዳጆች ሆይ፥ “ቸሩ እግዚአብሔር የግርማዊ ክብሩን ባለ ጠግነት በማወቅ ባይባርከን ኖሮ፥ በመንጋው መካከል አናታችንን ለማሾል በነፍሳችን መቅበጥበጥ በቋመጥንበት በዚያው ቅጽበት፥ የውርደት ሽብልቅ በእርግብግቢታችን እምብርት በጠለቀብንና ከነሕመማችን በከሰምን ነበር፤ ከሕያዋን ምድር በተወገድን፥ ተስፋም ባልኾነልን ነበር። ራርቶልን አድኖናል፤ ያድነንማል። “እጅግ የሚምርና የሚራራ” አምላክ አለ (ያዕ. 5፥11)፤ ቡሩክ እኮ ነው — እግዚአብሔር መሐሪያችን” (“የተቈረሱ…”፥ 18)።

 

እንግዲህ ልብ ያለው ልብ ይበል። እንግዲህ ዐዲስ ብለን በምንጀምረው ዘመን፥ ዝቅ በማለት የምትገኘውን ከፍታ በወንጌል እንደ ተማርናት እንፈልጋት። “ራሱን ከፍ የሚያደርግ ኹሉ ይዋረዳል፥ ራሱንም የሚያዋርድ ኹሉ ከፍ ይላል” (ማቴ. 23፥12)። ደቀ መዝሙርነት ከዚህ ውጭ ሌላ ትርጕም አለው? በማይኾን “የከፍታ” ሩጫ እንደ አሮጌ ላም እንገፍ እንገፍ እያልን ዘመናችንን ከማስበላት ጌታ ያስተማረንን መንገድ እየተከተልን የታዘዝነውን ኹሉ ካደረግን በኋላ፥ “የማንጠቅም ባሪያዎች ነን፥ ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል” (ሉቃ. 17፥10) የማለትን ብፅዕና ለመቀዳጀት ያብቃን። አለዚያ ግን አልበርት አንስታይን አለው እንደሚባለው፥ “አንድን ነገር በተመሳሳይ መንገድ ደግመን ደጋግመን እየሠራን የተለየ ውጤት የመጠበቅን የለየለት ወፈፌነት” በሕይወታችን እንለማመዳለን። — Insanity is doing the same thing over and over again, but expecting a different result.”

 

“ወፍቅረ ዚኣየ ምስለ ኵልክሙ በክርስቶስ ኢየሱስ—ፍቅሬ በክርስቶስ ኢየሱስ ከኹላችሁ ጋር ነው” (1ቆሮ. 16፥24)! የምሬን!

 

መልካም ዐዲስ ዓመት ለኹላችን።

*ኅሩይ ወልደ ሥላሴ፥ "የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በአውሮጳና መካከለኛው ምሥራቅ [1903 ዓ.ም.]"፥ ዐዲስ አበባ፥ የኢትዮጵያ አካዳሚ ፕሬስ፥ 2009 ዓ.ም.
** ሰሎሞን አበበ ገብረ መድኅን፥ "የተቈረሱ ነፍሶች"፥ ዐዲስ አበባ፥ 2009 ዓ.ም.

Read 6100 times Last modified on Tuesday, 12 September 2017 05:08
Solomon Abebe Gebremedhin

ከሁለት ደርዘን ዓመታት በፊት በእግዚአብሔር ቸርነት በተሐድሶ የወንጌል አገልግሎት ውስጥ የዳግም ልደት ብርሃንን ያየው ሰሎሞን አበበ መጋቤ ወንጌል ሲኾን በኢቫንጀሊካል ቲዎሎጂካል ኮሌጅ  (ETC) እና በኢትዮጵያ ድኅረ ምረቃ ነገረ መለኮት ት/ቤት (EGST) የቅዱሳት መጻሕፍት መምህር ነው፤ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ምስባኮች በመስበክም ይታወቃል። ሰሎሞን ባለትዳርና የሁለት ሴቶች ልጆች አባት ነው።

Website: solomonabebe.blogspot.com Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 39 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.