You are here: HomeSermonትንሣኤ ሙታን

ትንሣኤ ሙታን

Written by  Tuesday, 07 April 2015 00:00

የክርስትና እምነት ምንድነው? ይህ ጥያቄ በአንደኛው ክፍለ ዘመን ለሚኖር ሰው ቢቀርብለት፣ ያለምንም ማመንታት “የትንሣኤ እንቅስቃሴ ነው!” ሊል እንደሚችል መገመት አያስቸግርም። ለዚህም በርካታ ማረጋገጫዎች አሉ። ከብዙዎቹ ጥቂቶቹን ላንሳ፡ -

 

የትንሣኤው ምሥክሮች፡ - ጌታ ኢየሱስ አገልግሎቱን የጀመረው ምሥክሮቹ የሚሆኑትን የዛሬ ደቀመዛሙርት የነገዎቹንም ሐዋርያት በመጥራት ነበር። የኃይማኖት መናኽሪያ ከሆነችው ኢየሩሳሌም ርቆ መልካም ነገር ሊወጣባት ይችላል ተብላ በማትገመተው የገሊላዋ ናዝሬት ሰዎችን መጥራት ጀመረ። ያልተማሩ ማንበብና መጻፍ የማያውቁ አሣ አጥማጆችና ቀራጮችን ሰብሰበ። በርግጥ እንኯን ሌላው ሰው፣ ራሳቸውም ቢሆኑ የተጠሩበትን ዓላማ በጊዜው አልተረዱም። የወንጌላውያኑን ትረካ በትዕግሥትና በጥሞና ስንከታተል ግን የተጠሩበት ዓላማ ፍንትው ብሎ ይታየናል። ይኽውም የትንሣኤው ምሥክሮች እንዲሆኑ ነው። መወለዱ ምሥክር አላስፈለገውም፣ ምክንያቱም ሰው ሁሉ ይወለዳል፣ በሰዎች መሃል መኖሩ የመወለዱ ማርጋገጫ ነው። መጠመቁ ምሥክር አላስፈለገውም፣ ማንም ሰው ይጠመቃላ! ሞቱም ቢሆን ምሥክር አላስፈለገውም፣ የተሰቀለውና የሞተው በሰው ሁሉ ፊት ነዋ! ካህናት ነበሩ፣ ፈሪሳውያን ነበሩ፣ ጻህፍት ነበሩ፣ ወዳጆቹ ነበሩ፣ የሮማ ወታደሮች ነበሩ፣ ምኑ ቅጡ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሁሉ የሞቱን ዜና ሰምቷል፣ ደግሞም ሰው ሁሉ ይሞታል! ስለዚህ ምሥክር አላስፈለገውም። ነገር ግን በአካል ከሙታን መነሳቱ ምስክሮች አስፍልገውታል። ምክንያቱም የሞተ ሰው ተነስቶ አያውቅም፣ የኢየሱስ ትንሳኤ ከሞት መንቃትና ነፍስ መዝራት ሳይሆን ሙሉ በሙሉ በተለወጠና ልዕለ ተፈጥሮአዊ በሆነ የሕይወት ኃይል ነው የተነሳው። ተነስቶም አርባ ቀናት በብዙ ማስረጃ የታየው ለእነዚሁ ለመረጣቸው ምሥክሮቹ ነው። ምንም እንኩዋ ምሥክሮቹ አብና መንፈስ ቅዱስ፣ የነብያት ድምፆች የሆኑት ቅዱሳት መጻህፍት ጭምር ቢሆኑም የሐዋርያቱ ምሥክርነት ግን ድርሻው የማይናቅ ነው፣ ለሰው ልጅ ቅርብ ናቸዋ!   

 

እምነት-  ሐዋርያቱ ከሥፍራ ሥፍራ እየተዘዋወሩ ወንጌልን ሰበኩ። ለመሆኑ የሰበኩት የምሥራች ወንጌል ምንድን ነበር? ስለ ሰው ልጆች ኃጢአት የተሰዋው መሢሁ ኢየሱስ ከሙታን መነሳቱ ነው። ስለዚህ ያወጁት ትንሳኤውን ነው። ሉቃስ በሐዋ. 4፡33  “ሐዋርያትም የጌታን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ በታላቅ ኃይል ይመሠክሩ ነበር፣ በሁሉም ላይ ታላቅ ፀጋ ነበረባቸው” ይለናል። የኢየሩሳሌም ሐዋርያት ሆኑ የአሕዛብ ሐዋርያ ሊሆን የተሾመው ጳውሎስ ከትንሣኤው ውጪ የሰበኩት ወንጌል የለም። የተሰበከላቸውም ሰዎች እንዲያምኑ የተጠየቁት ሌላ ሳይሆን ስለ በደላችው የሞተው ኢየሱስ ከሙታን መነሣቱን ነው። እንደ ሮሜ መልዕክት ከሆነ መጽደቅም ሆነ መዳን የሚገኝው ሰው የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ ሲያምን ብቻ ነው። ለዚህም ይህን ክፍል  እንደ ዋቢ መመልከት ይበቃል። “ኢየሱስ ጌታ እንደሆነ በአፍህ ብትመሠክር፣ እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህ” ሮሜ 10፡9። ስለዚህ በአዲስ ኪዳን የሚሠበከውም ትንሣኤ፣ የሚታመነውም ትንሳኤ ነው። አብርሃም የእምነት አባት ነው። “የእምነት አባት” ምን ማለት ነው? እግዚአብሔር የአብርሃምን እምነት ደረጃና ልክ አድርጎ መድቦታል። የሚቀበለው፣ የሚያከብረውና በምላሹም ጽድቅን የሚያጎናፅፈው እምነት የአብርሃም ዓይነት እምነት ነው። የአብርሃም እምነት ምን ነበር? ትንሳኤ ነበር። እግዚአብሔር ለሙታን ሕይወትን ይሰጣል፣ የሞቱትን ያስነሣል ብሎ አመነና እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት። አብርሃም ትንሳኤን በጥቂቱም ቢሆን የተለማመደው በራሱ ሰውነትና በሚስቱ በሣራ ሰውነት ላይ ነው። “የመቶ ዓመትም ሽማግሌ ስለሆነ እንደ ሙት የሆነውን የራሱን ሥጋና የሣራን ማህፀን ሙት መሆኑን በእምነቱ ሳይደክም ተመለከተ . . . ስለዚህም ደግሞ ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት” ሮሜ 4፡19፣22። ስለዚህ ማንም ‘እግዚአብሔር ሙታንን ያሥነሣል፣ ኢየሱስንም ከሙታን አስነሥቶታል’ ብሎ ቢያምን በእርግጥ የአብርሃም ልጅ ሆኗል፣ እግዚአብሔርም እምነቱን ጽድቅ አድርጎ ቆጥሮለታል። ለዚህ ነው ‘የአዲስ ኪዳን እምነት የትንሣኤ እምነት ነው’ የምንለው።

 

የእግዚአብሔር ማንነት፡- እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ ነው። ነገር ግን መታወቅም ሆነ መታመን የሚፈልገው በአንድ ነገር ነው። “ለሙታን ሕይወትን የሚሰጥ፣ የሌለውንም እንዳለ አድርጎ የሚጠራ አምላክ” ሆኖ። [ሮሜ 4፡17] ለምን? እግዚአብሔር የሕይወት መንፈስ ነዋ! እርሱ ራሱ የዘላለም ሕይወት ነው። የማይሞት፣ የማይጠፋ፣ የማያልፍ የሕይወት ኃይል! ይህ ሕይወት የሕብረት ሕይወት ነው፤ ከአንድ በላይ የሆኑ አካላት በአንድ ጊዜ ሊካፈሉ የሚችሉት አስገራሚ ሕይወት። እግዚአብሔር በፀጋው ባለጠግነት ይህን ሕይወት ከስው ልጅ ጋር ሊካፈለው  ወደደ። ትንሣኤን ከሥላሴ አንፃር ብናየው፣ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሳው ማነው? ለሚለው ጥያቄ የተለያዩ መልሶች እናገኛለን። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር አብ እንዳስነሣው ይነግረናል፣ ነገር ግን አንድ ሥፍራ ጌታ ራሱ “ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና፣ ስለዚህ አብ ይወኛል። እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም። ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ፣ ይህችን ትዕዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ” ዮሐ. 10፡18  ሲል እናነባለን። በሌሎች ክፍሎች ደግሞ መንፈስ ቅዱስ እንዳስነሳው እናነባለን። እነዚህን ክፍሎች ስንገጣጥማቸው የምናገኝው ሥዕል አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ ሙታንን የሚያነሣ የትንሣኤ አምላክ መሆኑን ነው።   

 

ሞት፡- የሰውን ልጅ ሁሉ ያንበረከከ፣ ጀግኖችን ያልፈራ፣ ነገሥታትን ያላፈረ፣ አዛውንትን ያላከበረ የሰው ጠላት ከሞት በላይ ማን ይኖር ይሆን!? በኃጢአት በኩል ወደ ዓለም ገብቶ በሥጋ ሁሉ ላይ የነገሠ፣ ከአዳም አንስቶ እስከ ሙሴ ከሕግ በፊትም ሆነ ከሕግ በኃላ የተንሰራፋ፣ የሰውን ልጅ ሁሉ አይሁድ ግሪክ ሳይል አንገት ያስደፋ ከሞት በላይ ማን ይኖር ይሆን? ሰው የፈለገውን ያህል ሃብት ቢያከማች፣ ዲግሪ ቢደረድር፣ ማዕረግ ቢጭን፣ ዝናው ቢናኝ ቀና ብሎ ነገን ሲያስብ አንድ ነገር ተስፋውን ያጨልምበታል። ሞት! ለዚህ ይሆን ያገሬ ሰው ልጁን “ሞት ባይኖር” ብሎ ስም የሚያውጣው? ሞት የሚያስፈራራን ሲገድለን ብቻ ቢሆን ምንኛ መልካም ነበር? ሞት አንዴ ነዋ! ነገር ግን እንደ ዕብራዊያን መልዕክት ጸሐፊ በሕይወታችን ዘመን ሁሉ ያስፈራራናል፡-

 

“እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፣ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፣ ይኽውም ዲያቢሎስን ነው፣ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነፃ እንዲያወጣ፣ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ” ዕብ. 2፡14-15።

 

በዓለም ታሪክ ከሞት ወዲህ በሥጋ ሕይወት ላሉ የሰው ልጅ ችግሮች ሁሉ ሰው መፍትሄ ከማበጀት አልቦዘነም። እስቲ ትራንስፖርት፣ መገናኛ ብዙሃን፣ የህክምና ሳይንስ ወ.ዘ.ተ የደረሰበትን እንመልከት። ችግራችን ገንዘብ ቢሆን፣ ጤና፣ እውቀት ቢሆን ዝና ሰዎች ሊፈቱት ይችላሉ። ችግራችን ሲገለጥ ወዳጅ ዘመድ ይረባረባል፣ የቅርብ የሩቁ የራሱን ድርሻ ይጫወታል። ነገር ግን አንዴ ሞት ጥላውን ካጠላ ሰብዓዊ መፍትሄ ይሟጠጣል፣ ተስፋ ይቆረጣል፣ ከዋይታና ከሰቀቀን በስተቀር ሊዋጣ የሚችል መላ የለም። ሞት ግን ለእግዚአብሔር ብቻ የሚተው ጉዳይ ነው። ለዚህ ነው እግዚአብሔር ለሙታን ሕይወትን የሚሠጥ አምላክ ሆኖ የተገለጠው። እግዚአብሔር የሚፈልገው አንድ ነገር ብቻ ነው። መታመን! የሞቱትን ሰውነታቸው የበሰበሰውንና የፈረሰውን እንደገና የክብር ሕይወት ሰጥቶ እንደሚያነሣ፣ ይህንንም መሢህ ኢየሱስን ከሙታን በማስነሣቱ እንዳረጋገጠ፣ ቀን እንደቀጠረ በዚያም ቀን ሙታንን በእርግጥ እንደሚያነሣ፣ አስቀድሞ የእርሱ የሆኑትን በኃላም ሁሉን አስነስቶ ክብር ለሚገባው ክብርን፣ ውርደት ለሚገባውም እንደ ሥራው ለሁሉ እንደሚከፍል መታመን ይፈልጋል። እምነት ማለት ይህ ነው፣ ለሙታን ሕይውትን በሚሰጥ አምላክ ተደግፎ በሞት ላይ የሚስቅ ሕያው እምነት።

 

ተስፋ፡- ጌታ ኢየሱስ ከሙታን እንደተነሣ ምንም ያህል አስቀድሞ፣ ደጋግሞ የነገራቸው ቢሆንም ትንሣኤን ለማመን  ልባቸው የዘገየውን ደቀመዛሙርቱን ለማስረዳት ያደረገው ነገር ቢኖር መጽሐፍትን ያስተውሉ ዘንድ አዕምሯቸውን መክፈት ነው። ይህም ትንሣኤው አስቀድሞ የተሰጠ መለኮታዊ ተስፋ መሆኑኑ ያረጋግጥልናል። እግዚአብሔር የተስፋ አምላክ ነው። ታዲያ ተስፋ መስጠት የጀመረው የተስፋው ወራሽ የሆነው ሰው ከተፈጠረ በኃላ ብቻ አልነበረም። ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ መረዳት ወደ ዘላለም መጥቆ ዐለም ሳይፈጠር ስለተከናወነ አንድ ተግባር ይተርክልናል፡-

 

“ስለዚህም ሕይወት የማይዋሽ እግዚአብሔር ከዘላለም ዘመናት በፊት ተስፋን ሰጠ” ቲቶ 1፡2

“በክርስቶስ ኢየሱስ እንደሚሆን የሕይወት ተስፋ በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ  ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ” 2ጢሞ. 1፡1

“… ይህም ፀጋ ከዘላለም ዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተሰጠን፣ አሁን ግን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ ታይቷል። እርሱ ሞትን ሽሯልና … በወንጌል ሕይወትንና አለመጥፋትን ወደ ብርሃን አውጥቷል” 2ጢሞ. 1፡9-11

 

ይህ የዘላለም ተስፋ ነው በዘመናት ውስጥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለአባቶች የተሰጠው። ተስፋው በሙሉ ከትንሳኤ ጋር የተያያዘ ነው። እግዚአብሔር በዘመናት ውስጥ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ኪዳን የገባ ቢሆንም “ቅዱስ” ተብሎ የተጠራ ኪዳን እግዚአብሔር ከአብርሃምና ከዳዊት ጋር የገባው “የተስፋ ኪዳን” ነው። ተስፋችን ስንሞት ሥጋችን ወደ አፈር፣ ነፍሳችን ወደ እግዚአብሔር ሄዳ በዚያ ለዘላለም መኖራችን አይደለም። በፍፁም አይደለ! ምንም እንክዋ ነፍሳችን ከሥጋችን ከምትለይበት አንስቶ ጌታ ዳግመኛ እስኪመጣና የአካል ትንሣኤ እስኪሆን ድረስ ሕያው የሆነች ነፍሳችን በጌታ ዘንድ የምትቆይ ቢሆንም ያ ተስፋችን አይደለም። እዚያም ሆነን በናፍቆት የምንጠብቀው ተስፋ የሥጋ ትንሣኤን ይመሥለኛል። ለዚህ አይደል የጌታን ዳግም መምጣት ሲያወሳ ጳውሎስ “የተባረከው ተስፋችን የታላቁ የአምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ” [ቲቶ 2፡11-13 በማለት የሚጠራው? ስለዚህ እኛም መገለጡን ከሚጠባበቁ አዕላፋት ቅዱሳን ጋር ተጨምረን “ማራናታ፡- አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ቶሎ ና!” እንበል። በቅድስና በመኖር ወንጌልንም በማሰራጨት መምጣቱን እናፋጥን። 

Read 11460 times Last modified on Tuesday, 07 April 2015 12:04
Yared Tilahun

President, Golden Oil Ministry

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 63 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.