You are here: HomeOpinionsቴክኖበላይነት

ቴክኖበላይነት

Written by  Tuesday, 23 August 2016 04:54

ቴክኖፖሊ (Technopoly) የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ ያዋለው ኒል ፖስትማን (Neil Postman) የተባለ አሜሪካዊ የባህል ሃያሲ (cultural critic) ሲሆን ትርጉሙም ቴክኖሎጂ ጠቀሜታ ብቻ ያለው ተደርጎ የሚታመንበት ፣ የሰው ልጅ የቴክኖሎጂ ተገዢ ወይም አምላኪ የሆነበት ሁኔታን ይወክላል። በኒል ፓስትማን አገላለፅ

 

‘‘ቴክኖሎጂ ጥሩ ጓደኛ ነው። ምቾት (comfort) ፣ ፍጥነት (speed) ፣ ጤና (hygiene) ፣ ብዛት (abundance) ይሰጠናል ፣ ረጅምም ዕድሜ ያጠግበናል። ጓደኛ ነው ስንል ግን ምንም ዋጋ አያስከፍልም ማለታችን አይደለም ፤ የራሱ የሆነ ጎጂ ጎን አለው። ልጓም ያልተበጀለት (ጥንቃቄ ያልታከለበት) የቴክኖሎጂ መስፋፋት ለሰው ልጅ ህይወት ወሳኝ የሆኑትን አእምሮአዊ አስተሳሰብና ማህበራዊ ግንኙነትን ያዳክማል። ለዚህም ነው ቴክኖሎጂ ወዳጅም ጠላትም ነው የምንለው።’’

 

ኒል ፖስትማን አንድ ማህበረሰብ ቴክኖሎጂን ለተፈጠረበት አላማ ብቻ የሚያውል ከሆነ ቴክኖሎጂ (ቁሳቁስ) የሚጠቀም ባህል (tool-using culture) ብሎ ሲጠራው ፤ የቴክኖሎጂ አምልኮ የተንሰራፋበትና በቴክኖሎጂ የሚነዳ ባህል ከሆነ ግን ቴክኖፖሊ (Technopoly) ብሎ ሰይሞታል።

 

ቴክኖፖሊ የሚለውን የኒል ፖስትማን ቃል የሚወክል የአማርኛ ቃል ስላላገኘሁ ‘ቴክኖበላይነት’ የሚል ቃል ይገለፀዋል ብዬ አሰብኩ። በዚህ የሉላዊነት ዘመን ኮምፒዩተር ፣ ቴሌቪዥንና ስልክ የመሳሰሉ የፈጠራ ውጤቶች የቦታን ርቀት በማጥበብ የሰው ልጅ በፍጥነት መረጃ እንዲለዋወጥ በማስቻል ዓለምን ወደ አንድ መንደር እየቀየሯት ይገኛሉ። በአገራችንም በሚፈለገው መጠንና ፍጥነት ባይሆንም ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ እየተስፋፋ የመጣው የኢንፎርሜሽንና ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ በአገሪቱ ኢኮኖሚና ዲሞክራሲ ግንባታ ሂደት ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ይገመታል። አርሶ አደሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሸቀጦች የገበያ ዋጋ እንዲያውቅ ፤ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የተከሰተ አወንታዊም ይሁን አሉታዊ ፖለቲካዊ ፍፃሜ የአለም ህብረተሰብ እንዲያውቀው በማድረግ ቴክኖሎጂ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ የተሳሰረ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ማህበረሰብ ለመገንባት ድር እና ማግ ሆኖ እያገለገለ ነው። ቴክኖሎጂ ይህን የመሰለ ገንቢ አስተዋፅኦ ቢኖረውም በአግባቡ ካልተጠቀምንበት የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅእኖ ሊያሳድር እንደሚችል ባደጉ አገሮች የተደረጉ ጥናቶች ይጠቁማሉ። በምዕራብዊያን ዘንድ ለግለሰባዊነት ማበብና ለማህበራዊ ግንኙነት መላላት ቴክኖሎጂ ተወቃሽ የሚያደርጉ የጥናት ውጤቶች ተጠቃሽ ናቸው። በዴንማርክ ዋና ከተማ ኮፐንሀገን ለትምህርት በቆየሁበት ጊዜ በቆየታዬ ስለታዘብኩት ነገር እንድናገር በአንድ መድረክ እድል አግኝቼ ነበር። ሰዉ ሁሉ በመግባቱና በመውጣቱ ከቴክኖሎጂ ጋር በመጣበቁ ምክንያት ብቸኝነት ስላማረረኝ ብሶቴን እንደሚከተለው ነበር የገለፅኩት።

 

‘‘የቀን ውሎዬን የምጀምረው ሜትሮ (Metro) በመሳፈር ነው...ለእኔ እንግዳ የሆነብኝና በዚህ ከተማ አራት አመት ቆይቼ እስከ አሁን መልመድ ያልቻልኩት ነገር አለ። ሜትሮዎቹ ሾፌር ስለሌላቸው አይደለም...በአፍሪካ ተሰምቶ የማያውቅ ነገር ቢሆንም። ሜትሮ ውስጥ ሰዎች ሲነጋገሩ አትሰሟቸውም...አልፎ አልፎ ‘ይቅርታ’ እና ‘አመሰግናለሁ’ ከሚባባሉት በስተቀር። ሜትሮው ጢም ብሎ ሞልቶ እያለም ቢሆን ሲያወሩ አታይዋቸውም። ሁሉም በራሱ ዛቢያ ውስጥ ይሽከረከራል። አንዳንዶቹ ሞባይላቸውን ይጎረጉራሉ...አንዳንዶቹ የጆሮ ማዳመጫ (ኢርፎን) ጆራቸው ላይ ሰክተው ጎናቸው የተቀመጠውን ከጨዋታ ውጭ አድርገውታል...የቀሩትም ባዶ አየር ላይ ያፈጣሉ። አንዳንዴ ቤተሰቦቼን ቫይበር ላይ ካላገኘኋቸው ወይም አሜሪካ የሚኖረውን ጓደኛዬን ስካይፕ ላይ ካላወራሁት ሁለት ወይም ሶስት ቀናት አንድም ሰው ሳላወራ ላሳልፍ እችላለሁ። የሚሰማኝ ብቸኝነት ቀላል አይደለም።...ለእናንተ አዲስ ነገር ላይሆን ይችላል ለኔ ግን እንግዳ ነገር ነው። እኔ የመጣሁበት ሀገር በትራንስፖርት ላይ ማንም ሰው አብሮት ከተቀመጠ ተሳፋሪ ጋር በቀላሉ ንግግር መጀመር ይችላል።

 

በእውቀቱ ስዩምም በውጭ አገር ቆይታው የታዘበውን የማህበራዊ ህይወት ክፍተት እንዲህ እያዋዛ ይገለፀዋል...

 

‘‘ፈረንጆች ያለተገደበ የንግግር ነፃነት አላቸው። ምን ዋጋ አለው ታዲያ ፤ በፈረንጅ አገር ሰው እርስ በርሱ አይነጋገርም። ኒውዮርክ ወይም ለንደን ውስጥ ባቡር ተሳፈር። ምድረ ፈረንጅ ምላሱን ቤቱ ጥሎት የመጣ ይመስል እንደተለጎመ ተሳፍሮ እንደተለጎመ ይወርዳል። ልታወራው ስታቆበቁብ ፊቱን እንደ ቪኖ ጠርሙስ በጋዜጣ ውስጥ ይሸፍናል። ለፈረንጅ ጋዜጣ ማለት ከጎረቤት የሚከልል ግድግዳ ማለት ነው። አበሻ አሜሪካ ውስጥ ብዙ ዘመን በስብሶ እንግሊዝኛውን ባያሻሽል አይግረምህ። ከማን ጋር ተነጋግሮ ያሻሽለው? ... ድሮ በደጉ ዘመን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያገኛትን ተካፍሎ ይበላ ነበር። አሁን ደግሞ ያገኛትን ተካፍሎ ያወራል። ለምሳሌ የአዲስ አበባ የታክሲ ወያላ ከተሳፋሪው ጋር ያወራል። ከሾፌሩ ጋር ይከራከራል። ተሳፋሪውና ሾፌሩ ስልክ ይዘው ጆሮ ከነፈጉት በመስኮት አንገቱን አውጥቶ ከጎረቤት ታክሲ ወያላ ጋር ይፎጋገራል። በስነልቦና ሳይንስ ማውራትና መደመጥ ከህክምና ይቆጠራል። ወሬኛ ማህበረሰብ ጤነኛ ማህበረሰብ ነው።

 

በአገራችንም በከተሞች አካባቢ የሞባይል መምጣት ተከትሎ ታክሲና አውቶብስ ውስጥ ቀስ በቀስ ፀጥታ እየሰፈነ የመጣ ይመስላል። ባለፈው ከቃሊቲ እስከ መገናኛ በታክሲ ስጓዝ እጎኔ የተቀመጠችው ተሳፋሪ ሞባይልዋን እየጎረጎረች ለአፍታም ቀና ሳትል እመወረጃዋ ደረሰች። እንደኔ አይነቶቹ ላጤዎችስ የመታየቱ ዕድል ካላገኙ እንዴት ነው ውሃ አጣጫቸውን ማግኘት የሚችሉት? ማን ነበር ‘‘ቴክኖሎጂ ዘመነ ፤ ሰው ከሰው መነነ’’ ያለው?

 

በአገራችን ያለው የኢንፎርሜሽንና ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ስርጭት (penetration) ከአገሪቱ ስፋትና ከህዝቡ ቁጥር አንፃር ገና በእንጭጭ ደረጃ ያለ ቢሆንም ቀጥዬ ለመዘርዘር የሞከርኳቸውን የቴክኖሎጂ አሉታዊ ተፅእኖዎች [እነርሱ ብቻ (exhaustive) ባይሆኑም] ቀድመን አውቀን አስፈላጊውን ጥንቃቄ ካደረግን የቴክኖሎጂን መርገም ቀንሰን የበረከቱ ተቋዳሾች መሆን እንችላለን ብዬ አምናለሁ። ፈረንጆች ‘‘አስቀድሞ ያወቀ አስቀድሞ ታጠቀ’’ (Forewarned is forearmed) እንዲሉ።

 

1. ቴክኖሎጂ እና ልጅ አስተዳደግ

ልጆች ከልጅነታቸው ተኮትኩተው እንዲያድጉ ወላጆች የማይተካ ሚና አላቸው። የእግዚአብሔር ቃል በምሳሌ 22:6 ‘‘ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው፥ በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም’’ ይላል። ይሁን እንጂ በርካታ ወላጆች ለልጆቻቸው መምህራን መሆናቸውን አይረዱም። ቤተሰብ ትምህርት ቤት ነው ፣ ወላጆችም ደግሞ መምህራን ናቸው። በተለይ ባሁኑ ጊዜ በመደበኛ ትምህርት ቤት ውስጥ ትኩረት የተነፈጋቸው እንደ ግብረገብነትና ሥነ-ምግባር ያሉ ጉዳዮች በማስተማር ረገድ ወላጅና ቤተሰብ ምትክ-የለሽ ሚና ይጫወታሉ። ወላጆች ጊዜ ወስደውና እንደ ጓደኛ ቀርበው የልጆቻቸውን ስብዕና መቅረፅ ካልቻሉ (Parental deficit ካለ) ቴክኖሎጂ አመጣሽ ለሆኑ ብልሽቶች ተጋላጭነታቸው ሰፊ ነው። ይህም ማለት በቤታችን ውስጥ ለመዝናኛና ወቅታዊ ኢንፎርሜሽን ለማግኘት የሰበሰብናቸው ቴሌቪዥን ፣ ኮምፕዩተር ፣ አይፓድና የእጅ ስልክ የመሳሰሉት ቁሳቁስ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ጥቅም ላይ ካልዋሉ ልጆች ክፉና ደጉን በማይለዩበት ጨቅላ እድሚያቸው ዝሙት ፣ ግድያ ፣ አልባሌ ሱስ ለመሳሰሉት ባህሪያት የመጋለጥ እድላቸው የሰፋ ነው። ልጆችን የጠቀምናቸው መስሎን ልቅ ከመልቀቅ ይልቅ በዙሪያቸው የከበቧቸውን ነገሮች እንዴት ባግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው ብናስተምራቸው ይበጃል። በቅርብ ስራውን የጀመረው ቃና የቴሌቪዥን ቻናል ልጆቻችሁን እንዳያዘናጋ እየተባለ በትምህርት ቤቶቸ በኩል ማስጠንቀቂያ ይሰጥ እንደነበር ልብ ይሏል። አንዳንዴም ቤታችን ውስጥ ያሉትን ቴሌቪዥንና የእጅ ስልክ የመሳሰሉ ቁሳቁስ ለተወሰነ ጊዜ ከአጠገባችን አርቀን (ሁሉንም ነገር አጠፋፍተን) ከልጆቻችንና ከልጆቻችን ጋር ብቻ ጥሩ የቤተሰብ ጊዜ ልናሳልፍ ይገባል።

 

2. ቴክኖሎጂ እና የስራ-እረፍት ምጣኔ (Work-Life Balance)

ቴክኖሎጂ የስራና የእረፍትን ድንበር በማፍረስ በስራ ጊዚያችን እንድናርፍ በእረፍት ጊዚያችን ደግሞ እንድንሰራ ያስገድደናል። አንዳንዴ ወይ ስራችንን አጥርተን አንሰራ ወይም እረፍታችንን አጥርተን አናርፍ። በስራ ሰዓት ቢሮ ውስጥ ሆነው ፌስ ቡክ ላይ ‘ፖስት’ እና ‘ኮሜንት’ የሚያደርጉ እንዳሉ ሁሉ በእረፍት ጊዚያቸው ባለቤቶቻቸውን እና ልጆቻቸውን ረስተው ላፕቶፓቸውና ሞባይላቸው ላይ የሚያፈጡትን ቤቱ ይቁጠራቸው። በሰለጠኑት አገሮች ዜጎቻቸው በስራ ሰዓት የግል ስልክ ጥሪ ወይም ኢሜይል መልእክት አይመልሱም ፤ በእረፍት ሰአታቸው ደግሞ የስራ ስልካቸውን አጥፍተው ፣ የስራ ኢሜይላቸው ላይ በ‘አውቶ ሪፕላይ’ እረፍት ላይ እንዳሉ የሚገልፅ መልእከት ትተው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ጥሩ

 

የእረፍት ጊዚያቸውን ያጣጥማሉ። እንደ ኢትዮጵያ ያለ ታዳጊ አገር ዜጎች የስራና የእረፍት ሰዓታቸውን ለይተው ፣ በቴክኖሎጂ ተነድተው ሳይሆን ቴክኖሎጂን ገዝተው እና ገርተው ኑሮአቸውን ለማሸነፍ መታተር ይገባቸዋል።

 

3. ቴክኖሎጂ እንደ ሰው ዋጋ (Worthiness) መለኪያ

አንዳንዴ የሰዎችን ዋጋ በያዙት የቴክኖሎጂ ውጤት በሆነ ቁሳቁስ (gadget) መለካት የሚቃጣን ጊዜ አለ። በአገራችን ካለው ሰፊ የሃብት ልዩነት ጋር ተያይዞ እነዚህን ቁሳቁስ በእጅ ይዞ መገኘት የሃብት ፣ የአዋቂነትና የዘመናዊነት መለኪያ

 

ተደርገው ይታሰባሉ። ለዚህ ይመስለኛል ቢያንስ ሌባ እንኳን ፈርተን በኪሳችን ወይም በቦርሳችን ልንይዘው የሚገባን የአስራ ስድስት ሉክ ደብተር የሚያክለውን ሞባይል ለታይታ በእጃችን ይዘነው ወዲያ ወዲህ የምንለው። ብዙ ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባን ነገር እያለ ወላጆቻችን ወይም ውጭ የሚገኙ ዘመዶቻችን ረቀቅ ያለውን ሞባይል እንዲገዙልን እንወተውታለን። እስኪ ለመሆኑ በእጃችን የያዝናቸውን ቴክኖሎጂዎች ከታይታ (Show-off) በዘለለ የሚሰጡትን አገልግሎት አሟጠን ለመጠቀም የምንሞክር ስንቶቻችን ነን? ሰው ክብርና እውቅና ሊሰጠው የሚገባው ቴክኖሎጂን ምን ያህል እውቀቱን ለማበልፀግና ሌሎችንም ለመጥቀም ተጠቀመበት በሚል እንጂ በሰበሰበው ቅራቅንቦ መሆን የለበትም። በአርአያ ሥላሴ የተፈጠረ ፣ ክርስቶስም ዋጋ የከፈለለት ክቡር ፍጡር ቀፎ በመሰለ ተራ ነገር ዋጋዉን ስንተምነው እግዚአብሄር ምን ያህል ያዝንብን ይሆን? ስብዕና የሚገነባው በቁሳዊ እሴት (material value) ብቻ ሳይሆን ከሁሉም በላይ በኀሊናዊና መንፈሳዊ እሴቶች ነው።

 

4. ቴክኖሎጂ እንደ ማዘናጊያ (Technology as Distraction)

አንዳንዴ ቴክኖሎጂ በአግባቡ ካልተጠቀምንበት ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባንን ስራ በአትኩሮት (concentration) እንዳንሰራ ፣ ማህበራዊ ግንኙነታችን እንዲላላ ምክንያት ሊሆን ይችላል። መፅሓፍ በማንበብ ላይ እያለን አንዴ ሞባይል

 

መነካካት ከጀመርን የያዝነውን ስራ አስረስቶን ይዞን ጭልጥ ይላል። በየደቂቃው በእጅ ስልካችንና ኮምፕዩተራችን ላይ የሚመጡት መልእክቶችና ጥሪዎች በያዝነው ስራ ላይ እንዳናተኩር ወይም የያዝነውን ሀሳብ እንዳናሰላስል ያደርጉናል። አብረን ለመዝናናት ካፌ ገብተን በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ የተቀመጥን ጓደኛሞች በፌስ ቡክ ‘ቻት’ የምናደርግ ይመስል እንደገባን ፌስ ቡክ ላይ እናፈጣለን (We are physically together, but we are not totally focused on and paying attention to each other.)። ለዚህ ለዚህ እማ ተቀጣጥረን መገናኘቱ ምን አስፈለገ? ድሮ በአንድ ሰሀን ወይም ጠረጴዛ ዙሪያ ተሰብስበን ምሳ ወይም እራት እምንበላው አሁን አሁን የየራሳችን ሳህን ይዘን ግማሻችን ቴሌቭዥን እናያለን ፣ ግማሻችን ሞባይላችን እንጎረጉራለን። ‘‘ነገር በአይን ይገባል’’ እንዲሉ ፊት ለፊ እየተያየን ፣ እየተናበብን ማውራት እንዳንችል ዙሪያችንን የከበቡን ቁሳቁስ አትኩሮታችንን ይከፋፍሉታል። አሜሪካዊው ኮሜድያን ሊዊስ ሲ.ኬ. (Louis C.K.) ከቴክኖሎጂ ጋር የፈጠርነውን መጣበቅ (attachment) በቀልድ እንዲህ ይገለፀዋል...

 

‘‘ኢየሱስ ክርስቶስ ተመለሶ ቢመጣና ከፊታችን ቆሞ ሊያነጋግረን ቢሞክር (እርሱን መስማት ትተን) ሁላችንም ወደ ትዊተር (ሶሻል ሚዲያ) ገብተን እንዲህ የሚል መልእክት ለመፃፍ በተሯሯጥን...‘‘ኦ ማይ ጋድ...በዚህ ሰዓት ኢየሱስ ከፊቴ ቆሟል...ይኼውና ያነሳሁት ፎቶ...ኦ ማይ ጋድ ስለ ኢየሱስ የላኩት መልእክት ተወዳጅ ሆኗል (እዩ ብዙ ‘ላይክ’ እና ‘ሼር’ እያገኘ ነው)”

 

‘‘I think if Jesus comes back and starts telling everyone everything, everybody’s gonna be twittering.. "Oh my God, Jesus is right in front of me right now. I have a Twitpic of Jesus! Oh my God – Jesus is trending! Look! Jesus is trending!”

 

5. የባህል ፣ እምነት ፣ ግብረገብነት መሸርሸር

ቴክኖሎጂ ባህልን ለማስተዋወቅና እምነትን ለማስፋፋት አይነተኛ መሳሪያ ነው። የብዙ ብሔርና ብሔረሰቦች መናሃሪያ (mosaic) የሆነችው አገራችን ባህላዊ ትውፊትዋን ለአዲሱ ትውልድና ለተቀረው አለም ለማስተዋወቅ አስችሎናል። ሃይማኖት (እምነት) ከማስፋፋት ረገድም ቴክኖሎጂ መዝሙር ፣ ስብከትና ፅሑፎች በእጅ ሞባይል ወይም በላፕቶ ኮምፕዩተራችን ፍንትው አድርጎ በማምጣት አምላካችንን እንድናውቅ ያግዘናል። በቦሌ አካባቢ እሚገኙ ቤተክርስትያኖች ‘‘ምእመናን አይፓዳችሁ/ሞባይላችሁ ላይ መፅሓፍ ቅዱስ ክፈቱ” መባል ተጀምሯል ተብሎ ሲቀለድ ሰምቻለሁ። ባግባቡ ካልተጠቀምንበት ግን የጥቅሙን ያህን ቴክኖሎጂ የራሱ ጉዳት እንዳለው ሳይታለም የተፈታ ነው። የቴሌቪዥን የሞባይልና የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ የአገራትን ባህል በመሸርሸር አለምን በምዕራባውያን ባህል ለማጥለቅለቅ እየተሰራበት ይገኛል። አለም አንድ መንደር ሆናለች ተብሎ በሚለፈፍበት በዚህ ዘመን የፊልም ፣ የዘፈንና የእግር ኳስ ኢንዱስትሪዎች የልጆችና የወጣቶችን አእምሮ በመቆጣጠር የራሳቸውን ባህልና ቋንቋ ንቀው በምዕራባዊያን ባህልና ቋንቋ እንዲጠመቁ ለማደረግ እየሰሩ ፣ እየተሳካላቸውም ይመስላል። የገዛ አገሩን ታሪክና ታዋቂ ግለሰቦችን የማያውቅ የሆሊውድና የፕሪምየር ሊግ ታዋቂ ግለሰቦችን ደሞዝ ፣ ትዳርና ውሎ ግን ተንትኖ ሊያስረዳ የሚችል ትውልድ እየተበራከተ ነው። በጊዜ ካልነቃን ቀስ በቀስ አሁን የምንጠየፋቸው ፖርኖግራፊ ፣ ተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ የመሳሰሉ ከባህላችንና ከወጋችን ጋር የሚፃረሩ ማህበራዊ ነውሮች በቴክኖሎጂ ታግዘው የትውልዱን አእምሮ ሊመርዙብን ይችላሉ።

 

ቀደም ሲል ነውር የሚባሉ ነገሮችን ሳይንስና ቴክኖሎጂ ይፋ አውጥቷዋል። ጭራሽ ነውር የሚባል ነገር የሌለ ይመስል በተለያዩ ፊልሞችና የቴክኖሎጂ ውጤቶች አማካይነት መሆን የማይገባቸው ነገሮች በሙሉ ለተመልካቾች ፣ አድማጮችና አንባቢዎች ይቀርባሉ። ይህ ማለት በዚች አለም ላይ ምንም ዓይነት ነውር ወይም ሚስጢር የለም እስከ ማለት የተደረሰ ይመስላል። መሆን የሌለበት ነገር ከሌለ ትክክልና ስህተት ፣ ጥሩና መጥፎ የሚባል ነገር ሊኖር አይችልም። ትክክልና ስህተት በመባል የሚገመገም ድርጊትና ጠባይ ከሌለ ደግሞ የግብረገብነት መኖር አስፈላጊ አይደለም። የሰው ልጅ እኩይ ድርጊቶችን የማስወገድና ሰናይ ሕይወትን የማዳበር እንቅስቃሴና ግብ አይኖረውም። ያለግብረገብ ስለሚኖርና ስለሚያድግ ሕብረተሰብ ማሰብ ይቻላል? ከሰለጠኑት አገራት ብዙ የምንማራቸው መልካም ነገሮች እንዳሉ ሁሉ ከመሰልጠን ወደ መሰይጠን የተሸጋገሩባቸው ነገሮችን ሳናውቅ አግበስበስን አላስፈላጊ ዋጋ እንዳንከፍል ከፍተኛ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል።

 

6. ሞዴፊክ ጓደኝነት

እኔና ወንድሜ አንድ ድሮ የምናውቀው ጓደኛችንን በቀጠሮ አገኘነው። ከወንድሜ ጋር ከተገናኙ አንድ አስር አመት ይሆናቸዋል። እንደተገናኘን ወንድሜ ‘‘ሁል ጊዜ ፌስ ቡክ ላይ ስለምንተያይ የተገናኘን ነበር የመሰለኝ’’ ይለዋል። አንድ ከተማ ውስጥ እየኖርን ፣ ከቅርብ ጓደኞቻችን ጋር በሶሻል ሚድያ ላይ ስለምንተያይ ብቻ ስልክ የማንደዋወል ወይም በአካል እማንገናኝ ከሆን ቴክኖሎጂ እያቀራረበን ሳይሆን እያራራቀን ነው። እንደ ፖላንዳዊ ሶሽዮሎጂስት ዛይግሙንት ቦማን (Zygmunt Bauman) አስተሳሰብ

 

‘‘አብዛኞቻችን ማህበራዊ ሚዲያን የምንጠቀምበት ራሳችንን ክፍት ለማድረግ ሳይሆን ፣ በራሳችን የምቾት ቀጠና (Comfort zone) ለመዝጋት ነው። በቴክኖሎጂ አማካይነት የምንመሰርተው ግንኙነት በአካል የምናደርገውን ግንኙነት (ማህበራዊ ህይወት) ያቀላጥፍ እንደሆነ እንጂ ሊተካው አይችልም። ሶሻል ሚዲያ ላይ የሴት ወይም የወንድ ጓደኛ በቀላሉ ማግኘት ይቻል ይሆናል። ሁነኛ የትዳር አጋር ለማግኘት ግን ጊዜ ወስዶ ፣ በአካል ተገናኝቶ መተዋወቅ ፣ እርስርስ መናበብና መጠናናት ግድ ይላል። በትግራይ ‘‘በአሸንዳ በዓል ላይ ያየሃትን ሴት አታግባ’’ እንደሚባለው ማህበራዊ ሚድያ ላይ ከምናየው ውበት ተነስተን በአእምሮአችን የምንቀርፀው ምስልና በአካል የምናገኘው ማንነት ለየቅል ሊሆን ይችላል። በየጊዜው ከምንተዋወቃቸው (Add ከምንደራረጋቸው) ጓደኞች ውስጥም የቅርብና የልብ የምንላቸው ሊኖሩን ይገባል...‘‘የሁሉም ጓደኛ የማንም ጓደኛ አይደለም’’ና (‘‘A friend to all is a friend to none.’’)

 

7. ቴክኖሎጂና የሰው ሁለንተናዊ እድገት (Personal Development)

ቴክኖሎጂ በሰው ልጅ ሁለንተናዊ ማለትም አካላዊ (Physical)፣ አእምሮአዊ (Mental) እና መንፈሳዊ (Spiritual) እድገት ላይ ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ ያደርጋል። ለአካላዊ እድገታችን የተመጣጠነ ምግብና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ፣

 

ለአእምሮአዊ እድገታችን ማንበብና መወያየት ፣ ለመንፈሳዊ እድገታችን ደግሞ ፀሎትና የእግዚአብሔር ቃል ማንበብ የማይተካ ሚና አላቸው። የቴክኖሎጂ እድገት የእነዚህን ነገሮች ተደራሽነት በማቀላጠፍ (አቅርቦት በመጨመር) ከመቼውም ጊዜ በላይ ለሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አጋዥ ተራ እየተጫወተ ይገኛል። ሆኖም ቴክኖሎጂ በአግባቡ ካልተጠቀምንበት ለሰው ልጅ አድገት ሳይሆን ለሰው ልጅ ሁለንተናዊ መቆርቆዝ አሳዛኝ አስተዋፅኦ ሊያደርግ ይችላል። ቴክኖሎጂ በእውቀት እንድንበለፅግ የሚያግዘንን ያህል በአግባቡ ካልተጠቀምንበት ጊዜአችንን በእንቶ ፈንቶ ነገር ላይ ልናውለው እንችላለን። በዚህ በኢንተርኔት ዘመን መፅሓፍ ወይም ጥናታዊ ፅሑፍ በማንበብ ስለአንድ አርዕስት ጠለቅ ያለ እውቀት እንዲኖረን ከመሞከር ይልቅ ከዚህም ከዚያም የተለቃቀመ ቅንጥብጣቢ እውቀት ሰበስበን አዋቂ መባል ሊዳዳን ይችላል። በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚደረጉ ጥናቶችም የራስ ጥናት ያልታከለበት የኩረጃ (plagiarism) ውጤት ሊሆን ይችላል። ቴክኖሎጂ በስፖርት የተገነባ ጤናማ ሰውነት እንዲኖረን የሚያግዘንን ያህል የቴክኖሎጂ ሱስ ከብዙ ነገር ሊያስተጓጉለን ይችላል። ተነስተን መንቀሳቀስ ፣ ሰውነታችንን ማማሟቅ ፣ የበላነውን ማድቀቅ እያለብን ሪሞት ይዘን ሶፋ ላይ እምንወዘፍ ፣ የመኪናችንን መሪ የሙጥኝ ብለን የምንይዝ ፣ ኮምፕዩተር ላይ አፍጠን የምንውል ከሆንን ጤናችን እክል ይገጥመዋል። በመንፈሳዊም ህይወታችንም ቴክኖሎጂ መፅሐፍ ቅዱስ ሁል ጊዜ በቀላሉ በእጅ ስልካችን እንድናገኝ ፣ ከክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች የቦታ ርቀት ሳይገድበን እንድንገናኝ ፣ ስብከትና መዝሙር እንድናዳምጥ የረዳንን ያህል ቁጥራችን ቀላል ላይደለን ሰዎች ጊዚያችን እንቶ ፈንቶ በሆነ ነገር እንድናሳልፍ ፣ በቴክኖሎጂ ታግዘው በሚሰራጩ ልቅ የወሲብ ምስሎችና ቪድዮዎች ተጠላልፈን እንድንወድቅ ምክንያት ሆኖናል።

 

8. አምልኮተ-ቴክኖሎጂ (Deifying technology)

ቴክኖሎጂ የሰው ልጅን ችግር በመቀነስና ምቾት በመጨመር የሚያደርገው አስተዋፅኦ የሚካድ አይደለም። ሰው እግዚአብሔር በሰጠው ጥበብና እውቀት ተጠቅሞ የደረሰበት የቴክኖሎጂ ስልጣኔ ኑሮውን ለማሻሻል ሲያውለው ከማየት የበለጠ ምን ደስ የሚል ነገር አለ? ነገር ግን ችግር የሚፈጠረው ሰው በእጁ የፈጠረውን ነገር ከሰው በማስበለጥ ብሎም በማምለክ ፈጣሪውን መካድ ሲጀምር ነው። ይህ ደግሞ የለየለት ውድቀት ይሆናል። ሰው የደረሰበት የቴክኖሎጂ ስልጣኔ አስደናቂ ከሆነ ይህንን መስራት የሚያስችል ጥበብና ማስተዋል ሰጪ ፣ የሰማይና የምድር ፈጣሪ እግዚአብሔር እማ

 

ምንኛ ድንቅ ነው። ሰው ወዶ ራሱን ለአንድ አምላክ ካላስገዛና በእጁ የሚሰራቸው ነገሮች የእርሱ ስጦታ እንደሆኑ እውቅና ካልሰጠ ሳይወድ ምድራዊ ለሆነ ቁሳቁስ ራሱን ያስገዛል። ይባስ ብሎም የሰው ልጅ በእጁ ያሉት ነገሮች ሌሎችን ሊያገለግልበት በባለአደራነት (Stewardship) የተሰጡት መሆናቸውን ከዘነጋ የፈጠረውን ቴክኖሎጂ የገዛ ወንድሙን ለመግዛትና ለመበዝበዝ ሊጠቀምበት ይችላል። ይህም የሰው ልጅን ክቡር ዋጋ አልባሌ (Dehumanize) ያደርገዋል። ሰው ማሽንን የሚያገለግል ሌላ ማሽን ሆነ ማለትም አይደል (Man simply becomes the mechanical servant of the mechanical system.)።

 

ቴክኖሎጂ ጠቃሚ ብቻ አድርጎ ከሚወስድ የቴክኖበላይነት አስተሳሰብ ወጥተን ቴክኖሎጂ በአግባቡ ጥቅም ላይ ካልዋለ ብዙ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ማመን መቻል አለብን። ይህ ማለት ግን ቴክኖሎጂ በራሱ ጎጂ ነው ማለታችን ሳይሆን ሽንኩርት ልንከትፍበት የፈበረክነው ቢላዋ ሰው ላይ ጉዳት ልናደርስበት እንደምንችል ሁሉ ቴክኖሎጂም በጥንቃቄ ተይዞ ለታለመለት አላማ ካልዋለ ጎጂ ሊሆን ይችላል ማለታችን ነው። የቴክኖሎጂ እድገት (technological progress) የሰው እድገት (human progress) ማምጣት ካልቻለ የቴክኖሎጂ ጥቅሙ ምኑ ላይ

 

ነው? በየጊዜው የሚወጡትና እጃችን ውስጥ የሚገቡት የቴክኖሎጂ ውጤቶች ከታይታ በዘለለ መልኩ አጠቃቀማቸውን አውቀን የሚሰጡትን አገልግሎት አሟጠን ለመጠቀም ብንሞክር ራሳችንን እና ወገናችንን እንጠቅምበታለን። ቴክኖሎጂን ከሰው ጋር ያለንን ግንኙነት ለማጠናከርና የሰውን ልጅ ኑሮ ለማሻሻል ማዋል እንጂ የሰውን ልጅ እንዲገዛና እንዲበዘብዝ ልንፈቅድለት አይገባም። ወላጆች በአደራ የተረከብናቸውን ልጆች ቴክኖሎጂን በአግባቡ እንዲጠቀሙበት እንጂ እንዳይጠቀምባቸው መርተንና ገርተን የማሳደግ ኃላፊነታችንን ልንዘነጋው አይገባንም። ሰው እግዚአብሔር በሰጠው ጥበብና እውቀት ተጠቅሞ የሰራቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ከእግዚአብሔር ሊያርቁትና ፈሪሃ እግዚአብሔር ሊያጠፉበት አይገባም። ምዕራባውያን ያስመዘገቡት የሳይንስና የቴክኖሎጂ አብዮት ፈሪሃ እግዚአብሔርን አስጥሎ ፣ ሰውን ከሰው ነጥሎ ሊወጡት ከማይችሉት የማህበራዊና መንፈሳዊ ህይወት መላሸቅ ውስጥ ከቷቸዋል። እኛም ከነሱ ተምረን ያለንን አፍርሰን ከመገንባት ይልቅ መተዛዘን ፣ መደጋገፍና ፈሪሃ እግዚአብሔር የመሳሰሉትን መንፈሳዊ ሃብቶች አስጠብቀን ቁሳዊ ሃብት መጨመሩ ላይ ብንሰራ አትራፊ እንሆናለን። ቁሳዊ ሃብት ማህበራዊና መንፈሳዊ ባዶነታችንን ሊሞላ ይችላል ብሎ ማሰብ ግን ሞኝነት ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው። አንድም የነፍሳችን ጥማት ያረኩልናል ብለን የምናግበሰብሳቸው ቁሳቁስ በእጃችን ሲገቡ የጠበቅነውን እርካታ አይሰጡንም (ተራ ነገር ይሆኑብናል) ፤ ሁለትም ቴክኖሎጂ በየጊዜው ስለሚያድግ (ቶሎ ቶሎ ስለሚለዋወጥ) እና ቁሳቁስ ወዲያው ፋሽንነታቸው ስለሚያልፍ (obsolete ስለሚሆን) ሩጫችን ሁሉ ነፋስን እንደ መጎሰም ይሆናል። መፅሐፍ ቅዱስ በመክብብ 1:8 እንደሚናገረው ‘‘ዓይን ከማየት አይጠግብም ጆሮም ከመስማት አይሞላም።’’

 

  • ጠና ደዎ (2008) ሰው ፣ ግብረገብና ሥነ-ምግባር ፤ የዘመናችን ቁልፍ ጉዳዮች አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ
  • በውቀቱ ስዩም ፣ አልፎ ሂያጁ ማስታወሻ
    Judy Casey (201, December). The Impact of Technology on Work and Family Lives. The Huffington Post. Neil Postman (1993). Technopoly: The Surrender of Culture to Technology. Vintage Books.
    Ricardo De Querol (2016, January) Zygmunt Bauman: “Social media are a trap”. Interview. El País.
Read 8299 times Last modified on Tuesday, 23 August 2016 05:03
ዳዊት ሀይሌ ገብረእግዚአብሔር

ዳዊት ሀይሌ ገብረእግዚአብሔር ለስድስት አመታት ያክል ባንክ ውስጥ ስሰራ ቆይቼ በቅርቡ ከኮፐንሀገን ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የማስተርስ ዲግሪ ተመርቄ ወደ አገሬ በመመለስ ስራ እያፈላለግኩ እገኛለሁ (ከሰማችሁ ጠቁሙኝ)። ጌታን እንደግል አዳኜ ከተቀበልኩ 11 ዓመት የሆነኝ ሲሆን በመንፈሳዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ፅሁፎችን ማንበብ ፣ መፃፍና መወያየትን እወዳለሁ። አስተያየታችሁን አድርሱኝ

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 90 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.