ብዙ ጣጣ ቢኖርበት ''ምን አባቱ " ብለን መተው ከማንችላቸው የሕይወት ጉዳዮች አንዱ መሪነት ነው:: የምናተኩርበት አውድ ቤተ ክርስቲያን ይሁን ወይም ቤተሰብ : አገር ይሁን መንደር መሪነት በጥሞና መታሰብ ያለበት ጉዳይ ነው :: ስለ መሪነት ሳስብ ከማስታውሳቸው ንባቦች አንድ መንደርደሪያ ልውሰድ : ቻርልስ ሲምፕሰን የተባሉ የቤተክርስቲያን መሪ ገጠመኝ ነው ::
"መኪና ተከራይቼ ወደ ሎሳንጀለስ አየር ማረፊያ የነዳሁበት ያ ቀን ትዝ ይለኛል::ከዚህ በፊት መንገደኛ ሆኜ ባውቀውም መኪና እየነዳሁ ለመሄድ ግን የመጀመሪያ ጊዜዬ ነበር ::ባለ ስድስት መስመር ፈጣን አውራ ጎዳና ውስጥ ገብቼ ሳሽከረክር ባለቤቴ የከተማውን ካርታ ይዛ ትረዳኝ ነበር:: ብዙ ከሄድን በኋላ ነው ራሱን ሎሳንጀለስን አልፌ እንደወጣሁ ያወቅሁት::
ምንም አይደል በቂ ጊዜ አለ አልኩና ከዋናው መንገድ ፈቀቅ ብዬ ቀይ መብራት ያቆመውን ነጂ ' ወደ አየር ማረፊያው የምደርሰው እንዴት ነው?' ብዬ ጠየቅሁ::'ወደ ኋላ ዙርና ወደ ደቡብ ሂድ ; የሚቀጥለውን ዋና ጎዳና በቀኝ በኩል ያዝና ብዙ ኪሎ ሜትር ወደ ፊት ሂድ : አታጣውም አለኝ::
ዞረን ወደ ደቡብ ሄድን : የሚቀጥለውን ቀኝ ያዝንና ብዙ ነዳን : ግን ኤርፖርቱ የለም :: ቀኑ እየመሸ መጣ : ጊዜም እያነሰ ነው::'ምን አልባት አውሮፕላኖቹ የሚበሩበት አቅጣጫ ይመራኝ ይሆን?' ብዬ አሰብኩ : ግን እርሱም አልሰራም::
ከዋናው መንገድ እንደገና ወጣሁና 'የቤንዚን ማደያው ሰራተኛ ሊረዳኝ ይችላል' ብዬ ወደ ማደያው መኪናዬን አስጠጋሁ : ቦታው ጨለምለም ብሎአል ::
እባክዎ ሊረዱኝ.....?
እኔ እንግሊዝኛ ስናገር እርሱ በስፓኒሽ ይመልስለኝ ጀመር::
ሌላ የሚረዳኝ.........?
ምንም መግባባት አልተቻለም : ስፓኒሾች ሰፈር ነበር የገባነው ::ቦታው እንደጠፋኝ በደምብ ገባኝ ::በልቤ 'ምነው የማውቀው ባይመስለኝ ኖሮ' አልኩና አንድ መንገድ ላይ ስንወጣ መብራት አቆመን::
'እባክዎን ወደ ሎሳንጀለስ አየር ማረፊያ እንዴት እንደምንደርስ ሊነግሩኝ ይችላሉ?' አልኩና አጠገቤ የነበረውን ሌላ አሽከርካሪ ጠየቅሁ::
'ተከተለኝ ' አለኝና እንደረፈደብኝ ያወቀ ይመስል ይከንፍ ጀመር::
ሰውየውን አላውቀውም : መንገዱን ማወቁንስ በምን አውቃለሁ? አንድ ነገር ግን እርግጥ ነበረ : መንገዱን እኔ አለማወቄ:: እሱ ወደቀኝ ሲዞር እኔም ወደቀኝ: ወደግራ ሲዞር እኔም ወደግራ : ቢጫ መብራት ሲጥስ እኔ ቀይ እየጣስሁ ሲያፈጥን እያፈጠንሁ የ እርሱን ጅራት ብቻ እንደተከተልሁ ከ አስር ደቂቃ ግስገሳ በሁዋላ የሎስ አንጀለስ አየር ማረፊያ ላይ ከቸች ስንል መንግስተ ሰማይ የገባሁ ነው የመሰለኝ:: ምስጋናዬን በታላቅ ፈገግታ ገልጬ ተሰናበትኩትና ወደ አውሮፕላኑ አመራሁ:ለጥቂት ሳይዘጋ ደረስሁ::
መሪነት ምን እንደሆነ የገባኝ ያን ቀን ነው :: መሪነት የሩቅ ጥቆማ አይደለም:መሪነት ማመላከት አይደለም: መሪነት ወደሚፈለገው ግብ ራስ ሔዶ ማሳየት ነው ::
ይህን ያሉት ቻርለስ ሲምፕሰን ናቸው :: የ እርሳቸውን እዚህ ላይ እንግታና ወደ እኛ ወደ ሃገራችን ወደ ቤተክርስቲያናችን እንመልከት::
እኛ መሪዎች አሉን ወይ? ዛሬ በቤታችን ውስጥ : በቤተክርስቲያን : በአገር ደረጃ: በህብረተሰብ መካከል የሚሄዱበትን የሚያውቁ: ወደ ርግጠኛ ግብ የሚገሰግሱ : ይዘው የሚያደርሱን መሪዎች አሉን? እኔ እንጃ! እኔ እንጃ! እኔ እንጃ!
በየቦታው: በየመደቡ : "መሪዎች" መሾማቸው : በየስብሰባው "መሪዎች" መምረጣችን : ማሰልጠናችንና መሰየማችን አልቀረም :: ይህ ሁሉ ግን እርግጠኛ መሪዎች እንዳሉ ማስተማመኛ የሚሆን አይመስለኝም ::ምናልባት እያፈራን ያለነው ''ነገር አርቃቂዎች" ; "ካርታ ነዳፊዎች ብቻ" : " እስከጊዜው ይዤ ልቆይ ተግደርዳሪዎች " : "ኢላማቢስ ተኩአሾች" ወዘተርፈ... ቢሆንስ?ገና በበቂ ያልተመለሰ የመሪነት ጥያቄ አለ : በቤተ ክርስቲያንና ከዚያም ውጭ የ እውነተኛ መሪ ጥማት ሕዝቡን እንዳንገበገበ ነው : ብዙ አይኖች ይንከራተታሉ : "ኑ በዚህ" የሚላቸው ሰው ፍለጋ :: የማን አይኖች? የወጣቶች : የሽማግሌዎች : የሴቶች : የሰባኪዎች; የዘማሪዎች : የነጋዴዎች : የተማሪዎች ...:: ዛሬ ገብተው የሚያስገቡ መሪዎች እንዲበዙልንና በዚህ አገልግሎትም ውስጥ ካለን ገብተን የምናስገባ እንድንሆን ጸሎትና እርምጃ እንጀምር!