You are here: HomeOpinionsጥልቅ ፍሥሓ

ጥልቅ ፍሥሓ

Written by  Monday, 18 January 2016 11:20

በእግዚአብሔር መደሰት ይቻላል? ማለቴ ልናምነው እንችላለን፤ ልንፈራው እንችላለን፤ ልናገለግለው እንችላለን፤ ግን እርሱን ተድላና ፈንጠዝያ ልናደርገው እንችላለን? በሚሰጠን ስጦታ መደሰት እንችላለን፤ ስሙን በየስፍራው እንጠራለን፤ ግን ራሱን እርሱን ስናስብ ደስታ ጢቅ ያደርገናል?

 

ይህ ያለንበት ዘመን ለብዙዎች የእንግልትና የሥቃይ የሞቼ ባረፍኩት ዘመን ነው ቢባልም ወዲያውም ደግሞ መግቻ የሌለው የፈንጠዝያ ፍላጎት ነበልባል የሚንቀለቀልበት ተድላ አሳዳጅ ዘመን ነው፡፡ “ስለሌለኝ ነው እንጂ ቢኖረኝ የዐለሙን ሁሉ ደስታና ጨዋታ በአንድ ጆንያ ቋጥሬ ቤቴ ባገባሁ፤” የሚለው ሰው ብዙ ነው፡፡

 

የሕይወቴ ዋና መሪ፣ የኑሮዬ ዋስትና እግዚአብሔር ነው የምንለው ሰዎች እንኳ በእግዚአብሔር መደሰታችንን እጠራጠራለሁ፡፡ በምን አወቅህ ብትሉኝ ግንባራችን ነገረኛ! ድምጻችን፣ ዐይናችን፣ ሁለንተናችን ያሳጣናል፡፡ ስመ እግዚአብሔር ሲጠራ እንጨምታለን፣ ሰብሰብ እንላለን፣ ሌላ ካባ እንለብሳለን፤ ሰማይ ሰማይ፣ ጣራ ጣራ እናያለን፤ ቃላት እንመርጣለን፤ ቢቻል ቢቻል ጠቅላላው ትዕይንት ቶሎ እንዲልቅም እንፈልጋለን፡፡ እግዚአብሔር እንግዳ ነው፤ እዚያ ማዶ ነው፤ የማይዙት የማይተውት ግድ ነው፡፡

 

መጽሐፍ “እግዚአብሔርን ተድላ አድርግ”1 ይለናል “Enjoy God” እንደሚለው እንግሊዝኛ አቀማመጥ፡፡ ዕንባቆም የተባለ ነቢይ “በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል”2 ይላል፡፡ ጳውሎስ የተባለ ሐዋርያ “በጌታ ደስ ይበላችሁ”3 ይላል፤ ዘማሪው እግዚአብሔርን “ነፍሴ አንተን ተጠማች፣ ሥጋዬ አንተን ናፈቀች” ይልና ሲያገበው ደግሞ “ነፍሴ በቅቤና በሥብ እንደሚረካ ሰው ትረካለች”4 ይለዋል፡፡ 

ደስታን የሚጠላ ማነው? ማንም፡፡ ሆኖም እልፍ ደንቃራ ወደ ደስታ የሚወስደው ጎዳና ላይ የተደረደረ ይመስላል፡፡ በእግዚአብሔር እንዳንደሰት ከሚከለክሉን ነገሮች አንዱ የበደል ወቀሳ ነው፡፡ በደል የሚባለው ነገር አእምሮ የሚፈጥረው ሕልውና የሌለው ጭልታ ወይም ቅዥት አይደለም፡፡ ንጹህ አምላክ እስካለ ድረስና ሳች የሰው ልጅ እስካለ ድረስ በደል ተረት ሳይሆን እውን ነው፡፡ በደለኛነት ደስታ ቢያተፋብን አይገርምም፡፡ የሚገርመው የበደልንና የኃጢአትን ስርየት ተቀብለን ወደ ደስታዊ ግንኙነት መመለስ ስንችል ዳር ቆመን ማልጎምጎማችን፣ መሬት መሬት እያየን፣ ግንባር እያሻሸን፣ ቀኑን እየረገምን፣ ራሳችንን እየተጸየፍን፣ የውሸት ሳቅ እየሳቅን በልብ መሰቀቅ መኖራችን ነው፡፡

 

“ኃጢአታችንን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዐመፃ ሁሉ ሊያነፃን እርሱ ታማኝ ጻድቅ ነው”5 ቃሉን የማያጥፍ ታማኝ ነው፤ ፍርዱን የማያዛባ ጻድቅ ነው፡፡ ስለኢየሱስ ደም ንጽህናና ስለታላቅ ምህረቱ የነፃነት ችቦ ተለኮሰ በዚህ የብርሃን ወጋገን ውስጥ ፍልቅልቅ የሚያደርግ ደስታ አለ፡፡ ኩራትና ሐከሄት ልባችንን ዳተኛ ካላደረጉት በስተቀር የደስታው ምንጭ ቅርብ ነው፡፡

 

ሌሎች ፈንጠዝያዎችም የሰማዩን ደስታ ቦይ ሊደፍኑ ይችላሉ፡፡ ሆዱን ከየጎዳናው ላይ በወደቀ ፍርፋሪ የሞላ እብድ ጤና ሰጪውን እንጀራ እንደምን ያጣጥማል) አበሳችን እኮ በእግዚአብሔር አለመርካት ብቻ አይደለም፣ ለእግዚአብሔር ምላስ ማጣትም እንጂ፤ የአፒታይት እጦት ከእንጀራ እጦት የባሰ ፍዳ ነው፡፡ እስቲ ቆም ብላችሁ የነፍሴ ቀለብ ምንድነው ብላችሁ ጠይቁ፡፡ የወዳጆች ጨዋታ፣ ደስ የሚል መጽሐፍ አዲስ የወጣ ፊልም፣ ሽክ ብሎ መዞር፣ ብር ያሳበጠው የደረት ኪስ፣ በዓይን፣ በእጅ፣ በእግር፣ በአፍ፣ በጆሮ የሚገባው ነገር ሁሉ…… አሁን እኔ ከዘረዘርኳቸው ከአብዛኞቹ ነገሮች ጋር አልጣላም፡፡ ከደጋግ ነገሮች ጋር አታጣሉኝ፡፡ ሆኖም እነዚህ ሁሉ በነፍሴ ሆድ ውስጥ ተጎዝጉዘው የጠገብኩ ያስመሰሉኝ ቀን ቀንደኞች ጠላቶቼ መሆናቸውን አልክድም፡፡

 

ኢየሱስ ክርስቶስ የአንድ አፍታ አዳኝና የፍርድ ቀን ጠበቃ ብቻ እንደሆነ ለምን እናስባለን) እርሱ ራሱ እኮ “እኔ እንጀራ ነኝ” ብሎ እንድንበላው፤ የየዕለት ማዕዳችን ሆኖ ራሱን አቅርቧል፡፡ ይህን ያለው ዓሣ ጥብስ በዳቦ ስለበሉ ሊያነግሡት ለፈለጉ እንጀራ አሳዳጆች ነው፡፡ ዳቦም ዓሣም የሚሰጠን የሚያስደስተን ጌታ ስሙ ይባረክ፤ ዓሣ በዳቦ አጣጥሞ በልቶ ፈገግ ማለት የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ ሆኖም ጌታችንን ዳቦ ጋጋሪ ብቻ አድርገን በነፍስ ራብ መጠውለጋችን አሳዛኝ ነው፡፡ “ሰው እንዳይሞት ይበላው ዘንድ ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ”6 ሲለን ተጋበዙልኛና ተደሰቱብኝ ማለቱ ነው፡፡ በልታች ጥገቡ፣ በቅልውጥ አትሙቱ፤ “ለማያጠግብ እንጀራ” ዕድሜያችሁን አትፍጁ፤ ማለቱ ነው፡፡

 

ኢየሱስን መመገብ ማለት ከእርሱ ሕይወት መካፈል ማለት ነው፡፡ ባልንጀርነቱን፣ ጌትነቱን መድኃኒትነቱን ንጉሥነቱን ጥበቡን ትዕግሥቱን ፍቅሩን ጸጋውን በጥልቅ መረዳት በዚሁም መርካት ማለት ነው፡፡ ሕይወት ከሚተላለፍበት አሸንዳ ሥር መሆን ማለት ነው፡፡

 

“ሥጋዬን የሚበላ፣ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፣ እኔ በእርሱ እኖራለሁ፤ ሕያው አብ እንደላከኝ እኔም ከእርሱ የተነሣ በሕይወት እንደምኖር፣ የሚበላኝም እንዲሁ ከእኔ የተነሣ በሕይወት ይኖራል፡፡”7

 

ይህን ንግግር በቅዱስ ቁርባን ወቅት ብቻ እንዲነበብ የቆለፈበት ማነው) ይልቁን የየዕለቱ ትኩስ ሕይወት ከኢየሱስ ጋር በሚደረግ ተራክቦ የሚገኝ መሆኑን የሚያበሥር ምሥጢር ነው፡፡

 

እኛ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የተጠራን ሠራዊት ተልዕኮአችን ከፍተኛ ተጋድሎ ያለበት መሆኑን አንረሳም፡፡ ከኃጢአት ጋር ደም አፍሳሽ ትግል ውስጥ አለን፡፡ ስለዚህ ግንባራችን ኩስትርትር፣ ጡንቻዎቻችን ግትርትር ቢሉ አይገርምም፡፡ ይሁን እንጂ በጥልቅ ነፍሳች ውስጥ ንጹህ የደስታ ዜማ እንዲቆረቆር ታዞልናል፡፡

 

የክርስቶስ አርበኛ ጳውሎስ እንደሚለው፡-

 

“የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ሐሤት ነው፡፡”8 መንግሥተ እግዚአብሔር የደስታ እንጂ የባርነት ቤት አይደለችም፡፡ ደስታዋም በመብልና በመጠጥ የሚገኝ ብን-ትን የሚል ተርታ ደስታ አይደለም፤ ይልቁን በመንፈስ ቅዱስ የሚገኝ ጥልቅ መሠረትና ዘላቂነት ያለው ሐሤት ነው፡፡ ኦ-መንፈስ ቅዱስ ሌላው አስደሳች፣ ሌላው አጽናኝ፡፡ በእግር ብረት የቆሰለ ገላ ጥዝጣዜ ያላዋቂ ተራቃቂ መርዛም ምላስ የገረፈው ነፍስ ተሸክሞ በውድቅት ሌሊት በእስር ቤት ውስጥ ማሕሌት “የሚያስቆም” መንፈስ በምንም ዓይነት ጨፍጋጋነት ባሕርዩ ሊሆን አይችልም፡፡

 

ኦ! መንፈስ ቅዱስ እውነተኛው አጽናኝ

በልቤ ገብተህ አስደስተኝ፡፡

የነፍሴን መዘውር ንካ፣ የልቤን አውታር አንዝር

የደስታ ጎርፍ ይውሰደኝ፣ በጣዕመ ዜማህ ልሽከርከር፡፡

 

  1. መዝ 37፡4 (የጥንቱ ትርጉም)
  2. ዕንባ 3፡18
  3. ፊል 4፡4
  4. መዝ 63፡1፣5
  5. 1ኛ ዮሐ 1፡9
  6. ዮሐ 6፡50-51
  7. ዮሐ 6፡56-57
  8. ሮሜ 14፡17

  

Read 9701 times
Negussie Bulcha

Website: www.negussiebulcha.com Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 18 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.