You are here: HomeOpinionsየማይናወጥ የዘላለም መሰረት።

የማይናወጥ የዘላለም መሰረት።

Written by  Thursday, 22 October 2015 10:20

ክርስቶስን ማዕከል ያላደረጉ፣ የክርስቶስ ማዳንና የቤዛነት ስራ ደምቆ የማይነገርባቸው፣ የመስቀሉ እውነት የዘላለም የጸና መሰረት እንደሆነ ደጋግሞ የማይታወስባቸውና በዚያ መሰረት ላይ የማይቆምባቸው ቤተክርስቲያኖች ሁሉ መጨረሻቸው አያምርም፡፡ ቅዱሳን ከእነዚያ ጉባኤዎች እግሬአውጭኝ ብለው ሊፈረጥጡ ይገባል፡፡ ምክንያቱም እውነተኛ መሰረት ላይ ስላልቆሙ ጥፋቱ እጅግ ከባድ ነውና!

 

በመጽሃፍ ቅዱሳችን የአማኞች ህይወት እንደቤት ይመሰላል፡፡ እውነተኛ መሰረት ላይ ከተሰራ ምንም አይነት ነገር ቢመጣ የማይናወጥ የማይወድቅ የማይፈርስ ቤት ስለሆነ ተማምኖ ማለፍ ይቻላል፡፡ ካልሆነ ግን ‹‹ቤቱ›› ህይወት ስለሆነ ችግርና ተግዳሮት በመጣ ጊዜ መፈራረሱ አይቀርም፡፡ ያኔ ደግሞ ‹‹ቤቱ›› ‹‹ህይወት›› ስለሆነ ጉዳቱ ታላቅ ይሆናል፡፡ የስህተት ትምህርት ችግሩ እዚያ ላይ ነው፡፡ ትምህርት ብቻ ሆኖ ቢቀር ኖሮ ችግር አልነበረውም፡፡ ‹‹መዝሙር እኮ ነው›› እንዳለው ‹‹ትምህርት እኮ ነው›› ብቻ ብሎ ኑሮውን ግን በጥንቃቄ ይኖር ነበር፡፡ ሆኖም ግን ሰው በሚሰማው ትምህርት ላይ ህይወቱን፣ ተስፋውን፣ ኑሮውን፣ እድሜውን፣ ዘመኑን እየገነባ ነው፡፡ ስለሆነም ያ ትምህርት ያዋጣል ወይ? ያዛልቃል ወይ? ብሎ መጠየቅ ብልህነት ነው፡፡ ለጥያቄው ምላሽ ለማግኘት ደግሞ ጥሩ ምርመራን ማድረግ ይበጀዋል፡፡

 

አንድ ሰው ቤት ሲሰራ ሲፈልግና ግብዓቶቹን ሲሰበስብ ‹‹ይሄ ብረት ወይም ሲሚንቶ ጥሩ ነው ወይ?›› ብሎ ቀድሞ ቤት ከሰሩ ሰዎች ይጠይቃል፡፡ ይሄም ጥቅሙ ከትርፋቸውና ከጉዳታቸው ለመማር ነው፡፡ የአንዳንዱ ምላሽ ‹‹አዎ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ይሄው ቤቴን በዚህ ሲሚንቶና ብረት ነው ከሰራሁት እጅግ ቆየሁ፡፡ አልተሰነጠቀም፤ አልፈረሰም፤ ብዙ እድሳትም አላስፈለገውም›› ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ‹‹ተው ይቅርብህ፤ የኔን ቤት በዚህ ሲሚንቶ ወይም ብረት ሰርቼ ስንቴ እንዳለፋኝ ብዙ እንዳስወጣኝ ልነግርህ አልችልም›› በማለት በጎ ምክሩን ከጉዳቱ ተነስቶ ይመክራል፡፡ ስለሆነም ጉዳዩ የዋጋ መርከስ ብቻ ሳይሆን የዘለቄታዊነትም ጉዳይ ስለሆነ ብልህ ቤተሰሪ ከየትኛው እንደሚማር በምክሩ ላይ ተመስርቶ ይወስናል፡፡

ህይወትም እንዲህ ነው። በአንዳንድ ትምህርቶች ላይ ተንጠላጥለው የኖሩና ከጊዜ በሁዋላ ግን የትምህርቱ ተስፋ ርቆ እንደተሰቀለ ዳቦ የውሸት መሆኑን ሲረዱ እጅግ ተጎድተውና ተሰባብረው ጥጋጥጋቸውን ይዘው ድጋሚ የጌታን ስም መስማት የማይፈልጉ ስንቶች ናቸው? ከተከተሉት ትምህርት የተነሳም በስንት ጣጣ ውስጥ አልፈው ጌታ ረድቷቸው ተላልጠውና ተጋግጠው የተነሱም ጥቂቶች አይደሉም፡፡

 

አሁን በከተማችን ገንነው ከሚሰሙ ትምህርቶች ውስጥ ‹‹የእምነት ትምህርት›› አንዱ ታሪካዊ ትምህርት ነው፡፡ ሰው ትምህርቱን ሲሰማውና በትምህርቱ መነጽር የእርሱን futurity ሲያይ አስተማማኝ፣ ተስፋ ሰጪ፣ የተሳካ፣ የተሟላ….ወ.ዘ.ተ ይመስለዋል፡፡ ትምህርቱ በዚህ ተስፋው እያባበለና እያጫወተ ወስዶ አንድ ስፍራ ላይ ግን ጌታ እንደተናገረው ‹‹ንፋስና ጎርፍ…..›› መጥቶ ቤቱን በሚመታው ጊዜ ቤቱ ሲፈርስ፣ ኗሪውም እጅግ ሲጎዳ ከብዙዎች ህይወት አይተናል፡፡ መሰረቱ ‹‹ክርስቶስ›› አይደለምና ጉዳቱም እጅግ ታላቅ ይሆናል፡፡

 

(‹‹እምነት›› በምህጻረ ቃል ውስጥ የተደረገው አስተማሪዎቹ ‹‹እምነት›› ይበሉት እንጂ መጽሃፍ ቅዱሳዊው እምነት ስላልሆነ ነው! ሐዋርያው ‹‹በውሸት እውቀት ከተባለ ፍልስፍና ራቅ›› እንዳለው ‹‹በውሸት እምነት የተባለው›› ደግሞ ይሄ እንደሆነ ያስተውሏል፡፡) የ‹‹እምነትን›› ትምህርት ብዙ ታላላቅ ሰዎች ሲቃወሙት ‹‹ጭፍን ተቃውሞ›› ይመስለናል፡፡ ሆኖም ግን እንደዚያ አይደለም፡፡ አንድም በቃሉ መነጽር አጉልተው ሲያዩት ‹‹ክርስቶስ ክርስቶስ ›› ይበል እነጂ ክርስቶስን እንደመሰረት ያልተቀበለ ሰዋዊ ፍልስፍና መሆኑን አብጠርጥረው ስላዩት አንድም ደግሞ ሌሎች ሰዎች በዚያ ጎዳና ካለፉ በኋላ የገጠማቸውን ጉዳትና ውድቀት ካዩ በኋላ ነው፡፡

 

የባህርይ ለውጥ የሌለበት፣ የአፍ ብቻ የሆነ ክርስትናን የሚያላብስ፣ ድግምታዊ የሚመስል የአፍ ‹‹confession›› ያመጣልሃል ብለው የሚሉት ብልጽግና ወይም በረከት ውሸትነት፣ የስህተት ምስክርነቶች፣ የሚያገለግሉትን ሰዎች ብቻ ባለጠጋ የሚያደርግ የጮሌዎች መደጎሚያ፣ ለሌሎች ከመኖር ይልቅ ለራስ ማግበስበስን የሚያስኖር፣ ለ‹‹ሁሉም ›› የማይሆንና የተወሰኑትን የሚገፋ መሆኑ፣ የባለጠጎች ስግብግብነትንና አለመርካትን መሰረት በማድረግ ለእነርሱ ብቻ የሚሆን ድሃውና ጎስቋላው ደግሞ የተወሰነ ጊዜ ሰምቶና ጠብቆ አልሆንለት ሲል እየተንገዋለለ የሚወጣበት የባለጠጎች ስብስብ…..ወ.ዘ.ተ መሆኑ ከዳር ቆመን ለምናይ ሰዎች ግልጥ የሆነ መለያ ነው፡፡

 

ከዚያም አልፎ ግን ኢ-መጽሃፍ ቅዱሳዊ በሆኑት ጥልቅ ትምህርቶቹ ሰውን ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር እኩል ለማድረግና በተገላቢጦሹ ክርስቶስን ከፍ ብሎ ካለበት ዙፋኑ ዝቅ ለማድረግ የሚጥርንና የመሳሰሉትን የሃሰተኛው ክርስቶስ መንገድ ጠራጊ ትምህርቶች የሚፈለፈሉበት አሸን ምድብ መሆኑ ደግሞ ሌላው ስነመለኮታዊ ችግሩ ነው፡፡

 

ሰዎች ሆይ አምልጡ! ውጡ! ተለዩ! ወደክርስቶስ መሰረት ኑና ተመስረቱ! በእርሱ ላይም ተገንቡ፡፡ የማይናወጥ የዘላለም መሰረት እርሱ ነውና፡፡ ‹‹እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት መሆን ወደ ፊት አይገባንም፥ ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ!›› ‹‹እነሆ በጽዮን የተፈተነ የማእዘን ራስ ድንጋይን አኖራለሁ፤ በእርሱ የሚያምን አያፍርም!››

Read 6150 times Last modified on Thursday, 22 October 2015 11:07
Yared Ashagre

Website: https://www.facebook.com/Yaredashagre Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 52 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.