You are here: HomeOpinionsዘምር በለው - ስማ በለው

ዘምር በለው - ስማ በለው

Written by  Friday, 06 November 2015 06:37

ዘማሪውና መልእክቱ

 

ዘማሪው አዝናኝ ነው መልእክተኛ? የተጠራው ጉባኤ ሊያደምቅ ነው ወይስ የሳተ ሊያርቅ? በመድረክ ላይ ተውኔቱ ሊያስደንቀን ነው ወይስ ከተፋተነው አምላክ ጋር ሊያስታርቀን? የተደጋገመ÷ የታከተ የቃላት ናዳ በዜማ ገመድ ጎትቶ ሊያወርድብን ወይስ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ወደ ልባችን ዘልቆ ሊናገረን?... ዘማሪው ሥራው ምንድነው?

 

እሺ እስቲ አደብ ገዝቼ ልናገር፡፡ ተዝናኖት (entertainment) መጥፎ ነገር ነው ለማለት አልደፍርም፡፡ ሙዚቃ ያዝናናል፡፡ ይህም የጧት ዕጣው ነው፡፡ አለበለዚያ ቃላት እየቀመሩ ሰሌዳ ላይ መለጠፍ ብቻ ይበቃ ነበር፡፡ የዜማ ዕቃ መሰብሰብ፣ የድምጽ አካላችንን ማሰልጠን፣ ምት ጠብቆ ማንጎራጎር… ምንም ቦታ አይኖረውም ነበር፡፡

 

ክርስቲያን ዘማሪ ከሙዚቀኛነቱ በላይ ግን መልእክተኛ ነው፡፡ “መልእክት የሌለው ዘማሪ÷ ግብ የሌለው ዕውር መሪ”፡፡ መጠየቅና መመለስ ግን ያለብን ተገቢ ጥያቄ “መልእክቱ ምንድነው?” የሚል ነው፡፡

 

የዘማሪው መልእክት የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ነው፤ የወንጌል መልእክት ነው፡፡ ወንጌሉስ ምንድነው? ወንጌሉማ “ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡- በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለተወለደው፣ … ከሙታን በመነሣቱ በኀይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለተገለጠው ስለጌታችንና መድኃኒታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በቃ ሌላ መልእክት የለም? አዎን ምንም ሌላ የለም፡፡ ዕድሜ ዐድሎት ስለዚህ ጌታ ከተናገረ ዘመንም አይበቃው፤ ይህ መልእክት ዜማም አይጨርሰው፤ እንኳን በዚህ ዓለም በዘላለሙም ‘ጊዜ’ ተወርቶ አያልቅም፡፡

 

“ለወደደን፣ ከኀጢአታችንም በደሙ ላጠበን፣መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት እንድንሆን ላደረገ÷ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብርና ኀይል ይሁን አሜን፡፡” ራእይ 1÷6

 

ስለ እርሱ የምንናገረው የገባንን ያህል ነው፡፡ የሚገባንም ወደ መጽሐፉ ቃል የዘለቅን ያህል ነው፡፡ ወደ መጽሐፉ አምላክም የተጠጋን ያህል፡፡ ነቢያቱ÷ ነገሥታቱ÷ ጠቢባኑ÷ ወንጌላውያኑ÷ ሐዋርያቱ የጻፉልን ትልቅ መዝገብ እኮ በእጃችን አለ፡፡

 

እምቅድመዓለም ካባቱ ጋር የኖረው የመለኮት እኩያነቱ÷ የፍጥረት መገኛነቱ÷ ሁሉ በእርሱነቱ÷ የሕዝቡ ምስጢራዊ መሪ ሆኖ የተጓዘበት የምድረበዳ ዐለትነቱ÷ የወደቀች እስራኤል ተስፋ ሆኖ በነቢያቱ አፍ ስለእርሱ ሲነገር የቆየ ትንቢቱ÷ ከሰማየ ሰማያት የወረደበት ምስጢረ ትሥጉቱ÷ በምድር የኖረው እንከን አልባ ሕይወቱ÷ ተዝቆ የማይጨረስ ልሑቅ-ምጡቅ ትምህርቱ÷ ሎሌያዊ ምሳሌነቱ÷ ሰው ወዳጅነቱ÷ የፈውስ የሰላም ምንጭነቱ÷ በሰይጣን መንግሥት ላይ መዝመቱ÷ ልጆቹን ለመሰብሰብና በዓለምም ሊፈርድ ዳግመኛ መምጣቱ፡፡

 

ይህ ሁሉ የዘመሪው ጥሬ ሃብት ነው፡፡ ይህን እየመነዘረ÷ በመንፈስ ቅዱስ ኀይልና ጥበብ እየቀመረ÷ ለሰው አፍአዊ ጆሮ ብቻ ሳይሆን ለዕዝነ ልቡናው መናገር ዋና ጥሪው ነው፡፡

 

“በመንፈሳዊ ቅኔ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ” ማለት’ኮ ይህን የማይለወጥ ወንጌል ለዛሬ እንዲሰማ ጥበባዊ ቃና እየሰጣችሁ መልእክቱን ተቀባበሉ ማለት ነው፡፡

 

እርሱ እኔ እነርሱ

የመዝሙር ነገር ካነሣን እንግዲያው አንድ ግልጥ መሆን ያለበት ብርቱ ጉዳይ በምንም ዓይነት መልእክቱ እኛ ልንሆን እንደማንችል መገንዘባችን ነው፡፡ እኛ መልእክተኞች ነን እንጂ መልእክት አይደለንም፡፡ ስለዚህ የሚበዛውን ጊዜ ወይም ደማቁን ንግግር ስለ እኛ ሳይሆን ስለ እርሱ ልናደርገው ወንጌላዊ ማንነት ያስገድደናል፡፡ ስለ እኛ የምናነሣ ከሆነ እርሱን ለማሳየት እንዲረዳን ብቻ ነው፡፡ የሚዜ ግርግር ሙሽራ ለማድመቅ ነው መሆን ያለበት፤ አጓጉል እያምታታ ሙሽሪትን ካማለለ ግን ነውር ሠራ፡፡ የሰው ሁሉ ዓይን አንድ ቦታ ላይ ብቻ እንዲያተኩር እንዴት ረቂቅ ጥበብ ይጠይቃል”! ብርቱ ኮምጫጫነትም፡፡

 

ዘማሪው የሚኖረው ምድር ላይ ነውና የምድር ሰዎችን ሕይወት የሚመለከት በሰማይ ዕይታ የተቃኘ መልእክት ሊያመጣ ይጠበቅበታል፡፡ ሰዎች ማኅበራዊ ኑሮ አላቸው፤ ይግባባሉ÷ ይጣላሉ÷ ይታረቃሉ÷ ይነጋገራሉ፡፡ ሰዎች እግዚአብሔር በፈጠረው ድንቅ ተፈጥሮ ውስጥ ይመላለሳሉ፤ ሰዎች ይሠራሉ÷ ይበላሉ÷ ይጠጣሉ፤ ከፍጥረት ጋር የማያቋርጥ መስተጋብር ያደርጋሉ፤ ሰዎች ይጋባሉ÷ ይወልዳሉ÷ ቤት ይመሠርታሉ፤ ሰዎች ታሪክ አላቸው በታሪካዊ ማንነታቸው ይኮራሉ÷ ያፍራሉ፡፡ ሰዎች በፖለቲካዊ ዓለም ውስጥ ይኖራሉ ይሠጋሉ፣ ይጓጓሉ፣ ይደናገራሉ፤… እግዚአብሔር አምላክ ስለ እነዚህ ነገሮች ምን ይላል? ዘማሪው እንደ ሰብአዊ ቤተሰብ ይህን ሲታዘብና አብሮም ሲኖር ምን ይሰማዋል? መንፈስ ቅዱስ ለዘመኑና ለሕዝቡ የሚናገረው ምንድነው?

 

“ጻድቅ ሎጥ በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በዓመፀኛ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን ያስጨንቅ ነበርና” ከተባለ ዘማሪው ቢጨነቅ ተገቢ ነው፡፡ ለምን የጭንቀቱን ዜማ አያንጎራጉርም? ለምን የሰማይን ፍርድ እያሰማ አያስጠነቅቅም? ለምን እግዚአብሔርን ለሚፈሩ ታዳጊነቱን አያውጅም?

 

ዘማሪው ከቃሉ የቀዳውን መልእክት ሊያስተላልፍ ይገባዋል ብንልም በየጊዜው የሚነሡ ከጤናማው ቃል የራቁ የተሳሳቱና የሚያደናግሩ ትምህርቶች መኖራቸው አልቀረምና ራሱን ከነዚህ ሊጠብቅም ይገባዋል፡፡

 

“የእውነትን ቃል በትክክል የሚናገር የማያሳፍር ሠራተኛ ሆነህ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ” 2ኛ ጢሞ 2፡15

‘በስግብግብነት ወንጌል’ ዙሪያ የሚናፈሰው ገላባ፣ ለኀጢአት ፈቃድ የሚሰጠው “ሥጋ ዋጋ የለውም የፈለግኸውን አድርግበት” የሚል አጉል ድፍረት “ጸሎትና ልቅሶ ምን ይሠራል ሁሉ ተከናውኗል፤ የኔ ነው ብለህ ብቻ መቀበል ነው” የሚል ባዶ ጩኸት እና ይህንንም የመሳሰሉ የእግዚአብሔርን ሉዐላዊነት የሰውንም በእግዚአብሔር ላይ ተደጋፊነት የሚጻረሩ ለመንግሥተ እግዚአብሔርና ለጽድቁ ጥማት እንዲኖረን የሚቀሰቅሱ ሳይሆን ለምድራዊ ስኬት ከበሮ የሚደልቁ አሰተሳሰቦችን ልብ ብሎ አጢኖ ዘማሪው እንደዚህ ካለው ዐውድማ እልፍ ክንድ ሸረር ሊል ይጠበቅበታል፡፡ ከእውነት ጋር ብቻ ለመቆም የሰማይን እርዳታ መለመን ታላቅ ጥበብ ነው፡፡

 

ስብሐትና ስብከት

የክርስቲያን ዘማሪ ጥሪ ሁለት መስመር ያለው ይመስላል፡፡ አንዱ ክህነታዊ ሆኖ ሰማይና ምድርን ለፈጠረ ለልዑል አምላክ ከኀጢአታችንም ሊያድነን ራሱን ቤዛ አድርጎ ለሰጠን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ውዳሴ ቅዳሴ ማቅረብ ነው፡፡ የዕድሜ ልክ ስብሐት እያሰማ÷ መስዋዕቱን ማሳረግ ጥሪው ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ነቢያዊ ሆኖ የሕዝቡ ባለቤት እግዚአብሔር እንዲያስተላልፈው እንዲናገረው የሚልከውን የፍቅር የምሕረት÷ የፍርድ የቅጣት÷ የዕውቀት የጥበብ÷ የዕርቅ የንስሐ… መልእክት ማስተላለፍ መስበክ ክቡር ጥሪው 

 

ዘማርያንና ዘማርያት እንደየልቦናቸው አወቃቀር÷ ጌታም እንደሚቃኛቸው አንዳንድ ጊዜ ወደዚህ ሌላ ጊዜም ወደዚያ የሚያጋድሉ ቢሆኑም በተቻለ መጠን በሁለቱ ጥሪ መካከል ሚዛን ጠብቀው መጓዛቸው ይጠቅማል ወይም በወል አምልኮአችን ሚዛኑ መገኘት አለበት፡፡ ሁሉም ዘማሪ አንድ ዓይነት መልእክትና ቅዳሴ እንዲያቀርብ መጠበቅ የለብንም ምክንያቱም ቤተክርስቲያንን በምልዐት የሚያንጸው በተለያየ ቀለም እግዚአብሔር የሚልከው ጸጋ ድምር ውጤት ነውና፡፡ ይሁን እንጂ ማንኛችንም ያለ ሰማያዊ መልእክት እየተመላለስን ዘልማድና ተሰጥዖ ብቻ የሚያወዛውዘን ልንሆን አይገባም፡፡

 

ከየትና እንዴት?

ዘማሪው ንጹሕና አስሚ መልእክት ሊያቀርብ የሚችለው ከልዑሉ ገበታ ያልተለየ እንደሆነ ነው፡፡ ዘወትር አሸር ባሸር የሚኖር ሰው ጉልበቱ ቢብረከረክ መላሱም ቢጎለድፍ ምን ይገርማል? ማዕዱ ሰፊና መብሉም ምርጥ ከሆነው ከሰማይ ገበታ የሚውል ግን መንፈሳዊ ወዘናው ደማቅ÷ መልእክቱም ረቂቅ ይሆናል፤ ሲዘምር ያሰማል÷ ቅኔውም ወደ ውስጥ ልቡና ይሠርጋል፡፡

 

ለክቡር አምላክ የሚቀርብ ምስጋናም ሆነ ልመና፣ ለሰው ጆሮም እንዲቀርብ የምናዘጋጀው የዜማ መልእክት ሥነጽሑፋዊ ለዛውም ሆነ የአሳቡ ክብደት ተራ እንዳይሆን ኪናዊ ሸማ ብናለብሰው ያምርበታል እንጂ አያስቀይመውም፡፡ ለሙዚቃ ጥቃቅን የድምፅ ንዝረቶች እንደምንጨነቅ ሁሉ ለመዝሙሩ ግጥምና ቃላት የሰላ ጆሮ ማበጀት ያሻናል፡፡ ሰማያዊው ጌታ የውበት ፈጣሪ  ነው እንጂ ፀረ ውበት አይደለም፡፡

 

እንግዲህ ዘማሪው ምን ይሁን? ወደ ላይ አንጋጣጭ ይሁን፤ መልእክትም ረድኤትም የሚገኝ ከዚያ ነውና፡፡ ደሞ ወደታች መርማሪም ታዛቢም ይሁን፤ የሚናገር መሬት ላይ ለምንገኝ ሰዎች ነውና፡፡ የጥልቅ ነፍሱን አምልኮ ለጌታው ሲያቀርብ እኛም ጆሮአችንን መጣላችን አይቀርምና እንዲገባን አድርጎ ይቀድስ፤ ያን ጊዜ አብረነው ሠራዊተ ስብሐት እንሆናለን፡፡ የሰማይ መላእክትም ሳይተባበሩን አይቀርም፡፡

Read 8486 times
Negussie Bulcha

Website: www.negussiebulcha.com Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 169 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.