You are here: HomeOpinionsአምልኮን ማምለክ

አምልኮን ማምለክ

Written by  Wednesday, 11 March 2015 00:00

በተለያዩ የአምልኮ ስፍራዎች ተገኝታችሁም ሆነ (ቴክኖሎጂ ይመስገንና) በማህበራዊ ድረ-ገጾች ጭምር የአምልኮ ፕሮግራሞችን ተከታትላችሁ የራሳችሁን አስተያየት (ጥሩም ይሁን መጥፎ) በልባችሁ አስተያየት መስጫ ስር አስቀምጣችሁ ታውቁ ይሆናል፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ያነሳሁት አንድ ጥያቄ ተመልሶ ስለመጣብኝ ዛሬ ላወራው ተገድጃለሁ፡፡ አምልኮአችን እግዚአብሄርን እያስደሰተው ነው ወይስ እኛን እያዝናናን ነው? የእግዚአብሄር ህዝብ ረሃብስ ቃሉን ነው ወይስ መዝናናትን? ከዚህ ጥያቄ ትኩሳት ውስጥ ሳንወጣ ሌላ ጥያቄ፤ እግዚአብሄርን እያመለክን ነው ወይስ አምልኮን?


የሙዚቃው ዕድገት፣ ጥሩ ማቀናበር (መክተፍ)፣ በጥሩ ድምፅ መዘመር... ወዘተ የአምልኮ መገለጫ እየሆነ ከመጣ ሰንበትበት ብሏል፡፡ በመዝሙር አስፈላጊነት፣ እግዚአብሄርን በእርሱ ማምለክን፣ ከእውነት በሆነ የዝማሬ አምልኮ ውስጥ እግዚአብሄር ስራን እንደሚሰራ በሚገባ አምናለሁ፤ መፅሀፍ ቅዱሳዊም እውነት ነው፡፡ የምናመልከው እና የምንዘምርለት ዕድሉን ያገኘን እኛ ግን የእግዚአብሄርን አምልኮ የያዝንበት መንገድ እጅግ አሳዛኝ ሆኖብኛል፡፡ ‘አሪፍ አምልኮ ነበር’፣ ‘ቀውጢ ጊዜ ነበረን’ የሚል ትውልድ እየበዛ ሲሄድ እያየን ነው፤ ለመዝናናት እና ለጭፈራ ብቻ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጣ ወጣት እያፈራንም ነው፡፡ የሚዘምር ወይም አምልኮን የሚመራ ሰው መድረክ ሲይዝና ማይክ ሲጨብጥ የጩኸት እና ከያሉበት ለጭፈራ መሰባበሰብን ሳናስበው እየለመድነው ነው፡፡ የጭፈራ እስታይሎችን እየተለማመዱ ለመድረክ የሚዘጋጁና ‘የታለ ሞራል’ የሚሉ ዘማሪዎችን በየመድረኩ ማየትና መስማት ከጀመርንም ቆየት አልን፡፡ የኮንፈራንስ አደባባዮቻችን በጭፈራ ብዛት አቧራውን ሲያጤሱት እና መዝሙር መሪዎች ከምን ጊዜውም በላይ ላብ በላብ እስኪሆኑ ድረስ በጭፈራ ድክም ሲሉ እያየን ነው፡፡ በህዝቡ ዘንድ ከመዝሙራቸው ይልቅ የሚያሳዩት እንቅስቃሴ (Act) መለያቸው እንዲሆን የሚጥሩ መዝሙረኞችን ማየት - ሲብስ ደግሞ መድረክ አልበቃ ብሏቸው ሲሽከረከሩ እየተደነቃቀፉ የማይክ ሽቦ ጠልፎ ሲጥላቸው እያየን እየተሸማቀቅን እየሳቅንም እያዘንንም ነው፡፡


አንድን አምልኮ መንፈሳዊ ነው አይደለም እግዚአብሄር ተቀብሎታል ወይስ ከንቱ ጩኸት ነው ለማለት ልብ የሞላ ድፍረት አይኖረኝም፤ ይህንን የእግዚአብሄር መንፈስ ብቻ የሚያውቀውና ደግሞም የሚወስነው ስለሆነ፡፡ ነገር ግን አምልኮ በነገሮች ላይ የተንጠለጠለ ሲሆን፣ ሙዚቃ ከሌለ አምልኮም ሲጠፋ፣ ሁልጊዜ ሁሉም ሰው እግዚአብሄርን የሚያመልክበት መንገድ ተመሳሳይ ሲሆን፣ እግዚአብሄርን በማምለክ ሂደት ውስጥ ሰዎች የበለጠ ራሳቸውን ለአምላካቸው በማስገዛት ነፍሳቸውን በፊቱ በማፍሰስ እርሱን ከፍ ለማድረግ እነርሱ መውደቅን ካላወቁ፣ ይሄንን አምልኮ ጥያቄ ውስጥ ማስገባት ክፋት የለውም፡፡ ምክንያቱ አንድም አለማወቅ ሊሆን ስለሚችል ማለት ነው፡፡ በአምልኮ ሂደት ውስጥ የምንጠቀማቸው መሳሪያዎች (የሙዚቃ፣ የዜማ፣ የመብራት...) በሙሉ የራሳቸው ጥቅም ቢኖራቸውም በመሳሪያዎቹ ላይ የተንጠለጠለ አምልኮ ግን መሳሪያው ሲኖር ብቻ ማምለክ የምንችል የአምልኮ አምላኪዎች ያደርገናል፡፡


ከምንም በላይ ደግሞ የከፋው ትሁት የሆኑ ጥሩ ስነ ምግባር ያላቸውን ዘማሪዎች ማግኘት እጅግ ከባድ እየሆነ የመምጣቱ ጉዳይ ነው፡፡ የተሰጣቸው አገልግሎት ከላይ እንደሆነ ያልተገነዘቡ (አንዳንዶቹ እንኳን በመድረክ ብዛት ነው ፀባያቸው የተቀየረው፤ ከጥንት ሲጀምሩ እንዲህ አልነበሩም!) ገንዘብ አሳዳጆች፣ ምቾት ፈላጊዎች የሚያደርጉት የአገልግሎት የዋጋ ድርድር ጉዳይም ገራሚ እየሆነ ነው፡፡ አንድ መንፈሳዊ ፕሮግራም ላይ ዝማሬ/አምልኮ ከሌለ ፕሮግራሙ ፕሮግራም አልመስል እያለንም መጥቷል፡፡ እግዚአብሄርን ትተን/ረስተን አምልኮን ስናመልክ እንደዚህ ይሆናል ማለት ነው፡፡ እጅግ አሳሳቢ የሆነው ደግሞ ለብዙዎቻችን እነ ዘማሪ እገሌ ጣዖቶቻችን ሆነውብን እነርሱን የምናመልክ ሁሉ እያስመሰለብን መሆኑ ነው፤ እገሌ የሚዘምርበት ቸርች እየሄድን መካፈል የብዙዎቻችን ልማድ ሆኗልና፡፡


የጠቀስኳቸው መሰረታዊ ችግሮች እያንዳንዳችን ከምን ያክል ከፍታ እንደወረድን እንድናስብ፤ ራሳችንንም እንድናይ ለሌሎችም የለውጥ ምክንያት እንድንሆን ለማሳሰብ (brainstorming) እንጂ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ትንተና ለመስጠት አይደለም፡፡ የእግዚአብሄርን ሰዎችን በፍሬያቸው ብቻ እንድንመስላቸው ቃሉ ያዘናል፤ ከዚህ ውጭ ግን በየትኛውም ችሎታቸው እንድንመስላቸው ወይም እንድንከተላቸው መፅሃፍ አይለንም፡፡ ምክንያቱም ይህ ሰዎችን ወደማምለክ ይዞርብናልና!!! በባህሪያቸው የሚገለጥ የመንፈስ ፍሬን የሚያፈሩ ዘማሪዎች በሙዚቃም ያለሙዚቃም ከነገሮች ሁሉ በላይ ክርስቶስን ለሚያገለግሉት ህዝብ ማሳየት ይችላሉ፡፡ እርሱ ሁልጊዜ ሊልቅ እና ሊታይ ይገባልም ይገባዋልም፡፡ ስለዚህ ትህትናን እንደልብስ በመልበስ ነገሮቻችንን ሳይሆን አምላክን በእውነትና በመንፈስ እናምልክ፤ ሌሎችም እንዲያመልኩት እንርዳ፡፡ ሰዎችን ሳይሆን አምላክን በእውነትና በመንፈስ እንፈልግ እናምልከውም፤ ደግሞም አምልኳችን ከእውነተኛ ህይወት የሚመነጭ ይሁን፤ መንፈስ ለሆነ ጌታ የምናቀርበው አምልኮም በተሰበረ ልብ እና በመንፈስ ሊሆን ደግሞ የግድ ይላል፡፡

Read 7569 times Last modified on Wednesday, 11 March 2015 13:09
Asrat Mulachew

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 353 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.