You are here: HomeOpinionsArt Articleየወንጌል ኪነጥበብ ጽንሰ-ኃሳብ

የወንጌል ኪነጥበብ ጽንሰ-ኃሳብ

Written by  Saturday, 12 July 2014 00:00

ኪነጥበብ  በአጭሩ ሲተረጎም በሰውነት እንቅስቃሴ፤ በቁስ፤ በድምጽ፣ በጽሑፍ፣ በአቀማመጥ፤ በብልሀት ተቀናብሮ የሚቀርብ የሚታይ፣ የሚደመጥ፣ የሚዳሰስ ውበት ነው። ኪነጥበብ በብልኃት፣ በዝርዝርና በጥልቀት ከማከናወን የሚገኝን ውበት ይወክላል። የኪነ-ጥበብ ዓላማውም ተግባሩም ውበትን በውበት ማቅረብ ነው። መጥኖና ቆጥቦ አሳምሮና አቀናብሮ ማሳየት፣ ማስደመጥ - ኪነጥበብ ነው።

 

በውበትና ውብ አድርጎ በመስራት፣ የሰራውንም ለሰው ልጆች በመግለጥ እግዚአብሔርን የሚስተካከለው የለም። የሰው ልጅ ኪነጥበብን የሚማረው ከእግዚአብሔር ነው። ዙሪያችንን ስናስተውል፤ ራሳችንን ስንመረምር የእግዚአብሔርን ማስተዋልና ጥበቡን እንማራለን። መጽሐፍ ቅዱሳችን (የእግዚአብሔር ቃል) ወደር የማይገኝለት የኪነ-ጥበብ መዝገብ ነው። ዛሬ በአለማችን ላይ የመጠቁ ቴክኖሎጂዎች የስኬት ምስጢር በዙሪያችን ያለውን የእግዚአብሔር ጥበብ ጠንቅቆ በማጥናትና በመቀጸል(ኢሚቴት በማድረግ) የተገኙ ናቸው። 

 

የኪነጥበብ ሂደቱም ሆነ ትግበራው (The process and the practice) ማስተዋልና ዕውቀትን ይጠይቃል። “እግዚአብሔር በጥበብ ምድርን መሠረተ። በማስተዋልም ሰማያትን አጸና። በእውቀቱ ቀላያት ተቀደዱ፤ ደመናትም ጠልን ያንጠባጥባሉ።” ምሳ 3፡19-20 ተብሎ እንደተጻፈ። 

 

የኪነጥበብ ዘርፎች

ሥነ-ግጥም (Poetry)፣ ሥነ-ጽሁፍ (Literature)፤ ድራማና ቲያትር (Theatre Arts)፣ የመልዕክት አጻጻፍ (Epistolary Writing)፣ ሙዚቃ (Music)፣ ታሪክ መንገር  (Story Telling)፣ ውዝዋዜና አቋቋም (Dance and Choreography)፣ ፎቶግራፍና ፊልም (Photography and Cinematography)፤ ንድፍና ስዕል (Design and Painting)፤ መፈልፈልና ቅርጽ (Carving and Sclupture)፣ መፋቅና መጥረብ (Carpentry and Hewing)፤ ሥነ-ህንጻና የቅጥር ውበት (Arctecture and Gardening)፤ ቤት ውስጥን ማስዋብ (Interior Decor)፤ ጥልፍ፣ ሽመናና ስፌት (Embroidery and Weaving) ፤ ሸክላ ስራ (Pottery)። መኳኳልና መሸላለም (Makeup and Hair style)፤ የጌጣጌጥ ስራ (Ornament and Jewellery) የመናገርና የመግለጽ ጥበብ (Communication)፤ የህዝብ ግንኙነትና የመገናኛ ብዙሀን ሥራዎች (Public Relation and Media)፣ ጋዜጠኝነት (Journalism)፣ የፋሽን ትርኢት (Fashion Show)፣ . . . በሙሉ ኪነጥበብ ማዕቀፍ ውስጥ ሊካተቱ የሚችሉ የሙያና የስልጠና ዘርፎች ናቸው። 

 

የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን፤ ኪነጥበብና ዓለም

ቤተ ክርስቲያን ከዓለም ይልቅ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል እምቅ የኪነ-ጥበብ መዝገብና ሀብት ይዛለች። በውበት ፈጣሪነት እጹብ ድንቅ የሆነ ችሎታ ያለው እግዚአብሔር አምላክ የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው። ተበልቶ የማይጠገበው የእግዚአብሔር ውብ ቃሉ የቤተ ክርስቲያን መመሪያ ነው። “እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብ ነው፤ . . .” ኢዮ 28፡28 ተብሎ ከእግዚአብሔር የተነገረን የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ የሆነው እግዚአብሔርን መፍራት በምዕመኑና በቤተ ክርስቲያን የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች ዘንድ አለ። ሙያው የሚፈልጋቸውን ዲስፕሊኖች ደግሞ ከዓለማውያን ይልቅ በክርስቲያኖች ዘንድ ስለሚገኝ ቤተክርስቲያንን ለኪነጥበብ መተግበሪያ አመቺ ስፍራ ያደርጋታል።  ታዲያ ምንድ ነው የሚቀረን? ሙያውን ዋጅተን በቤተ ክርስቲያን በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል።

 

በአሁኑ ወቅት ኪነጥበብ በዓለም ውስጥ ያለአግባብ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ነው። ብዙዎቹ የኪነጥበብ ዘርፎች በጠላት ዲያቢሎስ ይዞታ ስር ሆነው ትውልዱን እያረከሱ ወደ ሲኦል የሚያደርገውን ጉዞ በድምቀት እያጀቡት ናቸው። ለምሳሌ ሙዚቃው ለዘፈን፤ ስዕልና ቅርጻቅርጹ ለጣኦት ማስመለኪያ፤ ፊልሙና የፋሽን ትርዒቱ ለዝሙት ንግድና በዚህ አለም ለሚገኝ ክብር ማግበስበሻ እየዋለ ነው። የኪነ-ጥበብ ሙያዎች በአገራችንም ሆነ በውጪው ዓለም የእግዚአብሔርን መንግስት ለማስፋት ከሚሰጡት ጥቅም ይልቅ ለዓለም የሚሰጡት ግልጋሎት ይጎላል። በዚህም ምክንያት ብዙዎቹ የኪነ-ጥበብ ሙያዎች በዓለም ተወርሰው ለእግዚአብሔር ክብር መዋል የማይችሉ እስከሚመስለን ድረስ ዓለምና ገዢዋ የሰውን ልጅ ለማታለያ ዓላማ በባለቤትነት ወርሰው ይዘውታል።  የአገራችንንም ባህል አሳድፈውታል።

 

የኪነ-ጥበብ ውጤቶች የክርስቶስ ኢየሱስን ወንጌል ለፍጥረት ሁሉ የምናደርስባቸው ሁነኛና ውጤታማ ዘዴዎች ናቸው። ለሰው ጥልቅ ስሜት ቅርብ በመሆናቸው በአቀራረባቸው ሰዎችን የሚማርኩት የኪነ-ጥበብ ሥራዎች የክርስቶስ ኢየሱስን ወንጌል በዚህ ትውልድ መካከል በቀላሉና ልብ በሚደርስ መልኩ ለመንገር ተመራጭ ናቸው። የኪነ-ጥበብ ውጤቶች በእግዚአብሔር ቃልና በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ሲሠሩ በጌታ ቤት ያለነውን ካለንበት የዛሬ ክርስትናችን እልፍ አድርገው አዲስ መረዳት ውስጥ ሊያስገቡን የሚችሉ መሳሪያዎች ናቸው። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እስከ ዛሬ ድረስ የተከናወኑት የኪነ-ጥበብ እንቅስቃሴዎች እጅግ አበረታች ውጤት ያስገኙ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። በበቂ ዝግጅት በስፋት ቢከናወን ኪነጥበብ ብዙ ፍሬ ማፍራት የሚቻልበት መስክ መሆኑንም አመላክተዋል። ሙያዎቹን ዋጅቶ ለጌታ ክብር ማስገዛት ከክርስቲያን ባለሙያዎች የሚጠበቅ የመጀመሪያው ተግባር ነው።  ባለሙያዎች ከዓለምና ከዓለማውያን ተጽእኖ ውጭ እንደየዝንባሌአቸው የሚሰለጥኑበትና እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በነጻነት ተሰጥኦአቸውን ለእግዚአብሔር ክብር የሚያውሉበት ሥርአት በቤተክርስቲያን መፍጠር ያስፈልጋል። ህጻናት በኪነጥበብ ሙያ ውስጥ ሲያድጉ የግንዛቤና የአመለካከት አድማሳቸው ይሰፋል። የኪነ-ጥበብ ሥራዎች ሰዎችን ከእግዚአብሔር ቤት እያስኮበለሉ ማስወጣታቸው ቀርቶ ሰዎች ከዓለም ኮብልለው ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚመጡባቸው ሁነኛ መሳሪያዎች እንዲሆኑ ያስፈልጋል። መንፈሳዊ መረጃዎች ከአንዱ ወደ ሌላው፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ በኪነ-ጥበብ ሙያ እየተከሸኑ መተላለፍ አለባቸው። የኪነ-ጥበብ ሙያ ቤተክርስቲያን የተሰጣትን መለኮታዊ ተልዕኮ እንድታሳካ አጋዥ ሆኖ መቀረጽ አለበት። ኪነጥበብ የኢትዮጵያን ባህላዊ እምነት የማደስና ወደ ትክክለኛው ስፍራ የመመለስ ኃላፊነት ያለበት ሙያ ነው።

 

የባለሙያዎች ጥቆማ

ጌትዬ ተፈራ ከአዲስ አአበባ ዩኒቨርስቲ ሥነ-ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት በሚውራል አርት (የግርግዳ ላይ ስዕሎች) ተመርቆ ለ14 ዓመታት ያህል በባህልና ቱሪዝም መስሪያ ቤቶች በማሠልጠን፣ በጥናትና ምርምር፤ በቅርስ ጥገናና እድሳት ላይ የሠራ ወንድም ነው። በኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን በአንድ አጥቢያ ሽማግሌ ነው። ጌትዬ ከሁሉ አስቀድሞ የኪነጥበብ ሥራና ጠቢባኑ ከእግዚአብሔር የተሰጡ ለመሆናቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ አጣቅሶ ትምህርቱን እንደሚከተለው አቅርቦልናል። 

 

የጽሑፍ ጥበብና የድንጋይ ጥርብ ሥራ ቀድሞ በእግዚአብሔር ዘንድ ያለ ለመሆኑ ማስረጃው እግዚአብሔር ድንጋይ አስተካክሎ ጽሑፍን በእጁ ጽፎ ለህዝቡ መስጠቱ ነው። “እግዚአብሔር ከሙሴ ጋር የተናገረውን በፈጸመ ጊዜ በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈባቸውን ከድንጋይ የሆኑ ሁለቱን የምስክር ጽላቶች ሰጠው።” ዘጸ 31፡18 “ጽላቶቹም የእግዚአብሔር ሥራ ነበሩ። ጽሕፈቱም በጽላቶች ላይ የተቀረጸባቸው የእግዚአብሔር ጽሕፈት ነበረ:፡” ዘጸ 32፡16 ንድፍ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይሰጣል። እግዚአብሔር የማደሪያ ድንኳኑን ልክ፤ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን አይነትና መጠን በዝርዝርና በተሟላ ሁኔታ ነው ለሙሴ ያሳየው። “በመካከላቸውም አድር ዘንድ መቅደስ ይስሩልኝ፤ እኔ እንደማሳይህ ሁሉ፤ እንደ ማደሪያው ምሳሌ፤ እንዲሁ ሥሩት።” ልጁ ሰለሞን የሚሰራውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ እግዚአብሔር ራሱ ለንጉስ ዳዊት በዝርዝር በጽሑፍ አሳውቆታል። “ዳዊትም፦ ‘የሥራውን ሁሉ ምሳሌ አውቅ ዘንድ ይህ ሁሉ በእግዚአብሔር እጅ ተጽፎ መጣልኝ’ አለ።” 1ዜና 28፡19 እግዚአብሔር ባለሙያዎችን ከሚያስፈልጋቸው ዕውቀትና ችሎታ ጋር (አርቲስቶችን) አዘጋጅቶ ለአገልግሎት ይለያል፡፡  “እግዚአብሔርም እነሆ ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ እይ ከይሁዳ ነገድ የሚሆን የሆር የልጅ ልጅ፤ የኡሪ ልጅ ባስልኤልን በሥሙ ጠርቼዋለሁ። በሥራ ሁሉ ብልሀት በጥበብም፣ በማስተዋልም በእውቀትም የእግዚአብሔርን መንፈስ ሞላሁበት። የጥበብን ሥራ ያስተውል ዘንድ በወርቅና በብር በናስም ይሠራ ዘንድ ለፈርጥ የሚሆነውን የዕንቁ ድንጋይ ይቀርጽ ዘንድ፤ እንጨቱንም ይጠርብ ዘንድ፤ ሥራውንም ሁሉ ይሠራ ዘንድ። እኔም እነሆ ከእርሱ ጋር ከዳን ነገድ የሚሆን የአሂሳሚክን ልጅ ኤልያብን ሰጠሁ፤ ያዘዝሁህን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ በልባቸው ጥበበኞች በሆኑት ሁሉ ጥበብን አኖርሁ።”  በእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እግዚአብሔር ራሱ ጥበበኛ፤ ጥበብንም የሚሰጥ እርሱ መሆኑን እንረዳለን። ከዚህ በተጨማሪ እሱ የሚሰጠንን ጥበብና እውቀት ለትዕዛዙና ለክብሩ ለሆኑ ነገሮች እንድንጠቀምበት ያዛል። 

 

የሥዕልን ጥበብ እግዚአብሔር በሚከብርበትና እንደ እርሱ ፈቃድ በሆነ መልኩ መሥራትና ጥቅም ላይ ማዋል እንችላለን። ሥዕል በቀላሉ ገላጭና አመላካች፤ ከጽሑፍና ከንግግር ይልቅ መልዕክትን ለማስተላለፍና ለማስተማር የተሻለ አቅም ያለው በመሆኑ በዘመናት መካከል የሥነ መለኮትን ትምህርት ለማስተማር በሥፋት ጥቅም ላይ ውሏል። ከእነኚህ መካከል የሊዮናርዶ ዳቬንቺና የሚካኤል አንጀሎ ስዕሎችን መጥቀስ ይቻላል። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነትና፤ መንፈሳዊ መረዳቶችን አጉልቶ ከማውጣት አንጻር በሥፋት የሚጠቀሰው እ.ኤ.አ. ከ1606 እስከ 1669 የኖረው ኔዘርላንዳዊው ሬምብራንት ሐርመንዙን ነው። ሬምብራንት ቀለም ቅብን፤ ጭረትን፤ ብርሃንና ጥላን ለሥዕል ሥራዎቹ በሥፋት የሚጠቀም ሲሆን በተለይ በጨርቅ ላይ በሚሰራቸው ህትመቶቹ ይታወቃል።    ከሥራዎቹ መካከል ሙሴ ጽላት ሲሰብር(1659)፦ ሙሴ ከእግዚአብበሔር የተሰጠውን ጽላት በቁጣ ከእጁ ሲጥለው የሚያሳይ(ዘጸ 32፡19)፤ የብልጣሶር ግብር(1635)፦ የባቢሎኑ ንጉስ ብልጣሶር  ታላቅ ግብዣ አዘጋጅቶ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ እቃዎች ጥቅም ላይ ይውሉ ዘንድ ባልተፈቀደበት ቦታ በመጠቀሙ ምክንያት አረከሳቸው። በዚህም እግዚአብሔርን ባለማክበሩ ከእግዚአብሔር ተላከች የሰው ጣት በግርግዳው ላይ ወጥታ በአረማይክ ቋንቋ “ማኔ፣ ቴቄል፣ ፋሬስ” ብላ ስትጽፍ የሚያሳይ(ዳን 5፡6) ሦስቱ መስቀሎች(1653)፦ የክርስቶስ ኢየሱስንና በቀኝና በግራው አብረውት የተሰቀሉትን ሰዎች ስቅለት የሚያሳየው የህትመት ሥራው (ሉቃ 23፡32) የሚጠቀሱት ናቸው። በቤተክርስቲያን ያለውን ገሀድ እውነት በሥዕል ማሳየት ይቻላል። በአዲስ አበባ ሥነጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ከ1984 ዓ.ም ተመራቂዎች አንዱ የሆነው ወንድም ቴዎድሮስ አድማሱ ለመመረቂያው ስሎ ያቀረበው ሥዕል ቤት የሚበረብሩ ወታደሮችንና ተገነጣጥሎ የወደቀ አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የመሳሪያ አፈ ሙዝ ተደቅኖበት ያሳያል። ይህንን ሥዕል የተመለከተ ሰው ሌላ አስረጂ ሳያፈልገው በዘመነ ደርግ በቤተክርስቲያን ላይ የደረሰውን ስደት በቀላሉ መገንዘብ ይችላል።    

 

ሦስቱ መስቀሎች (15 በ 18 ኢንች) በጨርቅ ላይ የታተመ፦ በሬምብራንት ሐርመንዙን። በብሪቲሽ ሙዚየም ለንደን የሚገኝ።

 

ይሁን እንጂ አንድ የሥዕል ሥራ ከሚያስተላልፈው መልዕክት ባለፈ ለሥዕሎቹ የሚኖረን የፍቅር፤ ወጣ ያለ አክብሮትና በልብ ውስጥ የተለየ ሥፍራ የመስጠት ዝንባሌ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት። ሥዕሎቹ የማንም ይሁኑ የማን፤ የቱንም ያህል ይዋቡ ከብሩሽ፤ ከጨርቅና ከሸራ ወይንም ከሌላ ቁስ ተሰርተው በፎቶ ኮፒ ማሽን አልያም በሌላ ዘዴ ተባዝተው እኛ ጋር የደረሱ መሆናቸውን እንዳንዘነጋ። የአሳሳል ጥበቡን ማድነቅ የአባት ነው። ይህንን ይመስል ነበር ብለው ወቅቱንና ሁኔታውን ከማሳየት በቀር ስዕሎቹ የተሳለውን ተክተው በልባችን ውስጥ ስፍራ ሲይዙ መንፈሳዊ ነገራችንን ልንመረምር ይገባል። ጠላት ሊያጠቃን ሸምቆ የሚጠብቀው ለተዋቡ ነገሮች በቀላሉ የሚሸነፈውን ደካማ ጎናችንን ስለሚያውቅ ነው። የሥዕሎቹ ውበትና የመወከል አቅማቸውን ብቃት ተመልክተን ልንስማቸው፣ ልንሳለማቸው፣ ልናወጋቸው . . . ከዳዳን ክፉው መሹለኪያ ቀዳዳ አግኝቶ ወደ ልባችን ለመግባቱ ምልክቶች ናቸው። መረሳት የሌለበት የአምላካችን ጽኑ ትዕዛዝ አለ፦ “በላይ በሰማይ ካለው፤ በታች በምድር ካለው፤ ከምድርም በታች በውኃ ካለው የማናቸውንም ምሳሌ፤ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ፤ አትስገድላቸው፣ አታምልካቸውም” ዘጸ 20፡4-5 ሥዕላሥዕሎችን ማሽሞንሞን፤ ማጠን፤ መሳምና መሳለም ከጣዖት አምልኮ ጋር ዝምድና ያለው እግዚአብሔር የሚጠላው ተግባር ነውና ከዚህ አይነቱ ልምምድ ፈጥነን ልንርቅ ይገባል። 

 

ሠዓሊያን፣ ቀራጽያን ሌሎችም የኪነጥበብ ባለሙያዎች እንደ ሌላው ሰው ሁሉ ክርስቶስ ኢየሱስ የሞት ዕዳ ጽሕፈታቸውን ሰርዞ የዘላለምን ህይወት ሊያወርሳቸው ሞቶላቸዋል። በክርስቶስ ኢየሱስ አምነው በእግዚአብሔር ልጅነት በተሰጣቸው የከፍታ ደረጃ መመላለስ ይገባቸዋል። በሥራዎቻቸውም የእግዚአብሔርን መንግስት ምሥጢር ለፍጥረታት ሁሉ መግለጥ ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ ከሚጠፋ ዓለም ጋር ሊጠፉ የተገቡ ሥራዎቻቸውን እያመረቱ እነሱም ጠፍተው እንዳይቀሩ ሳይውሉ ሳያድሩ ማንነታቸውንና ጊዜአቸውን ከተቆጣጠረው የአዕምሮ መጠበብና የእጅ ሥራቸው ለአፍታ ያህል እረፍት ወስደው መንገድም፣ እውነትም፣ ህይወትም ከሆነው ከክርስቶስ ኢየሱስ ተርታ ሰልፋቸውን ያስተካክሉ። 

 

ቤተ ክርስቲያን ይህንን ለመሳሰሉት የሙያ ዘርፎች ሥፍራ መስጠት፤ በጌታ ቤት ላሉት ባለሙያዎች ጆሮዋን ማዋስ ይገባታል። ሙያውንና ሙያተኞችን በክርስቶስ ኢየሱስ ደም ዋጅታ በቅዱስ መንፈሱ ቀድሳ ለወንጌሉ ሥራ የምታውልበትን አዲስ አተያይ በመሪዎቿ ዘንድ ማንሸራሸር፤ ዕቅድ መተለምና ሳትውል ሳታድር ወደ ተግባር መሸጋገር ይጠበቅባታል። 

 

ያሬድ ተሾመ ገጣሚና የቲያትር ጥበባት ባለሙያ ነው። “ሞኙ ምስጢረኛ”፣ “ፍለጋ” የተሰኙ የግጥም መድብሎችን አሳትሟል። ያሬድ አንድ ግጥሙንና ኪነጥበብ ለወንጌል ሊኖር የሚገባውን ግልጋሎት አስመልክቶ ቀጥሎ ያለውን ሀሳብ አካፍሎናል።

የመስታወትገበያ

እንዲያ ባቶቢሱ፣ በጐኑ መስታየት

እንዲያ በመሂና፤ በጐኑ መስታየት

እንዲያ ‘ዳልተጋፋን፤ መልካችን ለማየት

እንዲያ ዳልተሳልን፤ እሱኑ ለመግዛት

ቀን ወጣለትና፣ መስታወት ረክሶ

አሁን ጥንቡን ጥሎ፣ አገናው ቀንሶ

አይን ኩል ተኩሎ፣ ፀጉር ተተኩሶ

ሁሉ አበጣሪ ሁሉ ባለ ጋርሶ

ሁሉ ሆነ መልከኛ፣ ሁሉ ከማን አንሶ

ጉድፉን ተመልካች አቁሞ ምሰሶ፡፡

ጁን 2008

 

በወንድምህ ያለውን ጉድፍ ስለምን ታያለህ?

በአይንህ ግን ያለውን ምሰሶ ስለምን አትመለከትም?

ማቴ 7፡3

 

ኪነጥበብ ለዛ ባለው አቀራረቧ ዓለምንና ዓለማውያንን የመማረክ ጸጋ አላት። ኪነጥበብ የእግዚአብሔርን ምስጢር እንድናውቅ ከላይ የተሰጠን ችሎታ ነው። ኪነጥበብ ለተለመደው የወንጌል ሥብከት አማራጭ፣ የሚስብና ማራኪ ዘዴ ሆኖ መቅረብ ይችላል። በምንሰራቸው የሚስቡ የኪነጥበብ ሥራዎቻችን የሰዎችን ትኩረት ማግኘት እንችላለን፤ ቀጥሎም በምንኖረው ኑሮና በምንናገረው መልዕክት ሰዎችን በወንጌል እንገዛለን። የኪነ-ጥበብ ሥራዎች ቤተክርስቲያን ወደ ዓለም ከምትዘረጋቸው እጆች ዋናዎቹ ሆነው መቀረጽ ይችላሉ። ወንጌል በኪነጥበብ ተሰብኳል። ክርስቶስ ኢየሱስ በርካታ ትምህርቶቹን በምሳሌ አቅርቧል። የተለያዩ የትረካ ሥልቶችንም ተጠቅሟል። መጽሐፍ ቅዱስ የተሳካለት(ፐርፌክት) የሥነ-ጽሑፍ ሥራ ነው። የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎች በውበታቸውም ሆነ በአቀራረባቸው ሰዎችን የማዕዘን ራስ ወደ ሆነው ወደ ክርስቶስ ኢየሱስ የማዳን ሥራ የሚጠቁሙ ከሆነ የመንፈሳዊነታቸው የመጀመሪያው መስፈርት ነው። ተራው ሰው ዕለት ዕለት ከሚኖረው ኑሮ ላይ በመነሳት፤ ሁሉም የሚነጋገረውንና የሚያግባባንን ቋንቋ በመጠቀም፤ በገሀድ የሚታየውን እውነት ሳንክድና ሳንሸሽ እጅግ ጥልቅ የሆነ መንፈሳዊ መልዕክት ማስተላለፍ ይቻላል - በኪነጥበብ። ዓለም ከነሥርዐቷ ምንኛ ፍትህ አልባ እንደሆነች ለሌሎች የምናሳውቅበት በምትኩም የእግዚአብሔርን መንግስት ውበትና ደስታ የምንገልጽበት፤ አለምና ዓለማውያንን የምንወቅስበት፤ ዘላለምን በሕይወት ለመኖር ዘዴው በክርስቶስ ኢየሱስ አዳኝነት ማመን ብቻ እንደሆነ የምንመሰክርበት፤ ትውልድን ከሚሄድበት የተሳሳተ ጎዳና እንዲመለስ የማንቂያ ደወል ማቃጨል የሚቻልበት፤ መርገምን ሊያሰብር የሚችል መረዳት ውስጥ ገብተን ሌሎችን የምናስገባበት ውጤታማ ዘዴ ኪነጥበብ ነው። ይህ ደግሞ ለኪነጥበብ የተሰጠ ጸጋ ነው። በኪነጥበብ ሥራዎች ውስጥህን ትገልጻለህ። በኪነጥበብ ራስህን ትተህ የሌሎችን ጩኸት መጮኽ ትችላለህ። በውበት ውስጥ የዚህን ዓለም አላፊነትና ከንቱነት ማንጸባረቅ ትችላለህ። የክርስቲያንም የዐለማዊም የጋራ መለኪያ የሆነውን ሞራልና ግብረገብ መንፈሳዊ መነሻቸውን በማጉላት ተቀባይነታቸውን ታጠናክራለህ። የዘመኗ ቤተክርስቲያን ኪነጥበብን በተገቢው መጠን ጥቅም ላይ ስታውለው አትስተዋልም፡፡ ኪነጥበብን ከዓለም መማረክና ወደ ሥፍራው መመለስ ያስፈልገናል። 

 

ቤተክርስቲያን በተለምዶው እየሄደችበት ባለው ባህላዊ መንገድ ብቻ ፍልሚያውን መምራት የውጊያው ስትራቴጂ ከመኸሩ ብዛት ጋር እንደማይጣጣም ያሳየናል። በዚህ ረገድ ብዙ እየተሠራ አይመስለኝም። ቤተክርስቲያን ከለመደችው አካሄድ ጎን ለጎን ኪነጥበብን እንደ ሌላ አማራጭ የወንጌል መልዕክት ማስተላለፊያ መንገድ ጥቅም ላይ ማዋል ይጠበቅባታል፡፡ ቤተክርስቲያን የላቀ ብቃት ያላቸውን የኪነጥበብ ሥራዎች እየያዘች ወደ ሰፊው አውድ መዝለቅ አለባት። እውነቱ የእግዚአብሔር ቃል ነው። ቃሉ በእጃችን ነው። ውበቱንና ህያውነቱን አጉልተን በሥነ-ግጥም፤ በፊልም፣ በቲያትር . . . ይዘን ልንወጣ ይገባል።

 

ወንድም ከበደ መርጊያ የፊልም ባለሙያ ነው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የብዙኀን መገናኛ (ማስ ሚዲያ) መምህር ሆኖ አገልግሏል። አሁን “የመዳን ቀን” የተሰኘ መንፈሳዊ የቴሌቪዥን ፕሮግራም  ያቀርባል። ከበደ መገናኛ ብዙሀንን (ኪነጥበብን) ለወንጌል ሥራ ለማዋል ሊደረግ የሚገባውን ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንደሚከተለው ይጠቁመናል። 

 

ሚዲያ ስንል በርካታ ነባርና አዳዲስ የብዙሐን መገናኛ ዘርፎችን፦ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ ሕትመት፤ የጥበብ ዘርፎች፦ ሥነጽሑፍ፣ ሙዚቃ ወይንም ዝማሬ፣ ድራማ፣ ፎቶግራፍና ፊልም፤ እንዲሁም ዘመኑ ያፈራቸው አኒሜሽንና ኢንተርኔት ብሎም እዚህ ውስጥ ያልተጠቀሱትን ሌሎች የመረጃ ማስተላለፊያ ዘዴዎችንና አውታሮቻቸውን ያጠቃልላል። በእነኚህ የሙያ ዘርፎች ረገድ ቤተክርስቲያን ገዢ መሬትን(ከፍታን) ለመያዝ ያመቻት ዘንድ ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የሚዲያ ጥምረት(አውታር) መመስረት ግድ ይላል። ጥምረቱ የመቋቋሙ አስፈላጊነት ያለንን ዕውቀት፣ ልምድ፣ ገንዘብና መሣሪያ በመጋራትና በመደጋገፍ የእግዚአብሔርን መንግስት ሥራ ለማፋጠን የሚካሄደውን ጥረት ማገዝ፤ የሚዲያንና የብዙሀኑን ሥሜትና ትኩረት መሳብና ከተፈለገው ዓላማ ጎን እንዲቆሙ ለማድረግ ያለውን ኃይል ለወንጌል ትምህርትና ስርጭት በሙላት መጠቀም ማስቻል ነው። በተለይ ህጻናትና ወጣቶች በእግዚአብሔር እምነትና ፍቅር ውስጥ እንዲያድጉ የሚረዱ፤ በአሁኑ ጊዜ ቴሌቪዥንና ኢንተርኔት የሚያራግፉባቸውን የማደናገሪያ ፊልሞች የሚተኩ ፕሮግራሞችን ተረባርቦ ማዘጋጀት ያስፈልጋል። የሚዲያና ኦዲዮ ቪዥዋል አገልግሎቶችን በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት በዲኖሚኔሽን ደረጃ፤ በክልል፣ በአጥቢያዎች፣ በሕብረቶች፣ በገጠርና በከተማ በዓለም አቀፍ ደረጃ አስተባብሮ አሁን የተጀመረውን ራዕይ ማሳደግ ያስፈልጋል። በሚዲያ አገልግሎት ውስጥ የሚያገለግሉ ወገኖችንም ሙያዊ ብቃት ማሳደግ። የዚህ ቅንጅት ግብ መሆን ያለበት ሙያዊ መስፈርቶችን ያሟሉ ስብከቶችን፣ ትምህርታዊ ፕሮግራሞችን፣ ቃለ መጠይቆችን ወዘተ፤ በተንቀሳቃሽ ምስል ወይንም በቪዲዮ፤ በአኒሜሽን፣ በፎቶግራፍ፣ በድምጽና በጽሑፍ ቀርጾና አቀነባብሮ በዲቪ፣ በዲቪዲ፣ በቪሲዲ፣ በሲዲ በተፈላጊው ፎርማት ማዘጋጀት። ይህንን ውጤት ለማምጣት መጋቢዎች፣ ወንጌላውያን፣ መምህራን፣ ነቢያት፣  ሐዋርያት፣ መዘምራን  . . . ሌሎችም አገልጋዮች ሰዎችን በወንጌል ለመድረስ በሚያቅዱበት ጊዜ ራዕያቸው ላይ በመመስረት መወያየት፣ በየደረጃው ጥናት ማድረግ፣ መጸለይ፣ ለአሠራር አመቺና ከአገልግሎቱ ባህርይና ሊደረሱ ከታቀደላቸው ወገኖች አንጻር አመቺ የሆኑትን የመገናኛ ብዙሐን አይነቶች መምረጥን ይጠይቃል። ክርስቲያን ባለሙያዎች የሙያ ሥነምግባርን አሟልተው መገኘት፤ መንግስት ለሚያወጣቸው ህጎች ተገዢ ሆኖ መገኘት፤ ከሁሉ በላይ በቅድስና ማገልገልን መርህ አድርገው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል። በሚገኙት የሥልጠና እድሎች እራሳቸውን ከዘመኑ ቴክኖሎጂዎች ጋር ማስተዋወቅም ተወዳዳሪ ሆኖ ለመስራት ይጠቅማል። ውጤቶቹን ለብሮድካስት ሚዲያ(ለሬዲዮና ቴሌቪዥን)፣ ለህትመት፣ ለግለሰቦች በነፍስ ወከፍ፣ በኢንተርኔት ድረ ገጾች በማሰራጨት የወንጌል ሥርጭትን ማገዝ ይቻላል። 

Read 10120 times Last modified on Monday, 14 July 2014 21:58
Mihret Massresha

Theatre Arts and Communication Practitioner, Gospel Art Curator and The Ethiopian Full Gospel Believers Church Public Relation Head

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Latest from Mihret Massresha

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 199 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.