You are here: HomeOpinionsቅባቱ በዛ

ቅባቱ በዛ

Written by  Thursday, 24 April 2014 00:00

ለአጠቃላይ ምርመራ የሰጠሁትን ደምና ሌላም ሌላም ናሙና ሐኪሙ ዘንድ ቀርቦ ውጤት ለመስማት ወደ ጤና ተቋሙ አመራሁ፡፡ ሐኪሙም የኮምፒውተሩ ምስል ላይ ዐይኑን ተክሎ ከላብራቶሪ የተላለፈለትን መረጃ እየተመለከተ ትንተናውን በአኀዝ ደግፎ አቀረበልኝ፡፡

 

“ይሄ እንዲህ ነው የመጣው…ስለዚህ ጥሩ ነው…ያም እንዲህ ነው” እያለ እንከን አልባ ባይሆንም በህክምናው ሚዛን ሰናይ ሊባል የሚችለውን ውጤት ዘረዘረልኝ፡፡ ‘“ጉድ’ ኮሌስትሮልህ” ግን መጠኑ ዝቅተኛ ስለሆነ እርሱን ማጎልበት አለብህ አለኝ፡፡ “ጉድ ኮሌስትሮል ምንድነው?” አልኩ፡፡ ስለ መጥፎው እንጂ ስለ ጥሩው ብዙ እንደማይታወቅ ሌሎችም የመረጃ መረብ (ኢንተርኔት) መጣጥፎች አረጋገጡልኝ፡፡ 

 

ኮሌስትሮል በደም ውስጥ የሚገኝ ጠጠር ያለ ንጥር ሲሆን የሚመረተውም በጉበት ነው፡፡ ለሴሎች አስፈላጊ የሆነው ይሄ ውኀድ ለሐሞት አሲድና ሌሎችም ሆርሞኖች ግንባታ ዋነኛ ግብአት ነው፡፡ ስብ ተሸካሚ የሆነው የህ ንጥር ሲበዛ ግን ዋነኛ የደም ባንቧን ቀስ በቀስ በመዝጋት ደም ወደ ልብ እንደልብ እንዳይደርስ በማድረግ ከፍተኛ የጤና መስተጓጎል ሊያስከትል ይችላል፡፡ ይሄ እንግዲህ “መጥፎ” የሚባለው ነው፡፡ “ጥሩው” በበኩሉ በደም ስር ውስጥ የተጋገረውን እየቀረፈ ወደ ጉበት በመመለስ ከሰውነት እንዲወገድ ያደርጋል፡፡ መጥፎውን ስብ የበዛባቸውን ምግቦች በመቀነስ መቆጣጠር ሲቻል፣ ጥሩውን ደግሞ በሰውነት እንቅስቃሴ ማበልጸግ ይቻላል፡፡ 

 

ሙሉ ወተት (ቅባቱ ወይም ቅቤው ያልወጣለት) ለምሳሌ በሰውነታችን ውስጥ ያለውን የቅባት መጠን ከተፈላጊው በላይ ስለሚያደርገው የኮሌስትሮልን መጠን ያበዛል፤ ያም ከደም ጋር ተዋኀዶ ሲመላለስ በየስፍራው እየተንጠባጠበ ቧንቧውን እያጠበበ ይሄዳል፡፡ ውጤቱን እንግዲህ ማሰብ ነው፡፡

 

ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ ገጠመኙ መንፈሳዊው ላይ የሐሳብ ጥላ አሳረፈ፡፡ ሰው እንደአካለዊው ሁሉ መንፋሳዊውን ምግብ ቤቱም ውጭም ነው የሚያገኘው፡፡ እንደውም አብዛኛው፣ ስለሚቀል ወይም ይሻላል ብሎ ስሚያስብ፣ ከቤቱ ውጭ በየቤተ ክርስቲያኑና በየፕሮግራሙ የሚበላው ነው ሕልውናውን ያቆየለት፡፡ 

 

የውጪ ምግብ ግን አቀራረቡ እንጂ አሠራሩ መች ታውቆ! ቢጥም ለምላስ እንጂ ለሰውነት ጤና መሆኑ አይፈተንም፡፡ ቅባት ያለው ምግብ ለዐይን ወዙ፣ ለምላስ ጣዕሙና ለአፍ ምቾቱ ለየት ይላል፡፡ ቅባት የበዛበትም ስብከት (ትምህርት) እንዲሁ ነው፡፡ (ይህ ማለት ግን የመንፈስ ቅዱስን ማረስረስ ለማመልከት አይደለም፡፡) “ባርኮት” (ያውም ምድሩን ያገናዘበ)፣ “መከናወን”፣ “መውጣት”፣ “መውረስ”፣ “ራስ መሆ”ን፣ “ጥርመሳ”፣ ወዘተ ብቻ ከሆነ ቅባቱ በዝቷል ማለት ነው፡፡ 

 

ከሰማዩ ገበታ የተቅለጠለጠውን ብቻ መርጦና እርሱን አዘጋጅቶ በማቅረብ ሕዝብ ለአሁን እንዲጠረቃ ወይም ደስ እንዲለው ማድረግ ይቻላል፡፡ በሽታን (ገዳይ ስህተትን) ለመከላከል፣ ዕድገትን ለመጠበቅና ብስለትን ለማረጋገጥ ግን አይቻልም፡፡ 

 

በብዙ “አሜን” የታጀቡ መልክቶች አሉ፡፡ ደስታና ኹካታ እንዳለበት ገበታ እንዲህ ዐይነት መልእክቶች ያሉበት ጉባዔም እንዲሁ ነው፡፡ በተመጠነ ጊዜ ወይም አልፎ አልፎ ይህ ሊያስፈልገን ይችላል፡፡ ሁልጊዜ ግን ልንሻው ወይም ልንሠራው አንችልም፡፡

 

የዕብራውያን ጸሐፊ እንዲህ አለ፤ “ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅምና፤ ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በሥራቸው የለመደ ልቦና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው” (ዕብ 5፣13-14)፡፡ “ጠንካራ ምግብ” ካልጀመርን ሕፃን መባል አይቀርልንም፡፡ የስቡ መብዛት አንዱ ችግር ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ገብቶ መስመሩን ዘግቶ ሌላው ለሰውነት የሚያስፈልገው ንጥር ትምህርት እንዳያልፍ መከላከል ነው፡፡ 

 

“መልክ በአፍ ይገባል” እንዲሉ ሰው የበላውን ነው የሚሆነው፡፡ መንፈሳዊ ማንነት ደግሞ የዘላለም ስለሆነ ለዘላቂው እንጂ ለአሁን ብቻ እንዴት ይታሰባል? “በያይነቱ” እንዲሉ የተመጣጠነው የነፍስ ምግብ ይቅረብ፤ አለበለዚያ ጥጋብ-ቁንጣን ብቻ ይሆንና በወዲያኛው (በስኬት ስብከቶች ባልተዳሰሰው) የሕይወት ምዕራፍ ሲገቡ በቂ ኀይል ጠፍቶ የሚወጡት አቀበት የሚወድቁበት ይሆናል፡፡ “የተማረና የበላ አይወድቅም!” ነው ያሉት፤ መቼም አመጣጥኖ ያደረገ ማለታቸውም እንደሆነ አስባለሁ፡፡ 

አጥግቦ ያርካችሁ!

 

Read 19251 times Last modified on Thursday, 01 May 2014 09:58
Nahu

Nahusenay Afework is a freelance writer and communications consultant. His study at Addis Ababa University earned him MA in Literature. He takes pleasure in writing and consulting people. He is also involved in church ministry in the domain of teaching.

Website: https://www.facebook.com/nahusenay.afework Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
More in this category: Who is in control? »

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 194 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.