You are here: HomeTheologyጤና ቢሱ ነገረ ክርስቶስ

ጤና ቢሱ ነገረ ክርስቶስ

Written by  Saturday, 21 May 2016 07:16

ራሱን ሐዋርያ ያደረገው ዘላለም ጌታቸው (ፖዝ)፣ “ኤክሶደስ ቲቪ ሾው” ከተሰኘ የቴሌቭዥን ፕሮግራም ጋር በቅርቡ ቃል ምልልስ አካሂዷል። በዩቲዩብ በተለቀቀው በዚህ ውይይቱ፣ የተዛቡና ጤና ያጡ ትምህርቶቹ ተቀባይነት እንዲያገኙ በብዙ ሲጥር ታይቷል። “ፓስተር ነኝ” የሚለው ፍሬው ቤዛ ደግሞ፣ “ከእውነት የሚበልጥ እውነት” የሚል ርእስ ሰጥቶ በዚህ ዓመት ባሳተመው መጽሐፍ፣ እንደዚሁ በርካታ ጤና ቢስ አስተምህሮዎችን እያስተላለፈ ነው።

 

እነዚህ ሁለት ሰዎች ኢትዮጵያዊቷ ቤተ ክርስቲያን ለገባችበት የአስተምህሮና የልምምድ ውጥንቅጥ ማሳያዎች ናቸው ማለት ይቻላል። የቤተ ክርስቲያን የአስተምህሮና የልምምድ ውጥንቅጥ፣ ከዕለት ዕለት እየከፋ ሄዷል። የአስተምህሮው መበላሸት ወደ ተበላሸ ልምምድ፣ የልምምድ ብልሽቱም ወደ ተበረዘና ድብልቅልቁ ወደ ወጣ አስተምህሮ እያንደረደራት፣ የማይበጠስ አዙሪት ውስጥ የከተተን ይመስላል። ምንም እንኳ ብርዘቱ ብዙውን ጊዜ የሚያነጣጥረው ነገረ (ትምህርተ) ክርስቶስ ላይ ቢሆንም፣ ነገረ እግዚአብሔር እና ነገረ ሰብእም ከዚሁ ጋር ተቈራኝተው እየተበረዙ ነው። ይህ ጽሑፍም የሁለቱን ግለ ሰቦች አጓጉል ትምህርቶች በመጠኑ ዳስሶ ጤናማውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ በግልጽና በቀላል ቋንቋ ለማቅረብ ይሞከራል።

 

ይህም ጽሑፍ ይፋ ከመሆኑ በፊት ሁለቱን ሰዎች በማነጋገር ጽሑፉን በቅድሚያ እንዲያገኙት ተደርጓል። ከጥቂት ቀናት በኋላም፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ የተገለጠ አምላክ፣ “ፍጹም ሰው፣ ፍጹም አምላክ” መሆኑን ያምኑ እንደ ሆነ ይህንኑ በይፋ እንዲገልጡ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። ነገር ግን ኢየሱስ በምድር አምላክ እንደ ነበረ ለማመን ፈቃደኞች ሆነው አልተገኙም።

 

1. አጓጉል ትምህርቶች

ዘላለም ጌታቸው ከላይ በጠቀስነው ቃለ ምልልሱ፣ ጤናማ ያልሆኑ አስተምህሮዎቹ ጤናማ አስመስሎ ለማቅረብ ሲጣጣር ነበር። እነዚህም ከነገረ ክርስቶስ ጋር የተቈራኙ ሲሆኑ፣ ለዛሬ አንዱን ብቻ መዝዘን እንመለከታለን። ዘላለም በውይይቱ ውስጥ ኢየሱስ በምድር ሳለ አምላክነቱን አለመጠቀሙን ለማስረዳት የሚሞክር ቢመስልም፣ ወጥነት በሚጎድለውና እዚህም እዚያም በሚረግጠው ሙግቱ የሚያስተላልፈው መልእክት ግን፣ ጌታችን በምድር ሲመላለስ “ሰው ብቻ ነበር” ብሎ እንደሚያምን የሚያስረዳ ነው። ኢየሱስ በምድር ሲኖር አምላክ እንደ ነበር ይህ ሰው አንዴም ለመናገር አለመድፈሩን እና ቃለ መጠይቅ አቅራቢዋም እንዲህ በማመኗ ሲያጣጥላት መታየቱን ለዚህ በዋቢነት መጥቀስ ይቻላል።

 

ይኸው ግለ ሰብ “የኢትዮጵያ ራእይ” በተሰኘው አነስተኛ መጽሐፉም፣ “ኢየሱስ ወደ እግዚአብሔር ገብቶ በቀኙ በተቀመጠ ጊዜ እግዚአብሔር የመለኮት ማንነትን ሁሉ ሰጠው” በማለት ኢየሱስ መለኮትነትን ከትንሣኤውና ከዕርገቱ በኋላ የተቀበለው ነገር እንጂ፣ ማንነቱ (ባሕርይው) እንዳልነበር ጽፏል።[1] ስለ ቃል ሥጋ መሆን ከዚህ በፊት ለቀረበለት ጥያቄም፣ “ይሄ ቃል ምድር ላይ ሲመጣ ‘ሰው ሆነʼ ስንል፣ በመሠረታዊ ሐሳብ ተቀየረ ብለን የምናምነው ባሕርይው ነው” ሲል መልሷል።[2] ይህንንም፣ “ክርስቶስ የተመላለሰበት ባሕርይ፣ የተመላለሰበት ማንነት የሰው ከሆነ፣ ‘አይ በስውር እናውቃለን፤ የአምላክነት ባሕርይ አለውʼ የሚባል ከሆነ፣ እንግዲህ እኛ እናውቃለን የምንለው የተገለጠውን ነው። ያልተገለጠ ነገር በባሕርይ ደረጃ ካመንን እንዲህ ነው ብለን መቀበል አንችልም” በማለት ሐሳቡን ለማብራራት ሞክሯል።[3]

 

ይህም አስተምህሮ የግለ ሰቡ ነባር አቋም መሆኑን፣ ይህ ጸሓፊ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከዘላለም ጌታቸው እና ከተማሪዎቹ ጋር ካካሄዳቸው ተደጋጋሚ ውይይቶች ተገንዝቧል። ዘላለም፣ ጌታ “ራሱን ባዶ አደረገ” የሚለውን ጥቅስ (ፊል. 2፥7) ተመርኩዞ ሲያብራራ፣ ጌታ ራሱን ከመለኮትነቱ ማላቀቁን ያስተምራል። ከዚያም ባሻገር፣ “ኢየሱስ ተመልሶ ጌታ የሆነው” በትንሣኤው መሆኑን ለማስረዳት፣ “እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ” በማለት ሐዋርያው ጴጥሮስ መናገሩን ይጠቅሳል (የሐዋ. 2፥36)።

 

ፍሬው ቤዛ ደግሞ በቅርቡ ባሳተመው “ከእውነት የሚበልጥ እውነት” የተሰኘ መጽሐፉ[4] ይህንኑ ኑፋቄ ዘርቷል። መጽሐፍ ቅዱስን፣ “ኢየሱስ ምን ነበር?” ብለን ብንጠይቀው “አምላክ ነበረ” ብሎ እንደሚመልስልን፣ “ከዚያስ ምን ሆነ?” ብንል፣ “ሰው ሆነ” እንደሚለንና በመጨረሻም “ወደ አምላክነቱ ገባ” እንደሚለን ግለ ሰቡ ያትታል (ገጽ 58)። “አንዳንድ ሰዎች የኢየሱስን ምድራዊ ሕይወት አስመልክተው በአቋም ደረጃ ‘ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክʼ ነው ይላሉ። ችግሩ ማለታቸው ሳይሆን፣ ለደረሱበት ድምዳሜ ምንም ያህል መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃ ማቅረብ አለመቻላቸው ነው” (ገጽ 58)። ስለዚህም፣ “‘በአንዴ ሰውና አምላክ ነውʼ የሚለው … ብዙም አዋጭ የማይመስል አስተሳሰብ ነው” (ገጽ 59)። “አምላክነትና ሰውነት በኢየሱስ ማንነት ላይ አልታየበትም” (ገጽ 60)። “ስለ ኢየሱስም ስንናገር አምላካዊ ባሕርይ ነበረው፤ ሰብአዊ ባሕርይ ወሰደ እያልን ነው። … አምላካዊ ባሕርይውን ሲለቅ፣ ያልነበረውን ሰው መሆኑን ይገልጻል” ይለናል (ገጽ 122)።

 

ፍሬው ቤዛ ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ ሥጋውን ትቶ መንፈስ ብቻ እንደ ሆነ ጽፏል። ይህንንም ሲያስረዳ፣ “ኢየሱስ ከሞት ከተነሣና ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ፣ ልክ እንደ እግዚአብሔር አብ መንፈሳዊ ማንነትን ተላብሶ እየኖረ እንደሆነ” እና “ኢየሱስ በምድር ላይ በሥጋ ሰው ሆኖ በመመላለስ ተልእኮውን [አጠናቅቆ] … ከዚህ ወራት በኋላ ግን ሌላ መንፈሳዊ ማንነትን እንደ ተላበሰ” መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያመለክት ተናግሯል (ገጽ 60)።

 

ፍሬው ቤዛ በዚህ ሳይወሰን፣ የኢየሱስ ትንሣኤ የሥላሴ ሥራ እንዳልሆነና ጌታ ኢየሱስ በትንሣኤው ላይ አንዳችም ድርሻ እንዳልነበረው ሊያስረዳን ይታትራል። እንዲያውም፣ “በአንድ ለእናቷ የዮሐንስ ወንጌል 2፥19 ጥቅስ ላይ ተንጠልጥሎ ኢየሱስ ራሱን በድርሻው እንዳስነሣው” በማመናቸው ወንጌላውያን አማኞች ሊጠየቁ እንደሚገባ ሐሳብ ያቀርባል (ገጽ 68)። “ለመሆኑ በዮሐንስ 2፥19 መሠረት የኢየሱስን ሰብአዊ ማንነት ከሞት ያስነሣው ሌላው የራሱ መለኮታዊ ማንነት ነውን? መልሱ አይደለም ነው!!” (ገጽ 118)። ኢየሱስን ከሞት ያስነሣው አብ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ከ18 ጊዜአት በላይ መናገሩን ጥቅሶችን በመዘርዘር ያስረዳና (ገጽ 68-71) “አብ፣ ወልድ (ራሱን ማለት ነው)፣ መንፈስ ቅዱስ ተረዳድተው ኢየሱስን አስነሡት መባሉ ምንም ትርጉም” እንደማይሰጥ ያክልበታል። ሰው ብቻ የሆነው ኢየሱስ ራሱን ካስነሣ “በእኛም የትንሣኤ ሥነ-ሥርዐት ወቅት ‘የራሳችን ድርሻʼ እንዳለበት ልንቀበል እንገደዳለን” ሲል ይሳለቃል (ገጽ 72-73)። ኢየሱስ ክርስቶስን ከሙታን ስላስነሣው የእግዚአብሔር መንፈስ (መንፈስ ቅዱስ) የሚናገረውን ጥቅስ (ሮሜ 8፥11) አብ እንዳስነሣው የሚናገር አድርጎ ከማቅረቡም በላይ (ገጽ 70) ክፍሉ ስለ እግዚአብሔር አብ እንደሚናገር “ምንም ክርክር የማያሻው መሆኑ ዓውዱ ግልጽ ማሳያ ነው” ይለናል (ገጽ 72)። ስለዚህም “አምልኮ መቅረብ ያለበት ለአባት (ለአብ) ብቻ ነው” ቢባል ፈጥነን ቱግ እንዳንል ይመክራል (ገጽ 129)።

 

ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ ሥጋውን (ሰብእናውን) አራግፎ መለኮት ብቻ ሆኗል የሚለው ፍሬው ቤዛ፣ ወንጌላውያን ክርስቲያኖችን የኢየሱስን አምላክነትና ትስብእት (ሰውነት) ነጣጥለው የሚያቀርቡ ንስጥሮሳውያን ያደርጋቸዋል። “ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድ ጊዜ ‘ሰውና አምላክ ነውʼ ካልን፣ ‘ለመሆኑ ስለ ሰው ልጆች ኀጢአት የሞተው ማን ነው? ሰው የሆነው ኢየሱስ ወይስ አምላክ የሆነው ኢየሱስ?ʼ ተብለን ብንጠየቅ፣ የምንሰጠው መልስ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ሊኖረው ይገባል” ካለ በኋላ (ገጽ 60)፣ “ለመሆኑ፣ ‘ነፍሴን አነሣት ዘንድ አኖራለሁʼ ያለው ማን ነው?” (ገጽ 118)፤ “የሰው ልጆችን የኀጢአት ዋጋ የከፈለ የኢየሱስ የትኛው ክፍል ነው? … በአንዱ ኢየሱስ ላይ ስንት ማንነት አለ?” (ገጽ 59) ሲል ይጠይቃል። “አምላክ የሆነው ኢየሱስና ሰው የሆነው ኢየሱስ ከእግዚአብሔር አብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ሲደመሩ፣ ወደድንም ጠላንም አራት አካላት ማግኘታችን ግድ ነው” እያለ፣ በክርስቶስ ሰው የሆነ አምላክነት ላይ ተቃውሞውን ያጠናክራል (ገጽ 60-61)።

 

ግለ ሰቡ በባሕርይ እና በማንነት ትርጓሜ ላይ ጕልህ እንከንም አለበት። እንደ እርሱ አባባል ከሆነ፣ “ባሕርይ ሊለወጥ፣ ሊጠፋ ይችላል (ዳን. 4፥34)። … ስለ ኢየሱስም ስንናገር አምላካዊ ባሕርይ ነበረው፤ ሰብአዊ ባሕርይ ወሰደ እያልን ነው። … አምላካዊ ባሕርይውን ሲለቅ፣ ያልነበረውን ሰው መሆኑን ይገልጻል።” (ገጽ 122)። “በመጀመሪያ ደረጃ ኢየሱስ ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክ ነው ሲባል የተሰጠው መግለጫ ሁለት ማንነትን አመላካች መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። … በዚህ መሠረት ኢየሱስ ሁለት አካል እንደ ነበረው በግልጽ መናገር ለምን ‘ያሳፍረናልʼ ያስፈራቸዋል?” (ገጽ 123)።

 

2. ኢየሱስ፡ ሰው የሆነ አምላክ (አምላክ-ሰው)

የጌታ ኢየሱስ ማንነት የሁልጊዜም ጥያቄ ነው። ትክክለኛውን መልስ ያገኙ፣ ሕይወትን ያገኛሉ፤ መልሱን የሳቱም የሕይወት ጎዳናን ይስታሉ። እግዚአብሔር ግን ልከኛውን መልስ በራሳችን እንድናገኝ ለራሳችን አልተወንም፤ ቅዱሱን መጽሐፍ፣ ቅዱሱን መንፈስ እና ቅዱሳን አባቶችን ሰጥቶናል። እነርሱም የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ፍጹም ሰውነት እንዲሁም ፍጹም አምላክነት ያስተምሩናል። በዚህ ጽሑፍ ትኵረት የምናደርገውም፣ ቃል ሥጋ ሲሆን አምላክነቱ እንዳልተቋረጠና አምላካዊ ሥራና ማንነት ያለው መሆኑ ላይ ነው። እንደዚሁም ከትንሣኤው እና ከዕርገቱ በኋላም ሰው መሆኑን እንዳልተወ እንሞግታለን። ስለዚህ የዚህ ጽሑፍ ጭብጥ ሐሳብ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ  ቃል ሥጋ ከሆነበት ቅጽበት ጀምሮ እስካሁንም ድረስ “ፍጹም ሰው፣ ፍጹም አምላክ” (fully human, fully divine) እንደ ሆነ ማስረዳት ነው።

 

2.1 መጠሪያዎቹ

2.1.1 ጌታ እና ክርስቶስ

 ዘላለም ጌታቸውና መሰሎቹ እንደሚያስቡት ኢየሱስ ጌታም ክርስቶስም የሆነው ከትንሣኤው በኋላ አልነበረም። ለኢየሱስ ክርስቶስ መጠሪያነት የዋለው “ጌታ” የሚለው ቃል (በግሪክኛው ኩርዮስ κύριος) የእግዚአብሔር ስም አቻ ነው።[5] ይህን ደግሞ ኢየሱስ ምድራዊ ሕይወቱን ገና ከመጀመሩ አንሥቶ ተጠርቶበታል። ኢየሱስ ሲወለድ መንጎቻቸውን ይጠብቁ ለነበሩ እረኞች፣ “መድኀኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋል” የሚል የምሥራች መላእክት ነግረዋቸዋል (ሉቃስ 2፥11)። ስለዚህ የተወለደው ሕፃን ጌታም ክርስቶስም ነበር፤ ጌታም ክርስቶስም ለመሆን ትንሣኤን መጠበቅ አላስፈለገውም።

 

የኢየሱስ ክርስቶስነት ከትንሣኤውም በፊት ግልጥ ነበር። ጴጥሮስ፣ “አንተ ክርስቶስ … ነህ” ማለቱን ጌታ አጽድቆለታል (ማቴ. 16፥16-19)፤ ሳምራዊቷን ሴትም፣ “እኔ እርሱ ነኝ” ብሏታል (ዮሐ. 4፥25-26)። ገና መከራ እየተቀበለም ክርስቶስ ነበር (ሉቃ. 24፥26፡46፤ የሐዋ. 3፥18)፤ የተሰቀለውና የተነሣውም ክርስቶስ ነው (የሐዋ. 4፥10)። እንድርያስ (ዮሐ. 1፥42)፣ ማርታ (ዮሐ. 11፥27)፣ ሄሮድስ (ማቴ. 2፥4) እና ጲላጦስ (ማቴ. 27፥17) ክርስቶስ ሲሉ ጠርተውታል። አጋንንትም ክርስቶስነቱን ዐውቀዋል (ማር. 1፥34፤ ሉቃ. 4፥41)፤ በሌሎችም ስፍራዎች ክርስቶስነቱ ተገልጧል (ማቴ. 22፥41-42፤ ዮሐ. 7፥26-27)።

 

ደቀ መዛሙርትም ኢየሱስን በተለያዩ ጊዜአት ጌታ ብለው ጠርተውታል። ለምሳሌ፣ ስምዖን ጴጥሮስ ለአገልግሎት በተጠራ ቀን፣ በኢየሱስ እግር ሥር ወድቆ፣ “ጌታ ሆይ፥ እኔ ኀጢአተኛ ነኝና ከእኔ ተለይ” ብሏል (ሉቃ. 5፥8)። ጌታ ለአገልግሎት የላካቸው ሰባዎቹ ደቀ መዛሙርት (አርድእት) ከአገልግሎት እንደ ተመለሱ ደስታቸውን ለኢየሱስ የገለጹት፣ “ጌታ ሆይ፥ አጋንንት ስንኳ በስምህ ተገዝተውልናል” በሚል ዘገባ ነበር (ሉቃ. 10፥17)። እነዚህ ሁሉ ሰዎች “ጌታ ሆይ” እያሉ ሲጠሩት ተሳስተው ይሆን? ኢየሱስስ መሳሳታቸውን ለምን አልነገራቸውም?

 

እርሱማ ትክክል መሆናቸውን ነው ያጸናላቸው፤ “እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ። እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፥ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል” ሲል መክሯቸዋል (ዮሐ. 13፥13)። ኢየሱስ ይህንን መጠሪያ በሌሎች ጊዜአትም ተጠቅሞበታል (ማቴዎስ 22፥44ን ይመለከቷል!)።

 

ከጌታ ጐን የተሰቀለው ወንበዴ፣ “ጌታ ሆይ፤ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ” ብሎ ሲለምን፣ በጎ ምላሽ አግኝቷል (ሉቃ. 23፥42)። ቅዱስ ጳውሎስም፣ “ዐውቀውስ ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር” (1ቆሮ. 2፥8) በማለት ኢየሱስ ሲሰቀልም ጌታ፣ የክብር ጌታ እንደ ነበር አስተምሯል። ስለዚህም በመስቀል ላይ የሞተውና የተነሣው ኢየሱስ ያው ዐልፋና ኦሜጋው አምላክ ነው፤ ምክንያቱም፣ “ሞቶ የነበረው ሕያውም የሆነው ፊተኛውና መጨረሻው” እርሱ ነውና (ራእይ 2፥8)። 

 

የኢየሱስ ጌትነት በብሉይ ኪዳንም ተተንብዮአል። ነቢዩ ሚልክያስ፣ “መልእክተኛዬን እልካለሁ፥ መንገድንም በፊቴ ያስተካክላል፤ እናንተም የምትፈልጉት ጌታ በድንገት ወደ መቅደሱ ይመጣል” በማለት ጌታ እንደሚመጣ ተናግሯል (ሚል. 3፥1)። ነቢዩ ኢሳይያስ ይህንኑ ትንቢት፣ “የእግዚአብሔርን መንገድ በምድረ በዳ ጥረጉ፥ ለአምላካችንም ጎዳና በበረሃ አስተካክሉ” በማለት የሚመጣው እግዚአብሔር መሆኑን ይገልጻል (40፥3)። ሐዋርያው ማቴዎስ ደግሞ እዚህ ትንቢት ውስጥ ያለውን “እግዚአብሔር” የሚል ቃል “ጌታ” በሚል ተክቶ ያቀርበዋል፤ “በነቢዩ በኢሳይያስ፦ የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ የተባለለት ይህ ነውና” በማለት (3፥3)። ይህም እንደሚያሳየን የአዲስ ኪዳን ጸሓፊዎች ኢየሱስን ለመጥራት የሚጠቀሙበት “ጌታ” የሚል መጠሪያ “እግዚአብሔር” (ይሖዋ ወይም ያህዌ יהוה) ከሚለው የብሉይ ኪዳን ቃል ጋር አንዳችም ልዩነት የለውም፤ በኢሳይያስ 40፥3 የተጻፈው ቃልም ይኸው ነው።[6]  እግዚአብሔር ወልድ ሰው ከመሆኑ በፊት፣ ሰው ከሆነም በኋላ አሁንም ድረስ ጌታ ነው። ሲወለድም ጌታ፣ ሲያገለግልም ጌታ፣ ሲሲቀልም ጌታ፣ ሲነሣም ጌታ፣ ዐርጎ በአብ ቀኝ ተቀምጦም ጌታ ነው። ጌትነቱ ለአፍታ አልተቋረጠም!

 

2.1.2 የእግዚአብሔር ልጅ

 እስራኤል (ዘፀ. 4፥23፤ ኢሳ. 63፥16፤ 64፥8) እና መላእክትም (ኢዮብ 1፥6፤ 2፥1፤ 38፥7) የእግዚአብሔር ልጆች ተብለዋል። እነዚህ ግን አምላክ አይደሉም። ወደ ጌታ ኢየሱስ ሲደረስ ግን ትርጓሜው የተለየ ነው። “ከቶውንም እግዚአብሔርን ያየ ማንም የለም፤ ነገር ግን በአብ ዕቅፍ ያለው አንድያ ልጁ የሆነው አምላክ እርሱ ተረከው” (ዮሐ. 1፥18 - አ.መ.ት.)።  ይህም የኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነት ትርጓሜው አምላክነት መሆኑን በማያሻማ መንገድ ያስረዳል። ዮሐንስ 1፥14ም ተመሳሳይ መልእክት ይዟል። አጋንንትም ማንነቱን ተረድተው፣ “ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ” በማለት ጮኸዋል (ማቴ. 8፥29)።

 

የኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነት ከትንሣኤ በኋላ አልጀመረም። ቀድሞውኑም የእግዚአብሔር ልጅ ነው። ጌታችን የ12 ዓመት ልጅ ሳለም እግዚአብሔር አባቱ መሆኑን ያውቅ ነበር (ሉቃ. 2፥49)። ስለዚህም እግዚአብሔር አባቱ፣ እርሱ ደግሞ ልጁ መሆኑን ደጋግሞ አስተምሯል (ዮሐ. 5፥17)። በጌታችን ልዕለ ተፈጥሯዊ ዕውቀት የተደነቀው ናትናኤል ገና ከመጀመሪያውኑ፣ “የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብሎታል (ዮሐ. 1፥50)። ሌሎቹ ደቀ መዛሙርትም፣ “በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብለው ሰግደውለታል (ማቴ. 14፥33)፤ በዚህም የእግዚአብሔር ልጅነቱ እና ስግደትን መቀበሉ ቊርኝት እንዳላቸው እናስተውላለን።

 

ጌታችን ደቀ መዛሙርቱ ስለ እርሱ ምን መረዳት እንዳላቸው ሲጠይቃቸው፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” በማለቱ፣ “በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህም” በማለት ጴጥሮስ ትክክለኛውን መረዳት እንዳገኘ ጌታ መስክሮለታል። የቤተ ክርስቲያን መሠረትም ይኸው መገለጥ ነው (ማቴ 16፥16-17)። ስለ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነት ትክክለኛው ግንዛቤ በሌለበት ወይም በዚህ ላይ የተሳሳተ መረዳት ባለበት ቦታ ቤተ ክርስቲያን የለችም! ወንጌሉም ይኸው ነው፤ “ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ” ነው ተብሎ ተነግሮናልና (ዮሐ. 20፥31)።

 

የኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነት ልዩ እና ብቸኛ ልጅነት፣ አንድያ ልጅነት ነው። መለኮትነት ነው። ጌታ ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ ወይም እግዚአብሔርን አባቴ ብሎ ሲጠራ አይሁድ ምን ማለቱ እንደ ሆነ ፈጽሞ አልደበዘዘባቸውም፤ በትክክል ገብቷቸዋል። ጌታ ኢየሱስ፣ “ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ … ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር” (ዮሐ. 5፥18)። እርሱ ግን እግዚአብሔር አባቱ መሆኑን ከመናገር አልታቀበም (ዮሐ. 10፥29)። ይህም እግዚአብሔርን ከመሳደብ ተቈጠረበት (ቁ. 36)። ጌታ ኢየሱስ ተይዞ ለፍርድ ሲቀርብ፣ “በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ፤ አንተ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንክ ንገረን” የሚል የእምነት ክህደት ጥያቄ የቀረበለት ለዚህ ነው። እርሱም፣ “አንተው ራስህ ብለኸዋል” የሚል ማረጋገጫ ከሰጠ በኋላ፣[7] ጉዳዩን ከዳግም ምጽአቱ ጋር አስተሳስሮ ይበልጥ አብራራው እንጂ አልካደም (ማቴ. 26፥63-64 - አ.መ.ት)። ሊቀ ካህናቱ ይህንን ሲሰማ ልብሱን ቀድዶ፣ “በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ተናግሮአል … በእግዚአብሔር ላይ የስድብን ቃል መናገሩን እናንተው ሰምታችኋል” በማለቱ ሸንጎው በኢየሱስ ላይ ሞት ፈረደ (ቁ. 65-66)። ከሳሾቹ፣ “ሊሞት ይገባዋል፤ ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ አድርጎአልና” ብለው የኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነት ራስን ከእግዚአብሔር ጋር ማስተካከል መሆኑን አስረገጡልን (ዮሐ. 19፥7)።

 

ለመሆኑ ራሷ እስራኤል የእግዚአብሔር ልጅ ሆና ሳለ፣ አይሁድም አዳምን የእግዚአብሔር ልጅ አድርገው እየቈጠሩ ሳለ (ሉቃ. 3፥37)፣ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ሲናገር፣ እግዚአብሔርን እንደ ተሳደበና በዚህም፣ ሞት እንደሚገባው እንዲያስቡ ያደረጋቸው ምንድን ነው? ብንል መልሱ ግልጽ ነው። ጌታ ኢየሱስ የሚናገረው የእግዚአብሔር ልጅነት ልዩ እንደ ሆነና አምላክነቱን እንደሚገልጽ ገብቷቸዋል። ጌታ ይህን ሲናገር፣ በአድማጮቹ ዘንድ ምን ዐይነት ትርጓሜ እንደሚኖረው፣ እንዲያውም ምን ዐይነት ውጤት እንደሚያስከትል በትክክል እያወቀ የተናገረው ነው። እርሱም፣ “ንግግሬን በዚህ መንገድ መረዳታችሁ ስሕተት ነው የሚል ማስተባበያ አላቀረበም፤ ይህም [ትርጓሜአቸው] ትክክል መሆኑን የሚያመለክት ነው።”[8]

 

2.1.3 የሰው ልጅ

ጌታ ኢየሱስ “የሰው ልጅ” የሚለውን መጠሪያ ከሌሎቹ መጠሪያዎቹ ይልቅ ያዘወትረው እንደ ነበር (ለ84 ጊዜአት ያህል ተጠቅሞታል) ከወንጌላቱ መረዳት ይቻላል።[9] በመጀመሪያ ደረጃ “የሰው ልጅ” የሚለው መጠሪያ፣ አንዳንዶች አማኞች እንደሚያስቡት “ሥጋ ለባሽ/ሰው” የሚልን ሐሳብ የያዘ ሳይሆን፣ ይልቁኑም ዳንኤል በራእይ ባየው ትንቢት ላይ የተመሠረተ ነው። “እነሆም የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ፤ … ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው፤ ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፤ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው።” (7፥13-14)። ኢየሱስ ደግሞ ትንቢቱ ለእርሱ የተነገረ መሆኑን ገልጾታል (ማር 14፥62)። ይህም ጌትነቱን፣ ገዥነቱን፣ አምላክነቱን የሚገልጥ ነው።

 

“የሰው ልጅ” የተሰኘው ስያሜ ትርጓሜው ልዕለ ሰውነት ወይም መለኮትነት መሆኑን ኢየሱስም አይሁድም ያውቃሉ። ለምሳሌ ጌታችን፣ “እንግዲህ የሰው ልጅ አስቀድሞ ወደነበረበት ሲወጣ ብታዩ” በማለት፣ ወደ ምድር ከመውረዱም በፊት ያለውን ማንነት ከዚህ መጠሪያ ጋር ያያይዘዋል (ዮሐ. 6፥62)። ኢየሱስ ከመወለዱም በፊት ሕልውና እንዳለው ለማሳየት “የሰው ልጅ” የሚለውን መጠሪያ በሌሎች ቦታዎችም ደጋግሞ ተጠቅሟል (ዮሐ. 3፥13-14፤ 6፥27፡53፡62፤ 8፥28)።[10] በተጨማሪም፣ “የሰው ልጅ”ነቱን ኀጢአትን ይቅር ከማለት ሥልጣን ጋር ሲያያይዘው በግልጽ ታይቷል፤ “በምድር ላይ ኀጢአትን ያስተሰርይ ዘንድ ለሰው ልጅ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ” በማለት (ማቴ. 9፥6)። ይህም መለኮትነት ነው። ሰማያት ተከፍተው መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ማየታቸው እንደማይቀርም ተናግሯል (ዮሐ. 1፥51-52)።

 

በሌላ ጊዜ ደግሞ ከዳግም ምጽአቱ ጋር አይይዞ፣ “የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋራ ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፥ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል” በማለት ሲናገር (ማቴ. 25፥31)፣ “በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅ ደግሞ በአባቱ ክብር ከቅዱሳን መላእክት ጋራ በመጣ ጊዜ በእርሱ ያፍርበታል” ሲል አስጠንቅቋል (ማር. 8፥38)። ከእግዚአብሔር ልጅነቱ ጋርም አስተሳስሮታል። በሊቀ ካህናቱ ለቀረበለት የምርመራ ጥያቄ፣ “ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኀይል ቀኝ ሲቀመጥ፥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ” የሚል ምላሽ ሰጠ (ማቴ. 26፥63-64)። ይህም “አምላክ ነኝ” ማለት መሆኑ ገብቶታልና፣ “ሊቀ ካህናቱ ልብሱን ቀዶ፣ ‘በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ተናግሯል፤ ከዚህ ሌላ ምን ምስክርነት ያስፈልገናል? በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል መናገሩን እናንተው ራሳችሁ ሰምታችኋል፤ ምን ይመስላችኋል?ʼ አላቸው። እነርሱም፦ ሞት ይገባዋል ብለው መለሱ።” (ቁ. 65-66 - አ.መ.ት)። “የሰው ልጅ” መባሉ የመለኮትነቱ መገለጫ መሆኑን ከዚህ እንገነዘባለን። ይህም ከትንሣኤው በኋላ የጀመረ እንዳልሆነ እስከ አሁን ተመልክተናል። 

 

ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤውም ሆነ ከዕርገቱ በፊትም አምላክ እንደ ሆነ የሚያሳዩ ሌሎች በርካታ ማስረጃዎችም አሉ። ከድንግል የተወለደው ሕፃን አምላክ እንደ ሆነ ኢሳይያስ በትንቢቱ ተናግሯል (ኢሳ. 9፥6)። “በዚህ ዐውድ ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ኀያል አምላክʼ እንደ ተባለው ሁሉ፣ እግዚአብሔር አብም ‘ኀያል አምላክʼ ተብሏል (10፥21)።” [11] በሌላም ስፍራ “ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም ዐማኑኤል ብላ ትጠራዋለች” ተብሎ በነቢዩ በኢሳይያስ የተተነበየው (7፥14)፣ በኢየሱስ መወለድ መፈጸሙ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ” የመሆኑ ማስረጃ ሆኗል (ማቴ. 1፥23)። በዚህም የኢየሱስ ክርስቶስ አብሮ ኋኚነት፣ ከእግዚአብሔር አብሮ ኋኚነት ጋር አንድ መሆኑን እናያለን፤ ኢየሱስ እግዚአብሔር ነውና!

 

የጌታችንን አምላክነት የሚያስረዱ ሌሎች መጠሪያዎችም አሉ። ለምሳሌ፣ “አዳኝ” ተብሏል (ሉቃስ 2፥11 እና ዮሐንስ 4፥42ን ከኢሳይያስ 45፥11 እና 45፥21-22 ጋር ያነጻጽሩ)፤ “እረኛ”ም ተብሏል (ዮሐንስ 10፥11 እና ዕብራውያን 13፥20ን ከኢሳይያስ 40፥11 እና መዝሙር 23 ጋር ያነጻጽሩ)።[12]

 

2.2 ቃሉ እና ግብሩ

2.2.1 ቃሉ

ጌታ ኢየሱስ፣ “አብርሃም ቀኔን አይቶ ደስ አለው” ብሎ በመናገሩ፣ አይሁድ “ገና ዐምሳ ዓመት ሳይሆንህ?!” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም፣ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ” አላቸው። አይሁድ ይህንን ሲሰሙ ወዲያውኑ፣ “ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ፤ ኢየሱስ ግን ተሰወራቸው” (8፥57-59)። ኢየሱስ፣ “አብርሃም ሳይወለድ እኔ ነበርሁ” አላለም፤ “እኔ አለሁ” እንጂ። እግዚአብሔር ለሙሴ ሲገለጥ፣ ራሱን ያስተዋወቀው በዚሁ ስያሜ እንደ ነበር (ዘፀ. 3፥14) አይሁድ ጠንቅቀው ያውቃሉና ኢየሱስ፣ “እግዚአብሔር ነኝ” ማለቱ እንደ ሆነ ገብቷቸዋል። ጌታችን በሌላ ጊዜም ይህንኑ ተናግሯል። በውሃ ላይ ሲራመድ ያዩት ደቀ መዛሙርት ሲብረከረኩ፣ “አይዟችሁ እኔ ነኝ” ሲል አጽናናቸው (ዮሐ. 6፥20)። ግሪኩ በቊሙ ሲወሰድ (ἐγώ εἰμι ኤጎ ኤይሚ) “It’s I” ሳይሆን፣ “I am” የሚል በመሆኑ በዮሐንስ 8፥58 “እኔ ነኝ” በማለት ከተናገረው ጋር አንድ ዐይነት ነው።[13] በዘፀአት 3፥14 እግዚአብሔር ለሙሴ ስለ ማንነቱ የተናገረው ስም፣ በሰባ ሊቃናት የግሪክ ትርጉም የሚገኘውም ይኸው “እኔ ነኝ” የተሰኘው ቃል (εγω ειμι) ነው። ይህም የሚያረጋግጠው ይህ ክርስቶስ ያ ለሙሴ ራሱን የገለጠው እርሱ መሆኑን ነው።

 

ጌታ ኢየሱስ “እኔን ያየ አብን አየ” ሲልም ሆነ (ዮሐ. 14፥9) “እኔና አብ አንድ ነን” ሲል (ዮሐ. 10፥30) አምላክነቱን እየነገረን ነው። የብሉይ ኪዳን ነቢያት “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” በማለት ሲናገሩ፣ ጌታ ኢየሱስ ግን ሕግጋትን ለሕዝቡ የሰጠው “እኔ ግን እላችኋለሁ” በማለት ነበር (ማቴ. 5፥22፡28፡32፡34፡39፡44)። አልዓዛርን ከሞት ሲያስነሣ፣ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ” (ዮሐ. 11፥25)፣ በሌላ ጊዜም፣ “መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ” (ዮሐ. 14፥6) ብሏል። ታዲያ እግዚአብሔር ካልሆነ በቀር ሕይወት፣ ትንሣኤ፣ እውነት መሆን የሚችል ሥጋ ለባሽ ይኖራልን? መለኮታዊ ሕግጋትን ከራሱ አፍልቆ የሚናገርስ? ከቶ አይኖርም!

 

2.2.2 ሁሉን ዐዋቂነቱ

ጌታችን አገልግሎቱን በጀመረበት ወቅት፣ ወደ እርሱ ሲመጣ ያየውን ናትናኤልን ወዲያውኑ፣ “ተንኰል የሌለበት በእውነት የእስራኤል ሰው፥ እንሆ” ሲል ገለጠው። ከዚያም ናትናኤል ከበለስ ዛፍ በታች ሳለ፣ ገና ወደ እርሱ ሳይመጣ እንዳየው በመናገሩ ናትናኤል ተደነቀ። ይህ ዕውቀት ሰዋዊ አለመሆኑን መገንዘቡም፣ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ” አስብሎታል (ዮሐ. 1፥48-50)። ሐዋርያው ዮሐንስ ስለ ጌታ ዕውቀት በወንጌሉ የመሰከረው፣ “ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና … ራሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና” በማለት ነው (2፥24-25)። ሌሎቹ ደቀ መዛሙርቱም፣ “ሁሉን እንድታውቅ፥ ማንምም ሊጠይቅህ እንዳትፈልግ አሁን እናውቃለን፤ ስለዚህ፥ ከእግዚአብሔር እንደ ወጣህ እናምናለን” ብለውታል (ዮሐ. 16፥30)። ተሳስተው ይሆን?

 

በተግባርም የታየው እንደዚያው ነው። እነማን እንደማያምኑት እና ማን አሳልፎ እንደሚሰጠው ገና ከመጀመሪያውም ጌታችን ያውቅ ነበር (ዮሐ. 6፥64)። ሰዎች በልባቸው የሚያስቡትንም ያውቃል (ማር. 2፥8)። ደቀ መዛሙርቱ ወንጌል ሲሰብኩ፣ ከማይቀበል ቤት ወይም ከተማ ይልቅ፣ በፍርድ ቀን ለሰዶምና ለገሞራ እንደሚቀል ተናግሯል (ማቴ. 10፥15፤ ማር. 6፥11)። እርሱ ራሱ ብዙ ታምራት ያደረገባቸው ከተሞች ሳያምኑት ሲቀሩ፣ እነዚያ ተአምራት በሰዶም ተደርገው ቢሆን ኖሮ “[ሰዶም] እስከ ዛሬ በኖረች ነበር” ካለ በኋላ “በፍርድ ቀን … ለሰዶም አገር ይቀልላታል” በማለት የመጨረሻው ፍርድ በማን ላይ እንደሚከብድ እና እንደሚቀል ግልጽ አድርጓል (ማቴ. 11፥23-24)። በቅፍርናሆምና በሌሎቹ ከተሞች የተደረጉት ተአምራት፣ በሰዶም ተደርገው ቢሆን ኖሮ፣ ሰዶም አምና ከጥፋት ትድን እንደ ነበርም ዐውቋል። ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ “አንተ ሁሉን ታውቃለህ” በማለታቸው ልክ ነበሩ። ሁሉን ዐዋቂነት ደግሞ የእግዚአብሔርነት መገለጫ ነው።

 

2.2.3 ስግደትን/አምልኮን መቀበሉ

ጌታ ኢየሱስ ስግደትን (አምልኮን) በተለያዩ ጊዜአት ተቀብሏል፤ ከትንሣኤውም በፊት። ስግደት ታዛዥነትን ለመግለጽ በአምላክ (ወይም በጣዖት) ፊት በመውደቅ የሚደረግ አምልኮ ነው። እስራኤል ይህንን ለማንም እንዳታደርገው ከባድ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷታል (ዘፀ. 34፥14)። ስግደት የሚለው ቃል በግሪክኛው “ፕሮስኩኒዎ” (προσκυνέω proskuneō) ሲሆን፣ ጌታ ኢየሱስ በሰይጣን ሲፈተን፣ “ለጌታ አምላክህ ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ” በማለት መልስ ሲሰጥ፣ አምልኮ ለሚለው ቃል የተጠቀመው ይህንኑ የግሪክ ቃል ነው (ማቴ. 4፥10፤ ሉቃ 4፥8)። በራእየ ዮሐንስ መጽሐፍም ዮሐንስ በአንድ መልአክ ፊት ለመስገድ ሲዳዳው፣ መልአኩ ተከላክሎ “ለእግዚአብሔር ስገድ” ሲለው ይህንኑ ቃል ተጠቅሟል። ወንጌላቱ እንደሚነግሩን፣ ለምጻሙ ሰው (ማቴ. 8፥2)፣ ኢያኢሮስ (9፥18)፣ ሲሮፊኒቃዊቷ ሴት (ዮሐ. 9፥38)፣ ሌጌዎን (ማር. 5፥6)፣ ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደው ሰው (ዮሐ. 9፥38)፣ ደቀ መዛሙርቱ (ማቴ. 14፥33) ለኢየሱስ ሰግደዋል።[14] እነዚህ ሰዎችና አጋንንት ለኢየሱስ ክርስቶስ ስግደትን ማቅረባቸውን ወንጌላቱ ሲጽፉ፣ ይህንኑ የግሪክ ቃል ማለትም “ፕሮስኩኒዎ”ን መጠቀማቸው የሚያሳየን ለኢየሱስ የቀረበለት ስግደት ለእግዚአብሔር ብቻ የሚቀርብ አምልኮ መሆኑን ነው። ቃሉ ስግደትን ብቻ ሳይሆን፣ አምልኮንም እንደሚጨምር የኮይኔ ግሪክ መዝገበ ቃላት ያስረዳሉ።[15] እንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱሶች፣ ይህንኑ የግሪክ ቃል “worship” በማለት የሚገልጹት ለዚህ ነው። ኢየሱስ ለእግዚአብሔር ብቻ የሚቀርብ ስግደት ሲቀርብለት ካልተቃወመ እግዚአብሔር ነው ማለት ነው! በብሉይ ኪዳን ሰዎች ለሰዎች ለሰላምታና አክብሮት ሲሰግዱ ይታያል፤ በአዲስ ኪዳን ግን የአምልኮ እንጂ ያንን የመሰለ ስግደት አናይም።

 

2.2.4 ትንሣኤው

የጌታ ኢየሱስ ትንሣኤ የእርሱ ማንነት ለቀሪው ዓለም (ለሰዎችም ሆነ ለመናፍስት) የተረጋገጠበት ነው። ጌታችን፣ “እኔ እና አብ አንድ ነን” ቢልም፣ “የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ” ብሎ ቢናገርም፣ “ጌታ ነኝ” ብሎ ቢያውጅም ሞትን ድል አድርጎ ባይነሣ ኖሮ፣ ነኝ ያለውን ሁሉ ለመሆኑ ዋስትና ባልነበረን ነበር። ስለዚህም ከሞት መነሣቱ የማንነቱ ማረጋገጫ ነው (ሮሜ 14፥9)። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ “ከሙታን መነሣት የተነሣ በኀይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለ ተገለጠ” በማለት ይህንን ያስረዳል (ሮሜ 1፥4)። ቅዱስ ጴጥሮስም፣ “የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በርግጥ ይወቅ” ሲል የሰበከው ለዚሁ ነው (የሐዋ. 2፥36)። ትንሣኤው የማንነቱ አስረጋጭ እንጂ አስጀማሪ አይደለም!

 

ጌታ ኢየሱስ በራሱ ትንሣኤም ላይ ተሳትፎ አድርጓል። “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ” በማለት የተናገረው ስለ ሥጋ ትንሣኤው ለመግለጥ ነበር (ዮሐ. 2፥19፡21-22)። በሌላ ስፍራም፣ “ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል። እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም። ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ” በማለት ይህንኑ አጽንቶታል (ዮሐ. 10፥17-18)። በትንሣኤው ላይ የራሱ (የወልድ)፣ የመንፈስ ቅዱስ (ሮሜ 8፥11፤ 1ጴጥ. 3፥18) እና የአብ (የሐዋ. 2፥32) ድርሻ መኖሩ የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ የሥሉስ አምላክ ሥራ መሆኑን ያጸናል።

 

2.2.5 ሌሎች ሥራዎች

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድርም ሳለ አምላክ በመሆኑ ሥራዎቹ ሁሉ ከማንነቱ ጋር ይጣጣማሉ። ለምሳሌ፣ ኀጢአትን የማስተሰረይ ሥልጣኑን ተጠቅሟል፤ ይህም እግዚአብሔራዊ ሥልጣን በመሆኑ ጻፎች፣ “ይህ ሰው ስለ ምን እንደዚህ ያለ ስድብ ይናገራል? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኀጢአት ሊያስተሰርይ ማን ይችላል?” ብለዋል (ሉቃ. 5፥17-26)፤ የትኛውም ሰው ይህ ሥልጣን የለውም። ጌታችን ጸሎትን እንደሚመልስ ተናግሯል (ዮሐ. 14፥14)። ስግደትን ተቀብሏል (ማቴ. 28፥17)፤ ለመለኮት ብቻ ተገቢ የሆነውን ሙሉ ፍቅርና መሰጠት ከተከታዮቹ ጠይቋል (ማቴ. 10፥37)። መንፈስ ቅዱስን ላኪ መሆኑን አሳውቋል (ዮሐ. 15፥26)። የዘላለም ሕይወት ሰጭነቱን ዐውጇል (ዮሐ. 10፥28)። እነዚህ ሁሉ በእግዚአብሔር ብቻ የሚደረጉ ወይም ለእርሱ ብቻ የተገቡ ናቸው። ታዲያ እነዚህ ሁሉ እንደ ደመና የከበቡን ቃለ እግዚአብሔራዊ ምስክሮች እያሉን፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊነቱን በምድር አልተጠቀመም ማለት እንዴት ይቻላል? ወይም ጭራሹኑ በምድር አምላክ አልነበረም ማለትስ እንዴት ይደፈራል?

 

3. ከትንሣኤውና ከዕርገቱ በኋላስ?

“በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና” መጽሐፍ እንደሚል (ቈላ. 2፥9) ኢየሱስ መለኮትና ሰውነት የተጣመሩበት ነው። ከትንሣኤውም ሆነ ከዕርገቱ በኋላም ፍጹም ሰው፣ ፍጹም አምላክ እንደ ሆነ ቀጥሏል። የማንነት ለውጥ ስለ ማካሄዱ መጽሐፍ ቅዱስ አያስተምርም። ጌታችን ከሞት የተነሣው ከነሥጋዊ አካሉ ነው። ይህንንም፣ “እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት መንፈስ ሥጋና ዐጥንት የለውምና እኔን ዳስሳችሁ እዩ” በማለት አረጋግጧል (ሉቃ. 24፥39)። እጆቹ ላይ በምስማር፣ ጐኑ ላይም በጦር የተወጋባቸው ቊስሎች ነበሩ (ዮሐ. 20፥27)። ደቀ መዛሙርቱም እግሩን ይዘው ነው የሰገዱለት (ማቴ. 28፥9)። ስለዚህም ከሞት ከተነሣ በኋላም ማንነቱ አልተቀየረም ማለት ነው፤ ሰው መሆኑ ቀርቶ አምላክ ብቻ አልሆነም። እግዚአብሔር አብ ለኢየሱስ አባቱም አምላኩም የሚሆነው ከዚህ አኳያ ነው (ዮሐ. 20፥17)።

 

ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ያረገው እጆቹን ዘርግቶ ደቀ መዛሙርቱን እየባረከ ነው (ሉቃ 24፥50-51)። ከዚያም “እያዩት ከፍ ከፍ አለ”፤ ደቀ መዛሙርቱ “ትኵር ብለው ሲመለከቱ” ሁለት መላእክት ተገለጡላቸውና፣ “ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፣ እንዲሁ ተመልሶ ይመጣል” አሏቸው (የሐዋ. 1፥9-11)። እናም ጌታ ተመልሶ ሲመጣ በሄደበት ሁኔታ ነው የሚመጣው፤ ከነሥጋው። የትንሣኤው አካል (የከበረ ሥጋዊ አካል) የሚበሰብስ አይደለምና (1ቆሮ. 15፥42-43፤ 2ቆሮ. 5፥1) እዚሁ አልቀረም። ቃል ሥጋ ሲሆን፣ ሥጋ ልብሱ አልሆነም፤ ዘላቂ ማንነቱ እንጂ።

 

ጌታችን አሁን በሰማይም ሰው የሆነ አምላክ እንደ ሆነ ነው ያለው። “ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ” የማያምኑ አሳቾች መብዛታቸውን ሐዋርያው ዮሐንስ ሲጽፍ፣ “እንደ መጣ” (has come) እንጂ “መጥቶ እንደ ነበረ” (came) በማለት ያልገለጸው ለዚህ ነው። የኢየሱስ የመለኮትና የሥጋ ጥምረት የአንድ ወቅት ጉዳይ ሆኖ አሁን ያበቃለት ባለመሆኑ፣[16] እግዚአብሔር አብ የኢየሱስ ክርስቶስ “አምላክና አባት” ሆኖ ቀጥሏል (2ቆሮ. 1፥3፤ 11፥31፤ ኤፌ. 1፥3፤ 1ጴጥ. 1፥3)፤ አሊያማ ዛሬም አምላኩ እንዴት ይሆናል!? እግዚአብሔር በእኛ መልክ (ሰው ሆኖ) መምጣቱን የጻፈው ጳውሎስ (ፊልጵ. 2፥5-8)፣ የምንጠባበቀው ኢየሱስ “ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል” በማለት በዚያው መልእክቱ ያስተምራል (3፥20-21)። በመሆኑም ጌታችን አሁንም ድረስ የከበረ ሥጋ አለው፤ እኛም ወደፊት እርሱን እንመስላለን። እርሱን መምሰላችን የእግዚአብሔር ውሳኔ ነውና (ሮሜ 8፥29) ኢየሱስ ሰው መሆኑ ከቀረ ማንን ልንመስል ነው? ቅዱስ ጳውሎስ በሌላ ስፍራም፣ “አንድ እግዚአብሔር አለና፤ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፤ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” ሲል ጌታችን ዛሬም ሰው መሆኑን ያጸናል (1ጢሞ. 2፥5)።

 

የጌታ አሁንም አምላክ-ሰው መሆን የሊቀ ካህናትነቱ መሠረት ነው። ክህነቱ ደግሞ ለዘላለም ነውና (ዕብ. 7፥3) ዛሬም አላበቃም። ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬም አማላጃችን የመሆኑ (ሮሜ 8፥34፤ ዕብ. 7፥25) መሠረትም ይኸው ሰውም አምላክም መሆኑ ነው። እግዚአብሔር እኛን ለማዳን የነሣውን ሥጋ ሰማይ ሲሄድ አውልቆ በመጣል እኛን አልጣለንም!

 

4. አካል እና ባሕርይ

ብዙውን ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የሆነ አምላክ (አምላክ-ሰው) መሆኑን የሚክዱ ሰዎች፣ የኢየሱስ ክርስቶስን አካል (person) እና ባሕርይ (nature) ሲያምታቱ ወይም ሲምታታባቸው ይስተዋላል። ከላይ በክፍል 1 እንደ ተመለከትነው ፍሬው ቤዛም ይኸው መደናገር ውጦታል። ስለዚህም በዚህ ክፍል ጤናማውን አስተምህሮ ማሳየት ይኖርብናል።

 

ይህንንም ለመጀመር በቃላቱ ላይ ብያኔ ማቅረብን ማስቀደም የግድ ነው። አካል የሚለው ቃል፣ የሚዳሰስንና የሚጨበጥን ነገር እንደሚያመለክት ሁሉ፣ ከዚያ የሚያልፍ ትርጓሜም አለው። የእንግሊዝኛውን “person” - “እኔ” የሚልን ሕላዌ፣ ይኸውም ሰዎችን፣ መላእክትን፣ እግዚአብሔርን ይገልጻል። የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት፣ “አካል” የሚለውን ቃል፣ “ራሱን የቻለ ለራሱ የበቃ ሕላዌ፣ … የባሕርይ፣ የግብር፣ የስም ባለቤት እገሌ የሚባል፤ እኔ ማለትም የሚገባ ዕውቀት ቀዋሚነት ላላቸው ለማይሞቱና ለማይጠፉ ለሦስት ብቻ ነው፤ ለአምላክ፣ ለመልአክ፣ ለነፍስ” በማለት ይፈታዋል።[17]

 

ስለዚህም ስለ ጌታ ኢየሱስ ስንነጋገር የምናወራው ስለ አንድ አካል ነው፤ ስለ አንድ ሕላዌ። ስለ አንድ “እኔታ” ነው - ስለ አንድ “person”። ስለ ጌታችን ባሕርይ ስናነሣ ደግሞ ስለ ማንነቱ ነው የምናወራው። በባሕርይውም አምላክ ነው፤ ሰውም ነው። አካላዊው ቃል፣ ቃል ሥጋ ከሆነበት ቅጽበት ጀምሮ ሰው የሆነ አምላክ ነው። ፍጹም ሰው፣ ፍጹም አምላክ። ባሕርይ አይቀየርም። ባሕርይ እና አካልም አንድ አይደሉም። የላይኛው መዝገበ ቃላት፣ ባሕርይን “የነገር ሁሉ ሥር መሠረት፣ ምንጭ፣ መውጪያ፣ መፍለቂያ፣ መገኛ ጠባይዕ፣ ሕላዌ ክዋኔ” ካለ በኋላ፣ “ባሕርይ … አካል አይባልም፤ አካልም … ባሕርይ አይባልም” ሲል ያብራራዋል።[18]

 

ባሕርይን ከተፈጥሮ ጋር እንጂ ከጠባይ ጋር በጭራሽ ማመሳሰል የለብንም። ድንጋይ የድንጋይ ባሕርይ አለው፤ አይቀየርም። ውሃ የውሃ ባሕርይ አለው፤ አይቀየርም። እንስሳት የእንስሳነት ባሕርይ ነው ያላቸው። ሰዎችም የሰው ባሕርይ ነው ያላቸው፤ ስለዚህ ይወለዳሉ፣ ያድጋሉ፣ ይራባሉ፣ ይጠማሉ፣ ይደክማሉ፣ ይሞታሉ። እግዚአብሔርም የእግዚአብሔር ባሕርይ አለው፤ ባሕርይው አይለወጥም። እግዚአብሔር አይለወጥምና (ሚልክ. 3፥6) ቃል ሥጋ ሲሆን፣ ቃልነቱን ትቶ/ለቅቆ አይደለም። እግዚአብሔር ሰው ሲሆን እግዚአብሔርነቱን አልለቀቀም። እግዚአብሔር እግዚአብሔርን ላለመሆን አይችልምና!

 

5. አንዱ ኢየሱስ

ቤተ ክርስቲያን ገና ከጅማሬዋ የክርስቶስን ማንነት የሚመለከቱ የአስተምህሮ ተግዳሮቶችን ተጋፍጣለች። አውጣኪ የተባለው መነኩሴ “የኢየሱስ መለኮትነት ትስብእቱን ዋጠ፤ ስለዚህ ኢየሱስ አምላክ ብቻ ነው” ሲል፣ ንስጥሮስ ደግሞ የኢየሱስን ትስብእትና መለኮትነት ነጣጥሎ ማቅረቡ ይነገራል። ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን በ451 ዓ.ም ጉባኤ በማካሄድ  ሁለቱንም ትምህርቶች አውግዛ የኬልቄዶንን የእምነት መግለጫን አወጣች። ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ “ሳያሻማ፣ ሳይለወጥ፣ ሳይከፋፈል፣ ሳይለዋወጥ፣ በሁለት ባሕርያት የተገለጠ፣ የእያንዳንዱ ባሕርያት ማንነት በሌላኛው የማይቀማ፣ እያንዳንዱ ባሕርይ ሳይለወጥ በአንድነት በአንድ አካል ተስማምቶ የሚኖር፣ የማይቈረስ ወይም ለሁለት አካላት የማይከፋፈል” መሆኑን ያትታል።[19] ወንጌላውያንን ጨምሮ የካቶሊክ እና የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት መግለጫውን ይቀበሉታል።

 

ኦርየንታል ኦርቶዶክሳውያን ግን፣[20] በመግለጫው ውስጥ የተካተተው “ሁለት” የሚል ቃል ወደ ንስጥሮሳዊነት እንዳያዘም በመሥጋት “ሁለት” የሚለውን ቃል ላለመጠቀም ወስነዋል። ግና ክርስቶስ ሰው የሆነ አምላክ መሆኑን፣ ኢየሱስ መለኮትና ሥጋ ያለ መለየት፣ ያለ መቀላቀል፣ ያለ መለወጥ በአንድ አካል እና በአንድ ባሕርይ የተጣመሩበት አምላክ-ሰው መሆኑን ያምናሉ።[21] ይህንንም በብረትና እሳት ይመስሉታል። ብረቱ የትስብእቱ፣ እሳቱ ደግሞ የመለኮቱ ምሳሌ ነው። ብረቱ እሳቱ ውስጥ ሲገባና ፍም እስኪሆን ሲግል፣ ብረቱንና እሳቱን መነጣጠል አይቻልም። ብረቱ የእሳቱን ሙቀት፣ ግለትና ብርሃን ይወስዳል፤ ብረቱን ስንመታውም እሳቱ አብሮ መመታቱ አይቀርም። እሳቱ ብረት፣ ብረቱም እሳት ሆነው አልተለወጡም፤ አንድ እስኪሆኑ ግን ተጣምረዋል።[22] ኦርቶዶክሳውያኑ ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ አካል ያለው “ፍጹም ሰው፣ ፍጹም አምላክ” መሆኑን ይገልጻሉ።[23] ጉባኤ ኬልቄዶንን የሚቀበሉና የማይቀበሉ ኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናትም በርካታ ጉባኤዎችን አካሂደው የምስጢረ ሥጋዌ (የቃልን ሥጋ መሆን) አቋሞቻቸውን ከፈተሹ በኋላ፣ ልዩነታቸው “የቃላት አገላለጥ እንጂ የምስጢር ልዩነት” እንዳልሆነ ተግባብተዋል።[24] ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ፣ ፍጹም ሰው የሆነ አንድ አካል መሆኑን የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ያምናሉ ማለት ነው!

 

ነገር ግን እምነታችን በቤተ ክርስቲያን ውሳኔ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በቃለ እግዚአብሔርም ላይ የተመሠረተ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ክርስቶስን ሁሌም በነጠላ ቊጥር እንጂ፣ “ኢየሱሶች” ወይም “ይሄኛው ኢየሱስ እና ያኛው ኢየሱስ” በማለት አያቀርበውም። ጌታችንም ራሱን ሲገልጥ በ“እኔ” በማለት እንጂ በ“እኛ” አይደለም። አንድ ጊዜ በአምላክነቱ ሌላ ጊዜ በሰውነቱ እየተቀያየረ ተገልጦ አያውቅም። ኢየሱስ አንድ ነው። ከፅንሰቱ እስከ ውልደቱ፣ ከውልደቱ እስከ ዕድገቱ፣ ከዕድገቱ እስከ መስቀል ሞቱ፣ ከሞቱ እስከ ትንሣኤውና ዕርገቱ ሕይወቱን ብናጠና የምንገናኛው አንዱን ኢየሱስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን በሰውነቱና በመለኮትነቱ እየበለተ አያሳየውም። የተራበውም ሆነ የተራቡትን የመገበው ያው ኢየሱስ ነው። የባርያን መልክ ይዞ ሰው ሆኖ የተወለደውም ሆነ፣ “እኔና አብ አንድ ነን” ያለው እርሱ ራሱ ነው። የሞተውም ሆነ “ሕይወት ነኝ” ያለው አንዱ ኢየሱስ ነው። ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር ያስተካከለውም ሆነ “ከእኔ አብ ይበልጣል” ያለው፣ ወደ እግዚአብሔር የጸለየውም ሆነ ስግደትንና አምልኮን የተቀበለው እርሱ ነው። የመንፈስ ቅዱስን ቅባት የተቀበለውም ሆነ መንፈስ ቅዱስን ወደ ምድር የላከው እርሱ ነው። መዋቲውም ኢመዋቲውም፣ ረቂቁም ግዘፉም እርሱ! አንዱን ኢየሱስ ሰነጣጥረን ለመመልከት የመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ አይፈቅድልንም።

 

ኢየሱስ በመወለዱ እግዚአብሔር በሥጋ ተገለጠ (1ጢሞ. 3፥16)፤ ኢየሱስ ሲሞትም እግዚአብሔር በሥጋ ሞተ (1ጴጥ. 2፥24፤ 3፥18፤ 4፥1)።[25] ኢየሱስ ሰው ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ ሰው ብቻ ሊያድነን አይቻለውምና ድነታችን ዋጋ ቢስ በሆነ ነበር። አምላክ ብቻ ቢሆን ኖሮ መሞት ባልቻለ ነበር! መለኮትነቱና ሰውነቱ ላይለያዩ ተጣምረዋል፤ የኢየሱስ ልዩታ (uniqueness) ይህ ነው! ኢየሱስ አንድ ነውና የሥጋውን ተግባራት መለኮቱ ገንዘቡ ያደርጋቸዋል። ስለዚህም መለኮት ደም እንደሌለው እየታወቀ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያኑን “በገዛ ደሙ” እንደ ዋጃት ቅዱሱ መጽሐፍ ያሳስበናል (የሐዋ 20፥28)። ትስብእቱም የመለኮትነቱን ተግባራት ገንዘቡ አድርጓል። ጌታችን ያኔም ሆነ አሁን የሚያደርጋቸውን የትኞቹንም ነገሮች፣ “ይህንን በሰውነቱ አደረገ፤ ያኛውን ደግሞ በመለኮትነቱ” ብለን ነጣጥለን ለማቅረብ አንዳችም መሠረት የለንም!

 

6. መሠረት ሲናጋ

ነገረ ክርስቶስ ሲናጋ ሁሉም ክርስቲያናዊ አስተምህሮ ይናዳል፤ የክርስትና እምብርቱ ክርስቶስ ነውና! እግዚአብሔር ሰው የሆነው እግዚአብሔርነቱን ትቶ ከሆነ፣ እግዚአብሔር ይለወጣል ማለት ነው። እርሱ ግን፣“እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም” ብሏል (ሚልክ. 3፥6)። በተጨማሪም እግዚአብሔር እግዚአብሔርነቱን መተው ከቻለና በሌላ ጊዜ ደግሞ፣ እግዚአብሔርነትን ሌላኛው የሥላሴ አካል የሚያበረክትለት ከሆነ፣ እግዚአብሔርነት ባሕርይ (ማንነት) መሆኑ ይቀርና ሹመትና ሽልማት ይሆናል። አውልቀው የሚያስቀምጡት፣ በኋላም አንሥተው የሚያጠልቁት ልብስ፣ ወይም ቈርጠው የሚጥሉት፣ ሲሻቸውም የሚለጥፉት ማዕርግ ይሆናል።[26] ይህ ግን በጭራሽ የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር አይደለም!

 

ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር በተመላለሰባቸው 33 ዓመታት ገደማ ሰው ብቻ ከሆነ፣ በእነዚያ ዓመታት ሥሉስ አምላክ የለም ማለት ነው። ይህም የእግዚአብሔርን ማንነት ስለሚቀያይረው መጀመሪያ ሦስት፣ ኢየሱስ ሲወለድ ደግሞ ሁለት፣ ከክርስቶስ ትንሣኤ በኋላ ደግሞ እንደገና ሦስት አካላት ያሉት እግዚአብሔር ምን ዐይነት ሥሉስ አምላክ ሊሆን ነው!? ኢየሱስን ሰው ብቻ ማድረግ ምስጢረ ሥላሴንም ያፈርሳል። ይህን የሚያምኑ ሰዎችም ሥላሴያውያን አማኞች አይደሉም።

 

ኢየሱስ በምድር ሳለ ሰው ብቻ ከነበረ፣ አምላክነቱ ከቀረ፣ የዓለምን ሁሉ ኀጢአት መሸከም አይችልም። አዳኝም አይሆንም፤ ሰው ብቻ ሊያድነን አይቻለውምና! “አልፋና ዖሜጋ” (ራእይ 1፥8፤ 21፥6፤ 22፥13) ሊሆንም አይበቃም፤ አምላክነቱ በመካከል ተቋርጧልና! በሰማይም በአምላክነቱ ብቻ ከቀጠለ፣ አሁን አማላጃችንም (ሮሜ 8፥34፤ ዕብ. 7፥25)፣ ሊቀ ካህናትም (ዕብ. 7፥3)፣ እግዚአብሔርንና ሰዎችን የሚያገናኝ መካከለኛም (1ጢሞ. 2፥5) አይደለም። ይሄ ሌላ ኢየሱስ ነው!

 

7. ምክንያቱ ምን ይሆን?

በእንዲህ ዐይነት መሠረታዊ አስተምህሮዎች ላይ የሚደረጉ ፍተሻዎችን የሚያግዙ በርካታ የመጻሕፍት ማስረጃዎች በቅርባችን ቢኖሩም፣ ዘላለም ጌታቸው እና ፍሬው ቤዛ እነዚህን የመጠቀም ፈቃደኝነት ወይም ዐቅም ያጡ ይመስላል። ብዙም አላስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ግን “ግሪኩ፣ ዕብራይስጡ” እያሉ ያደናግራሉ፤ “ሌባ ለዐመሉ ዳቦ ይልሳል” እንዲሉ።

 

ለምሳሌ፣ ዘላለም ጌታቸው ለራሱ የለጠፈውን “ፖዝ” የተሰኘ ቅጽል ስያሜ ለማስረዳት “ግሪክኛው እንዲህ ይለዋል” ለማለት ኮንኮርዳንስ ይጠቅሳል።[27] “ዝብርቅርቁ ዓለም” በተሰኘው ዝብርቅርቅ መጽሐፉም ተመሳሳይ ተግባር ይፈጽማል፤ “የሂብሩ መዝገበ ቃላት ወይን ጠጅ የሚለውን ቃል ሲፈታው ቃል (word) ይለዋል” ዐይነት።[28] መሠረታዊ አስተምህሮዎች ላይ አስፈላጊውን ማስረጃ ሲፈትሽ ግን አይታይም። ይህም የዐቅም ማነስ ወይም የማን አለብኝነት ምልክት ሊሆን ይችላል። ሳይማር እንደሚያስተምር ያልካደው ዘላለም፣ የማስተማር ጥማት እንጂ ለመማር የመፈለግ ቅንነትም አይታይበትም።

 

ሌላኛው ግለ ሰብ ፍሬው ቤዛ ደግሞ፣ “የተመለሱ እና ያልተመለሱ ጥያቄዎቼ” የሚለውን መጽሐፍ አንብቧል፤ ያነበበውን በቅጡ የመረዳት ችግር ግን አለበት። ለምሳሌ በዚያ መጽሐፍ ውስጥ ወንጌላውያንን ወክሎ የተጠየቀው በልሁ ደለለኝ፣ ክርስቶስ በምድር ላይ ሰው ብቻ ነበር የሚልን አቋም ያራመደ አድርጎ አቅርቦታል። ይህንንም “ለትውልድ አሳቢና የእግዚአብሔርን ቃል አክባሪነታቸውን ስለ ተረዳሁ ‘እጅግ አከብራቸዋለሁʼ ብል የአድናቆት መብቴን የሚቃወም እንደሌለ አምናለሁ” ሲል አሳውቋል (ገጽ 123)።

 

የመሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የነገረ መለኮት መምህር የሆነው በልሁ ደለለኝ ግን፣ “የተመለሱ እና ያልተመለሱ ጥያቄዎቼ” በሚለው መጽሐፍ ውስጥ ይዞ የቀረበው ግለ ሰቡ ከተናገረው በተቃራኒ ጤናማውንና መጽሐፍ ቅዱሳዊውን አቋም ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በምድርም ሆነ አሁን ፍጹም ሰው፣ ፍጹም አምላክ መሆኑን፣ ሰው የሆነ አምላክ መሆኑን፣ በአንድ አካል መገለጡን በዚያው መጽሐፍ በአግባቡ ገልጿል። 

 

ለምሳሌ፣ “አምላክ-ሰው የሆነ ክርስቶስ! … መጽሐፍ ቅዱስ የሚያሳየን የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ ሆኖ መምጣቱን ነው። ሰው በመሆኑም ከአምላክነቱ አንዳችም አላጐደለም” (ገጽ 185)። “መለኮት ሰው በሆነ ጊዜ መለኮትነቱን እንዳጣ … የሚያሳይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃ ግን አናገኝም። ይልቁንም በእግዚአብሔር መልክ መገለጡን ነው የምናገኘው” (ገጽ 186)። “በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አማኞች ሥነ መለኮትም ክርስቶስ ሞተ ስንል የክርስቶስን አምላክነትና ሰውነት ነጣጥለን አይደለም።” “በጭራሽ! ከሰውነቱ አልተነጠለም ተግባሩ ግን ያው የመለኮት ነው። ምክንያቱም አሁን ራበኝ፣ ጠማኝ በሚልበት ሁኔታ ውስጥ አይደለም። በማንነቱ ግን ያው አምላክ-ሰው የሆነ ክርስቶስ ነው! የማዳን ሥራውን ከመፈጸም አኳያ ግን አሁን በአብ ቀኝ መቀመጡ፣ በመለኮት ግብር በሰማይ መኖሩን እናምናለን!” (ገጽ 188)። ኢየሱስ አምላክ ብቻ አለመሆኑንም ተናግሯል (ገጽ 194)። የምሥራቅ ኦርቶዶክሳውያኑን “አንድ ባሕርይ” የሚመርጠው በልሁ፣ “በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን ክርስቲያኖች ከኦቶዶክሳውያኑ ጋር በጣም ይስማማሉ። ሁለቱም ክርስቶስን የሚገልጡት ‘አምላክ-ሰውʼ ብለው ነው። የሞተልኝ ብለው የሚያምኑትም ‘አምላክ-ሰውʼ የሆነውን ክርስቶስን ነው” ሲል አስረድቷል (ገጽ 202)። የብረቱንና የእሳቱን ጥምረት ምሳሌም አቅርቧል (ገጽ 189)።

 

በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ ይህንኑ አቋሙን ያንጸባረቀበትን “እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” የሚል መጽሐፍ ያሳተመው በልሁ፣  አሁንም ቢሆን አቋሙ ከዚህ ፈቀቅ እንዳላለ፣ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ራሱን በልሁን ጠይቆ ማረጋገጥ ችሏል። ይህን ሁሉ አንብቦ በቅጡ መረዳት ያቃተውና ተቃራኒውን የተረዳው ፍሬው ቤዛ፣ ከዌይን ግሩደም “ስልታዊ ነገረ መለኮት” መጽሐፍ ሲጠቅስ ቢታይም፣ የተጠናወተውን ኑፋቄ ሙጭጭ ብሎ መቅረቱ አያስደንቅም። ይልቁኑ ሁለቱ ግለ ሰቦች (ዘላለም ጌታቸው እና ፍሬው ቤዛ) የሐዋርያትን አስተምህሮ ሳይቀበሉ ራሳቸውን ሐዋርያ እና ፓስተር በማለት ለመጥራት መድፈራቸው ነው የሚያስደንቀው። ይህም የአላዋቂ ድፍረት ብቻ ሳይሆን፣ ቀልድም ነው - መራራ ቀልድ!

 

እዚህ ጋ ኢትዮጵያዊቷ ቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ አስተምህሮዎችን ለአባላቷ በአግባቡ ለማስታጠቅ የተጠና መርሓ ግብር አዘጋጅታ መትጋት እንዳለባት ማሳሰብ ግድ ነው። ለዚህም አገልጋዮቿን በቅጡ ከማስታጠቅ መጀመሩ ያዋጣታል። አሊያ ደፋር አላዋቂዎች ጤና ቢስ አስተምህሮዎችን ሲነዙ፣ ግር ብለው ሞትን የሚሸምቱ አባላት ይበዛሉ። ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች እዚህም እዚያም ሲበራከቱ፣ ምእመኖቿን በሰንበት ስብከት ብቻ ለማኖር የምታስብ ቤተ ክርስቲያን ከተጠያቂነትና ከፍርድ አታመልጥም።

 

አባቶች ያስቀመጡልንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እና ጤናማ መሠረት ከመናድ እግዚአብሔር ይጠብቀን!

 

ማስታወሻ

1. ዘላለም ጌታቸው፤ የኢትዮጵያ ራእይ (አዲስ አበባ፤ 1995) ገጽ 9፤ ከማቴቴስ መጽሔት ቁጥር 18፤ ግንቦት 2003 እትም የተወሰደ።
2. ማቴቴስ መጽሔት ቁጥር 18፤ ግንቦት 2003 እትም፣ ገጽ 3።
3. ዝኒ ከማሁ፤ ገጽ 4።
4. ፍሬው ቤዛ፤ ከእውነት የሚበልጥ እውነት - የታሪክ ሠሪውና የታሪክ ተናጋሪው ትውልድ የክብር ልዩነት (አዲስ አበባ፤ 2008)።
5. ዌይን ግሩደም፤ ስልታዊ ነገረ መለኮት፤ ቅጽ 1፤ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ መግቢያ (አዲስ አበባ፤ ኤስ አይ ኤም፤ 2003) ገጽ 608-9።
6. የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ያህዌ የሚለውን ቃል የተረጐመው (ወደ ሰባት ሺህ ጊዜ) ኩርዮስ” (ጌታ) ብሎ ነው። የሐዲስ ኪዳን ጸሓፍያንም ከብሉይ ኪዳን ሲጠቅሱ፣ የሚጠቅሱት ከማሶሬቲኩ ቅጅ ሳይሆን ከሰብዓ ሊቃናት ትርጉም እንደ ሆነ ልብ ይሏል።
7. ይህ ፈሊጣዊ አነጋገር ነው። በዘመኑ፣ “አንተው ብለኸዋል” ማለት “እንዴታ!” ወይም “ትክክል!” እንደ ማለት ነው። አንዳንድ ሰዎች፣ “አንተ አልህ እንጂ እኔ እንደዚያ አላልሁም” የሚል ትርጕም እንዳለው ያስባሉ፤ ይህ ስሕተት ነው። 
8. ተስፋዬ ሮበሌ፤ የትምህርተ ሥላሴ መሠረታውያን - መጽሐፍ ቅዱሳዊ፣ ታሪካዊና ምክንዮአዊ ትንታኔ (አትላንታ፤ ተስፋ ዐቃብያነ ክርስትና ማኅበር፤ 2015) ገጽ 63።
9. ግሩደም፤ ስልታዊ፤ ገጽ 611።
10. L. Berkhof, Systematic Theology (Grand Rapids: Eerdmans, 1979), 313.
11. ተስፋዬ፤ ትምህርተ ሥላሴ፤ ገጽ 54።
12. ዝኒ ከማሁ፤ ገጽ 59-60።
13. Craig L. Blomberg in Lee Strobel, The Case for Christ: A Journalist’s Personal Investigation of the Evidence for Jesus (Grand Rapids: Zondervan, 1998), 29.
14. R. Sutcliffe, The Trinity Hurdle: Engaging Christadelphians, Arians, and Unitarians with the Gospel of the Triune God (Eugene: Wipf and Stock Publishers, 2016), 81.
15. ለምሳሌ የሚከተለውን ሌክሲከን ይመለከቷል። James Swanson, Dictionary of Biblical Languages with Semantic Domains: Greek (New Testament), electronic ed. (Oak Harbor: Logos Research Systems, Inc., 1997).
16. John Piper, Finally Alive: What happens When We are Born Again (Ross-shire: Christian Focus, 2009), 146.
17. ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ መወዝገበ ቃላት ሐዲስ (አዲስ አበባ፤ ደስታ ተክለ ወልድ፤ 1948) ገጽ 218።
18. ዝኒ ከማሁ፤ ገጽ 262።
19. ግሩደም፤ ስልታዊ ነገረ መለኮት (አዲስ አበባ) ገጽ 623-24።
20. አምስት ሲሆኑ፣ እነርሱም የእስክንድርያ (ግብፅ)፣ የሶርያ፣ የአርመን፣ የሕንድ ማላንካራ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው።
21. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይህንን ጥምረት “ተዋሕዶ” በማለት ትገልጸዋለች፤ ቃሉም ቅልቅልን የሚያመለክት አይደለም!
22. ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ  ፲፪፥፲፪፤ ዘብንያሚ  ፹፱፥፳፮-፴።
23. ለምሳሌ፣ ሃይማኖተ አበው ዘቴዎዶስዮስ፣ ፺፪፥፲፪፤ ዘአባ ገብርኤል ፺፬፥፲፫፤ ዘዲዮናስዮስ ፺፱፥፳፰፤ ዘሱኑትዩ ፩፻፱፥፲፮፤ ዘዘካርያስ ፩፻፲፮፥፫።
24. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ ፳፻ (2000) ዓ.ም. (አዲስ አበባ፤ የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ.፤ 2000) 302-3።
25. እዚህ ጋ “እግዚአብሔር በሥጋ ሞተ” እንጂ “የእግዚአብሔር ሥጋ ሞተ” እንዳልተባለ ልብ ሊባል ይገባል።
26. ጌታ “የባርያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ” በማለት ሐዋርያው ጳውሎስ የሚናገርበት የፊልጵስዩስ 2፥7 ጥቅስ፣ አምላክነቱን ተወ ማለት ሳይሆን፣ ዐውዱ በትክክል እንደሚገልጸው፣ ራሱን ያለ ልክ/ያለ ገደብ ዝቅ አደረገ ማለት ነው። 
27. አገላለጹን ከነቀረበበት ትችት በዚህ የድረ ገጽ አድራሻ ያገኛሉ፤ http://deqemezmur.com/2016/04/19/የሐዋሪያዎቻችን-ኢየሱስ-ክፍል-አንድ/
28. ዘላለም ጌታቸው (ፖዝ)፤ ዝብርቅርቁ ዓለም (አዲስ አበባ፤ ተልእኮ ለትውልድ፤ 2000) ገጽ 43፣ 33።

Read 61608 times Last modified on Wednesday, 25 May 2016 05:40
Paulos Fekadu

ጳውሎስ ፈቃዱ ባለ ትዳርና የሁለት ልጆች አባት ሲሆን፣ በሞያው መምህር ነው። በነገረ መለኮት እና በኮምፒውተር ሳይንስ፣ ከኢትዮጵያ ሥነ መለኮት ድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት (EGST) እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማስተርስ ዲግሪዎች ያሉት ጳውሎስ፣ እግዚአብሔርን በአእምሮውም ለመውደድ የሚሻ አማኝ ተደርጎ ቢወሰድ ይመርጣል።

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 18 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.