You are here: HomeSocial Issues Poetry - ግጥሞችየሰማይ ሽሽት (ሰቆቃወ እኛ)

የሰማይ ሽሽት (ሰቆቃወ እኛ)

Written by  Published in Poetry - ግጥሞች Friday, 19 June 2015 00:00

ድንጋይ ዳቦ ነበር አሉ ድሮ እየተገመሰ እሚበላ

ልፋት ጣመን ሳያውቀን ሣቅ ጨዋታ ጥጋብ ተድላ፡፡

ሰማዩም ቅርብ ነበረ አሉ ባናት ጠጉር የሚዳሰስ

የፍጥረቱ ሁሉ ወዳጅ ቤተኛ ዘንካታ ልስልስ፡፡

ቅርብ ነበር አሉ ሰማይ

እስቲሳከር ታችና ላይ

ማንም ምስኪን አዳሜ እጁን ዘርግቶ ሚነካው

እማይጣላ ገር አንሶላ ልስልስ ንጣፍ ለምለም ገላው

            

ለምለም ጨሌ ሣር ግጣ ግጣ ጥጋብ ሆን ሲነፋት

እግረ መንገዱን አልቀረም ልቡናዋንም ሳይነድፋት፤

         በቅሎይቱን፡፡

ባበጠ ል ተገፋፍታ በማን አለብኝ ክፉ እብሪት

የትአባቱ ብላ ተዳፍራ ተሞልታ በአጉል ትዕቢት

ላ እግን አንፈራጥጣ

በፊት እግ ሣር ቆንጥጣ

በሰኮናዋ አጎነችው ልስልሱን ሰማይ ረግጣ!

አቤት አቤት!

  

ከዚያ ወዲያማ ምን ይነገር ሰማይ ሸሸ አሉ ወደላይ

አይደረስ አይታሰስ አይከሠስ አይወቀስ አይከሰት ረቂቅ ራዕይ፤

ድንጋዩም ደነገየ ዳቦ መሆኑ ቀረ

የሰውጣፈንታም መከነ ድፍን ዐለት ሥር ተቀበረ፡፡

እና ሰማይ ሸሸ አሉ ወደ ላይ

ትቶልን ሥቃይ ብካይ፡፡

  

አሁን ከስንት ዘመን በላ ተረቱን ሜዳ ትተን

      ወደ እውነታው ዘልቀን ስናይ - ወደ ራሳችን ውስጥ ስናይ

       እውነትም ርል ሰማይ!

ምን እንዲህ አራቀው ሰማዩን ብቻችንን እኛን ጥሎ

የማይሰማ የማይገባው ባይተዋር እንግዳ መስሎ

ምን አሸሸው ሰማዩን ከሰማያውያን ፊት ግንባር

ለብቻችን ትቶን ሄደ እኛም ወጣን ከርሱ ምሕዋር

  

ሰማይን የሚያሸሽ ርግጫ ሳናራገጥ አልቀረንም

አለበለዚያ ይህን ያህል አምርሮ አይኮበልልም፡፡

እርሱ ሲሔድ ተለይቶ የሚዳኘን ሰው ቢጠፋ

የራሳችን አለቆች ሆንን የእውነት ጽዋ ተደፋ፡፡

ፈቃድ መጠየቅ ቀረ እንዳሻችን ተንለልን፤

በመልካችን አስቀርጸን ማኅተም ሠርተን በልካችን

አሳብ ኑሮ ሥራችንን አጸደቅን በራሳችን፡፡

ሰማያውያን የሆን እኛ ሰማይ የሌለ ያህል ኖርን፡፡

   

ሰማይ ሸሸ አሉ ወደላይ ወደማይደረስበት ምጥቀት

ሰውም ማንጋጠጥ አቃተው የአንገቱ ዋልታ ላላበት

ይቀር ይሆን በዚያው ወጥቶ ለዘላለሙ ተጣልቶ

በአሽክላዋ እንድትጠመድ ምድርን ለራ ትቶ?

ወይስ

ይወርድ ይሆን ራርቶልን የጥንት ኪዳኑን አስታውሶ

ድንጋዩን ልብ ሥጋ ሊያደርግ የጠፋውን ክብር መልሶ፡፡

ይወርድ ይሆን በብርቱ ኀይል በራሱ ቅናት ተቀስቅሶ

የተከመረብንን አበሳ ድርብርብ ኀሣር ጠርምሶ፡፡

ምነው ሰማዮቸን ቀድደህ ብትወርድ!

    

ምነው ተራሮች ቢጤሱ ምነው ስምህ ቢገለጥ!

የትድግናህ ጦር ተምዘግዝጎ በጠላት ወገብ ቢሰምጥ!

ምነው ያንተ ክብር ቢደምቅ የሰው ሁሉ ክብር ወይቦ

መና የቀረን እንዳንሆን ብኩን ዘዋሪ ፋይዳ አልቦ፡፡

  

አንተ የኛ ፈጣሪ እኛ የእጆችህ ጭቃ

የሕልውናችን መሠረት የእስትንፋሳችን አለቃ

ምነው ወርደህ ብታነሣን ከማቀቅንበት ሰቆቃ

ብትነጥቀን ምን አለ አሁን ከነበልባል የሳት ላንቃ

ከሠርክ መዓት ከፍዳት ማታ ጣር ሲቃ

ከሸሸንበት ጥልቅ ዋሻ ከገባንበት አረን

መልሰን እንመለስ የሞት አዙሪት ይብቃ!

Read 11758 times Last modified on Friday, 19 June 2015 07:51

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 233 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.