You are here: HomeSermonከትንሳኤ ማግስት፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መንፈሳዊነት

ከትንሳኤ ማግስት፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መንፈሳዊነት Featured

Written by  Wednesday, 25 April 2018 16:31

ቤተክርስቲያን ስላለችበት ሁኔታ እንዲሁም በውስጧ እየሆኑ ስለሉት ስብራቶችና ግራ የሚያጋቡ ነገሮች ስታስቡ “ኧረ መንፈሳዊነት ምን ማለት ነው?” የሚል ጥያቄ አይፈጠርባችሁም? ክርስቶስ የሞተውና የተነሳው “ለዚህ ነው?” አያስብላችሁም? ወይም ይህንን ጥያቄ እንደገና አንስተን እንደገና መመለስ እንዳለብን የዘነጋነው የቤት ሥራ አይመስላችሁም? ስለ ችግሩ እየተወያየንና አስተያየቶቻችንም እየቸርን የቤት-ሥራችን ግን ተቆለለ አይደል? እኔ ተቆልሎብኛል። ልክ የትዳር ሕይወት ከሠርግ ማግስት እንዲጀምር መጽሐፍ ቅዱሳዊውም “እውነተኛ ሕይወት” [ያ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ እየደጋገመ እንደ አዝማች ያሳሰበው ጉዳይ] እንዲሁ ከትንሳኤ ማግስት ይመስለኛል። መቼም ሞቱንና ትንሳኤውን አክብረን ስናበቃ ራሳችንን ማሳሰብ ያለብን ብዙ ነገሮች እንዳሉን ይሰማኛል። ከእነዚህ አንዱና ዋነኛ ግን “መንፈሳዊነት ምን ማለት ነው?” የሚለው መሆን አለበት። ይህ ወቅት ሞቱንና ትንሳኤውን ይዘን ሳናሰልስ ወደ ሥራ የምንሔድበት እንጂ፤ ወደ ሌላ ርእሰ-ጉዳይ የምንሸጋገርበት እንዳልሆነ ሁላችንም እናውቃለን። ይህ የሰሞኑ የመስቀልና የትንሳኤ ጉዳይ፣ ሌሎች አንገባጋቢ ጉዳዮቻችንን ወደ ጎን የሚያደርግ ሳይሆን፤ በእያንዳንዱ ጉዳዮቻችን ውስጥ ግን እንደ ጅማት ሊዘረጋ፤ እንደ ደም ስር ሊቀጣጠል፤ እንደ ደም በመላ የክርስትና ሕይወታችንና የቤተክርስቲያን ጉዳዮቻችንን ሊሰራጭ ይገባል። ጭንቅላት የሰውነት ብልቶች ተግባሮቻቸውን እንዲያከናውኑ ሁሉን እንደሚቆጣጠር፣ ይህ የሰሞኑ እውነታ የተግዳሮታችን ሁሉ ዓውድ ይሆን ዘንድ ልባዊ ጸሎቴ ነው። ስለዚህ መንፈሳዊ ሕይወት የመስቀልና የትንሳኤውን እውነታ የሚያንጸባርቅ መሆን አለበት። እንዲህ ከሆነ መንፈሳዊ ህይወት መስቀሉንና ክርስቶስን እንዲሁም በመስቀሉ ሥራ ላይ የተሳተፉት ስሉስ መለኮታዊ አካላትን የሚገልጥ መሆን አለበት። ትዝ አይላችሁም በቆሮንቶስ የነበረው የጸጋ-ሥጦታን አጠቃቀም ያለማወቅ ችግር? ምክኒያቱ? ስሉሱን አምላክ ያለማወቅ ችግር እንደሆነ ጽፎልናል “ስለ መንፈሳዊ ነገርም፥ ወንድሞች ሆይ፥ ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ…መንፈስ አንድ ነው…ጌታም አንድ ነው…እግዚኢብሔር [አብ] አንድ ነው” (1 Co 12:1-6). ” መንፈሳዊ ስጦታ የእግዚአብሔርን ክብርና ማንነት የሚገልጥ ነው እንጂ፣ ይለናል ጳውሎስ፤ የራሳችን እውነታ የምገልጥበት መንፈሳዊ-ልዕልና አይደለም። ይህም ከመንፈሳዊ ህይወት ጀርባ ጥልቅ ነገረ መለኮታዊ እውነታ አለ ማለት ነው፡፡ እናም አሁን የሰነበትንበት መንፈስ (የሰሞኑ መስቀል ተኮር ስብከት፤ መዝሙር፤ ጸሎት ምሥጋና፤ ይህ በትንሳኤው ሐይል ላይ የተደገፈ የሰሞኑ መታመናችን፤ ይህ ክርስቶስ ራሱን ለብዙዎች እስኪሰጥ ድረስ የወደደበት መውደድ ላይ የተመሰረተው ፍቅራችን) እንዴት ሳያቋርጥ ይቀጥል የሚለው ጥያቄ መታሰብ ያለበት ነው። መቼም ብዙ የሚያሳስበኝና የምጸልይበት ጉዳይ የዚህ የመንፈሳዊነት ጉዳይ ነው። “መንፈሳዊነት ምን ማለት ነው?” በየግል ሕይወታችን ውስጥ ለሚንጸባረቀው እንዲሁም በህብረት በየአብያተ-ክርስቲያናት በየእሑዱ ለምናካሒደው ስብሰባ ምን ፋይዳ አለው? ይህ ጥያቄ በአንድ ወገን በጣም ቀላል የሆነ፣ በክርስቶስ አምኖ የዳነ ሁሉ የቀመሰው እውነታ ነው። ነገር ግን በዚያው ልክ ጥልቅም ጥያቄ ነው። መንፈሳዊነት ትናንት ወደ መንግሥቱ የተጨመረ ሕጻን ሊዋኝበት የሚችል ገንዳ ነገር ግን ደግሞ ታላላቅ መርከቦችንም የሚያስተናግድ ባሕር ነው። በሕይወታችን የተለማመድነውን በቃላት ማስቀመጥ አንዳንዴ ትልቅ ጥበብን ይጠይቃል። ለምሳሌ ያህል የገላትያ ቤተክርስቲያን “ይህን ብቻ ከእናንተ እንድማር እወዳለሁ፤ [እንዴት] መንፈስን ተቀበላችሁን? (ገላ 3:2)” ሲል እነዚህ ሰዎች ጥልቅ የወንጌልን እውነት ሳይረዱ እንኳ ሕያው የሆነው መንፈስ ትልቅ መንፈሳዊ ሐይልን እንዲለማመዱ አብቅቷቸዋል። እዚህ ጋር ማብቃት ግን ትልቅ አደጋ ነው። ብስለት ባለው በጥበብ ቃል ይህንን ልምምድ መጽሐፍ ቅዱሳዊና ነገረ-መለኮታዊ በሆነ መንገድ መግለጥ እስካልቻልን ሲወሰድብንም፤ ከዚያም ስተን ስንወጣም (በሌላ መንፈስ) አናውቅም። ስለዚህ “መንፈሳዊነት ምንድር ነው?” የሚለውን አስፍተንና አጥልቀን እንደገና ማሰብ ያለብን ጉዳይ ይመስለኛል።

 

በበሰሉት መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን

በመጀመሪያ ስለመንፈሳዊነት ስናስብ ወደ ልባችን የሚመጡ አያሌ መፍትሔያት መልካም እና ሊበረታቱ የተገቡ ቢሆኑም፤ ነገር ግን ይህ ጥያቄ ከግል አስተያየት ያለፈ ሙሉውን የቅዱሳት መጻህፍትን ምክር ያካተተ ሊሆን ይገባል። እንጂ ሽራፊ መልስ ይዞ የመሸምጠጥን ፈተና እምቢ ብለን መግታት ይኖርብናል። ለምን? ምክኒያቱም እንዲህ ዓይነቱ ችኮላ እ/ር በደሙ የዋጃትን ቤት እንደ መንፈሳዊ “ላብራቶሪ” የመጡልንን ሐሳቦች የምንሞካክርባት ሪሰርች-ማዕከል ስለሚያደርጋት ነው። ይህች ቤት የእ/ር ናት፤ ሕይወቷም የተቀየሰላት ከሰማይ ነው። ስለዚህ እንደ ክርስቶስ አንድ አካል ቅዱሱን መጽሐፍ ከፍተን በጋራ በመወያየት ወደ በሰለ መፍትሔ መድረስ አማራጭ የሌለው ነው። ልክ የመንፈሳዊነትን ጥያቄን አለመመለስ ትውልድ አጥፊ መዘዝ እንዳለው ሁሉ፤ ለጥያቄዉም ሙሉና መጽሐፍ ቅዱሳዊ እይታን ያልያዘ መልስም እንዲሁ እጅግ አስከፊ መዘዝ አለው። አንድ ነገር አበክረን ከጅምሩ መናገር ያለብን ነገር፤ የመንፈሳዊነት ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ከዘፍጥረት እስከ ራእይ ጠይቆ የመለስው ጉዳይ መሆኑን ነው። እግዚአብሔር እኮ ልጁንና መንፈሱን ወደ ምድር የላከበት ዓላማ ይህ የመንፈሳዊነትን ጥያቄ ነው። ይህ በአንድ ቃል መ.ቅ. “ኪዳን” ይለዋል። ‘እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል መመላለሱና እርሱ አምላካቸው እነርሱም ደግሞ ሕዝቡ’ የመሆን ጥያቄ ነው። ስለዚህ እኔ መልስ ነው ብዬ እንደ አርማ ያነገብኩት መንፈሳዊነት በእ/ር ቤት እንደመፍትሔ ከመቅረቡና ጉባኤው ምላሽ እንዲሰጥ ከመጠየቁ በፊት፤ በቅዱስ መጻሕፍት ሊፈተሽ፤ ሙሉነቱ ሊለካ፤ በበሰሉ መሪዎች ሊመዘን ደግሞም በቅዱስ ጉባኤ ሊመከርበትና አጥጋቢ መልስ እንደሆነ ከታመነበት ብቻ በፈሪሃ እ/ርና በትህትና ሊተገበር የሚገባው ነገር ነው።

 

ሁሉት ነገሮች…

የመንፈሳዊነት ጥያዌ ሁሉት ነገሮችን በጥልቀት ገንዘቡ ያደረገ መሆን አለበት

 

► (1) የቅዱሳት መጻሕፍትን ሙሉ ምክር በጥልቀት ያገናዘበ

በመጀመሪያ ደረጃ፤ ከላይ እንዳየነው፣ የቅዱሳት መጻሕፍትን ሙሉ ምክር ስሌት ውስጥ ያስገባ ሊሆን ይገባዋል (Biblical Exposition and Theology)። ምን ያህል ቃሉን በጥልቀት እናውቃለን? ይህ በተለይ የመንፈሳዊነት ጥያቄን መመለስ የእለት-ተለት ሥራችን ለሆንን በተለየ መልክ መቅረብ ያለበት ማሳሰቢያ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “መንፈሳዊ” ለተባለው ማዕድ ቅመማ-ቅመም አይደለም። ይህ ምን ለማለት ነው፤ አንዳንዴ አቀራረባችን ልክ መጽሐፍ ቅዱስ ጥሬ ሽንኩርትና ድንች ሆኖ፤ እኛ በተለየ ጥበባችን አብስለን ማቅረብ ያለብን ነገር ይመስለናል። ሆኖም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናየው መንፈሳዊነት፤ በስሉሱ አምላክ አቀናባሪነት ለሰው ልጆች በዓመታት መካከል ተቁላልቶ የበሰለ ምርጥ ማዕድ ነው። ይህ ማዕድ አያረጅም፤ በዘመናት መካከል ቃናው አይለውጥም፤ ተበላሽቶም አይሸትም። ስለዚህ የመጀመሪያው ጥሪ የመስማት ጥሪ ነው። እ/ር ያቀረበውን ማዕድ ለሕዝብ የማቅረብ ሃላፊነት ነው። የታማኝነት ጥሪ እንጂ የመጠበብ ጥሪ አይደለም። ከዘይቤው ልውጣና፤ ለቆሮንቶስና ለሮሜ ሰዎች የተጻፉት ደብዳቤዎች ዓላማ ከርስቶስ መሰል መንፈሳዊነት ምን ማለት እንደ ሆነ ለመመለስ ነው። ስለዚህ መፈሳዊነት ምንድር ነው ለሚለው አጥጋቢ መልስ ለማግኘት በመጀመሪያ የሮሜን መጽሐፍ በጥልቀት መመልክትና መገንዘብ ይኖርብናል (ወይም 66ቱንም መጻሕፍት)። ለምሳሌ ሮሜ 6 ላይ “በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን” የሚለው የመንፈሳዊ ህይወት መልስ ነው። ምን ለማለት ፈልጌ ነው፣ ቅዱሳት መጻሕፍት በሙሉ የሚጠይቁትና የሚመልሱት ረዕሰ ጉዳይ የዚህ የመንፈሳዊነት ጥያቄ ነው። ሰለዚህ መንፈሳዊነት ምንድር ነው? ለሚለው ጥያቄ ጥልቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊና ነገረ-መልኮታዊ እውቀት አማራጭ የለሽ ነው። በቃሉ ውስጥ የተገለጠውን የእ/ርን ሙሉ ምክር ለመጨበጥ እና ለመማር ፈቃደኛ ያልሆንን ሁሉ ይህንን መልስ ለመመለስ ገና ብቁ አይደለንም።

 

► (2) ዘመናዊ ጥያቄ በጥልቀት ያገናዘበ

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ መንፈሳዊነት የዘመኑን ዘመናዊ ጥያቄ በጥልቀትም የተገነዘበ ሊሆን ይገባዋል (Contextualization and Relevance)። እኛ አሁን በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን በቆሮንቶስ ከተማ አይደለም የምንኖረው። የአይሁድና የአሕዛብ የእርስበርስ ግንኙነት፤ አብሮ ከአንድ ማዕድ የመብላት ጥያቄ፤ ቀናትን የማክበርና ሰንበታትን የመጠበቅ ጉዳይ እንዲሁም እነዚህ ከወንጌል ጋር ያላቸውን እንደምታ በጥልቀት መዳሰስ ለእኛ በቀጥታ ርባናው (relevance) ጥቂት ነው። ያ ጥያቄ የኛ ጥያቄ ስላልሆነ። ይህ ማለት ግን በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ተጠይቆ ሲመለስ የምናየው ጥያቄ ለጥያቄያችን ረብ-የለሽ (irrelevant) ነው ብሎ ማሰብ ግን ስህተት ነው። ምክኒያቱም እ/ር የእኛን ጥያቄ ሊመልስ የወደደው በእነርሱ ጥያቄ ውስጥ ነውና። ጌታም ሲናገር “ለእናንተም የምነግራችሁ ለሁሉ እላለሁ” (ማር. 13:37) እንዳለው ነው። ለእኛ ለዘመናዊዎቹ ሰዎች የቀረበልን ሕይወት የተሰጠን በጥንታዊው ዓለም ቡሉኮ ውስጥ ነው። የሰማይና የምድር ገዢ የሆነው እግዚአብሔር ማንነቱንና ዓላማውን፣ እንዲሁም ለሰው ልጆች ሕይወት ያለውን ዕቅድ የገለጠልን (divine disclosure) “ሰማያዊው ንጽረተ-ዓለም በዚያ በጥንታዊው ንጽረተ ዓለም” ውስጥ በነበረው «ንኪኪ» ውስጥ ነው። በዚህ ንኪኪ ውስጥ ዘመን መጠቅ የሆነው ነገረ-መለኮታዊው እውነት ተሠጠን (timeless biblical/theological truth)። ስለዚህ ዘመን መጠቅ እና ድንበር ዘለል የሆነው እውነት ለማግኘት የመጀመሪያይቱን ቤተክርስቲያን አንገባጋቢና ወቅታቂ ጉዳይ ማተት ይኖርብናል። ጥያቄዋ እና የተሰጣት መልስ ሲገባን፤ የክርስቶስ ሐሳብ ይገባናል። ይህ የመጀመሪያ ተግዳሮት ነው። ይህ የማይለወጠው አምላክ ፈቃድ በእኛም ዘመን እንዲገለጥ ከዘመናችንም ጋር «ንኪኪ» ልንፈጥር ይገባናል። ለዚህም በዙሪያችን ያለውን አንገብጋቢ ጉዳይ በእኩል አጽኖት ጠንቅቆ መረዳት ያስፈልጋል። ምክኒያቱም ሕይወታችን የምትኖረው በዚህ ዓውድ ውስጥ ስለሆነ። የአማኞችን ልብ ያንጠለጠለው ጉዳይ ምንድር ነው? በውጪ ያለው ፈተና ምንድ ነው? ጣኦት የሆነብን ነገር ምንድር ነው? ሕይወትን አንቆ የሚይዝ ስጋት ምንድር ነው? የግጭታችን መንስኤ ምንድ ነው? ወዘተ….እነዚህ የቅዱስ ቃሉ ጥያቄዎች ሳይሆኑ የዘመናችን ጥያቄዎች ናቸው። ይህ ካልሆነ እንዴት አገልጋይ ህዝቡን ያክማል። ሐኪም ዝም ብሎ መድሃኒት አያዝም፤ በመጀምሪያ ምርመራ ያካሒዳል፤ ከዚያ በሽታው ከታወቀ በኋላ ነው መድሃኒት የሚታዘዘው። በሽታው ሳይታወቅ መድኃኒት ማዘዝ በራሱ በሽታ ነው። በበሽታውና በምርመራው ላይ አተኩሮ መድሐኒቱን ግን አለማወቅ እንዲሁ በራሱ በሽታ ነው። ስለዚህ ሁለቱንም በአንድ ላይ የማገናዘብ ጥበብ በተለይ የቤተክርስቲያን መሪዎች ሊካኑ የሚገባው ጥበብ ነው። ይህ ጥበብ ደግሞ በብዙዎች ምክር የሚጸና እንጂ በአንድ ሰው አስተያየት ላይ የተመሰረተ ሊሆን አይገባም።

 

ስለዚህ ክርስቶስን ያማከል፤ መስቀልና ትንሳኤውን ጅምሩና ግቡ በማድረግ ለሰመረ መንፈሳዊ ህይወት የሚከተሉት በአጣዳፊ ተደራርበን ልናክማቸው የሚገቡ ሕመማችን ናቸው።

 

► የመሪ ያለ፤ የእረኛ ያለ (1 ጴጥሮስ 5:1-4 )
ብቃት ያላቸው መሪዎች፤ ለጠብና ለግጭት የማይቸኩሉ፤ ከራሳቸውና ከእኔነታቸው በላይ ለመንጋው ፍቅር ያላቸው “የሚጤሰውን ጧፍ የማያጠፉና የተቀጠቀጠውን ሸንበቆ የማይሰብሩ” ብድራታቸውን የእረኞች አለቃ ሲመለስ ያደረጉ።

 

► የጸሎት ያለ፤ የሕብረት ያለ (ሮሜ 15:1-7)
በክርስቶስ የመስቀል ፍቅር መዋቅር ላይ የተመሰረተ የጉባኤ ሕይወት። የክርስቶስን አርዓያነት ያነገበ መተሳሰብ እና ርህራሄ።

 

► የስብከት ያለ፤ የትምህርት ያለ (ሐዋርያት 20፡ 25-32)
መጽሐፍ ቅዱን በመተንተን ላይ ያተኮረ፤ ክርስቶስን ያማከለ፤ ሙሉውን የእግዚአብሔር ምክር ያካተተ። ስንት አብያተ ክርስቲያናት በ10 ዓመት ቆይታዋ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን (ምንም እንኳ ጥቅስ በጥቅስ ባይሆንም ግን እያንዳንዱን መጽሐፍ ምእራፍ ጭብጥ ሐሳብ) ለመእመኗ ‘በስልታዊ መንገድ አስተምሬያለሁ’ ትል ይሆን? ይህ ካልሆነ እንዴት እንደ ጉባኤ መንፈሳዊ ህይወትን መመስረት እንችላለን?

 

ይህ ውይይታችን ይቀጥል ዘንድ ጸሎቴ ነው!

ኢየሱስ ይልቃል!

Source: http://www.samsontblog.com/

Read 5636 times Last modified on Friday, 25 May 2018 07:15
Samson Tilahun

 am Samson Tilahun. I feel a bit awkward telling you about myself. I would rather take every opportunity to tell you about Christ instead. However, increasingly, most of you who follow this blog site has not met me in person.

I’m a fellow follower of Christ, a husband to my dearest wife Betty- to whom I am eternally grateful for she has shared in my walk with the Lord as well as the ministry since our early twenties. I worship the LORD with the saints at Emmanuel Worship Center, NY. I’ve served in this local church in various capacities for over 15 years, starting from leading Choir groups, playing music, teaching Sunday adult classes…etc. I’ve also served as part of the eldership team for about 7 years.

I have a Masters of Divinity (M.Div.) in Biblical and Theological Studies from the Southern Baptist Theological Seminary, in Louisville KY, and currently working on Th.M. in New Testament.

Website: www.samsontblog.com/ Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 37 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.