You are here: HomeSermonየንስሓ እና የትዕግሥት ጥሪ

የንስሓ እና የትዕግሥት ጥሪ

Written by  Saturday, 10 September 2016 10:54

ከ2008 ዓ.ም መባቻ አንስቶ በየሥፍራው እንድሰብከውና እንዳስተምረው እግዚአብሔር በልቤ ያስቀመጠው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የያዕቆብ መልዕክት ነበር። ይህን መልዕክት ዓመቱን ሙሉ በመድረክ፣ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በጽሁፍና በተለያየ መንገድ እግዚአብሔር ባበዛልኝ ጸጋ መጠን ሳሰራጭ ቆይቻለሁ። አሁን 2008 ዓ.ም ተገባዶ የ2009 ዓ.ም ዋዜማ ላይ እንገኛለን። እኔም የአሮጌውን ዓመት ጉዞ የምቋጨውና በደጅ ያለውን አዲስ ዓመት እነሆ የምለው ከዚሁ ከያዕቆብ መልዕክት በተወሰደ ‘’የጊዜው ቃል’’ ነው። በመልዕክቱ እንደምትባረኩና ወቅቱን የሚመጥን የብርሃን ስንቅ እንደምታገኙ ያለኝን እምነት እየገለጽኩ ጌታ በነገር ሁሉ ማስተዋል እንዲሰጣችሁ እጸልያለሁ።

 

እናንተ ኃጢአተኞች፥ እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ፥ ልባችሁን አጥሩ። ተጨነቁና እዘኑ አልቅሱም፤ ሳቃችሁ ወደ ኀዘን ደስታችሁም ወደ ትካዜ ይለወጥ። በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ ከፍ ከፍም ያደርጋችኋል።” ያዕ. 4፥8-10

 

እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ታገሡ። እነሆ፥ ገበሬው የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እስኪቀበል ድረስ እርሱን እየታገሠ የከበረውን የመሬት ፍሬ ይጠብቃል።ያዕ. 57-8

 

ይህ ክፍል በውስጡ ያዘለውን ትክክለኛ መልዕክት ለማግኘትና “እዚህና አሁን” እግዚአብሔር ለእኛ ምን እያለን እንደሆነ ለመረዳት “እዚያና ያኔ” የመልዕክቱ የመጀመሪያ አንባቢያን የነበሩበትን ሁኔታ መረዳት የግድ ይላል። የመልዕክቱ ተቀባዮች እምነታቸውን በሚፈትን መከራ ውስጥ የሚያልፉ ናቸው [1፡2-3]። መከራቸው በዋነኛነት ከኢኮኖሚና ከኑሮ ሁኔታ ጋር የተሳሰረ ነበር [1፡9-11]። ከነበረባቸው የኑሮ ተጽዕኖ የተነሳ እድፍ ልብስ ለብሰው ጉባኤ ለመግባት ይገደዱ ነበር [2፡2] ። አንዳንዶቹ ገላቸው ላይ የሚጥሉት ልብስ፣ ሆዳቸው ውስጥ የሚያኖሩት ጉርስ ይቸገሩ ነበር [2፡15]። በአሠሪዎቻቸው የድካማቸውንና የላባቸውን ዋጋ ይነፈጉ ነበር [5፡4]። እስኪዝግና በብል እስኪበላ ድረስ ወርቁንና ብሩን፣ ልብሱንና እህሉን ለራሳቸው ከምረው በረሃብ የሚቀጧቸው የጊዜው ባለጠጎች በኑሮ የሚበድሏቸው አንሶ ያስጨንቋቸውና ወደ ፍርድ ቤት ይጎትቷቸው ነበር። [2፡6] ፍርድ ቤቱም ለማን እንደሚፈርድ ሳይታለም የተፈታ ነው። በአመጸኞች የተሞላው የዓለም ፍርድ ቤት ይቅርና የአማኞች ስብስብ የሆነችው የቤተክርስቲያን አገልጋዮች እንኳ ለባለጠጎቹ ጠብ እርግፍ እያሉ በኑሮ የተገፉትንና የተፈተኑትን የእምነት ቤተሰቦች ወግድልኝ ሲሉ ይታያል። [2፡6]

 

በዚህ ሁሉ ውስጥ ያዕቆብ ሁለት ጥሪዎች ያስተላልፋል። ለጨቋኞቹ ባለጠጎች የንስሓ ጥሪ፣ ለተጨቋኞቹ ድሆች የትዕግሥት ጥሪ። ሆኖም እነዚህ ሁለት ጥሪዎች የሚጋሩት አንድ ተመሳሳይ ነገር አለ። የጠገቡትንም ለንስሓ፣ የተገፉትንም ለትዕግሥት የሚጠራው ከጌታ ዳግም ምጽዓት ጋር አገናኝቶ ነው።

 

በገንዘብ ሰክረው ለሚፋንኑት “እንደ ሣር አበባ ያልፋልና። ፀሐይ ከትኵሳት ጋር ይወጣልና፥ ሣርንም ያጠወልጋልና፥ አበባውም ይረግፋልና፥ የመልኩም ውበት ይጠፋልና፤ እንዲሁ ደግሞ ባለ ጠጋው በመንገዱ ይዝላል።” [1፥10-11] ይላቸዋል። ያዕቆብ በዚህ ብቻ አያበቃም ትዕቢታቸውን ሲገሥጽ “አሁንም፦ ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህ ከተማ እንሄዳለን በዚያም ዓመት እንኖራለን እንነግድማለን እናተርፍማለን የምትሉ እናንተ፥ ተመልከቱ፥ ነገ የሚሆነውን አታውቁምና። ሕይወታችሁ ምንድር ነው? ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፍዋለት ናችሁና። በዚህ ፈንታ። ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም ይህን ወይም ያን እናደርጋለን ማለት ይገባችኋል። አሁን ግን በትዕቢታችሁ ትመካላችሁ፤ እንደዚህ ያለ ትምክህት ሁሉ ክፉ ነው” [4፡13-17]  ይላቸዋል። በመቀጠልም ስስታቸውንና ክፋታቸውን ሲያጋልጥ “አሁንም እናንተ ባለ ጠጎች፥ ስለሚደርስባችሁ ጭንቅ ዋይ ዋይ እያላችሁ አልቅሱ። ሀብታችሁ ተበላሽቶአል፥ ልብሳችሁም በብል ተበልቶአል። ወርቃችሁም ብራችሁም ዝጎአል፥ ዝገቱም ምስክር ይሆንባችኋል ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላል። ለኋለኛው ቀን መዝገብን አከማችታችኋል። እነሆ፥ እርሻችሁን ያጨዱት የሠራተኞች ደመወዝ በእናንተ ተቀምቶ ይጮኻል፥ የአጫጆችም ድምፅ ወደ ጌታ ፀባዖት ጆሮ ገብቶአል። በምድር ላይ ተቀማጥላችኋል በሴሰኝነትም ኖራችኋል፤ ለእርድ ቀን እንደሚያወፍር ልባችሁን አወፍራችኋል” 5፥1-5 ይላቸዋል።

 

በእነዚህ ሶስት ክፍሎች ውስጥ ያዕቆብ ድሆችን የሚንቁትንና የሚጨቁኑትን ባለጠጎች ፈራጅ በደጅ እንድሆነ በማመልከት ወደ ንስሓ ሲጠራቸው የተጠቀመባቸው ቃላት ማስተዋል ይበጃል። ምንም እንኳ እነዚህ ሰዎች በማህበረሰቡ ዘንድ የተፈሩና የተከበሩ ቢሆኑ፣ ምንም እንኳ ራሳችሁን እጅግ ከፍ አድርገው የሚቆጥሩ ቢሆኑም “በፀሐይ ትኩሳት የምትጠወልጉ ሣር ናችሁ፣ አሁን ታይቶ እንደሚጠፋ እንፋሎት ናችሁ፣ ለእርድ ቀን እንደሚወፍር እንሰሳ ናችሁ” በማለት በድፍረት ይገሥጻቸዋል፤ ፀሐይ ሳትወጣና ሳይጠወልጉ፣ ሙቀት ሳይመጣና መትነን ሳይጀምሩ፣ የእርድ ቀን ደርሶ ሳይታረዱ ንስሓ ‘ዋይ፣ ዋይ እያላችሁ አልቅሱ’  ይላቸዋል። 

 

አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ ጭቆና ውስጥ ላሉት አማኞች ያዕቆብ የሚያቀርበው ጥሪ የትዕግሥት ጥሪ ነው። ትዕግሥት ባሕሪ ነው፤ ያውም የእግዚአብሔር የራሱ ባሕሪ። ሰው በባሕሪው ትዕግሥቱ አጭር ናት። ለመፍረድ ይጣደፋል። እግዚአብሔር ያለው ኃይል ኖሮን፣ እግዚአብሔር የሚያውቀውን ሁሉ ብናውቅ ኖሮ በምድር ላይ ውሎ የሚያደር ሰው የሚኖር አይመስለኝም። እግዚአብሔር ግን ምሕረቱን ለሚፈልጉ ምሕረት እየሰጠ፣ ትዕቢተኞችን እየቀጣና ለፍርድ ቀን እየጠበቅ ሁሉን በትዕግሥት ወደ ፍጻሜው ይመራል። እኛም ከብርሃናት አባት የተወለድን የብርሃን ልጆች ነንና ይህን ባሕሪውን እንድንጋራ ይጠራናል። [1፡17-18]  

 

ሆኖም ትዕግሥት በመከራ ውስጥ የሚጎመራ ፍሬ እንጂ ከሰማይ የሚዘንብ መና አይደለም። [1፡2-4] አንድ ጊዜ አንድ ሰው ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል እንደ ጸለየ ይነገራል፡-  “እግዚአብሔር ሆይ ትዕግስት እንድትሰጠኝ እለምንሃለሁ። ነገር ግን እንድትሰጠኝ የምፈልገው አሁኑኑ ነው።” ይህ ሰው ትዕግሥት እየለመነ ትዕግሥትን በትዕግሥት ለመጠበቅ ትዕግሥት አልነበረውም። ትዕግሥት የእምነታችን እውነተኝነት ሲፈተን ከውስጣችን የሚፈልቅ ውድና ክቡር ባሕሪ ነው። ትዕግሥት ካለን በኑሯችን ሁሉ አንዳች የማይጎድለን ፍጹማንና ምሉዓን እንሆናለን። [1፡4]

 

አንዳንዴ መከራ ሲጸናብን፣ ፈተና በፈተና ላይ ሲደራረብብን “የምታገሠው እስከ መቼ ነው?” እንል ይሆናል። ያዕቆብ “እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ታገሡ።” [5፡7] ይለናል። የክርስትና ሕይወት በትዕግሥት የመጠበቅ ሕይወት ነው። ሆኖም ትዕግሥቱና ጥበቃው ለከንቱ አይደለም ትልቅ ፍሬ አለው። ያዕቆብ የክርስቲያንን ሕይወት የሚመስለው በገበሬ ነው። ገበሬ በዋነኝነት የሚያርሰው በአመት አንዴ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ የሚያሳልፈው በጥበቃ ነው። ከሰማይ ዝናብ ይጠብቃል። ለማረስ የፊተኛውን ዝናብ፣ ለመዝራት የኋለኛውን ዝናብ ይጠብቃል። ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ እንደሚመጣ እርግጠኛ ስለሆን በትዕግሥት ይቆያል፣ ከዚያም የከበረውንም የምድር ፍሬ ይቀበላል። እኛም ከሰማይ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባብቃለን።

 

ለውጥ ጥሩ ነው። ነገር ግን በምድር ላይ በዙሪያችን የሚሆኑ ለውጦች ሁሉ በጌታ ዳግም መምጣት ከሚሆነው ጋር ሲነጻጸሩ ኢምንት ናቸው። ስለዚህ ዘወትር በናፍቆት ልንጠብቀው የሚገባ ለውጥ የተባረከው ተስፋችን የታላቁ አምላካችንና የመድሃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ክብር መገለጥ ነው። እናም መገለጡን ከሚጠብቁ ሁሉ ጋር “አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ቶሎ ና” እያልን መንግሥቱንና ክብሩን በትዕግሥት እንጠብቅ። 

 

Read 10911 times Last modified on Saturday, 10 September 2016 11:01
Yared Tilahun

President, Golden Oil Ministry

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 152 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.