You are here: HomeSermonየቅዱሳን ቤተኝነት በዓለም (II)

የቅዱሳን ቤተኝነት በዓለም (II)

Written by  Tuesday, 10 May 2016 01:39

“ዓለምን ያልጠገበ መናኝ ልጃ-ገረዶችን ይሰናበታል” ይባላል በሀገራችን፡፡ “ዓለምን ያልናቀ” ቢል ኖሮ የተሻለ ይገልጸው ነበር፤ ምክንያቱም ዓለምን ማን ጠግቦ ያውቃል? የጠገባት የመሰለውስ ደጋግሞ እየቀያየጠ ጭማቂዋን ይጨላልጣል እንጂ ምነናን ከምርጫው መኻልስ ይከተዋል? መጥገብ ቀርቶ በበቂ እንዳልቀመሳት የደመደመ ደግሞ እንደጎመዣትና አነጣጥሮ እንዳለመባት፣ እንዳለማት ይኖራል። ይሁንና የአማርኛው ምሳሌያዊ አባባል መልዕክት “ጌታ ሆይ፥ እከተልሃለሁ፤ ነገር ግን አስቀድሜ ከቤቴ ሰዎች እንድሰናበት ፍቀድልኝ…” ብሎ ለጠየቀው ሰው ኢየሱስ “ማንም ዕርፍ በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም…” (ሉቃ. 9፡59) ሲል የመለሰለትን ሳያስታውሰን አይቀርም፡፡ የላይኛው ጥሪ ደርሷቸውና ልባቸው አንዴ በጌታ ተማርኮ ሲያበቃ ከዓለም ጋር ስንብት-ወዳጆች ካሉ ከመሰንበት ሲልም በዚያው ከመቅረት አይተርፉም (ዕብ. 6:4-8)። በዓለም ሳለን ከዓለም ክፋት ለመጠበቅ የቀደመውን የኃጥአት ኑሮ መተውና ከልማዶቹ ሁሉ በመለየት ልባችንን አንጽተን ክርስቶስን በዚሁ ዓለም መካከል እያበሩ መከተል የጥሪው አካል ነው (ዮሐ. 17፡15)። መንገዳችን ዋጋ የሚያስከፍል ነገር ግን እጥፍ ሽልማትና ዘላቂ ተስፋ ያለው የልብ መንገድ ነው፡፡

 

በቤት ፈንታ “ቤቶችን”!!

 

“… እውነት እላችኃለሁ፥ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እህቶችን ወይም እናትን ወይም አባትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ፥ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን ወንድሞችንና እህቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ፥ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ህይወት የማይቀበል ማንም የለም፡፡” ሲል ጌታ ኢየሱስ ተናግሮአል (ማር. 10፡28)፡፡ ስለ ጌታ ሲል የተወውን ሁሉ የተወ ፈጽሞ ባዶ አይቀርም፤ ተስፋው “ከስደት ጋር” “በመቶ እጥፍ” ሌሎች ቤቶችን፣ ሌላ ኑሮንና ቤተሰብ ነው፡፡ ሁሉ ሌላ ሌላ፤ እጅግ ልዩ!! በቤት ፈንታ “ቤቶችን”!! በመቶ እጥፍ ሲል ቁጥርን ብቻ ለማመልከት ሳይሆን የማይነጥፍና ጣፋጭ ደስታውን፣ ሰላሙንና ፍቅሩን ለማመልከትም ጭምር ነው፡፡

 

“ከስደት ጋር” ይላል! ወደ ጌታ ፊቱን ያዞረ በዓለም ለዓለም እንግዳ ነው፤ ስደተኛ፡፡ ዓለም ሁሉ በክፉ ስለተያዘ (1ኛ ዮሐ. 5፡19) በክርስቶስ ያመንን ሁላችን ከዓለም የተሰደድን የምድር “እንግዶችና መጻተኞች” ነን (1ኛ ጴጥ. 2፡11)፡፡ ቅዱሳን በዓለም ቤተኞች ሆነው ቢኖሩ ዘላለማዊውንና የማይጠፋውን ችላ ለማለት ይገደዳሉ፤ በእግዚአብሔር ቤትም እንዴት መኖር እንዳለባቸው ይቸገራሉ፤ ነፍሳቸውም ተንከራታና ከስራ ትኖራለች (1ኛ ጢሞ. 6:6-10)፡፡ ነገር ግን ቅዱሳን እንደ እንግዶችና መጻተኞች በዓለም ከኖሩ ሰማያዊውን ፍቅር የሚቀምሱበትን ቤተሰብና ለመልካም ስራ የሚነቃቁበትን (ዕብ. 10፡24) መሸሸጊያና መታጠቂያ ስፍራ ከወገኖቻቸው ጋር፣ ዓለም ብቻ አይደለም የገሃነም ደጆች የማይቋቋማትን ቤተክርስትያንን በመካከላቸው ያገኛሉ (ማቴ. 16:18)፡፡

 

ዘመነ-ግርንቢጥ

 

ስለዚህ በዘመነ-ግርንቢጥ ካልሆነ በቀር ውሃ ሽቅብ አይፈስምና ቅዱሳንም ባለመታዘዝና በመታለል ካልሆነ በቀር ዓለምም ቤት አትሆናቸውም፡፡ በእምነት ባለመታዘዝ ጠንቅ በሚመጣ አበሳ የእግዚአብሔር ሕዝብ ብዙ ታሪክ አለው፡፡ ከምድር ሕዝብ ሁሉ በምድር ዙሪያ በየሀገሩና በየሥፍራው በመሰደድ እንግዶችና መጻተኞች በመሆን የእስራኤልን ህዝብ በታሪክ የሚወዳደር እስከ አሁኑ ዘመን እንኳ ድረስ የለም፡፡ የቅርብ ታሪክ እንደሚመሰክረው እስራኤል በሮማውያን በ70 ዓ.ም. ከወደመችና ከህዝቧም ያለቀው አልቆ የተረፈው ከተበተነ በኃላ እንደ ሀገር እንኳ መመስረት የቻለችው ከአንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ አርባ አመታት ያህል በላይ በምድር ገጽ ሁሉ ላይ ተበታትነው ከኖሩ በኃላ እ.አ.አ2 በ1948 ዓ.ም. ከ68 ዓመታት በፊት ብቻ ነው፡፡ የእስራኤል ታሪክ ሲጀምርም “ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ…” (ዘፍ. 12፡1) በተባለለት በአብርሃም ታሪክ ነው፡፡ አብርሃም እግዚአብሔርን ታዞ ወደማያውቀው ሥፍራ ተሰደደ፡፡ የአብርሃም ዘር የሆነው የእስራኤል ህዝብ ግን እግዚአብሔርን ባለመታዘዝና በአመጸኛነት መዘዝ በምድር ሁሉ ላይ ሲሰደዱና እንደገና ሲሰበሰቡ ኖሩ፡፡ አብርሃም እግዚአብሔርን ታዞ በስደት ሲኖር እንደ መጻተኛ በእርሱ ተስፋ ኖረ (ዕብ. 11፡8-10)፡፡ እግዚአብሔርን ባለመታዘዛቸው እስራኤላውያን በተሰደዱና በተቸገሩ ቁጥር ግን ያለእርሱ የትም ሥፍራ ዕረፍትና ሰላም እንደሌለ የቅርብና የሩቅ ታሪካቸው ሁሉ አሳበቀባቸው (ዕብ. 3፡18-19)፡፡ የቤተክርስትያን አባቶች ከሚባሉት ውስጥ እጅግ ታዋቂ የሆነው ቅዱስ አውግስጦስ እንዳለው “ኦ ጌታ ሆይ! አንተ ለራስህ ሰርተኸናልና በአንተ እረፍት እስክናገኝ ድረስ ልባችን ከቶውኑ እረፍት የለውም፡፡3  በእግዚአብሔር ፍቅር ውስጥ ስንኖርና ስንታዘዘው በተስፋ ጽናት ደስ ተሰኝተንና ከዓለም ተለይተን በምድር እንኖራለን፡፡ 

 

የእግዚአብሔርና የእኛ ዓለም

 

“መምህር ሆይ፥ ከሕግ ማናቸይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት? ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፡- ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርስዋም፡- ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት። በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል።” (ማቴ. 22፡36-40) ሰው እንደ እግዚአብሔር “በፍጹም ልቡ በፍጹም ነፍሱና በፍጹም አሳቡ” ሊወደው የሚገባ የለም፤ ምክንያቱም እርሱ የተቆረጥንበት ድንጋይ፣ የተቆፈርንበት ጉድጓድ ነው (ኢሳ. 51፡1) ፡፡ ፍንክትካቾቹ ነን፤ ያለእርሱ ግንጥል ጌጥና ጎዶሎዎች እንሆናለን፡፡ ከእርሱ ሌላ ከፍጥረታት ሁሉ ለልብ፣ ለነፍስ ለአሳባችን የሚመጥን የለም፡፡ የእርሱ ከእርሱ በእርሱ ነን፡፡ “በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን” (ሐዋ. 17፡28)፡፡ እንደ እግዚአብሔር የወደደን የለምና ፍጹም ፍቅራችን በቅድሚያ ለእርሱ ይገባዋል፡፡

 

“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” (ዮሐ. 3፡16) እግዚአብሔር ልጁን እስኪሰጠን ድረስ ዓለምን ሁሉ እንዲሁ ወዶአል! እንዲሁ ማን ይወዳል? በሕያው አምላክ እንዲሁ እንደመወደድ ምን ነገር ለሰው ልጅ ተስፋ ይሆናል? እግዚአብሔር ዓለምን ሁሉ እንዲሁ ወደደ! የመጨረሻውን ብቸኛና ውድ የፍቅር ስጦታውንም ክርስቶስን ሰጠን!! አንድያ ልጁን ሰጠን! ያለልጁ ለሰው ልጅ ህይወትም ተስፋም የለም!

 

እግዚአብሔር ዓለምን ስለመውደዱ የነገረን ያው ዮሐንስ “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።” (1 ዮሐ. 2፡15-17) ሲል ደግሞ ይመክረናል፡፡

 

ዮሐንስ ስለራሱ ሲናገር ጌታ ኢየሱስ ይወደውና ወደ ደረቱ ያስጠጋው የነበረ ደቀመዝሙሩ እንደነበር ደጋግሞ ይናገራል (ዮሐ. 13፡23፣ 19፡26፣ 20፡2፣ 21፡7፣ 21፡20) ፡፡ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” (1ዮሐ. 4፡16) ብሎ የነገረን ዮሐንስ ነው፡፡ ስለፍቅር ጠንካራ መልዕክት አለው - “ወዳጆች ሆይ፥ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ፥ የሚወደውም ሁሉ ከእግዚአብሔር ስለ ተወለደ እግዚአብሔርንም ስለሚያውቅ፥ እርስ በርሳችን እንዋደድ። ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፥ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና።” ብሎናል (1ዮሐ. 4፡7-8)

 

ታዲያ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ “ዓለምን እንዲሁ” ሲወድድ እኛ ግን “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ” የተባልነው ለምንድን ነው? የእግዚአብሔር ዓለም የትኛው ነው? የእኛስ ዓለም የትኛው ነው?                        

 

የእግዚአብሔር ዓለም መልኩንና አምሳያውን በያዙ ነገር ግን ከክብራቸው በጎደሉና ያለ እርሱ ፍጹም ፍቅርና የልጁ ረድኤት ምስኪኖችና ጎስቋሎች በሆኑ የሰው ልጆች የተሞላ ነው፡፡ የእኛስ ዓለም? የእኛ የእያንዳንዳችን ዓለም “በሥጋ ምኞትና በዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም በሆነ መመካት” የተሞላ ዓለም ነው፡፡ የእግዚአብሔር ዓለም በሰዎች የተሞላ ነው፤ የእኛም የእያንዳንዳችን ዓለም ውስጥ በእርግጥ ሰው አለ፤ ያ ሰው ግን ሰፍነንና ገነን እኛው ራሳችን ነን፡፡ የእኛ ዓለም እጅግ የጠበበ፣ በገዛ ራሳችን ብቻ የተሞላ ዓለም ነው፡፡ እግዚአብሔር ወደ እርሱ ቀና እንድንል ወደ እኛ ሲመለከት እኛ ከራሳችን መላቀቅ አቅቶን ወደራሳችን እንዳቀረቀርን ነን፡፡ እርሱ ወደእኛ፤ እኛም ወደእኛ - መፍትሄ የለም! ያየንን ስናየው ግን ለጥማታችን ምንጭ ይፈልቃል (ዘፍ. 16:13)፤ በእርሱ እንረካለን፡፡

 

ሰዎች ሁሉ የማይረካን የግል ደስታ እንደሥጋቸው ምኞት ያሳድዳሉ፤ የዓይናቸውን አምሮት ተከትለው ወደቆጥ ሲንጠራሩ ዋናቸውን ይጥላሉ፡፡ ቢኖራቸውም ቢጎድላቸውም በገንዘብ ፍቅር እየተነዱ ንብረትንና ሀብትን ከክብር ጋር ለማከማቸት ሲሉ በትዕቢት ለትዕቢት በዕውር-ድንብር ሩጫ ይባትላሉ፡፡ እኛ ግን በአንጻሩ እርሱን ስንወድና “ዓለማችን” ስናደርገው እርሱ ይለጥቅና እንዲሁ ወደ ወደደውና ልጁን ወደሰጠው ዓለም፣ ወደ ሰዎች ፊታችንን ይመልሰዋል፡፡ ለነጭ፣ ለቀይ፣ ለጥቁር፣ ለወንድ፣ ለሴት፣ ለአዋቂ፣ ለልጅ፣ ለድሃ፣ ለባለጠጋ፣ ለኃጥአን፣ ለጻድቁ ለሁሉ ሰው ፍቅርና መልካም ልቦና እንዲኖረን ያደርጋል፡፡ ከሰው ሁሉ ጋር ከኃጢአታችንና በክርስቶስ ካለን ተስፋ የተነሳ አንድ መሆናችንን እናያለን፡፡ ከሰፊው የእግዚአብሔር ዓለም ካለንበት ከጥጋችን ተነስተን ሰውን በወርቃማው ህግ በፍቅርና በርህራሄ እናክማለን (ማቴ. 7፡12)፡፡ ጌታ አምላካችን በልጁ ሰፊ ፍቅሩን ለዓለም ሁሉ እንደገለጠ እንዲሁ እኛ ደግሞ በእርሱ ፍቅር ነጸብራቅ ባልንጀራችንን እንወድዳለን፡፡ ያን ጊዜ የእግዚአብሔርና የእኛ ዓለም ይገጥማል፡፡ 

 

“ባልንጀራዬስ ማነው?”

 

ወዲያውኑ “ባልንጀራዬስ ማነው?”  ብሎ እየተመጻደቀ ተዘልሎ በምቾት ከተቀመጠበት በትምክህትና በዳተኝነት የሚጠይቅ አለ፡፡ ከችግሩና ከጭንቁ የተነሳ “ባልንጀራዬ ከቶ ማነው? ማን ይደርስልኛል?” ብሎ የሚጮህ በየመንገዱና በየቤቱ ሞልቶ በፈሰሰበት ምድር ራሱን ላጸደቀውና ለትምክህተኛው ጠያቂ የጠቢቡ ጌታ ምላሽ በሳምራዊው ሰው ምሳሌ “ሂድ አንተም እንዲሁ አድርግ” (ማቴ. 17፡ 29 - 37) የሚል ጥሪ ነው፡፡ ሩህሩህ መሆን ትክክል ከመሆን ይበልጣል (1ኛ ቆሮ. 8፡1)፡፡ እንግዲያውስ ጥሪው ከአዋቂነታችንና ከምቾት ሰገነታችን ወርደን፣ ንፉግነትን ጥለን፣ ስስትን ጠልተን ሩህሩዎችና ቸሮች እንድንሆን ነው፡፡ “ከራስ በላይ ንፋስ”ን በ “ከራስ በላይ ክርስቶስ” እንድንተካውና በዓለም ከዓለም ተጠብቀን በቤቱ በፍቅር እንድንኖር ነው፡፡ ጸጋው ይብዛልን!!

 

  1. የቅዱሳን እንግድነት በቤተክርስቲያን (I) ከሚለው የቀጠለ
  2. እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር
  3. “You have made us for yourself, O Lord, and our heart is restless until it finds its rest in You.” ― St. Augustine 

 

 

Read 9520 times Last modified on Tuesday, 10 May 2016 02:06
Henok Minas Brook

ሔኖክ ሚናስ ከሁለት አሥርት አመታት በላይ ለእግዚአብሔር መንግስት በመቅናትና የቤተክርስትያንንም አንድነትንና ፍቅርን በመሻት በተለያየ መልኩ ጽሑፎችን የሚያዘጋጅና ከሁሉ አብልጦ ከቅዱሳን ጋር እንደቤተሰብ መኖርን የሚከታተል፥ በሙያው የፕሮጀክት አመራርና አስተዳደር አማካሪ ሲሆን ባለትዳርና የሁለት ሴት ህጻናት ልጆች አባት ነው።

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 68 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.