ምነው . . . . !
የጉረሮ ንዝረት ተግ ቢል
የአሳብ ንዝረት እንዲሰማ
ከልቡና ማማ
ወደ ልብ ጠልቆ
ወደ መንፈስ ዘልቆ
ስርክርክ፥ ድብልቅልቅ፣ ወመኔ ዱቅንዱቅ
ኳኳታ፥ ጫጫታ፥ ፋታ የል ሁካታ
በኮሾ ድልቅታ በተራ ላይ ላይታ
በጩኸት ረገዳ
በድምፅ ቱሪናፋ በአሉባልታ ናዳ
በደማቅ ድምፅ ፀሐይ፥ በብርቅርቅ ሐሩር
ነፍስን ግልብልቢት አካልቦ ማሳረር
ምነው፡፡
ምነው . . . . !
የጉረሮ ንዝረት ተግ ቢል
የአሳብ ንዝረት እንዲሰማ
ከልቡና ማማ
ወደ ልብ ጠልቆ
ወደ መንፈስ ዘልቆ
ኳኳታ፥ ቧገታ ድብልቅልቅ ጫጫታ - ሰንበት ሠርክ
አፍኖ ሊገድለን! ሲጥ ሊል እሳቦት?
በድምጽ ነበልባል በጩኸት እንፋሎት!
ሲጥ ሊል የሰው ነፍስ፥ የአሳብ ርግብግቢት
ድንቁርና ነግሦ ሲጎስም ነጋሪት
ሆሆ . . . !
አርምሞ ነጻነት፥ አርምሞ ዕረፍት ነው፤
በልቡና ጓዳ የጥበብ ጉዝጓዝ ነው፡፡
ቀምሞ ቀምሞ ከጠሊቅ ምንጭ ቀድቶ
ነፍስን የሚያሳርፍ ዐዲስ ዜማ ቃኝቶ
ዝምታ ድምፅ ነው የአልባሌ ማጥሪያ
ነፍስ ጓዳ ዘልቆ ግሣንግስ መጥረጊያ
ኑ ታጥቀን እንዝመት በከንቱ ጩኸት ላይ
አፍ ሁሉ ይለጎም ውስጥ መንፈስ ይታይ
ዝምታ ይደንስ በሙዚቃ ሠናይ
እኛም እንጠሙን ሹክሹክታውን ትተን
ወደ ውስጥ እንስማ አፍአዊውን ንቀን
እስቲ ዝም እንበል - - ዝም፡፡