You are here: HomeSermonወደቀኝ ወይንስ ወደ ግራ?

ወደቀኝ ወይንስ ወደ ግራ?

Written by  Thursday, 08 January 2015 00:00

ውድ ወዳጆቼ እስቲ ልብ ብላችሁ ከፅሁፉ በላይ/ጎን ያለችውን ይህቺን ምልክት አስቀድማችሁ ተመልከቷት። ደግማችሁ ፣ ደጋግማችሁ ተመልከቷት። ለእኔ ጥልቅ መልእክት ሰጥታኛለች። ጥቂት ላካፍላችሁ?

  • ሁለት ቀስቶች ይታያሉ
  • ትልቁ ቀስት ወደ ቀኝ ይመራል
  • ትንሹ ቀስት ደግሞ ወደ ግራ ይጠቁማል

 

እስቲ በጉዞ ላይ ይህን ምልክት ብታዩ ወደ የትኛው አቅጣጫ ታቀናላችሁ? ወደቀኝ ወይንስ ወደ ግራ? ግራ የሚያጋባ ነገር ነው። እስቲ እኔ በዚህ ምልክት በኩል የገባኝን ትንሽ ልበል። መቼም በአንድ ተራ ስእል አይናገረውም ባትሉኝም በጥቅስ አካሄዴን ላፅድቅ። 

 

ኢዮብ 33፡14፤ እግዚአብሔር በአንድ መንገድ በሌላም ይናገራል፤ሰው ግን አያስተውለውም።

 

ይህ ምልክት ዛሬ በክርስቶስ ቤተክርስቲያን ያለውን ግራ መጋባት ለእኔ ወለል አድርጎ አሳይቶኛል በምስሉ ላይ ትልቁ ቀስት ዋናው ይመስለኛል ዋናውን አቅጣጫ ጠቋሚ፣ ዋናው ምልክት፣ ዋናው መልእክት ደግሞ ትንሿ ቀስት ትልቁን ምልክት እንደ ሰሌዳ ተጠቅማ (ተንተርሳ) ሌላ አቅጣጫ የምትጠቁም ሌላ ምልክት፣ሌላ መልእክት?

 

ዛሬ ዛሬም ዋናውን ፡- የዘላለሙን ወንጌል፣ የመንግስቱን ወንጌል ፣ የስሙን ወንጌል ታላቅ፣ ዋና አቅጣጫና መልእክት እንደ ሰሌዳ ብቻ (ማሳያና፣ማሳመኛ፣ መንተራሻ ብቻ) በመጠቀም ወደ ሌላ ተፃራሪ አቅጣጫ (ምድራዊነት፣ስጋዊነት፣ አለማዊነት ፣ወዘተ...) የሚመሩ ብዙ " ትንንሽ ቀስቶችን (ስብከቶች፣ ዝማሬዎች፣ትምህርቶች፣ ልምምዶች፣ ትንቢቶች) እያስተዋልን ነው። ታዲያ ወዳጆቼ ምን እናድርግ?

 

እኔ የገባኝ ሁል ጊዜ ትልቁ ቀስት የሚጠቁመውን የዘላለሙን፣ የመንግስቱንና የስሙን ክብር ወንጌል አቅጣጫና መልእክት በዋነኛነት ጠበቅ አድርጎ መያዝና በዚያ መስመር መጓዝ ነው ደግሞ ትልቁን ምልክት ተንተርሳ አቅጣጫ የምታስቀይረውን የትንሿን ቀስት ጥቆማ አለመከተል፣ መናቅና እምቢ ማለት ብቻ ሳይሆን ከትልቁ ቀስት ላይ ለመፋቅም ለእውነተኛው የክርስቶስ ወንጌል መጋደልም ያስፈልጋል፤በወንጌል ስም መደናገርንና ማደናገርን ለማስቆም።

 

ይሁዳ 1፡3 ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ። 

 

ወገኖቼ ቃሉም እንዲህ ሲል ይመክረናል

 

2 ቆሮ 11፡2 በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፤ 3 ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። 4 የሚመጣውም ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ (ሌላ ኢየሱስ?) ቢሰብክ፥ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ (ልዩ መንፈስ?) ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል (ልዩ ወንጌል?) ብታገኙ፥ በመልካም ትታገሡታላችሁ።

 

ሉቃ 21፡8 እንዲህም አለ። እንዳትስቱ ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች። እኔ ነኝ፥ ዘመኑም ቀርቦአል እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ እነርሱን ተከትላችሁ አትሂዱ።

 

ገላ 1፡8 ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን።9 አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።10 ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሁን እሺ አሰኛለሁን? ወይም ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? አሁን ሰውን ደስ ባሰኝ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁም።11 ወንድሞች ሆይ፥ በእኔ የተሰበከ ወንጌል እንደ ሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ፤ 12 ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ እኔ ከሰው አልተቀበልሁትም አልተማርሁትምም።

 

ገላ 3፡1 የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?

 

2 ቆሮ2፡14 ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን በእኛም በየስፍራው ሁሉ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ ለአምላክ ምስጋና ይሁን፤15 በሚድኑቱና በሚጠፉቱ ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ ነንና፤16 ለእነዚህ ለሞት የሚሆን የሞት ሽታ ለእነዚያም ለሕይወት የሚሆን የሕይወት ሽታ ነን። ለዚህም ነገር የሚበቃ ማን ነው?17 የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት እንደ ብዙዎቹ አይደለንምና፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን።

 

• ከላይ ባየናቸው የቃሉ እውነቶች ሁሉ ውስጥ አንድ የጋራ መልእክት ይነበባል፤-

 

በስሙ ፣ መንፈሱ ፣ በወንጌሉ፣ በቃሉ ሰሌዳ ላይ ተቀላቅለው፣ ተሸቅጠውና ተንተርሰው ስለተፃፉ፣ ስለሚነገሩና ስለሚተገበሩ ሌላና ልዩ መልእክቶች፤ ከእነርሱም ደግሞ እንድንርቅ የሚያሳስብ ቁልፍ ፣ወሳኝና ወቅታዊ መልእክት። ጌታ በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጠን!!!

 

አንድ ትንሽ ምክር ልጨምር? በትልቁ ቀስት ሰሌዳ ተንተርሳ የምትሳለዋን ትንሿን ቀስት ለመለየት፣ በመሰረቱ የቱ ንግግር ከእግዚአብሔር እንደሆነና እንዳልሆነ ለመለየትም የሚከተለው ቃል ቁልፍ ቃል ይመስለኛል። እንዲህ ይነበባል

 

ዩሐ7፡ 16 ስለዚህ ኢየሱስም መለሰ እንዲህም አላቸው። ትምህርቴስ ከላከኝ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም፤
(ሁሉም እንዲህ ሊል ይችላል። መለያችን ምንድር ነው?)

 

17 ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር፥ እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር ቢሆን ወይም እኔ ከራሴ የምናገር ብሆን ያውቃል። (ሰው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሊያደርግ ብቻ ከወደደ ከእግዚአብሔር የተነገረውንና ከሰው ልብ የተወለደውን መለየት ይችላል። የብዙዎቻችን የመሳትና የመደናገር መሰረታዊ ምንጩ የራሳችንን ፈቃድ ለማድረግ የምናደርገው የምኞት ቅኝት ነው - የራሳችንን ፍላጎትና ምኞት (ፈቃድ) በእግዚአብሔር ለማሟላት ስንሮጥ በእንደዚህ አይነት ወጥመድ እንወድቃለን)

 

ወገኖቼ እንዲህ ግን ብንል ።

 

ቢመቸኝ፣ ባይመቸኝ፤ ቢጠቅመኝ ፣ ባይጠቅመኝ፤ ቢያስደስተኝ፣ ቢያስከፋኝ ፤ ለህይወቴ የፈቃድህን እውቀት ላደርግ ብቻ ነው የምፈልገው ብንል ከግራ መጋባት፣ በቀላሉና በከንቱ ከመሳት እንጠበቃለን

 

18 ከራሱ የሚናገር የራሱን ክብር ይፈልጋል፤ የላከውን ክብር የሚፈልግ ግን እርሱ እውነተኛ ነው በእርሱም ዓመፃ የለበትም።

 

(የክብር አቅጣጫም የመልእክትን ምንጭ ጠቋሚ ነው - ነገሩ እግዚአብሔር የሚከበርበት ወይስ ሰው፣ ተቋም ??? )

ጌታ በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጠን!

Read 7848 times Last modified on Thursday, 08 January 2015 12:03
Pastor Abby Emishaw

Pastor Abby Emishaw is the visionary, founder and senior pastor of the U7000 church. He is focused on seeing the Body of Christ globally grow into maturity. He is dedicated to the teaching, development and training of leaders; and the advancement of God's present truth purposes on the earth.

Website: unique7000church.org Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 369 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.