You are here: HomeOpinions"ዓለም ተስፋ ቁረጭ አልተገናኘንም!"

"ዓለም ተስፋ ቁረጭ አልተገናኘንም!"

Written by  Tuesday, 25 July 2017 20:18

"ከሀጢያት በስተቀር የቀረብን የለም
ዛሬም አለም ተስፋ ቁረጭ አልተገናኘንም!"
ሙሉቀን መለሰ


ባሳለፍነው እሁድ EBS በእንጨዋወት ፕሮግራሙ የጥንቱን ድንቅ ድምፃዊ ጋሽ ሙሉቀን መለሰን ቃለመጠየቅ ለእይታ ካበቃ በኋላ ከፊል ዘመን ባላደበዛዛቸው ዘፈኖቹ በትዝታ ሲወዘውዝ ገሚሱ ከአመታት በፊት ያስደመጠውን የዝማሬ ሰንዱቅ ከሸጎጠበት ፈልጎ እያዳመጠ በትውስታ ግርሻ ስሙን እያነሳሳ ነው::

 

አድናቆት እና ትችት ሀዘኔታና ፍርድ እየተግተለትለ የተለመደው የድረ-ገፅ ምልልስ ላይ የአንዳንድ ግለሰቦች ነቆራና አስተያየት የሚያሸማቅቅ ከመሆኑም ብሶ በተዛባ ሚዛን ይህን አንጋፋ ሰው ሽቅብ ቁልቁል ሲያንገላታ ማየት ያስተዛዝባል:: በተለይም በገጠመው የረጅም አመት የጤና እክል ሳቢያ ተክለ-ስውነቱ ላይ በሚታዩ እና ባለፈበት ተደጋጋሚ የህክምና ውጣ ውረድ ሰበብ እንደልብ አለመንቀሳቀሱ ላይ የሚሰነዘሩ አላግባብ አስተያይየቶች ክብረ-ነክ ናቸው:: በቃለመጠይቁ ላይ የታየበት አካላዊ ሁኔታ ላይ ለእማኝ እንኳን እዚህ መጥቀስ የማይገቡ ነውረኛ ንግግሮች እየተነበቡ ይገኛሉ:: በሰው የእድሜ ልክ ውጣ ውረድ ላይ እንደው መፃፍ ስለቀለለ በመረጃ መረብ ጥላ ተከልሎ መሳለቅ ነውር አይደለም እንዴ?

 

ያ በእንዲህ እንዳለ ለቀረቡለት ጥያቄዎች በተለይም ስለመንፈሳዊ ህይወት አጀማመሩ ያቀረበው ገለፃ ለሰፊው ህብረተሰብ ለመረዳት የሚቀል ይሁንም አይሁን ወይንም በተሻለ ማብራሪያ ሊያቀርበው ይችል እንደነበር መወያየት ሌላ ጉዳይ ሆኖ ስለምላሹ የቀለሉ ንግግሮችን ግን መሰንዘር የተገባ አይመስለኝም:: መንፈሳዊ ነገር ባብዛኛው ግላዊነቱ የሚያመዝን የህይወት አስተውሎ ነው ማንም ስለማንም የነፍስ ምርጫ እና መለኮተ-ሀሳብ በሙላት ለመናገር ሊደፈር አይገባውም::

 

ለማንኛውም ግን ለተነሱት አነጋጋሪ ጉዳዩችም ሆነ ነቀፌታዎች ከረጅም አመታት በፊት በነዛሪ ድምፁ የከሸናቸው ድንቅ ዝማሬዎች በቂ መልስ እና ማብራሪያ ይሰጣሉ እና ዳግም በተሀድሶ ቢደመጡ እላለሁ::

 

ከብዙዎቹ ስድቦች እና ነቀፋዎች ጥቂቱን ከመዝሙሩ ምላሽ ጋር:

 

"አይ ሙሉቀን ለካ ከድጡ ወደማጡ ነው የሄደው ...አቤት የሰው ልጅ ፈተናው! እንዲህ ከሚቸገር ቢዘፈን ይሻለው ነበር" እያሉ ከንፈር እየመጠጡ ላሉ የርሱ ዜማዊ ምላሽ እንዲህ ነው "ከጌታ ጋራ ሲሄዱ ከኢየሱስ ጋር ሲሄዱ እንዴት ያምራል ጎዳናው እንዴት ያምራልም መንገዱ! እይታው ከዚህ ስጋ እና ምድራዊ ነገር ማትሮአልና እንዲህ ብሎ ያለበትን እረፍት ነግሯል " ከርሱ ጋር ኖረን ምንም አላጣንም ከሀጢያት በስተቀር የቀረብን የለም ሁሉ በሁሉ ነው አጥተን አልለመንም አለምን ዞር ብለን ሙይልን አላልንም"

 

"በጨለማ ያለህ ቅዥታም " ላሉትም ስላለበት የውስጥ ብርሀን የተቀኘውን ያስታውሳል " የህይወት ብርሀን የሱስ የኔ አለኝታ ምን ጠፍቶ ካንተ ቤት ከነስምህ ጌታ"!

 

"ሌባ! ድሮም ተስፋ ሲቆርጥ ነው እዛ ሄዶ የተደበቀው ...ብልጥ እግዚአብሄርን አወኩ ካለ በኋላ አስፈቅዶ ነው ለስድስት አመታት ሲዘፍን የነበረው? በማለት እያንቋሸሹ ላሉ የሂወቱን ትግል እና ከዘፈኑ አለም ለመውጣት የነበርውን ትንቅንቅ በቅኔው ኑዛዜ ነፍሱን እንዲህ ሲል ሞግቷቷል "በተከፈለ ልብ ለምን ትኖሪያለሽ የሁለት ጌቶች ባሪያ እንዴት ትሆኛለሽ? ነፍሴ ሆይ ምረጪ ማንን ትወጃለሽ ከየሱስ ከአለም የቱን ታመልኪያለሽ ?"ሲልም ከነበረበት ምድራዊ ዝናና እና ተድላ መላቀቅ ምንኛ ከባድ እንደነበረ እየዘመረ መስክሮአል:: "ባለም ፍርፋሪ እየተደለለ ጠንካራ አቋም አጣሁ ልቤ ተከፈለ:: ልቤ ልፍስፍስ ነው መቁረጥ ያቅተኛል አሁንም ካለም ጋር ጨዋታ ያምረኛል"

 

አንዳንዶችም "አለም አብልታህ ስትጠግብ እግዚአብሄር ትዝ አለህ?! እያሉ አይደል? እርሱ ግን የአለምን ተድላ እንዲህ አራክሶታል " አለሁ ባይነትሽ አስመሳይነትሽ አለም ውሸታሟ በቃ ማጭበርበርሽ አዲስ ማታለያ ዘዴ አላገኘሽም አለም ተስፋ ቁረጭ አልተሳካልሽም" እኔን አምነሽ ነበር አይከዳኝም ብለሽ የበለጠ አግኝቼ ዛሬ ጉድ አረኩሽ" ፍልሚያው አልቆ ሙሉ ህይወቱ ለገባው እውነት በተማረክ ጊዜም " አለም ተስፋ ቁረጭ አልተገናኘንም አምላክ ከኔ ጋር ነው አታሸንፊኝም" እያለ ፅኑ አቋሙን ከአምላኩ ጎራ አድርጓል::


ብዙዎች "ዲያብሎስ ወዳላወከው መንፈስ ወስዶሀልና እባክህ ፀበል ተጠመቅ" መድሀኒአለም ነፃ ያውጣህ" በማለት ያለውቀት በስላቅ እየተናገራችሁ ነው:: ጋሽ ሙሉቀን ግን ከሰማይ በታች እንድንበት ዘንድ በተሰጠን አንድ እና ብቸኛ ስም አምኖ ዲያብሎስን እንዲህ ያስበረግገዋል እንጂ በውነቱ እንደቃላችሁ አይደለም "በእድሜ ዘመን ሁሉ እገስፅሀልሁ የምነት አርበኛ ነኝ እቋቋምሀልሁ በጉባኤ መሀል አዋርድሀልሁ በኢየሱስ ስም ውጣ እያልኩ አዝሀለሁ" "ለፅድቅ የሚሰደድ የዚህ አለም መናኝ የተስፋ አገር ወራሽ የምነት ወታደር ነኝ::

 

ይህ ሰው በዘመኑ እና በሀገሩ በተወዳጅነት በስኬት ማማ ላይ ከነበሩ ብርቅ ኮክብ ድምፃዊያን አንዱ እና ስመ ገናናው ነበረ :: ረብ ይኑራቸውም አይኑራቸውም ትውልድ እየተቀባበለ የሚደመጣቸው ዘፈኖቹ የማይረሳ አድርገውታል ነገር ግን ከሙያው እና ንኪኪ ካላቸው ነገሮች ዙሪያ አርቆ ያስቀመጠው የህይወት ምርጫ እና የነፍስ ትሩፋት ነው:: ከሙያው አንፃር ለምድር ተድላ የሚበጀው እጅግ ፈታኝ እና ከባድ የእንቁልልጭ ግብዣዎችን እምቢ ያስባለው ሀያል የአምላኩ ፍቅር እንጂ ሌላ እንዳይደለ በቅርበት ስላየሁት ለመናገር እደፍራለሁ:: እንደባከነ እያሰቡ በቁጭት በሚንገበገቡለት ያን የመሰለ ድምፁ "እምቧ ዘቢደር ዘቢደር" "ወይ ሰውነቷ" "ናኑ ናኑ ነይ" አልልበትም ብሎ ከማለ እንግዲህ ምን ታረጉታላቸሁ?! ካልገባን በዝምታ ማለፍ ወይም መጠየቅ እንጂ ማንጓጠጥ የሚገባ ነገር አይደለም:: ሆ!

 

 

የቃለ-ምልልሱን የመጀመሪያ ክፍል ለማየት የሚከተለውን ሊንክ ይጫኑ
https://www.youtube.com/watch?v=WpvZEA3IPU4&t=141s

Read 7507 times Last modified on Friday, 28 July 2017 17:27
Marefia Mengistu

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Latest from Marefia Mengistu

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 24 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.