You are here: HomeOpinionsየኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ሚናና ኃላፊነት ምንድን ነው? ምጋቤያዊ ደብዳቤ

የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ሚናና ኃላፊነት ምንድን ነው? ምጋቤያዊ ደብዳቤ

Written by  Thursday, 11 June 2015 00:00

ይህ ደብዳቤ ከሁለት ሳምንት በፊት “Open Pastoral Letter to the Ethiopian Christians” በሚል ርእስ የቀረበ ግልጽ ምጋቤያዊ ደብዳቤ ነው።ጽሑፉ በወጣ በሦስተኛው ቀን 204 ሺህ አንባቢዎች እጅ መድረሱን የፌስ ቡክ መረጃ አገኘሁ። ይህ አኃዝ ታዋቂ ክርስቲያናዊ ድረ ገጾችንና ኢሜይል ሥርጭቶችን አይጨምርም። ከህዝበ ክርስቲያኑና ከተለያዩ በአገርና በውጭ ካሉ መሪዎች በአብዛኛው የደረሰኝ ጥያቄ፣ ወደ አማርኛ እንዲመለስ ነው። የእግዚአብሔር ሉዓላዊ እጅ በዚህ ውስጥ አለበት ብዬ ስላመንሁ፣ አንዳንድ እርማቶችን አድርጌ በዚህ መልክ አቅርቤዋለሁ።

 

በቅድሚያ ዐላማዬን ላስተዋውቅ፤ ይህ ምጋቤያዊ ደብዳቤ የተጻፈው ክርስቲያኖች ራሳቸውን እንዲመረምሩ፣ በጸሎት እንዲተጉና መንፈስ ቅዱስ ለአገራችን የሚናገረውን በጥሞና እንዲያስተውሉ ትንቢታዊ “ዘር” ለመዝራት ነው። ደብዳቤው በጸሎት፣ በፍቅርና በርኅራኄ ተገርቷል። በመሆኑም ፖለቲካዊ የውስጥ ግፊት የለውም፤ ወገኝተኝነቱም ከእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅ ሥራ ጋር ብቻ ነው። ብሔራዊ ሐዘን ደርሶብናል። የሁላችንም በተለይም የኀዘኑ የመጀመሪያ ተጐጂ ቤተሰቦች ልብ ተሰብሯል። “ምን ይበጃል?” የሚለው ጥያቄ የእያንዳንዳችንን ቤት አንኳኩቷል፤ ብሔራዊ ጥያቄም ሆኗል። የችግሮቻችንንም መንሥኤና መፍትሔ በተመለከተም ፈርጀ ብዙ የሆኑ ምላሾች እየተሰነዘሩ ናችው። በዚህ አገራዊ ውይይት (national dialogue) ውስጥ የክርስቲያኖች ኃላፊነትና ድርሻ ምንድን ነው? በዚህ አንጻር የደብዳቤው ዐላማ የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት እንደ አምላካዊ ተቋምነታቸው፣ ምእመናን ደግም እንደ እግዚአብሔር ሕዝብነታቸው እውነተኛ አማራጭ እንዲሆኑ ጥሪ ማቅረብ ነው።

 

ቤተ ክርስቲያን የግራም የቀኝም፤ የመንግሥትም ሆነ የተቃዋሚ ድርጅቶች ልሳን አይደለችም። ቤተ ክርስቲያን ምንጊዜም የእግዚአብሔርን ተልእኮ እንድታራምድ በራሱ በእግዚአብሔር የተመሠረተች መለኮታዊ ተቋም ናት። ተልእኮዋ እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት የጀመረውን የድነት ሥራ፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በቃልና በተግባር ለዓለም ሁሉ ማብሰርና ከፍጻሜ ማድረስ ነው። የውቅሯ እሴት መለኮታዊ ነው። ይህም ማለት ማንነትዋና ተልእኮዋ የተመሠረተው በእግዚአብሔር ማንነትና ዓላማ ላይ ነው። ይሁን እንጂ በዚህ ምድር እስካለች ድረስ ማኅበራዊ ማንነት አላት። ይህም ማንነት ከአገሪቱ ተግዳሮቶችና በረከቶች ጋር ትስስሮሽ አለው። ደብዳቤው ፈውስ፣ ዕርቅ፣ ሰላም፣ አንድነትና እድገት እንዲመጣ በሚደረገው ብሔራዊ (አገር ዓቀፋዊ) ውይይት ውስጥ፣ ቤተ ክርስቲያን የራሷን ተኣማኒነት ያለው ትንቢታዊ ድምፅ እንድታሰማ በትሕትና ጥሪ ያቀርባል።

 

እኩይ ተግባርና ሥቃይ ሕይወታችንን በድንገት ሲያጨልመው፣ “እግዚአብሔር ለምን ዝም ይላል?”፣ “እግዚአብሔር ወዴት ነው?”፣ “ጣልቃ ገብቶ ለምን አላስቆመም?” የሚሉ ብርቱ አስተምህሮአዊና ፍልስፍናዊ ጥያቄዎች በውስጣችን ይፈጠራሉ። በእውነቱ ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢም መልስ ማግኝት ይቸግራል። ከብዙ ዓመታት በፊት ነቢዩ ዕንባቆም ተመሳሳይ ጥያቄ አስተጋብቷል፤ “አቤቱ እኔ ስጮኽ የማትሰማው እስከ መቼ ነው?” (1፥2)። ዕንባቆም “እግዚአብሔር በግፈኞች እጅ መከራ የደረሰባቸውን ሰዎች ጩኸት አይሰማም” ወደሚል ድምዳሜ የደረሰ ይመስላል። ዳዊት በመዝሙሩ፣ “አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ? እኔን ከማዳን ከመቃተቴም ቃል ለምን ራቅህ?” (መዝ 22፥1) በማለት ያነሣውን ጥያቄ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ባሰማው የጣር ድምፅ ወስጥ ተስጋብቷል። ይህም ጣር የሚያሳየን በእውነት አምላካችን የመከራችን ተካፋይ መሆኑን ነው። ተስፋችን የተመሠረተው በእርሱ ሉዓላዊ ገዥነትና ሁሉን ዐዋቂነት ላይ ነው። “ምሥጢሩ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው፤ የተገለጠው ግን የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ እናደርግ ዘንድ ለእኛ ለዘላለምም ለልጆቻችን ነው።” (ዘዳግም 29፥29)።

 

ራሱን “አይሲስ” (ISIS) በማለት የሚጠራው እስላማዊ አሸባሪ ተቋም፣ በንጹሐን ወንድሞቻችን ላይ ያደረሰው አረመኔአዊ እኩይ ተግባር ልባችንን በእጅጉ አድምቶታል። ይህ የሆነው ለሥራ አገራቸው በሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ሌሎች አፍርካውያን ዜጐች ላይ የደቡብ አፍሪካ ጽንፈኞች ባደረሱት ግድያ የተፈጠረው ቊስላችን ገና ሳይሽር በመሆኑ፣ ሐዘናችንን ይበልጥ አክብዶታል። አፓርታይድ በደቡብ አፍሪካውያን ላይ የፈጸመውን ግፍና ዐመፅ አሁን እነዚያው የአፓርታይድ ሰለባዎች መፈፀማቸው ትልቅ ምጸት (irony) ነው። በአንድ ወቅት በግፈኞች እጅ ሥቃይ የደረሰባቸው ደቡብ አፍሪካውያን፣ እነርሱ ራሳቸው በሌሎች ምስኪን ዜጐች ላይ የሚያደርሱት ሥቃይ እነ ኔልሰን ማንዴላ ከተፋለሙለት የነጻነት ሕልም (ትግል) ጋር በእጅጉ ይቃረናል። እንግዲህ ነጻነት በአስተሳሰብ ለውጥ ካልተተካ ለጭቆና ዑደት (Cycle of Oppression) ይዳርጋል ማለት ነው። ይህም ማለት በአንድ ወቅት በግፍ የተበደሉ፣ የነጻነት ቀን ሲበራላቸውና የበላይ ሲሆኑ፣ ኢፍትሐዊነትን ደርበው በዳይ ከሆኑ ስለ ፍትሕ ባሰሙት ጩኸትና የትግል ዝክር ላይ ጥላሸት መቀባት እንዲሁም ውለታ ቢስ መሆን ነው።

 

ይሁንና ነገሮች እየከፉ፣ ዓለም አቀፋዊ የሰላም መረበሽና የፍትሕ ቀውስ እየከረረ በመጣበት በዚህ ዘመን እንደ ክርስቲያን ተስፋ የምናደርገው ልዑል እግዚአብሔርን ነው። እግዚአብሔር አሁንም በዙፋኑ ላይ ነው። ቃሉም እንደሚል፣ “እነሆም፥ ዙፋን በሰማይ ቆሞአል፤ በዙፋኑም ላይ ተቀማጭ አለ” (ራእ 4፥2)። እግዚአብሔር የታሪክን ሂደትና አቅጣጫ በሉዓላዊነቱ ይገዛል፤ ትርጉም ወዳለው ፍጻሜም ይመራል። ከእርሱ የፍትሕ ዐይኖች የሚሰወር ምንም ነገር የለም። እግዚአብሔር ከአቤል ዘመን ጀምሮ የንጹሐንን ደም ሲያፈሱ ከነበሩት ግፈኞች ይልቅ እጅግ ብርቱ አምላክ ነው፤ አንድ ቀን ከዙፋኑ ፍርድ ይሰጣል። በገዛ ወንድሙ ከተገደለው ከአቤል ጀምሮ፣ በአይሲስ እስከ ተገደሉት ወንድሞቻችን ድረስ የፈሰሰው (ወደ ፊትም በዓለም ዙሪያ የሚፈሰው) የንጹሐን ደም በከንቱ አይቀርም። ዓለም በልዑል እግዚአብሔር እጅ እንጂ፣ በግፈኞች እጅ አይደለችም። አምላካችን የፍትሕ አምላክ ነው።

 

ታዲያ እንደ ኢትዮጵያዊ ክርስቲያን ሚናችን ምንድን ነው? ኃላፊነታችን ምንድን ነው? አንድ ነገር አበክሬ ልናገር፤ በንጹሐን ወንድሞቻችን ላይ የደረሰው ግፍ፣ በእኛም የደረሰ ግፍ ነው። ምንም እንኳን በክርስቶስ ሥራ ዜግነታችን በቅድሚያ ሰማያዊ ቢሆንም፣ በዚች ምድር እስካለን ድረስ ማኅበራዊ ማንነትም (sociological entity) አለን። ምድራዊው ኑሮአችን ከቶ ላይነጠል ከዜግነታችን ሕይወትና ትግል ጋር ተጋምዷል። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚሆነው ነገር ሌሎችን በሚመለከትበት መጠንና ደረጃ እኛንም በደጉም በክፉም ይመለከታል። ለፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውሶች ባይተዋር ልንሆን አንችልም። ተልእኮአችን ብሔራዊ ዕርቅና ተሐድሶ እንዲመጣ በሚደረገው ትግል ውስጥ ክርስቶስን ያማከለ ተሳታፊ መሆንንም ይጨምራል። በትውልድ ላይ የጽድቅ ተጽዕኖ ማለት ይህ ይመስለኛል። ክርስቲያን ሆንን ማለት አገራዊ ጒዳይ አይመለከተንም ማለት አይደለም። የተጠራነው ለጨለማው ዓለም ብርሃን እንድንሆን ነው፤ በመደበኛው አገላለጽ “አምላካዊ ተልእኮ የተቀበለ አማራጭ ማኅበረሰብ” እንድንሆን ነው። ከተለያየ ባህል፣ ቋንቋ፣ መደብ፣ ወዘተ የመጣን ሰዎች ብንሆንም በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ተዋጅተን ከእግዚአብሔር ጋር እንዲሁም እርስ በእርሳችን ታርቀናል። ይህ ዕርቅ (የማስታረቅ ሥራ) ለምድራችን ሁለንተናዊ ፈውስ ማምጣት መቻል አለበት። እግዚአብሔር ልጁ ክርስቶስን በመጨረሻ መፍትሔነት ለዓለም ሰጥቷል፤ የክርስቶስ ሕይወቱና ሥራው የነካውና የቀየረው ትውልድ ብቻ ነው፣ እውነተኛ ምስክርና ለትውልዱም ፈውስ መሆን የሚችለው። በአጭሩ የመልእክታችን የመለወጥ አቅም የሚወሰነው፣ በተነካንበት አምላካዊ ጣት የጉልበት መጠን ነው።

 

በአሁኑ ጊዜ የሦስቱ ታላላቅ ቤተ እምነቶች፣ ማለትም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የወንጌላውያን አማኞችና የካቶሊኮች ቊጥር 62% እንደሚደርስ ይገመታል። የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ የኦርቶዶክሳውያን ቊጥር 42–45%፣ የወንጌላውያን አማኞች ቊጥር 18–21%፣ የካቶሊኮች ቊጥር 1% ይሆናል። ይህን ስሌት ያመጣሁት ክርስቲያኖች ሰላምና ዕርቅ እንዲመጣ በሚደረገው ትግል ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ቢያደርጉ ሊያበረክቱ የሚችሉትን ድርሻ ለመጠቆም ነው።

 

በቅርቡ ከሰብእና ውጭ በሆነ መለኩ በአይሲስ አርመናዊ ድርጊት ሕይወታቸውን ያጡት ወጣቶች እምነታችንን አንቀይርም በማለት ስለ ክርስቶስ ተሰውተዋል። ምናልባት በቃለ እግዚአብሔር ላይ ያላቸው ዕውቀት ጠንካራ ላይሆን ይቸላል። ይሁን እንጂ ኑሮ ማሸነፍ ከከፈሉት ዋጋ ይልቅ ለእምነታችው የሰጡት ዋጋና የከፈሉት መሥዋዕትነት በልጧል። ክርስቶስን በመካድ ከሚገኘው ጊዜያዊ ተድላ ይልቅ፣ በአንዲት ነፍሳቸው ላይ መጨከናቸው በሁላችን ልብ ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ እንዲኖራቸው አድርጓል።

 

ይህ እውነት እንዳለ ሆኖ፣ የእነዚህን ወጣቶች ሕይወት ለብርቱ አደጋ ያጋለጠው ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው? በማለት ራሳችንን መጠየቅ አለብን። በጥቅሉ ሲታይ በሕይወታቸው ቈርጠው፣ በተገኘው መንገድ ከአገራቸው የሚፈልሱ (የሚወጡ) ወጣቶች፣ አብዛኛው ምክንያታቸው ድኽነትን ሽሽት ወይም የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ነው። አይሲስ በመስቀል ወዳጆች ሁሉ ላይ የሞት ዐዋጅ ባወጀበት የጭክና ጐዳና ላይ ወገኖቻችንን የጣላቸው ይኸው ምክንያት መሆኑን በቅን ልብ ልንጋፈጠው የሚገባ ተግዳሮት ነው። ድኽነትን ለመፋለምና የአገራችንን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል፣ ቊርጠኛ አቋም መውሰድ እንዳለብን ልንገነዘብ ይገባል። ኢትዮጵያ ከድኻ አገሮች አንዷ በመሆኗ፣ ድኽነትና ረሀብ በተነሣ ቊጥር በምሳሌነት የምትጠቀስበትን የታሪክ መልክ የመለወጥ አደራ በእኛ ላይ ወድቋል። አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ለምናየው ድኽነት ተጠያቂው ማን ነው? ከተጠያቂነት ለመሸሽ ካልተፈለገ በስተቀር ጨቋኝና አምባገነን አገዛዞች ለድኽነታችን ተጠያቂዎች ናቸው፤ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥሪቶቻችን ተጠያቂዎች ናቸው፤ የእርስ በእርስ ጦርነት (በቅርቡ ከኤርትራ ጋር የነበረንን ጦርነት ያስታውሷል) እንዲሁም ድርቅና ረሀብ ተጠያቂዎች ናቸው (እርግጥ ምንጫቸው ሰውም ተፈጥሮም ነው)። እነዚህ ሁሉ የኢትዮጵያ መጥፎ ገጽታዎች ናቸው – መለወጥም ይገባቸዋል።

 

ከእነዚህ በተጨማሪ መንግሥታዊና ከመንግሥት ዐቅም ጋር የማይተናነሱ፣ ድንበር ዘለል ኮርፖሬሽኖች (Transnational Corporations) የሚያራምዷቸው ድኻን አግላይና በዳይ የሆኑ ፍትሕ የጐደላቸው ዓለም አቀፋዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ርዕዮተ ዓለሞች፣ የችግራችንን ጫና አክብደውታል። ዓለም ከምንጊዜውም ይልቅ እንደ ተቀራረበ ለማንም ግልጽ ነው፤ ይህን ቅርርብ ለመግለጽ “መንደረተኛነት” (ልዑላዊነት) (globalization) የሚል ቃል ተቀምሯል። መላው ዓለም በተለይም ምዕራቡ ዓለም በመንደረተኛነት ሥሪት ተዋቅሯል።ኢትዮጵያ ከዚህ ሥሪት ሩቅ ትሁን አትሁን ራሱን የቻለ ጥያቄ ቢሆንም፣ በዚህ እጅግ እየተቀራረበ በመጣው ዓለም ኢፍትሐዊነት፣ አምባገነንነት፣ አግላይነት፣ ጒስቊልናና ድኽነት የዕለት ተዕለት ክሥተት መሆናቸው ሁላችንንም ከተኛንበት ሊያነቃን ይገባል። በጥቅሉ ሲታይ የዓለም ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ውቅር ከሁለት ተከፍሏል – የበለጸጉ አገሮችና ድኻ አገሮች በሚል። ድኾች ይበልጥ ድኻ እየሆኑ ባንጻሩም ብልጡጐች ይበልጥ ብልጡግ እየሆኑ መጥተዋል። ይህም ማኅበራዊ ውቅር በአገራቸን በግልጥ ይታያል። አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ መንደረተኛ ዜግነቱ ከዓለም ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትሩፋት ተጠቃሚ አልሆነም። ዓለም ይበልጥ እያነሰች ከዚህም የተነሣ ሕዝቦች ይበልጥ እየተዛመዱ ቢመጡም፣ በሚሊዮኖች የሚቈጠሩ ኢትዮጵያውያን ሕልም ገና እውን አልሆነም። ብዙዎች ገና ንጹሕ ውሃ፣ መብራት፣ የጤና ክብካቤና የትምህርት ዕድል አላገኙም። እናም የድኾች ጒዳይ የአገር አቀፋዊው ውይይት ዐቢይ ርእሰ ጒዳይ መሆን አለበት።

 

በዚህ መልእክት በመጠኑ እንደምንዳስሰው የአገራችን ክርስትና ሦስት ዐበይት ተግዳሮቶች መጋፈጥ ይኖርበታል። ከላይ እንዳየነው አንደኛውና አጣዳፊው ተግዳሮት አስከፊ ድኽነት ነው። ሁለተኛው ተግዳሮት በብሔር ብሔረሰቦች መካከል በመንገሥ ላይ ያለው ውጥረት ነው። ሦስተኛው ተግዳሮት በሃይማኖት ተቋሞች መካከል የደመነው(ያንዣበበው) ውጥረት ነው (ልብ በሉ፤ ውጥረት “ደምኗል” ወይም “አንዣቧል” ነው ያልሁት)። ይህም ደመና ቢያንስ የራሱ የሆነ ሦስት መልኮች አሉት። አንደኛው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና በወንጌላውያን አማኞች መካከል ያሉትን ታሪካዊ የአግላይነት ውጥረት ይበልጡን የሚያከሩ የእርስ በእርስ ውግዘቶች፤ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሚዛንና ብስለት ያጡ አስተምህሮቶች ናቸው። ሁለተኛው በእነዚሁ ሁለት ታላላቅ ቤተ እምነቶች ውስጥ ያለው ጐሳዊ፤ ብሔርተኛና ፖለቲካዊ ጽንፈኝነትን የተላበሰ የእርስ በእርስ መከፋፈል ነው። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ማለት ይህ አይደል? እስቲ በቅን ልቦና ፍረዱ! ሦስተኛውና የመጨረሻው በክርስትናና በእስልምና መካከል የቆየውን የመከባበርና የመቻቻል ባህል የሚያደፈርስ የጽንፈኛነት ደመና ነው። ማንኛውም ዜጋ “እውነት ነው፤ ያዋጣኛል” የሚለውን የራሱን እምነት ያለፍርሃትና ያለምንም ተጽዕኖ መከተል መቻል አለበት። ይህ መሠረታዊ የኀሊና ነጻነት እግዚአብሔራዊ ነው። ሕገ-መንግሥታዊና ሕዝባዊም ሊሆን ይገባዋል። ከምንጊዜውም በላይ ለዚህ በምንም መልኩ ሊሸረሸር ለማይገባው መብት እንደ አንድ ሕዝብ መቆም ይኖርብናል። ዩጐዝላቪያን፣ ሩዋንዳን፣ ኮንጐን (“የአፍሪካ ዓለም ጦርነት” በሚባል የሚታወቀው ሁለተኛው ጦርነት)፣ ሰሜናዊ አየርላንድንና ሌሎች በርካታ አገሮችን በደም ያጠበ ጐሳዊና ሃይማኖታዊ ጽንፈኝነት፣ የቅርብ ጊዜ ትዝታ መሆናቸውን ልብ ልንል ይገባል።

 

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ከ80 በላይ ቋንቋዎች በሚነገሩበት አገር፣ ዕውቀትን ብስለትንና መከባበርን መሠረት ያደረገ “መቻቻል” ዐይነተኛ መፍትሔ እንደ ሆነ ለመግለጽ እወዳለሁ። የዚህን “መቻቻል” ጤንነት መጠበቅ ልዩ አጽንዖት ሊሰጠው ይገባል። በመሠረቱ መቻቻል ለእኛ ለኢትዮጵያውያን አዲስ ነገር አይደለም። ሆኖም ይህንን ተቻችሎ የመኖር አንድነት፣ ሊያናጋ የሚችል ጐሳዊ፣ ሃይማኖታዊም ሆነ ርዕዮተ ዓለማዊ ጽንፈኝነት በር እንዳይከፈትለት ከምንጊዜውም በላይ ልንጠነቀቅ ይገባል። ጽንፈኝነት ደምኖ ከዘነበ፣ ሕዝብና አገር ይተራመሳል። ወደ ፊት መሄዳችን ተገትቶ ባለንበት መቆም ከዚያም ወደታች ማሽቆልቆል ይመጣል። የድኸነቱም ዑደት ይቀጥላል። በእኔ እምነት ብሔር ብሔረሰባዊ ልዩነቶቻችን እግዚአብሔር በፍጥረት መግቦቱ (providence) የሰጠን ውበት እንጂ፣ በፈጠጠ ወገንተኝነት፣ አግላይነትና አድሎአዊነት ሌሎችን እንደ ሁለተኛ ዜጋ የምናይበት ማንነት አይደለም። ልዩነት አይጉላ ሲባል ግን፣ አንድ ዐይነትንት ይስፈን ማለት አይደለም። ይልቁንም ልዩ ልዩ መሆናችን ከእግዚአብሔር የተቀበልነው ውበት መሆኑን በመገንዘብ፣ በመቻቻልና በመተሳሳብ ለጋራ ብልጽግና እንሰለፍ ለማለት ነው። ጽንፈኘነት ለአንድነት አይበጅም፤ ይልቁንም አንዱ ለሁሉም ሁሉም ለአንዱ አሳቢ መሆን አለበት።

 

በቅርቡ በሲና በረሓ፣ በደቡብ አፍሪካና ከሁለት ሳምንት በፊት ደግሞ በሊብያ አስከፊ ዐመፅ በኢትዮጵያ ዜጐች ላይ ተፈጽሟል። ጌታ ምሕረት እንዲያወርድ መጸለይ አለብን። የእግዚአብሔርን ፊት መፈለግ ይኖርብናል። የግልና ብሔራዊ ልብ ፍተሻና ንስሓ ያስፈልገናል። እየጸለይን “ምን ይበጃል?" “የሚሻለው ምንድን ነው?” “የትኛውን መንገድ ብንከተል ያዋጣል?” በማለት ከቅን ልብ ልንጠይቅ ይገባል፤ አገራዊ ምክክር ልንጀምርና ተግባራዊ እርምጃ ልንወስድ ያስፈልጋል። ክርስቲያናዊውን ተስፋ ተመርኩዘን በብሔራዊ (አገር አቀፋዊ) ውይይት ወስጥ የበኩላችንን ድርሻ ማበርከት ይኖርብናል። ይህም ድርሻ ብሔራዊ ዕርቅ፣ ሰላም፣ ፍትሕና ብልጽግና ይመጣ ዘንድ እንደ ክርስቲያን ዜጋ የሚጠበቅብንን ኃላፊነት በትጋት መወጣትን ይጨምራል። በዚሁ መሠረት ከላይ የተወሱት ሦስት ተግዳሮቶች ምላሽ እንዲያገኙና በክርስቲያናዊ ተልእኮ ላይ የተመሠረተ ውይይት እንዲጀመር ግድ የሚሉን አምስት ወሳኝ ጒዳዮች አሉ፤

 

ለድኾች የፍትሕ ጩኸት ግድ የሚለው ክርስቲያናዊ ተልእኮ ክርስቶስ የአገልግሎቱ መጀመሪያ ያደረገው ወንጌል ለድኾች (የነፍስንም፤ የሥጋንም) የምሥራች መሆኑን በማብሰር ነበር፤ “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድኾች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፥ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል” (ሉቃ 4፥17-19)። በአገራቸን በተለያዩ ግዛቶች ስላለው የልማት፣ የአቅም ግንባታና ድኽነትን የመፋለም እንቅስቃሴ እግዚአብሔርን ልናመሰግን ይገባል። በጭፍን ፖለቲካዊ አዘመሞት (poltical bias) ምንም ጥረት እንዳልተደረገ መሞገት ሚዛናዊነት ያሳጣናል። ይሁን እንጂ ሐቁን እንነጋገር ከተባለ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ድኻ ነው።[2] ድኽነት እንዲህ በሚሳለቅብን ሰዓት የተሻለ ኑሮ ለመፈለግ ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው በሚንከራተቱ ወገኖች ላይ ዐመፅ በትሩን አሳረፈ። ድኸነት ብርቱ ጠላት ነው። መቼም በጥቅሉ ሲታይ፣ የድኽነት መንሥኤም መፍትሔም ከአንድ መንግሥት አወቃቀርና ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ልብ ልንል ይገባል።

 

የሰው ሁሉ የእኩልነት መሠረት፣ ሰው ከፍጥረቱ/ከኑባሬው (ontologically) የአምላካዊው ምስል ተሸካሚ መሆኑ ነው። ይኽም የክርስትና ዘላለማዊ አውራ እውነት ነው። ከዚህ አንጻር፣ ድኽነት በእያንዳንዱ ሰው ላይ የታተመውን አምሳለ መለኮትነት (the image of God) አይደመስስም። ስለዚህ የሰው የክቡርነት ዋጋ በማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሥሪት ውስጥ ባለው ስፍራ መለካት የለበትም። የራሳችንንም ሆነ የአጋር ዜጐቻችንን ኑሮ ለማሻሻል ተግተን እንድንነሣ የሚያደርገን ይህ በአምሳለ መለኮትነት የተፈጠርንበት እውነታ ነው። እንደ ክርስቲያን ድኽነትን የምንፋለምበትም እሴት መመሥረት ያለበት በዚህ ዘመን በማይሽረው እውነት ላይ ሊሆን ይገባል። ሰውን ለድኽነት አሳልፎ የሚሰጥ አስከፊና በዳይ የሆነ ማንኛውም ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲ ከዚህ እውነት ጋር ይቃረናል። ሰው ሁሉ የምድርና የሰማይ የተፈጥሮ በረከት እኩል ተካፋይ መሆን አለበት። በአገራችን አብላጫ ቊጥር ያላቸው ክርስቲያኖች፣ በዚህ እውነት ላይ በመቆም ድኽነትን በጋራ ለመዋጋት ቢቆሙና እጅ ለእጅ ቢያያዙ ሊያመጡ የሚችሉትን ለውጥ እስቲ እናስብ!

 

ብሔር ማንነት (ልዩነት) ሀገራዊ አንድነት መካከል ጤናማ የሆነ ሚዛናዊነት የሚያመጣ አምላካዊ ተልእኮ በብሔር ብሔረሰቦች መካከል ሥር እየሰደደ የመጣው አግላይነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። እርስ በእርስ መገፋፋት (exclusion)፣ አለመተማመን፣ ጥላቻ፣ ቂም በቀል፣ ለራስ ወገን ብቻ አሳቢነት የዘመኑ ጣዖታት ሆነው በየቦታው ብቅ እያሉ ነው። ጐሳዊ ጽንፈኛነትና ሌላውን ወገን አግላይነት ፈጽሞውኑ እግዚአብሔራዊ አይደሉም። ይልቁንም በሰው ማንነት ላይ የታተመውን አምሳለ መለኮትነት የሚጋፋ ናችው። የብሔር ማንነት ወይም ክልላዊ ልዩነት ሲከር የአገርም ሆነ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ይናጋል። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን እንደ ክርስቶስ አካልነቷ ብሔርተኛነት ከጋረጠው አደጋ በላይ ከፍ ማለት አለባት። የብሔርተኛነት አንዱ አደጋ በማእከላዊነትና በክልላዊነት መካከል ያለውን ውጥረት “ለእኔ ወይም የእኔ ብቻ” በሚል ንፉግነት ማክረሩ ነው። ይህ ክረት ከተበጠሰ ትልቅ አደጋ እንዳለው መርሳት የለብንም። ልብ እንበል፤ አንድ እንሁን ማለት አንድ ዐይነት እንሁን ማለት አይደለም። ይልቁንም ጤናማ፣ ሚዛናዊና ተደጋጋፊ የሆነ ክልላዊና ብሔራዊ ትሥሥር ያስፈልገናል ለማለት ነው። ስንከፋፈል ኃይል አይኖረንም፤ ለጠላትም እንጋለጣለን። እጅ ለእጅ ስንያያዝ ግን ወደ ኋላ እየጐተተ ለሚቀብረን ችግር መፍትሔ መስጠት እንችላለን። ተከፋፍሎ ያደገ ሕዝብ እንደሌለ ታሪክ ምስክር ነው።

 

በተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ጐሳዊ እንዲሁም ሃይማኖታዊ ጽንፈቶች (polarities) ለምትታመሰው ዓለም ቤተ ክርስቲያን አስታራቂና ፈውስ እንድትሆን ተጠርታለች። በመስቀሉ ሥራ ለተገኘው አዲስ ማንነት በመኖር፣ ክርስቲያኖች ከእነዚህ ሁሉ ሰው ሠራሽ የክፍፍል ግድግዳዎች በላይ ከፍ ብለው መታየት አለባቸው። በዚህ ተወጋጋጅነትና ጽንፈኛነት በነገሠበት ዓለም፣ ልዩ የእግዚአብሔር ሕዝብ (the unique people of God) መሆን ምን ማለት እንደሆነ ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። በትውልድ ላይ የጽድቅ ተጽዕኖ ማምጣት የሚቻለው ልዩ የእግዚአብሔር ሕዝብ በሆንበት መጠን ያህል ብቻ ነው። በእርግጥ ልዩ የእግዚአብሔር ሕዝብ ከሆንን፣ የሚገዛን ዋናው መለያችን ደግሞ ከሕዝብ፣ ከነገድና ከቋንቋ በመስቀሉ ሥራ የተዋጀንበት ማንነት ከሆነ፣ እርስ በእርስም ሆነ ሌሎችን በብሔርተኛነት መነጽር ልንመለከት አንችልም። ቃሉ እንደሚለው፥ “የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፤ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ፤ በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ። ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፣ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም። ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ ሁሉም አዲስ ሆኖአል።" (2ቆሮ 5፥14-17)

 

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሕዝቡን አብላጫ ቊጥር መያዟ ትልቅ የእግዚአብሔር ቸርነት ነው። ይሁን እንጂ ብሔራዊ የሆነ ሁለንተናዊ ፈውስ በማምጣት አንጻር በብዙ መልኩ ወደ ኋላ ቀርታለቸ። እውነተኛ መታደስና መለወጥ እንግዲህ ከተግዳሮቶች በላይ ከፍ ብሎ መገኘት ነው፤ ማለትም ለብሔርተኛነት ሳይሆን ለእግዚአብሔር መንግሥት መገዛት ነው። ሰዎች የፈጠሯቸው ድንበሮች በሙሉ በመስቀሉ ለአንዴና ለዘላላም ተወግደዋል፤ የክርስቶስ ተከታይ የሆኑ ሁሉ አይሁዳዊ ወይም አሕዛብ፣ ባሪያ ወይም ጨዋ፣ ወንድ ወይም ሴት ከሚለው ልዩነት በላይ ከፍ ብለው እንዲታዩ ተጠርተዋል። የክርስቶስ ወገን የሆኑ ሁሉ አዲስ ማንነት ተቀብለዋል፤ ለአሮጌው ማንነት ሞተው ለእግዚአብሔር መንግሥት ኑሮ ተነሥተዋል። ከመስቀሉ ሥራ የተነሣ የዚህ ማኅበረሰብ መታወቂያውም ሆነ ውቅሩ ዘር፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ መደብ ወይም ፖለቲካዊ ርእዮተ ዓለም አይደለም። ይህን ማኅበረሰብ ከእነዚህ ሥሪቶች ሁሉ ልዩ (distinct) የሚያደርገው በክርስቶስ የተገኘው አዲሱ ማንነት ነው።

 

ሙስሊሙን ኅብረተሰብ በወንጌል የሚደርስ ተልእኮ ኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ብሔሮች፣ ሃይማኖቶችና ባህሎች ተከባብረው የሚኖሩባት አገር ናት። በመሆኑም ርእዮተ ዓለማዊም ሆነ ሃይማኖታዊ ጽንፈኛነት ስፍራ ሊኖረው አይገባም። ይልቁንም እንዲህ ዐይነቱን ዝመት ልንቋቋመው ይገባል። እንደሚመስለኝ ከሆነ ልንፋለማቸው የሚገቡ ሁለት ብርቱ ጽንፈታዊ አደጋዎች አሉ። አንደኛው ሙስሊም ኢትዮጵያውያንን አይሲስ በሚታይበት ዐይን መመልከት ነው። በታሪክ እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ውስጥ ክርስትናና እስልምና አንጻራዊ በሆነ ሰላም ተቻችለው ኖረዋል። ይህን መቻቻል መጠበቅ ይኖርብናል። ሁለተኛው አደጋ ጽንፈኝነት የሠለጠነበት፣ አስተምህሮና አካይስታዊነት (diabolical cruelty) የነገሠበት የአይሲሶች ተግባር በኢትዮጵያ ሙስሊሞች መካከል የሚበቅልበት ለም አፈር ካገኘ ነው። እነዚህ ሁለት አደጋዎች እንዳይከሰቱ ተግተን መጸለይ ይኖርብናል። የአይሲስ መንፈስ፣ እስላማዊ ሥነ-አፈታትና እኩይ ተግባር በኢትዮጵያ ውስጥ ፈጽሞውኑ ድርሻ ሊሰጣቸው አይገባም።

 

በዓለማችን ላይ በአሁኑ ወቅት ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ ግጭቶችን ዐውድ ግምት ውስጥ ያስገባ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በሃይማኖቶች መካከል በተለይም በክርስትናና እስልምና መካካል ያለውን የቆየ አንጻራዊ መቻቻል በመመርኮዝ ሊዳብር ስለሚገባው ጤናማ ግኑኝነት የሚዳስስ ጽሑፍ ወደ ፊት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለማቅረብ እሞክራለሁ። ለጊዜው ግን ሁለት ፍልስፍናዊም ሆነ አስተምህሮአዊ እውነት መሰል ተፋልሶዎች (fallacies) ጠቁሜ ማለፍ እፈልጋለሁ።

 

አንደኛው የክርስትናን መሠረታዊ እሴቶች (the core foundation of the Chrsitian faith) የሚያደበዝዝ ብዝኃተ-ሃይማኖተኛነት (religious pluralism) ነው። ይህም አመለካከት በሃይማኖቶቸ መካከል ያለውን ልዩነት አንጻራዊ በማድረግ ሁሉንም “የአንድ እውነት” የተለያዩ ገጽታዎች አድርጐ ይሟገታል። መቼም በሁለት ተጻራሪ መንገድ ላይ ያሉ “እውነቶች” ወደ አንድ መድረሻ አያደርሱም። ሁለቱም ሐሰት ሊሆኑ ይችላሉ፤ ሆኖም ሁለቱም በአንድ ጊዜ ትክክል ሊሆኑ አይችሉም። ነገሩን ከዚህ አመክንዮ አንጻር ስንመዝነው፣ በክርስትናና እስልምና መካከል ምንጊዜም የማይታረቁ አስተምህሮአዊ ልዩነቶች አሉ። ከእነዚህም መካከል መጽሐፍ ቅዱስና ቁርኣን፣ ነገረ ሥላሴ፣ ነገረ ክርስቶሰ፣ ኀጢአትና ድነት ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ስለዚህ ሁለቱን እምነቶች “የአንድ እውነት” ሁለት ገጽታዎች አድርጐ መመልከት ተኣማኒነት የጐደለው ድምዳሜ ነው። ደግሞም የከፋ ስሕተት ነው።

 

ሁለተኛውና በጣም አደገኛው በሁለቱም እምነቶች መካከል ያለውን ልዩነት በዐመፅ ኃይል (violence) አስወግዶ፣ ሰዎች በፈቃዳቸው ሳይሆን በግድ የአንዱ እምነት ተከታይ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። ይህ የአይሲስ መንፈስ ነው። እንዲህ ዐይነቱ ተግባር እግዚአብሔር ለሰው የሰጠውን መሠረታዊ የሕሊና ነጻነት ያፈርሳል። ይህ ለየትኛውም አገር በተለይም ለኢትዮጵያ አያዋጣም። ከዚህ ይልቅ የሚያዋጣው ጥበብና ማስተዋል እንዲሁም ከማንኛውም ፍርሃትና ተጽዕኖ ነጻ የሆነና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ሰላማዊና ሃይማኖታዊ ውይይት (intelligible dialogue) ነው። ደግሜ አበክሬ ላሳስብ፤ የኅሊናና የማሰብ ነጻነት፣ ሐሳብን የመግለጥና ያሹትን እምነት መከተል ወይም መለወጥ በምንም መልኩ ሊፋቅ የማይገባው (Inherent) ለሰዎች የተሰጠ አምላካዊ ነጻነት ነው። ይህን መሠረታዊ መብት ሕዝብም መንግሥትም ሊጠብቀው ይገባል።

 

የእኛ የክርስቲያኖች አደራና ኃላፊነት ምንድን ነው? በቅድሚያና ከሁሉም በላይ እግዚአብሔር ሰው ሁሉ እንዲድን ክርስቶስን ምትክ በሌለው መፍትሔነት የሰጠበትን የመጨረሻ ፍቅር በአክብሮት፣ በትጋትና በሕይወት ምስክርነት ማወጅ ነው። ይህ ልዩና ድንበር የለሹ አምላካዊ ፍቅር በሚሊዮኖች ለሚቈጠሩ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን እንዲደርስ መንገድ መሆን አለብን። የወንጌል ተሐድሶ እንዲመጣ፣ የብዙዎች መንፈሳዊ ዐይን እንዲከፈት መጸለይና መናፈቅ ይኖርብናል። ኢየሱስ ክርስቶስ የዘላለም ሕይወት የሚሰጥ የእግዚአብሔር ልጅ ነው። ብቸኛ፣ ወሳኝና አቻ የለሽ አዳኝ ነው፤ ወደ እውነተኛው አምላክ መድረሻው መንገዱ እርሱ ብቻ ነው፤ ሌላ መካከለኛና አማራጭ የለም። የክርስቲያኑ ማኅበረሰብ አዋጅ እውነተኛነት የሚፈተነው አማኞች ከአንዱ ቃል ይኸውም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሚገጥም ሕይወት በኖሩበት መጠን ያህል ነው።

 

ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥረዋልና እግዚአብሔርን የሚጠማ ልብ አላቸው። በመሆኑም ወንጌልን በመስበክ መትጋትና ፍለጋ የሌለው የማይመረመር የእግዚአብሔር ፍቅር ለሙስሊሞችም ይደርስ ዘንድ መሣሪያዎቹ ልንሆን ይገባል። ከሙስሊሙ ኅብረተሰብ ጋር ጐን ለጐን ለመሰለፍ የሚያስችሉና ለወንጌል በር የሚከፍቱ በርካታ የጋራ ድንበሮች አሉ። ለምሳሌ የሕይወት ክቡርነት (the sanctity of life)፣ ድኽነትን መዋጋት፣ የቤተሰብ እንዲሁም የጋብቻ እሴቶች ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው። እነዚህም የመተባበር የጋራ ድንበሮች በጥቅሉ ለኢትዮጵያ ሰላምና ብልጽግና በጋራ ለመሥራት የሚያስችሉ ዕድሎች ናቸው። እንዲያውም በመከባበር ላይ የተመሠረተ ውይይት እንዲያብብ መንገድ ይጠርጋሉ። ሙስሊሞችን በክርስቶስ የፍቅር ዐይን መመልከት ይኖርብናል። ክርስቶስ “መልካሙን ሥራችሁን ዐይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ።” (ማቴ 5፥16) እንዳለ በመስቀል የተገለጠውን እግዚአብሔርን ፍቅር በእኛ ውስጥ ማየት መቻል አለባቸው። ሕይወት የጐደለው ምስክርነት አቅም የሌለው ከንቱ ልፍለፋ ነው። “እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷል” ስንል፤ ይህንን “መውደድ” ያገኙት ይሆን? የሚለውን ጥያቄ ልናስብበት ይገባል። ከጌታ በአደራ የተቀበልነው የማስታረቅ፣ አገልግሎት እኛን ከከፋፈለን ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ከእግዚአብሔር ጋር በክርስቶስ ታረቁ ብለን መመስከር እንዴት እንችላለን?

 

ከእግዚአብሔር ለተቀበልነው ተልእኮ ተገቢ የሆነ ትጋት። እንደ ጐርጐሮሳውያኑ የዘመን አቈጣጠር በ 1960ዎቹ የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች ቁጥር ከአገሪቱ ሕዝብ ብዛት 1% ብቻ ነበር። የምሥራቹ ወንጌል በምድራችንና በዳያስፖራው መካከል ተስፋፍቶ፥ በአሁኑ ጊዜ የወንጌላውያን አማኞች ቊጥር 18-20 % ደርሷል። ክብሩ የሥራው ባለቤት ለሆነው ለእግዚአብሔር ይሁን። የወቅቱ የኢትዮጵያ ክርስትና ከጅማሬው ጋራ ሲነጻጸር ትልቅ የመልክ ልዩነት ይታይበታል። ይህም አንድ ትውልድ ወንጌልን የተቀበለበት፥ የተረዳበትና የኖረበት ዐውድ ከሌላው ትውልድ የተለየ የሚያደርገው የራሱ ባሕርይ እንዳለው ያሳየናል። ልክ እንዲሁ ያለንበት ዘመን ክርስትናም የራሱ የሆነ ዐውዳዊ ቃና (accent) አለው። ትውልዱ ይቀያየር እንጂ ከሰዎች ወይም በሰው ያልሆነው የወንጌል መልእክት ምንጊዜም አንድ ነው። ወንጌል የሚተላለፍበትም ጉልበት እንደየትውልዱ ትጋት ይለያያል።

 

ከደርግ ውድቀት በኋላ ያለው ዘመን፥ የወንጌል እንቅስቃሴ በአፋጣኝ ያደገበት፥ ክህደት በታወጀባቸው አደባባዮች ወንጌል የተሰበከበት፥ ዝማሬዎች የበዙበትና ዲያስፖራው በሚኖርባቸው አገሮች በርካታ አብያተ ክርስቲያናት የተተከሉበት ዘመን ነው። ስለዚህም የሥራው ባለቤት ለሆነው እግዚአብሔር በድጋሚ ክብር ይሁን።

 

ይህ እንዳለ ሆኖ፥ ወንጌል የሚተላለፍበት ጉልበት እንዲደክምና መከራ ያልፈታው የአማኞች ኅብረት ልል እየሆነ እንዲመጣ ያስገደዱ ቤተ ክርስቲያን ወለድ ተግዳሮቶች በዝተዋል። በአሁኑ ውቅት በአገራችንም ሆነ በክርስቲያኑ ማኅበረሰብ መካከል የሚታዩት መንፈሳዊ፣ ምግባራዊና ግብረ ገባዊ ውድቀቶች፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ተልእኮና መልእክት ተኣማኒነት ጥያቄ ውስጥ እየከተቱ ይገኛሉ። ቤተ ክርስቲያን “ጨውነቷን” የሚያሳጣት ትንቅንቅ ላይ ገብታለች። ብስለት ማጣትና ጠባብ ራእይ የወልዷቸው የአመራር ቀውሶች መበርከታቸው ችግሩን አባብሶታል። መጽሐፍ ቅዱሳዊና አስተምህሮአዊ ትክክለኝታቸው ያልተመዘነ ድንበር ዘለል መንፈሳዊ ልምምዶች ለዚህ ችግር አስተዋጽዖ አበርክተዋል።

 

የቀድሞዋ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ምንም እንኳን የፍትሕ ሲቃዋ ባይደመጥም፣ የማምለክ መብቷን ለማስከበር ለመንግሥት አቤቱታ ታሰማ ነበር። በአንጻሩ አሁን የመንግሥትን ዳኝነት የጠየቁ የመብት ሙግቶች ለእርስ በርስ መከፋፈል ዳርገውናል፤ ጦርነቱ ከጠላት ጋር መሆኑን ረስተን እርስ በርስ ተወጋግደናል። ድኅረ ዘመናዊነት ያፈራቸው በጐ ባህል አፍራሽ ልቅነቶችና ግብረገባዊ አንጻራዊነት (moral relativism) የወጣቶችን ልብ ሲሰርቁ፣ ቤተ ክርስቲያን “ተዉ! አያዋጣም! ከሁሉም በላይ ይህ እግዚአብሔራዊ አይደለም!” እንዳትል የርስዋም የሞራል መሠረቶች ተናግተዋል። በአገር ቤትና በዳያስፖራው መካከል ተፎካካሪ የሆኑ አብያተ ክርስቲያናትና አግልግሎቶች በዝተዋል። ትልልቆቹ ለቁጥር፥ ትንንሾቹ ደግሞ ተኣማኒነት ለማግኘት ይታገላሉ። ቁጥር እንጂ ጥራት፣ ቅርጽ እንጂ ይዘት ብዙ ትኩረት አልተሰጣቸውም። ዓለምንና ቤተ ክርስቲያንን የሚለዩ የድንበር እሴቶች ደብዛቸው እየጠፋ ነው። ልቡ በአንደበቱ ላይ የሚፈርድበትና ምግባር አልቦ የሆነ የስም ወንጌላዊነትን (evangelical nominalism) ባሕርዩ ያደረገ ትውልድ እያፈራን ይሆን?

 

ተሐድሶ ያስፈልገናል። በግል ሕይወት ከሥጋዊነት ወደ መንፈሳዊነት፤ ከወጋዊ ወይም ከልማዳዊ ሃይማኖተኛነት ወደ እውነተኛ ምስክርነት፤ ቃል ብቻ ከሆነ ባዶነት ወደ ክርስቶሳዊ ሥነ ምግባራዊነት፤ ከጣዕም የለሽነት ወደ ጨውነት ልንታደስ ይገባል። በቤተ ክርስቲያን ደረጃ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ባይተዋር ከሆነበት ማኅበራዊነት ወደ ክርስቶሳዊ አካልነት መታደስ አለብን። በአገልግሎት አንጻር ችሎታ በስጦታ፣ ፉክክር በመቀባበል፤ ብልጠት በፈሪሃ እግዚአብሔ፤ ስሜታዊነት በብስለት ሊተኩ ይገባቸዋል። ቤተ ክርስቲያንን ክርስቶሳዊ አካልነትዋን ቸል አስደርጐ፣ እንደ ማንኛውም ተራ ማኅበራዊ ስብስብ እንድትሆን ከሚያስገድዳት መንገድ የሚመልሳት ተሐድሶ ያስፈልጋታል። ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ የወንጌልን ሀብት ለትውልድ የማውረሻው መንገዱ ይኸው ነውና።

 

ስለዚህ እኛም እንደ ዳዊት፡- “የሠራዊት አምላክ አቤቱ መልሰን፤ ፊትህንም አብራ፤ እኛም እንድናለን” (መዝ 80፥19) ብለን ልንጮኽ ይገባል። በርግጥም እንደ ዕንባቆም፡- “እግዚአብሔር ሆይ ዝናህን ሰምቻለሁ ... በኛም ዘመን አድሳቸው፤ በኛም ዘመን እንዲታወቁ አድርግ፡፡” (ዕን 3፥2) በማለት የእግዚአብሔርን የማዳን ኃይል የሚዘክረውን ጸሎት፥ የአገልግሎታችን ሁለንተናዊ የውስጥ ግፊት ልናደርገው ይገባል። የግል ተሐድሶ የቤተሰብ ተሐድሶ ያመጣል፤ የቤተሰብ ተሐድሶ የቤተ ክርስቲያን ተሐድሶ ያመጣል፤ የቤተ ክርስቲያን ተሐድሶ የአገር ተሐድሶ ያመጣል። የጽድቅ ተጽእኖ የማምጫው መንገዱ ይኸው ነው። ክርስቶስ “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም” (ማቴ 5፥13) በማለት ሲናገር የተጠራንበትን ዐላማ እየገለጸ ነው። ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር መንግሥት ልዩ ምልክት እንድትሆን ተጠርታለች። ጨው ብዙ ሥራ አለው። ጣዕም ይሰጣል፤ ምግብ እንዳይበላሽ ያደርጋል፤ ቁስል ያለዝባል፤ ለሌሎችም ብዙ ተግባሮች ይውላል። ልክ እንዲሁ ቤተ ክርስቲያንም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ዓለምን እየወቀሰች የጽድቅ መንገድ አመልካች በመሆን መፍትሔ መሆን የምትችለው ከሙታን የተነሣው ጌታ ቤተ ክርስቲያን ንብረት ስትሆን ነው። ዓለም በታመመበት በሽታ እርሷም ከተያዘች እንዴት ፈውስ ልታመጣ ትችላለች? በእርግጥ አማኝ የሆነ የክርስቶስ እውነተኛ ደቀ መዝሙር፣ እንደ ቀደመው ሕይወቱ ሊኖር ወይም ዓለምን በቀደመው ዐይኑ ሊመለከታት አይችልም። የዘመነኛዋ ቤተ ክርስቲያን ተግዳሮት “መናገር” ሳይሆን “መኖር” ነው፤ ማለትም “ቃል” ሳይሆን “ተግባር” ነው። ለእግዚአብሔር ክብር የሚያመጣውና ዓለምም ከቶ ልትቋቋም የማትችለው በተግባር የሚገለጥ ፍሬአማ ሕይወት ነው።

 

ለእግዚአብሔር ክብር የሚያመጣ የአመራር ተሐድሶ። የአንድ ክርስቲያን ትውልድ መንፈሳዊ ልምምድ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለው ተደማጭነት፣ እንዲሁም የጽድቅ ተጋቦት በመሪዎቹ መንፈሳዊ ብስለት፥ የውስጥ ግለት (passion) እና የራእይ ልቀት ይወሰናል። ተመሪ የሚመስለው መሪውን ነው! ለአመራር ቀውስ እግዚአብሔር በመፍትሔነት ለሕዝቡ በስጦታነት (በሰው ባልሆነ ማንኛውም መመዘኛ!) የሚሰጠው እንደ ልቡና እንደ አሳቡ የሚያገለግሉ መሪዎችን ነው። በኀጢአት ቃል ኪዳናቸውን በማፍረሳቸው ምክንያት ወደ ባቢሎን በግዞት ከመወሰዳቸው በፊት እግዚአብሔር ለሕዝቡ አስቀድሞ የገባላቸው የተስፋ ቃል፣ “እንደ ልቤም (የሆኑ) በግ ጠባቂዎችን (እረኞች) እሰጣችኋለሁ፥ በዕውቀትና በማስተዋልም ይጠብቁአችኋል” የሚል ነው፤ (ኤር 3፡15)። ስለዚህ መሪ ስጦታ ነው፤ የአመራሩ ስኬት ደግሞ እንደ መሪው በእግዚአብሔር ፊት የሚኖር የጽድቅ ኑሮና ፍጹም መሰጠት ይወሰናል። እግዚአብሔር የሀልዎቱ መተላለፊያ ያደረጋቸው ባሮች የትውልድ ስጦታ ናችው። እንደ እነዚህ ያሉ መሪዎች፣ የክርስቶስ ክብርና የእግዚአብሔር መንግሥት መስፋት እንጂ የራሳቸው የግል አጀንዳ የላቸውም። የሰውን ጐሽታ በመፈለግ ሳይሆን፣ በቃሉ ለተገለጠው እውነት ብቻ ይኖራሉ። የመቆማቸውም ምክንያት “እኔ ብቁ አይደለሁም” ባሉበት ሁኔታ ውስጥ የፈሰሰላቸው የእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ መሆኑን የተረዱ ናችው።

 

የክርስቶስ ሕይወቱና ሥራው የነካውና የቀየረው መሪ፣ ለትውልድ በረከት ነው። በዓለም አቀፍ ሉተራን ፌዴሬሽን ጣልቃ ገብነት ከእስር ቤት ተፈተው ስደቱ ጋብ እስኪል ከሀገር እንዲወጡ መንገድ ቢመቻችላችውም፣ ከመንጋው ጋር መከራን ለመቀበል በመወሰናቸው በደርግ ጭከና ሕይወታቸው በለጋነት የተቀጨው የመካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን መሪ የነበሩት የቄስ ጉዲና ቱምሳ የመጨረሻ ቃል በኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ክህነታዊ አደባባዮች እንደ ገና ሊስተገባ ያስፈልገዋል። ይኽም፣ “በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ።" (2ቆሮ 5፥15) የሚለውን ከጠቀሱ በኋላ “በፍጹም አላመልጥም፤ አላደርገውም!” ያሉት የሰማዕትነት ቃል ነው። ለወንጌል እውነትና ተልእኮ መኖርና ትውልድን ማገልገል ማለት ይኸው ነው። የክርስቶስ ሕይወቱና ሥራው የነካውና የቀየረው ትውልድ ብቻ ነው እውነተኛ ምስክር መሆን የሚችለው። የመልእክታችን ጉልበት የሚወሰነው በተነካንበት አምላካዊ ጣት የጉልበት መጠን ነው። ያልተነካና ያልተለወጠ ምስክር ሊሆን አይችልምና! ዳዊት በገዛ ዘመኑ የእግዚአብሔርን አሳብ እንዳገለገለ፣ የመንግሥቱን ፈቃድ በሙሉ ልብ በማገልገል ያረፈ፣ የትውልድን ጥያቄ በመመለስ ያሳረፈ ትውልድ ያድርገን።

 

ኢትዮጵያ ከምንም በላይ ብዙ የተለወጡ፣ አሁን ላለውም ሆነ ለወደፊት ትውልድ የሚያስቡ ባለራእይ አገልጋይ መሪዎች ያስፈልጓታል። ለራሳቸው ግለኛ አጀንዳ የማይኖሩ፤ ለገዛ ወገኖቻቸው ጥቅምን ብቻ ሳይሆን ለመላው ሕዝብ፤ በተለይም ለድኾች መብትና ጥቅም፣ እንዲሁም ለሚልቀው አገራዊና ሁለንተናዊ ፈውስ የሚጋድሉ መሪዎች ያስፈልጓታል። ጽድቅ፣ ፍትሕና ምሕረት የወንበራቸው መሠረት የሆነ፤ አገር መሪዎች፣ ሕግ አውጭና አስከባሪዎች፣ ዳኞች፣ ኃይላትና ሥልጣናት፣ ወታደሮች፣ አሠሪዎች፣ ባለሙያዎች፣ ኢንቨስተሮች (ባለ ሀብቶች)፣ ነጋዴዎች ወ.ዘ.ተ. ያስፈልጓታል። ከእነርሱ የተሻሉ መሪዎች ማፍራት ረሀባቸውና ትጋታቸው የሆነ፤ በተሰጣቸው ዘመን ትውልዱንና እግዚአብሔርን ካገለገሉ በኋላ፣ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለአደራ ለሚበቁ መሪዎች በሰላምና በክብር ለማስረከብ አፍቃሬ ሥልጣን ወይም ወገኝተኝነት እንቅፋት የማይሆንባቸው ያስፈልጉናል። እንደነዚህ ያሉ ባለራእይ መሪዎች በአገርም በቤተ ክርስቲያንም ደረጃ ማፍራት ትልቅ ሀብት ነው።

 

መቼም ቢሆን ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው፣ በጽድቅ፣ በፍትሕና ምሕረት ላይ የተመሠረተ አመራር ለብሔራዊ አንድነትም ሆነ ለጋራ ብልጽግና ወሳኝ መሆኑን ማሳስብ ያስፈልጋል። በዚህ አንጻር የአገር መሪዎች የሥልጣን ሁሉ ባለቤት የሆነውን እግዚአብሔርን በመፍራት በፍትሕ፣ በጥበብና በማስተዋል እንዲያስተዳድሩ ቤተ ክርስቲያን መማለድ ይኖርባታል። ቅዱስ ቃሉ እንደሚያስተምረው፣ መንግሥት “ለመልካም ነገር የህዝብ አገልጋይ” ነው (ሮሜ 13፥4 - God's servant for the common good of all):: ስለዚህ የየትኛውም ዐይነት መንግሥት ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የአስተዳደር መርሆና ውቅር ተኣማኒነት የሚለካው በዚህ እውነት ነው። የአገራችንም ፌደራላዊና ክልላዊ መስተዳድሮችም የዚህ መሠረታዊ እሴት አዳሪዎች እንዲሆኑ ቤተ ክርስቲያን መማለድ አለባት። በተለይም ለድኾችና ከዕውቀት ማነስ የተነሣ ለራሳቸው መብት መቆም ለማይቸሉ፣ ከሀገሪቱና ከዓለም እድገትና ብልጽግና ክልል መስመር ውጭ ያሉ ዜጐች ልዩ ትኩርት እንዲያገኙ በተግባርና በጸሎት መትጋት ይኖርባታል። ትርጒም ያለው ውይይትም ሆነ የጋራ ዕድገት የሚመጣው በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አሠራር ሲኖር ነው። ይህም ማለት ሚዛኑን በጠበቀ፣ ፌደራላዊና ክልላዊ ብልጽግናን ባማከለ ራእይ መመራት መቻል ማለት ነው።

 

ወደ መንፈሳዊ ተቋማት ስንመጣ አብያተ ክርስቲያናት ተከፋፍለው መመልከት በእጅጉ ያሳዝናል፤ ያሳፍራልም። በአማኙ ማኅበረሰብ መካከል የሚነሱ የአመራር ግጭቶች፣ የብሔርተኝነት ልብስ ሲለብሱ የቤተ ክርስቲያን ውበት ይሸፈናል። የክርስቲያኖች ነገረ መለኮታዊ አቋምም ሆነ ርእዮት አመለካከት፣ የራስ ብሔር ብቻ ወዳድ በሆነ እይታ መገራት ሲጀምር መከፋፈል ይከሰታል። “በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አብያተክርስቲያናት መካከል ክፍፍል ለምን ነገሠ?” ቢባል ከመልሶቹ አንዱና ምናልባትም ትልቁ ብሔርተኛነት ነው። እነዚህ ሁሉ የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት ካባ የለበሰ ሌላ ዐቅም-አልባ ተቋም ያደርጓታል።

 

በምድር ላይ ቤተ ክርስቲያን ዮሐንስ በራእይ ያየው የሰማዩ ሕዝብ ነጸብራቅ ናት፥ “ከዚህ በኋላ አየሁ፥ እነሆም፥ አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፤ በታላቅም ድምፅ እየጮሁ። በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው አሉ።” (ራእ 7፥8-10)። የእግዚአብሔር ሕዝብ ውብቱ ልዩነቱ ነው። የአንድነቱና የሚሲዮናዊ ተልእኮው መሠረቱም ይኸው ልዩነት ነው። በእርግጥ እግዚአብሔር የራሱ ሕዝብ በሆነበት መጠን ያህል ብቻ ነው ለሌላው ሕዝብ የሰላም አማራጭ የሚሆነው። ጴጥሮስ እንዳለው ስንሆን ማለት ነው፤ "እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጐነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ። (1ጴጥ 2፥9)

 

ነገሬን ልቋጭ። ብሔራዊ ጉብኝት እንዲመጣ መጸለይና የበኩላችንን ድርሻ መወጣት አለብን። ጸሎት የቤተ ክርስቲያን ጉልበት ነው። የጐደፈው መንፈሳዊነታችን እንዲነጻ፣ የተከፋፈለው አንድነታችን እንዲፈወስና ድኽነት ካመጣብን ጉስቁልና እንድንወጣ እንጸልይ። የሥራ ትጋትን፣ ሥነ ምግባራዊነትን፣ ለሌሎች አሳቢነትንና ለጋሽነትን በተመለከተ ሥር ነቀል የሆነ የአሰተሳሰብ ለውጥ እዲመጣ መጸለይ ይኖርብናል። በኢትዮጵያ ውስጥ ብሔራዊ (አገራዊ) ሁለንተናዊ ፈውስ፣ ሰላም፣ ፍትሕና ብልጽግና እንዲሰፍን፣ ከሁሉም በላይ የእግዚአብሔር ጽድቅ የሚጠይቀውን ሕይወት መኖር ይገባናል። እግዚአብሔር የሚፈልገው ዐይነት ጾምና ጸሎት ያስፈልገናል። ከየትኛውም እኩይ ማኅበራዊ፣ ባህላዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መዋቅር ጀርባ የክፋት ኃይሎች አሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለክፋት ኃይሎች የተሰጠው መጠሪያ “ክፉ፣ ነፍሰ ገዳይ፣ የሐሰት አባት፣ መንፈሳዊ ዐይን አሳዋሪ፣ የክርስቶስ ጠላት” የሚል ሲሆን ሰይጣን በሥራ ላይ መሆኑን ምንጊዜም ልንዘነጋ አይገባም። መጋደላችን ቅዱስ ቃሉ እንደሚል፤ “ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፤ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ” (ኤፌ 6፥12)።

 

እስከዚያው ግን በሊብያ፣ በየመንና በሌሎችም የዓረብ አገሮች የታገቱ ኢትዮጵያውያን ዜጐችን ነጻ የሚያወጣ ቡድን ከሃይማኖት መሪዎች፣ ከሰብአዊ መብት ድርጅቶችና ከመንግሥት አካላት በአፋጣኝ መመሥረት ይኖርበታል። ጥረቱም ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች፥ ለምሳሌ ከUNHCR እና ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል ድርጅቶች ጋር መቀናጀት ይኖርበታል። ከዚህም በተጨማሪ በፈቃዳቸው ወደ አገራቸው ለሚመለሱና ወደ ሕዝባቸው ለሚቀላቀሉ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ የሚሰጥ ተቋም መፍጠር ይኖርብናል።

 

ድኽነት ከሚያስከትላቸው ጉዳቶች አንደኛው አንከራታችነት ነው። ይሁን እንጂ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ አገር ለቆ ስደተኛ መሆን ሊያመጣ የሚችለውንም ክስረትና የሕይወት ጥፋት ልብ ማለት ያስፈልጋል። መገናኛ ብዙሃን ያልዘገቧቸው ብዙ እልቂቶች በወገኖቻችን ላይ መድረሳቸው ይታወቃል። የተደፈሩና የተጠለፉ ወጣት እኅቶቻችንን፣ ውሃና አውሬ የበላችውን፣ በሸታ የጨረሳቸውን፣ ለህክምና ኮንትሮባንድ ንግድ የውስጥ አካላቸው ተለቅሞ ሬሳቸው በሲና ምድረ በዳ የተጣለውን ወገኖቻችንን ቁጥር አምላክ ብቻ ነው የሚያውቀው። ከሞት ያልተናነሰ ምርጫ የሌለው አጣብቂኝ ውስጥ ካልተገባ በስተቀር፣ አደገኛ ውርርድ (risk) በራስ ነፍስ ላይ አውጆ በየትኛውም መንገድ አቆራርጦ ወደ ባእድ ምድር መሄድ የሚያዋጣ ነው ወይ? ብሎ ማጤን ያስፈልጋል። ከእንዲህ ዐይነቱ ጭፍን በአንዲት ነፍስ ላይ ከሚደረግ ውርርድ (risk) በሕይወት ሰንብቶ ኑሮን ለማሸነፍ መታገል ይሻላል እላለሁ - ከብዙ ትሕትና ጋር። ቢያንስ እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ ቀንን መጠበቅ ይሻላል። ቃሉም በመደጋገም፤ “እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ በርታ ልብህም ይጽና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ።” (መዝ 27፥14) ይላልና። ባለጸጐች ኢትዮጵያውያን እስቲ ይህን አደገኛ ውርርድ (risk) ለመቀነስና ወደ አገር መመለስ ለሚፈልጉ ተስፋ የሚሰጥ ምክንያት ለመሆን መላ ፍጠሩ!

እንደ ሕዝበ ክርስቲያን ተስፋ የምናደርገው ፍቅሩ ልዩ የሆነውን መልካሙን እረኛ ልዑል እግዚአብሔርን ነው፤ እርሱም፥ “እኔ ራሴ በጎቼን እሻለሁ፤ እፈልግማለሁ” በማለት ተናግሯል (ሕዝ 34፥11)። በእርግጥ ለአገራችን እውነተኛ ሰላምና ብልጽግና የሚመጣው ከራሱ ከእግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር በበረከቱ ይጐበኘን ዘንድ የሚጸልይ፣ በጽድቅ፣ በፍትሕና በትጋት የሚኖር ሕዝብ መሆን አለብን። በአለፉት 1700 ዓመታት ከውስጥና ከውጭ የተነሡ ተግዳሮቶችን በጽናት የተቋቋመ ሕዝብ በመሆናችን በጸሎት በአንድነት እንቁም። እርስ በእርስ እየተሳሰብን እንዲህ በማለት እንዘምር፤ “ልቅሶ ማታ ይሆናል፤ ደስታ ጠዋት ይመጣል” (መዝ 30፥5)። አይሲስ (ISIS) ካደረሰብን ሽብር በላይ ከፍ እንበል። ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ ነው፤ መንግሥቱም ሁሉን ትገዛለች። የገሃነም ደጆች ቤተ ክርስቲያንን አይቋቋሙም፤ ምክንያቱም ከሙታን የተነሣው ጌታ በአብ ቀኝ ተቀምጧል፤ እርሱም ሁልጊዜ እስከ ዓለም መጨረሻ ከእኛ ጋር ነው (ማቴ 28፥20)። ጨለማ ከቶ የማይቋቋመው የክርስቶስ ብርሃን ለሕዝቦችና ለዓለም ሁሉ ይብራ። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከዚህ ሐዘን አገግመን ዳግመኛ ለክርስቶስ ልዕልና፣ ለመንግሥቱም መስፈንና መስፋት ትጋታችንን እንድንቀጥል በሚያደርጉት ጥረት ሁሉ ውስጥ ጸጋ፣ ጥበብና ሞገስ እንዲበዛላቸው በጸሎታችን እናስባቸው።    

 

መልካሙ እረኛችን እግዚአብሔር ደማቸው በግፍ የፈሰሰባቸውን ቤተሰቦች ያጽናና፤ አገራችንንም ይፈውስ! አሜን።

 

ከልብ በሆነ ጸሎት፣ ፍቅርና አክብሮት

[1] http://christianserviceworker.org/a-pastoral-letter-from-girma-bekele/ በትርጒም የረዳኝን ምኒልክ አስፋውን ከልብ አመሰግናለሁ።    
[2] እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቈጣጠር በጥር 2015 ዓ. ም. በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ አማካይነት የታተመ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው 87.3% የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ “ድኻ” በሚባለው መደብ ተፈርጇል። http://www.dataforall.org/dashboard/ophi/index.php/mpi/country_briefings ድኸነትን ለመቀነስ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለችውን ጥረት የሚያመሰግነው ዓለም አቀፍ ባንክ “ድሆች የባሰ ድሆች ሆነዋል” ሲል፤ (http://www.worldbank.org/en/news/press-release/2015/01/20/poverty-ethiopia-down-33-percent) በሰው እድገት (HDI) ከ187 አገሮች ኢትዮጵያን 173ኛ ላይ ያስቀመጣት የተባበሩት መንግሥታትም በተመሳሳይ መልኩ የድኽነት ቀረፋውን ጥረትና ውጤት ቢያደንቅም፣ ቀንበሩ አስጨናቂ መሆኑ ገልጧል። http://hdr.undp.org/sites/all/themes/hdr_theme/country-notes/ETH.pdf። የእነዚህ ዘገባዎች ትንታኔ ከሙያዬ ውጭ ነው። ሀሳቤ ድኽነት ዋናው ተጋድሮት መሆኑንና በዚህ ድኽነትን የመፋለም ተጋድሎ ውስጥ የቤተ ክርስቲያንን ልውጠታዊ (transformative) ድርሻ ለማሳሰብ ነው።  

 

Read 8364 times Last modified on Tuesday, 30 June 2015 11:23
Dr. Girma Bekele

Dr. Bekele is a Missions and Leadership Consultant, and Adjunct Professor of Global Missions and Development Studies at Wycliffe College, University of Toronto.

He is a contributing author to the book  “Evangelicals Around the World: A Global Handbook for the 21st Century”. His chapter deals with East Africa and Sub-Saharan regions. Click here to view the Thomas Nelson page about the book.

Dr. Bekele is married to Genet (for 21 years) and they have two teens (Yonathan and Mahilet), and a five year old (Joel) who keeps him on his toes!

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 102 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.