You are here: HomeOpinionsይፈለጋል! የቁጣ ችሎታ ያለው

ይፈለጋል! የቁጣ ችሎታ ያለው

Written by  Tuesday, 12 May 2015 00:00

የእግዚአብሔር ሰው ማለት ድምፁን አለዝቦ፣ ዐይኑን አቅለስልሶ፣ ፊቱን አለስልሶ፣ በቀኝም በግራም ሰላምታ እየሰጠ፣ ለአላፊ ለአግዳሚው ፈገግታ እየረጨ፣ የሰዎች ክፋት ሰማይ ሲደርስ “የባሰ አታምጣ” እያለ፣ ቤተ ክርስቲያን ቆሽሻ፣ መቀመጫ ሲጠፋ መሐረቡን በአቧራው ላይ ጥሎ “ተቀመጡ” እያለ “ወተት ነጭ ነው? ጥቁር?” ተባብለው ሲጣሉ “ሁለታችሁም ልክ ናችሁ” እያለ፣ በመቅደሱ ውስጥ ውሾች ቢተኙበት “ሳስል ከእንቅልፋቸው እንዳላባንናቸው” ብሎ አፉን በመሃረብ እየለጎመ፣ ሸካራ ቃላትን ለምሳሌ፡- “ዘለፋ፣ ኀጢአት፣ ቅጣት” የተባሉትን በተለሳለሱ ቃላት ለምሳሌ “ምክክር፣ የምርጫ ነጻነት፣ ተጽእኖ” በሚሉ እየለዋወጠ የሚኖር እሳት አልባ ፍጡር ነው፡፡ እውነት ወይስ ሐሰት? ሐሰት፡፡

 

አንድ የእግዚአብሔር ሰው ነበረ ሙሴ የሚባል፡፡ ልዑል አምላክ የሰጠውን ጽላቶች በእጁ ጥሎ ሰበራቸው፡፡ ሕዝቡ በስንት መዋጮ የሠራውን የወርቅ ጥጃ አቃጥሎ ፈጨው፤ ትቢያውን በውሃ አጠጣቸው፡፡ ወደ ወንድሙ ወደ አሮን ዞር ብሎ “ይህ ሕዝብ ምን አደረገህ እንዲህ ዐይነት ፍዳ ውስጥ የምትከተው? አለው፡፡ ወደ ሕዝቡ ዞሮ “ተነሥታችሁ ወንድሞቻችሁን ግደሉ” አለ፤ ሦስት ሺህ ሰው ያን ቀን ሞተ፡፡ ከሁሉ የሚገርመው “በረከትን እንዲያወርድላችሁ በልጃችሁና በወንድማችሁ ላይ እጃችሁን ለእግዚአብሔር ቀድሱ” ያለው ነው፡፡ “ግደሉና እጃችሁን ንጹህ አድርጉ” ማለቱ ነው፤ እንዴት ያለ ታላቅ ቁጣ ነው! እንዴት ያለ ታላቅ መንፈሳዊ ቁጣ ነው!

 

ሙሴ አንድ ምሳሌ ብቻ ነው፤ ሳሙኤልስ ቢሆን፣ አሞጽስ ቢሆን፣ ኤርምያስስ ቢሆን፣ ጳውሎስስ ቢሆን፡፡ ከሁሉ ይልቅ ደግሞ ያ የደግነት ምሳሌ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእውነተኛ ቁጣም ምሳሌ ነው፡፡

 

የቁጣ ቴዎሎጂ ሳያስፈልገን አይቀርም፡፡

 

ለመሆኑ እኛ ዘንድ የቁጣ መጠን አንሷል እንዴ? ቁጣማ እንዳለ በየመስኮታችን የሚትጎለጎለው ጢስ ይነግረናል፡፡ ለምንድን ነው የምንቆጣው ነው ጥያቄው፡፡

 

“ስንት ዓመት በጌታ የቆየሁት እኔ እያለሁ ትናንት የመጡትን ነው ቦታ የሚሰጧቸው”

“ጌታ የባረከኝ እንደሆን ለሁሉ ሰው ገንዘብ መበተን አለብኝ እንዴ? አላበዙትም!”

“የማን ብሔረሰብ ከማን ያንሳል? አስበው አይናገሩም?”

“እነሱ ሙስና ውስጥ ተዘፍቀው እኔ ትንሽ እንከን ቢገኝብኝ ይህን ያህል ማውገዝ ምን ይባላል?”

 

ቁጣማ ሞልቷል፤ የቁጣችን ምክንያት ግን ምንድን ነው? “የእኔ ምቾት፣ የእኔ ክብር፣ የእኔ ስም፣ የእኔ ጥቅም” ማእከላዊ የሆነበት ቁጣ ከሆነ አሁን ከምንነጋገረው ጋር አይመጣጠንም፡፡

 

የእግዚአብሔር ሰው የሚቆጣው በኀጢአት ላይ ነው፡፡ የሚቆጣው እውነትን ለማጽናትና ስሕተትን ለመገሠጽ ነው፡፡ እንዲያውም ይህ ሰው የሚቆጣው እግዚአብሔር ስለሚቆጣ ነው፡፡ የአምላኩን ቁጣ ነው የሚያስተጋባው፡፡ ወደ እግዚአብሔር በኩል ያለው ነፍሱ ከመሳሳቱ የተነሣ የአምላኩ ድምጽ ጮክ ብሎ እየተላለፈበት ነው፡፡

 

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን ታላላቅ የቁጣ ምክንያቶች በግርድፍ እናስተንትን ብንል ምናልባት ሦስቱ ጎልተው ይታያሉ፡፡

 

  1. በእግዚአብሔር ላይ ያለንን ታማኝነት ማጉደል (በእግዚአብሔር ላይ ማመንዘር)
  • ሙሴ በምድረበዳው ጉዞ (ዘፀ 32)
  • ነቢዩ ሆሴዕ ለኮብላይዋ ለእስራኤል የተናገረው (ሆሴዕ1-2)
  • ጌታችን ኢየሱስ ለመቅደስ ውስጥ ነጋዴዎች የተናገረው (ማቴ 21)

 

  1. በሰዎች ላይ የሚሠራ ግፍና ዐመጽ፡- የፍትሕ ማዛባት በኢኮኖሚያዊ፣ በሥነ ልቦናዊ፣ በማኅበራዊ ግንኙነት የሚፈጸም በደል
  • አሞጽ ለጽዮን ዓለመኞች (አሞጽ4)
  • ነህምያ ከምርኮ ለተመለሱ አይሁ ባለጠጎች (ነህ 5)
  • ኢሳይያስ ለሕዝቡ (ኢሳ 58)

 

  1. በሃይማኖት ስም የሚታይ አስመሳይነት፣ ግብዝነትና ማታለል
  • ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሃይማኖት መሪዎች ላይ (ማቴ 23)
  • ነብዩ ሕዝቅኤል በእስራኤል እረኞች ላይ (ሕዝ 34)
  • ሐዋርያው ይሁዳ በሐሰተኞች አስተማሪዎች ላይ (ይሁዳ)
  • ነቢዩ ኤርምያስ በሐሰተኞች ነቢያት ላይ (ኤር 23)

 

እነዚህ የቁጣ ምክንያቶች ዛሬ እኛ ዘንድ የሉምን? ያሉ ከሆነስ የቁጣውን ድምጽ ጥርት ባለ ሁኔታ እየሰማን እያሰማንስ ነውን? ወይስ ተፈራርተን፣ ተከባብረን ተቀምጠናል፡፡ ኀጢአት ባለበት ክብር የለም ሰውን መፍራት የሞት መንገድ ነው፡፡

 

በቤታችን፣ በቤተ ክርስቲያናችን፣ በኅብረተሰባችን ጽድቅ ሲጓደል፣ ፍትሕ ሲዛባ፣ ግፈኞች ከፍ ሲሉ ለመናገር በምንችልበት ሁኔታ መጠላትን ከመፍራት “እንዳልጠመድ” ከመስጋት የተነሣ ስንት ጊዜ እንተሻሻለን?

 

በቤተ ክርስቲያን የተከበረ ሰው ንጹህ ያልሆነ ሥራ ሲሠራ እያየን በጽድቅ ሚዛን በመለካት ፈንታ ሚዛኑን ለርሱ ስንል እናስተካክልለታለን፡፡ “እውነቱን ተናግረን በመሸበት በማደር” ፋንታ በእውነት ሽያጭ ገንዘብ ተሳፍረን ሳይመሽ ቤት መግባት ለምደናል፡፡ ይህ ከፍርሃት የተነሣ ያደረብን ልማድ በሰውነታችን ተሠራጭቶ እየቆየ ሲሄድ የእውነትና የሐሰት ልዩነትም እየጠፋብን እንዳይሄድ ያሰጋል፡፡ ምላሳችንን ዘወርዋራ መንገድ አስተምረነዋልና አቅንቶ መናገር አይችልም፡፡ ዐይናችን ሸውራራ ነው፡፡

 

የሐቅ ሚዛን፣ የእውነት ፍርድ፣ የጽድቅ ቁጣ በሌሎች ላይ ከመሰንዘሩ በፊትና በላይ ራስን ሊያስተናግዱበት ግድ ነው፡፡ “ጣዖትን የምትጸየፍ ቤተ መቅደስን ትዘርፋለህ? ብሏል ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ “ራሳችንን ብንመረምር ባልተፈረደብንም ነበር” ማለት እኮ አስቀድመን እኛው በእኛው ላይ ከፈረድንና ከተስተካከልን ሌላ ፍርድ አይጠብቀንም ማለት ነው፡፡ ሌሎችስ ሲወቅሱንና ሲዘልፉን በጥሞናና በአክብሮት እንሰማለን ወይስ ቱግታችን ከራሳችን ሌላ የማንንም ድምጽ እንዳንሰማ ያግደናል?

 

ቁጣ ብንል ግን ሰውን ለማጥፋት አይደለም፡፡ የቁጣን ትንታግ እያየን የወላፈኑ ቀለም የሚያስደስተን ከሆነ ተሳስተናል፡፡ ለጽድቅም ብለን፣ ለእግዚአብሔር መንግሥትም እንኳ ብለን “እሳት ከሰማይ ወርዶ ይብላቸው” ብንል “የሰው ቁጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራም” ይለናል መጽሐፍ፡፡ ቁጣን የምንፈልገው ለቁጣነቱ አይደለም፤ ምንም ጌጥ የለውም፤ መቆጣትም በራሱ በቂ ግብ አይደለም፡፡ ኀጢአትን እየተጸየፍን በመርዙ የተያዙትን ለማውጣት በፍርሃት እንድንምር ታዘናል፡፡ “የሙሴ ቁጣ ተቃጠለ ሕዝቡን አመድ አጠጣቸው” ቢለንም መጽሐፉ ብዙ ሳይርቅ፣ በዚያው ምዕራፍ “አሁን ይህን ኀጢአታቸውን ይቅር በላቸው ያለዚያ ከጻፍከው መጽሐፍህ እባክህ ደምስሰኝ” ብሏል ይለናል፡፡ ወንድሞቼ የምንቆጣ ከሆነ ቁጣችንን የሚበልጥ ፍቅር በጉያችን መኖሩን እናረጋግጥ ያለበለዚያ የሞት መልእክተኞች ሆነን መቅረታችን ነው፡፡

 

የእግዚአብሔርን ቁጣ ለመቆጣት፣ የሚፈርድ፣ የሚያድንም እሳት ለማግኘት አንዱ እንዳለው “የጽድቅ ሰውነት” ያስፈልገናል፡፡ በአንድ አዳር በቁጭት ተነስተን የምንሆነው ነገር አይመስለኝም፡፡ ልስላሴንና እንደ ድመት መፍረግረግን፣ አድርባይነትን እድሜ ልካችንን ስንለምድ ኖረናልና የእውነት ጭፍራ ለመሆንም መሠልጠን የስፈልገናል፡፡ “የመንፈስ ቆዳችን” የእውነትንና የሌብነትን አካል ዳስሶ ለመለየት የሚሰማው መሆን አለበት፡፡

 

ይህ “የጽድቅ ሰውነት” እንዴት ይገነባል? እግዚአብሔርን በማወቅ ነው፤ ባሕርዩን በመረዳት ነው፡፡ በፍጹም ብርሃን ውስጥ የሚኖረውን የሰውን ፊት አይቶ የማያደላውን የማይለወጠውን አምላክ ማወቅ ስንጀምር ስሜቱን እንጋራለን፡፡ የኀጢአትን አጥፊነት ስናውቅ ልባችን ይጨክናል፡፡ ኀጢአት ላይ ፈርደን ኀጢአተኛውን ለማዳን፡፡ በሁሉ ላይ የመጨረሻው ባለሥልጣን ልዑል እግዚአብሔር እንደሆነ ስንረዳ ትናንሽ መሳፍንትን አንፈራም፡፡

 

“ሰዎችን አትፍሩ” አለ ጌታ ኢየሱስ “ቢበዛ ምን ያደርጓችኋል? ይገድሏችኋል እንጂ፤ ከገደለ በኋላ ወደ ገሃነም ለመጣል ሥልጣን ያለውን ፍሩ” እንደዚህ ያለው ፈሪሃ እግዚአብሔር ሲለምድብን ነው “የጽድቅ ሰውነት” የሚገነባው፡፡

 

“ተቆጡ፤ ኀጢአትንም አታድርጉ፡፡” (ኤፌ 4÷26)

Read 16923 times Last modified on Tuesday, 12 May 2015 12:55
Negussie Bulcha

Website: www.negussiebulcha.com Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 62 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.