You are here: HomeOpinionsለ “ቤተ ክስያን” ሂያጆች

ለ “ቤተ ክስያን” ሂያጆች

Written by  Thursday, 26 March 2015 00:00

በየሰንበቱ ÷ የተጋን እንደሆነም በየሠልሰቱ ቤተ ክርስቲያን የምንሔደው ለምንድን ነው? የነፍስ ዕዳዬን ለመክፈል፣ ሰማዩ እንዳይቆጣ፣ የባዶ ቤት ድብርቴን ለማባረር፣ ማኅበራዊ አንቱታ እንዳላጣ፣ ደግሞስ የክት ልብሴን መቼ ልልበሰው?

 

በአውሮጳና አሜሪካ ወደ ቤተ ክርስቲያን/ቤተ ጸሎት የሚሄደው ሰው ቁጥር እያሽቆለቆለ እንደመጣ ይነግሩናል፤ እየሰማንም እናዝናለን፡፡ እኛ አገር ቤተ ክርስቲያን ሂያጅ ብዙ ቢሆንም አካሄዱ እንዴት ነው የሚለው ያሳስበናል፡፡ ረጋ ብለን መጠየቅም መጠያየቅም ያለብን ይመስለኛል፡፡

 

ለመሆኑ ከነአካቴው ቤተ ክርስቲያን መሄድስ አለብኝ ወይ? ከሚለው ጥያቄ ጀምሮ የደጀ ሰላም ምልልሴ በሕይወቴ ላይ ያመጣው ለውጥ ምንድን ነው? እስከሚለው ድረስ በጥሞና መወያየት ይገባናል እላለሁ፡፡ ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከልጅነቱ ጀምሮ ወደ አይሁድ ምኩራብ ይሄድ ነበረ፡፡ ሄዶ በቤተ መቅደስ ካሉት መምህራን ጋር ይወያይ ነበር፡፡ “እንደ ልማዱም በሰንበት ወደ ምኩራብ ገባ” የሚለው የሉቃስ አገላለጽ ጌታችን ቤተ ጸሎት አዘውታሪ እንደነበር በቂ ፍንጭ ይሰጣል፡፡ ቀዳሚዎቹ ክርስቲያኖች በሳምንቱ ፊተኛ ቀን (እሁድ) ይሰበሰቡ እንደ ነበረ አዲስ ኪዳናዊ ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡ ተገናኝተው ምን ያደርጉ ነበረ? ቃለ እግዚአብሔር ያደምጡ ነበር፤ ይጸልዩ ነበር፤ የጸጋ ስጦታዎችን ይካፈሉ ነበር፤ የተቸገሩትን ለመርዳት ለወንጌልም ሥራ ገንዘብ ይሰበስቡ ነበር፤ ፍቅራቸውን ችግራቸውንም ይካፈሉ ነበር የጌታን ራት በመቁረስ ኅብረታቸውን ያጠነክሩ ነበር ወዘተ…፡፡

 

የመንፈሱ ማደሪያ እንድንሆን ጸጋውን ሰጥቶናልና በግንብ ያነጽነው ቤት ወይም በላስቲክ ከለላ ያዋቀርነው ዳስ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያን እኛ ነን፡፡ እኛ ራሳችን ነን፡፡ ክርስቶስ አካላዊ አንድነታችንን ለመግለጽና ለማጽናት እንሰበሰባለን፡፡ ይህን ማድረጋችን ተገቢ ነው፡፡

 

  • ስንሰበሰብ የሥላሴን ሀልዎት/መገኘት እየናፈቅን ከእርሱ ጋር ተመስጦም፣ ሐሴትም ለማድረግ እየጓጓን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንሂድ፡፡ ከ 14ኛው ፕላኔት የመጣ እንግዳ ዛሬ ይሰብካል ስለ ተባለ ሳይሆን ከሰማየ ሰማያት የወረደው ጌታ በመንፈሱ ይገኛል እያልን በእግዚአብሔር ፍቅር ተጎትጉተን እንምጣ፡፡

 

  • የምሄደው የሰማዩን አባት ለማነጋገርና ለመስማት ብቻ ሳይሆን ወንድሞቼንና እህቶቼን ለማየት ነው ብለን እንሂድ፤ በደረስኩም ጊዜ ፍቅሬንና ናፍቆቴን ደስታዬንና ሥጋቴን ላካፍላቸው፤ ቤትስ ልጆችስ፣ ላሞችስ ጥገቶችስ እንዴት ናቸው? እያልሁ ልጠይቅ፡፡ የጸሎት አርእስት ተቀብዬ ሰጥቼም ልምጣ፡፡

 

  • በሕያው አምላክ ፊት በትህትናና በጥሞና በደስታና በማስተዋል ልሁን እንጂ “የአብዬ ፈለቀን ልጅ የሚሠራትን እኮ አሳጣት እስኪ ያረገችውን ጆሮ ጌጥ ተመልከት፤ ስማ አንተ የእነገሌ ቤተ ክርስቲያን ፓስተር በምን ኀጢአት እንደ ወደቀ ሰምተሃል?” ማለቴን ልተወው፡፡

 

  • ቤተ ጸሎት የደስታ ቦታ ቢሆንም የጥሞናና የስክነት አደባባይም ስለ ሆነ ተጀምሮ እስኪጨረስ እየዘለልሁና መንፈሴን ባዶ፣ ጸሎቴን ድጋምና ፉከራ እያደረግሁ ግልብ ሩጫ እንዳልሮጥ ልጠንቀቅ፤ መንፈሱ እንዲቀሰቅሰኝ ለውዳሴም ለትካዜም፣ ለሽብሸባም ለሰጊድም፣ እርሱ እንደሚመራኝና በጋራም እንደሚቃኘን ለመሆን ልሰናዳ፡፡ ደንብ ለማስፈጸም ግዴታ የለብኝም፡፡

 

  • ቤተ ክርስቲያን ሂያጆችና ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሁልጊዜ በልማድ ጠፍር የምንቀፈደድ ስለምንድን ነው? አንዳንድ ቀን “አባታችን ሆይ” የሚለውን ጸሎት በስብሰባው መጀመሪያ ብናደርገውስ? አንዳንድ ቀን የሚዘመረው መዝሙር ሁለት ብቻ ቢሆንስ? አንዳንድ እሁድ ስብከቱን ሃያ ደቂቃ አድርጎ የቀረውን ሃያ ደቂቃ በጋራ ብንጸልይበትስ? አንዳንድ ጊዜ ከአጭር ትምህርት በኋላ የቡድን ውይይት ቢኖርስ? አንዳድ ቀን በአንድ ሰው ስብከት ፈንታ የመድረክ ላይ የሕይወት ምስክርነት ቃለ መጠይቅ ቢኖርስ? አንዳንዴ (በአንድ ቤተ ክርስቲያን እንዳየሁት) ስለ ወንጌል ስርጭት ትምህርት ተሰጥቶ ከፊሉን ጊዜ ለ ወንጌል ምስክርነት ቢወጣስ? ሁልጊዜ በልማድ ጠፍር የምንቀፈደድ ስለምንድን ነው? መንፈስ ቅዱስ የሚመራን አዲስ መንገድ ካለ ለምን ዐይናችንን እንጨፍናለን?

 

  • አንዳንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዳየሁት ከስብሰባው በኋላ ብቸኞችን፣ እንግዶችን፣ ይዞ ወደ ቤት መውሰድ ምሳ መጋበዝ ወይም በሻይ ዙሪያ ልባቸውን ማዳመጥ ወይም ይህንን የመሳሰሉ ምግባረ ሠናያት የትስ ቦታ ቢሆን ቢለመድ ምን ክፋት አለበት?

 

  • እሁድ ቤተ ክርስቲያን ሄደን ልዑሉን አምላክ እንደምንወድስ ረቡዕ ጧት ገበያው ውስጥ አምላክን የማናከብረው ለምንድን ነው? ሐሙስ ማታ የትምህርት ክፍላችን ውስጥ በፈሪሃ እግዚአብሔር የማናመሽ ስለ ምንድን ነው?

 

  • አሁን በቅርቡ ቤተ ክርስቲያን የምትሄዱት መቼ ነው? በደስታ ሂዱ፤ በጥንቃቄ ሂዱ፤ በንቁ ልቦና ሂዱ፡፡ እንደ ቴአትር ተመልካች ሳይሆን እንደ አባታችን ቤት ልጆች የባለ ቤትነትና የአስተዋይ ተሳትፎ ልብ ይዘን እንሂድ፡፡
Read 9895 times Last modified on Monday, 30 March 2015 05:55
Negussie Bulcha

Website: www.negussiebulcha.com Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 96 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.