You are here: HomeOpinionsየባለምርኩዙ ምኞት

የባለምርኩዙ ምኞት

Written by  Saturday, 12 July 2014 00:00

የቀኑ አመሻሽ ላይ ወደቤት እያዘገምኩ ነበር፡፡ ከፊት ለፊት የሚመጣው ሰው መሆኑ፣ ከዚያም አልፎ ፆታው እንጂ ማንነቱ በደንብ በማይታወቅበት በዚያ ድንግዝግዝ አንድ ሸምገሉ ያሉ ሰው ከፊት ለፊቴ ከዘራቸውን ተደግፈው ወደጎን ወደፊት ይላሉ፡፡ ርምጃቸውን ያስረጀው ዕድሜአቸው አይመስልም፤ ስካራቸው አንጂ! ምርኩዛቸው ሲቀር ሌላው የሰውነታቸው ክፍል በአልኮሉ ተጽዕኖ ስር ወድቋል፡፡

 

አልፌአቸው እንደሄድኩ ከፊት ለፊት የሚመጡትን ሦስት ወጣቶች -- ሁለት ሴቶችና አንድ ወንድ ይመስሉኛል -- “በ…ደ…ህና ግቡ ል…ጆች!” ብለው መረቋቸው፤ አፍም እንደ እግር ውትርትር እያለ፡፡  

 

ምኞትና ገሃድ እውነት? ለወጣቶቹስ ተመኙ፣ እርሳቸው በደህና ይገቡ ይሆን? ብዬ አሰብኩ፡፡ የናወዘው እግር ነው፤ ምርኩዙ ደህና ነው፡፡ ምን ቢጠጡ ወደ በትር አይሄድ፡፡ እግር በደም በኩል አልኮል ቢጋራ በትር ሕይወት ስለሌለው ባለበት ይቀጥላል፡፡ ችግሩ ግን ምርኩዙ በራሱ መቆም አለመቻሉ ነው፡፡ የያዘው እጅም እንደ እግር ሁሉ በአልኮሉ ስለሚንከላወስ መሬት መደገፍ ባለበት ቅጽበት አየር ይጎስምበታል፡፡  

 

ትዕይንቱ ለእኔ የመጀመሪያ ቢሆንም ለሰውየው ግን አኀዝ የለሽ ሊሆን ይችላል፡፡ መንገዱንም፣ ምሽቱንም፣ ሞቅታውንም ቢለምዱትም አይደል የመልካም ምኞት መግለጫቸውን ያስተላለፉት፡፡ 

 

የሰላም ምኞት ከየስፍራው እየተለካና እየተሰፈረ ይቀርባል፡፡ ሰላምን ማስፈን ወይም ማደፍረስ የሚችለውም ሆነ ምንም ተጽዕኖ ማሳረፍ የማይችለው ምኞቱን ይገልጻል፤ ልክ እንደኛ ምርኩዘኛ፡፡ ሰላም ግን በምኞት ገመድ ብቻ ታስራ የምትጠበቅ አይደለችም፡፡ ፈላጊ፣ ዘብ፣ አሳዳጊና ተንከባካቢ ትሻለች፡፡ 

 

የመልካም ምኞት መግለጪያ በየርዕሳነ ሰሞናት ከሚያበስሩልንና ሰላማቸውን ከሚተዉልን ሁሉ የላቀ ሰላም የተወልንን በንጽጽር እንይ፡፡ የተነጻጻሪዎቹ ልዩነት የትናየት ቢሆንም ርዕሰ ጉዳዩ አንድ ስለሆነ ማስተያየቱ ተገቢ ይሆናል፡፡

 

ጊዜው ምሽት ነበር፡፡ የተስፋ ጎህ ቀዶ፣ ውሉ ግን አለይ ብሎ ቤት የተዘጋበት ዕለት፡፡ የተሰማው ወሬና የታየው እውነታ ዕርስ በርሱ ቢስማማም ፍጹሙ ማስረጃ ስላልቀረበ ጭንቀትና ተስፋ እንደተፈራረቁ ውለዋል፡፡ ሴቶቹ (እነ መቅደላዊት ማርያም) ያበሰሩት ብስራትና ወንዶቹ ሄደው የተመለከቱት የቀኑ ወግ ብቸኛው ርዕስ ነበር፡፡ 

 

አስራአንዱም በራቸውን በተነሳው ሳይሆን በገዳዮች ላይ ዘግተው ከውስጥ በአንጻራዊ ፀጥታ በነበሩበት፣ መዝጊያን ስለማንኳኳት ያስተማረውና አልፎም በሎዶቅያ ቤተ ክርስቲያን ደጅ ሆኖ ማንኳኳቱን የገለጸልን ጌታ በቅጽበት ዓይን በመካከላቸው ተገኘ፡፡ ወዲያውም “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው፡፡ ከክስተታዊው ሀልዎት (መገኘት) ባለፈ ንግግሩ ነፍስን የሚያሳርፍ ነበር፡፡ 

 

ሁሉንም እኩል የሚመለከት ቃል፤ ችግሩ የጋራ ሲሆን ማጽናኛውም የወል ይሆን የለ፡፡ ኀብረታቸው ብርቱ ቢሆንም የየግላቸው አቅም ግን ተንዷል፡፡ ወዳጅ፣ አስተማሪ፣ ጠባቂ፣ አማካሪ፣ መጋቢ፣ ፈዋሽ፣ ጌታ…ብዙ ነገራቸው ነበር፡፡ ከመካከል እንኳን የጎበዝ አለቃ ሳይሾም ነበር የሞትን መንገድ ፉት ያደረጋት፡፡ የጠላት ሰይፍ በአንድ ጣራ ስር ያኖራቸው ምስኪኖች! “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” በእርጋታ ለተቀመጡ እንጂ በፍርሃት ለተኮማተሩ አይደለም፡፡  

 

ለተጨነቀ፣ ተስፋው(ን) ለተወሰደ (ወይም ላሶሰደ) እና ግራ ለተጋባ ሰው የሚሰጥ ፍቱን ማረጋጊያ፣ ሰላም፡፡ በዚያው ቤት ሁለት ጊዜ ነው “ሰላም ለእናንተ ይሁን” ያላቸው (ዮሐ 20፣19፡21)፡፡ በሳምንቱም ጠያቂው ቶማስ እንግዳ በሆነበት መሰባሰብ ላይ እንዲሁ በተዘጋ ቤት ውስጥ ተገኝቶ ይህንኑ ቃል ደገመላቸው፤ በ8 ቀን 3 ጊዜ! 

 

ሁሉ በሥልጣኑ ቃል የተፈጠሩና የተደገፉ ጌታ ንግግሩ ከመልካም ምኞት ያለፈ፣ ድርጊታዊና ኩነታዊ ነው፡፡ ተናግሮ መንገድ የማይቀር፣ ተመኝቶ የማይስተጓጎል፣ ቃልን ከፈቃዱ እንጂ ከስሜቱ የማያወጣ አምላክ “ሰላም” ይሁን ካለ ሆነ እንጂ ሌላም አልሆነ፡፡ 

 

የሰላም ፈላጊዎች አልፎም ሸማቾች ብዙ ቢሆኑም አለቃዋ ግን አንድ ነው፡፡ ሰላም እንደሰላምነቷ ደግሞ ታዛዥ ነች፡፡ የዕርቅና የምህረትን መንገድ ሄዶ ሰላምን ያበሰረ፣ ያሰፈነና ያካፈለ እርሱ ነው፡፡

 

“የሰላም አለቃ” የሆነው የእግዚአብሔር ልጅ ዕረፍታችሁን ያብዛው! እርሱን ተመርኮዙ፤ ሰላምን ተመኙ፤ በምኞታችሁ ግን ጠብ አይግባ፡፡

በሰላም ያሰንብተን!

Read 14433 times Last modified on Saturday, 12 July 2014 10:12
Nahu

Nahusenay Afework is a freelance writer and communications consultant. His study at Addis Ababa University earned him MA in Literature. He takes pleasure in writing and consulting people. He is also involved in church ministry in the domain of teaching.

Website: https://www.facebook.com/nahusenay.afework Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 187 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.