የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ ላይ በዋለው ችሎት ታሪካዊ የሆነ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ፍርድ ቤቱ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ በሁሉም 50 ስቴቶች ህጋዊ መሆኑን ደንግጓል፡፡
በቅድሚያ 3 ስቴቶች ብቻ ይፈቅዱት የነበረው የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ ወደ 37 ስቴቶች አድጎ የቆየ ሲሆን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ግብረ ሰዶማዊነትን ጠቅልሎ ህጋዊ ተግባርና የሁሉም ዜጎች መብት እንደሆነ ወስኗል፡፡
ፍርድ ቤቱ ጋብቻ ምን እንደሆነ ገለጻም ሆነ ትርጉም አልሰጠም፡፡ እንዲው በደፈናው ከተመሳሳ ጾታ ጋር ጋብቻ መፈጸም እንደሚቻልና የሁሉም አሜሪካዊ ዜጋ መብት እንደሆነ ውሳኔውን አስተላልፏል፡፡
የፍርድቤቱን የመጨረሻ ውሳኔ በመጠበቅ ላይ የነበሩ በርካታ ሰዎች የፍርድቤቱን አካባቢ በጩኸትና በፌሽታ አድምቀውታል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ሌሎች በርካቶች ተቃውሞአቸውን በተለያየ መንገድ በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡
የአሜሪካ መንግስትና ሌሎች በሥልጣኔ ጫፍ ወጥተዋል የምንላቸው ምዕራባዊ ሀገራት ነገረ ሥራ ሁሉ ጥንት መንግስታቶቻቸውና ሕዝቦቻቸው የቆሙለትን ሞራላዊና ኃይማኖታዊ እሴቶችን በመናድ (እነሱ በፈረንጅኛቸው እንደሚሉት - re-define) ማድረጉን ተያይዘውታል፡፡
በአሜሪካ የተደረገው ማንኛውም ነገር በቀረው ዓለም የሚኮረጅ እንደመሆኑ ወይም በተለያዩ የዲፕሎማሲ መሥመሮች በዕርዳታና በብድር ውዴታ ግዴታ መንገዶች ነገ በእኛ ላይም መጫኑ ስለማይቀር ነቅተን ምድራችንን በጸሎት ልንናጠቅ ይገባል፡፡
ጋብቻ የአሜሪካ መንግስት ከመፈጠሩም በፊት የነበረና ሰዎችን ወንድና ሴት አድርጎ በፈጠረው በእግዚአብሔር አምላክ በራሱ የተፈጠረ ተቋም ነው፡፡ ወንድና ሴት አድርጎ የፈጠራቸው እግዚአብሔር በሥራው ትክክልና የማንንም ማስተካከያ አይሻም፡፡
ወሬው ሁሉ፣ የሚሰማው ሁሉ አስፈሪና የጌታን ዳግም ምጽአት የሚያመላክት በመሆኑ ነቅተን ዘመኑን ልንዋጅ ይገባል፡፡