You are here: HomeNews/Events“የደነበረው በቅሎ”፡ የአስተምህሮ “ልጓም” ይሻል የተሰኘው መጽሐፍ ተመረቀ

“የደነበረው በቅሎ”፡ የአስተምህሮ “ልጓም” ይሻል የተሰኘው መጽሐፍ ተመረቀ

Published in News and Events Tuesday, 16 December 2014 00:00
Solomon Abebe Solomon Abebe The Author

በሰሎሞን አበበ ገብረ መድኅን የተጻፈውና  የደነበረው በቅሎ የአስተምህሮልጓምይሻል የሚል ርእስ ያለው ዐዲስ መጽሐፍ በሕዳር 21 ቀን 2007 .. በደማቅ ሥነ ሥርዓት ተመረቀ። የመጽሐፉ ምረቃ በኢንተርናሽናል ኢቫንጀሊካል ቸርች (IEC/ETC) የተካሄደ ሲኾን እጅግ በርካታ ታዳሚዎች ተገኝተውበታል። በኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የታወቁ አገልጋዮች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የጸሐፊው ወዳጆችና አናባቢዎች የታደሙበት ይህ የምረቃ ሥነ ሥርዐት ከቀኑ 900-1200 የዘለቀ ነበር።

 

መርሐ ግብሩ በአቶ ዘላለም አበበ እና በወይዘሪት ትዕግሥት ተስፋዬ የመድረክ አስተባባሪነት የተመራ ሲኾን፣ / ክሪስቶፈር ቤታም የመክፈቻ ጸሎት አድርገዋል። ዘማሪት ሐናና ዘማሪ ዳዊት ጌታቸው የዝማሬ አገልግሎት ሰጥተዋል። በተጨማሪም፣ ሥነ ግጥሞች፣ መነባንቦች፣ ዐጫጭር ጽሑፎችና ታዳሚውን እያዋዙ ቁምነገር የሚያስጨብጡ የተለያዩ ዝግጅቶች፣ ከዕለቱ መርሐ ግብርና ከመጽሐፉ መሪ ጭብጥ ባላፈነገጠ መልኩ፣ በተለያዩ ወንድሞችና እኅቶች ቀርበዋል።

 

አቶ ሽፈራው ወልደ ሚካኤልሊታረም የማይችል ስሕተት ከመፈጸም እንጠንቀቅበሚል ርእስ የቃለ እግዚአብሔር ትምህርት ያቀረቡ ሲኾን የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን በመጥቀስ ከዘመናችን ጋር በማዛመድ አስጠንቅቀዋል። በመልእክታቸውም፣ ዐዲሱ መጽሐፍ የተሸከመው ሐሳብ እውነት መኾኑንና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንአስደንጋጭካሉት ኹኔታ ውስጥ እንድትወጣመነጋገር እጅግ አስፈላጊመኾኑን አጽንዖት ሰጥተዋል።

 

የመጽሐፉ ይዘት፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነገረ መለኮታዊ ጭብጥና ፋይዳውን አስመልክቶ ሠላሳ ደቂቃ የፈጀ ዝግጅታቸውን ያቀረቡት መጋቢ በቀለ ወልደ ኪዳን ነበሩ። ዐሥር ጥያቄዎችን በማንሣት መጽሐፉን ከገጽ ገጽ ያስቃኙት መጋቢ በቀለ፣የደነበረው በቅሎ መጽሐፍ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃዎች የበለጸገ በጥናትና ምርምር የዳበረ፣ መአቀራረብ ሚዛናዊነት የሚታይበትና እጅግ ወቅታዊ፣ የበላንን የሚያክክ አንገብጋቢ ጕዳዮችን የሚያነሣ መጽሐፍ ነውብለውታል። በተጨማሪም፣ መጽሐፏ ስሕተት አነፍናፊ ሳትኾን በወንጌላውያን ክርስቲያኖች መካከል በመታየት ላይ የሚገኙትን ግድፈቶች በማሳየት የመፍትሔ ሐሳቦችን የምትጠቍም መጽሐፍ መኾኗን አሳይተዋል።

 

መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማርና በመስበክ የሚታወቁት / ማሙሻ ፈንታ በበኩላቸው መጽሐፉንበሰባኪ ዐይንገምግመውታል።እኛ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ወዲያ ወዲህ ስንል፣ ውስጥ ድረስ ገብታ ቊስላችንን አፍረጥርጣ ለማከም የሞከረች መጽሐፍ ናትያሉት / ማሙሻ፣ የገበያ ግር ግር ለሌባ ይመቻልናየበቅሎው መደንበርተጠቅመው አንዳንድ ሰባክያን ጥቅም ማጋበሻ አድርገውት ቢኾንስ? በማለት የዘመናችን አገልጋዮች ቆም ብለው እንዲያስቡበት የምታሳይ መጽሐፍ ናት ብለዋል። በእውነት ለሚሄዱት አገልጋዮች ደግሞ እንደ አበረታችአሯሯጭየምትታይ፣ አንቂና አነቃቂ በመኾን ታገለግላለች ብለዋል።

ዘማሪ ገዛኸኝ በበኩላቸው መጽሐፉን በዘማሪ ዕይታ ቃኝተው አቅርበዋል። ጸሐፊው ሰሎሞንም ለመጽሐፉ ሥራ በተለያየ መንገድ ላገዙት ወገኖችና ጥሪውን አክብረው ለተገኙት ታዳሚዎቹ ምስጋና በማቅረብ እንዲሁም ሐሳብና ውጥኖቹን በዐጭሩ በማሳየት ንግግር አድርጓል። በመጨረሻም፣ መጋቢ / ቤዛለም ፍሰሐ መጽሐፉን በይፋ መርቀው መርሐ ግብሩ በጸሎት ተጠናቋል።

 

የደነበረው በቅሎመጽሐፍ በቅዱሳት መጻሕፍት እውነት፣ በታሪካዊው የክርስትና ርትዐዊ አስተምህሮና በአባቶች ተጋድሎ በዘመናት የተላለፈውን እውነተኛ ወንጌል ትምህርት ወደየአብያተ ክርስቲያናቱ ሾልኮ በመግባት ላይ ከሚገኙ የኑፋቄ ትምህርቶች፣ እንግዳ ልምምዶችና የተበላሹ ሥርዐተ አምልኳዊ መደበላለቆች መጠበቅና መከላከል እንደሚገባ በጥልቅ ምጥና ጩኸት የተስተጋባበት መኾኑን ብዙዎች መስክረዋል።

 

ይህን መጽሐፍ በማንበብና ለሌሎችም በማስተላለፍ ታሪካዊ ግዴታችንን እንወጣ።

Read 8076 times Last modified on Tuesday, 16 December 2014 14:59

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 364 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.