በሰሎሞን አበበ ገብረ መድኅን የተጻፈውና “የደነበረው በቅሎ”፡ የአስተምህሮ “ልጓም” ይሻል የሚል ርእስ ያለው ዐዲስ መጽሐፍ በሕዳር 21 ቀን 2007 ዓ.ም. በደማቅ ሥነ ሥርዓት ተመረቀ። የመጽሐፉ ምረቃ በኢንተርናሽናል ኢቫንጀሊካል ቸርች (IEC/ETC) የተካሄደ ሲኾን እጅግ በርካታ ታዳሚዎች ተገኝተውበታል። በኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የታወቁ አገልጋዮች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የጸሐፊው ወዳጆችና አናባቢዎች የታደሙበት ይህ የምረቃ ሥነ ሥርዐት ከቀኑ 9፡00-12፡00 የዘለቀ ነበር።
መርሐ ግብሩ በአቶ ዘላለም አበበ እና በወይዘሪት ትዕግሥት ተስፋዬ የመድረክ አስተባባሪነት የተመራ ሲኾን፣ ዶ/ር ክሪስቶፈር ቤታም የመክፈቻ ጸሎት አድርገዋል። ዘማሪት ሐናና ዘማሪ ዳዊት ጌታቸው የዝማሬ አገልግሎት ሰጥተዋል። በተጨማሪም፣ ሥነ ግጥሞች፣ መነባንቦች፣ ዐጫጭር ጽሑፎችና ታዳሚውን እያዋዙ ቁምነገር የሚያስጨብጡ የተለያዩ ዝግጅቶች፣ ከዕለቱ መርሐ ግብርና ከመጽሐፉ መሪ ጭብጥ ባላፈነገጠ መልኩ፣ በተለያዩ ወንድሞችና እኅቶች ቀርበዋል።
አቶ ሽፈራው ወልደ ሚካኤል “ሊታረም የማይችል ስሕተት ከመፈጸም እንጠንቀቅ” በሚል ርእስ የቃለ እግዚአብሔር ትምህርት ያቀረቡ ሲኾን የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን በመጥቀስ ከዘመናችን ጋር በማዛመድ አስጠንቅቀዋል። በመልእክታቸውም፣ ዐዲሱ መጽሐፍ የተሸከመው ሐሳብ እውነት መኾኑንና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን “አስደንጋጭ” ካሉት ኹኔታ ውስጥ እንድትወጣ “መነጋገር እጅግ አስፈላጊ” መኾኑን አጽንዖት ሰጥተዋል።
የመጽሐፉ ይዘት፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነገረ መለኮታዊ ጭብጥና ፋይዳውን አስመልክቶ ሠላሳ ደቂቃ የፈጀ ዝግጅታቸውን ያቀረቡት መጋቢ በቀለ ወልደ ኪዳን ነበሩ። ዐሥር ጥያቄዎችን በማንሣት መጽሐፉን ከገጽ ገጽ ያስቃኙት መጋቢ በቀለ፣ “የደነበረው በቅሎ መጽሐፍ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃዎች የበለጸገ በጥናትና ምርምር የዳበረ፣ መአቀራረብ ሚዛናዊነት የሚታይበትና እጅግ ወቅታዊ፣ የበላንን የሚያክክ አንገብጋቢ ጕዳዮችን የሚያነሣ መጽሐፍ ነው” ብለውታል። በተጨማሪም፣ መጽሐፏ ስሕተት አነፍናፊ ሳትኾን በወንጌላውያን ክርስቲያኖች መካከል በመታየት ላይ የሚገኙትን ግድፈቶች በማሳየት የመፍትሔ ሐሳቦችን የምትጠቍም መጽሐፍ መኾኗን አሳይተዋል።
መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማርና በመስበክ የሚታወቁት ዶ/ር ማሙሻ ፈንታ በበኩላቸው መጽሐፉን “በሰባኪ ዐይን” ገምግመውታል። “እኛ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ወዲያ ወዲህ ስንል፣ ውስጥ ድረስ ገብታ ቊስላችንን አፍረጥርጣ ለማከም የሞከረች መጽሐፍ ናት” ያሉት ዶ/ር ማሙሻ፣ የገበያ ግር ግር ለሌባ ይመቻልና “የበቅሎው መደንበር” ተጠቅመው አንዳንድ ሰባክያን ጥቅም ማጋበሻ አድርገውት ቢኾንስ? በማለት የዘመናችን አገልጋዮች ቆም ብለው እንዲያስቡበት የምታሳይ መጽሐፍ ናት ብለዋል። በእውነት ለሚሄዱት አገልጋዮች ደግሞ እንደ አበረታች “አሯሯጭ” የምትታይ፣ አንቂና አነቃቂ በመኾን ታገለግላለች ብለዋል።
ዘማሪ ገዛኸኝ በበኩላቸው መጽሐፉን በዘማሪ ዕይታ ቃኝተው አቅርበዋል። ጸሐፊው ሰሎሞንም ለመጽሐፉ ሥራ በተለያየ መንገድ ላገዙት ወገኖችና ጥሪውን አክብረው ለተገኙት ታዳሚዎቹ ምስጋና በማቅረብ እንዲሁም ሐሳብና ውጥኖቹን በዐጭሩ በማሳየት ንግግር አድርጓል። በመጨረሻም፣ መጋቢ ዶ/ር ቤዛለም ፍሰሐ መጽሐፉን በይፋ መርቀው መርሐ ግብሩ በጸሎት ተጠናቋል።
የደነበረው በቅሎ … መጽሐፍ በቅዱሳት መጻሕፍት እውነት፣ በታሪካዊው የክርስትና ርትዐዊ አስተምህሮና በአባቶች ተጋድሎ በዘመናት የተላለፈውን እውነተኛ ወንጌል ትምህርት ወደየአብያተ ክርስቲያናቱ ሾልኮ በመግባት ላይ ከሚገኙ የኑፋቄ ትምህርቶች፣ እንግዳ ልምምዶችና የተበላሹ ሥርዐተ አምልኳዊ መደበላለቆች መጠበቅና መከላከል እንደሚገባ በጥልቅ ምጥና ጩኸት የተስተጋባበት መኾኑን ብዙዎች መስክረዋል።
ይህን መጽሐፍ በማንበብና ለሌሎችም በማስተላለፍ ታሪካዊ ግዴታችንን እንወጣ።