የአዲስ አበባ ክልል መሠረተክርስቶስ ቤተክርስቲያን የመዘምራን አገልግሎት የተመሠረተበትን የ40ኛ ዓመት በዓል ከትላንት በስቲያ ግንቦት 30 እና በትላንትናው ዕለት ሰኔ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. በደማቅ ሁኔታ በምስራቅ መሠረተ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ተከብሮ ውሏል።
የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኀብረት ዋና ፀሐፊ ቄስ ዓለሙ ሼጣ የእንኳን አደረሳችሁ መልእታቸውን በማስተላለፍ ፕሮግራሙን የከፈቱ ሲሆን ፥በእነዚህ ዓርባ ዓመታት መዘምራኑ ከራሳቸው ቤተ እምነት አልፈው ለመላው ወንጌላውያን አማኞች በረከት የሆኑበትን መንገድ በማስታወስ ፥ ወንጌላውያን አማኞች ባለፉበት የስደት እና የመከራ ጊዜያት ሁሉ የፅናትና የማበረታቻ ዝማሬዎችንና ዓውድን የጠበቁ መልዕክቶችን ለልባችን በማድረስ ባርከውናል ብለዋል።
አቶ ቴዎድሮስ በየነ የመሠረተ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ሊቀመንበርም ፥ "ይህ የመዘምራን ቡድን ይህን ምስክርነት ሳይለቅ የሚተኩ ትውልዶችን እየተቀባበለ እስከ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት እንዲቀጥል ጸሎቴ ምኞቴም ነው" ብለዋል።
የመዘምራኑ መሪ አቶ ሰለሞን ደምሴ ፥ የአዲስ አበባ ክልል መዘምራን የተመሠረተበትን 40ኛ ዓመት በዓልን ለማክበርና በዘመናት ሁሉ የረዳቸውን እግዚአብሔርን ለማመስገን ታስቦ የተዘጋጀ ፕሮግራም መሆኑን ጠቅሰው የመዘምራኑን የ40 ዓመታት አገልግሎት ታሪክ በአጭሩ ለታዳሚው አቅርበዋል።
በመዘምራኑ እስከዛሬ የተዘመሩ መዝሙሮችን በድህረገጽ በነጻ መለለቀቃቸውንና ፥ማንም ሰው online ማድመጥ ፥ download ማድረግና social network ድህረገጾች ላይ share ማድረግ እንደሚችል ፥ የድህረገጹም አድራሻ www.mkchoir.org እንደሆነ ገልጸዋል።
በእነዚህ ሁለት ቀናትም የተለያዩ ዝግጅቶች የቀረቡ ሲሆን ፥ ከዝግጅቶቹም መሃል የአጥቢያዎች ዓውድርዕይና ለዚህ በዓል ብለው ከባህር ማዶ የመጡ የመዘምራኑ አባላት ምስክርነት ይገኙበታል።
Semayaiw Thought በዚህ አጋጣሚ ለመዘምራኑ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክቱን እያስተላለፈ እግዚአብሔር ቀጣይ አገልግሎታችሁን ይባርክ ይላል።