You are here: HomeYouth Cornerወጣት አልወጣት

ወጣት አልወጣት

Written by  Monday, 10 August 2015 04:32

መጀመሪያ ወጣት

 

ልክ ልካችሁን ብነግራችሁ ትቆጡኛላችሁ? ማለቴ ‹‹የተገለጠ ዘለፋ ከተሰወረ ፍቅር ይሻላል።›> ሰው በየጓዳው ያማችኋል። ‹‹የዘንድሮ ልጆች የጉድ ልጆች ናቸው›› ይሏችኋል። ከሁሉ ከሁሉ ‹‹ሰው አይሰሙም፥ የራሳቸውን ካልሆነ ሌላ የሚያዳምጥ ጆሮ የላቸውም፥ ገና አንድ ቃል ሲናገሯቸው በእልፍ ቃላት እሩምታ አፍ ያዘጋሉ ፥የሰከነ ውይይት የሚሉት አያውቁትም፥ አይወዱትም፥ በራሳቸው ድምጽ ጢም ተደርገው ተሞልተዋል እና እንዴት እናናግራቸው?›› ይሏችኋል። ወጣቶች ይህ እውነት ነው እንዴ?

 

ምናልባት ‹‹መካሪዎች ነን›› ባዮች የዕብነ በረዱ አስረኛው ፎቅ ላይ ሆነው እናንተን ወደ መሬት እያዩ ስለሚናገሩ ይሆን? እውነት የምትወዱት ድምጽ የራሳችሁን ነው? ‹‹ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለቁጣ የዘገየ ይሁን ›› የሚል ቃል እንዳለ አታውቁም?

 

የሚሏችሁን ልንገራችሁ? ወጣቱ ሁሉ አጫፋሪ ነው፥ የራሱ የሆነ ማንነት አውጥቶ አውርዶ የተቀበለው እውነት የለውም፥ የእነ ገሌ አጨብጫቢ ብቻ ነው፥ አንድ የታወቀ ሰው ወይም ቡድን ያገኘ እንደሆን በርሱ ዙሪያ እንደ ንብ መትመም ነው እንጂ ክፉና ደጉን ለመለየት በርጋታ ማጤን የሚባለውን በፍፁም አያውቅም፥ ‹‹ ዘራፍ እኔ የከሌ አሽከር!›› ነው ፉከራው ‹‹ጀግና›› የሚለውን ሰው ሲነኩበት እንደ ግስላ ይገሠላል እንደ አንበሳ ይከመራል እንደነብር ዓይኑ ይቀላል - ከዚያ በኋላማ ለሚነካው ወዮለት ‹‹ጀግኖች›› የሚላቸው ሰዎች ሥጋና ደም እንዳለባቸው፥ ስህተት አንዳንዴ እንኳ ነፍሳቸውን እንደሚያዘምም ሊቀበል ያዳግተዋል፡፡

 

ምናልባት ይህ የመጣው ከወጣት ጀግና ፈላጊ ተፈጥሮ የተነሳ ሊሆን ይችላል። ጀግና መፈለግና እርሱን ለመምሰል መሞከር ምን ክፋት አለበት? ምንም! ግን ሁልጊዜ ጀግናና እንከን የለሽ አለቃ አንድ ብቻ ነው። የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ። እርሱን ምን ታወጡለታላችሁ? በፍቅር ቢሆን፥ በጥበብ በቃል ቢሆን፥ በሥራ ቢሆን ፥በርህራሄ ቢሆን፥ በኃይል ቢሆን ማን ይመልሰዋል? በሚያሳቅሉት ጠላቶች ፊት ለፊት ቆሞ ‹‹ከእናንተ ስለ ኃጢያት የሚወቅሰኝ የሚከሰኝ ማን ነው?›› ብሎ በድፍረት የጠየቀ፥ ክስም ስላልተገኘበት ሰውን ሁሉ ያስደመመ የእውነት ፊታውራሪ ነው። ወጣቶች ስሙ! አብራችሁ መክነፍ ካስፈለጋችሁ የማንንም ቀለማም ጨርቅ አታውለብልቡ። የዚህን ሰው የፍቅር አርማ አንግቡ። ማንም አያንበርክካችሁ ለአላፊ አግዳሚ ሎሌ አትሁኑ። ነፍሱን የሰጣችሁ ጌታ እያለ።

 

ሌላም ሚሏችሁ አለ። "መለኪያቸው ተሳስቷል፥ መንፈሳዊነትን የሚመዝኑት በምድር ብልጥግና፥ በብርቅርቅነት፥ በታይታ፥ በጌጥና በቄንጥ ሆኗል። የእግዚአብሔር አገልጋይ ነኝ ብሎ የሚለውጠው ኮት ከሌለው ፤የድህነት መንፈስ ተጠናውቶታል፥ በእግሩ የሚኳትን ከሆነ፤ ‹‹ራስ እንጂ ጅራት አላረግህም›› የሚለው ቃል አልገባውም፤ ትሉታላችሁ አሉ። በጣም መንፈሳዊ ሆኖ ቢሆን በኪሱ በብር ይታጨቃል፥ ዝናብ የሚያፈስ ደሳሳ ጎጆ ውስጥ እየኖረ እንዴት የንጉስ ልጅ ነኝ ይላል?" ትላላችሁ እተባለ ነው። እውነት እንዲህ ትላላችሁ? መቼም እንደዚህ የምትሉ ከሆነ የአዲስ ኪዳንን ክቡራን ሰዎች አፈር ድሜ እያገባችሁ ይመስለኛል። እዚያ መፅሐፍ ላይ ክቡራን የተባሉት የበግና የፍየል ሌጦ የለበሱ፥ ቀበሌ የማያውቃቸው ተንከራታቾች ናቸው። ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስም እኮ ጦሙን እንዳያድር (አንዳንድ ቀን ጦሙን ሳያድር አልቀረም) በትርፍ ጊዜው ድንኳን ሚሰፋ፥ ከዚያችውም ለሌሎች የሚሰጥ አገልጋይ ነበረ። በባንክ የሚያከማቸው ብዙ ገንዘብ የነበረው አይመስልም። የኢየሱስ እናት ማርያምስ ብትሆን ፤ባለ ብዙ ገንዘብ ብትሆን ኖሮ ለመሥዋዕት ርግብ ታቀርብ ነበርን? ‹‹በእጅ ያልተሠራች ሰማያዊት ሀገር ይናፍቁ ነበርና እንደ መጻተኛ ኖሩ›› የሚለው ይልቅ የእግዚአብሔር ሰው አመለካከት ነው።

 

ሪቫይቫል ታሳድዳላችሁ ይሏችኋል? ምንድነው ሪቫይቫል? ሞቅታ ነዋ! በኪቦርድ ታምቡር ድምድምታ፥ ባልተለካ ድምጽ ጩኸት  ‹‹የፈለገውን ይሁን ጎረቤት›› ድፍረት አብሮ መሆን። እንደዚህ የሚሏችሁ ሰዎች እውነት እናንተ የምትፈልጉት ገብቷችሁ ይሆን? እናንተ የምትፈልጉት መነቃቃት ለጌታ በተከፈተ ልብና አካል አክብሮት መስጠት ሳይቆጥቡ ለርሱ መገዛት አይደለም እንዴ? ግን በሌላ ተተርጉሞባችኋል። አገር እየረበሹ ነው፥ ከእነርሱ ጋር ለ10 ደቂቃ እንኳ መፀለይ አይቻልም፥ ጩኸት በጩኸት ነው፥ ጆሮህ ይታመማል፥ በፍፁም ጥሞና የሚባል ነገር አያውቁም፥ ጨፋሪውን ሁሉ ጠጋ ብለህ ብታነጋግረው ጥልቀት የሌለው ዘላይ ብቻ ነው፥ የሕይወትን ውስብስብ ሊፈታ የማይችል፥ የጊዜውና የአሁን ሰው ብቻ ነው፥ ከየቦታው የቆነጠረውን አንዳንድ ቅመም ደበላልቆ ነው ሪቫይቫል የሚለው፥ ጌታን የማዳመጥ፥ በርጋታ የማምለክ፥ የሌሎችን የጸሎትና አምልኮ ልማድ የማክበር ብቃት የለውም። ሆይሆይታና ጥድፊያ ብቻ ነው ሚገዛው ይሏችኋል።

 

እውነተኛ ሪቫይቫል - ደስታ አለበት። ስለዚህ በሙቀት ብትዘምሩ እኔ ክፋቱ አይታየኝም። እውነተኛ ሪቫይቫል ንሰሐም አለበት። በጥሞና ኑዛዜ በማድረግ ራስን መመርመርም ተገቢ ነው። ነጻነታችንን ለማንም መሸጥ አያስፈልገንም፤ ግን የእኛ መብት ለሌሎች እንቅፋት እንዳይሆን ተጠንቀቁ ተብለናል። አርነታችንም ክፋትና የሥርዓት አልበኝነት መሸፈኛ አይሁን። እውነተኛ ሪቫይቫል ጥልቀት አለው። የሚጀምረው ከእግዚአብሔር ዘንድ ስለሆነ የሰውን መዝሙር ብቻ ሳይሆን፤ የዕለት ኑሮውን ይነካል ‹‹ሃ ሌ ሉ ያ›› እንደሚያሰኝ ሁሉ፤ ሰው እንድንወድ ያደርገናል።

 

ሌላ ደግሞ ‹‹ ሁሉ ነገር ዛሬ ካልሆነ…..›› ትላላችሁ አሉ። ምን ማለታችሁ ነው? ፈጣሪ እንኳ በአንድ ቀን ሥራውን አልጨረሰም።

 

ቀጥሎ አልወጣት

ከወጣትነት ተርታ በዘመን ቁጥር ምክንያት የተፈናቀለ።

 

ወጣቱን በጎሪጥ የምታዩ አላፊ ትውልድ ሆይ! ወጣቱ የሚላችሁን ስሙ። አንሰማም ብትሉ እንዳኮረፋችሁ መሄዳችሁ ነው። የሚበጀው ማዳመጡ ነው።

 

መጀመሪያ ነገር እኛን ወጣቶችን በሙሉ በደምሳሳው ይጠረጥሩናል። አያምኑንም። ‹‹ለኮንፈረንሳችን ጋሽ እከሌን እንጋብዝ›› ብንል ዶክትሪን ሊገለብጡ ነው! ይሉናል ለቤተክርስቲያን የሚያስቡ፥ ለእውነት የቆሙ እነሱ ብቻ የሆኑ ይመስል ፤በስንት መከራ አስፈቅደን ያገኘነውን መሰብሰቢያ ቤት ‹‹ምን እንደሚሰሩ ስለማናውቅ እኛ አላፊ አንሆንም›› ብለው ይዘጉብናል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስንወጣ እህቶችና ወንድሞች ሁለት ሁለት ሆነን ከሄድን፤ የሚያስቡን በአንድ መንገድ ብቻ ነው። ለምን አታምኑንም?

 

እውነት ለምን አታምኗቸውም? ፍላጎቱ ቢኖራቸውም ብቃቱ የላቸውም እያላችሁ ይሆን? መጀመር ቢያውቁም ጽናት የላቸውም እያላችሁ ይሆን? ችግራችሁ ይገባኛል። ግን ስሙ! ሳሙኤል በእስራኤል ሁሉ የታመነ ነብይ እንደሆነ ከመታወቁ በፊት ኮ፤ እግዚአብሔር በልጅነቱ ድምፁን አሰምቶታል ፥ሥራም ሰጥቶታል። ዳዊት ጎሊያድን ዘርሮ ሆ! ከመባሉ በፊት እኮ ከስንት አንበሳና ድብ ጋር ታግሏል። የመለማመጃውን ሜዳ ለምን ትከለክላላችሁ? እናንተስ ብትሆኑ የምትንገዳገዱበት ጊዜ የለም? እየታረመ፥ ጎሽ እየተባለ፥ አይዞህ እየተባለ የሚኬድበት ጎዳና ነው፤ ሕይወት እራሱ።

 

እንደዚህም ይሏችኋል ‹‹ አዋቂ›› ነኝ ባዩ ኅብረተሰብ ለውጥን እንደጦር ይፈራል። ጥንት ከለመደው ሥርዓት ውጭ አንድ ነገር እንኳ እንዲነቃነቅ አይፈልግም። ሌላው ቀርቶ በአንድ እሁድ ጠዋት ሁለት መዝሙር በመዘመር ፈንታ፥ ዛሬ አምስት ይዘመር ቢባል፤ በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የተፈጠረ ከፍተኛ ነውጥ አድርጎ ያስባል። በወር አንድ ጊዜ እሁድ ጠዋት በአምልኮ ፈንታ ምዕመኑ ሁሉ ለምስክርነት ይሰማራ ቢባል ‹‹አዲስ ትምህርት መጣ›› ይላል፡፡ ወዳጆቼ አዋቂዎች በጎ ውጤት መምጣቱንና መሠረታዊ ጤነኛነቱን መመርመሩ እንጂ አዲስ ነገር አትፍሩ! አንዳንድ ቀን ‹‹አባታችን ሆይ›› የሚለውን ፀሎት የስብሰባው መክፈቻ ፀሎት አድርጉት፡፡

 

ትላልቆች ሆይ ሌላም እየተባላችሁ ነው ‹‹እኛ ወጣቶች ሥራ እንፈልጋለን! ጉልበት አለን! ጉጉት አለን! ዕድሜያችን ጠቃሚ ተግባር ላይ እንዲውል እንፈልጋለን! ነገር ግን የሚያሰማራን የለም። ሥራ ካልሰጡን እኛ ሥራ መፍጠራችን አይቀርም። ቦይ ቀደው በዚህ ሂዱ ካላሉን ግንብም ቢሆን በስተን እንወጣለን። እኛ ይህንን እንስራ ስንላቸው ‹‹እኛ በምንሰራው ኑሩ ይሉናል›› ቤተክርስቲያን ቁጭ ብሎ ተቀላቢ መሆን ደከመን፥ ጡንቻዎቻችን የሚያንቀሳቅስ ነገር ስንሞክር ቤቱን ልንንደው የተነሳን ይመስላቸዋል፥ ከተናደ ይናዳ! ሌላ ሰፊ ቤት ለመገንባት ዕድል የሠጠን ይሆናል።››

 

እውነት እናንተ አዋቂዎች ሰው ያለሥራ ሲቀመጥ ሊያብድ እንደሚችል ዘንግታችሁት ነው? ወይስ ‹‹የተሰጣቸውንስ በቅጡ መች ሠሩት ብላችሁ? ስሙ- የእግዚአብሔር መንግስት ሰፊ ናት መከሩም እጅግ ብዙ ነው። ወጣቶች በዚህ መስክ ላይ ሊሠሩት የሚፈልጉትና የሚችሉት ጉዳይ ያለ ከመሰላቸው እናንተ እኮ መደሰት ነው ያለባችሁ። ቅርፅ ከሰጣችሁ ከኋላ መከታተል ነው ጥሪያችሁ። አንዱ ወጣት እጅ ሁለት ዓሳ ቢገኝስ፤ ጠጋ ብላችሁ እዩ፥ አንዳንዴ ልጆቹ ራእይና ቅዠትን መለየት እያቃታቸው ቢተራመሱም በማጥሉ ስራ ልትረዷቸው ይገባል እንጂ፤ እንዲቦዝኑ አትተዋቸው። ‹‹በመጨረሻው ዘመን መንፈሴን በስጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈሳለሁ …..ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ።››

 

ሽማግሌዎች ፥አዋቂዎች፥ መሪዎች፥ ትልልቆች ሆይ ብዙ ነገር ብትባሉም ከሁሉ ከሁሉ የሚያሳስበኝ ‹‹እነዚህ መሪዎቻችን ግብዞች ናቸው!›› የሚለው ነው የሚናገሩት ሌላ የሚሰብኩት ሌላ፥ የሚሰሩት ሌላ የሚኖሩት ሌላ። እኛ በተቻለ መጠን እንደቃሉ መኖር እንፈልጋለን። ለምሳሌ ሁለት ልብስ ያለው ለሌለው ያካፍል ካለ አባቴ፤ ከስድሰት ኮቱ አንዱን ለምን ለአየለ አይሰጠውም? ትናንት ቤታችን መጥቶ ሲፀልይለት ‹‹የሥራ ዕድሉን የዘጋህበት ጋኔን ለቀህ ጥፋ›› እያለ ሲጮህ ነበር። ፆምና ፀሎት ጠቃሚ እንደሆነ ሲናገሩ ቢውሉ አይደክሙም። ግን ለአንድ ሰዓት ተንበርክኮ መፀለይ ያቁነጠንጣቸዋል። ‹‹ቅድስና ጠፋ›› እያሉ ብዙ ግዜ ያወራሉ። እኛ ቤተክርስትያን እንኳን በዚህ አመት አራት ጊዜ በዚህ ርዕስ ላይ ትምህርት ሲሰጥ ነበር፤ ግን መሪዎቻችን ከስብሰባ ውጭ አንዱ የአንዱን ጉድ እያወሩ ሲተማሙ ስንሰማ ይዘገንነናል፡፡

 

አዋቂዎች ይህን መቼም ምንም ልንጨምርበት አልፈልግም። እኔ አንድ ነገር ልንገራችሁ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ መሬት ቢመጣ (እንደድሮው ዘመን) ጠቡ ከማን ጋር ይመስላችኋል? ማጅራት መቺዎች ጋር ሄዶ ከመውቀሱ በፊት፥ሴተኛ አዳሪዎችን ምንም ከመናገሩ በፊት፥ ከቤተክርስቲያን አለቆች ጋር የሚፋጠጥ ይመስለኛል። መስሎኝም እፈራለሁ። ሁሉን የሚታገሰው ጌታ፤ግብዞችን ግን ብዙ መታገሡን እጠራጠራለሁ።

 

ወጣቶች ባለብዙ ስህተት እንደመሆናቸው ሁሉ፥ ባለብዙ ቅንነትም ናቸው። ስሟቸው። ታገሱዋቸው። አቅኑዋቸው። ከሁሉ ይልቅ ደግሞ ውደዷቸው። የልባቸውን በር የሚከፍቱላችሁ በፍቅር ጣት ብታንኳኩ ነው።

 

በመጨረሻም፤ ለወጣትም ለአልወጣትም ይህን ስጽፍላችሁ፥ ሁላችሁንም በእርግጥ የምወዳችሁ መሆኔን በፊርማዬ አረጋግጣለሁ።

Read 21890 times Last modified on Monday, 10 August 2015 12:29
Negussie Bulcha

Website: www.negussiebulcha.com Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 22 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.