You are here: HomeSocial Issues ትውልድ ተኮር ራዕይ

ትውልድ ተኮር ራዕይ

Written by  Wednesday, 23 September 2015 11:42

ጊዜው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ጥር 2010 ነው፣ ለወንጌል አገልግሎት በአውስትራሊያ ከተሞች ስዘዋወር አድሌይድ የተሰኘ ከተማ ደርሻለሁ። ከአገልግሎት በኋላ ከቤተክርስቲያን መሪዎች እንዱ ለጉብኝት ወደ አንድ ፓርክ ወሰደኝ። ተዘዋውሬ ከተመለከትኩ በኋላ አውስትራሊያኑ ምድሪቱን እንዴት ባለ ንጽህና ውበት እንደያዙት ሳይ ተደነቅሁ። በአጠገቤ የነበረውን ብቸኛ እስጎብኚዬን “ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ምሥጢሩ ምንድነው? ብዬ ጠየቅሁት። የመለሰልኝ መልስ መቼም ከውስጤ አይጠፋም። እንዲህ አለኝ “አውስትራሊያን አንድ አባባል አላቸው፣ ይህንን የሚሉት ለማለት ብቻ ሳይሆን ከልባቸው ነው። ምክንያቱም በየጊዜው ከሚወስኑትና ከሚሠሩት ሥራ ግልጽ ሆኖ ይታያል” በማለት ከፊቱ የተንጣለለውን በሕብረ ቀለማት ያሸበረቀውን መናፈሻ አሻቅቦ እየተመለከተ “ይህችን ምድር ከአባቶቻችን የወረስናት ብቻ ሳትሆን፣ ከልጆቻችንም የተዋስናት ናት” ይላሉ። በማለት አወጋኝ።

 

ይህ የአውስትራሊያን አባባል በ2006 የኖርዌ ፓርላማ ያሳለፈውን ውሳኔ አስታወሰኝ። ኖርዌ በ1969 በሰሜን ባህር ድንበሯ አካባቢ የነዳጅ ክምችት ካገኘች ወዲህ በዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ በአለም ቀዳሚ ሃገር ሆናለች። ሆኖም የዛሬው ስኬትና ዕድገት ብቻ ሳይሆን የመጪው ትውልድ ጉዳይ ያሳሰባቸው መሪዎቿ ካለው ክምችት ውስጥ ከ47 ከመቶው በላይ እንዳይወጣና አሁን ከሚወጣውም ገንዘብ ተቀንሶ ለሚመጣው ትውልድ አበል ሆኖ እንዲቀመጥ ወስነዋል። በዚህም መሠረት “ለሚመጣው ትውልድ” በሚል ከነዳጅ ሽያጭ የተቀመጠው ገንዘብ 5.534 ትሪሊዮን የኖሬዥያን ክሮነር (857.1 ቢሊዮን ዶላር)ሲሆን በዓለም ላይ ትልቁ የአበል ክምችት አሰኝቶታል።   

 

እነዚህን ገጠመኞች ያነሳሁ ስለ ትውልድ ጥቂት ለማለት ፈልጌ ነው። ከማንም ይልቅ እግዚአብሔር ስለ ትውልድ ግድ ይለዋል። ለዚህ ነው የአባቶቹን፣ የራሱንና ተተኪውን ትውልድ ያየው ሙሴ በምድረበዳ ጸሎቱ፡-

 

“አቤቱ፡- አንተ ለትውልድ ሁሉ መጠጊያ ሆንህልን። ተራሮች ሳይወለዱ፣ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ አንተ ነህ።” መዝ. [90] 1-2

የሚለው። 

 

እግዚአብሔር አንድ ትውልድ ፈጥሮ ያ ትውልድ ለዘለዓለም እንዲኖር አላደረገም ወይም አንድ ትውልድ ኖሮ ካበቃ በኃላ ሌላው በፈረቃ እንዲተካ አላደረገም ነገር ግን ትውልድ በትውልድ ማህፀን ውስጥ እንዲጸነስና በቀዳሚው ትውልድ ሥር አድጎ በተራው ቀጣዩን ትውልድ ለማሳደግ የሽግግር በትሩን እንዲረከብ አድርጓል። እንግዲህ ይህ ነው ስለ ትውልድ እንድናስብ፣ እንድናስብ ብቻ ሳይሆን ትኩረት ሰጥተን እንድንሠራ ግድ የሚለን። የነቢዩ ሚልክያስ መልዕክቶች ይህንን ያስረግጡልናል፡-

 

“እግዚአብሔር የሕይወትን መንፈስ [በባልና ሚስት መካከል] እንድ አድርጎ ጠብቆልን የለምን?  እርሱም የሚፈልገው ምንድነው? ዘር [እግዚአብሔርን የሚፈራ] አይደለምን? ስለዚህ መንፈሳችሁን ጠብቁ፣ ማንም የልጅነት ሚስቱን አያታልል። መፋታትን እጠላለሁ ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር . . .” ት. ሚል. 2፡ 15-16

 

“እነሆ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ነቢዩን ኤልያስን እልክላችኋለሁ። መጥቼም ምድርን በእርግማን እንዳልመታ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፣ የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል።” ት. ሚል. 4፡5-6

 

እነዚህ ክፍሎች እግዚአብሔር ስለ ትውልድ ያለውን ሥፍራ በጉልህ የሚያሳዩን ሲሆን በተለይ በ 4፡5-6 ላይ ያለው ስለ ትውልድ ቅብብሎሽ ትልቅ መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው። በ “አባቶች” የተሰየመው ቀዳሚ ትውልድ ልቡን “ልጆች” በተባሉት ቀጣይ ትውልድ ላይ ካላሳረፈና በራሱ ነገር ከተወጠረ፣ “ልጆች”ም ለ”አባቶች” ትሩፋትና ቅርስ ስፍራ ካልሰጡና መዘመን ላይ ብቻ ካተኮሩ ለዘመናት ሲቀባበል የመጣው የግብረገብ፣ የበጎነት፣ እግዚአብሔርን የመፍራት እሴት ይመነምንና ልቅነት፣ ዋልጌነት፣ ራስ ወዳድነት፣ አመፀኝነት እያየሉ ይሄዳሉ፣ በፍፃሜውም የእግዚአብሔር ቁጣ ይገለጣል፣ ምድርም በእርግማን ሥር ትወድቃለች። ለዚህ መፍትሄው በጊዜ ስለ ትውልድ ማሰብና ትውልድ ተኮር ሥራ መሥራት ነው።

 

ይህ ርዕሰ ጉዳይ የሁሉንም አገሮች ሕዝቦች፣ መሪዎችና አብያተ ክርስቲያናት የሚመለከት ቢሆንመ አገራችንን ኢትዮጵያን ግን በብርቱ ይመለከታታል። ለምን? ምክንያቱ አገራችን “ጥንታዊት ወጣት” በመሆኗ ነው።

 

ኢትዮጵያ እንደ አገርና እንደ መንግስት የ3000 ዓመታት ታሪክ እንዳላት ይነገራል፣ ሆኖም ይህች የ3000 ዓመታት የዕድሜ ባለ ፀጋ “አዛውንት” በአለም በወጣት ከትሞሉ አገሮች አንዷ ናት። የአለም አቀፍ ፖፒሌሽን ፒራሚድ ድረ-ገጽ እንደሚያሳየው ባለንበት 2015 98 ሚሊዮን ከሚጠጋው የኢትዮጵያ ሕዝብ 52, 835, 028 የሚሆነው ከ 0-19 ዓመት ዕድሜ ያለው ወጣት ነው።

 

ይህን እውነታ በአሃዝ ለማስደገፍ፡- 98,942,000 ከሚቆጠረው ሕዝባችን 53.4% ማለትም 52,835,028 የሚሆነው ከ 0-19 ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚሰፍር ነው። ከሌሎች አገሮች ጋር አነፃጽሮ ለማየት፣ በሕዝብ ብዛት ከእኛ ጋር የምትጠጋጋው ጀርመን 82,562,000 ከሚሆነው ሕዝቧ ከ 0-19  የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው 14,778,598 ብቻ ነው። ይህም ኢትዮጵያ ምን ያህል የሕጻናትና የወጣቶች አገር እንደሆነች ያሳያል።

 

እንግዲህ እነዚህን የዛሬ ህጻናትና ወጣቶች ችግሮቻቸውንና ተግዳሮቶቻቸውን ምን ያህል ተረድተናል? አስተሳሰባችንንና ቋንቋችንን ምን ያህል በእነርሱ ቃኝተናል፣ ምን ያህል በክርስቶስ ኢየሱስ ወንጌል ልንደርሳቸው ተዘጋጅተናል? ምን ያህል የክርስቶስ ደቀ-መዛሙርት ልናደርጋቸው ታጥቀናል? . . .???

 

እኛ ይህን ባናደርግ በተቃራኒው ሊነጥቃቸው የሚያሰፈስፍ ብዙ ኃይል አለ። ድህረ ዘመናዊነት፣ የአዲሱ ዘመን እንቅስቃሴ፣ የሥህተት ትምህርቶች፣ የሩቅ ምሥራቅ ፍልስፍናዎች፣ አክራሪነትና ሽብርተኝነት . . . አረ ስንቱ!!!

 

ይህ ግዙፍ ኃላፊነት በአንድ ግለሰብ፣ በአንድ አገልግሎት፣ በአንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ሊሰራ አይችልም። ነገር ግን የቀጣዩ ትውልድ ሸክም ያላቸው ግለሰቦች፣ አገልግሎቶችና አብያተ-ክርስቲያናት ቢተባበሩ ታሪክ መሥራት ይቻላል።

 

የትውልድ ሁሉ አምላክ ዘመንዎን ይባርክ

Read 9641 times
Yared Tilahun

President, Golden Oil Ministry

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 98 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.